April 4, 2018
37 mins read

ምርኮኛ – አገሬ አዲስ

መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓም(04-04-2018)

ምርኮ ወይም መማረክ የሚለው ቃል መሞኘት፣ መታለል፣ መሳብ፣ መያዝ፣መጠመድ፣እጅ መስጠት፣መቸነፍ ፣መደለል… በሚሉ ትርጉሞች ሊገለጽ ይችላል።የሰው ልጅም ሆነ እንስሳ የሚጠመድበት ዘዴ ብዙ ነው።ከደካማ ጎኑ በመነሳት አንዱ ሌላውን ሊይዝበትና  ሊያንበረክክበት የሚችልባቸው መንገዶች ብዙ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ በጥቅም፣በሆድ፣በገንዘብ፣ በስልጣን፣በፍቅር፣በንግግር፣በሃሳብ….የማጥመድ ዘዴዎች በግልጽ የሚታዩና የተለመዱ ናቸው።

በትግል ወይም በጦርነት  ላይ ተፈታታኙን ለማሸነፍ የሚያስችል ስልት መጠቀም አንዱ የድል መሳሪያ ነው።በተሳሳተ መረጃና የተስፋ ቃል ተወናብዶ የተቀናቃኙ ሃይል ትጥቁን እንዲፈታ ማድረግ አንዱ ስልት ነው።

አበው ሲተርቱ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ይላሉ።ብልህ የጦር መሪ  በጦር ሜዳ ጥይት ሳይባክን፣ሰው ሳይሞት የጠላትን ሃይል  ለመበታተንና    እጁን እንዲሰጥ ለማድረግ ከሚጠቀምበት ዘዴና አንዱ ቀዳሚ ስልት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማካሄድ ነው።ይህ አይነቱ ቅድመ ውጊያ በወታደር አጠራር ነጭ ወሬ የመንዛት ዘመቻ ይባላል።ነጭ ወሬ የሌለን ወይም ሊያደርጉ የማይችሉትን የተስፋ ቃል በማራገብ የተቀናቃኙን ጎራ በማማለልና ፍርሃት እንዲንደው በወሬ እሩምታ ተሸብሮ እጁን እንዲሰጥ የማድረጉ ብልሃት ነው።በዚህ ውዥንብር የተደናገጠ፣ ዓላማውን የረሳና የጠላቱን ጸባይ ያላወቀ ሰራዊት የመዋጋት አሞቱ  ፈሶ፣ወኔው ቀዝቅዞ እጁን ለመስጠት ይሽቀዳደማል።ቀድሞ እጁን በመስጠቱ የተሻለ እንክብካቤ፣ ጉርሻ ወይም ሹመት ከጠላቱ የሚያገኝ እየመሰለው ከጎኑ አብሮ የተሰለፈውን ጓዱን ደፍጥጦ ወይም ገሎ ታማኝነቱን ለማስመስከር ይጣደፋል።የሱ መጨረሻ ግን ጠላት ካዘጋጀለት መቀመቅ ጉድጓድ ውስጥ መግባት ይሆናል።በጅልነቱ፣ በስግብግብነቱ ብሎም በከሃዲነቱ የተናቀና የተጠላ እንጂ የተከበረና የተፈራ አያደርገውም።

የሰው ልጅ ለሚሰራው ስራና ለሚወጥነው ዓላማ ከግብ ላይ የሚደርሰው ወይም የሚፈልገውን ሊያገኝ የሚችለው ነገራትን አገናዝቦ ተፈጥሮ በለገሰው አዕምሮ አውጥቶና አውርዶ አመዛዝኖ  የሚያወጣውን ስልት በተግባር ሲገልጸው ብቻ ነው። ስልቱንም የሚነድፈው ከተጨባጩ ዓለም በመነሳት እንጂ በግምትና በይሆናል ቀቢጠ ተስፋ አይደለም። ወይም ጆሮው እየሰበሰበ የሚያመጣለትን ወሬ አዕምሮውን ተጠቅሞ ሳያመዛዝን መልካምና የሚጥም ወሬ በሰማ ቁጥር እልልታውን፣ መጥፎና የሚጠላውን በሰማ ቁጥር ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ኡኡታውን እያቀለጠ በመሄዱ አይደለም።እንደዚያ ከሆነ ጆሮ የአዕምሮን ቦታ በመውሰድ አዕምሮ የጆሮ ታዛዥ ሆኗል ማለት ነው።እንዲያ ከሆነ የሰው ልጅ የተግባር  ሳይሆን የወሬ ምርኮኛ ሆኗል ማለት ነው።

