March 10, 2018
17 mins read

ኢትዮጵያ፡ ጆሮ ያለው ይስማ (ከዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

 

ይድረስ ለተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ። በመጀመሪያ ፓርቲዎ ኢሕአዴግ ሕዝብን የመስማት አገልግሎት ለመጀመር እርስዎን በጠ/ሚኒስቴርነት በመሾም ተስፋ እንዲጭር መልካም ምኞቴ ነው። ከጦረኛ መንግስትነት ወደ አዋላጅ መንግስትነት መሸጋገር የእርስዎ ብቸኛ ትኩረትዎ እንዲሆን ማስተዋል እንዲበዛልዎት እመኛለሁ። አብዮት ከመወለዱ በፊት ኢትዮጵያ እንደገና እንድትወለድና ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርበትና በዲሞክራሲ የምንዳኝበት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ዕውን በማድረግ መንግስትዎንና ሀገራችንን ከጉድ ለማትረፍ ጥሪዎን እንዲወጡ ፀሎቴ ነው።  አዋላጅ መንግስት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከዚህ በታች ለማስረዳት እሞክራለሁ።

 

እስካሁን በተሄደበት መንገድ በጦር የመጣ መንግስት ስልጣንን እንደ ክፍያውና ዋጋው አድርጎ ይወስዳል። “ማን በደማ ማን ይነግሳል?” ይላል። በእርስዎ አመራር መንግስትዎ አዋላጅ መንግስት ሆኖ፥ ይህ አዋላጅ መንግስት በጦር የመጣው ለመንገስ ሳይሆን፥ ደም ዳግም ለዘላለም እንዳይፈስ ምርጫን በሀቅ ወዶ ሕዝብን ለማንገስ እንዲሆን እርስዎ መንገድ እንዲሆኑ በተስፋ ይጠበቃሉ። ይህች የመጨረሻዋ ሰዐት ናትና የኢትዮጵያ አምላክ ታላቅ የታሪክ ዕድል ባለ አደራ አድርጎዎታል።

 

ኢትዮጵያ በሁሉ አደገች እየተባለ፤ ነገር ግን በዋናው ጉዳይ በዲሞክራሲ ወደ ቁልቁል ተንደርድራ ስትሄድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። የኢትዮጵያ አዋላጅ መንግስት ምኞት በዋነኝነት ስልጣንን በምርጫ እስከ ማስረከብ የተዘጋጀ መሆን አለበት። ለዚህም መገለጫ የመንግስት ጤንነት ልብ ትርታ የሚለካው በተዘረጋው የዲሞክራሲ ባህልና እሴት እድገት ነው። ቀን ባለፈ ቁጥር ይህ መንግስት አዋላጅ የመሆን ዕድሉን እያጣ ይሄዳል። ዕድሉን በአብዩት ይነጥቅና ለሌላው ደግሞ ያስረክበዋል። አብዮት ደግሞ እሳት ነውና በጥፋት ውስጥ አሳልፎ ሕልማችንን ያዘገየዋል። ተስፋችንንም ያጨነግፈዋል።

 

ታሪክና አጋጣሚ የኢትዮጵያ አዋላጅ መንግስት ለመሆን የሚያድለው ለአንድ መንግስት ብቻ ነው። ይህ መንግስት በእርስዎ መሪነት አዋላጅ መንግስት ለመሆን ጊዜው የሰጠውን ዕድል ይጠቀምበት ይሆን? እንቢ ብሎ ራዕዩ ለራሱ ስልጣን ባለቤትነት ከሆነ ያው አምባገነንነትን የሙጥኝ ብሎ በተራው እስኪወድቅ ድረስ መንገታገት ይችላል። ግብ ግብ እየገጠመና በፊቱ ያለውን እየገደለና እያሰረ ዕድሜውን ትንሽ ያስረዝም ይሆናል። ይሁን እንጂ በጠብ መንጃ ዕድሜ ልክ መግዛት አይቻልምና ስፍራውን ሲለቅ ያኔ አዋላጅ መንግስት የመሆኑን ዕድል ለሚቀጥለው አስረክቦ በራሱ ላይና በሀገር የታሪክ ጠባሳ ጥሎ ይቀራል።

 

ነገር ግን የአዋላጅ መንግስት ራዕይ በአንደኛ ደረጃ አገር ማልማት ብቻ አይደለም። ሀገር ማልማት በሁለተኛ ደረጃ መያዝ ያለበት ራዕይ ነው። የአዋላጅ መንግስት የአንደኛ ደረጃ ተልዕኮ ስልጣንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዝብ ማዛወርና ጊዜው ሲሞላ በክብር ዘወር ማለት ነው። ምንም በሕዝብ በእውነተኛነት ቢመረጥ እንኳን የአዋላጅነትን ክብር የሚጎናፀፈው ጊዜው ደርሶ በምርጫ ሲሰናበት ነው። አምባገነን መንግስት ስልጣኑን ለማራዘም ድንጋይ ይፈነቅላል። አዋላጅ መንግስት ግን እውነተኛ ምርጫ እንዲዳኝ ይናፍቃል። ታሪክን ጨብጦ ስልጣኑን መልቀቅ ራዕይው ነው። አንድ ቀን በሌላ ተመራጭ እንደሚተካ በመገንዘብ ሌላውን በክብርና በቅንነት ያስተናግዳል። እርሱ ራሱ ታሪክ እንዲሰራ አማራጭ ሃይሎች ታሪክ እንዲሰሩ ይፈቅዳል። ምክንያቱም አዋላጅነት አብሮ በማሸነፍና በዚያም በኩል ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ማድረግን ይጠይቃልና። አዋላጅ መንግስት ተባባሪ አዋላጅ የሆነው አማራጭ ሃይል ያስፈልገዋል።

 

በአገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ በውጭ የሚኖሩት አማራጭ ሀይሎች ጭምር ለምርጫው ውድድር የሚያሳትፍ ጥሪ በማድረግ ሰላማዊው ጉዞ በአሸናፊነት ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ዲሞክራሲ አለ ማለት ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲ የሚተገበርበትን መድረክ አብሮ ማዘጋጀትና መስጠት ያስፈልጋል። ለሰላማዊ ትግል ሞራል የሚሰጥና የአመፅ ትግልን የሚያስጥል አካሄድ በመሄድ በፍጥነት መንቀሳቀስ ይበጃል እንጂ አስቸኳይ አዋጅ እያሉ ጊዜ መግደል ትንሽቷን ፋታ ያሳጣና በመጥፋትና በመጠፋፋት ኪሣራ ይደመደማል። እሳትን ማዳፈን እሳትን ማጥፋት አይደለምና።

 

በዲሞክራሲ መንገድ ሄደን ስለማናውቅ የዲሞክራሲ ባህል እንዲዳብር አማራጭ ሃይልን የሚያሳትፍ መድረክ ከዛሬ ጀምሮ የሁልጊዜ ፕሮግራም መሆን አለበት። ቋሚ የሆነ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽርና ሁሉም ጎራ ፕሮግራሙን የሚያስተዋውቅበትና ለሕዝብ የሚያደርስበት መድረክ ማበጀት የአዋላጅ መንግስት ትልቁ ስራው ነው። የመንግስትን ሚዲያዎች ለሁሉም ከፍቶ በእኩልነት የሁሉንም አሳብ በሕዝብ ፊት እንዲወያዩበት ማድረግ አለበት። የአምባገነን ትኩረት ሚዲያን ለራሱ ስልጣን ማጠናከሪያ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ነው። የአዋላጅ መንግስት ትኩረት ግን ሚዲያን ለመግባባት፥ለመማሪያ እና ለማስተማሪያ ማድረግ ነው። ከሁሉም በላይ ምርጫው በሁሉ ዘንድ ተዐማኒ እንዲሆን እንደ ምርጫ ቦርድና የመሳሰሉት ምርጫውን በተመለከቱ ነገሮች ላይ ሁሉ ሁሉም ተሳታፊዎችና ያገባኛል የሚሉ ሁሉ በእኩልነት ለፍትሀዊና እውነተኛ ምርጫ መሰረቱን ይጣሉ።

 

አዋላጅ መንግስት ዓላማው ጊዜው ሲሞላ በምርጫ ተዳኝቶ ስልጣን ለቆ ታሪካዊ መሆን ነው። ስለዚህም የሚሄድበት አካሄድ ሕዝብን በመስማትና በማገልገል ነው። ምክንያቱም ባለስልጣን ሊያደርግ የሚፈልገው ሕዝብን ነውና። አዋላጅ መንግስት በሕዝብ በሐቅ መንገድ ቢመረጥ እንኳን ይህ ሆኖ መገኘቱ አሳብ ያስይዘዋል እንጂ አያስፈነጥዘውም። ምክንያቱም የአዋላጅ ሕልም ስልጣንን ለሕዝብ መስጠት እንዲታወቅለት ስልጣን ማስረከቡን ነው የሚናፍቀው። ለአዋላጅ መንግስት ኩራቱ በምርጫ ተሰናብቶ ኢትዮጵያን ማዋለድ ነው። እስከዚያው ድረስ መድረኩን ለነፃ ውይይት መልቀቅና ፍትሀዊ ምርጫ የሚደረገበትን አካሄድ ሁሉ በአሳታፊነትና በአብሮነት ከሚመለከተው ሁሉ ጋር መቅረፅ ዋነኛ ስራው መሆን አለበት።

 

ይህ መንግስት ለዘላለም ለመግዛት ፈልጎ በአምባገነንነቱ ቢቀጥል ሊገዛ የሚችልበትን ዕድሜ አብዮት ያደናቅፈውና ዕድሜው እጅግ አጭር ይሆንበታል። ግን ይህ መንግስት አዋላጅ ለመሆን ፈልጎ በምርጫ ሰማዕትነትን አሳይቶ ኢትዮጵያን ለማስወለድ አንደኛ ዓላማው ቢሆን ሊገዛ የሚችልበት ዕድሜ ረጅም ሊሆንለት ይችላል። ምክንያቱም መንግስት ይህን የላቀ ራዕይ ይዞ ቢንቀሳቀስ፥ ከእርሱ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ተቃዋሚው የበለጠ ስራ መስራት ስለሚኖርበት ነው። መንግስት ልቆ ከተገኘ፥ ሕዝብ ያለውን መንግስት ይመርጣልና ነው። መንግስትን የሚለውጠው የተሻለ አማራጭ እስካገኘ ድረስ ብቻ ነው። ስለዚህ ተቃዋሚው ስልጣን የሚያገኘው ራሱ በሚሰራው ስራ እንጂ መንግስት ባልሰራው ስራ ላይ የተመሰረተ አይሆንም።

 

መንግስት በአምባገነንነቱ ከቀጠለ፥ ለዓመፅና ለጦር ቤንዚን እንደማንከርከፍ ይቆጠራል። እሳቱ አብዝቶ እንዲነድ አድርጎ ሲያበቃ ያንን ለማጥፋት ሃይሉን ቢጠቀም የማታ ማታ ቃጠሎው እርሱንም ይዞ ይሄዳል። ኢትዮጵያም ከዜሮ እንድትጀምር ትገደዳለች። ከዜሮ መጀመር ድሮ ተችሎ ይሆናል። ዛሬ ግን ከዜሮ ለመጀመር የሚደረገው ፉክክር አገሪቷን አደጋ ላይ ይጥላታል። በዜሮም እንድትቀር ያደርጋታል። ይህ መንግስት ግን አዋላጅ መሆንን ቢመርጥ የወደፊቱ መንግስት እርሱ በገነባው ላይ እንዲቀጥል ያደርጋል። ያኔ ከመንበረ ስልጣኑ እንኳን ቢለቅ ታሪኩና ስራው ለዘላለም ይኖራል። ያ ብቻ ሳይሆን ተመልሶ ወደ ስልጣን መጥቶም ሌላ የላቀ ምግባር ሊያከናውን በሩ ክፍት ይሆንለታል። ኢትዮጵያም ከዜሮ ከመጀመርና ሁሉንም ነገር በዜሮ ከማባዛት ትድናለች።

