ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ… – ነፃነት ዘለቀ

 

“ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም” ይባላል፡፡ ወያኔ ራሱ የማይቀበለውንና የማያምንበትን ባለኮከብ የሉሲፈር ዓርማ ሕዝቡ አንዲወድለት መፈለጉ ከመነሻው ስህተትና ሕዝብን መናቅም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይመክርበትና ሳይስማማ በጨረባ ተዝካር መሰል የአፈንጋጮች ጉባኤ ላይ በመለስና ቡድኑ በቀረበ ባንዴራ ስትደዳደር ይሄውና ኢትዮጵያ ሀገራችን 27 ዓመት ሊሆናት ነው፡፡ በዚህን ረጂም ዘመን ሕዝቡና ባንዴራው ውኃና ዘይት እንደሆኑ አሉ፡፡ ጊዜው ግን እንዴት ይነጉዳል? ከኔን መሰሉ ተራ ግለሰብ አንስቶ እስከ ሀገር ደረጃ ከዕድሜ ላይ የ27 ዓመት ውድ ጊዜ ሲቃጠል ምን ያህል የእግር እሳት ሊሆን እንደሚችል አስቡት፡፡ ኢትዮጵያ ነፃ ስትወጣ ወያኔ ያቃጠለብኝ ዕድሜ ተቀናሽ እንዲሆን ለሚመለከተው ሁሉ እንደማመለክት ከአሁኑ ነጥብ ማስያዝ እፈልጋለሁ፡፡ በውነቱ ይህን የገማና የገለማ የወያኔ ጊዜ የኖርኩበት አይመስለኝም፤ ያሣፍረኛልም፡፡ የሀገሬ የአሁንና ያለፉት 26 ዓመታት ጠረን በልጅነት ጊዜየ ከነበራት ከአሁኑ ሲነፃፀር አልባብ አልባብ ይል ከነበረ ጠረን በእጅጉ ተለይቶብኝ በየሄድኩበት ቦታ ሁሉ በሚያጋጥመኝ ወያኔያዊ ክርፋት ምክንያት ስሳቀቅ እንደምውል መሸሸግ አልፈልግም፡፡ የክርፋቱ መንስዔ ተቆጥሮ አያልቅም – የዘረኝነቱ ጥምባት፣ የዘር ማጽዳቱና የጄኖሳይዱ ቅርናት፣ የሙስናው ግማት፣ የማይምነቱና የአስተሳሰብ ድህነቱ ቅርሻት፣ የአድልዖው ብስናት፣ የአጎብዳጅነትና አሽቃባጭነቱ ቁናስ፣ …. በስማም! ስንቱ ዝቅጠት ተነግሮ ይዘለቃል ወዳጄ፡፡ የሚገርመኝ ወደላይ መጓዝ ባይቻል ባሉበት መርገጥም ዕርም ሆኖብን ይቅር? አንድ ሀገርና አንድ በታሪክ የታወቀ ሕዝብ ወደፊት መራመድ ቢያቅተው ቢያንስ የደረሰበትን የሥልጣኔና የዕድገት ደረጃ ጠብቆ መቆየት ይገባው ነበር፤ የኛ ግን ወዳልነበርንበት የውድቀት ደረጃ ለመድረስ በሰፊው ያቀድን ይመስል በብርሃን ፍጥነት የኋሊት እየከነፍን እንገኛለን፡፡ በታሪክ ፊተኞች እንዳልነበርን ዛሬ ከኋለኞች መጠጋም እንኳን አቅቶን ውራነታችን ቅጥ አጣ፡፡ …

ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ወያኔ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ብሎ የመንግሥት ሠራተኞችንና ሕዝቡን ባጠቃላይ እያተራመሰ ነው፡፡ ወያኔዎችን ፀጥታ ይረብሻቸዋል፡፡ ጭር ሲል የማይወዱት ሕወሓቶች አገር ምድር ፀጥ ረጭ ሲል ደም ብዛታቸው ያሻቅባል፤ የስኳር ህመማቸው ልኬት ይጨምራል፤ ራስ ምታታቸውም ከወትሮው ያይላል፡፡ እኚህ ጉዶች ከማይወዷቸው አበይት ነገሮች ዋነኛው ፀጥታ ነው፡፡ በበዓሉ ግርማ አገላለጽ በፀጥታ አደንቋሪነት ወያኔዎች ለምን እንደሚሸበሩና እንደፊጋ ከብት እንደሚበረግጉ እስካሁን  ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ዝምታ የሚያሰቃያቸው ፍጡራን ወያኔዎች ብቻ መሆን አለባቸው፡፡ ስለዚህም ሀገር የተረጋጋ ሲመስላቸው፣ ሕዝብ ዝም ጭጭ ያለ መስሎ ሲሰማቸው ይህን እርጋታ ለማወክ የማይደርሱት ድራማ፣ የማይበጥሱት ቅጠልና  የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እንደሚመስለኝ አማካሪዎቻቸው ኃይለኞች ናቸው፡፡ ወያኔ መቼስ በራሱ ኃይል ኢትዮጵያን እየገዛ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ የሌት ዕንቅልፍና የቀን ዕረፍት የሌላቸው የጥልቁ ጨለማ አበጋዞች ከጎኑ ባይኖሩና ሁለንተናዊ ድጋፍ ባያደርጉለት ኖሮ ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁርስ ከመሆን አይዘልም ነበር – እንኳንስ የምኒልክን ቤተ መንግሥት ሊወርሱ ከደደቢትም ባልወጡ፡፡ ስለሆነም ይሄ ሁሉ ተንኮልና ሤራ የአማካሪዎቻቸው አስተዋፅዖ እንጂ ከነሱ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ለዘመናት ያጠመዱት ወጥመድ ያዘላቸውና እንዳንሆን አደረጉን፡፡ ታላላቆች በታናናሾች ተረቱ፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅልም ድንጋይን በደቦል ድንጋይ ያጥረገርገው ገባ፡፡ ይህን ዘመንና ይህን አገዛዝ ብዙ ተማርንበት፡፡ ግዴለም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ያልነበር የነበር፤ የነበርም ያልነበር የሚሆኑበት ጊዜና ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የነገሮች ልውውጥ ጊዜም እየደረሰ ይመስላል፡፡ ደግሞም ዕድሜ ለእምቦጭ፡፡ እምቦጭ እንኳን ባቅሟ ሥራዋን እየሠራች ነው – ከዚች እምቦጭ ከሚሏት ነገር እስኪ አንዳች ነገር እንማር ጎበዝ፡፡ የነአባዱላ እንቅስቃሴም ቀላል አይደለም፡፡ ከጅማሮው ፍጻሜውን መገመት አይከብድም፡፡ በፖለቲካ ውስጥ የሚናቅ ነገር የለም፡፡ የቤት ሠራተኛ ማመፅ ራሱ ዋጋ አለው –  እንኳንስ መናጆ በሬ በጌታው ላይ ሸፍቶ ይቅርና – መሸፈቱም እውነት ከሆነ ነው ሊያውም፡፡ ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባችም፤ በአንድ ሌሊትም አልፈረሰችም፡፡  ወያኔም በአንድ ሌሊት የምትፈርስ ተለማማጅ የሠራት ሙግድ አይደለችም፡፡ አማሮሞች የናቋት 11 ቁጥር ምስማር አላላውስ ብላ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የሚሊዮኖችን ሸኮና ስትቀጠቅጥና ግዳይ ስታስቆጥር ባጀች፡፡ አሁን ታዲያ ትረፋ! ወንድ ይብቀል፡፡ ብልኃተኛ ዜጋ ይወለድ፡፡ የኢትዮጵያ ችግር እስከወዲያኛው የሚወገደው በጉልበትና በዕብሪት ወይም በሽለላና በፉከራ ወይም በመሣሪያ ብዛትና በኃይል ሚዛን መለዋወጥና መበላለጥ ወይም ጎራና ጎሣ እየለዩ በነገር ቱማታና በጦር መሣሪያ መተጋተግ ወይም በሰንደቅ ዓላማና በተቃዋሚ ብዛትና ጎራ እየለዩ በተረሳ የፊተኞች ጥፋትና ልማት ሥራዎች መወራከብ … አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ እስክንጠግብ አየነው፡፡ አንዱም አልፈየደልንም፡፡ ይልቁንስ ጥበበኛ የሀገር ግንባታ መሃንዲሶች ይወለዱልን፡፡ እነዚህን መሰል የፍቅርና የመተሳሰብ ፊታውራሪዎችን ከየጎሣና ነገዱ ፈጣሪ እንዲልክልን፣ የቁስሎቻችንን ፈዋሾች አንድዬ ባርኮ በመላዋ ሀገራችን እንዲያሰማራልን ወደርሱም እንጩህ፡፡ ያኔ  እኛም ከስደትና ከሞት ሀገራችንም ከድህነትና ከጦርነት እናርፋለን፡፡ ችግራችን ውስብስብ ቢመስልም ለአንድዬ የሴከንዶች ትዛዝ ናት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰበር ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች - ኢህአዲግ እና ተቃዋሚዎች ወሳኝ ነጥብ ላይ ናቸው

በነገራችን ላይ ለውጥ የግለሰብም ሆነ የማኅበረሰብ ቅመም ነው፡፡ ለውጡ ልባዊ እስከሆነ ድረስ ማንም መቼም ይለወጥ ተቀባይነት ሊያጣ አይገባም፡፡ እናስታውስ – ሣዖል ክርስቶስን አሳዳጅ ነበር፡፡ ተለወጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሆኖም በአዲሱ ስሙና ማንነቱ ለክርስቶስ ሲል ሕይወቱን ሰዋ፡፡ የአስቆረቱ ይሁዳ የክርስቶስ ታማኝና የግምጃ ቤት ኃላፊም ነበር፡፡ ተለወጠ፡፡ ከአሉታዊ ለውጡም በኋላ ላልበላው 30 አላድ ክርስቶስን በመሳም አሳልፎ ሸጠው፡፡ መለስ ዜናዊም ላልበላው የቢሊዮኖች ዶላርና ላላደመቀው አምባገነናዊ ሥልጣን ወላጅ እናቱን ኢትዮጵያን እንደይሁዳ ክዶ መቀመቅ ከቷት ሞተ፡፡ አቤል ለፈጣሪው በሚቀርበው ንጹሕና የተመረጠ መስዋዕት የቀናው ወንድሙ ቃየል የገዛ ወንድሙን ገደለና የመጀመሪያውን ሞት ገለጠ፤ ትግሬ ወያኔዎችም በሆነ ነገሩ የቀኑበትን ወንድማቸውን አማራን ከምድረ ገጽ ሊያጠፉት ቆርጠው ተነሱ፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ መነሳቱ አዲስ አይደለም፤ ከዱሮ ጀምሮ  የነበረ ነው፡፡ የኛ ብሶ የተገኘው ወንድሞቻችን ትግሬዎች እሳቱ ለማይበርድ ሠይፉ ለማይዶለዱም የመከራ ሕይወት ዳርገውን ብዙ ዐሠርት ዓመታት መንጎዳቸውና ይህም በታሪክ ትልቁ የጄኖሳይድ ዕልቂት ሆኖ መገኘቱ ነው – በኔ ግንዛቤ መሠረት፡፡…

ሰዎች ወደ አእምሯቸው በተመለሱ ጊዜ ሁሉ ጎራ ቢቀይሩ ብዙም ልንፈርድባቸው አይገባም፡፡ የዘገዬ ለውጥ መኖር የለበትም ብዬ አላምንም፤ የመሸበት ምሕረትም እንዲሁ፡፡ ለውጡ ከአንጀት እስከሆነ ድረስ የጊዜ ገደብ ባይጣል ይመረጣል፡፡ እርግጥ ነው “በዚያኛው ጎራ የልቡን ካደረሰ በኋላ ለሌላ ተልእኮ/ዓላማ ወይም ለግል ጥቅም ሲል ወደዚህኛው ጎራ ዞረ” የሚል አስተያየት ሊሰነዘር  ይችላል፡፡ ይህ አስተያየት ውኃ አያነሳም ማለትም የምንችል አይመስለኝም፡፡ ቢሆንም የሰዎችን ለውጥ ማጣራት፣ መፈተንና መመርመር ተገቢ መሆኑን ተገንዝበን ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል እንጂ በደፈናው ጎራ ቀያሪዎችን መኮነንና መንገድ መዝጋት ሌሎችን ተስፋ ያስቆርጥና ትግልን ሊያበላሽ/ሊያጓትት ይችላል፡፡ የሰዎች ተፈጥሮ ከባድ መሆኑንና እንደነእንቶኔ በየኹነቶች እንደ እስስት እየተለዋወጡ በጮሌ አንደበታቸው ሰውን የሚያፈዙ መኖራቸውን መርሳት አይገባም – እንደነአባ መላ ለማለት ስላልፈለግሁ ነውና ይቅርታችሁን፡፡

እንግዲህ በከንቱ አንወቃቀስ፡፡ ያለፈው አለፈ፡፡ ካለፈው ግን እንማር፡፡ ወደ ልባችን እንመለስ፡፡ ወደኅሊናችን እንምጣ፡፡ የደም ጭቃ ውስጥ እየዳከርን መኖሩ ይብቃን፤ ይሰልችንም፡፡  አባዱላ ትናንት አንድን ዜጋ በአማራነቱ ብቻ በሽጉጥ ይገድል እንደነበር ሰምተናል፡፡ ዛሬ ግን ያ ሥራው ፀፅቶት ከተመለሰና መመለሱም እውነተኛ ከሆነ በዚህኛው ጎራ ሊቀበለውና ሊያስታምመው የሚገባ ወገን መኖር አለበት፡፡ ከብአዴኖች ውስጥም ቀዳዳ በር እየፈለጉ የሚገኙ የገዛ ኅሊናቸው እስረኞች ይኖራሉና መንገድ እንዳናጠብባቸውና ባሉበት እንዳይቀሩ ምክንያት/እንቅፋት ከመሆን መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ መጪው ጊዜ ምርቱ ከግርዱ፣ ስንዴው ከእንክርዳዱ፣ ገለባው ከፍሬው የሚለይበት ይመስለኛልና ከመበቃቀልና ከመወነጃጀል ተቆጥበን ለአወንታዊ ስኬት መጣደፍ ይገባናል፡፡ ጊዜ የለንም፡፡ ጊዜያችንን ወያ እምሽክ አድርጎ በልቶ ጨርሶታል፡፡ ስለዚህም እንኳንስ ለመጣላትና ለመቦጫጨቅ ለመፋቀርም ያለን ጊዜ አነስተኛ ነውና ወደመተዛዘኑና ወደመተሳሰቡ በቀጥታ እናምራ፡፡ ሁላችንም ከተቀፈደድንበት የግል ዓለም ወጥተን መሀል መንገድ ሊያገናኘን በሚችል ሥልት ላይ መሥራት ይገባናል፡፡ ተንኮልና ምቀኝነት አያሳድጉም – ያጫጫሉ፤ ያቀጭጫሉ፡፡ እንጠየፋቸው፡፡

ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የላትም – አሁን በዓለም ልትታወቅበት የሚገባት ኦፊሻል ሕዝባዊ ባንዴራ ማለቴ ነው፡፡ አሁን ያለው ባለ አምባሻው ባንዴራ የማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ሕዝቡ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የቆረበው ኢትዮጵያ ዱሮ በምትታወቅብት የአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ንጹሕ ባንዴራ/ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው የቁጩው(በልጆች ቋንቋ ‹የፉጌው‹) ወያኔ የፈበረከልን ባንዴራ እንጂ ሀገሪቱንና ሕዝቡን የሚወክል እንዳልሆነ በተለይ በመላው ዓለም በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚያውለበልቧቸው የግድግዳ ላይና የእጅ ባንዴራዎች በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ግን በግዳችን እየቀፈፈንም ቢሆን የወያኔን ባንዴራ ለማውብለብ እንገደዳለን፡፡ የዱሮውን ስታውለበልብ ብትገኝ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት እስራት ይፈረድብህና ዘብጥያ ትወርዳለህ፡፡ በሌሎች ሀገራት አንድ ዜጋ ከፈለገ ባንዴራውን ማቃጠልም ይችላል፡፡ እኛ ጋ ግን ይቺም መብት ሆና ያሻንን ሰንደቅ ዓላማ መያዝ እንኳን አንችልም – አንድን ነገር ደግሞ በግድ ሰው እንዲወድልህ ማድረግ አትችልም  – ፈረንጆች እንዲህ ይላሉ – A man can take a horse to a river, but twenty can’t make it drink. እውነት ነው፡፡ ከህዝብ ጋር እልህ የተጋባ የወንበዴ መንግሥት እስካለ ድረስ  አንተ የምትፈልገውን ሳይሆን እማትፈልገውን ነገር እየፈለገ ይጭንብህና ናላህን ያዞረዋል፡፡ ነገረ ሥራው ሁሉ ከሕዝብ እምነትና ስሜት ተቃራኒ ነው – እንደዚያች ገልቱ ሚስት፡፡ እንግዳ እቤታቸው ሲመጣ ባል ሆዬ እንዲህ ይላታል –  “እኔና እንግዳው እቆጡ ላይ፣ አንቺና ልጆችሽ እመደቡ ላይ እንተኛለን”፡ እርሷ ደግሞ ነገረ ሥራዋ ሁሉ እንደወያኔ የተገላቢጦሽ ነውና “አይ፣ አንተና ልጆችህ እቆጡ ላይ ፤ እኔና እንግዶ እመደቡ ላይ ነው እምንተኛ” ትለዋለች፡፡ … ያቺን ሴት ጎርፍ ይወስዳታል አሉ፡፡ ባልና ጎረቤት ለፍለጋ ሲሄዱ በሴትዮዋ የተገላቢጦሽ ድርጊት አንጀቱ የነፈረው ባል “ወንድሞቼ፣ ይቺን ሴት የምንፈልጋት ከወንዙ ወደታች ሳይሆን ከወንዙ ወደላይ ነው፤ ምክንያቱም ሥራዋ ሁሉ ግራ ስለሆነ እርሷ ወደላይ እንጂ ወደታች አትሄድም፡፡” ወያኔዋ ሚስት በባሏ ጥያቄ መሠረት ወደላይ ተፈልጋ  ትገኝ አትገኝ አላውቅም፡፡ የሚገርመው ግን ወያኔ ከህጎች ሁሉ በተቃርኖ እንደቆመ 30 ዓመታትን ሊደፍን መቃረቡ ነው፤ በጣም ዕድለኞች መሆን አለባቸው – በዚህ መልክ በታሪክ መዝገብ መስፈርና በመጪ ትውልዶች ዘንድ ለሕጻናት ማስፈራሪያነት መብቃት ዕድለኛ ካስባለ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሀገርና ወገን አድን ክተት ጥሪ ክፍል ፭ - ቅድመ ምርጫ የኢትዮጵያ መንግስት አዋላጅ ካውንስል ስለመመስረት- ከአባዊርቱ

ዛሬ ጧት ወደ ሥራ ስገባ ፌዴራል ፖሊስ ተብዬዎቹን ስመለከት አዘንኩላቸው፡፡ በከተማዋ ተሰራጭተው ያን የኢትዮጵያን ጥንታዊ ባንዴራና  የዲያብሎስን ዓርማ አዳቅሎ የያዘ እራፊ ጨርቅ በየደረታቸው ሸጉጠው ሲሄዱ ሳይ ከልብ አሳዘኑኝ፤ (ይሄ አንድ እንጀራ ለካንስ ይህን ያህል መጥፎ ነው)፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ በባንዴራው እንደማያምኑበትና እንደሚጠየፉት ከአኳኋናቸው ተረድቻለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ከኋላቸው ነው እንደዋዛ ሻጥ ያደረጉት፡፡ አንዳንዶቹ ግማሽ በግማሽ ከቀበቷቸው በታች ወደ ሰውነታቸው አስገብተውት ላመል ያህል ብቻ ነው የሚታየው፡፡ ልብ ብሎ ላስተዋለ በርካታዎቹ ይህን ጨርቅ እንደሚጠሉት በሚገባ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ራሳቸው ሕወሓቶችም የሚወዱት አይመስለኝም፡፡ ባለቤት የሌለው ባንዴራ ሲውለበለብ የምታየው እንደታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ውስጥ ነው፡፡ ሀገሪቱም ባንዴራውም ባለቤት የላቸውም፡፡ አላፊ መንገደኛ የሚጫወትባት ነው የምትመስልህ- ኢትዮጵያ፡፡ “ሀገር ሲያረጅ” ጃርት ብቻ ሣይሆን “ ወያኔም ያፈራል” ማለት ይቻላል፡፡ ሀገር ያለ መንግሥት፣ ሕዝብ ያለ መሪ የሚኖሩባት አስገራሚ ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያ፡፡ እንደዜጋ ብታብጥ ብትፈነዳ የኔ ነው የሚልህ አካል የለም፡፡ በገዛ ሀገርህ የባይተዋርነቱ ስሜት ሊያሳብድህ ይችላል፡፡ የምትንሰፈሰፍላት እናትህ በባዕዳን እጅ ገብታ በየቀኑ ስትደፈር ስታይና አንተ ደግሞ እርሷን ለማዳን ምንም አቅም እንደሌለህ ስትረዳ ያኔ የሥነ ልቦናው ቀውስ ቅስምህን ይሰብረዋል –  እንኳንስ ተሰደድክ አንተስ፡፡

ይህን ባንዴራ ሕዝብ ቢወደው ኖሮ እንደሚከተለው አይሆንም ነበር፡-  በብዙ መሥሪያ ቤቶች ይህ ጨርቅ እንደተሰቀለ ውሎ እንደተሰቀለ ያድራል፡፡ የባንዴራ መስቀልና ማውረድ ሥነ ሥርዓት ከ1983ዓ.ም ወዲህ ቀርቷል፡፡ የወያኔ ባንዴራ እየተሰቀለ ሰዎች እያደረጉት ያለውን ነገር አያቋርጡም – ተነስተው በተጠንቀቅ ክብር ሊሰጡት ይቅርና፡፡ ሲሰቀልም ሆነ ሲወርድ ሰቃዩና አውራጁ ትዝ ባለው ሰዓት እንጂ በደንቡ መሠረት ሰዓቱን ጠብቆ አይደለም – ከጓደኛው ጋር ወሬውን እየጠረቀ ባንዴራ የሚያወርድም ሞልቷል – ጉድ ነው፡፡ በየፖሊስ ጣቢያውና በየቀበሌው ያለው ባንዴራ ከባንዴራነት ይልቅ አንድ ዓይነት ቀለም ወዳለው ብጭቅጫቂ ጨርቅነት ተለውጧል – በፀሐይ ምክንያት ቀለሙ ለቅቆና ነታትቦ፡፡ ብዙው ባንዴራ ተቀዳዶ አንዱ ባንዴራ ራሱ ተሰነጣጥቆ ከፊሉ ወደ ምሥራቅ ከፊሉ ወደምዕራብ ሲውልበለብ ለሚመለከት ሀገሪቱ ለይቶላት የጠፋች ያህል ሊሰማው ይችላል፡፡ ልብ አድርግ – ለምሣሌ በአንድ የኮሚቴ አባላት ምርጫ ሂደት ላይ ዕጩዎች ተጠቆሙ እንበል፡፡ ከተጠቋሚ ዕጩዎች መሀል አንደኛውን ዕጩ ሊመርጠው እጁን የሚያወጣ አንድም ሰው እንኳን ካጣ የአካሄድ ስህተት ወይም የግንዛቤ ችግር  አለ ማለት ነው፡፡ ያ ተጠቋሚ ቢያንስ አንድ ሰው ሊደግፈው ይገባል – የጠቆመው ሰው፡፡ የወያኔ ባንዴራም ሌላው ቢጠላው ቢያንስ እነሱ ሊደግፉትና የጠቃቀስኳቸውን ከመሰለ ውርደት ሊታደጉት በተገባ ነበር፡፡ ለዚህም ነው እንግዲህ ወያኔ ራሱ የማይወደውንና የማይቀበለውን  ባንዴራ ሕዝብ ላይ በግዴታ ይጭናል የምንለው፡፡ ዕንቆቅልሽ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በእውነቱ ኢትዮጵያ መንግሥት አላትን? አማራውስ አሁን ምን ማድረግ አለበት?

በትግራይ ግን ሕዝቡም ሆነ ካድሬው የሕወሓትን ባንዴራ ተንከባክበው ሲይዙ ነው የምናይ – በቲቪ እንደምናየው ማለቴ እንጂ እውነቱ ከዚህ የተለዬም ሊሆን እንደሚችል ቢያንስ መጠራጠር ለሚፈልግ የመጠርጠር መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ በየትኛውም ክልል በማይስተዋል ሁኔታ የወያኔ የትግራይ ክልል ባንዴራ በትግራይ ትከበራለች፡፡ በሌሎቻችን ዘንድ ብዙም ሊለመድ ባልቻለው ኦሮሚያ በሚባለው የሀገራችን ክፍል ግን ከማንኛውም ባንዴራ ይልቅ የኦነግ ባንዴራ እንደሚውለበለብና በአንጻራዊነት የበለጠ ተቀባይነት እንዳለው በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብዙ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ወያኔና አባቶቹ የዘረጉልንን ወጥመድ አንድዬ ይበጣጥስልን እንጂ ዕዳችን ብዙና በቀላሉ የማንወጣው ይመስለኛል፡፡ ለአንዲት የበሬ ግምባር ለማታህል ሀገር 30 ባንዴራ የፈጠረልን ወያኔና ጌቶቹ ምድር አትቅለላቸው፤ ነፍሳቸውም አትማር፡፡ በምድር የሰዎችን ስቃይ የሚያበዛ አካል በሰማይ የርሱ ሰቆቃ እንደሚበዛ ሳይታለም የተፈታ ነውና የእምዬ ኢትዮጵያን የመቃብር ጉድጓድ የቆፈረና ያስቆፈረ ሁሉ ዘላለማዊ እሳት የመጨረሻ ዕጣ ክፍሉ ይሁን፡፡

እኔ ብዙውን ዕድሜየን በአማርኛ ተናጋሪዎች አካባቢ አሳልፌያለሁ፡፡ ስለሆነም የአማሮች የሆነ ነገር የኔም የሆነ ያህል ቢሰማኝ ከወቅቱ የጎሣ ፖለቲካ ቅኝት አኳያ ብዙም አይፈረድብኝም፡፡ ከዚህ አኳያ ወያኔ ለአማሮች የጠፈጠፈላቸውን ባንዴራ ስመለከት የሚሰማኝ አንዳችም ነገር እንደሌለ የምገልጽላችሁ ባንዴራ ሲባል ማንም እየተነሳ በቤተ ሙከራ የሚፈጥረው የሸቀጥ ዕቃ ሳይሆን በዘመናት የደምና የአጥንት ማኅበረሰብኣዊ ሽመና አማካይነት የሚፈጠር  ቋሚ  የታሪክ አሻራ መሆኑን በመጠቆም ጭምር ነው፡፡ በየዓመቱ ባንዲራ የሚፈጥር ኅብረተሰብ ካለ ንፋስ በነፈሰ ቁጥር አቅጣጫ እየቀያየረ እንደሚወዛወዝ ዛፍ ሆኗል ማለት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሰሜን እነራስአሉላና አፄ ዮሐንስ እንዲሁም እነአፄ ቴዎድሮስና ዘራይ ደረስ፣ ከደቡብ እነኮሎኔል አብዲሣ አጋና እነ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ከምሥራቅ እነራስ መኮንንና ልጃቸው አፄ ኃ/ሥላሤ፣ ከምዕራብ እነበላይ ዘለቀና ሌሎችም ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች የተዋደቁላትና የሞቱላት ግሩም ሰንደቅ ዓላማ አለችን – ደባደቦ የሌለባት ንጹሕ  አረንጓዴ ቢጫና ቀይ፡፡… ዛሬ ወያኔ መጥቶ ታሪክን ልቀይር ቢል አይሆንለትም፤ ብዙ ሞክሮም አልተሣካም፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ እንደማያገኘው ያውቀዋል፤ “ዓለም አቀፉ”ን ማኅበረሰብ ያታለለ እየመሰለው ግን ብዙ ያልተዋጡለት ድራማዎችን አከናውኗል፤ እያከናወነም ይገኛል፡፡ ለምሣሌ ሚያዚያ 29 97 በዕለተ ቅዳሜ የሠራው ድራማ በማግሥቱ ሚያዝያ 30 በአኩሪ ሁኔታ ተሽሮበታል፡፡ አንዲት ሴተኛ አዳሪ ከመጣው ሁሉ የምትተኛውና የምትገለፍጠው አፍቅራው ወይም ወዳው እንዳልሆነ ሁሉ በወያኔ አነስተኛና ጥቃቅን የእንጀራ ገመድ የታሰረ ወጣት ሁሉ የንብ ካኔቴራ ቢለብስና የሣጥናኤልን ባንዴራ ቢያውለበልብ ወያኔን እውነት እንዳይመስለው – ለነገሩ እነሱ እውነቱን ስለሚያውቁት አይሸወዱም – አዳሜ ለሆዱና ለጥቅሙ እንደሚጎናበስ ያውቃሉ፡፡ ዋናው ለታይታም ቢሆን ግብረ በላው ሁሉ ግር ብሎ በሚዲያ መታየቱ ነው፡፡ መለስ ሲሞት  በማስመሰል ወደር የማይገኝልን እኛ በዓለም አንደኛ የሆነ ልቅሶ አሳይተናል፡፡ ስንገርም! ቀን ሲለወጥ ደግሞ ለለውጡ  የትናንት አሽቃባጮች የነገውንም ሥርዓት አዋላጆችና ዋና አቀንቃኞች ሆነን ግልብጥ እንላለን፡፡

ለማንኛውም ወያኔ ራሱ የማያከብረውን ሰንደቅ ዓላማ ሌሎች እንዲያከብሩለት መጠበቅ የለበትም፡፡  ለነገሩ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ወያኔ ማለት ልብ አድርቅ ነውና የሚያደርገው ሁሉ የሰውን ስሜት እንደማይገዛም እያወቀ “ሞኝ እንዴት ያሸንፋል” ቢባል “እምቢ ብሎ” እንደሚባለው በከንቱ ያደርቀናል፡፡ ለዚህና ለመሳሰለው ፕሮፓጋንዳውና ለምርጫ ትያትሩ በየጊዜው የሚገፈግፈው የሀገር ሀብትና ንብረት በሙስና ከሚያግበሰብሱት ገንዘብ ጋር ተደማምሮ ሲታይ ደግሞ በቁጭት ላይ ቁጭት የሚደርብ ትልቅ ሀገራዊ በደል ነው፡፡ ይህች ሀገር ምን ያህል እንደተረገመች በቅጡ የምንረዳው ይሄ የወያኔ ሥርዓት ዛሬም ይሁን ነገ ተወግዶ የሕዝብ መንግሥት ሲቆም ነው፡፡ ለዚያ ያብቃን፡፡ ጸሐፊዎችና ታሪክ መዝጋቢዎችም የሚረሳ ነገር እንዳይኖር ተግታችሁ ክተቡልን፡፡ ከየዘርፉ የነበሩን ሁነኛ ሰዎች እያለቁብን ቢሆንም ፈጣሪ ሳይደግስ አይጣላምና ውጅምጅሙ እስኪያልፍ በየስርጓጉጡ ተደብቃችሁ ያላችሁ ሀገር ወዳዶች ሳትሰለቹ ይህን ግም ዘመን በምትችሉት ሁሉ ቀርፃችሁ አቆዩልን፡፡ ድረገፆችም እንዲሁ አሁን የሚባለውንና የሚጻፈውን ስንክሳርን የሚያስንቅ ሀገራዊ ታሪክ እየሰበሰባችሁ በታሪክ ማኅደር አስቀምጡ፡፡ ለገዳይ ልብን ይስጥልን፤ ለሟች መንግሥተ ሰማይን ያውርስልን፤ አሜን፡፡

Share