ይህንን ሁሉ እንድል ያስገደደኝ ስልጣን ላይ ያለውን የወያኔ መራሹን ቡድን እንታገላለን፣ከስልጣን መውረድ አለበት፣ የስርዓት ለውጥ እንፈልጋለን ….እያሉ ላለፉት አያሌ ዓመታት ያዙን ልቀቁን ይሉ የነበሩት ምሁራን፣የተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከሁለት ቀናት በፊት በተደረገው የጠ/ሚኒስቴር ሹም ሽር ውዥንብር ውስጥ ገብተው  ይጠይቁ የነበረውንና ቆመንለታል የሚሉትን ዓላማ ሙሉ ለሙሉም ባይሆን በግማሹ መድረሱን፣ያቀርቡ የነበረው ጥያቄ መመለሱን ሳይመለከቱ በሚሰሙት የሚጣፍጥ ቃላት ሲደለሉና በጠላት ስልት ተማርከው እጃቸውን ለመስጠት ሲዳዳቸው በማዬቴ ነው።

ወያኔ “ኢሕአዴግ” በሚለው ጃንጥላው ስር የሰበሰባቸው ግብረአበሮቹ  በመሰረቱት ጨካኝ፣አገር አፍራሽ፣ሕዝብ አጫራሽ በሆነው ስርዓት የሚተገበረው ግድያ ፣ዘረፋ፣ማፈናቀል፣ማሰር፣ ማሳደድ ፣እብሪትና ዛቻ የሕዝቡን እምቢ ባይነት አጎልብቶት ስርዓቱ በትግል ማዕበል ለመገርሰስ እየተንገዳገደ ወደ ውድቀቱ እያመራ በመሄድ ላይ ባለበት ጊዜ ከደጋፊዎቹ የውጭ መንግሥታት ጋር በማሴር በነብስ አድን ዘዴ ሕዝቡ እጁን እንዲሰጥ የሚያደርግ ስልት ለመጠቀም ተገዷል።ስልቱም ከላይ ለማሳዬት እንደተሞከረው በጦር ሜዳ ላይ ፣ትጥቅ ለማስፈታትና ለመማረክ የሚገለገሉበት የነጭ ወሬ ፕሮፓጋንዳ መጠቀምን የሚመስል  ነው።

በተለመደው አካሄድ ሊገፋበት እንዳልቻሉ ወያኔና ግብረአበሮቹ አውቀውታል፤ያም ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚውን ስነልቦና በሚገባ ተገንዝበውታል።በአዕምሮው ሳይሆን በጆሮው እንደሚመራና በሚሰማው ብቻ እንደሚማረክና እንደሚረካ አውቀውታል።ለዚያ የሚረዳቸውንና ብቁ ነው ያሉትን  የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ድርጅት ከተባለው አጋር ድርጅት መካከል፣

ስርዓቱን በተለያዩ ተቋማት የስልጣን እርከኖች  ያገለገለ፣በትምህርት ደረጃው ከነስብሃት ነጋ፣ሞቶም በሚያመልኩበት ጣኦት ከመለስ ዜናዊ መቶ በመቶ የተሻለውን አንደበተ ስልጡን ሰው፣ ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድን ከመካከላቸው መርጠው ፣ በነሱው ፓርላማ  አቅርበው የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ቦታ ሰጥተውታል። እውነትም የተቃዋሚውን ብሎም የህብረተሰቡን ክፍል  ስሜት ለማማለልና  ለመቆጣጠር የሚችል፣ አብዛኛው ምሁርና ተቃዋሚ ነኝ ባይ በጆሮው በሚሰማው ቃላት የሚደለልና እጁን የሚሰጥ፣የላላ ቀበቶውን ከነጭራሹ የሚፈታ ደካማ መሆኑን የተረዳ ብልህ ሰው ነው።

ዶር /ኮሎኔል አብይ አህመድ ከሌሎቹ ልዩ መሆኑን አልክድም፤ግን ስርዓቱ ከሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከተባለ የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና የራቀና የተለዬ ነው አልልም።ያንን ፍልስፍና የተቀበለና የሚያስከብር የስርዓቱ ሹመኛ ነው።ሕገመንግስቱን ለማክበርና ለማስከበር ምሎና ተገዝቶ ቃል የገባ ሰው ነው። በኢሕአዴግ በተባለው አጥፊ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይል  ሰልጥኖ ለዚህ ደረጃና ማዕረግ የበቃ ሰው ነው።ሌላው ቀርቶ  በኢሕአዴግ ከተመለመለ በዃላ የፓርላማ አባላት ተብዬዎቹ መቀበል አለመቀበላቸውን ድምጽ የሰጡበት ሁኔታ ሳይኖር ለመሃላ መቅረቡ ትክክለኛ አሰራር አይደለም።ስልጣኑን ሲቀበል እንዳየነው የፓርላማው እረኛ አባ ዱላ ገመዳ አዲሱን ጠ/ሚኒስቴር በጭብጨባ ተቀበሉ በሚል ቀጭን ትዕዛዝ፣በየትኛውም አገር የፖርላማ ውሳኔ ባልታዬ መልኩ ሹመቱ ጸድቆለት መሃላ  የፈጸመ ሰው ነው።

ዶር አብይ ሹመቱን ተከትሎ ያደረገው ንግግር ለጆሮ የሚጥምና በተስፋ ልብን የሚያማልል ብቻ ሳይሆን ያለው ሁኔታ (Status quo)እንዳለ የሚቀጥል መሆኑን ” የሂሳብ መወራረድ አይኖርም” ሲል በግልጽ ተናግሯል። ያም ማለት የገደለ እንደገደለ በሕግ ሳይጠዬቅ፣የዘረፈና የሰረቀ የያዘው እንዲረጋለት፣የተፈናቀለና የተዘረፈ መብቱ ሳይከበርለት እንደተፈናቀለና ንብረቱን እንዳጣ ይኖራል ማለት ነው።ዜጎች በግል የያዙትን የከተማ ቦታ አቅማቸው የማይችለውን ፎቅ ስሩ እየተባሉ፣ በስበብ ባስባቡ እየተነጠቁ ለስርዓቱ ባለሟሎች መሰጠቱና ለቱጃሮች መቸብቸቡ ይቀጥላል ማለት ነው።ሕግ በማስከበር ሽፋን ለመብቱ የጮኸና የታገለ ወደፊትም ቢሆን በጥይት ይደበደባል ፣ይታሰራል፣ይገረፋል ማለት ነው።አሁንም በመካሄድ ላይ ነው።

“በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ንድፈሃሳባችን የተዘረጋው እድገታችን የሌሎቹን አገሮች ትኩረት የሳበና ያስደነቀ ነው፣አጠናክረን እንቀጥልበታለን” ያለውም ከእውነት የራቀና በዓይን ከሚታዬው የተለዬ ነው።እርግጥ ነው መንገዶችና ፎቆች በየከተማው ተሰርተዋል። ህንጻዎቹ የተሰሩት ግን በአገሪቱ የገቢ ምንጫ ሳይሆን በብድርና በእርዳታ የሚገኘው ተሰርቆ በውጭ አገር ባንክ ከሚቀመጠው ተርፎ በጎሳ ቅርበታቸው ብድር በሚሰጣቸው ሰዎች ነው።ይህም ብድርና እርዳታ ሰጭዎችን ለማታለል እረድቷል፤ የሕዝቡ ኑሮ ግን ከድጡ ወደ ማጡ እየገባና እያሽቆለቆለ ነው።ብዙሃኑ የበይ ተመልካች ሆኗል፤ነውም።የኑሮ ውድነትና ግሽበት ሰፍኗል።ይህም እድገትን ሳይሆን ውድቀትን አመላካች ነው።የምርት ማነስና ማሽቆልቆል የዋጋ ውድነትን ያስከትላል።የለማና ያደገ አገር በስራ አጥ አይጥለቀለቅም፣ ለእህል እርዳታ እጁን አይዘረጋም።የህክምና መጓደል፣ህዝብ ከፍሎ የማያገኘው በመሆኑ በቀላሉ ሊወገዱ የሚችሉ በሽታዎች የሰው ህይወት እየቀጩ ነው። ህዝቡ ለአደገኛና ቀኑ ላለፈ መድሃኒት ብዙ ብር እንዲያወጣ ተገዷል።ሃብታሙ በውጭ አገር ለመታከም መገደዱ የእድገቱ ምልክት አይደለም።የሕክምና ባለሙያዎች በጎሳቸው ወይም በያዙት የፖለቲካ እምነታቸው ወይም ያቋቋሙትን የሕክምና ተቋማቸውን ለባለስልጣናት በሽርክና አሳልፈው አለመስጠታቸው በሌላ የወንጀል ክስ ተተርጉሞባቸው በእስር ቤት እንዲማቅቁ ሆነዋል።ለዚህም ምሳሌ ሊሆን የሚችለው አንዱ ዶር ፍቅሩ ማሩ ነው።

ሌላው በተቃዋሚውና በምሁሮቹ ዙሪያ የሚነፍሰው ማዘናጊያ ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ ሚስቱ ጎንደሬ ናት፣ወላጆቹ ሙስሊሞች  ናቸው፣እሱ ፕሮቴስታንት/ክርስቲያን ነው ባደረገው ንግግር ውስጥ የኢትዮጵያን ስም 37 ጊዜ አንስቷል፤ከዚህ የበለጠ ኢትዮጵያዊነት የለም።ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የመጣ ሙሴ ነው …..ሌላም ሌላም ነገር ተብሏል፣ይባላልም።

እኔ ግን የኢትዮጵያ ሙሴ ሳይሆን ከጥፋት ሕዝባዊ ሞገድ ኢሕአዴግን ለማዳን የመጣ የኢሕአዴግ ሙሴ ነው እለዋለሁ። ለጨቋኙና ለአገር አፍራሹ ሕገ አራዊት እገዛለሁ፣አክብሬ አስከብራለሁ እንጂ ሕዝብ ድምጹን በሰጠበትና በፈለገው፣የአገርን አንድነትና የሕዝቡን የበላይነት በሚያረጋግጥ ሕግ እንዲቀዬር አድርጋለሁ አላለም፤ሊልም አይችልም።

ጎንደሬ ሚስት ስላለው የጎንደርን ሕዝብ በተለይም ወጣቱን ከሞት አላዳነውም፣የሙስሊም ቤተሰብ በመሆኑም የመብት ጥያቄ ያቀረቡትን የሚስሊሙን ተወካዬች ከስቃይና ከእስራት አላዳናቸውም፤ጢማቸው በእሳት እየተለበለበ፣ጥፍራቸው እየተነቀለ በእስር ቤት እሱ በመራውና ባጠናከረው የደህንነትና የስለላ ተቋም ስቃያቸውን ሲያዩ ለምን?ብሎ ድምጹን

አላሰማም።ክርስቲያንም በመሆኑ የመነኮሳት ገዳም ሲፈርስ፣ ሲበዘበዝ፣መነኮሳት ሲገደሉ፣ መብታቸውን በመጠየቃቸው ሲታሰሩ እያዬና እያወቀ ስህተት መሆኑን ደፍሮ ድምጹን አላሰማም።ኦሮሞም በመሆኑ እራሱ የበላይ በሆነበት ክልል የኦሮሞ ወጣቶች፣እናቶች በጥይት ሲቆሉ፣ሲገደሉ፣ሲታሰሩ፣ሲሰደዱ ፣ሲፈናቀሉ አይቶ እንዳላዬ ሰምቶ እንዳልሰማ በስልጣን ወንበሩ ላይ ተቀምጦ የቆዬ ነው።

በሹመት ንግግሩ ላይ የኢትዮጵያን ስም 37 ጊዜ ማንሳቱ ሳይወድ በግድ ማድረግ የሚገባው ነው።የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ነኝ ካለ የሆነበትን አገር ስም ማንሳትና ማውሳት የግድ ይላል።ለአገራችን አዲስ ስም የሰጠ ይመስል በቀን ከሽህ ጊዜ በላይ የምናነሳውንና የምንሰማውን፣ጠበበኞች በስዕል፣በዘፈን ፣በግጥም አሽሞንሙነው የሚያነሱትን ኢትዮጵያ የሚል ስም በዶር

ኮሎኔል አብይ አህመድ አፍ ሲወጣ ስለሰማን አዲስና ያልተለመደ፣የማናውቀው ነገር አድርገን  መቁጠሩ የግንዛቤያችንን ድክመት እንጂ የሱን ብስለት አያመለክትም።እንኳንስ ተወልዶ አርባ አምስት ዓመት የኖረባት፣የተማረባት፣ለስልጣን የበቃባት ሰው ቀርቶ ጠላቶቿ ሳይቀሩ በስሟ ይጠሯታል።የኢትዮጵያን ስም በማንሳት ብቻ ቀና መሪ ተደርጎ የሚያስቆጥር ቢሆንማ ኖሮ ንጉስ ሃ/ስላሴ በስልጣን ዘመናቸው ስንት ጊዜ ኢትዮጵያ አገራችን ብለው ነበር? ያ ከንቱ አረመኔ መንግስቱ ሃይለማርያምስ በየዲስኩሩ የኢትዮጵያን ስም እያነሳ ለፍልፎ አልነበረምን?ታዲያ  ያ ብቻውን ተወዳጅና ተቀባይ መሪ ያደርጋል?ከስልጣን ከመባረር አዳነው?ቁም ነገሩ የኢትዮጵያን ስም ደጋግሞ ማንሳቱ ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ጠቃሚ ስራ መስራቱ ነው። የዶር/ኮሎኔል አብይ ኢትዮጵያ  በሚያገለግለው ስርዓት ወደብ አልባ የሆነች፣ድንበሯ ተቆርሶ ለጎረቤት አገሮች የተሰጠ፣የክፍላተ ሃገር አዋሳኝ መሬት እየተቀማ ለባለጉልበተኛው የሚሰጥባትና ሕዝብ የሚፈናቀልባት ፣ፍትህ ያልሰፈነባት፣የጎሳ ፖለቲካ የሰፈነባት ፣እንደ አገር መኖሯ የሚያጠራጥር ኢትዮጵያ እንጂ የምንኮራባትና ሳንሸማቀቅ የምንኖርባት ኢትዮጵያ አይደለችም።  በታሪክ ጸሃፊዎቻችን የምናውቀውን  ታሪካችንን፣የአድዋን ፣የማይጨውን የመተማን የካራማራን ድል፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያደረገችውን እስተዋጽኦ በመናገሩ የተደበቀ ታሪክ ፈልፍሎ እንዳወጣ ታምረኛና ብቸኛ አድርገው የቆጠሩት ብዙዎች ናቸው።መለስና ሌሎቹ ሊያነሱ የማይፈልጉትን ብሏል፤ግን መለስ ይመራበት የነበረውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና መመሪያው እንደሆነ አልደበቀም።

እርግጥ ነው ባለፉት ሁለት ዓመታት የተቀጣጠለው ትግል በኢሕአዴግ ውስጥ ትርምስና የእርስ በርስ ውዝግብ መፍጠሩ አይካድም። ከነስብሃትና አባይ ጸሃዬ፣ከነስምኦንና ስዩም መስፍን እንዲሁም በሌሎቹ አጁዛ መሪዎቹ የሚመራው ህወሃት በዕድሜ ለግላጋ የሆኑት የሕዝቡን ስሜት በተረዱት በነዶር አብይ አህመድና  በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦሕዴድ ከብአዴን መሪዎች ጋር በማበር ባዛዣቸው በህወሃት ላይ አንገራግረዋል።ማንገራገር ብቻም ሳይሆን አንታዘዝም በማለት ፍጥጫ ላይ ነበሩ።ወያኔ የማይፈልገውን እርምጃ ሁሉ ወስደዋል።አሁንም በመውስድ ላይ ያሉት በተለይም በመናገር ደረጃ የሚገልጹት  ወያኔ ይፈልገውና ይከተለው  ከነበረው መንገድ የወጣ ነው።በስልት ይለያያሉ።ይህ ጎዳና እስከዬት እንደሚወስዳቸው የሚታወቅ አይደለም።እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ግን ወያኔ የማያንሰራራና ጥቅሙ የሚነካበት ከሆነ በዝምታ እንደማይቀበለው ነው።ጭልምተኛ(ፔሲሚስት)ነህ ባልባል

1 ዶር አብይን ምክንያት ፈጥረው በኩዴታ ወይም በአደጋ ሊያሶግዱ ይችላሉ

2 ሕጉን ተጠቅመው የኡጋዴውን አጋራቸውን አስከትለው የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል።በዚህ አገሪቱ ቀውስና ብጥብጥ ውስጥ ትገባለች፤ትግራይን ገንጥሎ ከኤርትራ ጋር የመቀላቀሉን  ምኞት ለማሳካት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።

እነዚህ አስፈሪና የማይፈለጉ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ ከተፈለገ የትግራይንና የኦጋዴን ሕዝብ ከወያኔና ከኦጋዴን አስተዳደር አመራር እጅ ፈልቅቆ ማውጣት ነው።ሕዝብ ለሕዝብ የሰላምና የመግባባት ግንኙነት መፍጠሩ ተገቢ ነው። አደጋውን ሊያሶግድና መሰሪ የህወሃትና የኦጋዴውን መሪዎች ነጥሎ  ዋሻ ይሆነናል ብለው የሚያምኑበት  ሕዝብ እራሱ እርምጃ እንዲወስድባቸው የሚያስችል ስራ መሰራት አለበት። በተጨማሪም የልዩነት ግምብ የሆነውን ጎሳ ተኮር ፖለቲካ አመለካከትና የክልልን ግምብ ማፈራረስ ነው።ወደ ቀድሞው የክፍላተሃገር አወቃቀር መመለስ አንዱ መፍትሔ ሲሆን የመለያዬት ጎዳና የከፈተውን ሕግ መሰረዝ ዋና አስተማማኝ መሳሪያ ነው።የጎሳ መተካካት ግን ችግሩን ቋሚና ውስብስብ ያደርገዋል።

የውጭ አገር ሃይሎች የአፍሪካን ሕዝብ ለዘመናዊና በእውቀት ላይ ለተመሰረተ የፖለቲካ ፍልስፍናና ስርዓት ብቃት እንደሌለው ይቆጥራሉ።በነሱ እምነትና ግንዛቤ ያፍሪካ ሕዝብ በጎሳ የተከፋፈለና ዓላማ ቢስ የሆነ፣ ከአውሬ የማይሻል፣፣የጎሳ

ውጣ ውረድ በማድረግ የሚረካ ነው።ለመውረርና ለመያዝ ሲያስቡም የሚጠቀሙበት መንገድ ይህንኑ ነው።ለኢትዮጵያም ሕዝብ ጥያቄ የሚሰጡት መልስና  ምክር ከዚህ በመነሳት ነው።በይፋ እንደሚናገሩት ባለፈው ስርዓት የአማራው ጎሳ ፣ ላለፉት 27 ዓመታትም እስከ አሁን ድረስ የትግሬ ጎሳ በመቀባበል የስልጣኑ ባለቤቶች ሆነዋል፤የወደፊቱ ደግሞ የኦሮሞው መሆን አለበት የሚል መርዘኛ ምክር ለግሰው በተግባር ላይ ለመታዬት በቅቷል።ነገ ደግሞ የጉራጌው፣የጋምቤላው፣ያፋሩ፣

….ተራ መሆን አለበት ብለው በጎሳ ንትርክ እየተጋጨን  ለአንድነትና ለሰላም ለልማትም ሳንበቃ እንደ ዘመነ መሳፍንት በእርስ በርስ ውጊያ  ደቀንና ደክመን የነሱ ጥገኞችና የጦር  መሳሪያ ሸማቾች ሆነን እንድንቀር የሚያደርገንን መርዝ መቀመማቸውን ልንገነዘብ ይገባል።በተለይም ለኢትዮጵያ ቀና ልቦና የላቸውም።ወረራቸውን ተቋቁማና አሸንፋ አዋርዳ የመለሰች፣ለሌሎቹ ያፍሪካና የሌላ ቀኝ ግዛት አገሮች የነጻነት ምሳሌና ረዳት የነበረች አገር በመሆኗ መኖሯን አይወዱም። የበቀል ኢላማ አድርገዋታል።ሊያጠፋት የተሰለፈውን ሁሉ በግልጽና በሚስጥር ከመርዳት አይመለሱም።ከነሱ በኩል መፍትሄ ይገኛል ብሎ የሚባዝነው ባተሌ በጣም ያሳዝናል።ለጥቅማቸው እንጂ ለእኛ ብለው የሚያደርጉት ነገር የለም።ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሚያዋጣን ትልቁ መሳሪያችን በራስ መተማመንና ህብረታችን ነው።

መቼም ምኞት አይከለከልምና ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ  ለለውጥ የተነሳ ነው፣ ጊዜ እንስጠው የሚሉት ሃሳብ ከግምት ውስጥ ይግባ ቢባል እንኳን ያለበትን ሁኔታ ማየቱ ተገቢ ነው። የሚወክለውና የመረጠው ኢሕአዴግ የተባለው ድርጅት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ዙሪያውን የከበቡት የወያኔ አገር አጥፊ ቡድኖች ናቸው።የጦር ሃይሉ፣የፖሊሱ፣የደህንነቱ፣የኤኮኖሚው አውታሮች ሁሉ በወያኔ ቁጥጥር ስር ናቸው።ከዚህ ስንነሳ ዶር አብይ በቅርጫት ውስጥ ያለ እርግብ ይመስላል ማለት ነው። እርግቧ ወይ አትበር፣ወይ አትራመድ በቅርጫቱ ውስጥ ተወስና  ለአጭር ጊዜ፣አሳሪዋ እስኪያባርራት ወይም በጩኸቷ ተናዶ እስኪያሶግዳት ድረስ በተሰጣት ቦታ ትኖራለች ማለት ነው።የዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድም እጣ ፈንታ ከዚህ የተለዬ ሊሆን አይችልም ብዬ እሰጋለታለሁ።በሰውነቱ ይህ አይነቱ አደጋ ሲደርስበት ማዬት ደግሞ ያሳዝነኛል።የተቀመጠበት ወንበር የእሳት ወንበር ነው።ሲያዩት ያምራል፣ ሲቀመጡበት ያቃጥላል።ቀደም ሲል፣ከወራት በፊት ባዘጋጀሁት ጽሁፍ እንደገለጽኩት ስልጣን በሩቁ ያጓጓል፣ደስ ይላል፣ሲቀርቡት ይሞቃል፣ጭራሽ ሲይዙትና ሲያቅፉት ያቃጥላል ብያለሁ። ስለሆነም ዶር/ኮሎኔል አብይን እንኳን ደስ ያለህ ሳይሆን የምለው  ጥናቱንና ብርታቱን ይስጥህ ፣አንተንም አገርህንም ከወያኔ ቅርጫት ያውጣችሁ ነው ።ሌላውን በጆሮው በሚሰማው ወሬ የሚማረከውንና እጁን የሚሰጠውን የህብረተሰብ ክፍል በተለይም በተቃዋሚ ጎራ ያለውን፣የስልጣን ተካፋይ ልሆን እችላለሁ ብሎ በጉጉት የሚጠብቀውንና  የሚዋዥቁትን ቡድኖች የነቃና የሚያመዛዝን፣ጆሮን የሚያዝ እንጂ በጆሮ የማይታዘዝ አዕምሮ ይስጣችሁ፤ከወያኔ ጉድጓድ ያድናችሁ እላለሁ።

የዓላማ ጥናት ያለው ዓላማው እስኪሳካ ድረስ አይፍረከረክም። በትግል ሂደትና ጉዞ ውስጥ ወጭና ወራጁ ብዙ ነው። በትግሉ መንኮራኩር ወይም ባቡር ላይ የሚሳፈረው ከሚፈልገው ጣቢያ(ፌርማታ) ላይ ሲደርስ ዱብ ይላል።እስከ መጨረሻው የባቡሩ ጣቢያ የሚዘልቀው ጥቂቱ ነው።አሁንም በዚህ አጭር ጊዜ ያዬነው ይህንኑ እውነታ ነው።በቄሮ ዙሪያ የማለሳለስና የመርካት አዝማሚያ እዬታዬ መጥቷል።ትግሉ ሃይለማርያም ደሳለኝ በዶር/ኮሎኔል አብይ መቀየር አለበት በሚል ፍላጎት ላይ ያተኮረና መልስ ያገኘ መስሎ ታይቷል።ነገ ደግሞ አንዲት ነጠላ ጥያቄ መልስ ካገኘች ከትግሉ ባቡር የሚወርድ አይጠፋም።ለስር ነቀል ለውጥ፣ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት፣ለዜጎችና ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዴሞክራቲክ ስርዓት መስፈን የሚታገለው ቆራጥ ክፍል ግን ሳይሽመደመድ በሚጥሙ ቃላት ሳይወናበድና ሳይማረክ የጀመረውን ትግል መቀጠል ይኖርበታል።

