የመከላከያ ምሽግ ይዞ የሚዋጋ ኃያል በድንገት ሽሽት ቢጀምር የአጥቂው ጦር አዛዥ ፈጥኖ ግፋ ወደ ፊት፣ አባረህ በለው የሚል ትእዛዝ አይሰጥም፡፡ በጦሩ ላይ የደረሰው ሰብአዊ ጉዳት ለበቀል ቢያነሳሳውም፣ የአሸናፊነት ስሜት ሰቅዞ ቢይዘውም እነዚህን ሁሉ ተቋቁሞ ረጋ ሰከን ብሎ ያስባል፡፡ በርግጥ የጠላት ጦር ምሽጉን ለቆ የሸሸው መቋቋም ተስኖት ወይንስ ወደ መግደያ ወረዳ ሊያስገባን፣ የሚሸሽበት የመሬት ገጽታ ምን ይመስላል፤ ፈጥኖ የሚደርስለት በቅርብ ርቀት ድጋፍ ሰጪ ኃይል አለው፤ የእኔ ጦርስ ምን ያህል ተጎድቷል፣በፍጥነት አጋዥ ኃይል ማኘት እችላለሁ፣ ቀለብና ጥይት በቂ አለኝ፤በቶሎስ ሊደርስልኝ ይችላል? ወዘተ የሚሉትን ጉዳዮች በፍጥነት በህሊናው አመላልሶ ተከታትሎ ለማጥቃት አለያም የጠላትን ምሽግ ተራምዶ መልሶ መቋቋም ለማድረግ ይወስናል፡፡ጠላት ሸሸ ተብሎ በድል ስሜት ግፋ ወደፊት አባረህ በለው አይባልም፡፡
ከደደቢቶቹ ወያኔዎች ጋር የሚደረገውም ትግል በተመሳሳይ ስልት ካልተከናወነ ውጤቱ መስዋእትነቱን ሁሉ ከንቱ ያስቀረ ይሆናል፡፡ወያኔዎች የሸሹ በመሰሉ ግዜ እጅ የሰጡ፣ የተንበረከኩ በመሰሉ ግዜ የተሸነፉ አድርጎ በማየት በስሜት ዘራፍ ማለት ሳይሆን ሰከን ብሎ ማሰብን በአስተውሎ መራመድን ይጠይቃል፡፡ አለበለዚያ ዛሬም እንደትናንቱ አያሌ የህይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል በወያኔ ሴራና ስራ መመስመሩን ሊስት ይችላል፡፡ ወያኔዎች በምንም ሁኔታ የዘረኝነት አስተሳሰባቸው መክኖ፣ የደደቢት ህልማቸው መና ሆኖ፣ ኢትዮጵያዊነት ገኖ ማየትና መስማት አይሹም፡፡ ይህ ከሚሆን ኢትዮጵያ እንደ ተለሙላት ዘጠኝ ቦታ ብትበጣጠስ ይመርጣሉ፡፡
ስለሆነም በርቀትም ይሁን በቅርበት በትግሉ አውድ የምትገኙ ከእያንዳንዱ የወያኔ ሽንፈት ከሚመስል ክንውን ቀጥሎ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የማህበራዊ መገናኛ ጀነራሎች ወያኔ ሲንገዳገድ ሊወድቅ፣ ሸብረክ ሲል እጅ ሊሰጥ አንዳንድ በጎ የሚመስሉ ርምጃዎች ሲወስድ ተሸንፎ እየመሰላቸው አባረህ በለው ግፋ ወደ ፊት አይነት አድራጎታቸውን መፈተሽ ይገባቸዋል፡፡ትግሉን በባለቤትነት የያዘው ህዝብ ወደ ወያኔ መግደያ መሬት እንዳይገባ ወይንም ለፍጅት ተመቻችቶ እንዳገይገኝ የዛሬውን ከትናንት እያገናዘቡ መጭውንም እየተነበዩ በግዜያዊ ድል ስሜታዊ መሆን ሳይሆን ለዘላቂው ድል አሸጋግሮ በማሰብ የሚሰሩ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡
ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው የሚለው ብሂል እንደተጠበቀ ሆኖ አንድም የጋለው ብረት በቀጥቃጩ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሁለትም ብረቱ የሚፈለገውን ቅርጽ ይዞ እንዲወጣ ሥራው በጉልበት ሳይሆን በዕውቀት፣በስሜት ሳይሆን በአስተውሎት ሊሆን ግድ ነው፡፡
የደደቢት ወያኔዎች በደም ተረማምደው ከያዙት የምንይልክ ቤተ መንግሥት የሚለቁት መዐበሉ ጠራርጎ ሲያወጣቸው ብቻ ነው፡፡ያ እስኪሆን ስልት እየቀያየሩ አንዴ በጦር ሌላ ግዜ በይስሙላ ድርድር፣ አንዴ ይቅርታ እያሉ በዛው ማግስት በገፍና በግፍ ህዝብ እየፈጁ ይቀጥላሉ፡፡ የእነርሱ አንድና አንድ ቀዳሚ አጀንዳ ወንበር ማስጠበቅ ነው፡፡ለዚህም ነው እነርሱ ሥልጣናቸውን የሚያጡ ከሆነ ህዝብ ቢተላለቅ ሀገር ቢፈርስ ደንታ የማይኖራቸው ፡፡የኢትዮጵያውያን ቀዳሚ አጀንዳ ግን የሀገር ህልውና ነው፡፡ ኢትዮጵያን ልጆቿ በፍቅር በሰላም፣ በእኩልነትና በአንድነት የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት ሀገር ማድረግ፡፡ይህ ስለሆነም ነው አርቆ ማሰብን አስተወሎ መራመድን ሰከን ብሎ ማሰብን ወዘተ የሚጠይቀው፡፡
ደደቢቶች የሚነሳባቸውን የተቃውሞ ትግል አቅጣጫ የማስቀየር ብቻ ሳይሆን ይዘቱን የማስለውጥ መሰሪ ሥራ የተካኑበት ነው፡፡ለወራዳውና ቆሻሻው ሥራ የሚያሰማሩዋቸው ህሊናቸውን በሆዳቸው የቀየሩ ቆመው ከመሄዳቸው ውጪ ሰው የሚለው መጠሪያ የማይገባቸው አያሌ ጀሌዎችም አሉዋቸው፡፡ ሰውን የማሰቢያ ክፍሉን አስወግዶና አደድቦ እንደ ግዑዝ ማሳሪያ የመጠቀሙን ጥበብ በእጅጉ ተክነውበታል፡፡
ስለሆነም ከእነዚህ ከሥልጣን በሻገር ለሀገርም ሆነ ለህዝብ ደንታ ከሌላቸው ሰዎች ጋር የሚደረግ ትግል በእያንዳንዷ ደቂቃ ከሚፈጠሩ ኩነተች በስተጀርባ ምን አለ ቀጥሎስ ምን ሊከሰት ይችላል፡ ወያኔዎች ይህ ሲያደርጉ ምን አስበው ይሆን፣ ሽንፈት ወይንስ ስልታዊ የማፈግፈግ ስልት ወዘተ እያሉ ማሰብንና እየሆነ ላላው ብቻ ሳይሆን ሊሆን ይችላል ተብሎ ለሚገመተው መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡
የህዝቡ አገዘዛዝ በቃኝ ትግል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የማይገታው ሆኖ እየታየ ባለው መልኩ ከቀጠለና ከውስጥ የተፈጠረው የወያኔ የበላይነት በቃ፣ የደደቢት ትልም የሆነው መርህ አልባ ግንኙነት ከእንግዲህ ተቀባይነት የለውም ከማለት አልፎ ቤተ መንግሥቱ በወያኔ አሻንጉሊት የሚያዝበትን ሂደት ለማክተም የሚደረገው እንቅስቃሴ ለደደቢቶች የመጨረሻው መጨረሻ ነውና ለማጨናገፍ የማይሞክሩት እኩይ ተግባር ስለማይኖር ትግላቸው ለቤተ መንግሥት ሳይሆን የሀገር ሉዐላዊነትን ለማስጠበቅና ለዴሞክረሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተማማኝ የመሰረት ድንጋይ ለማኖር የሆነ ወገኖች ትግሉ በምንም መልኩ ወይኔ በሚፈልገው አቅጣጫ እንዳይሄድ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግንና የየግል ጉዳያቸውን በዚህ ወሳኝ ወቅት ወደ ጎን ብለው እየተናበቡ ፣ ካልሆነም አንዱ ለአንዱ እንቅፋት ሳይሆን በመከባበር መስራትን ይጠይቃል፡፡
በምርጫ 97 ወቅት በሰለጠነው የፖለቲካ ክርክር ደደቢቶች ነጥብ ማስቆጠር ሲሳናቸው የኃይማኖት ልዩነት፣ የጎሳ መከፋፈል ለመፍጠር መሞኮራቸውና ይህ አልሰራ ሲላቸው ኢንተር ሐምዌ የሚል ነገር መድረክ ላይ ይዘው መውጣታቸውን የምንዘነጋው አይመስለኝም፡፡በደደቢቶች ዘንድ ግን ያሰቡትን ስለማሳካት እንጂ ያንን ለማሳካት ስለሚያደርጉትም ሆነ ስለሚሄዱበት መንገድ አይጨነቁም ብቻ ሳይሆን አያስቡም ማለት ይቻላል፡፡ ያለፈን መርሳትና ለእለት እለቱ መጮህ ዋንኛ ባህሪያችን ሆኖ ለወያኔዎቹ በጀናቸው እንጂ ሀያ ሰባት አመት የቤተመንግስት ድርጊታቸውን መለስ ብለን ብንቃኝ በጫካ ቆይታቸው ከእስታሊን መርሆዎች እኩል የማኪያቬሌንም በውስጣቸው ያሰረጹ ነው የሚመስሉት፡፡ውጤቱ የመጣህበትን መንገድ ይወስነዋል ነው የሚባለው? አሸናፊ ስትሆን በመንገድህ ላይ የፈጸምከው ኢ-ሰብአዊም ሆነ ኢ- ህጋዊ ነገር ይረሳል ብቻ ሳይሆን እንደ ቅዱስ ተግባር የሚወደስ እንደ ህጋዊ ተግባር የሚጠቀስ ይሆናል፡፡
ለደደቢቶቹ ወያኔዎች ሥልጣን ማጣት ማለት የምንልክን ቤተ መንግሥት መልቀቅ ብቻ አይደለም፡፡ተከትሎ ይመጣል ብለው የሚሰጉት ምን አልባትም ሌላው ኢትዮጵያዊ የማያውቀው ፈጽሞም የማይገምተው እነርሱ የሚሰጉበት ብዙ ነገር ሊኖር እንደሚችል ከነገረ ሥራቸው ተነስቶ መገመት ይቻላል፡፡ ከደደቢት እስከ ምንይልክ ቤተ መንግሥት ሲደርሱ የሰሩትን ያውቁታል፡፡ እግራቸው ቤተ መንግሥት ቢረግጥም ልባቸው ኢትዮጵያን እንገዛለን የሚል እምነት ባለሳደሩበት ወቅት የፈጸሙትን ዝርፊያም ያውቁታል፡፡ሀያ ሰባት አመት በእምነት ሳይሆን በጉልበት መዝለቃቸውንም አይክዱትም፡፡ ታዲያ እንዴት እንዲህ አንደ ዋዛ ሥልጣን ይለቃሉ፡፡ለነገሩ እኮ እኛ የመርሳት አባዜ ስላለብን እንጂ አስቀድመው በሀገር አማን የምትሹት የሚሆነው በመቃብራችን ላይ ነው ብለውናል፡፡
ስለሆነም ይህ ሕዝባዊ ትግል በተጠናከረ ቁጥር ብዙ ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት አስቅድሞ ለመዘጋጀት ይበጃል፡፡ከእዚህ መካከል ለእኔ የታዩኝንና ስጋት የሆኑብኝን ሁለት ነገሮች ልጠቁም፡፡
አንድ፣ የእርስ በእርስ ፍጅት፤
ነብሱን አይማረውና ትልቅ ነቀርሳ ተክሎብን የሞተው መለስ ሥልጣን በያዘ ማግሥት መቀሌ ላይ ህዝብ ሰበስቦ እኛ ሥልጣን ብንለቅ ነፍጠኞች በአንድ ቀን ይፈጁዋችኋል በማለት ትግረኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ መከታ ጋሻ፣ መደበቂያ ዋሻ ለማድረግ የዘራውን ዘረኝነት በሚገባ እየተንከባከቡ አሳድገውታል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ እምቢ አሻፈረኝ በማለቱ እንጂ እንደ እነርሱ ትልምና ፍላጎት ቢሆን በየጎሳችን ቅርጫት ነበረ ዛሬ መገኛችን፡፡ እንዴት አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ በአንድ ይሰለፋል ብለው እንደ እግር እሳት ሲያንገበግባቸው ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው የሚል የኦሮሞ ተወላጅ ያውም ከጉያቸው የኖረ ብቅ ሲል ደደቢቶች የደም ግፊታቸው አልጨመረም ማለት አይቻልም፡፡
ሌላውን ኢትዮጵያዊ ማናከሱ ቢከሽፍባቸውም ከትግረኛ ተናጋሪው ጋር ማጋጨቱ ግን ዛሬም እየሰሩት ያለ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ውስጥ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት በሚል የተገለጸውን ማጤን ነው፡፡ ይህ በርግጥ ትግረኛ ተናጋሪዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ ተብሎ የተወጠነ ሳይሆን ሌላውን ኢትዮጵያዊ በማበሳጨት ትግሉን እነርሱ ወደሚፈልጉት መስመር ለማዞር ነው፡፡በወሊሶ አካባቢ ስለሆነው ነገር ለአሜሪካ ድምጽ የተናገሩ ሰው በኦራል ተጭነው የሚሄዱት ወታደሮች በእጃቸው ያሳዩት የነበረው ምልክት የሚያበሳጭና ህዝብን ለኃይል እርምጃ የሚገፋፋ ነበር ነው ያሉት፡፡ ህዝቡ ትዕግስቱ ተሟጦ የሚገለን ወያኔ ነው፣ ወያኔ ደግሞ ትግሬ ነው ብሎ በሀሉም የሀገሪቱ አካባቢ በትግረኛ ተናጋሪዎች ላይ እንዲዘምትና ህዝባዊው የዴሞክራሲ ትግል ወደ ጎሳ ፍጅት እንዲዘቅጥ የሚሰራ ስለመሆኑ የእለት ተእለት ተግባራቱ ማስረጃ ናቸው፡፡ ስለሆነም በምንም መልኩ ይህ የወያኔ ፍላጎት እንዳይሳካ ኢትዮጵያውያን ሰከን ብለን ማሰብ፣ አስተውለን መራመድ ይኖርብናል፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ጀነራሎችም እንዲሁ፡፡
ሁለት መለያየት( መገንጠል)
አቶ በረከት የመረጃ ክምችት ላይ ተቀምጦ አሉባልታ በጻፈበት መጽሀፉ ውስጥ ለቅንጅቶች ከዘጠኝ መንግስት ጋር ነው የምትታገሉት ብለን ነገራናቸው ነበር ያለውም ሆነ ደደቢቶች እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚሉን እንዲሁ ለማለት ሳይሆን ያዘጋጁልንን ነው የሚነግሩን፡፡ ኦሮምያ ውስጥ በመሪዎቹ አካባቢ ጭምር ለወያኔ አንገዛም ባይነት ሲያቆጠቁጥ በምስራቁ የሀገራችን አካባቢ የተፈጠረውና ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው ግጭት በወያኔ የተሴረ አይደልም ብሎ የሚያብ ካለ ጥሩ የዋህ ነው፡፡ ያ ሴራ የተፈለገውን ውጤት አላስገኝ ሲል ደግሞ ኦጋዴንን የመገንጠል አጀንዳ ካለው ድርጅት ጋር ድርድር መጀመሩንና የምትሉትን ሁሉ እናደርጋለን ማለታቸውን እየሰማን ነው፡፡ አይሳካም እንጂ ኢትዮጵያን የመበታተን ስራ መሆኑ ነው፡፡
የእነ ለማ ኦህዴድ በቀጥታ በወያኔ የሚፈጸምበትም ሆነ ዛሬም ከአሽከርነት ባልወጡ ኦሮሞዎች ከውስጥ በሚደርስበት ተማሮ ከኢህአዴግ አባልነት እወጣለሁ፣ ከፌዴራል መንግሥቱም እፋታለሁ እንዲል ወያኔዎቹ አይፈልጉም፣ ይህ እንዲሆንም አይሰሩም ማለት ታማኝ በየነ እንዳለው ወያኔንን አለማወቅ ይሆናል፡፡ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ለይምሰል በመላ ሀገሪቱ ይባል እንጂ በእኔ ግምት ለኦሮምያ በተለይ ደግሞ ለውጥ ለውጥ ለሚሸቱት መሪዎች የታወጀ ነው፡፡ ለማም ሆነ አብይ ወያኔዎችን በቅርብ የሚያውቁ እንደመሆናቸው ለዚህ ቀድመው አልተዘጋጁም፣ከግምታቸው ውጪ የሆነ ነገር ሲያጋጥማቸውም ለመመከትም ሆነ ተሻግሮ ለማለፍ እውቀቱም ሆነ ጉልበቱም ያንሳቸዋል ባይባልም ሲበዛ ማርም ይመራል እንዲሉ ሆኖባቸው ከኢትዮጵያዊነት አምነታቸው ፈቀቅ ከአንድነት ዓለማቸው ነቅነቅ እንዳይሉ አደራ ስል ፈጣሪ ለእነርሱ ብርታትን ለወያኔዎቹ ሽንፈትን ይሰጥ ዘንድ እንደ አቅምቲ በመጸለይ ነው፡፡
ህዝቡ የወያኔን አገዛዝ የተሸከመበት ጫንቃው ተልጦ ከፖለቲከኞቹ ቀድሞ ከማማረር ወደ ማምረር ተሸጋግሮ ወያኔን እያንገዳገደው ነው፡፡ የህ አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትና አሁንም ሞት እስርና የአካል ጉዳት ያልተገታበት ትግል በወያኔ ሴራ መስመሩን እንዳይስትም ሆነ የድሉ ግዜ አንዳይራዘምና መስዋዕትነቱ ከዚህም የከፋ እንዳይሆን ፖለቲከኞች ሰከን ብለው ማሰብ ረጋ ብለው መወሰን እያስተዋሉ መራመድ ይጠበቅባቸዋል፡፡