የተቃዋሚ ጎራዉ የወያኔ መዉደቂያ ደረሰ የሚለዉ ወቅታዊ አጀንዳ መሰረቱ ምን ይሆን?

ሸንቁጥ አየለ
——————–

ይሄን ያህል ጀነራል: ይሄን ያህል ልብስ አልባሽ: ይሄን ያህል ሹም ከዳ እናም ወያኔ ሊወድቅ ነዉ እያለ ወቅታዊ አጀንዳዉን ያራግበዋል::ጥያቄዉ ከማን ወገን ነዉ የከዳዉ::ሀያ ስድስት አመታት ሙሉ ከወያኔ/ህዉሃት/ፓርቲ ወይም ጀነራሎች ዉስጥ አንድም ሀይል ከድቶ አያዉቅም::የወያኔ የስልጣን ነብስ: ልብ: አዕምሮ እና ስሜቱ ደግሞ ህዉሃት እና ህዉሃት ብቻ ነዉ:: ለበርካታ አመታት እንቶኔ ከዳ : እንቶኔ ለቀቀ ሲባል የህዉሃት ጀነራሎች ዉስኪያቸዉን እያንጫለጡ ይስቃሉ::የህዉሃት ፖለቲከኞችም የተቃዋሚዉ ሚዲያ የሚያርገበግባቸዉ ሚስጥር የሚመስሉ ነገሮችን አዉቀ ይለቃሉ::

ህዝብም ይሄንን የተቃዋሚ ሚዲያ ትንታኔ ተከትሎ እንዲህ ይላል::”ደረግም : ሀይለስላሴም ሊወድቁ ሲሉ እንዲህ በርካታ ባለስልጣኖቻቸዉ ይከዷቸዉ ነበር::እናም የወያኔ መዉደቂያዉ ደርሷል” እያለ ይተነብያል::ሆኖም በስሜት የሚግለበለበዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ለህዝቡ የማይነግሩት እና እራሳቸዉ ተቃዋሚዎችም የማያስተዉሉት ጥብቅ እዉነታ የወያኔ እና የቀደሙት የመንግስታት ስርዓት መሰረታዊ ልዩነት እጅግ ጥልቅ እና ዋናዉ የነገሮች ማጠንጠኛዉ መሆኑን ነዉ::

ከሀይለ ስላሌ ሚኒስቴሮች ዉስጥ አንድ ሚኒስቴር ቢከዳ ወይም ከደርግ ጀነራሎች ዉስጥ አንድ ጀነራል ቢከዳ አጠቃላይ የመንግስታቱን ስርዓት የመናጥ ጉልበቱ ከፍተኛ የሆነበት ዋናዉ ምክያት አንድ ወጥ የመንግስት ስርዓት በሀገሪቱ ስላለ ነበር:: የስርዓቱ ሚስጥራት: ሰነዶች : እንዲሁም ስትራቴጅዎች በአንድ ቋት ዉስጥ ስለነበሩ አንድ ቦታ የስርዓቱ ጆንያ ተቀደደ ማለት አጠቃላይ ስርዓቱ ማፍሰስ እና መቦርቦር ይጀምራል ማለት ነዉ::

የወያኔ ስርዓት ግን ከዚህ ፈጽሞ በጅጉ የተለዬ ነዉ::ለምሳሌ ወያኔ ኦፒዲኦም ሆነ ሙታኑ ብአዴን በአንድ ቀን ቢፈርሱ ምንም አይሆንም::ስልጣን በወያኔ ሰራዊት እና ደህንነት እጅ ናትና ሌላዉ ቀርቶ አለምን ለማታለያነት እና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለማላገጫነት ያዋቀረዉ ፓርላማ ቢፈርስም ወያኔ ቀጥ ብሎ በሽፍታ ስርዓስት ሀገሩን ይመራዋል:: ወያኔ የተለዬ ስርዓት ነዉና በተለመደዉ የመንግስት አወቃቀር ስልት ወያኔን ሊተነትኑት የሚሞክሩ ተቃዋሚዎችን እና ተንታኞችን ሁሌም እንዳታለላቸዉ እና እንደሸወዳቸዉ ነዉ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕወኃት - ጨዋታው እያበቃ ነው!!! Game Over!!  የሕወኃት መፍረክረክ የቅርብ ጊዜ ምልክቶች፣ መንስኤዎችና አንደምታዎች
Share