እስረኞችን መፍታት የሕዝቡ አንዱ ጥያቄ እንጂ ብቸኛውና የመጨረሻው ጥያቄ አይደለም!

ሕዝብ ጠንክሮ ከታገለ በመጨረሻ ላይ የድሉ ባለቤት መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው።ለዚያ ወሳኝ ደረጃ ለመድረስ በሚያደርገው የትግል ጉዞ መጠቃትና ማጥቃት፣ ድል መሆንና ድል ማድረግ ተፈራራቂ ክስተቶች ናቸው።እስከ አሁን ድረስ ለ27 ዓመታት በተጓዘበት የትግል ጎዳና የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ታላቅ ድል የተጎናጸፈበት ጊዜ ቢኖር በ1997 ዓም በተካሄደው ምርጫ ያገኘው ውጤት ነበር።ያ ድል ግን በአረመኔዎቹ የወያኔ አፋኝ ቡድንና ባጫፋሪዎቹ ተባባሪነት ተክዶ እስከ አሁን ድረስ ላለው ለበለጠ ስቃይና ጭቆና ዳርጎታል።ግፍ በበዛ ቁጥር የሕዝቡ እምቢባይነት እንደሚያገረሽ ያልተገነዘበው እብሪተኛው ቡድን የልብ ልብ ተሰምቶት አገዛዙን ዘላለማዊ ለማድረግ ባደረበት ቀቢጠ ተስፋ ታውሮ ዘረፋውን፣መግደሉን፣ማሳደዱን ማሰሩን በስፋት ተያያዘው፤ያም በመሆኑ የግፉ ጽዋ ሞልቶ መፍሰስ ከጀመረ ከሁለት ዓመታት በላይ ሆኖታል። የሕዝቡ ትግል ከዳር እስከዳር ተቀጣጥሎ የለውጥ ማዕበል ሆኖ አሁን ባለስልጣኖቹን ከከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል።በዚህ የሕዝብ ቁጣ የተደናበረውን የወያኔ መራሹን ቡድን የሚይዝ የሚለቀውን አሳጥቶታል።ችግሩን በዝግ ስብሰባ ያሶግደው ይመስል አንድ ጊዜ መቀሌ፣ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ በሚያካሂደው ስብሰባ እርስ በርሱ ከመጋጨትና ከመዘላለፍ የተለዬ ፣ የሕዝቡን ቁጣ የሚያበርድ፣ጥያቄውን ከሚመልስ አንዳችም ውሳኔ ላይ አልደረሰም።ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ጊዜ የማስፈራሪያና ዛቻ የተሞላበት በሌላ ጊዜ ለሰላም ተቆርቋሪና አሳቢ የሚመስል የማጭበርበሪያ መግለጫ ከሚለፍፍበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የስራ አመራር ተብዬው አካል ለአስራሰባት ቀን ቤት ዘግቶ ሲጨቃጨቅ ከቆዬ በኽላ ይዞ ብቅ ያለው ነገር ተስፋ ሰጭ ሳይሆን ይበልጥ አገሪቱንና ሕዝቧን ለባሰ መከራ የሚዳርግ የአምባገነን ስርዓትን የሚያጠናክር መመሪያ ነው።በዚያ ያልተንበረከከው ሕዝብ ከትግሉ ሜዳ አላፈገፍግ በማለቱና ይበልጥም ተቃውሞው ከደጋፊዎቹ አካባቢ ጭምር ሲነሳበት ሌላ የማጭበርበሪያ መግለጫ ይዞ ብቅ አለ።ይህ የማጭበርበሪያ መግለጫ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ተብየው ተላላኪ የተሰጠው የፖለቲካ እስረኞችን ፈትቼ የማሰቃያ ማእከል የሆነውን ተቋም ዘግቼ ሙዚየም አደርገዋለሁ በማለት የሰጠው ድንገተኛ መግለጫ ነው።ቀደም ሲል የፖለቲካ እስረኛ የለኝም ሲል የነበረውን ክህደት በራሱ ቃላት ሲንደው በዓለም አቀፍ መሳቂያና፣በደጋፊዎቹ ደግሞ ማፈሪያ አድርጎታል።የሕዝቡንና የተቃዋሚውን ክስና ጥያቄ ግን እውነተኛነት አረጋግጧል።ይህንንም መግለጫ ቢሆን ከውስጡ የሚቃወሙ በመነሳታቸው በማግስቱ ሌላ አድርጎ አቅርቦታል። የፖለቲካ እስረኞች እንደሌሉና እንደማይለቀቁ፣አሰቃቂው ማእከላዊ በማርጀቱና በመጥበቡ ምክንያት ይዘጋ እንደሆን እንጂ ማሰርና ማሰቃዬት ይቀራል ማለት እንዳልሆነ፣ሌላ በዘመናዊ የማሰቃያ መሳሪያና ጥበብ የተሟላ አዲስና ትልቅ ማእከላዊ እንደተሰራ ወይም እንደሚሰራ የሚያመላክት ማብራሪያ የኢንፎረሜሽን ቢሮ ባለስልጣኑ በሰጠው የእርማት መግለጫው የጠቅላይ ሚኒስቴር ተብዩውን ቅድመ መግለጫ ውድቅ አድርጎታል። ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ብዙ ሰው ይታሰራል፣ይገደላል፣ይሰደዳል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰጠው መግለጫ አስገዳጁ የሕዝቡ ተቃውሞ እንጂ ወያኔ ሰብአዊ ስሜት አድሮበት አይደለም።እንደ ወያኔ ፍላጎትና ምርጫ ቢሆንማ ኖሮ በተካነበት መንገድ ሁሉንም በጭስ አፍኖ በጨረሳቸው ነበር።ምናልባት ወደፊት እስረኞችን እንዲፈታ ከውስጥም ከውጭም ግፊት ቢበዛበት የሚለቃቸው በራሱ ምርጫ አደገኛ ይሆናሉ ብሎ የማያስባቸውን፣በጥርጣሬ ያሰራቸውንና ምናልባትም የተወሰኑ በውጭና በአገር ውስጥ ድጋፍና እውቅና አላቸው ብሎ ያሰባቸውን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ግለሰቦች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያቅትም። አንድም ሰው ቢሆን መፈታቱ አይጠላም።በወያኔ ስሌት በዚህ ቁንጽል እርምጃ እራሱን ለተሃድሶ የተዘጋጀ አድርጎ ለማሳዬት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል የሚሞክርበት ስልት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።ነገ ደግሞ የፖለቲካውን ምህዳር አሰፋሁ በሚል ማጭበርበር እራሱ የቀፈቀፋቸውን በስመ ተቃዋሚ በምርጫ ወቅት ድምጽ ለመሻማት የሚያሰልፋቸውን፣እራሱ ያረቀቀውን ሕገ-መንግስቱን የተቀበሉ አጋሮቹን በፓርላማ ውስጥ የተወሰነ ወንበር እንዲያገኙ የማድረግ ስልት ሊጠቀም እንደሚችል ማሰብ የወያኔን ተፈጥሮ ለሚያውቅ እንግዳ አይሆንበትም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚያነሳቸውና ከሚታገልባቸው ጥያቄዎች አንዱ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መሆኑ አይካድም።እውነት የሚፈቱ ከሆነ ደግሞ በሃሰት ተወንጅለው የስቃይ ሰለባ ለሆኑት እስረኞች፣ለቤተሰቦቻቸውና ለሁሉም
ኢትዮጵያዊና ለሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ታላቅ ድልና የምስራች ነው።በተጨማሪም ለደረሰባቸው ጉዳት ተጠያቂው ማን እንደሆነና የማገገሚያ ካሳ የማግኘቱም ጉዳይ አብሮ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። አሁን በተግባር የሚታዬው በየአቅጣጫው የማሰሩ፣የማሳደዱና፣የመግደሉ እርምጃ በስፋት እያደገ መሄዱ ነው።የስርዓቱ ተጠሪዎች ከተጨማሪ ወንጀል መራቅ ከፈለጉ ሁሉም እስረኛ ያለምንም ቅድመሁኔታ ተለቆ፣ለደረሰበት ጉዳት ካሳ እንዲሰጠው፣ ለወደፊቱ ማንም ዜጋ በፖለቲካ እምነቱና አቋሙ እንደማይታሰር፣እንደማይገደል፣እንደማይሰደድ የሚያረጋግጥ የመንግሥት ዋስትና በይፋ መውጣትና ከዚህ በፊት የወጡት አፋኝ አዋጆች በይፋ መሻር አለባቸው። በተጨማሪም በአረጀውና በጠበበው ማእከላዊ ምትክ ሌላ መሰራቱ ለቀጣይ መከራ መሰናዶ መሆኑን የሚያበስር እንጂi እስራት የሚያከትም መሆኑን አያመላክትም።ስለሆነም በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት እስር ቤቶች መዘጋት እንዳለባቸው ፣ያም በተግባር ማሳዬት ይኖርባቸዋል።በተግባር የማይታይ መግለጫ በማውጣት ጊዜ መግዣና ማደንዘዣ አድርጎ ለመጠቀም ታስቦም ከሆነ ሞኝነት ነው።ከአሁን በዃላ ሕዝቡ ለተጨማሪ ጥያቄዎቹ በጥናት ከመታገል እንደማያፈገፍግ ሊታወቅ ይገባል።ሕዝቡ ሌሎቹንም መብቶቹን በትግሉ እንጂ በችሮታ ከወያኔ እንደማያገኘው ያውቀዋል። አገራችንና ሕዝባችን የወያኔ እስረኞች ናቸው። ሙሉ በሙሉ ከእስር ለመላቀቅ ከተፈለገ አሳሪውን ስርዓት ማሶገድ ብቻ ነው። ትግላችን በሽርፍራፊ ለውጥ እንደማይቆም፣ በጎሳ ስርዓት መቃብር ላይ ሕዝባዊ የስርዓት ለውጥ ለመመስረት እንጂ ለጥገና ለውጥ እንዳልሆነ ሊታውቅ ይገባል።የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር አጥፊው የጎሳ ፖለቲካ ተወግዶ ያገራችንን አንድነትና የሕዝቡን እኩልነት የሚያረጋግጥ እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት እስኪመሰረት ድረስ ከትግሉ ሜዳ እንደማያፈገፍግ የታወቀ ነው።ወያኔም ከስልጣኑ ላለመውረድ ቤት ዘግቶ ከመምከር አልቦዘነም።አዲስ አበባ ውስጥ ውጥረቱ ሲያይልበት ወር ባልሞላ ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዋሻው ትግራይ ከተማ መቀሌ ተመልሶ ሰሞኑን ቤት ዘግቶ እየተማከረ ነው።ምን ይዞ እንደሚወጣ ባይታወቅም የባሰ የወንጀል ስራ እቅድ ይዞ እንደሚወጣ ይጠበቃል። ከእባብ የእርግብ እንቁላል እንደማይጠበቅ ሁሉ ከወያኔም መልካም ነገር መጠበቅ ጅልነት ነው።አንዳንዶቹ በተቃዋሚ ጎራ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ሕገመንግስቱን ተቀብለን በፓርላማ መድረክ የወያኔን ስርዓት ማሻሻል እንችላለን የሚሉትን ብዥታ አቁመው ለመሰረታዊ ለውጥ ከሕዝቡ ጋር መሰለፍ ይኖርባቸዋል። ትግሉ ወያኔን በማሶገድ ላይ ብቻ የተወሰነ መሆን አይኖርበትም። ከዚያ ባሻገር የአገራችንን የፖለቲካ ፣የኤኮኖሚና የማህበረሰብአዊ (ባህላዊ)ነጻነትና ልዑላዊነት ለማስከበር፣የውጭ ተጽእኖና የብዝበዛን ሰንሰለት የሚበጥስ እውነተኛ ብሔራዊ አርነትን ለሚያረጋግጥ ለውጥ የሚያበቃ መሆን አለበት።በወያኔ ላይ ድንጋይ የወረወረ ሁሉ ለምንፈልገው ለውጥ የቆመነው ማለት አይደለም፤ ምናልባት ለባሰ ስቃይ የሚዳርገን ሊሆን ይችላል።”ከደርግ የማይሻል አይመጣም” ብለን ወያኔን ለስልጣን ያበቃነው ስህተት እንዳይደገም ታሪክን ዘወር ብሎ ማየቱ ጠቃሚ ነው።”ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆመው ማውረድ ያዳግታል”እንዳይሆንብን መጠንቀቅ ብልህነት ነው።ለነጮች መንግሥታት ጥቅም የቆመ፣ የወያኔ ተቀያሪ ጎማ ሆኖ ሊያገለግላቸው የሚችል ቡድን በተለይም የጎሳን ፖለቲካ የተሸከመ በተቃዋሚው ጎራ እንዳለ መዘንጋት አይገባም።ስለሆነም ሁሉም ለእውነተኛ ለውጥና ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመ ተደርጎ መታዬት የለበትም፤ትግሉም መጥራት አለበት እንጂ ተግበስብሰው የሚሄዱበት ባቡር ሊሆን አይገባውም።የአንድነት ሃይሉ ጸድቶ መውጣት ይኖርበታል።
በቁርጠኝነት ከታገልን የአገራችንን ትንሳኤ የምናረጋግጥበት ጊዜው እሩቅ አይሆንም!
ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር !
አገሬ አዲስ

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ ፕሮ ፖ ጋ ንዳ “ ስትነዳ እንዳትገለበጥ ፤ በ2015 እንኳን  ተጠንቀቅ - ሲና ዘ ሙሴ
Share