October 12, 2017
62 mins read

ወዴት እየሄድን ነው? ከባይሳ ዋቅ-ወያ (ለውይይት መነሻ) – ባይሳ ዋቅ-ወያ

ሰሞኑን ካገር ቤት የሚደርሰው ዜና እንደሁ “ያለ ወትሮው” ቸር ወሬ ላለመሆን የወሰነ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት ሁለት ጄኔራሎች ከዱ ብለውን ”በመገረም“ ላይ እያለን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አጅቦ ለተመድ ስብሰባ ወደ ኒውዮርክ ሄዶ የነበረው ታዋቂው የልፍኝ አስከልካይ አሜሪካን አገር ጥገኝነት ጠየቀ ሲሉን “ዕጢያችን ዱብ ብሎ” ነበር። ዛሬ ደግሞ ማምሻው ላይ አቶ አባዱላ ገመዳ የአፈጉባዔነት ሥልጣናቸውን ለቀቁ የሚል ዜና ተደምሮበት “የባሰውኑ ሃሳብ ውስጥ ከተተኝ”። ታድያ እነዚህን ከያቅጣጫው የሚጎርፉትን “አስደንጋጭ ወሬዎች” ከሰማሁ ባኋላ፣ ባገሪቷ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነው? ወዴትስ እየሄድን ነው ያለነው? ስለአካሄዳችንስ ላንዳፍታ ቆም ብለን አሰላስለን እንደ አንድ ዜጋ መውሰድ ያለብንን እርምጃ ለይተን አውቀነዋል ወይ? የሚል አንዳች ነገር በአዕምሮዬ ውስጥ እየተመላለሰ ዕረፍት ስለነሳኝ በዚህ ጽሁፌ አማካኝነት ከናንተ ጋር ብወያይበት ይሻላል የሚል ሃሳብ መጣልኝና፣ ጭር ባለ ሌሊት ከኮምፒውተሬ ጋር እንካ ስላንቲያ ጀመርኩ። ደግነቱ ያለሁበት አህጉር የሰው ልጅ የማሰብና የመጻፍ መብት በደንብ የተጠበቀበትና፣ የወያኔ ሰላዮች ተከታለው ይህንን ጽሁፌን “የፀረ ሽብርተኝነትን ዓዋጅ” ለመጣሴ እንደመረጃ ቆጥረው ዘብጥያ እንደማያወርዱኝ ስለማውቅ ለጊዜው የሚፈታተኑኝን ድካምና ዕንቅልፍ አሸንፌ የሃሳቦቼን ቅርጫት “እንደወረደ” አቅርቤላችኋለሁና በቀና መንፈስ ተረከቡኝ። በተፈጥሮዬ የጨለምተኝነት ባህርይ ባይኖርብኝም፣ የዕድሜ ጉዳይ ይሁን ወይም ከሙያዬ ጋር ተያይዞ ባካበትኩት ልምድ ምክንያት እንደሆን አላውቅም እንጂ፣ ዛሬ አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታና ወዴት እየተጓዝን ነውየሚለውን ባሰብኩና ራሴን በጠየቅኩ ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ የሚታየኝ “ጎደሎ” እንጂ “ሙላት” ስላይደለ አሳስቦኛል። ትክክለኛ አይደለሁም ብዬ ራሴን ግን አልኮንንም። ያባት የናቴና የዘር ማንዘረ ትውልድ ምድር ስለሆነና እኔም ተወልጄ ያደግኩባት፣ አያቶቼና ቅድም አያቶቼ ደማቸውንና አጥንታቸውን ከስክሰውባት ያኖሯት አገሬ ስለሆነች፣ የህዝቦቿ የቀን ተቀን ኑሮና የወደፊት ዕድላቸው ቢያሳስበኝና ብቆረቆር ተፈጥሮአዊ ባህርይ በመሆኑ አያስገርምም ብዬ ከኅሊናዬ ጋር ላለመወቃቀስ ተስማምተናል።

በዚች ሰዓት ያሳሰበኝ የአባዱላ ሥልጣን መልቀቅ አይደለም። አባዱላ ቢሄድ በሌላ አባዱላ እንደሚታካ አውቃለሁና። ደግሞ የአባዱላ የአፈ ጉባዔነት የሥልጣን ወንበር ላገሪቷ ህዝብ አንዳችም ጥቅም የማይሰጥ በመሆኑ፣ እንኳን ሰውዬውን ይቅርና ወንበሩን ራሱን ከዚያ ቢያነሱት አሁን ከፊታችን ለተገተረው አገራዊ ችግራችን መፍትሄም መንስዔም አይሆንም ባይ ነኝ። እኔን ያሳሰበኝ አባዱላ ለዘመናት የተንሰራፋበትን የሥልጣን ወንበር እንዲለቅ ያስገደደውን ያገሪቷን አጠቃላይ ፖሊቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ አጥንተን፣ እንደ አንድ የነቃ የህብረተሰብ ክፍል ማድረግ ያለብን ምንድነው ብለን ተወያይተን አንዳች ገንቢ ሃሳብ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል ወይ የሚለው ነው። እስቲ ዘርዘር ላድርገው።

 

ወያኔ ሥልጣን ላይ ከወጣ ወዲህ አገሪቷ ያስተናገደቻቸውን የትየሌለ ቀውሶች ወደ ዳር አድርገን፣ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ያገሪቷ ክፍሎች ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ሲቀጣጠል የነበረውን ፖሊቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ በአንክሮ ብንመለከት፣ የምንገነዘበው አንድ ነገር ቢኖር፣ አገሪቷ እየተጓዘችበት ያለው ጎዳና ወደ ጥፋት እንጂ ወደ ልማት የማያመራ መሆኑን ነው። ያገሪቷ ህዝቦች በወያኔ ያገዛዝ ሥርዓት የሚወርድባቸውን የግፍ ዶፍ መሸከም አቅቶአቸው ከያሉበት ያለአንዳች የተማከለ አመራር በየአደባባዩ እየወጡ ስሞታቸውን ያለማቋረጥ ለማሰማት ቢሞክሩም፣ ያገኙት መልስ በጥይት መቆላት ወይም ታስሮ መገረፍን ነበር። አመራሩ የህዝቡን ብሶትና ቅሬታ ሰምቶ በበጎ እንደማስተናገድ፣ የመለሰላቸው “የሚበጅህን እኔ አውቅልሃለሁና አርፈህ ተገዛ” በሚል ዕብሪትና ድንቁርና የተሞላበት መልስ በመሆኑ፣ በህዝብና መንግሥት መካከል መኖርና

መከበር የነበረበት ማህበራዊ ውል (social contract) ተሽሮ፣ ዲን ዳንኤል እንዳለው “ህዝብን የማያዳምጥ መንግሥትና፣ መንግሥትን የማይሰማ ህዝብ” ሆነን አረፍን።

 

አንድ በጣም እያሳሰበኝ ያለው ጉዳይ የኛ በዲያስፖራ ያለነው፣ ከህዝቡ ምንም ዓይነት የውክልና ሰነድ ሳይኖረን፣ ህዝቦቹን “በመወከል” ላገሪቷ የሚበጃት የአስተዳደር ሥርዓት ይሄኛው ነው፣ አሃዳዊ እንጂ ፌዴራላዊ ሥርዓት አገሪቷን ለመከፋፈል ይዳርጋታል፣ ወዘተ እያልን ያልተቃኘ በገና ስንመታ የምንውለው ነው። በመሰረቱ ማንኛውም ሰው የሌሎችን መብት እስካልታጋፋ ድረስ የፈለገውን አስተያየት ለመሰንዘር ሙሉ መብት አለው። እኔም ይሄው እንደምታዩት መብቴን ተጠቅሜ ሃሳቤን ያለምንም ገደብ እየሰነዘርኩ ነው። ማለት ግን የማልችለውና ለማለትም የማልሞክረው፣ አንድን ህዝብ ወክዬ፣ ለምሳሌ ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ መፍትሄው ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ መኖር ነው ብዬ መናገር የኦሮሞን ህዝብ መብት መንካት ይመስለኛል። እኔ እንደ አንድ ኦሮሞ ግለሰብ ስለኦሮሞ ህዝብ የወደፊት ዕድል ራሴን ወክዬ በራሴ ግምት የሚበጀው መስሎ የሚታየኝን “የብሄር ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፣ ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከተመሰረተ የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ተለይቶ ሌላ አገር የሚፈጥርበት ምክንያት አይታየኝም” የሚል ሃሳብ ለመሰንዘር እችላለሁ። ግን ብቸኛው መፍትሄ ነው ብዬ በርግጠኝነት ለመናገር የማልችለውን ያህል፣ ለየት ያለ መፍትሄ የሚያቀርቡትን ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ደግሞ ትክክል አይደላችሁም ብዬ መኮነን አልችልም። ለማለት የፈለግሁት ከህዝብ ውክልና የተቀበለ አንድም ድርጅት የለም ነው።

 

ከዚህ ጋር ለማያያዝ የምፈልገው፣ ብዙውን ጊዜ በተለይም በኛ ውጭ አገር ባለነው “ፖሊቲከኞች” መካከል፣ ወያኔ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ሥርዓት አድርጎ ከደነገገ ባኋላ ባገሪቷ ላይ ስላንዣበበው የመበታተን አደጋና፣ ይህንንም አደጋ እንዳይከሰት ለማድረግ ብቸኛው መፍትሄ “ድሮ የነበረውን የአንድ አገር፣ አንድ ባንዲራ አሃዳዊ ሥርዓት” መልሶ መተካት ነው ከሚሉት ለየት ያለ ሃሳብ ለማቅረብ ነው። በኔ ግምት ይህ ሃሳብ በምንም መልኩ ዛሬ ለሚስተዋለው ቀውስ መፍትሄ ሊሆን አይችልም ባይ ነኝ። ምክንያቶቼን ላቅርብ።

 

አንደኛ፣ በኔ ግምት አንቀጽ 39 በህገ መንግሥቱ ውስጥ ባይካተት ኖሮ፣ ወያኔ ሥልጣን ላይ በወጣ ሰሞን በነበረው የሥልጣን ክፍተትና ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ይስተዋል በነበረው የመብት ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ የግዛትና የህዝቦቿ አንድነት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይገባ ነበር ባይ ነኝ። ከላይ እንዳልኩትም፣ ይህ አንቀጽ ሥራ ላይ ከዋለ ይሄው ሰላሳ ዓመት ሊሞላው ሆኖ በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን የአንድም ክልል ህዝብ የመገንጠል ጥያቄ አለማቅረቡ፣ አንቀጽ 39 እስከነጉድለቱ፣ የኢትዮጵያን ህዝቦች ተከባብሮ በእኩልነትና በፈቃደኝነት ባንድ ላይ የመኖር ፍላጎትና የግዛት አንድነት ዋስትና ሆኖ በመጠኑም ቢሆን አገልግሏል ባይ ነኝ። ልክ እንደ አንቀጽ 39፣ በ 1992 ዓመተ ምህረት ተሻሽሎ በቀረበው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ ውስጥ አንቀጽ 96 መካተቱ የትዳር ጓደኞችን በተለይም የሚስቶች ባላቸውን ለመፍታት የእኩልነትን መብት ለማስጠበቅ ዋስትና ሰጠ እንጂ፣ የአንቀጹ መካተት በኢትዮጵያ ውስጥ የፈቶችን ቁጥር ከፍ አላደረገም። በነገራችን ላይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው በጉልበት እንጂ አንቀጽ 39ን ተመርኩዛ ስላልሆነ፣ ዛሬም ለኢትዮጵያ የህዝቦችና የግዛት አንድነት ፀር ነው ብዬ የማስበውና የሚያስፈራኝ አንቀጹ ሳይሆን፣ በወያኔ የግፍ አገዛዝ የተንገፈገፈ ያንድ ክልል ህዝብ “በቃኝ አሻፈረኝ” ብሎ አንድ ቀን የመገንጠል ትግል ሊጀምር ይችላል የሚለው ነው።

 

ሁለተኛ፣ ዛሬ አገሪቷ ካላት መቶ ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ወደ ግማሽ የሚጠጋው ትውልድ ዕድሜው ከሰላሳ አምስት ዓመት በታች እንደሆን የተለያዩ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ዕድሜያቸው ከአሥር ዓመት ያንስ ነበር ማለት ነው። ይህ ማለት፣ ዛሬ በመካከለኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ህዝባችን ከሞላ ጎደል የሚያውቀው የኢትዮጵያን አገራዊ አስተዳደር ሥርዓት ወያኔ በተግባር ያዋለው በ “ክልል” የተዋቀረ የፌዴራል ሥርዓትን ነው ማለት ነው። ሳይድላቸው ቀርቶ እንደኔና የዕድሜ እኩዮቼ በንጉሡ ጊዜ ጠቅላይ ግዛትንና አገረ ገዢዎችን፣ በደርግ ዘመን ደግሞ ክፍለ ሃገርንና የኢሰፓ ሃላፊዎችን ሳያዩ ያደጉ ናቸው ማለት ነው። እኛ እንግዲህ በክፉም ሆነ በበጎ፣ ዛሬ ላይ ቆመን ያለፉትን ሁለቱን የቅድመ ወያኔ አገራዊ አስተዳደር ሥርዓትና ወያኔ ያመጣውን ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለማወዳደር ዕድል ሲኖረን፣ ግማሹ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ሊያወዳድር የሚችለው የኢትዮጵያን ፈደራላዊ ሥርዓትን አሉንታዊና አዎንታዊ ጎኖችን ከሌሎች ፌዴራላዊ ሥርዓት ካላቸው አገራት ጋር ማወዳደር እንጂ እንደኛ ወደ ኋላ ተመልሶ የቅድመ ወያኔ ኢትዮጵያ አገራዊ አስተዳደሮችን ሊያይ የሚችልበት መነፅር የለውም ማለት ነው። የማያውቁት አገር አይናፍቅም እንደሚባለው ነው።

የተደቀኑብን አገራዊ ችግሮችና የኛ ሚና፡

 

ችግሮቻችን መጠነ ሰፊ ከመሆናቸው የተነሳ፣ እነሱን ከመዘርዘር ይልቅ ችግር ያልሆኑትን መጥቀሱ ሳይሻል አይቀርም። እነሱ ደግሞ እፍኝም ስለማይሞሉና ሁሉም ስለሚያውቃቸው በዚያ ላይ ጊዜ ማጥፋት አስፈላጊ አይመስለኝም። እስቲ ከችግሮቹ መሃል እጅግ በጣም አንገብጋቢና ለህዝቦቿ አንድነትና ላገሪቷም ህልውና ያሰጋሉ ብዬ ከምገምታቸው ጥቂቶቹን ላካፍላችሁ።

 

አንደኛ፣ ወያኔ ዲያለክቲካዊ ህግን ተከትሎ አንድ ቀን መሞቱ የማይቀር ሃቅ ነው። ተወልዶ ያደገ ሁሉ መሞቱ አይቀሬ ነውና። ግን ይህንን ተፈጥሮአዊ ህግ አልቀበልም ብሎ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም በሚያደርገው ጥረት፣ “አገዛዙን የተቃወመውን ሁሉ “የኢትዮጵያን የግዛትና የህዝቦችን አንድነት” እንደተቃወመ ቆጥሮ በዜጎች ላይ ባወጀው ጦርነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን ገድሎ ወይም አስሮ የቁም ስቃይ እያሳያቸው እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ሃቅ ነው። ይህ አንዱ ችግር ነው።

 

ሁለተኛ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሌላው ችግር፣ ተቃዋሚ የተባለው ሁሉ ባገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር፣ ዓላማው ሁሉ ወያኔን ከሥልጣን ወንበር ላይ ማንሳት እንጂ፣ “ወያኔ እንዴት ይነሳል፣ በማንስ ይተካል” የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ በተማከለ መልኩ ተወያይቶበት ስምምነት ላይ ለመድረስ አንዳችም ሙከራ ሲያደርግ አይታይም። ዛሬ ወያኔ በሆነ ምክንያት ከሥልጣን ቢወርድ፣ የአራት ኪሎው የሥልጣን ወንበር ደግሞ ለሁሉም የተቃዋሚ ቡድን መሪ ስለማይበቃ፣ “እኔ ልቀመጥበት አንተ” በሚለው ንትርክ ሳቢያ ወደ የርስበርስ ጦርነት ልናመራ እንደምንችል ቆም ብለው ያሰቡበት ጉዳይ አይመስለኝም። ይህን የሚያክል ከባድና ቁልፍ የሆነ ጥያቄ ደግሞ አሁን “በሰላሙ ጊዜ” በሰከነ መንፈስ ካልተወያየንበትና መቋጠርያ ካላበጀንለት አራት ኪሎ ከተደረሰ በኋላ ጊዜው በጣም ያጥራል።

 

ሶስተኛ፣ ብዙዎቻችን ጊዜያችንን የምናጠፋው፣ ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ሰላምና ዕርጋታ በሰፈነበት ሁኔታ እኩልነትን መመርያው ባደረገው መድረክ ተገናኝቶ የሚበጀውን ውሳኔ እንዲወስድ ጎዳናውን መጠራረግና ማስተካከል ሳይሆን፣ እንደሁ ደርሶ “ለዚህ ህዝብ የሚበጀው ይሄ ነው፣ የለም ያኛው ነው” እየተባባልን ጠብመንጃ ቀረሽ የቃላት ውጊያ ላይ ነው። ይህ

 

ታሪካዊ ሚናችንን ለይተን ያለማወቅ ጉዳይ፣ አንድም የወያኔን ዕድሜ አራዝሞ የነበቀለ ገርባንና የነአንዱዓለም አራጌን የሥቃይ ዕድሜ ማራዘም ሲሆን፣ በወያኔ መዳከም ምክንያት ማዕከላዊው የፌዴራል መንግሥት እየተዳከመ ሲሄድ የየክልሉ አስተዳደሮች መጠናከር ደግሞ ምን ዓይነት አገራዊ ቀውስ ሊያመጣ እንደሚችል ጠንቅቀን እንዳናውቅ አርጎናል።

 

አራተኛ፣ ባብዛኛው የዲያስፖራው “ፖሊቲከኛና” ባገር ቤትም ያሉት አንዳንድ ተቃዋሚ ነን የሚሉ የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ ተቀዳሚ ተልዕኮአቸው አርገው የሚያስቡት የወቅቱን ያገሪቷን የፖሊቲካና ህብረሰባዊ ቀውስ ሳይሆን፣ ትናንትን እንደዛሬ በመኖር ነው። ከብዙ ምዕት ዓመት በፊት ተፈጽሟል የሚሉትን አወዛጋቢ የሆነ የታሪክ ሰነድ “ከተደበቀበት” ጎልጉሎ በማውጣት አንደኛው ህዝብ ለሌላኛው ዛሬ መክፈል ያለበት የታሪክ ዕዳ አለበት በማለት፣ ወቅታዊ ችግሮችን በቅንነት ተወያይቶ መፍትሄ እንደመፈለግ በሚከፋፍለው ነጥብ ላይ ብቻ ሲያተኩሩ ይስተዋላሉ። ይህ የትም የማያደርስ፣ ግን ደግሞ የችግሮችን ዕድሜ የሚያራዝም ቤንዚን በእሳት ላይ የመጨመር ያህል ነው። ለምሳሌ ባለፉት አራት ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ከዳር እስካዳር ሲያካሄድ በነበረው ዓመጽ ሰበብ ባንዳችም ቦታና ወቅት ኦሮሞ ባልሆኑ ዜጎች ነፍስና ንብረት ላይ አንዳችም እርምጃ አለመወሰዱ እየታወቀ፣ አንዳንድ ጽንፈኛ ኤሊቶች ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ በወያኔ የከፋፍለህ ግዛ መርሃ ግብር መሰረት በአማራ ግለሰቦች ላይ የተፈፀመውን የጉራ ፋርዳና ፉኛን ቢራ ዕልቂትን፣ ወይም ዲዴሳ አካባቢ በሚገኘው የመንግሥት እርሻ አካባቢ ይኖሩ በነበሩት ኦሮሞዎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ በመጥቀስ፣ የዚህን ወይም የዚያን ብሄር ህዝብ መወንጀል፣ መራራቅን እንጂ መቀራረብን እንደማያመጣ መገንዘብ የነበረባቸውና ያለባቸው ይመስለኛል።

 

አምስተኛ፣ አገሪቷ ለሁላችንም እኩል ናት፥ ማንም ከማንም በላይ የራሱ ሊያደርጋትም መሞከር የለበትም። ይህ የእኩልነት መብት በደንብ ያልገባቸው አንዳንድ ጽንፈኛ ኤሊቶች፣ ራሳቸውን ለኢትዮጵያ የግዛትና የህዝቦች አንድነት ዋስም ጠበቃም የሆኑ አድርገው ከልካቸው በላይ የተሰፋውን ባርኖስ ለብሰው በየአደባባዩ እየታዩ መስበክ ትክክል እንዳልሆነ ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት እስከሆነች ድረስ ደግሞ፣ አንዱን “መሲህ”፣ ሌላውን ደግሞ “የጠፋው በግ” አስመስሎ ማቅረብና፣ የጨዋታውን ህግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ባንድ ባልተስተካከለ ሜዳ ላይ ተንቀሳቃሽ የግብ እንጨት ተክሎ፣ ዳኛም ተጫዋችም ለመሆን መሞከር፣ መጠራጠርን እንጂ መተማመንን የማያመጣ መሆኑ መታወቅ አለበት ባይ ነኝ።

የኔ ስጋት፣

 

በኔ ግምት የኢትዮጵያ በፌዴራላዊ አስተዳደር ሥር መሆን ለኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት መጠናከርም ሆነ ላገሪቷ የግዛት አንድነት ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም። አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደሚሉት በውነትም ላገሪቷና ለህዝቦቿ ጠንቅ ቢሆን ኖሮ፣ ሥርዓቱ መንግሥታዊ መመርያ ከሆነ ይሄውና ሰላሳ አመት ሊያስቆጥር ጥቂት ዓመታት የቀሩት ሲሆን፣ በፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት በተደነገገው አንቀጽ 39ን ተጠቅሞ ተገንጥሎ የራሱን ነጻ አገር መመስረት ቀርቶ፣ ለመመሥረት እንኳ ጥያቄውን ያቀረበ አንድም ብሄር ወይም ብሄረሰብ የለም። ምክንያቱ በትክክል ባይገባኝም፣ ጥያቄው ብዙውን ጊዜ ተያይዞ የሚቀርበው ከኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥያቄ ጋር ቢሆንም፣ እስከዛሬ ድረስ የኦሮሞ ህዝብ ይህንን ጥያቄ በህገ መንግሥቱ እንደተደነገገው ለህዝቦች ምክር ቤት ያቀረበበት ወይም ሊያቀርብ የሞከረበት ጊዜ አልነበረም። ከዚህ ክስተት የምንረዳው፣ ሀ) የአንቀጽ 39 በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተት የብሄሮችን መገንጠል ወይም ለመገንጠል ሙከራ ማድረግን አላስከተለም፣ ለ) አንቀጹ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩልነት ተባብሮና ተከባብሮ ለመኖር ዋስትና ሰጠ እንጂ ትስስሩን አላዳከመም እላለሁ።

 

ይህ ማለት ግን ጥያቄው አልነበረም ወይም ለወደፊቱ አይመጣም ማለት አይደለም። ታሪክ ደግሞ የራሱን ቦይ ተከትሎ ስለሚሄድ፣ መጪው ጊዜ ምን ሊመስል ይችላል ለሚለው ትክክለኛ መልስ የለኝም። መገመት የምችለው አንድ ነገር ግን፣ ይህ የህዝብ ተወካይ ነን የሚሉት በሁለቱም ወገን ያሉት ጽንፈኞች፣ ሰከን ብለው በመከባበርና በእኩልነት መንፈስ ካልተወያዩና አንድ የጋራ አቋም ካልወሰዱ በስተቀር፣ ብሄሮቹ፣ አንቀጽ 39ን ሳይሆን ጉልበትን ተጠቅመው ልክ ኤርትራ እንዳደረገችው፣ ዛሬ ክልል መሆናቸውን መቀበል ያቃተንን ግዛት ራሱን ወደቻለ “አገር” ቀይረው አንድ ኢትዮጵያ ሳይሆን ዘጠኝ ጎረቤት አገሮች ሆነን እንዳንገኝ ነው። ይህ እንዳይሆን ከላይ እንዳልኩት ፎርማል በሆነ መልኩ ባንድ መድረክ ላይ ተገናኝተን መወያየት አለብን ባይ ነኝ። አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ መሆናችንን መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል።

 

ፌዴራላዊ አስተዳደር፣ ብዙ ብሄሮችን ላቀፈች አገር ፍቱን ሥርዓት የሆነውን ያህል፣ ለዘላለም ግን ህዝቦችን አንድ ላይ ለማኖር ሙሉ በሙሉ ዋስትና አይሰጥም። ሊሰጥም አይችልም። ለነገሩ እንኳን የተለያየ ብሄርና የተለያየ ቋንቋ ያላቸውን ህዝብ ይቅርና አንድ ህዝብ ሆነው አንድ ቋንቋ ያላቸውን ህዝቦች አንድ ላይ ለማኖር ዋስትና የሚሰጥ አስተዳደራዊ ሥርዓት የለም። አባባሌን በሶስት ምሳሌዎች ለዚያውም ራሴ በቅርብ ሆኜ የተከታተልኳቸውን፣ የሶቪዬት ኅብረት፣ የዩጎዝላቪያና የቼኮዝሎቫኪያን ፌዴራላዊ ሥርዓቶችን መፈረካከስ ለአብነት ባቀርብ የበለጠ ትረዱኛላችሁ ብዬ እገምታለሁ። (በቅርቡ የስኮትላንድ ህዝብ ከታላቋ ብሪታኒያና፣ የካታላን ህዝብ ደግሞ ከስፔይን ለመገንጠል ያካሄዱትንና በማካሄድ ላይ ያሉትን ጥያቄ ሁላችሁም እየተከታተላችሁ ስለሆነ እዚህ ማካተቱ አስፈላጊ አልመሰለኝም)።

 

የሶቪዬት ኅብረት ከሰማንያ በላይ የሆኑትንና ባያሌው በዘርም በሃይማኖትም የማይገናኙትን ብሄሮችን በፈደራላዊ አስተዳደር ለሰባ ዓመት ባንድ ላይ አድርጎ፣ የሶሻሊዝምን ዕድገት ደረጃ አጠናቀን አንድ ወጥ የሆነ “የሶቪዬት ዜጋ” ፈጥረን ወደ ኮሙኒስታዊው ሥርዓት ገብተናል ብሎ ለዓለም ካወጀ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ በ1991 ዓመተምህረት ልክ እንደ አሸዋ ካብ ሲናድ አይተናል። አንድ “ሶቪዬታዊ ህዝብ”፣ አንድ ማዕከላዊ መንግሥትና አንድ ፈዴራላዊ ቋንቋ፣ አንድ መከላከያ ሠራዊት፣ አንድ የውጭና ያገር ውስጥ ፖሊሲ የነበረውና ምድራችን ላይ ካሉት ሁለት ኃያላን መንግሥታት አንዷ የነበረችው ጠንካራ አገር፣ ፌዴራላዊው መንግሥት ሁኔታዎችን መቆጣጠርና እንደ በፊቱ መምራት ሲያቅተው፣ 15 ቱም ያገሪቷ ሬፑብሊኮች (እንደኛ ዘጠኙ የክልል መንግሥቶች ማለት ነው) ተለያይተው፣ ሶቪዬት ህብረት አንድ ታላቅ አገር መሆኗ ቀርቶ 15 አገር ሆና አረፈች። አንድ መታወቅ ያለበት ነገርና ለውይይታችንም ይረዳል ብዬ የማስበው ነጥብ፣ የመለያየቱን ውሳኔ የወሰዱት የየአገሬው ህዝቦች ሳይሆን፣ የጠንካራዎቹ ማለትም ሩሲያ፣ ኡክራይና እና ቤሎሩሲያ የፓርቲ መሪዎች ሲሆኑ፣ የተቀሩቱ ስድስት ሬፑብሊኮች ግን (ሶስቱን የባልቲክ ሬፑብሊኮች ግን ሳይጨምር) ሶቪዬት ህብረት እንዳትፈርስ ታግለው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ሳይደግስ አይጣላምና ታላቋ ሶቪዬት ፈርሳ በአስራ አምስት የተለያየ አገር የተተካችው ያለአንዳች ተኩስ ነው።

 

የፌዴራል ዩጎዝላቪያ ፈራርሳ ሰባት አገር መሆን ግን ከሶቪዬት ህብረት መፈራረስ በጣም የተለየ ነበር። ልክ እንደሶቪዬት ህብረቱ፣ ማዕከላዊው (ፌዴራላዊው) መንግሥት እየደከመ መጥቶ አገራዊ ቀውሶችን መቆጣጠር ሲያቅተው፣ ድሮውንም የመገንጠል ህልም የነበራቸውና የፌዴራሉ አካል የሆኑት ሬፑብሊኮች የራሳቸውን ነጻ አገር አወጁ። ባገሪቷ የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የበላይነት የነበራትና ላገሪቷ አንድነት የታሪክ ሃላፊነት አለብኝ ብላ ራሷን ትቆጥር የነበረችዋ የሴርብያ ሬፑብሊክ፣ በተገነጠሉትና ለመገንጠል ባሰቡት የፌዴራሉ አባል ሬፑብሊኮች ላይ ጦርነት አወጀች፣ በዚህ ከአራት ዓመት በላይ በቆየው የርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ነፍስ ከጠፋና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በስፋትም ሆነ በይዘት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የንብረት ጥፋት ከተመዘገበ በኋላ፣ ፌዴራላዊዋ ዩጎዝላቪያ ከስማ በቦታዋ ሌሎች ልዑልናቸውን ባስከበሩ ስድስት አገሮች ተተካች። የተበበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት ቁጥርም በዚያኑ ያህል ከፍ አለ።

 

ሌላዋ ከሶቪዬት ህብረትና ከዩጎዝላቪያ ለየት ባለ መልክ ፈዴራላዊ አስተዳደሯን አፍርሳ ሁለት አገር የሆነችዋ ቼኮዝሎቫክያ ነበረች። የነዚህ በጣም ለየት ያለና በሰላም ለመፋታት የመቻልን ጥበብ ለሌሎች ያስተማረ ነው ብለው የፖሊቲካ ጠበብት ገምግመውታል። ቼኮችና ስሎቫኮች በፓርላማ ደረጃ ተወያይተው ባመቱ መጨረሻ ማለትም ታህሳሥ 31 እኩለ ሌሊት ላይ እንለያያለን ብለው ወሰኑ። አንዲት ጥይት ሳትተኮስ፣ ጥር 1 ቀን ጧት ተነስተው የቼኮዝሎቫኪያን ባንዲራ አውርደው በቦታው ሁለት የተለያየ ባንድራ ሰቅለው ሁለት ጐረቤት አገር መሆናቸውን ለዓለም ህዝብ አሳወቁ። የተባበሩት መንግሥታት ቁጥርም እንደገና በሁለት አባላት ከፍ አለ።

 

የነዚህን ሶስት ፌዴራላዊ አስተዳደር አገሮችን መፍረስና እንዴት እንደፈረሱ ባጭሩ ለማስረዳት የፈለግሁት የሚከተሉትን ትምህርት እናገኝበታለን በሚል መንፈስ ነው። አንደኛ፣ ላገር መፈራረስ መንስዔውም መፍትሄው ምንም አይነት ሂሳባዊ ፎርሙላ የለም፥ እያንዳንዱ አገር የራሱ ልዩ የሆነ የአፈጣጠር ታሪክ ስላለው፣ የአሟሟቱም ሁኔታ እንደዚያው የተለያየ ነው። ሁለተኛ፣ የፌዴራላዊው (ማዕከላዊ) መንግሥት ከደከመና አገራዊ ቀውሶችን መፍታት ካልቻለ፣ የፌዴራሉ አካል የሆኑት (ለምሳሌ የክልል መንግሥቶቻችን) በተለይም የፓርቲና የክልል መሪዎች፣ የአስታራቂነትን ሚና ሊጫወት የሚችልና በየክልሎቹ ህዝቦች ዘንድ ተዓማኒነት ያለው የክልል መንግሥት ከሌለ፣ ፌዴራላዊውን አገር ከመበታተን የሚያድናት አንዳችም ኃይል አይኖርም። ሶስተኛ፣ ላንድ የፌዴራል መንግሥት መበታተን ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ደግሞ ብሄሮቹ (ሰፊው ህዝብ) ሳይሆን ያልተወከሉ፣ ግን ደግሞ ራሳቸውን ተወካይ አድርገው የሚያቀርቡ ከየብሄሩ የተወጣጡ ኤሊቶች ናቸው።

 

በኔ ግምት አገራችን ከምንጊዜው በላይ በጣም በተወሳሰቡ የችግር ክሮች ተወጣጥራለች። የችግሩ ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ወያኔ ቢሆንም፣ ተቃዋሚ ኃይሎችም በተለይም በዲያስፖራው ያሉት፣ በማንዣበብ ላይ ያለውን አደጋ በቅጡ ተረድተው፣ ወያኔን ከሥልጣን ለማስወገድ ከሚለው ውጪ፣ አንዳችም ገንቢ የሆነና አገሪቷን ለማዳን የተወጠነ የጋራ መርሃ ግብር ለማውጣት እንኳን ሊስማሙ ይቅርና የመወያያ መድረክ እንኳ ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ ባለመታየታቸው ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው ባይ ነኝ። ገሚሶቹ፣ ብዙ ምዕተ ዓመታት ወደ ኋላ እየተጓዙ ይሄኛው ብሄር በድሎኛል፣ ያኛው ብሄር መሬቴን ቀምቶኛል እና ሌላ ሌላም በማለት፣ የዛሬውን ችግር ላለመጋፈጥ የማሉ ይመስል፣ ባገር ቤት እየተከሰተ ያለውን አገራዊ ቀውስ ችላ ብለው ዘመናዊውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የድህረ ገጽ ጦርነት ፍልሚያ ላይ ይገኛሉ። ይህ የተቃዋሚ ኃይሎች የሁኔታውን አደገኝነት በቅጡ አለመረዳት ራሱ ታላቁ አደጋ ይመስለኛል።

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ከመሃል እይተዳከመ መምጣቱ ለሁላችንም ግልጽ ነው። የማዕከላዊው መንግሥት መዳከም ደግሞ የሚያስከትለውን መዘዝ ከላይ ባቀረብኳቸው ሶስት ተጨባጭ ምሳሌዎች ለማስረዳት እንደሞከርኩት፣ አሁን ዛሬ በጋራ ሆነን ካልተጋፈጥነው የአደጋው ሰለባ ላለመሆን አንዳችም ዋስትና የለንም። የሶቪዬት ህብረት መፈራረስ የርስ በርስ ጦርነትን ያላስከተለው ከአስራ አምስቶቹ ሬፑብሊኮች መካከል፣ የሩሲያ ሬፑብሊክ ጠንካራዋ በመሆኗና ሁላቸውንም ልታረጋጋ ስለቻለች ነው። የቼክና ስሎቫክም ህዝብ ወደርስበርስ ጦርነት ያላመሩት አንድም፣ ቀደም ብለው በደረሱበት ስምምነት መሰረት

 

ስለሆነና ከዚያም በላይ ደግሞ ሁለቱም ከሞላ ጎደል የተመጣጠነ ኃይል ስለነበራቸው እርስ በርስ ስለ ተከባበሩ ነው። ዩጎዝላቮች ግን ወደ መተላለቅ ደረጃ የተሻገሩት አንዳቸውም ከሌላው የተሻለና ጫና ሊያደርግ የሚችል ኃይል ከመሃላቸው ስላልነበረና የግጭት እሳቱን ለኩሶ በማጋጋል ከዳር ቆሞ የሚሞቋቸው ሌላም የውጭ ሃይል ስለነበረ ነው።

 

ባገራችን ዛሬ የሚስተዋለውን አገራዊ ቀውስ ቁጭ ብዬ ሳገናዝብ፣ የዩጎዝላቪያውን የመፈራረስ ሁኔታ ከፊቴ ድቅን ይልብኛል። ጨለምተኛ መሆኔ ራሴንም እየገረመኝ ቢሆንም፣ ሁኔታውን፣ ያኔ እንድ አንድ ወጣት የተበበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኛ ጦርነቱ ተጀምሮ በድርድር እስከሚያልቅ ድረስ ማለትም አራቱን ዓመት ሙሉ በቦታው ሆኜ፣ አንድ ብሄር፣ አንድ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ ለዘመናት አብሮ በወዳጅነት የኖረ፣ አንዱ ላንዱ ሚዜ የነበሩ፣ ወይም በጋብቻ የተቀላቀለ ህዝብ እንዴት ከመቅጽበት ወደ ጠላትነት እንደተሻገረና እጅግ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ መጋደል፣ በጅምላ ሰውን ከነነፍሱ መቅበር፣ ሴት ልጆችን በጅምላ መድፈር ወዘተ ላይ እንደደረሰ ሳስብ እስከዛሬም ማመን ያቅተኛል። በበኩሌ የደረስኩበት ድምዳሜ፣ የሰው ልጅ ከልጅነት ወደ ዓዋቂነት ከሚያደርገው ጉዞ ይልቅ፣ ከሰውነት ወደ አውሬነት ለመቀየር የሚወስደው ጊዜ በጣም ፈጣንና አጭር መሆኑን ነው። ሌሎች አገራዊ ፖሊቲካ ቀውስን ተከትለው የተከሰቱትን የርስ በርስ ጦርነቶችንም በተለያዩ አገራት በማየቴ፣ የዛሬውን ያገራችንን ሁኔታ ሳስብ ጨለምተኝነቴ ያለ ምክንያት አይደለም ባይ ነኝ።

ማድረግ ያለብን፣

 

በመጀመርያ ደረጃ፣ ይሄ ህዝባችንን እንደ ልዩ ፍጡር፣ ልዩ ታሪክና ተፈጥሮ እንዳለው አድርገን ራሳችንን ማታለል ብናቆም የተሻለ ይመስለኛል። እንደማንኛውም ህዝብ የራሳችን ጥንካሬና ድክመት ያለን፣ ሲመቸን ለመወዳጀት፣ አንድ ዴማጎግ ደግሞ መጥቶ ጭንቅላታችንን ከጠመዘዘ፣ እንደማንኛውም ሥጋ ለባሽ፣ ከሰው ልጅነት ወደ አውሬነት የመቀየር ባህርይ ያለን ፍጡር ነን። አንድ ህዝብ፣ በአንድ ባንዲራ ሥር የሚተዳደር፣ ጀግናው ህዝብ፣ የችግር ጊዜ ደራሽ፣ ላገሪቷ አንድነትና ለባንዲራው ሟች ወዘተ በማለት፣ እግዚአብሄር እነዚህን ባህርያት ለኛ ብቻ መርጦ የሰጠን እያስመሰልን ራሳችንን ማታለል እናቁም። ጣሊያን አገራችንን በወረረ ጊዜ ለግዛቷ አንድነት የተሰውት ጀግኖች የነበሩንን ያህል፣ ከጣልያን ጋር አብረው ደግሞ ወገኖቻችንን ያሰቃዩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን እንደነበሩም መዘንጋት የለብንም። ለኢትዮጵያ አንድነት ከመስቀል ጎን ጠብመንጃ ይዘው በጀግንነት የታገሉትን አርበኛውን አቡነ ጴጥሮስን የሞት ፍርድ የፈረዱበትም በጥይትም ደብድበው የገደሉት፣ እነዚሁ በሰላሙ ጊዜ “አገሩን ለባዳ ቆርሶ የማይሰጥ የጀግና ዘር” እያልን አብረን ቀረርቶ ስናሰማ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ነበሩ። በሰባዎቹም መጨረሻ አካባቢ በተካሄደው የቀይና ነጭ ሽብር ጊዜ ለሁለት ተከፍለው ሲገዳደሉ የነበሩት፣ ከዚሁ “በመፈቃቀርና በመከባበር አብሮ ለዘመናት ከቆየው“ ህዝብ የተወለዱ ”ለኢትዮጵያ ሟች ጀግኖች“ ነበሩ።

 

የርስ በርስ ጦርነት፣ ከውጭ ወራሪ ሃይል ጋር ከሚደረገው ጦርነት እጅግ በጣም የከፋ መሆኑን የውጊያ ጠበብቶች ይናገራሉ። የርስ በርስ ጦርነት የሚካሄደው በሁለት የርስ በርስ ገበናን በሚያውቁ ወገኖች መሀል ስለሆነ አንዱ አንዱን በቀላሉ ሊያጠፋ ይችላል ይላሉ። ከዚያም በላይ፣ የርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ የለውም። በጉልበት የበላይነት አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለማንበርከክ ቢችል ወይንም በዕርቅ ለመጨረስ ቢስማሙ እንኳ፣ በጦርነቱ ምክንያት በወደመው የላይ ላይ መዋቅር ብቻ ሳይሆን፣ ዘመዳሞች በነበሩ ሰዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የሚመጣው ምንጊዜም የማይድን ጠባሳ፣ የድህረ ጦርነቱን ህይወት የምስቅልቅል ጉዞ ያደርገዋል።

 

ዛሬ እጅግ በጣም እየደከመ የመጣው የፌዴራሉ ማዕከላዊ መንግሥት፣ ደጋግሜም እንዳልኩት አንድ ቀን ይሞታል። ይህ የማይታበል ሃቅ ነው። ግን የወያኔ መሞት ጉዳይ በጊዜ ካልታሰበበትና ተቃዋሚ ሃይሎች የድህረ ወያኔን የፖሊቲካ ወንበር ማን ወይም እነማን ሊቀመጡበት ይገባል ብለው ዛሬውኑ መመካከር ካልጀመሩ፣ የማዕከላዊው ሃይል እየተዳከመ መምጣት በዙርያው ላሉት ክልላዊም ሆነ ሌላ አገራዊ ሃይላት ጊዜያዊ ጥንካሬ ስለሚሰጥና ስለሚያበረታታ፣ ሁሉም ወንበሩ ይገባኛል ባይ ይሆንና ዛሬ በሰላሙ ጊዜ ረጋ ብሎ ተነጋግሮ ሊፈታ ያልቻለውን የዞረ ድምር በጥይት ለመፍታት ፍልሚያ ይጀምራል። እኛው እርስ በርስ መዋጋት እንጀምር እንጂ፣ ደግሞ ጠመብንጃና ጥይት አቀብለውን፣ በባሩዱ ስንቃጠል እያዩ ከዳር ቆመው የሚሞቁን ብዙ አሉ። ሁሉም በየፊናው የበላይነቱን ለማሳየት በሚያደርገው ጥረት፣ ከተቻለ፣ አንደኛው ወገን አሸንፎ የፖሊቲካ ወንበሩ ላይ ይቀመጥና ሌላ ዙር የጉልቤ መንግሥት ሥር እንወድቅና ጓደኛዬ ሰገድ በትክክል እንዳስቀመጠው “የመልመጃ ደብተር” መሆን እንጀምራለን። ወይም ደግሞ፣ ዘመናዊ የሆነ “ዘመነ መሳፍንት” ፈጥረን፣ አንድ ጠንካራ አገር ሳይሆን ደርዘን ደካማ አገሮችን “አብቅለን” እናርፋለን። ይህ ነው ትልቁ ስጋቴ።

 

ታድያ ምን ማድረግ አለብን?

 

ማድረግ ያለብንን ባለፉት ጽሁፎቼ የጠቃቀስኳቸው ስለሆነ ያንኑ መደጋገም ዘና ባያደርገኝም “መደጋገም የዕውቀት ሁሉ እናት ናት” የምትለውን የላቲን አባባል መከታ አድርጌ የሚከተሉትን ለማለት እፈልጋለሁ። የሚሰማኝን በግልጽ በማስቀመጤ አንዳንድ “አገር ወዳድ አርበኞችን” እንደማስቀይማቸው ከወዲሁ ባውቅም፣ ዛሬ “አካፋን አካፋ” ካላልን፣ ነገ ደግሞ ነገሮች እንዳልሆኑ ሆነው “አካፋን ዶማ” በሉ ስለምንባል፣ ዛሬውኑ የመናገርና ያስተሳሰብ ነጻነቴን መብት ተጠቅሜ፣ የተሰማኝን ከተናገርኩ፣ የታሪክ ግዴታዬን የተወጣሁ ይመስለኛል። ማድረግ ያለብን፣

 

ሀ) በመጀመርያ ደረጃ ወያኔ የችግሮቻችን ሁሉ መንስዔ የሆነውን ያህል፣ ችግሮቹንም ከሌሎች ጋር ሆኖ ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ እኩል ባለድርሻ ሆኖ መሆኑን ማወቅና ማሳወቅ አለብን። ወያኔ ከፈለገ እንደ አንድ የትግራይ ፓርቲ አለያም እንደ አንድ አገር ዓቀፍ የፖሊቲካ ድርጅት ራሱን አደራጅቶ፣ የወደፊቷን ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሙከራ ውስጥ መሳተፍ አለበት። ባጭሩ፣ ወያኔን ያላካተተና እሱን እንደ ዋነኛ ተደራዳሪ አካል የማይወስድ ሙከራ ሁሉ ከንቱ ይሆናል ባይ ነኝ

 

ለ) አንዳንድ ጽንፈኛ ኤሊቶች የሚነዙትና አንቀጽ 39ን የችግሮቻችን ሁሉ መነሻ አድርገው የሚያስቀምጡትን ውሃ የማይቋጥር ወሬ ማቆም ያለባቸው ይመስለኛል። በኔ ግምት፣ የአንቀጹ በህገ መንግስቱ ውስጥ መካተት ኢትዮጵያን ከመበታተን አዳናት ባይ ነኝ። ለዚሁ ማስረጃዬ ደግሞ፣ ይሄው አንቀጹ ሥራ ላይ ከዋለ በሃያ አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የአንድም ክልል ህዝብ ”ህገመንግስቱ በፈቀደልኝ መሰረት ከኢትዮጵያ ተገንጥዬ ነጻ አገር ላቋቋም” ብሎ የጠየቀ የለም የሚለው ነው።

 

ሐ) በዲያስፖራ የሚገኙ አንዳንድ ተቃዋሚ ኃይላት፣ ወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊቲካውን ዕውን ለማድረግ በሚሸርባቸውና፣ ከክልላቸው ውጭ በሚኖሩ የሌላ ብሄር ብሄረሰብ ዜጎች ላይ የሚያደርገውን የመግደልና የማፈናቀል ሴራ በብሄሮች መካከል የተደረገ የጥላቻ ድርጊት አስመስለው ህዝብን ለመከፋፈል ባይሞክሩ ጥሩ ነው እላለሁ። አለበለዚያ፣ ድርጊታቸው የወያኔም ድርጊት ሌላኛው ገጽታ ይሆናል ባይ ነኝ። ለምሳሌ የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያካሄድ በነበራቸው ህዝባዊ ዓመጽ ጊዜ፣ ያንን የሚያክል ስፋት ባለው ክልል ውስጥ በሚኖሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ አንዳችም የጥላቻ እርምጃ አለመወሰዱን የህዝቦቻችንን ተከባብሮና ተፈቃቅሮ የመኖር ገጽታ መሆኑን ተረድቶ እንደማወደስ፣ የኋሊት ተጉዞ ከሃያ ዓመታት በፊት ወያኔ በፈጸማቸውና ኦነግ ላይ ባስታከካቸው የጉራ ፋርዳና ፉኛን ብራ ዕልቂቶችን ዛሬ እንደ ናሙና ማቅረብ፣ ለህዝቦች መቀራረብም ሆነ ጊዜያዊ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ አንዳችም ፋይዳ አይኖረውም።

 

መ) ከሁሉም በላይ ግን፣ በተለይም በውጭ አገር የምንኖር፣ አጋጣሚ የለገሰንን በነጻነት የመናገርና የመሰብሰብ መብት ተጠቅመን በጊዜያዊ ጉዳዮች ላይ ተገናኝተን መወያየት አለብን። በተለምዶ ሁልጊዜ “ከሚመስሉን” ጋር ብቻ በመገናኘትና “የተጠመቁትን ከመስበክ” ወደ “ያላመነው” ወገን ሄደን ለማሳመን እንሞክር። ሁላችን በሁሉም ጉዳይ ላይ መስማማት ወይንም አንድ ዓይነት አቋም መውስድ የለብንም፣ ግን የተለያየ አቋም ይዘንና ባለመግባባታችን እየተስማማን፣ አንድ ላይ የማንራመድበት ምንም ምክንያት አይታየኝም። በበኩሌ፣ ከምንኖርባቸውም አገራት መቅሰም ያለብን ትልቁ እውቀት፣ የፖሊቲካ ጥበባቸው ነው እላለሁ። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ከማንም እኩል ተወዳድረን አንዳንዴም እያሸነፍን፣ ለምን የፖሊቲካ ጥበብን መቅሰም እንደከበደን አልገባ ካሉኝ ምድራዊ ጥያቄዎች ዋነኛው ነው።

 

ከላይ የጠቀስኩት አሰቃቂው የዩጎዝላቪያ የርስ በርስ ጦርነት ባገራችን እንዳይከሰት አንድ አስተማማኝ የሆነ፣ በህዝቦች መሃል ግጭቶች እንዳይፈጠሩና፣ ድንገት ከተፈጠሩም ሊያረግብ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል ጠንካራ አካል ያስፈልጋል። ወያኔ ካሁን በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮ የመኖርና ላገሪቷ የግዛት አንድነት ዋስትና የሚሰጥ ድርጅት አይደለም። በኔ ግምት፣ የዛሬውን አገራዊ ቀውስንም ሆነ ሊያስከትል የሚችለውን የርስ በርስ ግጭት ሊያረግብና ብሎም መፈረካከስን ለማቆም የሚችል አንድ ኃይል ቢኖር፣ በወያኔ ባለድርሻ አካልነት የሚያምን፣ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ትብብር ነው። ትብብሩ በምን መልክ ይከሰታል ለሚለው፣ አንዳችም ፎርሙላ የለኝም። በቁርጠኝነት ግን ለመናገር የምችለው እነዚህ ሁለት ታላላቅ ህዝቦች ከተባበሩ፣ የድህረ ወያኔዋ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ትሆናለች ብዬ እገምታለሁ። ይህ እውን እንዲሆን ከተፈለገ ደግሞ የሁለቱም ወገን ጽንፈኞች የዞረ ድምርን ለማወራረድ ከመሞከር ይልቅ፣ ወዳልተጠበቀ አደጋ እየወሰደን ያለውን የታሪክ ጎርፍ እንዴት አድርገን እናቆመዋለን በሚለው ሃሳብ ዙርያ ላይ ቅንነት የተሞላበት ውይይት ማካሄድ አለባቸው እላለሁ። በነገራችን ላይ ጎርፍም በትክክል ከተጠቀሙበት ልክ እንደ ኑክሌር ኃይል ለበጎም ለክፉም ሊውል ይችላል። ቆሻሻሽውን ጠራርጎልን የሚሄደውን ያህል፣ በትክክል ልንጠቀምበት ካልቻልን ግን ጎርፉ እኛንም ከቆሻሻው ጋር ጠራርጎን ይሄድና የታሪክ ተካፋዮች ሳንሆን ራሳችን ታሪክ ሆነን እንቀራለን። እግዜር ከንደዚህ ዓይነት መዓት ይሰውረን።

 