 

አዋላጅ መንግስት ተቃዋሚዎች ሁሉ ከተቃዋሚነት ወደ አማራጭ ሃይላት ይዛወሩ ዘንድ ተስፋ ይሰጣል። ያኔ የአማራጭ ሃይላት ትኩረት አንድነት ይሆናል። አዋላጅ መንግስት ስልጣን ለመልቀቅ ሰማዕትነትን ሲናፍቅ፥ አማራጭ ሃይላት ደግሞ ሰማዕት ሆኖ የግል አጀንዳ ለቆ በአንድ ልብ ይቀናጃል።

 

እውነት እንነጋገር ካልን፥ ጦረኛ መንግስት በራሱ ብቻውን ታሪክ ሰርቶ ሰማዕት ሆኖ ስልጣንን ለሕዝብ አስረክቦ በታሪክ ለመታወስ አይችልም። ኢትዮጵያ እንድትወለድ መንግስት ቀዳሚውን ሚና ቢጫወትም፥ የተቃዋሚዎችና የእያንዳንዳችንን አስተዋፅዎ ይፈልጋል። ተቃዋሚ ጦር ባይኖረውም ትልቁ ሃይሉ አንድነቱ ነው። ራሱን መስዋዕት የሚያደርገው የግልን ምኞትና አጀንዳ በመተው ለሀገር ሲባል በአንድነት መያያዝ ሲችል ነው። ይህ አዲስ አመለካከት የሚጠይቀው ያልተሄደበትን መንገድ መምረጥን ነው። ለዚህም እያንዳንዱ ተቃዋሚ ከራሱ ሩጫ ታቅቦና ከራሱ ማንነት ወጥቶ፥ ዓላማቸውንና ግባቸውን እንደገና በህብረት ሆነው ኢትዮጵያን ከማዋለድ ዓይን አንፃር ቀርፀውና አስተካከለው መነሳት ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን መሪነቱን የጨበጠው ሁሉ የግሉን ለቆ የራሱን አውራነት ሰውቶ በአደጋ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ለመታደግ የአንድነት ፋና ወጊ ለመሆን መሽቀዳደም ይኖርበታል። ያለውን መንግስት በካርድ ምርጫ መቀየር እንዲቻል ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል። ምንም ይሁን ምን ውልደት ምጥ ውስጥ ታልፎ ነው ሀሴት የሚበሰረው። ስለዚህም ነው የየግል አጀንዳቸውን ሰውተው ከተቃዋሚ ሃይሎችነት አንድ ወይ ሁለት ፈርጠም ያለ አማራጭ ሃይል መመስረት የሚገባው። ይህን የምንለውን አይነት አስተዳደር የሚመጥን ታላቅና ክቡር ነገር በምድራችን እንዲሆን ከተፈለገ የሁሉንም ሰማዕትነት ይጠይቃል። ያለውን መንግስት ስልጣን ልቀቅ ብሎ መሞገትና ሕዝብን ማነሳሳት ከራስ ጥቅም ያለፈ መሆኑ እንዲህ ካልተደረገ በምን ይታወቃል? የሚሞተው ሌላ፥ ሄዶ የሚነግሰው ሌላ እንዳይሆን ይሁን። የወጣቱ ደም ተገብሮ ስልጣን ላይ ከሚወጣ፥ የራስን ምኞትና አጅንዳ ገብሮ ኢትዮጵያን ማዳን አይሻልምን?

 

ሰሚ ያጣን ሕዝብ ፈጣሪ ይሰማና ይዳኘዋል። ፅዋው ሞልቶ ሳይፈስ መንግስትዎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጆሮ ይሰጠው ይሆንን?

 

 

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop