March 12, 2018
14 mins read

ዘመነ መሣፍንት እና ክልላዊ የስልጣን ሽኩቻው (በ ሙሉጌታ ገዛኸኝ)

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ዘይቤዎችን ስትከተል የኖረች አገር ናት፡፡ ከገጠሟት ብዙ ውጣ ውረዶች መካከል የኢማም አህመድ ግራኝ ወረራ ሰፊ ሽፋን ይይዛል፡፡ ጦርነቱን አጼ ገላውዲዎስ በድል ቢያጠናቅቅም የተስተጓጎለው አገግሞ ወደ ነባራዊው ሁናቴው የመመለሱ ጉዳይ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ በተከታታይ የነገሱ ወራሾችም ጎንደር ላይ ከትመው አገሪቱን ማስተዳደር ቀጠሉ፡፡ ቀስ በቀስ ሀይላቸው እየተዳከመ መጣና በምትካቸው አውራጃዊ መሣፍንቶች ጡንቻቸውን ማፈርጠሙን ተያያዙት፡፡ ነገሥታቱም የስልጣናቸውን ሀይል ሚዛን ሳይዛባ ለማስጠበቅ ሻል ያለ ሞግዚት ፍለጋው ላይ አማተሩ፡፡ ዘላቂ ውጤት እምብዛም ባያስገኝም በዘመኑ ጉልበተኛ ከነበሩት የየጁ እና የትግሬ መሣፍንት ፖሊቲካዊ ጋብቻ ትስስሩን ማደርጀት እንደሚበጅ ብልሀት ዘየዱ፡፡ ሆኖም በማያባራው የስልጣን ሽኩቻ ማዕከላዊነት እየደበዘዘ የአገሪቱ አንድነትና ሰላም መናጋትን አስከተለ፡፡

የዘመነ መሣፍንት ክስተት የቋራው አንበሳን ቁጭት ወለደ፡፡ ሥርዓት አልኝነት የተጠናወታቸው የጎጃም፤ የበጌምድር፤ የትግሬ፤ የየጁ፤ የሸዋ እና የወሎ መሳፍንቶችንም ፊለፊት ተፋለማቸው፡፡ ድባቅ በመምታት አገሪቱ ወደ ነበረችበት አንጻራዊ መረጋጋትና ማዕከላዊ አስተዳደሩ መልክ ለማስያዝ የበኩሉን ጥረት አደረገ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ለዛሬውም የአገር አንድነትና ክብር ወኔ ማሰሪያ ውል ገመዱ እሱ ሆነ፡፡ ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ለመቅደላ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ “የቋራው አንበሳ ካሳ፤ በመቶ ኣመቱ ቢያገሳ፤ ኧረ ስንቱን ቀሰቀሰውሳ፡፡” ሲል የቋጠረው ስንኝ ግሩም ነው፡፡

በአባ ታጠቅ ካሳ ጠንካራ ጡንቻ ተደቁሰው የክፍፍል ምኞታቸው ገታ ያሉት መሣፍንት  ቅሬታቸውን በጉያቸው ሸሽገው ምቹ አጋጣሚ ሲጠባበቁ ቆዩና እንከን ጋረጡበት፡፡ በእንግሊዞች ወረራ ወቅት የአጼ ቴዎድሮስ መዳከም ለስልጣን ፉክክሩ አግዟቸዋል፡፡ በተለይም ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ዋነኛ ተዋናይ በሆኑበት እንቅስቃሴ እንግሊዞች ወረሂመኖ ድረስ ያላንዳች እንቅፋት ሰተት ብለው ለመዝለቅ ቻሉ፡፡ ከመቅደላው ጦርነት በኋላም ስልጣን ለመረከብ ከወዲያ ወዲህ ሲራወጡ የነበሩትን የሰሜን ኢትዮጵያ ባላባቶችና መሣፍንቶች በእንግዘሊዞቹ ገሸሽ ተደረጉ፡፡ ደጃች በዝብዝ ካሳን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ስልጣኑን እንዲረከብ ለዋግሹም ጎበዜ ገብረመድህን(አጼ ተክለጊዮርጊስ ተብለው የነገሱት)ጥሪ አቀረቡላቸውና አስረክበው ወደ መጡበት እንግሊዝ እብስ አሉ፡፡ አፍታም ሳይቆዩ መታለላቸው ያስቆጫቸው በዝብዝ ካሳ ብልሀት ፈጥረው እህታቸውን ለአጼ ተክለጊዮርጊስ ጋብቻ አቀረቡ፡፡ በአማችነት አሳበው ሰልታኑን እንዴት እጃቸው እንደሚገባ ጉዳዩን ሲያጤኑ ሰነባበቱ፡፡ ለሦስት ዓመታት ብቻ የነገሱት አጼ ተክለ ጊዮርጊስ ዘውድ ለመንጠቅ በዝብዝ ካሳ ሸፈቱባቸው፡፡ በተካሄደው ውጊያ ደጃች በዝብዝ ካሳ ተሳካላቸው፤ አጼ ዮሐንስ ራብአይ ተሰኝተው በአክሱም ጽዮን ዘውድ ደፉ፤ ነገሱ፡፡

ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው የተማከለ አስተዳደር በመላው አገሪቱ ለማስፈን አጼ ዮሐንስ ልዩ ልዩ ጥረቶች ቢያደርጉም ባጋጠሟቸው ተደጋጋሚ የውጭ ወረራዎች ከግብፅ፣ ከኢጣልያ፣ በመጨረሻም ከድርቡሾች(መሀዲስት ሱዳን) ጋር ተዋግተው ለህልፈተ ህይወት ዳረጋቸው፡፡ የዘውድ ተቀናቃኛቸው የነበረው የሸዋው ምኒልክ በውጫዊ ሀይሎች ምክንያት የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ያላሰለሰ ጥረት አደረገ፡፡ በተለያየ ሁኔታ እያንገራበዱ ያስቸገሩ አውራጃዊ መሳፍንት ሁላ በምኒልክ ተመቱ፡፡ ቀጥሎም ወደ ስልጣኔ ጎዳና አገሪቱን ለመምራት መሰረቱ ተጣለ፡፡ ኢጣልያ የወረራ ምኞቷ ቅዠት ሆኖ በታሪካዊው የአድዋ ጦርነት ተጨናገፈባት፡፡ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነ ቢሆንም ከአጼ ምኒልክ መሞት በኋላ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ተገብቶ አገሪቱ እንደገና ታመሰች፡፡ የአቤቶ ኢያሱ ወራሴ መንግስት ተላልፎ ብዙም ሳይዘልቅ በአጭር ተቀጨ፡፡ የንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ እና የራሥ ተፈሪ መኮንን አልጋወራሽና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ ጥምር አስተዳደር ተዋቀረ፡፡ ከንግስቲቱ ሞት ማግስት በጥቅምት 1923 ዓ.ም ልዑል አልጋወራሽ ዘውድ ደፉ፤ አጼ ኃይለ ሥላሤ ተሰኝተው ነገሱ፡፡ ለስልጣናቸው መገዳደርን ላሳዩ ይገባኛል ባይ ባላባቶች በረቀቀው ‘ዘመናዊ’ ሕገ መንግስት ከጨዋታ ውጪ ሆኑ የኋላ ኋላም ፊት ተነሳቸው፡፡ ለይስሙላ ያህል የጎጃምና የትግራይ ባላባቶችንም በዘር ሀረግ ውርስ ከፊል ራስ ገዝነት ተፈቀደላቸው፡፡

ዘውዳዊ ሥርዓት በምድር አርዕድ ተቃውሞ እየተናጠ በ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ተገልቦ አከተመ፡፡ በወቅቱ የአገሪቱን ስልጣን ለመቆጣጠር የሚችለው ወታደራዊው ጁንታ ራሱን ደርግ በማለት ሰይሞ ወደ አደባባይ ብቅ አለ፡፡ የደርጉ መንግስት ስልጣንን በአንባገነናዊነት አጠናክሮ በሌተና ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም አማካኝነት ቀጠለ፡፡ የጊዜያዊ ወታደራዊ ሥርዓቱ ዲሞክራሲያዊነትን ያልተላበሰ በመሆኑ ከልዩ ልዩ ወገኖች በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ በረታበት፡፡

የትጥቅ ትግልን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመውሰድ የኤርትራ እና የትግራይ ነጻ አውጭ ቡድኖች ጫካ ገብተው ሥርዓቱን ፋታ ነሱት፡፡ ተገተጉት፡፡ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባርም ጥያቄውን አላቆመም ነበር፡፡ የአገሪቱም አንድነትና ህልውና ሳይዘልቅ በውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖ ስር የተፈተነው የደርግ መንግስት ከአስራ ሰባት ዓመት ግብ ግብ በኋላ ሽንፈትን ለማስተናገድ ተገደደደ፡፡ ከተገባበት አረንቋ ለመውጣት ያግዛል የተባለ አካሄድ በአሸናፊ ቡድኖች የበላይነት እንዲሁም በአሜሪካ ፍላጎት የሽግግር መንግስት ጥሪ ቀረበ፡፡ በወቅቱ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የፖሊቲካ ሀይሎች የተሳተፉበት ነገር ግን እያደር እየዋለ አዝማሚያውን አይተው አፈገፈጉ፡፡

የሽግግር ዘመኑ አምስት ዓመታት ቆይቶ በ1987 ዓ.ም በቋንቋ ማንነት ላይ መሰረቱን ያደረገው የብሔር ብሔረሰቦች አስተዳደር የፌዴራላዊ ሕገ መንግስት ተረቆ በስራ ላይ ዋለ፡፡ አራቱ ዋና ዋና ክልሎች ግንባር ፈጥረው የትግራይ(ህወሀት)፣ የአማራ(ብአዴን)፣ የኦሮሞ(ኦህዴድ) እና የደቡብ(ደኢህዴግ) ኢሕአዴግን መስርተው አጠናከሩት፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ የታዳጊ ክልሎችና አጋር ድርጅቶች የሚል ስያሜ አግኝተው ላላ ያለ የትብብር ግንኙነት ተመቻቸላቸው፡፡

የኢሕአዴግ የሚያጋጥሙትን ማናቸውንም ተግዳሮቶች ምንጭ በቀድሞዎቹ አገዛዞች ላይ አሸክሞ ድምዳሜ ላይ መድረስ ብቻ ሆነ፡፡ የሥርዓቱ ዋና መለያው ራሱን ከቀድሞ አገዛዞች ጋር እያነፃፀረ ቁንጅናውን መለፈፍ ሲሆን ድክመቶቸን ግን ማንም አይንገረኝ ይላል፡፡ የአሁኑ አስተዳደር ሲዘረጋና ሲተገበር የራሱ በርካታ እንከኖች እንዳሉበት እንኳ ፈፅሞ አይቀበልም፡፡ እንዲሁ በከንቱ ይሸፋፈናል፡፡ በአንድም በሌላም መንገድ የችግር አፈታት መፍትሄው በስራ ላይ በዋለው ሕገ መንግስት ብቻ እንደሚሆን ዘወትር ይነገራል፡፡ ግን…

በፌዴራሉ መንግስት እና በክልሎች መካከል የስልጣን መጋራቱንና ግንኙነቱን አስመልክቶ ምን መሆን እንዳለበት በህግ ተደንግጓል፡፡ በክልሎች በኩል አሁን በሚታየው አግባብ ግን ለፌዴራሉ መንግስት ያላቸውን ተገዳዳሪነት በይበልጥ እየጎለበተ መሆኑን ነው፡፡ ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ ክልላዊ ምስፍና በዘመናዊ መልክ ለማስተናገድ እየተገደደ መምጣቱን ለመታዘብ ይቻላል፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የስልጣን መተካካት እንደ መሣፍንቱ ዘመን እርስ በርሳቸው ክልሎች እየተሻኮቱ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው የጤና አይመስልም፡፡ አካሄዱ የሰለጠነ ነው ቢባልም አንዱ በሌላኛው ላይ እያደባ የጎሪጥ ተጠባብቆ መተያየቱ ዛሬም ላይ ሆነን ከዘመነ መሣፍንቱ አውራጃዊ አባዜ ገና ያልተላቀቀ ነው፡፡ ሥርዓቱ ከዚህ ዓይነቱ አዙሪት ይወጣል የሚል ግምት ማስቀመጥ ቢያዳግትም አካባቢያዊነት እየጦዘ ከጊዜ ወደ ጊዜ እርስ በርስ አገራዊ መግባባት ላይ እንኳ መድረስ የማይቻልበት አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ አንድነቱ ተጠብቆ የጋራ አገር የማቆየቱ አመለካከት እየላላና እየደበዘዘ ውዝግብ ማስከተሉም በራሱ ስጋት ያጭራል፡፡ በሁሉም ወገኖች ዘንድ የቀጭን ገመድ ያህል ትስስር ወደመለያየት እሳቤ አዘንብሏል፡፡ ይህንኑ ማስለላት ላይ ብቻ ያውጠነጠነ መሆኑ ግን ሳያስተዛዝብ አይቀርም፡፡ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም በቀጣይ የምንቃኝ ይሆናል፡፡ አገራችንን ሰላም ትሁን፤ ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!

1 Comment

  1. The current situation in Ethiopia can not be analogous to the so called `era of the princes or regional kings`. It misrepresents the reality in the country. The TPLF constitution itself ensures and provieds for regional authonomy and self rule. But the TPLF has remained in control of everything including the resources and in the end people have begun demanding their democratic rights. The struggle has involved the grassroot ansd is not the kind of ppwer struggle among the regional elites.

Comments are closed.

Previous Story

ኢትዮጵያ፡ ጆሮ ያለው ይስማ (ከዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

Next Story

ልጄ ሆይ፤ ሰው ሁን ! – መስፍን ማሞ ተሰማ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop