ነገሩ አንዳንዴ ቢሆንም፣ ከሐዘን ወደ ደስታ የሚወስድ ነገር መቼም አይታጣም። በዚህ አኳያ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ምድር ላይ ካላው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲተያይ ደስታዬን ከፍ አድርጎታል። ቀጥሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ የሚለው ግምቴም ትልቅ ነው። ገና ምኑ ታይቶ ሊባል ይቻላል፤ ተገቢ ነው።አላያማ ያመኑት… የተባለው ብሂል መከተሉ ነው። የታሰበው ካልሆነ የተለመደውን ብዕሬን ማሾሌ አይቀሬ ነው። ብቻ ለጊዜው ፍቀዱልኝና ደግ ደጉን ልበል! የለማ መገርሳ ቡድን አይበገሬውን ኃይል ተዳፍረዋልና ሊበረታታ ይገባዋል ባይ ነኝ። የለማ መገርሳ ቡድን ይህን ጥንካሬ ያገኘው ሕዝቡን በመስማቱና ከሕዝቡ ጋር በመወገኑ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሉታዊ ጥርጣሬም አብሮኝ አንዳለ ልደብቅ አልችልም። በወደፊት ጉዞችን ላይ አንዳችም ጋሬጣ አይኖርም ከሚሉት ወገን አይደለሁም። ሁሉም ተሳካ፤ ሁሉም ሰመረ፤ ድል በድል ሆንን ብዬ ሽንጤን ገትሬ፣ አፌን ሞልቼ የምናገርበት ጊዜ ላይ አልደረስኩም። ለጊዜው ግን ለሕዝባችንና ለዶ/ር አብይ አህመድ በጎውን ተመኝቻለሁ።
ዶ/ር አብይ የተረከቡት ሃላፊነት አገራችን በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ሰዓት ላይ ነው። በአንዳንዶች አባባል አገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ ቀውስ ሰፍኖባታል። የግዛት አንድነቷ ሳይቀር አደጋ ተደቅኖበታል። ዶ/ር አብይ የጥንቱን ኮሮጆ ዳበሰው፣ የድሮውን መዝገብ አገላብጠው ልምራ፣ ችግሩንም ልቅረፍ ካሉ፣ሁሉም ነገር ታጥቦ ጭቃ መሆኑ ነው። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ዓይነት ወጥመድ ተተብትበው ነበርና! በመሆኑም የፈየዱት አንዳችም ነገር የለም። ዶ/ር አብይ እራሳቸውን የሕዝብ ተመራጭና ተወካይ አድርገው ካልወሰዱ፣ ችግሩ የባሰ ሊሆን ይችላል።ኢትዮጵያን የሚያክል አገር፣ የአንድ ፓርቲ ብቻ ጥቅም አስጠባቂ ሆኖ መመራት ከቶም አያዋጣም። ይህንን ለማድረግ አሻፈረኝ ካሉ፣ኢህአዴግን ብቻ የሙጥኝ ካሉ፣ የሕዝቡን አመኔታና ድጋፍ በፍጥነት ሊያጡ ይችላሉ።ይልቁኑ ታሪክ የጣለባቸውን አደራ በሚገባ ቢወጡ፣ አገራችን እንድ እምርታ ወደፊት ትሄዳለች።
ማንኛውም የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች የተፈጠረውን በጎ ጅምር ለመጠቀም፣ በሰላማዊ መንገድ ዓላማቸውንና ፕሮግራማቸውን ለሕዝቡ ለማስተዋወቅ ከአሁኑ ማቀድ ይኖርባቸዋል። ዘወትር ጥላቻን ብቻ መንዛቱ ጠቃሚ አይሆንም። ሕዝቡን መሰማት፣ ከሕዝቡ ጋርም መመካከር ተገቢ ነውና። በጥላቻ ተመስርቶ የሕዝቡን አብሮ የመኖር ባሕል መሸርሸር ግን ለማንም አይጠቅምም።በተለያየ ምክንያቶች ጠመንጃ ያነገቡ ኃይሎች በሰላማዊው መንገድ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምኞቴ ነው። በዚህ አጋጣሚ የአገራችንን መከፋፈል የሚመኙ፣ የሚቋምጡ፣ አጋጣሚውንም የሚናፍቁ ካሉ እርባና ቢስና ቅዥት አራማጆች ናቸው።
ከዶ/ር አብይ አህመድና ከካቢኒያቸው በአስቸኳይ ምን ይጠበቃል?
- በሕዝባችን መካከል መቀራረብ እንዲዳብር ማድረግ፣የነበረውም እንዲቀጥል ማበረታት፣
- በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ ያሉትን የሲቪክ ማህብራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፣ ምሁራን፣ የሕዝብ ተወካዮችን …ወዘተ በአገራችን ጉዳይ ላይ በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፋና እንዲመክሩ ማስቻል፣
- አስችኳይ አዋጁን ማንሳት፣
- ጦሩ በድንበር ጥበቃ ላይ እንዲሰማራ፣ በአመራር ደረጃም ለውጥ ማድረግ። በደህንነት መሥሪያ ቤቱም ላይ የአመራር ለውጥና አገራዊ ጥቅም ባለው መልክ እንዲዋቀር ማድረግ፣
- የታሰሩ የፓለቲካ እስረኞችን ያለ አንዳች ቅደመ ሁኔታ መፍታት፣
- ፍርድ ቤቶች፣ ምርጫ ቦርድ፣ የፀጥታ ኃይሎች የአንድ ፓርቲ አገልጋይ እንዳይሆኑ ማስወሰን፣
- የመሰብሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍ፣ በጠቅላላው ዲሞክራሲያዊ መብት እንዲጠበቅ ማድረግ፣
- ብሔራዊ እርቅ የሚሰፍንበትን መንገድ ማመቻቸት፣
- በአጭር ጊዜ ውስጥ ዲሞክራሳዊ ምርጫ የሚካሄድበትን መንገድ ማሳናዳት፣
- የኢኮኖሚ ልማት እንዲካሄድ መጣር፣ ሁሉም ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን መሞከር፣
- ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ የነበሩ መርሐ ግብሮችንና ፖሊሲዎችን በድጋሚ መርመር፣ ጠቃሚ ያልሆኑትን ማስወገድ፣
- በጠላትነት ከተፈረጁት ጎረቤት አገሮች ጋር ግንኙነቱ የሚሻሻልበትን መንገድ ማጤን የሚሉትን ያጠቃልላል።
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ተጓዳኝ ሃሳቦች በሥራ ላይ ከዋሉ እሰየው ከሚሉት ወገን ነኝ። በድጋሜ ለለማ መገርሳ ቡድን፣ ለቄሮ፣ ለፋኖ፣ ለዘርማ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጋድሎ አድናቆቴን እገልጻለሁ።
ቸር ቸሩን ያሰማን !!