እያንዣበበ ያለው አደጋና ማድረግ ያለብን፣ ባይሳ ዋቅ-ወያ (ለውይይት መነሻ)

“ከየት እንደምጀምር ግራ ገባኝ እንጂ ማድረግ ያለብኝን ጠንቅቄ አውቃለሁ፣” አለች ቢምቢዋ ባህር ዳር ራቁታቸውን ፀሃይ ለመሞቅ የተኮለኮሉትን የነጭ ቱሪስቶች ዕርቃነ ሥጋ እየቃኘች።

መግቢያ

በቅርቡ “ድርድር ከወያኔ ጋር” የሚል ጽሁፍ ባንዳንድ ድህረ ገጾች አሳትሜ ነበር። በጽሁፎቹ ይዘት የረኩ በርካታ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ ሃሳባቸውን አካፍለውኛል። ብዙዎቹ “የመደራደርን” መሰረተ ሃሳብ ትክክለኛነት ባይክዱም፣ የወያኔ ባህርይ ግን ለየት ያለ በመሆኑ፣ በትግል ስልቱ ውስጥ የትጥቅ ትግልን ያላካተተ ተቃዋሚ ድርጅት ከወያኔ ጋር በአቻነት ተቀምጦ ሊደራደር አይችልም የሚሉ ነበሩ። በበኩሌ፣ ለፖሊቲካ ችግር መፍትሄ ሂሳባዊ ፎርሙላ ስለሌለው ይሄኛው የትግል ዘዴ ከዚያኛው የተሻለ ነው ብዬ መሞገት ባልችልም፣ ወያኔን ግን ከሥልጣን ለማውረድ ወይም እንዲ(ያ)ጋራ ለማስገደድ ብቸኛው መፍትሄ “ኃይል” መሆኑን አምንበታለሁ። ምን ዓይነት “ኃይል” በሚለው ላይ ግን፣ ከላይ ያሰፈርኩትን ሃሳብ ከሚያራምዱት ለየት ያለ አስተሳሰብ እንዳለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ። የትግል ሥልቱንና መጠቀም ያለብንን “የኃይል” ዓይነት ለጊዜው ወደ ጎን ትተን፣ አሁን ካለንበት አገራዊ ቀውስ በአሸናፊነት ለመውጣት በመጀመርያ ደረጃ መግባባት ያለብን፣ ከወያኔ ጋር መደራደር በሚለው መሰረተ ሃሳብ ላይ ነው ባይ ነኝ። የምንደራደረውም ወያኔን ወዳጅ ለማድረግ ሳይሆን ላገሪቷ የግዛት አንድነትና የህዝቦቿ ሰላም ሲባል፣ የግፍ አገዛዙና የጅምላ ግድያው አብቅቶ፣ አስራ አንድ ምናምን ከመቶ ዕድገቱም ቀርቶብን እስከነድህነታችን በሰላም የምንኖርባትንና ማንም ማንንም የማይገድልበት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ነው። ታሪክንማ በተመለከተ፣ ወያኔ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በጭካኔነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግፈኛ መንግሥት ነበር ተብሎ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ እንደሚወሳ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ አይኖረኝም። ያንን ደግሞ ለታሪክ እንተወው።

ዛሬ ባገራችን እየተከሰተ ያለው ነውጥ፣ ፊት ይካሄዱ ከነበሩት ሁሉ በቅርጽም ሆነ በይዘቱ ለየት ያለ በመሆኑ፣ እንደወትሮዬ “ደረቅ ሃሳቦችን” ብቻ ለውይይት ማቅረቡን ትቼ፣ መደረግ ባለበትና ማድረግ ባለብን (action oriented) ተግባሮች ላይ ብቻ ስለማተኩር፣ አንዳንዶቻችሁ በተለይም ካገር ውጭ ያላችሁ የፖሊቲካ ድርጅቶች “የትግል ስልታችሁንና ዕቅዳችሁን ለማስቀየር የተወጠነ” መስሎአችሁ ቅር እንደማትሰኙብኝ አምናለሁ። ዓላማዬ፣ ወያኔን “አላምዶ” ለድርድር እንዲቀርብ ለማስገደድና አገሪቷን ከአደጋ ለማዳን ብቻ ነው።
ወያኔን እንዲደራደር የሚያስገድደው ኃይል ብቻ ነው፣ ግን ምን ዓይነት ኃይል?

ለብዙዎቻችን፣ ትግል ማለት የጦር መሳርያን ያካተተ ክስተት ብቻ ነው የሚመስለን። በታሪካችን አንድም በጠብመንጃ ሳይደገፍ ሥልጣን ላይ የወጣ ያገር መሪ አፍርተን ስለማናውቅ፣ ያለመሳርያ የፖሊቲካ ሥልጣን መያዝና ይዞም ለመቆየት ይቻላል የሚለው አማራጭ በጭንቅላታችን ባለመቅረጻችን መወቀስ ያለብን አይመስለኝም። በበኩሌ፣ ይሄኛው የትግል ዘዴ ከዚያኛው የተሻለ ነው ለማለት ባልደፍርም፣ በትክክል ግን ለማለት የምችለው፣ በዛሬው ዘመን፣ በተለይም ዓለማችን የብዙ ጽንፈኛ ቡድኖች ሰለባ በሆነችበት ወቅት፣ ህዝባዊ ዓመጽ በአግባቡ ከተዋቀረና ከተመራ፣ ከትጥቅ ትግል በተሻለ መልኩ ውጤታማና ዓለም ዓቀፋዊ ተቀባይነት አለው ባይ ነኝ። የትጥቅ ትግል ጭቆናን ለማስወገድ ፈጽሞ አስፈላጊ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም። የታጠቀና የተደራጀ፣ ወያኔን በጉልበት አስወግዶ ሰላምና መረጋጋትንና፣ ብሎም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረት ለመጣል የሚችል የታጠቀ ህዝባዊ ሰራዊት ቢኖር እሰዬው ባልን ነበር፣ ግን ያ የለም፣ እንዲኖርም ሁኔታውም አይፈቅድም፣ ስለዚህ ያለን ብቸኛው የትግል ዘዴ ህዝባዊ አመጽ ብቻ ነው። ወያኔን የመሰለ የተደራጀ የፖሊስና መከላከያ ሰራዊት ያለውን ፀረ ህዝብ ኃይል መቋቋም ብሎም ማሸነፍ የሚቻለው ጥሩ አመራር ባለው ህዝባዊ አመጽ ብቻ ነው። ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝቦች ያለአንዳች መሳርያ ድጋፍ በሰላም ያካሄዱት ህዝባዊ ዓመጽ የወያኔን የሥልጣን ወንበር አነቃንቆ አስቸኳይ ጊዜያዊ ዓዋጅ እንዲያውጅ ማስገደዱ፣ ያለጠብመንጃ መንግሥትን ማንበርከክ ለመቻሉ ህያው ምስክር ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም።

በኔ ግምት፣ ከሕዝባዊው ዓመጽ ቀጥሎ ወያኔን ለድርድር እንዲቀርብ የሚያስገድደው ሌላው ዕውኔታ፣ አንጋፋውና ከደደቢት በረሃ የመጣው አፍቃረ-ጠብመንጃ “ነጻ አውጪ” ትውልድ የተፈጥሮ ህግን ተከትሎ ሲሸጋሸግ፣ ተተኪው ትውልድ ከፊተኞቹ የተለየ አመለካከት ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ። አባቶቻቸውም አስተማማኝና ለዘላለም የሚበቃቸውን ሃብት ስላከማቹላቸው፣ ይህ ወጣቱ ትውልድ፣ ህዝብን በጠብመንጃ አስፈራርቶ ከመኖር፣ ሥልጣንን በዕኩልነት ለመካፈልና የሰላም ኑሮን ለማጣጣም ዝግጁ የሚሆን ይመስለኛል። ትልቁ የወያኔ ደካማ ጎን፣ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጠላቱንና የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት ደግሞ የጭቆና አገዛዙን አቁመውና የፖሊቲካ ሥልጣንን ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በዕኩልነት ተጋርተው በሰላም መኖርን

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮሮና "ኩሩና" እና "ይህም ያልፋል" - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

መምረጥ እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ ብዬም እገምታለሁ። ካፒታል ደግሞ በመሰረቱ አብቦ የሚያፈራው ሰላም ሲኖር ብቻ ስለሆነ አባቶቻቸው “ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩላቸውን” ሃብት አጣጥሞ ለመኖር ይህ ወጣቱ ትውልድ አባቶቻቸው ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር እንዲደራደሩ ጫና ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በጥቂቱ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ላይ ተመርኩዤ ነው እንግዲህ ወያኔ ሥልጣን ለመጋራት “ፈቃደኛ” እንዲሆን “ሊገደድ” ይችላል የምለው። ተቃራኒው ምርጫ ደግሞ፣ ለማንኛችንም የማይበጅ የጥፋት ጎዳና እንደሆነ ወያኔም ጠንቅቆ ስለሚያውቅ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉለት ወይም ማስተማመኛ ካገኘ፣ ከመጥፋት ይልቅ ለድርድር ዝግጁ ይሆናል የሚል ፅኑ ዕምነት አለኝ።

አዎ! ወያኔ ካልተገደደ በቀር በፈቃዱ ሥልጣን አይለቅም፣ አይደራደርምም፣ ምክንያቶቹን ባጭሩ ልጥቀስ፣

ሀ) ወያኔ በጠብመንጃ ድጋፍ ሥልጣን ላይ እንደወጣ እንደማንኛውም መንግሥት፣ “ሁሉን አሸንፎ” የመጣ ስለሆነ፣ ሁሌም በጉልበት መግዛትና፣ ማህበረሰባዊም ሆነ ፖሊቲካዊ ችግሮችን በጉልበት መፍታት የሚቻል ይመስለዋል፣ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታትም ይህንን ጉልበቱን በደንብ ስለተጠቀመበት፣ ጠብመንጃ ለሥልጣን መወጣጫ ብቻ ሳይሆን የሥልጣን ዕድሜንም ለማራዘም ፍቱን ነው ብሎ ያምናል።

ለ) ወያኔ ሥልጣን ከመያዙም በፊት ሆነ ከያዘም በኋላ የትግራይንም ህዝብ ጨምሮ የብዙ ኢትዮጵውያንን ነፍስ ስላጠፋና እጁ በደም የተጨማለቀ ስለሆነ፣ ዛሬ ራሱን “ከህዝባዊ ፍርድ” ከሚከላከልበት የሥልጣን ወንበር ከወረደ፣ ደመኞቹ ከነነፍሱ ሊውጡት አሰፍስፈው እንደሚጠብቁት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በተቻለው መጠን ሥልጣን ላለመልቀቅ ይታገላል።

ሐ) ወያኔ በውስጡ ያቀፋቸውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኖኅ መርከብ ተሳፋሪዎች፣ ማለትም ደጋፊዎቹና የድርጅቱ አባላት ያካበቱትን ሃብትም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ለመጉዳት እየተጠቀሙበት ያለው የፖሊቲካ ሥልጣን ምንጩ ወያኔ በመሆኑ ይህን መሰል ጥቅምና ኃይል ላለማጣት ሲባል ብቻ ወያኔ ሥልጣን ላይ እንዲቆይላቸው የተቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ አይቆጠቡም። ወያኔም ይህንን ጠንቅቆ ያውቃል። ይጠቀምበታልም።

መ) የመከላከያ ሠራዊቱ፣ በታሪካችን ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፣ በንግድ ዓለም ተሰማርቶ፣ “ከልማታዊ ነጋዴዎችና” የትላልቅ የኩባንያ ባለሃብቶች ባልተናነሰ መልኩ ንግዱን እያጧጧፈው ስለሆነና፣ በተለይም ባለከፍተኛ ማዕረግ የሰራዊቱ አባላት (ባብዛኛው የትግራይ ተወላጅ የሆኑት) ይህን መሰል የቅንጦት ህይወት ዋስትና ሊሰጣቸው የሚችለው የወያኔ መንግሥት ብቻ መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ፣ የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም ሲሉ ራሳቸውን ለመሰዋት ዝግጁ ናቸው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ወያኔም ይህንን ዕውኔታ ስለሚያውቅ በደንብ ይተማመንባቸዋል።

ሠ) አምባገነኖች ሁልጊዜ ከዕውኔታ በጣም የራቁ ናቸው። በሥልጣን ዘመናቸውም የህዝቡን የልብ ትርታና ስሜት ማዳመጥ ያልለመዱ በመሆናቸውና፣ በጃሌዎቻቸው ደግሞ ዘወትር የሚነገራቸው የአገዛዛቸው አዎንታዊ ጎኑና አስገራሚ የሆነ የኤኮኖሚ ዕድገት ብቻ ስለሆነ፣ ባገሪቷ እየተከሰተ ያለውን ነውጥና ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በትክክል መገምገም አይችሉም። በመሆኑም መቃብር ጫፍ እስኪደርሱ ድረስ “አንዳንድ በጥባጮች ናቸው እንጂ፣ ህዝቡማ ከልቡ ይደግፈናል” እያሉና ራሳቸውን እያታለሉ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። (ብዙዎች ይህንን ክስተተ ከታይታኒክ መርከብ የመስጠም ሂደት ጋር ያመሳስሉታል፥ በላይኛው ፎቅ ውዱ ሬስቶራንት ውስጥ የነበሩ ሃብታሞች በሻምፓኝ ሲራጩ፣ የመርከቡ ታችኛው ክፍል ግን በውሃ ተሞልቶ ኖሮ ደሃው ህዝብ መስጠም ጀምሮ ነበር፥ ቀስ በቀስ ግን ላይ ያሉትም ሳይታወቃቸው ከነመርከቢቷ ሰጠሙ)። ሥርዓቱ ከሥር በስብሶ ተመልሶ ማገገም የማይችልበት ደረጃ እንኳ ደርሶ እያለ፣ ላይ ያሉት ሁኔታው እንደ ድሮ እየመሰላቸው በሻምፓኝ ሲራጩ፣ መጨረሻ ላይ ሳይታወቃቸው በድንገት ይሰጥማሉ። የሚያሳስበው ግን አይቀሬው የአምባገነኖች አወዳደቅ ሳይሆን የነሱን መወገድ ተከትሎ የሚመጣው መዘዝ ነው።
ታድያ ማድረግ ያለብን ምንድነው? ከየትስ እንጀምር?

በድርድር ግጭቶችን ማስወገድና በሰላም አብሮ የመኖርን ክቡርነት ጥቅም ሁላችንም የምናውቀው ብቻ ሳይሆን ላገራችንም የምንመኘው ስለሆነ፣ ተቃዋሚ ኃይሎችን ለዚያ ዝግጁ እንዲሆኑ የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል እላለሁ። ግን እንዴት አድርገን ነው ተቃዋሚ ኃይሎችንና ወያኔን ወደ አንድ ክብ የድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የምንችለው የሚለው ጥያቄ ደግሞ የጥያቄዎች ሁሉ እናት የሆነብን ይመስለኛል። የችግሮቻችን ውስብስብነትና አበዛዝ ብሎም መደረግ ያለበትና ማድረግ ያለብን እጅግ በጣም ብዙ ነው። የቸገረን ነገር ቢኖር ቢምቢዋም እንዳለችው፣ ከየት እንደምንጀምር ነው። አንድ መታወቅ ያለበት ዓቢይ ጉዳይ ግን ዛሬ ባገራችን በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ አመጽ፣ በፖሊቲካ ድርጅቶች ካልተመራና ካልተቀነባበረ፣ ሊያስከትል የሚችለው አላስፈላጊ የርስ በርስ ግጭት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ እየታየ ስለሆነ፣ ማድረግ ያለብንን ነገር በቀጠሮ ለማሳደር የማንችልበት ደረጃ ላይ መሆናችንን ከወድሁ ለማሳወቅ እሻለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለኢሳት፣ ለኦኤምኤን እና ለሕወሓት በያላችሁበት – ምሕረቱ ዘገዬ (አዲስ አበባ)

ወያኔ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ለመደራደር “በገዛ ፈቃዱ ተገዷል” እንበልና፣ ቀጥሎ የሚመጣው ትልቁ ጥያቄ፣ የመደራደርያ ነጥቡ ምንድነው የሚለው ነው። ለኔ መልሱ ቀላል ነው፣ ወያኔ የፖሊቲካ ሥልጣኑን ከእውነተኛ የህዝብ ተወካዮች ጋር በዕኩልነት ይካፈላል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የዛሬው የወያኔ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ተገርስሶ በምትኩ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብን የሚወክል የሽግግር መንግሥት መቋቋምና ብሎም በህዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ መንግሥትን ማቋቋም ማለት ነው። አራት ነጥብ። ወያኔ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖሊቲካ ድርጅት፣ ከፈለገ እንደ አንድ የትግራይ ብሄር ፓርቲ፣ ካሰኘውም ደግሞ እንደ አንድ አገር ዓቀፍ ፓርቲ ራሱን አደራጅቶ ከሌሎች ጋር በእኩልነት፣ አድልዖና ጫና ሳይታከልበት፣ አዲስ በሚወጣው የምርጫ ህግ መሰረት ተወዳድሮ ያሸነፈበትን ድርሻ ይዞ በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ መካፈሉን ይቀጥላል ማለት ነው።

በመቀጠል የሚቀርበው ሌላኛው ትልቁ ጥያቄ ደግሞ፣ ከተቃዋሚ ሃይሎች ወገን የኢትዮጵያን ህዝብ/ብሄሮችን ወክለው ከወያኔ ጋር ለድርድር የሚቀርቡ እነማን ናቸው የሚለው ይሆናል። ይህ የጥያቄዎች ሁሉ እናት ይመስለኛል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ አገር-ዓቀፍና ብሄራዊ ድርጅቶች ባገሪቷና በውጭ አገር እንደ አሸዋ ሞልተው በፈሰሱበት ምድር፣ ማን ማንን ወክሎ ለድርድር እንደሚቀርብ ለሁላችንም ራስ ምታት ሆኖብንና መምረጥ አቅቶን፣ ወያኔ “ባገራችን ሰላም እንዲሰፍን ብዬ ለድርድር ብቀርብ፣ ተደራዳሪ አጣሁ” ብሎ ለዓለም ህዝብ በማሳወቅ ያሳፍረናል ብዬም እሰጋለሁ። የድርጅቶቹ መብዛት የችግሮቹንም ዘርፍ መብዛት ያሳያል። በደርዘን ከሚቆጠሩት አገር-ዓቀፍና ብሄር ተኮር ድርጅቶች እንዴት ተደርጎ ተደራዳሪዎችን መምረጥ እንደሚቻል በበኩሌ አንዳች ዓይነት ሂሳባዊ ፎርሙላ የለኝም፣ በትክክለኝነት ለማለት የምችለው ግን፣ ሀ) የድርድር ጠረጴዛው የዚህን ሁሉ ድርጅት ተወካዮች በተናጠል ለማስተናገድ አይችልም፣ ለ) ስለሆነም ባገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የፖሊቲካ ድርጅቶች ካሁኑ የጋራ ምክክር ጀምረው፣ በጋራ ነጥቦች ላይ በመስማማትና የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም ተወካዮቻቸውን የመምረጡን አዳጋች ሥራ መጀመር አለባቸው፣ ሐ) የድርድር ነጥቦችና ብሎም የሽግግር መንግሥቱ ሰነድ ቅድመ-ዝግጅት ካሁኑ መጀመር አለበት።

እንግዲህ አገር ቤት ያሉትና ውጭ አገር ያሉትም ድርጅቶች ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ለድርድር የሚቀርቡበትን ተወካዮቻቸውን የመምረጡን ዘዴ ፈልጎ ተግባራዊ ማድረጉን ለነርሱ እንተውና፣ እኛ እዚህ ውጭ አገር ያለነው ግለሰቦችና ኢ- ፖሊቲካዊ የሆንን ድርጅቶችስ ደግሞ ምን ማድረግ አለብን ወደምለው ክፍል ስንሻገር የሚከተሉትን ታሪካዊ ግዴታችንን መጥቀስ እሻለሁ።

ሀ) በተቻለ መጠን በምንችለው መስክ ሁሉ ለተቃዋሚ ድርጅቶቹ ጥምረቱንም ለመመስረትና ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ብሎም ድርድሩም የተሳካ እንዲሆን ሁላችንም በየሙያችን የሚቻለውን ማዋጣት አለብን፥ በምንኖርባቸው አገራት የመረጥናቸውን የፓርላማ አባላትና የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ዲፕሎማቶችንና የአለም ዓቀፍ ተቋማትን እየቀረብን ስላገራችን ዕውኔታ ማስረዳትና ማሳመን፣ በምናስተምርባቸው ተቋማትም ሁሉ ተመሳሳይ ተልዕኮ ላይ ብንሰማራ ለድርድሩ መሳካት ትልቅ አስተዋጽዎ አደረግን ብዬ እገምታለሁ። የህግ ባለሙያዎችና የፖሊቲካ ጠቢባንም የሽግግር መንግሥቱን ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀት ብሎም በተቃዋሚ ድርጅቶችና በሰፊው ህዝባችን ተቀባይነት እንዲያገኝ መትጋት ሌላው ታሪካዊ ግዴታ ይመስለኛል።

ለ) በሆነ ባልሆነው ከመናቆር ተቆጥበን የምንጽፋቸውና የምንናገራቸው በሙሉ ላገሪቷ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ለሚደረገው ርብርብ ዕገዛ እንዲያደርጉ መጣር አለብን። ያለፉትንና ልንመልሳቸው በማንችላቸው ጉዳዮች ላይ “በመወያየት” ጊዜ ከማጥፋት፣ ዛሬ ልንቀይር በምንችላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ኃይላችንን እናስተባብር። ስብከታችንና ዲስኩራችን፣ ጭቆናን የማታስተናግደውን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንዴት በጋራ ልንገነባ እንችላለን በሚለው ላይ ብቻ ማነጣጠር አለበት።

ሐ) ወያኔን ለመደራደር የሚያስገድደው ህዝባዊ ዓመጽ ነው ብለን እስከተግባባን ድረስ፣ ሁላችንም ያለንን የግልም ሆነ የቡድን የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም ህዝቡ ባንድ ላይና ላንድ ዓላማ ባንድ ጊዜ እንዲነሳሳና በህዝባዊ ዓመጹ እንዲካፈል ማድረግ ግዴታችን ይመስለኛል። ህዝባዊ ዓመጽ ማለት ደግሞ ከመሳርያ ትግል በቅርጽም ሆነ በይዘቱ የተለይ መሆኑንና ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግም በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ አብሮ መድረስ ያለበት መልዕክት መሆን አለበት። አንዳንዶቻችን አሁን በማድረግ ላይ እንዳለነው፣ ካገር ቤት የሚደርሱንን መሰረተ-ቢስ የወያኔ የፕሮፖጋንዳ ወሬዎችን ዋቢ በማድረግ፣ አንዱ ህዝብ በሌላው ላይ ተነስቷል ብለን ከማናፈስ ተቆጥበን፣ በመጀመርያ ደረጃ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ፍቅር እንዲሰፍን መስበክ፣ ያንንም ደግሞ በማስታከከ ወያኔ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም በህዝቦች መካከል የጥላቻ መርዝ ከመርጨት እንደማይመለስ ለህዝባችን የተገኘውን ሁሉ አጋጣሚ ተጠቅመን ማስረዳት አለብን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በእውነቱ ኢትዮጵያ መንግሥት አላትን? አማራውስ አሁን ምን ማድረግ አለበት?

መ) ሌላው ትልቁ ሥራችን የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊቲካን ለማክሸፍ አንዱ ብሄር ባንዱ ላይ እንዳይነሳና የወያኔ ሰርጎ ገቦችም ህዝቡን እንዳያዘናጉ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ያለመታከት ማስረዳት ነው። አለበለዚያ ዛሬ በአምቦና በምሥራቅ ሐርርጌ የአግዓዚው ጦር ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ የኦሮሞ ወጣቶችን ሲጨፈጭፍ፣ በጎንደርና መቀሌ ያለው ህዝባችን

የተቃውሞ ድምጹን ካላሰማ፣ ዛሬ በአምቦና በነቀምቴ፣ በበደሌና በቤኒሻንጉል በግድያ ተልዕኮ ላይ የተሰማራው አሸባሪው የአግዓዚ ጦርና ሰርጎ ገብ ነፍሰ ገዳዮች፣ ነገ ደግሞ ወደ ጎንደርና መቀሌ ሄደው ተመሳሳይ ተልዕኮ ላይ መሰማራታቸው አይቀሬ ስለሆነ ከወድሁ ነቅተን ህዝባችን ክንዱን አስተባብሮ ለአንድነት መቆም እንዳለበት ማስተማር አለብን። አለበለዚያ በናዚ ጀርመን ጊዜ የኖረውና ሰባት ዓመት በጅምላው እስር ያሳለፈው ታዋቂው ፀረ-ናዚ የፕሮቴስታንት ቄስ ማርቲን ኒየምለር፣

“መጀመርያ ሶሺያሊስቶችን ሲገድሉ ሶሺያሊስት አልነበርኩምና ምንም ዓይነት የተቃውሞ ድምጽ አላሰማሁም። ከዚያ የሙያ ማህበራት መሪዎችን ሲገድሉ ምንም አላልኩም፣ የሙያ ማህበር አባል አልነበርኩምና። ቀጥሎም አይሁዶችን መግደል ሲጀምሩ ዝምታን መረጥኩ፣ አይሁዳዊ አይደለሁምና። መጨረሻ ላይ እኔን ሊገድሉ መጡ፣ ያኔ ግን ለኔ ድምጹን የሚያሰማ አልነበረም፣ ለካ ባካባቢዬ የነበሩ በሙሉ ተገድለው አልቀዋልና” ያለው ደርሶብን፣ አረመኔው የአግዓዚ ጦር ተራ በተራ እየለቀመ ለሞት እስኪዳርገን ድረስ እጆቻችንንን እግሮቻችንን አጣጥፈን ከተቀምጥን፣ የምንሞተው ከንቱ ሞት ብቻ ሳይሆን በታሪክ ፊትም በግድያው ተባባሪ ሆነን እንደምንቆጠር ማወቅ ያለብን ይመስለኛል። ዳንቴም “ገሃነም ውስጥ በጣም የሚያቃጥለው ክፍል በቅድሚያ የተያዘው ህብረተሰብ ውስጥ ቀውስ መፈጠሩን እያዩ ገለልተኝነትን ለመረጡ ግለሰቦች ነው” እንዳለው ማለት ነው።

መ) በኔ ግምት ወያኔ የጥቂት የትግራይ ኤሊቶችንና የሥርዓቱ ተጠቃሚ ጀሌዎችን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ እንጂ ሰፊውን የትግራይን ህዝብ አይወክልም ባይ ነኝ። የትግራይ ህዝብ ዛሬ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲ ተነፍጎትና በድህነት የሚኖር፣ ወጣቱ እንደማንኛውም የሌላው ክልል ወጣት ሥራ አጥቶ የሚንከራተትና ህዝቡም በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ሰለባ በመሆኑ፣ ወያኔን ስናወግዝ የትግራይም ህዝብ አብሮ እንዳይወቀጥ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። የትግራይ ሰፊ ህዝብም ይህንን የወንድሞቹናና እህቶቹን በጎ ሃሳብ ተገንዝቦ ሰልፉን ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አስተካክሎ የወያኔን ግፍ እንዲያወግዝ መቀስቀስ አለበን።
መደምደሚያ፣

በመካሄድ ያለው ህዝባዊ ዓመጽና ፍጥነቱ፣ ቁጭ ብለን ጊዜያችንን ወስደን እንደተለመደው የተንዛዛ ውይይት ለማካሄድና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለማውጣት ፋታ የሚሰጠን አይመስለኝም። ሰዎች በየቦታው አንዴ በአግዓዚ ጦር፣ አለያም ራሱ ወያኔ በሚቀሰቅሰው የርስ በርስ ግጭት ሳቢያ እየተገደሉና ሁኔታው ከቁጥጥር እየወጣ ሲሆን፣ ይህንን አገር ዓቀፋዊ ነውጥ ለማርገብና ሰላም የማምጣት ግዴታ ያለበት ማዕከላዊው መንግሥት ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደክሞ የታየበት ታሪካዊ ወቅት ነው። የፌዴራሉ የኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር የሚሰጠውን መግለጫ አንድ ተራ የብሮድካስቲንግ ኤጄንሲ ሥራ አስኪያጅ የሚያጣጥለው ከሆነና የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሚያስተላልፈውን ውሳኔ አንድ ተራ የእሥር ቤት ዘበኛ የማይቀበለው ከሆነ በርግጥም ባገሪቷ ሥልጣን በማን እጅ እንዳለም ግራ የሚያጋባ ነው። ታዲያ ማዕከላዊው መንግሥት እየተዳከመ፣ ህዝቡ የመብቱን መከበር በጠየቀ ቁጥር መልሱ ጥይት ከሆነና፣ ገዳዮቹ ደግሞ የማይጠየቁበትና ለፍርድ የማይቀርቡ ከሆነ፣ ተበደልኩ ባዩ ህዝብ በህግና ፍትህ መተማመኑን ትቶ፣ በራሱና በወገኖቹ ድጋፍ ህጋዊ ያልሆነ አፀፋውን መመለስ ይጀምራል፥ ፈረንጆች mob justice ወይም (የጅምላ ፍትህ) የሚሉት ባገሪቷ ይስፋፋና ህግና ሥርዓት ጠፍቶ ህገወጥነት ይስፋፋል። ያንን ነው መፍራት ያለብንና እንዳይከሰትም በጋራ መታገል አለብን የምለው።

ማድረግ ያለብንን በሙሉ መዘርዘር የሚቻል አይመስለኝም፣ ያም ሆኖ ግን፣ በእነዚህ ከላይ በዘረዘርኳቸው መሰረተ ሃሳቦች ከተስማማን ሌሎቹን ደግሞ እንዳመጣጣቸው ላካባቢያችን እንደሚመች አድርገን ተግባር ላይ ማዋል አለብን እላለሁ፡ ዋናው ነገር ለመሥራት ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት ነው እንጂ የሚሰራውማ በጣም ብዙ ነው። ሰላምን ለማምጣት ከወያኔ ጋር መደራደር አስፈላጊ መሆኑንና፣ ዛሬ ወገኖቻችን መብታችን ይጠበቅልን ብለው ህጋዊ ጥያቄ ብቻ በማቅረባቸው ብቻ በጥይት ሲቆሉ እያየን፣ ሰላምን ለማምጣት ድርድር አስፈላጊ መሆኑንና ለተደራዳሪዎች ደግሞ አንዳች ዓይነት የድጋፍ ድምጽ አለማሰማት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ችግሮቹ እንዲባባሱ አስተዋጽዖ ከማድረግ ባሻገር ለግድያውም ወንጀል ተባባሪ ከመሆን ሌላ ትርጉም አይኖረውምና በጥብቅ እናስብበት ባይ ነኝ። በቸር ይግጠመን!
****

ጄኔቫ፣ ዴሴምበር 2, 2017
wakwoya2016@gmail.com

1 Comment

  1. “ወያኔ ነፍጥ ካልያዙ የታቃዎሚ ሀይሎች ጋር ካልሆነ ለድርድር አይቀመጥም” የትኞቹ ነፍጥ የያዙ ሀይሎች ? የነፃነት ሀይሎች ከአፋቤት ወይስ የዲሲዎቹ ነፃ አውጪዎች ከሰሚን አሜርካ ምሽጋቸው ? እኮ የትኞቹ ? እንደዚህ ያለውን የጠጅቤት ወሬ የሚያናፍሱት የዲያስፓራ የፓለቲካ ንግድ ድርጅቶች ናቸው። ወያኔን ከስልጣን ላይ የሚያወረደው ሀገር በቀል በሆነው የአማራና ኦሮሞ ህዝባዊ አመፅ እና ነፍጥ ባነገቡ የጎበዝ አለቆች ታጅቦ ነው።

Comments are closed.

Share