ኢትዮጵያን ካለችበት ሁኔታ አወጣለሁ የሚል መሪም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት የሚከተሉትን ተግባሮች ማሟላት ይኖርበታል 1 እስረኞችን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት

2 የጊዜያዊ አዋጁን ማንሳት

3 የመከላከያና የፖሊስ ሃይሉን በሚመለከትው ተግባር ላይ ብቻ እንዲሰማራ ማድረግ፤አሁን በሕዝብ ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ ማገድና ወደ ጦር ሰፈሩ መመለስ።ለሙያው ብቃት እንጂ የጎሳ ማንነት እንዳልሆነ በተግባር ማሳዬት

4 በግፍ ለተገደሉና በእስር ቤት ለተሰቃዩት፣አካለስንኩላን ለሆኑት፣ ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች ካሳ በመስጠት ከደረሰባቸው የህሊና ስብራት እንዲያገግሙ፣በኖሩበት ቦታ ተመልሰው በሰላም እንዲኖሩ ዋስትና መስጠት

5 ወንጀል የፈጸሙ፣የገደሉ፣በሙስና የተጨማለቁ፣ ሕዝብ ያሰቃዩ፣የዘረፉ በፍርድ እንዲቀጡና የወሰዱት ንብረት፣ቦታ ለባለቤቱ ተመላሽ እንዲሆን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ

6 ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት፣ማህበር፣ግለሰብ በነጻነት ሃሳቡን የመግለጽ፣የመሰብሰብ፣የመቃወምና የመደገፍ  መብቱን ማክበር፤የሚዲያ ዘርፉን የሁሉም መገልገያ እንዲሆን ማድረግ፤በውጭ አገር ያሉ የተቃዋሚ ሃይሎች ካለምንም ስጋትና ገደብ አገራቸው ገብተው የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ዋስትና መስጠት።

7  የሚመጣው ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊና አስተማማኝ እንዲሆን ከአሁኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት፣የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፤ወያኔ የነደፈውንና ኢሕአዴግ የሚመራበትን “ሕገመንግስት”መቀበል እንደቅድመ ሁኔታ አለማስቀመጥ ፤ ለወደፊቱ በህዝብ ተሳትፎ የጸደቀ፣ ከመንግሥት በላይ የሆነ ሕግ እንዲሰፍን ማመቻቸት

8 ለአገር ሰላምና አንድነት፣ለሕዝብ አብሮነትና ትስስር ጸር የሆነውን የአሁኑን ስርዓት መሰል የሚያራምድ በጎሳና በሃይማኖት አቅጣጫ የሚደረግ ማንኛውንም ቅስቀሳና ፣የፖለቲካ ዓላማ ያለው አደረጃጀትን በሕግ መከልከል

9 ህዝቡን የለያዬውና የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ የጣለውን የመገነጣጠል አደጋን እንደ መብት ያስቀመጠውን ሕግና አንቀጽ በአስቸኳይ መሰረዝ።

10 በየመስሪያ ቤቱ ሕዝቡን በሙስና የሚያስጨንቁና ያልተገባ ውሳኔ የሚሰጡትን ባለስልጣኖች የሚከታተል፣የህዝቡን ብሶት የሚያዳምጥ(ዕምባ ጠባቂ)ቢቻል በየመስሪያ ቤቱ አለዚያም በአካባቢና በአገር አቀፍ ደረጃ ( Local and national ombudsman) አካል በአስቸኳይ ማቋቋም

እነዚህን ለማስፈጸም የተጀመረው ትግል መቀጠል ይኖርበታል፤በችሮታ ሳይሆን በትግል የሚገኙ ውጤቶች ናቸው።

የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት በጎሳ ፖለቲካ ያልተደራጀውና መደራጀትንም የሚቃወመው ኢትዮጵያዊ በያለበት በመሰባሰብ ሃይሉን መገንባት አለበት፣እጁን አጣጥፎ በመቀመጥ ወይም ሌላው ያደርግልኛል በማለት ከዳር ቆሞ ሊመለከት አይገባውም።

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኖራለች!

አገሬ አዲስ

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop