ይብላኝ ለህወኣትና ለተክላይ – መኮንን ሀብተጊዮርጊስ ብሩ (ዶ/ር)

”መኮንን” ሲል የሆነ ድምፅ ሲጠራኝ ተሰማኝና ወደ ኋላ ዞር ብዬ ተመለከትኩ። አልተሳሳትኩም የማዉቀዉ ሰዉ ፈገግ ብሎ እጁን ከፍ አድርጎ ሰላምታ ሰጠኝ። ተክላይ ነበር። እኔም አፀፋዉን መልሼ ያዘዝኩት ቡና ደርሶ ስለነበር ተቀብዬ ለሁለታችንም የሚሆን መቀመጫ ፍለጋ ጀመርኩ። እንደ በፊት አይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ከተክላይ ጋር ቢያንስ በሁለት ሳምንት አንዴ ሳንቀጣጠር እንገናኛለን። አሁን አሁን እንደበጋ ሳር አሞቱና ወኔዉ ጠዉልግ ይበል እንጂ በፊት በፊት አንድ መቀመጫ የሚበቃዉ የማይመስል ቁንጥንጥ ነበር።

“ታዲያስ መኮንታዉ” አለ አጠገቤ ያለዉን ወንበር ስቦ እየተቀመጠ። ተክላይ ሻይ እንጂ ቡና ሲያዝም ሲጠጣም አይቼዉ አላዉቅም።

“ታዲያስ ተጋዳላይ” ብዬ አፀፋዉን መለስኩ። ተክላይ የህወኣት አባልና ታጋይ በመሆን ብዙ ዘመኑን በርሃ ማሳለፉን ራሱ ደጋግሞ አጫዉቶኛል። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ በዋና ስሙ ጠርቼዉ አላዉቅም። እሱም ቢሆን አጠራሬ ይሁን የስያሜዉ ትርጉም ሞቅና ፈካ ሲያደርገዉ ሳይ ነፍሳቸዉን ይማርና ጊሚራ ሰፈር ይኖሩ የነበሩትን ሻምበል ባሻን ያስታዉሰኛል። ወንድ ይሁን ሴት ፤ ልጅ ይሁን አዋቂ “ባሻ” ብሎ ሲጠራቸዉ ፊታቸዉ የጠዋት ፀሐይን መስሎ ነበር መልስ የሚሰጡት። የዛሬን አያድርገዉና የተክላይም ፊት በደስታ ሲያብረቀርቅ አየዉ ነበር። አሁን አሁን ግን ከህወኣት ጋር የተጣመረ እሱነቱን ብዙም መስማትም መናገር አይፈልግም። ይልቁንም ኢትዬጲያ ኢትዮጲያ የሚለዉ ያልተለመደ የቅርብ ጊዜ ቋንቋዉ የቀድሞዉ የኢትዮጲያ ሕዝብ መዝሙር የናፈቀዉ የደርግ ወታደር አስመስሎታል።

“ምን አዲስ ነገር አለ?” ስል ጠየኩት።

“ምን እናንተ አልሰማ ብላችኋል። በሰላም እና በዕድገት ግስጋሴ ያለች ኢትዮጲያን በጋራ የበለጠ ከማሳደግ ይልቅ ነጋ ጠባ ብርሃኑ ነጋ ብርሃኑ ነጋ እያላችሁ ሀገር ስታምሱ ቆይታችሁ አሁን ደግሞ ኢህዴግን ልታፈርሱ አሰፍፋስችኋል።” አለና ንግግሩን ሳይጨርስ አቆመ። ብዙ ጊዜ ተገናኝተን ብዙ ጊዜ ስላወራን አንዳዴ እየተናገረ ያለዉን ሳይጨርስ የንግግሩን መጨረሻ አዉቃለሁ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የንግግሩ ዉል የጠፋበት ይመስል ንግግሩን ሳይጨርስ እመሃል ላይ ማቋረጡን አብዝቶታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አቤ ጆቤና ሥጋቱ - ይሄይስ አእምሮ

“ምነዉ?” ስል ጠየኩት

“ምነዉ?” ሲል እርሱም አተኩሮ ተመለከተኝ ። ፊቱ ላይ አብዝቶ የሚቀባዉ እፍተር ሼቭ በብርዳማዉ የትህሳስ ወር እንኳ ሳይቀር በበርሃ ፀሐይ ከሰል የመሰለዉን ፊቱን አብለጭልጮለታል። ንግግሩ ግን እንደቀድሞዉ ወኔ የተላበሰ አልነበረም። ድምፁ ለብዙ ግዜ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ በቅርቡ እያገገመ ያለ ይመስል በጣሙን ዝላል።

“ንግግርህን ሳትጨርስ አቆምክ። ‘መርዘኛዉ የደርግ ርዝራዣ አርጅቶ ሲሞትና ሲወገድ አዲሱ ትዉልድ ከኢህዴግ ጋር ይጓዛል የሚሉት የተለመዱ የመፈክር ቃላት የት ጠፉ ወይስ ልጆቹ ከአባታቸዉ ብሰዋል?” ስል አፈጠጥኩበት። መልስ ሳይሰጠኝ ዝም አለ። የሚለዉ እንዳጣ ገብቶኛል። በደደቢት ያረጀ ቀመር ለዘመናት ለሆዱ ባደረዉ አባዱላ ገመዳ ወይም ልደቱ አያሌዉ፣ ለማ መገርሳን፣ አንዱዓለምን… ወይም አብይን የመሰሉ መሪዎች ይፈጠራሉ የሚል ሕሳቤ ያልነበራቸዉ ደደቢቶች የታክሲ ሂሳብ የጎደላቸዉ ይመስል እዚህ እዚያ ሲርበተበቱ ማየት የፓለቲካ ሕይወታቸዉ ማብቃቱን ያበስራልና ዉስጤን ደስ እያለዉ እኔም በዝምታ አስተዛዝነዉ ጀመር። ተመስገን ነው።

የዛሬ ሰባት ዓመታት ገደማ ይሆናል። እዚሁ አሁን ያለንበት ቦታ ነበርን። ያኔ ግን ወቅቱ ብርድ ላልነበረ ሶስት ሆነን ዉጪ ተቀምጠናል። የቀኑ ብርሃን በለሊቱ ጨለማዉ ሊተካ በመቃረቡ መኪኖች የፊት ለፊት መብራታቸዉን ቦግ አድርገዉ በዌስት ታይመር ሰፊ የሂዉስተን ጎዳና ላይ ሽዉ ሽው ይላሉ። ጎዳናዉ ለእኔና ለተክላይ ፊት ለፊት የሚታይ ሲሆን ጓደኛችን ሄለን ደግሞ ፊቷን ወደኛ ጀርባዋን ደግሞ ለጎዳናዉ ሰጥታ ተቀምጣለች። በዚህ አጋጣሚ ሁሌም ሄለንን ሳያት የበዓሉ ግርማን ፍጡር ፊያሜታ ጊላይን ታስታወሰኛለች። በሆነ ባልሆነዉ “አንተ እናትክን” የሚለዉ አባባሏና ማራኪ ዉበቷ ፈልጌም ይሁን ሳልፈልግ በምናቤ ከአሜሪካ አስመራ ታመላልሰኛለች። ሄለን ግን ውብ የዶሮ ማነቂያ ሰፈር ልጅ ነች። እና እኔም ዓይኖቼን አልፎ አልፎ ሄለን ላይ አልፎ አልፎ ደግሞ ጎዳናዉ ላይ እየወረወርኩ እየጠጣን እንዳለነዉ የስታርበክስ ቡና ሞቅ ያለዉን ንትርካችንን ከተክላይ ጋር ተያይዘነዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሙስናው አዙሪትና ማረበሎቹ - ከ ሙሉጌታ ገዛኸኝ

ያኔ የሀገር ተስፋ የጨለመበት ጊዜ ነበር። እባቡም ከነመርዙ በጠቅላይ ሚንስተር ፅሕፈት ቤት ነበር። ያኔ እኔም በምንም መልኩ ልረዳዉ ያልቻልኩት የሰዉ ልጅ ለሆዱ ሲል ክብሩን ሸጦ ማደሩ በተዘዋዋሪ መንገድ ከተክላይ እሰማ ስለነበር ቆሽቴ የሚደብንበት ጊዜ ነበር። ተክላይ ግን ያንን ብዙ የሚያዉቅ አይመስለኝም። ሳያዉቀዉ እንደ ኦሮሚያ እንጨት ብዙ እአክስሎኛል። ያኔ እሱና መሰል ተጋዳላዮች እንደ ኮለምበስ ኢትዮጲያን ፈልገዉ ያገኙ ይመስል ለፈለጉት እየቆራረሱ ያድሉ ስለነበር እኔም በጥቂቱም ቢሆን ይደርሰኝ ዘንድ ጓደኛዬ ተክላይ ይመክረኝም ያስጠነቅቀኝም ነበር። እናም በዛች ምሽት ተጋዳላይ አንድ ፕሮፓዛል ይዞ እንደሚመጣ ነግሮኝ ነበርና ለመስማት ብጓጓም እንደተገናኘን ወደ ተለመደዉ ክርክር ነበር ያመራነዉ። ቆይቶ ግን በሄለን ጥረት ወደ ቁም ነገሩ አመራን።

ተክላይ በግለሰብ ደረጃ ለጋስ ነዉ። ብዙ ጊዜ ከአንደበቱ የሚወጡት ቃላትም የጠብ ሳይሆን ቁም ነገር አዘል መልካም ቃላቶች ናቸዉ። ቢሆንም ግን ሁሌም እጠራጠረዉ ነበር። ታዲያ በዛች ምሽት በምክርና በፕሮፓዛል ስም ሳያስበዉ የገለፀልኝ የዉስጥ እሱነቱ እስከዛሬ ድረስ በተብለጨለጨዉ ግንባሩ ዉስጥ የጥይት ባሩድ እንጂ የሰዉ ደምና ስጋ አለመኖሩን እንድጠራጠር አደረገኝ።

“ሙሉ በመ ሉ የትግራይ ምድርና ከፊል የአማራ ምድር ለብዙ ሺህ ዓመታት ታርሶ አፈሩ ደቋል”። ሲል ማብራራቱን ጀመረ ተክላይ። ቀጠለናም “በዚያ አካባቢ የሚኖረዉ ሕዝብ ደግሞ ለዛሬይቷ ኢትዮጲያ መፈጠር ደሙን አፍስሶ መሰረት በመሆኑ ሁሉም ባለ ዕዳ ነዉ። ኦሮሞም ይሁን ወላይታዉ ለዘመናት የነጭ ባሪያ እንዳይሆን ሰሜኑ ብዙ መስዋኋት ከፍሏል። ብዙ ሕይወት ተለግሶለታል። ስለዚህ ለሚመጣዉ መቶ ዓመታት የትም ሄደን ማረስ ብቻ ሳይሆን ብናስገብርም ልንወቀስ አይገባም።” ሲል ደነፉ አድዋን የዘነጋዉ ተክላይ። ያኔ ምንም ልመልስለት አልተቻለኝም። በጣሙን ግን አዘንኩ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስድስት:- ቃል ኪዳን፤ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ (ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

በመጨረሻ ም ዕቅዱን ነገረን። ከጥቂት መሰሎቹና እኔም ተባባሪ ከሆንኩ በጋምቤላ ምድር ሊሰሩ ያቀዱትን አብራራልኝ። ያኔ ተስፋዬን አስቆረጠኝ። ዝምታንና ከነሱ መራቅን እንድመርጥ አደረገኝ። ስንት የበቁ ሙሁራን እያሉ ኢትዮጲያ በዚህ መሰል ድንጋዬች መጫወቻ መሆኗ አበሳጨኝ።

ይብላኝ ለህወኣትና ተክላይ ዛሬ ግን አዲስ ቀን ነዉ። በጭላንጭልም ቢሆን ተስፋ ይታያል። ፈጣሪ ምስጋና ይግባዉና ሰዉ ሁሉ ሆድ ብቻ እንዳልሆነ እየተረዳን ነዉ። ተክላይም የድሮ ተክላይ አይመስልም። ከሄለን ወበትና ጣፋጭ ቃላት በስተቀር ሁሉም ነገር የተቀየረ ይመስላል።

የነገ ሰዉ ይበለን። አሜን

Share