February 11, 2018
33 mins read

“አፈ ጮሌን ላለማመን አብነቱ ሀብታሙና ልደቱ” – ግርማ በላይ

ተስፋ ከመቁረጥ የተነሣ ሊሆን ይችላል፡፡ “ምን አዲስ ነገር ላገኝ?” ከሚል ድምዳሜም ይሆን ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ዘመን-አመጣሽ የመልእክት ሣጥኔን(ኤሜይሌን) ለብዙ ጊዜ አላየሁትም ነበር፡፡ ዛሬ ስከፍተው ግን የሚያናድደኝን ነገር ቁጭ ብሎ አገኘሁት፡፡ “ምነው ባልከፈትኩት!” ብዬ ተናደድኩ፡፡ ግን ደግሞ እንኳንም ከፈትኩት፡፡ ትንሽ ልተንፍሳ! እስከመቼ ታፍኜ?

በተማሪነቴ ወቅት ርዕሳቸውን ከተመለከትኳቸው የተማሪዎች የሂስ ጽሑፎች አንደኛው ምን ጊዜም አይረሳኝም፡፡ “ልብ-ወለድ ላለማንበብ አብነቱ ‹የቀይ ኮከብ ጥሪ›ን ማንበብ” ይላል፤ ማራኪ ርዕስ ነው፡፡ “የኔንም ርዕስ ከዚያ ነው የኮረጅኩት” ለማለት ነው በዘወርዋራ፡፡

“የሀብታሙ አያሌው ቅጥፈትና የባዶ ቅል ጥሬ መንኳኳት ተምሳሌት”  ግዛቸው ሽፈፈራው(ኢንጂነር)

ሃብታሙ አያሌው
“አፈ ጮሌን ላለማመን አብነቱ ሀብታሙና ልደቱ” - ግርማ በላይ 1

ኢንጅነር ግዛቸው ስለ ሣተናው ወጣት ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው የጻፉትን ይህን ዘለግ ያለ ጦማር በአንድ የድረገጽ ባለቤትና አዘጋጅ ተልኮልኝ አገኘሁና አነበብኩት፡፡ ጽሑፉ በተለጠፈበት ወቅት ገረፍ ገረፍ አድርጌ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ነገር ግን ነገር ሲቆይ በደምብ ይገባል መሰለኝ አሁን ስደግመው የጽሑፉ ይዘት አለመታደላችንን ባገዘፈ መልኩ በንዴት አተከነኝ፡፡ “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” እንዲሉ በየመድረኩ በስሜት እየተንደቀደቁ ስለሕዝብና ስለሀገር ነፃነት የሚጮሁ “ወገኖች” (በቂ ማስረጃ እስከማገኝ “ተኩላዎች” ማለት ባለመቻሌ ማዘኔን ተረዱልኝና) ውስጣቸው ሲታይ ምን ዓይነት ገመና እንደታቀፉ አንድ ተግባራዊ ምሣሌ ለማየት ይህን የኢንጀነርን ጽሑፍ በጥልቀት ማንበብ ጠቃሚ ነው፡፡ ኢንጂነር ልክ እንደኔ አንድ እግራቸው በዚህኛው አንድ እግራቸው ደግሞ በዚያኛው ዓለም የሚገኝ እንደመሆኑ በሀብታሙ ላይ ያን ያህል ርቀት በመጓዝ ይህን የመሰለ አስደንጋጭ የሀሰት ወሬ ፈጥረው የልጁን “መልካም ስምና ዝና” ያጎድፋሉ ብዬ ለማመን በጣም እቸገራለሁ – ስለጽድቅና ኩነኔ ከሀብታሙ ይልቅ እርሳቸው በቂ ግንዛቤ እንዳለቸውም ስለማምን ይህን ያህል ወርደው በሀሰት የሰውን ስም የሚያጠለሹበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ በሌላም በኩል እርሳቸውን ልክ እንደ መልአክ ንጹሕ እምንጹሓን አድርጌ መውሰድም እንደሌለብኝ አውቃለሁ፡፡ ሰው እንደመሆናቸው ሊያጠፉ ወይም ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ ስህተታቸውን ካመኑና ይቅርታ ከጠየቁ ደግሞ በቀድሞ ስህተት ሲወቀሱ ሊኖሩ እንደማይገባ እረዳለሁ፡፡ ለማንኛውም ስለሀብታሙ በጻፉት ጉዳይ ላይና ሀብታሙ ስለርሳቸው ስለጻፈው ስድብና ዘለፋ አዘል ሀተታ እርሳቸውን በአካል አግኝቼ ተጨማሪ መረጃ ባገኝ ደስ ባለኝ፡፡ ግን እርሳቸው በጻፉት ላይና በተመሳሳይ ሌሎች ጽሑፎች ላይ ተንተርሼ የጥቂት መሰል አጭበርባሪ የሁለት ዓለም ሰዎችን ቁንጽል ታሪክ በዚህች አጭር መጣጥፍ ለማስታወስ ወደድኩ፡፡ ይህን ለማድረግ የደፈርኩት አካፋን አካፋ ካላሉት የሚያመጣው ዳፋ  ልክ እንደኛው ሁኔታ ሁሉ ሀገርን ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ እየጎተተ መቅኖ የሚያስቀረው ትልቁ ማኅበረሰብአዊ ነቀርሣ በአንድ በኩል ይህ ዓይነቱ የዜጎች እስስታዊ ባህርይና በሌላ በኩል ይህን መጥፎ ባህርያቸውን ለመግለጽ እኛ ሕዝቡ የምናሳየው ግዴለሽነት ወይም ይሉኝታ መሆኑን ለማስገንዘብም ጭምር ነው፡፡  በተረፈ የሀብታሙ ውስጣዊ ማንነት በመታወቁ እኔ ድምቡሎ አላገኝም፡፡ ሀገርና ወገን ግን ይጠቀማሉ፡፡ ከመሰል አጭበርባሪዎችና ከዓዞ ዕንባ አንቢዎች ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡

መተዋወቅ ጥሩ ነው፡፡  እንደመተዋወቅ ያለ ጠቃሚ ነገር የለም፡፡ ይሁዳ ክርስቶስን በመሳም አሳልፎ መስጠቱን እናውቃለን፡፡ ይህ ሰው ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ይልቅ በክርስቶስ ተመራጭ ነበር፡፡ ስለተመረጠም ነበር የግምጃ ቤት ኃላፊ የነበረውና ገንዘብና ማንኛውም ንብረት ሁሉ በርሱ ቁጥጥር ሥር እንዲውል የተደረገው፡፡ ሀብት ያሳሳል፡፡ ንብረት ያስጎመጃል፡፡ ገንዘብ ያባልጋል፤ የኅሊናንም ሚዛን  አዛብቶ የኃጢኣትና የወንጀል ጎተራ ያደርጋል፡፡ ስለዚህም ነው ይሁዳ ከክርስቶስ ፍቅርና የዘላለምም ክብር ወጥቶ ከጠባቡ የጽድቅ መንገድ ይልቅ በሰፊው የብልጭልጭ የኃጢኣት መንገድ በመጓዝ በዚያች መናኛ 30 አላድ ጌታውን አሳልፎ ለአራጆቹ የሸጠው፡፡ እርሱ ይህን ካደረገ እነልደቱና ሀብታሙ በምን ጎናቸው ይችሉታል ይህን ከባድ የሥጋ ፈተና? መፍረድ አስቸጋሪ ነው ወንድሞቼ፡፡ “ወልደህ ሳትጨርስ/ሳትጨርሽ…” የሚባል አባባል ደግሞ አሁን ትዝ አለኝ – (እንዲህ ያለ ግፍ አትናገር/አትናገሪ ለማለት ነው)፡፡

በመሠረቱ ብዙ መናገርም ሆነ መጻፍ አያስፈልግም፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያችን የሰው ድርቅ የመታት ዕድ-ቢስ ሆናለች፡፡ የምናምነው ይከዳናል፡፡ ሰዎችን ባስቀመጥናቸው ሥፍራ አናገኛቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ የኛን መስቀል ተሸክመው ብዙ መከራና ስቃይ የተቀበሉ የሚመስሉን እንደሀብታሙ ያሉ ወጣቶች ያን ፍዳ ለመቀበል የፈቀዱት ድብቅ ዓላማ ስላላቸው መሆኑን ስንረዳ የመረገማችን ምሉዕ በኩልሄነት ይከሰትልንና አንዳንዶቻችንና ነገሩ የገባን በጭንቀት የምንገባበትን እናጣለን፡፡ ብዙዎቻችን በንግግር ማማርና በሀሰትና በፈጠራ ታሪክ ተጋንኖ በተገነባ  ተክለ ሰውነት እንማረካለን፡፡ ከመማረካችንም የተነሣ ፈጣሪን እስከምንረሳ ድረስ በግለሰቦች ወደማመን እንደርሳለን፡፡ በዚህ ዓይነቱ አካሄዳችን ብዙ ተጎድተናል፡፡ ሀገራችንም ወደማትወጣው አዘቅት የገባችበት ዋናው ምክንያት በነዚህን መሰል የጭቃ ውስጥ እሾህ ዜጎች ነው፡፡ አጭበርባሪ ቁጭ በሉዎችም እኛ ሕዝቡም መቼ ልብ እንደምንገዛ አይገባኝም፡፡ እናሳዝናለን፡፡

አፈ ጮማዎች በንግግራቸው ሰውን ያነሆልላሉ፡፡ በዓለማችን ዙሪያ ብዙ አፈ ጮሌዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ ወደፊትም መኖራቸው አይቀርም፡፡ እነሱን አምኖ ገደል የገባውና አሁንም ድረስ እየገባ ያለው  ሕዝብ ደግሞ ቁጥሩ የትዬለሌ ነው፡፡

አንድ ወቅት በኔ በራሴ የደረሰ ነገር ላውጋችሁ፡፡ ወያኔ እንደገባች ሰሞን ነው፡፡ በዚያን ወቅት አካባቢ የጄኔራል ወርቁ ዘውዴ ዘበኛ እንደበረ የተነገረለትና በኋላ ላይ ኑሮ ሲከብደው ወዳልተበላበት የሃይማኖቱ ዘርፍ በመግባት “ባህታዊ ገ/መስቀል” በሚል የክት ስም ሕዝብን “የሚቀፍል” አጭበርባሪ ተነስቶ ነበር፡፡ እንዲህ በአነጋገሬ “የባለግሁት”ና ይህን ወንበዴ በዚህ መልክ የገለጽኩት ያኔ ስለዚህ ወሮበላ ሰውዬ ስል ከሰው ጋር የተጣላሁበትን ያለፈ ታሪክ ለማጣጣት ወይም ለማካካስ ነው፡፡ እናላችሁ በርሱ ስብከት ክፉኛ ከመነደፌ የተነሣ ስለሰውዬው አጭበርባሪነትና አታላይነት ጓደኞቼ ሲናገሩ ስሰማ ከምር እጣላቸው ነበር፡፡ በውነቱ ብዙ ጊዜ ተጣልቻለሁ፡፡ አንድ ሰው በስሜት ሲታወር ምን ሊያደርግ እንደሚችል ይህ ትዝታዬ በግልጽ ያስታውሰኛል፡፡ እንደኔ የዚያን ጊዜው እኔነቴ ዓይነት ሰዎች በስሜት ፈረስ እየጋለቡ ጥቁሩን “ነጭ ነው”፣ ነጩን “ጥቁር ነው” በሚል ስንትና ስንት ጉዳት በግለሰብም ሆነ በሀገር ላይ እንደሚያደርሱ ይታያችሁ እንግዲህ፡፡  … እየቆዬ እውነታውን ሳጣራና ወደኅሊናየ ስመለስ ግን ያኔ ስለ “ባሕታዊ”ው ይነገር የነበረው ተዓምር ሁሉ ሆን ተብሎ በአጋፋሪዎቹና በተከፋይ አሰለጦቹ እየተደረሰ የሚተወን ትያትር እንደነበር ገባኝ (በእሥር ቤት መላእክት እንደሚያናግሩት፣ እሥር ቤቱን በመለኮታዊ ብርሃን እንደሚሞሉት፣ …ብዙ ይነገርለት ነበር)፡፡ ስንቱን አታለለው መሰላችሁ! ሕዝባችን ደግሞ ለመታለል በጣም ምቹ ነው፤ መጠየቅንና መመራመርን እንደወንጀልና እንደኃጢኣትም የሚቆጥር ዜጋ በሚበዛበት ሀገር ወንጀለኞችና አጭበርባሪዎችም ይበዛሉና በጣም እየተጎዳን ነው፤ በዚያ ላይ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው “አትመራመር፤ ትቀሰፋለህ” የሚል ስለነበርና (ስለሆነም) ይህ ኢ-ክርስቶሳዊ ትምህርት ለአወናባጆች ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸው እስካሁን ዘልቋል – ክርስቶስ ግን ያለው “ሁሉን እዩ የሚበጃችሁን ግን ያዙ” ነው – “ኩሎ አመክሩ ወዘሠናየ አፀንዑ” “ እንዲል መጽሐፍ ቅዱሣዊ ብሂሉ፡፡ በነገራችን ላይ እያወቀም የሚታለል ሳይኖር አይቀርም፡፡ ያ ሰው አሁን አማርጦ ያገባትን ሴት ይዞ ቀጨኔ አካባቢ ልጆቹን እየፈለፈለ ይኖራል፡፡ ማንም ዝምቡን እሽ ያለው የለም፡፡

እርሱን መሰል ቁጭ በሉዎች በየሰበካው ሞልተዋል – ከጳጳስ እስከ ዲያቆን – ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፡፡ ለመታለል ዝግጁ የሆን ገልቱ ምዕመናን ደግሞ በሚሊዮን የምንቆጠር አለንላቸው፤ ታራጅ እስካለ የአራጅ ችግር የለም፡፡ የሀገር ግንባታና የነፃነት ጎሕ መቅደድ የሚታሰበውና የሚታለመው እንግዲህ በዚህ ዓይነቱ ማኅበረሰብኣዊ መቼት ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ ልደቱንና ሀብታሙን የመሰሉ እሳተ መለኮቶች ይቅሩና ታምራት ገለታንና እህተ ማርያም ተብዬዋን የመሰሉ ከ4ኛና ከ8ኛ ክፍል ያልዘለለ ትምህርት ያላቸው ቁጭ በሉዎች እንኳ በቀላሉ ያሞኙታል፡፡ ተጨንቀናላ! በወያኔ ግፍና በኑሮ ጣጣው ሳቢያ ሰማይ ምድሩ ዞሮብናላ! እንዴ – እኔም እኮ እግዜርን ፈርቼ እንጂ ሀሙስና ቅዳሜ መጋረጃ ጣል ባደርግ ታምራት ገለታን አስከነዳ ነበር፤ ለብቻየ እንደልቤ የማሾረው አንድ የግል “ቸርች” ባቋቁም እኮ እኮ ከጥበበ ወርቅየና ከታምራት ላይኔ በሚያስንቅ ሁኔታ “ሕዝበ ክርስቲያን”ን መግፈፍ እችል ነበር፤ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ የጨነቀውና የጠበበው ሁሉ እስራኤል ዳንሳንና ፓስተር ዳዊትን የመሰሉ የዘመናችን ሀሣይ መሢሆች የሚመሯቸውን ቤተ አምልኮዎችና የአባይ ጠንቋይ ቤተ ጣዖታት የሆኑ አውሊያ ቤቶችን ሲያጣብብ ማምሸት ማደሩን ስንገነዘብ ነዳጅ ያለቀባትና ኮምፓስ የጠፋባት መርከብ ፊታችን ላይ ድቅን ልትልብን ትችላለች – ኢትዮጵያን ተመስላ፡፡ በዚህ ዘመን ጠንቋይና ቄስ ወይም ደብተራና ፓስተር መሆን በጣም ያዋጣል፤ ወፍራም እንጀራም ያበላል፡፡ የትንግርት ዘመን ነው፡፡ ሰው እንዴት እየባሰበት ይሄዳል? ወደፊት መጓዝ ቢያቅተው እንዴት ያለውን  እንኳን ይዞ ሕይወትን መቀጠል አቃተው?

ካነበብኩት አንድ ነገር ላስታውስ፡፡ አንድ ራሱ በእግዚአብሔር የማያምን ሰው በቀን ሚሊዮኖችን በመስበክ የእግዚአብሔርን መኖር ያሳምን ነበር አሉ፡፡ በድራማውም ዓለም ብዙ ገጸ ባሕርያትን እናያለን – ያልሆኑትን ሆነውና መስለው ሲከውኑ፡፡ ይህ ዓይነቱ የማስመሰል ባሕርይ በነልደቱና ሀብታሙ ውስጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ እነዚህን መሰል ሰዎች የራሳቸው ማንነት የላቸውም፡፡ Simply put, they are vessels of some abstract being, most certainly, of devilish nature. ልደቱ ሲናገር እንዴት እንደሚያፈዝ እኔ በግል አውቃለሁ፡፡ በባሕርዩ ግን ሁላችንም ሰውዬውን በግልፅ እንደምናውቀው በገንዘብ ሊገዛ የሚችል 360 ዲግሪ ተጣጣፊ ሰው ነው፡፡ ይህንንም በምርጫ 97 ወቅት በሚገባ አሳይቷል (በተንሸራታች ባሕርይው ምክንያት ከወያኔ በሚያግበሰብሰው ይሁዳዊ ገንዘብ በአሁኑ ወቅት አክሱም ላይ ባለአራት ኮከብ ሆቴል ገንብቶ ሥራ ላይ አውሏል ይባላል)፡፡ እርሱን መሰል ፍጡራን ሥልጣን ወዳድ ናቸው፡፡ ዝና ያነፈልላቸዋል፡፡ የሀብት ፍቅር ያናውዛቸዋል፡፡  ለሀብትና ለሥልጣን ሲሉ የማይገቡበት ጉድጓድ የለም፡፡ ደግሞም የማንም መጠቀሚያ ናቸው፡፡ Money can buy. ሴተኛ አዳሪ እንኳ አንዳንዴና ኪሷ ሞቅ ሲል የምትመርጠውና የምታንጓልለው ወንድ አለ – የማታስተናግደው፡፡ በነዚህ ሰዎች ዘንድ ግን መምረጥ ቃሉም አይታወቅም፡፡ የከፈለ ይጠቀምባቸዋል፡፡ በቀላሉ ስለሚያኮርፉም ከአንዱ ወደሌላው ለመሸጋገር የሚወስድባቸው ቅጽበት ከዐይን እርግብግቢት ሊያንስም ይችላል፡፡ ጥንቃቄን ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ምሥጢረኛ ማድረግም አይቻልም፡፡  ከ“እኛ” ይልቅ “እኔ”ን የሚያበዙ፣ ናርሲሲዝም በሚባለው ራስን የማምለክ ሥነ ልቦናዊ ልክፍት  የተጠመዱ በመሆናቸው ስለ ሃይማኖት ያላቸው ግንዛቤ ሲቃኝ ደግሞ እጅግ ደካማ ነው፡፡ ስለሆነም እነሱን ወደ ሃይማኖት ለማስገባት መሞከር ከንቱ ልፋት ነው፡፡ ራስን ከማምለኩ ጋር በተያያዘ ጉረኝነትና ስለራስ ጀብድና ጉብዝና መደስኮር ዋና መገለጫቸው ነው፡፡ በሞቀበት ይዘፍናሉ፡፡ የቡድንንም ሆነ የግለሰብን ትኩረት (attention) በጣም ይፈልጋሉ፡፡ ትኩረት(attention) ያጡ ከመሰላቸው ያኮርፋሉ፤ ቡድንም ይለውጣሉ፤ ግለሰብም ከሆነ እንደማያውቁት ያህል ጥርቅም አድርገው ይዘጉታል፤ አያናግሩትም፤ ሰላምታም ይነፍጉታል፡፡ በሀሜተኝነትም እነሱን የሚስተካከል የለም፡፡ ሰውን በውሸት ማብጠልጠልና በፈጠራ ወሬ ማበሻቀጥ ትልቁ የተካኑበት “ሙያቸው” ነው፡፡  ምሥጋናና ሙገሣን አፍቃሪዎች ናቸው፡፡ ነቀፋንና ትችትን በሩቁ ይፈራሉ፡፡ ምክንያቱም ምንም ጉድለት እንደሌለባቸው የሚያምኑ ግብዝ ፍጡራን ናቸውና፡፡ የራሳቸው የሆነ አቋምም ሆነ የማንነት መገለጫ የላቸውም፡፡ ይሉኝታቢስነትና ሀፍረትየለሽነት ልብሳቸው እንጂ የሚያፍሩባቸው አይደሉም፡፡ የሚሸጥ ቢያጡ እናታቸውንና ሚስት ልጆቻቸውን ሣይቀር እንዳወጡ ይቸበችባሉ – ለገንዘብና ለዝና ሟች ናቸው፡፡ ትዝብት ብሎ ነገር አያውቁም፡፡ በንግግር ደፋሮች ናቸው፡፡ ንግግራቸው ምን እንደሆነ ሳይሆን ምን ውጤት እንደሚያመጣ ብቻ ነው ዋና ትኩረትና ጭንቀታቸው፡፡ የሕወት ጥሪያቸውን አያውቁም፤ ለማወቅም ጉጉቱ የላቸውም፡፡ ሀገርንና ሕዝብን እንደሚወዱ በንግግራቸው ያስምሩበት እንጂ አስመሳዮች ናቸው፤ እናም ሀገርና ወገን ከነሱ ጥቅም አይበልጥም፡፡ ስለሆነም የሀገርና የወገን ፍቅር የላቸውም፡፡ ጥዶ ዘለልነት የሚያጠቃቸው የብትን አእምሮ ባለቤቶች ናቸው፡፡ በጥቅሉ በቁም ሊለቀስላቸውና የቁም ተዝካር ሊወጣላቸው የሚገባቸው አሳዛኝ ስብዕና የተላበሱ ናቸው፡፡ ስለነዚህ ሰው መሳይ በሸንጎዎች ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን ብዙዎቻችን ስለምናውቃቸው ከዚህ በላይ መድከም አያስፈልግም፡፡

እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ውስጥ የሚከተሉትን በጉልኅ እናገኛለን፡፡ እኔ ትዝ ያሉኝን አስቀመጥኩ፡፡ እናንተ ደግሞ የምታውቋቸው ካሉ ተናገሩ፤ ደግሞም አሉ፤ ብዙም ናቸው፡፡ አዎ፣ በግልጽ መነጋገር ነው፡፡ የምንጠነስሰው ጠላ ሁሉ ገና በዝልሉ እየሾመጠረ ሀገርና ሕዝብ አጥተን የቀረነው በነዚህ ዓይነቶቹ ሞጭላፋ አሰለጦች በመሆኑ ለነሱ ማዘን በገዛ አንገት ላይ ገመድ እንደመጠምጠም ነው፡፡ ወደ ሥልጣንና ወደንግዱ እየገቡ ሀገርንና ማኅበረሰብን የሚያምሱት እነዚህን መሰል ሆዳሞችና ይሉኝታ ቢሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በጮሌ አፋቸው እንደሚወሻክቱት የሕዝብ ወገኖች ቢሆኑ ኖሮ – ለአብነት ያህል – ሀብታሙ አያሌው ይህን የመሰለ አስነዋሪ ስድብ በኢሜል በመላክ ባውለታውን አያስቀይምም ነበር፡፡

 

“እኔን አናድዳለሁ ብለህ ኮምፒውተር ላይ ስትውል ተጠናግሮ የሚያለቅሰው አይንህ እንዳይጠፋ። እኔ ንቄ ትቼሃለሁ ቅናት ያንገበገበህ ወራዳ መሆንህን ሁሉም ስለተረዳ ካልደከመህ ቀጥል።እኔ እንዳንተ ካለው እርባናቢስ ተጠናግሮ ከሚያክ ሰው ጋር ልመላለስ! ” (አፅንዖት የተጨመረ)

 

አንባቢ ይፍረደው፡፡  “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ይላሉ  የዱሮ አባቶች ይህን መሰል ውስብስብ ችግር ሲገጥማቸው፡፡ ይህን ዓይነት ክርት ጠባይ ይዞ የሚቃዥባት አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ቢገባ በቲቪ መስኮት ብቅ ብሎ “ እናንት ቅማላሞች የኢትዮጵያ ሕዝቦች … “ ብሎ በስድብ እንደማይሞልጨን ምንም ዋስትና የለንም፡፡ “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ” ማለት አሁን ነው፡፡ እግዜር ይሁነን እንጂ ወያኔ ያላስማረን ነገር የለም፡፡ ወጣቶቻችንም አንድም ሳያስቀሩ ሁሉንም የክፋትና የዘረኝነት “ትምህርት” ልቅም አድርገው ነው የተማሩት ፡፡

ክርስቶስ ስለኔ ተገረፈ፤ ተሰቃዬ፤ ተሰቀለም፡፡ ይሁንና በአንዱም የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ አልሰደበኝም – አከበረኝ እንጂ፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው “የሚሰድቧችሁን መርቁ” ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ወገን ለመሆን መታሰርና መገረፍ ብቻውን እንደማይበቃ ቢያንስ ከዚህ መጣጥፍ አንዳች ግንዛቤ ልንጨብጥ እንደሚገባን በታላቅነቴ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ “ታላቅ ነኝ” የምለው በዕድሜና ምናልባትም በተሞክሮ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ ሕዝብ የሚወደውንና የሚያከብረውን ይወዳል፡፡ የሚያዋርደውንና የሚሰድበውን ግን ይጠላል፡፡ የሕዝብ ሰው ነኝ የሚል ኑሮው በከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተመራ አሣሩ ብዙ ነው፡፡ ጥቃቅኗ ነገር ሁሉ ትመነዘርና ሕዝባዊ ክብርንና ፍቅርን ታጎድልበታለች፤ ታሳጣዋለችም፡፡ ቀን አድጦን አንዴ የምትቀለበስ የሕዝብ ፍቅርና ሙገሣ ደግሞ በቀላል አትመለስም – ሊያውም የምትመለስ ከሆነ፡፡ እነኃይሌ ገ/ሥላሤን ማየት ነው፤ እነሠራዊት ፍቅሬን መታዘብ ነው፤ እነሣምሶን ማሞን ማስታወስ ነው፤ እነአርቲስት ሸዋፈራሁን አለመርሳት ነው፤ … እነዚህና መሰል የወያኔ አሽቃባጮች ሁሉ ነገ የነፃነት ፀሐይ ስትወጣ በሀፍረት ካባ ተጀቡነውና አንገታቸውን ደፍተው የሚኖሩ ኅሊናቢስ ዜጎች ናቸው – እንደዔሣው በጭብጥ ምሥር ወንድሞቻቸውን የካዱ፤ እንደ ቃየል በክፉ መንፈስ ተለክፈው ወንድሞቻቸውን ከሚገድሉ ክፉዎች ጋር የተባበሩ ከይሲዎች ወይም ግድያውን ያልተቃወሙ አድርባዮች፤ እንደይሁዳ ለንዋይ ሲሉ እናታቸውን የካዱ ከርሳሞች…፡፡ በመሠረቱ እነዚህ ዜጎች ነገም ሆነ ከነገወዲያ እንደማንኛውም ዜጋ በነፃነት መኖሩን የሚከለክላቸው የለም፡፡ ኢትዮጵያ የነሱም ሀገራቸው ናትና፡፡ ግን ማንም ሳይገላምጣቸው በራሳቸው ታሪካዊ ስህተት ብቻ በሀፍረት እየተሸማቀቁ  ለመኖር የሚገደዱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህም ነው ሁላችንም በጥንቃቄ መኖር የሚገባን፡፡ የፈሰሰ አይታፈስም ወገኖቼ፡፡ ጉዳዩ ስላለህና ስለሌለህም አይደለም፡፡ አልማዝና ወርቅ ብታፈስም የጠፋ ስምህ አይታደስም፡፡ ያቺ የንብ ከናቴራ ማንን ጉድ እንደሠራች እናውቃለን ወንድሜ! ስለዚህ በምንም ነገር አንታበይ፡፡ መታበይ ካለብን በፈጣሪ ብቻ ይሁን፡፡ ሁሉም ነገር ደግሞ ያልፋል፤ በዚህም እንመን፡፡

  1. ዶክተር ፕሮፌሰር ኢንጂነር ፊልድ ማርሻል የዓለም ሎሬት የኖቤል ተሸላሚ ልደቱ አያሌው – የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የጦር ኃይሎች ኤታ ማዦር ሹም፤ የቀይ መስቀል የበላይ ጠባቂ፤ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊ/መንበር፤ የተ.መ.ድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሰብሳቢ፣ የህክምና ሊቅ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ የፍልስፍና ሊቀ ሊቃውንት፣ የከርሰ ምድር አጥኚ፣ የሕዋ ተመራማሪ፣….
  2. ዶክተር … ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) – የኢትዮጵያ የዕድሜ ልክ ፕሬዝደንት….(ከላይ ያለውን ለሁሉም ድገሙልኝ እባካችሁ!)
  3. ፕሮፌሰር … ሀብታሙ አያሌው – የኢፌድሪ ጠ/ሚኒስትር፣ …
  4. ዶክተር … አብርሃም ያዬህ … የቀድሞ የሕወሓት ታጋይ፣ የመንግሥቱ ኃ/ማርያም የቅርብ ጓደኛ፣ የመለስ ዜናዊ ዘመድና የዱሮ ሽርክ፣…
  5. ባህታዊ ገ/መስቀል – ርዕሰ ጳጳሣት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ርዕሳ ጳጳስ ዘአክሱም፣ የዓለም አብያተ ክርስቲን ጉባኤ አባል፣ የሁለት ሴቶችና የሁለት ወንዶች አባት……
  6. ሚዲያ የማያውቀንና በየመንደሩ ጁንታ መሆን የምንፈልግ በብዙ ሚሊዮኖች የምንቆጠር ግልብ ዜጎች …

 

እኛ እንዲህ ነን እንግዲህ፡፡ ከዚህ አስጠሊታ ዐውድ ካልወጣን ምኞታችን ህልም፤ ህልማችንም ቅዠት እየሆነ ምን ጊዜም የባለጌዎች መጫወቻ እንደሆን እንቀራለን፡፡ ወያኔ ነገ ይሄዳል – ወይም ዛሬ ማታ፡፡ ግን ጠባይና ምግባራችን በዚሁ መልክ ከቀጠለ በቁጥር እንጂ በግብር የማይለያዩ ወያኔዎችን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተናገድን እንኖራለን፡፡ ስለዚህ ውስጣችንን እንመርምር፡፡ በጭፍንና በወረት አንመራ፡፡ የሚጠቅመንን ከማይጠቅመን፣ እውነተኛን ከሀሰተኛ፣ ተኩላና ቀበሮን ከየዋሃን ምሥኪን በጎች የመለየት ዕውቀትና ችሎታን እናዳብር፡፡ ባለንበት መርገጥ ይብቃን፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop