April 13, 2018
33 mins read

የቶሎሣ ኢብሳ እናት ዘርሽ ይባረክ! – ነፃነት ዘለቀ

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አንዳንዴ መመሰጋገን መጥፎ አይደለም፡፡ እንደባህል ሆኖብን ይመስለኛል በሀገራችን ሰውን ማመስገን ብዙም አልተለመደም፡፡ በፈረንጆች ዘንድ ግን ሰውን ማወደስ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መልካም ነገር ነው፡፡ ሰለጠነ በሚባለው ዓለም “አመሰግናለሁ፤ ይቅርታ(in both senses of ‘sorry’ and ‘excuse me’)፤ እሽ፤ እግዜር ይስጥልኝ…” በጣም የተለመዱ ናቸው፡፡ ጥፋትን ለማረም ራሱ የሚጀምሩት በአወንታዊ አቀራረብ እንጂ እንደኛ ሰውን በመነጀስና የበላይነትን ወይም ዐዋቂነትን ለመግለጽ በሚመስል አኳኋን በመጀነን ስሜት አይደለም፡፡ እኛ ብዙ ይቀረናል በውነቱ፡፡ ብዙዎቻችን ማመስገንን እንደነውር ስንቆጥር መወነጃጀልንና በአሉታዊ መልክ መወቃቀስን ግን እንደጥሩ ባህል ሳንወስድ የምንቀር አይመስለኝም፡፡ መንገድ ላይና ዳር ሲጸዳዳ ቅር የማይለው ሰው መንገድ ላይና ዳር ሲበላ “ስቅጥጥ” እያለው እንደሚያፍረው ሁሉ ብዙ ነገራችን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ የቀጠሮ ሰዓት ማሳለፍን እንደጀግንነት፣ በሴት መፈቀርን እንደ ነውር፣ በወንድ መፈቀርን እንደ ጀብድ፣ አጥፍቶ ይቅርታ መጠየቅን እንደውርደት፣ “አመሰግናለሁ” ማለትን እንደ ኃጢኣት፣… መቁጠር ባህል በሆነበት ማኅበረሰብ መሀል መገኘት በርግጥም ግር ማሰኘቱ አይቀርም፡፡

ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የኛ ነገር ከብዙ አቅጣጫዎች አንጻር ለየት ይላል፡፡ ይህን አፈንጋጭነታችንን ከምሥጋና አኳያ ስንመለከተው ደግሞ በእጅጉ የሚደንቅ ክስተት እንታዘባለን፡፡ በተረታችን ሳይቀር “አመስጋኝ አማሳኝ” እንላለን – ምሥጋናን ለማጣጣል፤ “ሆድ ያመስግን”ም እንላለን፡፡ አንድን መልም የሠራ ሰው ብናወድሰው ምን እንሆናለን? እርግጥ ነው – በሌላ በኩል ምናልባት ተመስጋኝም በዚህ ዙሪያ አሉታዊ ድርሻ ይኖረው ይሆናል፡፡ ሲመሰገን ልቡ የሚያብጥና ወደ ጉራና ዕብሪት የሚሄድ ካለ የተበረከተለትን ምሥጋናና አድናቆት ገደል ከተተው ማለት ነውና በዚያ አካባቢም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

ለመንደርደሪያ ይህን ያህል ካልኩ አሁን ምሥጋናና አድናቆቴን ልሰነዝርላቸው ወደፈለግሁት ዕንቁ ልጆቻችን ልውሰዳችሁ፡፡

ሀገር ስትቸገር፣ በሞትና በሕይወት መካከል ሆና በጣር ስትያዝ ከየጎሣና ብሔሩ ጥቂት ብርቅዬ ዜጎች እንደሚኖሩና ከስቃይዋ ሊታደጓት እንደሚጥሩ በተግባር እያስተዋልን ነው፡፡ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየዶለቱ ሀገርንና ሕዝብን መቀመቅ የሚከቱ የተጨቋኝ ወገን አባላት የመኖራቸውን ያህል የዘርና የጎሣ ገመድ ሳይስባቸው ከጨቋኙ ነገድ ወይም ቡድን ራሳቸውን ነፃ በማድረግ ለተበደሉ ጎሣዎች ሕይወታቸውን እስከመስጠት የሚደርሱ ድንቅ ዜጎች በዓለማችን ዙሪያ አሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ታሪክ ከነጮች ጋር ወግነው ጥቁሮችን የሚገድሉና የሚያሰቃዩ ባንዳ ጥቁሮች እንደነበሩ ሁሉ ከነጮቹ ወገኖቻቸው አፈንግጠው በፀረ አፓርታይድ ትግሉ በመሰለፍ ለጥቁሮች ነፃነት የሚታገሉ ብዙ ነጮች ነበሩ፡፡ ይህን ዓይነት ተፈጥሮ መላበስ መታደል ነው፡፡ ለሆድም ይሁን ለፍርፋሪ ሥልጣን ተብሎ ዘርህን ከሚያጠፋ ዘውግ ወይም ቡድን ጋር ተባብረህ ወገንህን ማስጨረስ ደግሞ ከዕርግማኖች ሁሉ የከፋ ዕርግማን ነው፡፡ በዚህ ረገድ የነገነት ዘውዴ ነፍስ ወደየት እንደምትገባ መገመት አይከብድም፡፡ (በቅርቡ ጅፍጅፍ ብላ አርጅታ ሳያት ለዚህች አጭር ዕድሜ ብላ ያን የመሰለ አስጠሊታ ታሪክ በመሥራቷ  ለራሷ ከአንጀቴ አዘንኩላት፡፡ ሰው ለካንስ እንዲህ ከንቱ ነው! ሞታለች እኮ ብታይዋት! ይች ማፈሪያ!!)

በወያኔዎች አንቀልባ ታዝሎ ወደሀገራችን በመጣብን የዘረኝነት አባዜ ምክንያት ብዙ ነገር እየታዘብን ነው፡፡ አማራ፣ ኦሮሞና ትግሬ በሚል ባለፉት ጥቂት አሠርት ዓመታት  ውስጥ እያየነው ያለነው አበሳ ተወርቶ አያልቅም፡፡ አማራ ሆኖ ሳለ በዐዋጅ ዘሩን ለማጥፋት ምሎ ተገዝቶ ከተሰለፈ የወያኔ ትግሬ ጋር በማበር አማራን የሚያስፈጅ አማራ ማየት ከብርቅነት ያለፈ ገሃድ እውነታ ነው፡፡ በጎጃምና በጎንደር እንዲሁም በመላዋ ሀገራችን ከወያኔ ጋር ተሰልፎ አማራን እያስጨረሰ የሚገኝ አማራ ብዙ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ “ሰው” መግለጫ የሚሆን እኔ ቃል የለኝም፡፡ በተቃራኒው ትግሬ ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ እንደወያኔዎቹ ከሰውነት ተራ አልወርድም ብሎ ለኅሊናው ተገዢ በመሆን ስለአማሮች መጨፍጨፍና መሰቃየት የሚታገል በዚያም ሰበብ ብዙ እንግልት የሚደርስት ትግሬ አለ፡፡ ኦሮሞ ሆኖ ተፈጥሮ ሲያበቃ አማራን እንዲጠላና ከወያኔዎች ጋር ተደርቦ የአማራን ዘር እንዲፈጅ በመሠሪ የታሪክ አራሙቻዎች ምክርና ቅስቀሳ አእምሮውን ለጥፋት ያዘጋጀ የመኖሩን ያህል በግልብ ስሜት ሳይነዳና ኅሊናውን ሳይስት ለእውነት የቆመ ኦሮሞ ሲገኝ መንፈስን በሃሤት ይሞላል፡፡ ከዚህ አኳያ መመስገን የሚገባውን ማመስገን፣ መወቀስና መመከር ያለበትን ደግሞ መውቀስና መምከር “የቄሣርን ለቄሣር፤ የእግዜርን(ም) ለእግዜር” የመስጠት ዓይነት ተገቢነት ያለው መልካም አርአያ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎች ተኝተው እንቅልፋቸውን በሚደቁበት አስቸጋሪ ወቅት ስለሀገራቸው የሚጮኹና የማንቂያ ደወል የሚደውሉ ድንቅ ዜጎችን ማወደስ ሲያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም፡፡ እነይገረም ዓለሙና ሥዩም ተሾመ እንዲሁም ስማቸውን ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው ብዙ ወገኖቼ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ዘራቸው ይለምም፡፡

ኢትዮጵያውያንን እንደወያኔ በዘርና በጎሣ እያቃረጡ ማንሳትና መጣል በመሠረቱ አግባብ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ይህን አካሄድ አልወደውምም፡፡ ግን አማራጭ በሚጠፋ ጊዜ አንዳንዴ እንዲህ ይኮናልና ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ወጣት ቶሎሣ ኢብሳ በድረገፁ ሀገርን የማዳን ዘመቻ ተሰልፎ የበኩሉን ታላቅ ሀገራዊ ድርሻ በማበርከት ላይ የሚገኝ የኦሮሞ ተወላጅ ነው፡፡ ስንትና ስንቶች ወያኔ በቀደደው የዘረኝነት ቦይ እየፈሰሱ አንዱን ዘር ከሌላው ለማጋጨት እንቅልፍ አጥተው በሚገኙበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት ይህ ወጣት አክቲቪስት ያለ ዕረፍት ወገኖቹን ለማስማማትና ጠላታቸውን እንዲለዩ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ትልቅ ሀገራዊ አስተዋፅዖ ነው፡፡ እናም እናቱ ትባረክ፤ ወርቅ ትልበስ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ማኅጸኗን እስከመጨረሻው ትውልዷ ያለምልመው፡፡ በጨለማ ዘመን የሚያበራ ኮከብ ሰጥታናለችና በሕይወት ካለች የልጇን ትግል የመጨረሻ ውጤት ያሳያት፡፡ እርሱን መሰል ልጆቻችነንም ያብዛልን፤ ይባርክልን፡፡

ወዲሻምበል የሚባል አንድ የትግራይ ተወላጅ በዚሁ በድረገፅ ዘመቻ እያደረገው የሚገኘው ፀረ-ወያኔ ትግልም እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በምናሳልፈው መራር ማኅረሰብኣዊ የጋራ ሕይወት የተነሣ ““ትግሬን ማመን ቀብሮ ነው” እያልን ተስፋ በቆረጥንበት ወቅት ይህን መሰል ግሩም ዜጋ ከነዚህ ምስጦች የደም ቧንቧ ሥር ማግኘት ከንፍሮ ጥሬ እንደማግኘት ያህል መስሎ ቢሰማን አይደንቅም፡፡ ይህ ምርጥ ዜጋ ከነገብረ መድኅን አርአያና የኢትዮሰማዩ ድረገፅ አዘጋጅ  ጌታቸው ረዳ ጋር  ሲደመር ተስፋችንን ያለመልመዋል፡፡ በ“ያባትህ አገር ሲወረር አብረህ ውረር” መፈክር ስንቶች ደጋግ ተጋሩ ከወያኔ ጋር ተባብረው ወገኖቻቸውን በመንፈስም፣ በአካልም፣ በኅሊናም በሚያቆስሉበት ዘመን እነዚህን የመሰሉ ጀግኖች ማግኘት ብርታትን ይሰጣል፡፡ ዛሬ የተጎሳቆለ የሚመስለውን የነገን የአብሮነት ሕይወትም በጉጉት እንድንጠብቀው ያደርጋል፡፡ ስለዚህም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ እነሱን መሰል ቆራጥ ተጋሩ እንዲሰጠንና እንዲያበዛልን ፈጣሪን እንለምናለን፡፡

በጽሑፍ ረገድ ሁለጊዜ የምትገርመኝ አንዲት ፀሐፊ አለች፡፡ መስከረም አበራ ትባላለች፡፡ አንዲት የምሥጋና ቃል ልወረውር እልና በይደር አቆየዋለሁ ወይም በሌላ ጉዳይ ተሳንፌ እዘነጋዋለሁ፡፡ የምትጽፈውን ጽሑፍ ሳላነብ አላልፍም፡፡ የማደንቃት ምክንያት ወጣት ሆና ሳለ ስለሀገሯ ብዙ ከማንበቧ የተነሣ ይመስለኛል የምትጽፋቸው ጽሑፎች እጅግ ማራኪና ትንተናዎቿ ሀገራዊ እውነታዎችን በግልጽ የሚያሳዩ በመሆናቸው ነው፡፡ ቃና ላይ ተደቅና በመዋል በቅጡ የበሰለ ሽሮ እንኳን እንዲናፍቀኝ የምታደርገዋን የገዛ ባለቤቴን አይቼ መስከረምን መሰል ሊያውም በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የምትገኝን ይህን መሰል ዕውቀትና ሀገራዊ ግንዛቤ የተጎናጸፈችን ሴት ልጅ ባደንቅ ከፈጠጠው እውነት አኳያ ሊፈርድብኝ የሚችል ሰው መኖር የለበትም፡፡ ነገሩ የፆታ ጉዳይ ብቻም አይደለም፡፡ ከዚያ ያልፋል፡፡ ብዙ ወጣቶች የኔዎቹን ጉዶች ጨምሮ ሀገራቸው ማን እንደምትባል ሳይቀር የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ ወያኔዎች ተጫውተውብናል፡፡ ተንቀሳቃሽ በድን አድርገውናል፡፡ ወደ ተናጋሪ እንስሳነትም ለውጠውናል፡፡ በዚህ መሀል መስከረምን የመሰለ ወጣት ጸሐፊ ማግኘት ማለት በረሃ ስታቋርጥ በኃይለኛ ውኃ ጥምህ ወቅት በተዓምር ምንጭ እንደፈለቀልህ የሚቆጠር ታላቅ መለኮታዊ ስጦታ ነው፡፡ ትባረክ፡፡ ዘርም ይውጣላት፡፡ እንዲህ ሲሏት ትቆጣለች አሉ – ግን ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ትቆጣኝ፤ እችለዋለሁ፡፡ ባይሆን አመክሮ ታድርግልኝና ቁጣዋን ለስለስ ታድርግልኝ፡፡…

ዶር አቢይ አህመድ ጥሩ ንግግር አድርጓል፡፡ ይህ ወጣት ፖለቲከኛ ማንን እንደሚመስል ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ሥርዓት እንዲገረሰስ ትልቁን ሚና የተጫወቱትን ኤፍ ደብልዩ ደክለርክን ወይንስ የፑቲን ቀኝ እጅ ሆነው በፕሬዚደንትነት ያገለገሉትን ዲሚትሪ ሜድቬድቭን? ወይንስ ለራሽያ መበታተን እንደዐቢይ ምክንያት የሚታሙትን የቀድሞ የሶቭየት መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭን? ወይንስ መራጮቻቸውን ሁሉ በንግግር ማማር አነሁልለው ሲያበቁ በሴኔቱና በኮንግረሱ የውሳኔ ሰጪነት ከፍተኛ ጫና ሳቢያ የረባ ነገር ሳያከናውኑ የሥልጣን ዙራቸውን የጨረሱትን ባራክ ኦባማን? ወይንስ ከቤት ጠባቂነትና ከቅን ታዛዥነት ባላለፈ አሳፋሪ ሁኔታ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተጎልቶ የከረመውን ኃ/ማርያም ደሳለኝን? ወይንስ በቀድሞው ወያኔ-ትግሬ በሚካኤል ሥሑል አማካይነት በሰባ ዓመት ዕድሜው ተሾሞ ለጥቂት ጊዜ ቤተ መንግሥት ጠባቂ የነበረውን እጀ-ቆራጣ “ንጉሥ”? ወይንስ ወገኖቹን ከፈርዖናዊ ጭቆናና መሪር አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በእግዚአብሔር የተላከውን ሙሤን? የትኛውንም የመሆን ዕድሉ ለአቢይ ክፍት ነው፡፡ ግን ጽጌረዳ አበባ እንኳን በቀላሉ አበባዋን እንደማትሰጥ ሁሉ ለኢትዮጵያ መልካም ነገር ሊያደርግ የሚነሣ ዜጋም በተለይ በዚህን በጊንጥና በእባብ ዘመን አሣር እንደሚገጥመው አስቀድሞ መረዳትና ራሱንም ሆነ ውዶቹን ላለመጉዳትና ላለማሳዘን ልዩ ሥልት ነድፎ መንቀሳቀስ እንዳለበት መጠቆም ተገቢ ነው፡፡….

ስለአቢይ አሁን ላይ ብዙ መናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ በግልጽ ስለሚታወቁ ኹነቶች ግን መናገር ይቻላል፡፡  ወያኔዎች ቆመው በሕይወት እያሉ አቢይ የሚናገረውን የመሰለ ለውጥ በኢትዮጵያ ማየት ከንቱ ምኞት ነው፡፡ ህልም እንኳን መሆን የማይችል ተራ ቅዠት፡፡ ወያኔዎች ጦሩንና ደኅንነቱን ተቆጣጥረው ባለበት ሁኔታ፣ ወያኔዎች የሀገሪቱን የመንግሥት ሥልጣንና ሀብት ንብረቷን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ተቆጣጥረው እየተዘባነኑበት ባሉበት ሁኔታ አቢይ የሚለው ሁሉ በተስፋ ዳቦ ሆድን ከመቀብተት ባለፈ መሬት ላይ ሊታይ የሚችል  አንድም ነገር ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ የኢትዮጵያ ነፃነት የገና ዳቦ አይደለም፡፡ የገና ዳቦ ተቆርሶ እግር ለጣለው ሁሉ ይሰጣል – በእምነቱ ምክንያት ራሱ እምቢ ካላለና ዳቦው ካላለቀ  በስተቀር፡፡ ነፃነታችን ግን ገና ብዙ አሣር አሳይቶ ነው የሚገኘው፡፡ መምጣቱ ደግሞ አይቀርም፡፡ ግን በመስዋዕትነት ነው፡፡

መመኘት ነውር አይደለም፡፡ አይከለከለምም፡፡ አቢይ ጥሩ ጅምሮችን እያሳየን ነው፡፡ እግዚአብሔር ካገዘው ማን ያውቃል ካለብዙ ወጪ ኢትዮጵያ ከነዚህ ነቀዞች የምትገላገልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆናል፡፡ ራሴን እየተቃረንኩ አይደለም፡፡ አንድም ፐርሰንት ብትሆን ለዚህኛው አማራጭ መስጠት እንደሚገባኝ ስላመንኩ ነው፡፡ የፈጣሪ መምጫ መንገድ ደግሞ አይታወቅም፡፡ ምናልባት ከውጫዊው ይልቅ ውስጣዊው የለውጥ ሂደት ለኛ የተሻለ ሆኖ አግኝቶት ቢሆንስ? መጠርጠር ነው፡፡

እውነተኛ ለውጥ መጣ የምለው ግን በትንሹ የሚከተሉት ሁኔታዎች ከተሟሉ ነው፡-

  1. ከሁሉም በፊት ሕወሓት ኢትዮጵያን ማወቅ አለበት፡፡ They have to sincerely give due recognition to Ethiopia and her people; as both their discourses and actions have clearly been displaying that they are somewhat aliens to the land and the citizens as well, we cannot call them Ethiopians.
  2. ሕወሓት በ1968 ዓመተ ምሕረቱ የደደቢት ማኒፌስቶ ላይ ያሠፈረውን አማራንና ኦርቶዶክስን በጠላትነት የፈረጀበትንና ሊያጠፋቸው የቆረጠበትን አንቀጽ መሰረዝ ይኖርበታል፡፡ በዚያ ድርጅታዊ አቋም መሠረት ተጉዞ እስካሁን ያጠፋውን በሚሊዮን የሚቆጠር የሰው ነፍስና የንብረት ውድመት ሁሉ ማመንና መጸጸት ይቅርታም መጠየቅ እንዲሁም ለተጎጂዎች ካሣ መክፈል ይኖርበታል፡፡
  3. በየእሥር ቤቱ የሚማቅቁትን የኅሊናና የፖለቲካ እሥረኞች አለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታትና ተገቢውን ካሣ መክፈል ለተጎሳቆለ ሕይወታቸውና ለባከነ ዕድሜያው ይቅርታ መጠየቅ፡፡ ዜጎችን ለማሰርና ለማሰቃየት የሚሽቀዳደሙ በጥላቻና በቂም በቀለ የሠከሩ ደናቁርት የወያኔ የፀጥታና የደኅንነት አባላትን በማስተማር ወደልማት ሥራ እንዲዞሩ ማድረግ፡፡ የወያኔ አባላት ሰው እንዲሆኑ ከዐውሬነት ባህርያቸው ማላቀቅ፡፡ ሰው የገደሉና ንብረት የዘረፉትን ወደ ፍርድ ማቅረብ፡፡
  4. በየእሥር ቤቱ ምሥኪን ዜጎችን ይገርፉ፣ ወንዶችን በወንዶች ሴቶችንም በሴቶች ይደፍሩና ያስደፍሩ፣ ያሰቃዩ፣ አካል ያጎድሉ … የነበሩ ጭራቆችንና አዛዦቻቸውን ለፍርድ ማቅረብ፡፡ ዜጎች ዳግመኛ እንደነዚህ ባሉ ዐረመኔዎች እንደማይሰቃዩ ማስተማመኛ መስጠት፡፡
  5. ሕወሓት ከሌሎች ክፍለ ሀገሮች ወስዶ ወደ ትግራይ ያካለላቸውን መሬቶች አለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ወደቀድሞ ቦታቸው መመለስ፡፡ በነዚህ የተነጠቁ ቦታዎች ሳቢያ የተገደሉና የተሰደዱ ወገኖችን ይቅርታ መጠየቅ፤ መካስና ወደሥፍራቸው መልሶ ማቋቋም፡፡ በተጋሩ የተነጠቁባቸውን የእርሻና የመኖሪያ ቦታዎች ከነንብረቶቻቸው መመለስ፡፡
  6. ሕወሓት ከመላዋ ኢትዮጵያ የዘረፋቸውንና ወደትግራይና ሌሎች አጎራባች ሀገሮች ያሸሻቸውን ንብረቶች መመለስ፡፡
  7. ሕወሓት ወደትግራይ የወሰዳቸውን የማዕከላዊ መንግሥት መዋቅሮች ለምሣሌ እንደአየር ኃይል፣ የሀገሪቱን አጠቃላይ የመረጃ ቋትና መሰል ብሔራዊ ሀብቶችንና ተቋማዊ መዋቅሮችን ወደ መሀል አገር መመለስ፡፡
  8. በትግሬዎች ቁጥጥር ሥር የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለምሣሌ አየር መንገድ፣ ቴሌ፣ መብራት ኃይል፣ ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ሁሉም የሚኒስቴር መ/ቤቶች፣ በሁሉም ክልሎች ያሉ የጥቅምና የሥልጣን ቦታዎች ወዘተ. ለሁሉም ዜጎች እኩል በሚጠቅም ሁኔታ እንደገና እንዲዋቀሩ ማድረግ፡፡
  9. ሁሉም ኢትዮጵያውያን የእግዜር ፍጡር መሆናቸውን፣ ሁሉም የአንዲት ሀገር ልጆች መሆናቸውን ሕወሓት ከልብ ማመን ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ ለትግሬዎች ብቻ እንዳልተፈጠረች በተለይ አዲሱ ትውልድ አምኖ እንዲቀበል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በግልጽ መስጠት፡፡ ትምህርቱንም በተግባር ማሳየት፡፡
  10. በመላዋ ሀገራችን ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ውስጥ ሕወሓትና አባላቱ ከዜጎችና ከድርጅቶች አላግባብ የዘረፏቸውንና የነጠቋቸውን ንብረቶች፣ መሬቶችና ገንዘብ ለባለቤቶቹ እንዲመልሱ ማድረግ፡፡ አዲስ አበባንና መቀሌን መለየት እስከሚያቅት ድረስ ወያኔያዊ ተጋሩ ሸገርን መቆጣጠራቸው ይታወቃልና ይህን ሌሎች ዜጎችን በኃይል እያፈናቀሉ ሀብትና ንብረትን አላግባብ የማከማቸት ስግብግብነት በአስቸኳይ ማቆም፡፡ ተያይቶና ተሳስቦ በጋራ ለማደግም መወሰን፡፡
  11. ከላይ እስከታች የተንሰራፋው ሙስና እንዲቀንስና በሂደትም እንዲጠፋ፣ የጠፋው የትምህርት ጥራት እንዲመለስ፣ የተበላሸው ባህልና ወግ ልማድ እንዲስተካከልና ከዓለምም ጋር የተዛነቀው ሃይማኖት የመንፈሣዊነት ባሕርይውን እንዲላበስ፣ የቀዘቀዘው ብሔራዊ ስሜት እንዲነሳሳ፣ የተዳፈነው ሰብኣዊነትና የመተዛዘን ባህል ተገልጦ ርህራሄና የርስ በርስ መግባባት እንዲኖር፣… ግልጽ ሀገራዊ ዘመቻ አሁኑኑ መጀመር አለበት፡፡
  12. በአዲሱ የአቢይ አጠራር የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ወደ መድረክ ተጋብዘው ኢትዮጵያውያን በምርጫቸው መንግሥትና የመንግሥት አመራሮችን የሚሰይሙበት ሥርዓት በአፋጣኝ መተከል አለበት፡፡ ሕዝብ ባላቆመው ሕገ-መንግሥትና ሰንደቅ ዓላማ ምክንያት የዜጎች መንገላታትና መታሰር ሊቀጥል አይገባም፡፡ በሕዝብ ያልተደገፈን “ሕገ-መንግሥት” ተቀብሎ አዲስ የሚመስልን ወይን በአሮጌ አቅማዳ ለመጨመር መሞከርና ያን በሕዝብ የተጠላ ከባዶ ወረቀት ያነሰ ዋጋ ያለውን ሰይጣናዊ ሰነድ አሥሬ “ሕገ-መንግሥት፣ ሕገ መንግሥት” ማለት “ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ፣ አፌን አለው ዳባ” ዓይነት ራስን የማታለል ከንቱ ድካም ነው፡፡

ለማንኛውም መጪውን ጊዜ መልካም የተስፋ ዳቦ የምንገምጥበት ወይም አቢያዊው አዲስ የተስፋ ቃል ሁነኛ መስመር ይዞልን ከገባንበት ቅርቃርና መጨረሻው የማይታይ አዘቅት የምንወጣበት ያድርግልን፡፡ ደግሞም በዘርና በጎሣ ወይም በሃይማኖትና በትምህርት ልቀት አንወናበድ፡፡ በተግባር በሚለወጥ የተስፋ ቃል እንጂ በማንነት ዙሪያ የምንደሰትና የምናዝን ከሆነ በአንዲት አጥንት ምክንያት ከሚናከሱ ውሾች አልተሻልንምና ይህም መታሰብ አለበት፡፡ ኦቦ ደቻሣ ከአቶ ስንሻው ወይም ከአይተ ሐጎስ የሚሻልበት ዋናው መለኪያ ኦሮሞነቱ ሣይሆን ለአንዲት ሀገር ልጆች እኩል መቆሙ ነው – አፄ ኃይለ ሥላሤም፣ አባ መላም፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያምም፣ ጄ/ ተፈሪ በንቲም፣ ወዘተ. እኮ ኦሮሞዎች ነበሩ – ኦሮሞ በእሾህና በአሜከላ የታጠረ የጠ/ሚኒስትርነት ቦታ አይደለም የፈላጭ ቆራጩ የንጉሠ ነገሥትነት ቦታም ብርቁ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የጥንት አባቶቻችን እንኳን ያላለፉበትን  ወያኔ-ተከል የጎሠኝነት ልክፍት በአዲሱ ትውልድ ውስጥ ማስረግ አይገባንም፡፡ አንድ አማራ ስለተሾመ  ጎጃምና ጎንደር በአንዴ አያልፍለትም፡፡ አንድ ኦሮሞ ስለተሾመ አርሲና ባሌ በወርቅና በአልማዝ አይንቆጠቆጡም –  ብዙ ነገሮች በላይ ሲያዩዋቸው በስሜት ያማልላሉ፤ ግን ብዙው ነገር ቋንቋ ነው – ልክ እንደመወለድ፡፡ ከስሜት እንውጣ ይልቁናስ፡፡ ወንዝ ከማያሻግር የሥነ ልቦና መኮፈስ ራሳችንን ነፃ እናድርግ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ከእኔ ወደ እኛ ስንዛወር ነው – ከ“እኛ”ና “እነሱ” ጎራ ስንላቀቅም ጭምር፡፡ እኔ ያንተን የኔ የማድረግ ባህል ሳዳብር በተጓዳኝ አንተም የኔን ያንተ የማድረግ ባህል ማዳበር ይኖርብሃል – “አንድ እጅ አጨብጭቦ አንድ እንጨትም ነዶ” አይሆንምና፡፡ ያኔ ነው ታዲያ የእኔ ፍልስፍና በእኛ ፍልስፍና የሚሸነፈውና በእኛና በእናንተ መካከል የሚታየው ክፍተት ተወግዶ ዘላቂ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የሚገነባው፡፡ ለሰዎች ሰውነታቸው ብቻ ይበቃቸዋል – እንደሌሎች እንስሳት ደምና አጥንት ሊያነፈንፉ አይጠበቅባቸውም፡፡ ወረድ ስንል ደግሞ የጋራ አሰባሳቢያችን ኢትዮጵያዊነት አለልን፡፡ የጠላትን ስብከትና ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ እንርሳው – ለማንም ሳይሆን ለራሳችን ስንል፡፡  እስኪያንገሸግሸን አየነዋ!! ([email protected])

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop