ፕሮፌሰር ብርሃኑ በአና ጎሜዝ ጋባዥነት ለአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ስላለችበት ሁኔታ ሰፊ ትንታኔ እንደሰጡ አድምጠናል። ፕሮፈሰሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴርን ጨምሮ ትላልቅ ባለስልጣናትን ሳይጋበዙ በተደጋጋሚ በግልጽና በምስጢር በአውሮፓ ህብረት መጋበዛቸው ምንድነው ምስጢሩ የሚያስብል ጉዳይ ነው። የአገሬ ሰው ነገር አለ ጠርጥር ይላል።
ዲሴምበር 15 ከአውሮፓ ህብረት ጋር ከተወያየ በኋላ ዲሴምበር 17 በጀርመኗ ከተማ ሙኒክ ላይ ተጋብዘው ከአንድ ሰዓት ያላነሰ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ንግግር ካደረጉ በኋላ ከታዳሚው የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ለተጠየቁት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ በመስጠት ሰፋ ያለ ግዜ ወስዶ ነበር። ዲሴምበር 24 ደግሞ በሆላንድ አገር በመገኘት ከኢትዮጵያኖች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ የወጣው መርኀግብር ያሳያል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ ቀደም የተናገሩት ነገር በስራ ተለውጦ እያየነው ይሆንን? ወያኔም ግንቦት 7ትን ከመጠን በላይ የሚፈራውና የስም ማጥፋትና የክስ መአት የሚያወርዱበትስ ከምን የመጣ ይሆንን? ይሄንን ለማለት የቻልኩበት ምክንያት ከአመት በፊት የአርበኞች ግንቦት 7 ትግል ሁለገብ ነው። የትጥቅ ትግልን ጨምሮ በኢትዮጵያ በሙሉ የህዝብ አልገዛም ባይነትን በማቀጣጠል በወያኔ ላይ እንዲነሳ ማድረግ እና በሁሉም አገሪቷ አካባቢ በቡድን በቡድን እንዲደራጁ ማድረግ የሚል ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ይሄ አይደለምን? በአማራው እና በኦሮሞ ህዝብ ከዳር እስከዳር በመነሳት ለወያኔ አንገዛም እያለ አይደለምን? በደቡብ፣ በጋንቤላ፣ በአፋር፣ በአዲስ አበባ እንደተዳፈነ እሳት ታፍኖ ለመፈንዳት ግዜንና አጋጣሚን እየጠበቀ አይደለምን? ፕሮፌሰሩ በረቀቀ ሁኔታ ስራቸውን እየሰሩ ነው ሊያስብል አያስችልምን?። ህዝብን በፍቅርና በሰላም እንጂ በኋይልና በማስገደድ መግዛት አይቻልም።
ሲቀጥሉም በጀርመን አገር ከኢትዮጵያን ጋር ባደረገው ህዝባዊ ውይይት ላይ አንድ ታላቅ ነገር ተናግረዋል። እንደከዚህ ቀደሙ በእርግጠኝነት ድርጅታቸው ሊሰራ ያሰቡትን እና የሚሆነውን ነገር ሲናገሩ፦ አሁን አርበኞች ግንቦት ሰባት በሰፊው እና በጥልቀት የሰራውና እየሰራም ያለው መከላከያ ውስጥ ያለውን ኋይል የህዝብ የማድረግ ስራ ነው። መከላከያው ህዝብ ላይ እንዳይተኩስ እና ከህዝብ ጎን እንዲቆም የማድረጉን ስራ በመስራት ለወደፊት ለምትመሰረተው ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ የሰራዊቱ ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ እና ወደፊትም በነጻነት ለአገሩ እና ለህዝቡ ድጋፍና ሃይል የሆነ ሰራዊት እንደሚሆን የማሳወቁን ስራ በስፋትና በታላቅ ምስጢር እንሰራበታለን በማለት ለታዳሚው ገልጸዋል። ሲቀጥሉም ሰራዊቱ ከህዝብ ጋር አንድ ሆነ ማለት ያኔ ወያኔ አከተመለት ማለት ነው። ነገር ግን ወያኔን ጥለነው ህዝብ የሚያስተዳድረው ዲሞክራሲ ስርአት ተመስርቶ እስክናይ ድረስ ብዙም ፉከራ አናበዛም በማለት ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የተናገሩት በስራ እንደታየው ሁሉ አልገዛም ባይነትን ወደህዝቡ በማስረጽ አልገዛም ባይነትን እንዳቀጣጠሉት ሁሉ ዛሬም በንግግራቸው እንደገለጹት መከላከያውን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በማሰለፍ የኢትዮጵያን የነጻነት ንቀን በአጭር ግዜ ያመጡት ይሆንን? የተወሰኑ አሰራዊት አባል ህዝባችን ላይ አንተኩስም በማለት ከህዝብ ጎን መሆናቸውን እያሳዩ ነው ነገስ………?
ሌላው ያነሱት ሃሳብ ወያኔ በሃሳብ ድርቅ የተመታ ቡድን ሆኗል። አዲስ ሃሳብ ማምጣት ስለማይችሉ ያረጀውን ሃሳብ ነው ማስቀጠል የሚፈልጉት። ይሄ ደግሞ አደጋው ከፍተኛ ነው። በዚህ ምክንያት አገር መስቀልያ መንገድ ላይ እንድትቀመጥ አድርገውታል። አገር መስቀልያ መንገድ ላይ ስትቀመጥ ደግሞ ብዙ ነብያት ይመጣሉ ነገር ግን የትኛው ትክክለኛ ነብይ ነው የትኛውስ ነብይ ትክክለኛ አይደለም የሚለውን መለየት አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያን ጠንካራ መሰረት ላይ ማስቀመጥ አለብን። ጠንካራ መሰረት የመመስረት ስርአት ለማምጣት ብዥታ የሌለው አቋም ያስፈልጋል። ይህንን መሰረት በማድረግ ወደ ዋናው መዳረሻችን እንሄዳለን ያም የአገር አንድነት ነው። እዛ እንደምንደርስ ስለምናውቅ ዘላቂ አቋማችንን እንዲያሰናክሉብን ለየትኛውም አካል አንፈቅድም። ወደ እውነት የሚወስደው መንገድ ከባድ ነው። ቢሆንም ግን እውነት ሁል ግዜ አሸናፊ ስለሆነ እስከመጨረሻው እንገፋበታለን ብለዋል። በመቀጠልም ማሳሰቢያ ነገርም ጣል አድርገው አልፈዋል እንዲህ በማለት ሰው ማሰቢያው ከተወሰደ አውሬ ነው የሚሆነው እኛም ማሰቢያችን እንዳይወሰድብን ልንጠነቀቅ ይገባል በማለት።
ፕሮፈሰሩ ንግግራቸው ወቅታዊ እና በሳል ንግግር ነበር። ከንግግራቸው መሃል የተወሰነውን ነው በጽሁፌ መቃኘት የቻልኩት ሙሉውን የሙኒክ አዘጋጅ ኮሚቴ እና አባይ ሚድያ ስለቀረጹት ሙሉውን ንግግር ከዛ ላይ እንደምታገኙት በመጠቆም ጽሁፎን እቀጥላለው። በዚህ ትግል ውስጥ አሉ ፕሮፌሰሩ ንግግራቸውን በመቀጠል በዚህ የትግል ሂደት ውስጥ ማን ጥግ እንደሚደርስ አናውቅም። በዚህ ስሌት የሚወሰደው እርምጃ አንተ ብቻ ጥግ የምትደርስበትን መንገድ በመከተል በሰዎች ላይ ተረማምደህ መድረስ ያለብህ ቦታ እደርሳለው ብለህ የምታስብ ከሆነ አገርንም በማፍረስ ሂደት ላይ ወደኋላ እንደማትል እሙን ነው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች አደገኛ ስለሆኑ በአንክሮት ልናያቸውና ልንከታተላቸው ይገባል ብለዋል።
ሌላው የተናገሩት በኢትዮጵያ የወደፊት ጉዳይ ላይ ሁለት የተጋረጡ እውነታዎች አሉ። እነርሱም ጥሩ እና መጥፎ እንደሆኑ አስቀምጠውታል።
ወያኔ የመውደቁ ጉዳይ አይቀሬ ነው። ይወድቃል። ሲወድቅ ግን በሚወድቅበት ዋዜማ ላይ ተስፋ ሲቆርጥ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በሙሉ አደገኛ ስለሚሆኑ ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩ ስለሚሆን የኢትዮጵያ ማህበረስብም ሆነ ግለሰቦች በተረጋጋና በማስተዋል አዎንታዊ የሚባሉ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው በመጠቆም በአዲስ ህብረተሰብ በአዲስ መሰረት ላይ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርአትን መመስረት ነው በማለት ጥሩ ያሉትን ሲገልጹ
መጥፎ ያሉትን ደግሞ፦ ወያኔ መውደቁ ምንም ጥርጥር የለውም በምንም ሁኔታ መጥፋት ያለበት ስርአት ነው ይጠፋል። ወያኔ ሲወድቅ ግን ልባቸው በክፋትና በቂም በተሞሉ ሰዎች ላይ ስልጣኑ ከወደቀ በህዝብ ላይ ሊመጣ የሚችለው አደጋ ቀላል እንዳይደለ በመግለጽ ስጋታቸውን አስቀምጠውታል።
ንግግራቸውን በመቀጠልም ሊመጣ የሚችለውን አደጋ በመፍራት እጅ እና እግራችንን አጣጥፎ መቀመጥ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያመጣ በመግለጽ አገር የምትጠፋው ወያኔ በስልጣን እንዲቆይ በፈቀድንለት ግዜ ብቻ እንደሆነ አስምረው ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተነሱበት ርዕስ “ ኮስታራ ሐሞትና ለስላሳ ልብ የሚፈልግበት ግዜ” የሚል ሲሆን ንግግራቸውን የቋጩበት ደግሞ “የኢትዮጵያን ህዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ ራሱን የሚያስተዳድር ህዝብ እናደርገዋለን” የሚል ነበር።