መኮንን ሀብተጊዮርጊስ ብሩ (ዶ/ር)
እንደዛሬ በአርብ ሀገራት ገረድነትና በባርነት …እንዲሁም በመላዉ ዓለም ፊት በርሃብተኝነት ተዋርደን ብንገኝም ያኔ ታላቅና ኩሩ ሕዝብ ነበርን። አዎን! ያኔ በመላዉ ዓለም ጥቁሮች በባሪያ ንግድ እንደ ዕቃ ሲሸጡና ሲለወጡ በነበረበት ዘመን ፕላዉደን የተባለ የእንግሊዝ ተወላጅ በጎንደር ቤተ መንግስት የራስ አሊ ባለሟል ሆኖ ያገለግል እንደነበር አምባሳደር ተፈራ ኅይለ ስላሴ ‘ኢትዮጲያና ታላቋ ብሪታኒያ … ‘ በሚለዉ መፅሐፋቸዉ መቅድም አስፍረዉታል ።
እንደሚታወቀዉ ካሳ ኃይሉ (በኋላ ዐፄ ቴዎድሮስ የተባሉት) ራስ አሊን ድል ነስተዉና በበርካታ መሳፍንት አገዛዝ ተቦጫጭቃ የነበረችን ምድር መልሰዉ ሲጠግኑ ሰነባብተዉ በመጨረሻም ለሀገራቸዉና ሕዝባቸዉ ጥቅም ሲሉ በጊዜው የዓለም ቁንጮ ከነበረችዉ ብሪታኒያ ጋር ከቀይ ባሕር በሶስት መቶ ስልሳ ማይል ርቀት ላይ በምትገኘዉ መቅደላ ከናፒየር ሰለሳ ሺህ ጦር ጋር ሲፋለሙ ዉለዉ በመጨረሻም ለነጭ እጄን አልሰጥም ብለዉ በዕለተ ሰኞ April 13, 1968 ራሳቸዉን መግደላቸዉን የሲሪያዉ ተወላጅ የሆነዉና የንግስቲቱን መልህክት ለፀፄ ቴዎድሮስ ይዞ የመጣዉ ሞርሙድ ራሳምን ጨምሮ በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎች ዘግበዉታል (Mormuzd Rassam, Narrative of the British Mission to Theodore of Abyssinia; London 1869 ) ። አዎን! ያኔ እራሳችንን ከማንም አሳንሰን የማናይና ከዉርደት ይልቅ ራስን ማጥፋት የምንመርጥ ሕዝቦች ነበርን።
ላለፉት በርካታ ዓመታት ግን ታሪካችን እንደ ሀገርና ሕዝብ በጣሙን በሚያስቆጭና በሚያሳፍር ገፅታ ዉስጥ ይሆን ዘንድ ቢደረግም ያኔ ታላቅትን፣ መከበርንና፣ መፈራትን ለምነን ሳይሆን በአያት ቅድመ አያቶቻችን ደምና አጥንት የእኛ የአበሾች እሴት አድርገን ለዘመናት ኖረናል። ዛሬ በሚያቃትት የወያኔ የመለያየት እርኩስ መንፈስ ሰበብ ስቃይ ላይ ያሉት አንጋፋዉ ሙሁር ረዳት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ‘የኢትዮጲያ ፓለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች’ በሚል መፅሐፋቸዉ የጠቀሱልንን የሕንዳዊዉ አስተማሪያቸዉ አባባል ለኩሩነታችን ማረጋገጫ ይሆናል። ዶ/ር መረራ እንደፃፉት ሕንዳዊዉን አስተማሪያቸውን ሕንዳዊ ጓደኛቸዉ ‘የት ነዉ የምትሰራዉ’ ሲል ይጠይቃቸዋል። የመረራ አስተማሪም ‘ኢትዮጲያ የምትባል አንድ የአፍሪካ ሀገር ሲሉ ይመልሱለታል’። ይህኔ ሰዉዬዉ ይስቃል። ይህ ለበጥ ሳቁ ያናደዳቸዉ የመረራ አስተማሪም በጣሙን ተናደዉ ‘አንተ ከነዘር ማንዘሮችህ የእንግሊዞች ዉሾች ሆናችሁ ከአንድ መቶ አምሳ ዓመታት በላይ ስትገዙ እነሱ በነጮች ለአምስት ዓመታት አልተገዙም’ ብለዉ ይሉትል (ገፅ 29) ። አዎን! ዛሬ የረከስንና በየዓለማቱ የተሰደድን ሕዝቦች ብንሆንም ያኔ ታላቅና ኩሩ ነበርን።
በዚህ ወቅት ሕዝባችንና ሀገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛሉ። ወይ ተባብረንና ተፈቃቅረን ወደ ቀድሞዉ ክብርና ሞገሳችን እንጓዛለን አልያም የዉርደትና የስደት የቁልቁለት ጉዟችንን እንቀጥላለን። ይህን ደግሞ አቶ ለማ መገርሳም፣ አቶ ገዱ አስራትም፣ እንዲሁም መላዉ የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ አጥብቀዉ ሊያስብበት የሚገባ ነዉ። በፍራቻና በማፈግፈግ በአሁኗ ሰዓት ቤሩት ወይም ሪያድ በዓረብ ገረድነት እየተሰቃየች ያለችን የኦሮሞ ወይም የአማራ ወይም የሌላ ኢትዮጲያዊት ለግላጋ ወጣት መጪ ዕጣ መቀየር አይቻልም። ጀግኖች ጀግና ተብለዉ በታሪክ የወርቅ ቀለም ተፅፈዉ ለዘመናት ሲወደሱ የሚኖሩት በታሪክ እራሳቸዉን ባገኙበት ቦታ ለብዙሃን ሲሉ ሰዉ ሆነዉ መገኘት ሲችሉ ነዉ። ስለዚህ ዛሬ የኦሕዴድም ይሁን የብኣዴን አመራሮችና አባሎች እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ራሳቸዉን ባገኙበት የታሪክ አጋጣሚን መጠቀም ይችሉ ዘንድ ሰፊዉ ሕዝባቸዉ ይጠይቃቸዋል።
አቶ አሰፋ ጫቦ ‘የየትዝታ ፈለግ’ በሚለዉ መፅሐፋቸዉ ከአሜሪካ ሄዶ ወያኔን በሐቀኝነት ያገለግል ስለነበረ ሰዉ የፃፉትን ልብ ማለት ጥሩ ነዉ። የአቶ አሰፋ ዘመድ የሆነች ሴት አዲስ አበባ ደዉላ ይህንን የወያኔ አገልጋይ “ለመሆኑ የኢትዮጲያ ሕዝብ ምን ይልሃል?” ስትል ትጠይቃቸዋለች። ሰዉየዉም”….. ከመጠየፍ በስተቀር ምንም አይለኝም” ሲሉ ይመልሳሉ (ገፅ 240)። እንደ ሕዝብና እንደ ትዉልድ ብሔራዊ ዉርደትን እንደ ጋቢ ያከናነበንን የህወኣት መንፈስ በመፍራት ጊዜና ትውልዱ የሚጠይቀዉን ሰዉ የመሆን ጥሪ በምንም መልኩ ችላ ካልን የኢትዮጲያ ሕዝብ መጠየፍ ብቻ ሳይሆን አንቅሮ ይተፋል። ይህ ደግሞ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ያየነዉ ነዉ። በጭነት መኪና ላይ ሆኖ በመርካቶና በተክለ ኃይማኖት መንደር ሕዝብ እንደ ሙሴ ቆጥሮት ‘ማንዴላ… ማንዴላ’ እያለ በማንቆለጳጰስ መጪዉን ጊዜ በተስፋ እያየ ሲቦርቅና ሲከተለዉ የነበረዉን ሕዝብ በመክሊት የሸጠዉን የልደቱ አያሌዉን ታሪክ ማስታወስ ይቻላል። ሕዝብ ያያል። ሕዝብ ይሰማል። ሕዝብ መልስ ይሰጣል። ስለዚህ ዛሬ የኦሕዴድም ይሁን የብኣዴን አመራሮችና አባሎች እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሕዝብን መርጣችሁ ከብሔራዊ ዉርደት ተባብረን እንወጣ ዘንድ የታሪክ አጋጣሚዉን ተጠቀሙ።
በጨቦና ጉራጌ የተወለዱትና በደርግ ዘመን ብ/ጄኔራል የነበሩት ተስፋዬ ቆትየ ‘የጦር ሜዳ ዉሎ’ በሚለዉ መፅሐፋቸዉ ላይ ‘ላብ ደምን ያድናል’ ሲሉ የጀርመኑን ጨካኝ ፊልድ ማርሻል ኧርዊን ራሜልን አባባል አስፍረዋል። አዎን! ለነፃነትና ክብር ላብ መፍሰስ አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ደም ይፈሳል። ስለዚህ የኦሕዴድም ይሁን የብኣዴን አመራሮችና አባሎች ዛሬ ያልባችሁ ዘንድ ይሁን። አለበለዚያ እየመጣ ያለዉ ደም ነዉ። ምንም ይሁን ምን በባርነትና በዉርደት እየተሰደደ መኖርን የሚመርጥ ሕዝብ የለም። ያዉም ኢትዮጲያዊ!! ስለዚህ የጀመራችሁትን መንገድ በፍፁም እንዳትስቱ። ምርጫችሁ ምንጊዜም ሕዝባችሁ ይሁን።
አምላክ ካለንበት የሕዝብ ዉርደት ተባብረን እንወጣ ዘንድ ይርዳን። አሜን።