ኡፍ! በደንብ ተነፈስኩ አቦ! የነጻነት አየር በተሞላበት አገር ያለምንም ፍራቻ የልብን መናገር መቻልን የመሰለ ነጻነት የለም። እነበቀለ ገርባን፣ አንዱዓለም አራጌና ተመስገን ደሳለኝን ይህንን ነጻነት የነፈጋቸውን ሥርዓት ደምስሰን በምትኩ ዜጎች የመጻፍና የመናገር መብታቸውን ያለምንም ፍርሃት የሚጠቀሙበትን ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመገንባት፣ ዛሬ በቅንነት ላይ የተመሰረት ውይይት መጀመር አለብን የምለውም ለዚሁ ነው። ፈጣሪ ይርዳን።

ተደባብረን ከምንለያይ ግን፣ እስቲ አንድ ሩሲያዊ ጓደኛዬ የነገረኝን ቀልድ ላካፍላችሁና ሄጄ ልተኛበት፣

 

ዮሴፍ ዕንቅልፍ አልወስድ ብሎት ዓልጋው ውስጥ መገላበጡ ያሳሰባት ባለቤቱ፣ “ምን የሚያሳስብ ነገር አጋጠመህ ውዴ?” ብላ ስትጠይቀው፣ እያመነታ “ባለፈው ጊዜ ቸግሮኝ ከአብርሃም ገንዘብ ተበድሬ ነበር፣ በውሉ መሰረት ነገ መመለስ ነበረብኝ፣ ግን በጄ ምንም ስለሌለና ልከፍለው ስለማልችል ሃሳብ ገብቶኝ ነው“ ይላታል። ሚስትዬውም ትንሽ ካሰበች በኋላ፣ በፒጃማዋ ተሸፋፍና ወደ ባልኮኒው ወጣ አለችና፣ ልክ ከነሱ ፎቅ በላይ ይኖር የነበረውን አበዳሪውን አብርሃምን “አብርሃም አብርሃም“ ብላ ስትጣራ፣ አብርሃም ሮጦ ወደ ራሱ ባልኮኒ ወጣና በድንጋጤ “ሂሩት ምን ነካሽ በዚህ በእኩለ ሌሊት የምትጣሪው” ሲላት፣ “አይ በደህና ነው ግን ዮሴፍ ነገ ገንዘብህን ሊሰጥህ አይችልም” አለችውና ተመልሳ አልጋዋ ውስጥ ገባች። በነገሩ ግራ የተጋባው ዮሴፍም፣ ምን ማረግሽ ነበር ብሎ ሲጠይቃት፣ አይ ገንዘቡን ነገ እንደማትከፍለው ብቻ ነው የነገርኩት ብላ ስትመልስለት፣ እናስ? ሲላት፣ አንተ ብቻ ለምን ስትጨነቅ ታድራለህ፣ እሱም ሲጨንቀው ይደር” አለች ብሎ ከልቤ አሳቀኝ። እኔን ብቻ ለምን ይጭነቀኝ፣ እናንተንም ሲጨንቃችሁ ይደር ማለቴ ነው።

በቸር ይግጠመን።

*****

ባይሳ ዋቅ-ወያ wakwoya2016@gmail.com

ጄኔቫ,

10 October, 2017

11 Comments

  1. tooooooooooooooo long article

    The solution is

    govern your killil and if your children(regional governments ) fail hold them accountable

    equiatably participate in federal system .Period .

    THE FACT OF THE MATTER IS WOYANE IS THE ADMINSTARTOR OF TIGRAI .
    YOU ARE DAY DREAMING TO ELECT ON BEHALF OF TIGRAINS .

    RESPECT OTHERS TO BE RESPECTED .

  2. I think you know what articles 39 intention; it is purpose is TPLF’s last resort to destroy Ethiopia. It is lame to suggest that in the last 26 years no one separated or used article 39 to separate. If you don’t know why this is the case, I think you are dishonest. Once TPLF couldn’t control or dominate Ethiopian people at the eleventh hour it will make use of it. OLF was denied to separate and many of its membered where eliminated. Article 39 is a death sentence to Ethiopia cooked by EPLF and TPLF. And it will be used by TPLF once it loses control of the country. Do not forget the so called constitution is actually the jungle program of TPLF noting more or less it is a political program shaved in to Ethiopian throat. Furthermore; the second largest population of Ethiopia the Amhara’s were zero participation when this article was given to the people.

  3. Goraw, Come up with a practical solution. Do you want the TPLF to continue with its apartheid policy? ( I hope you are not a TPLF apologist). The author of the article provided what seemed to be a very reasonable solution. Blame is not goping to solve the problem. The Oromo people have said that they will no more be subject to Apartheid rule and they are, by all indications, revolting. You cannot impose your will on this people.

  4. Thx God! the time is coming that the most hated gangster of east africa go back to his beloved home land tigray. People PF Oromo and Amara will soon start to breath the peaceful fresh air. Haleluya!!!!

  5. ….አንቀጽ ፴፱ ወጥመድ ነው። ለመገንጠል ምክንያቴ “እኔ እናንተን አልመስልም” ብለህ ማመን አለብህ። እንግዲህ እናንተን አልመስልም ስትል፡ መጤ፡ ሰፋሪ፡ ተስፋፊ/ወራሪ ሆነህ እራስክን በራስህ ማንነትህን ጥለህ ለአፋልጉኝ እንድታለቅስ ያደርግሃል።ከማይመስሉህ ጋር ሜንጫ ትማዘዛልህ! *ከዚያ በኋላ ብሔር፫ ብሔረሰቦች፪ እና ሕዝቦች፩ በእኛ የተፈጠሩ፡ ለእኛ የሚኖሩ፡ ያለእኛ የሚበታተኑና የሚጠፉ ሲባል ቋንቋን ለፈጠረልኝ ፈጣሪዬ ህወሓ ተመስገን ትላለህ። “አዲሲቷ ኢትዮጵያ ፻ ዓመት ኖራ ፳፮ ዓመት እንዲህ ታለፈ..መግንጠል ስትጠይቅ ለማስተደዳደር የያዝከውን መሬት ለባለቤቶቹ ትመልሳልህ። አለበለዚያ የኢንዲስትሪ መር ኢኮኖሚ ግንባታና እስታዲየም ከቢራ ፋብሪካ ጋር የተገነባላቸው የድሮው አይመልስም ሲሉ የዛሬውን አስረክበው እንዲህ የጎጥና ቋንቋ ፌደራሊዝሙና ሕገመንግስቱ እንዲቀጥል እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ።
    youtube.com/watch?v=GKJtrXZhJvw
    (ስናፍቅሽ)
    “የዩኒቨርሲቲ ምደባ ይፋ ሆኖ 400 ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ አይደለሁም በማለታቸው እንዳልተመደቡ ሰማን፡፡ እንግዲህ አስራ ሁለት ዓመት የደከመ ተማሪ እንዲህ ያለውን ቅጽ ሲሞላ የሚመጣበትን በደንብ የሚያጤነው ይመስለኛል፡፡ ግን አልፈራም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብሔሩ ከዜግነቱ በላይ እንዲደምቅ ሲነገረው ያደገ አዲሱ ትውልድ ነው፡፡መንገዱን የት ድረስ እንደምንሄድበት ማሳያ ይመስለኛል፡፡ርቀቱንም ጥልቀቱንም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ አጋጣሚ ነው፡፡ ፬፻ ተማሪ መንግስት ፲፪ዓመት ኢንቨስት አድርጎበት ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ስላለ በምደባው አልተካተተም ብሎናል፡፡ይሄም ቢሆን ግን ተጠያቂ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡
    ኢትዮጵያዊ ያልሆነን ሰው ፲፪ዓመት አንድ ዜጋ የሚያገኘውን ጥቅም በመስጠት አስተምሮ አሁን ማግለል አይቻልም!፡፡ኢትዮጵያዊ አይደለንም ቢሉ እንኳን ያጭበረበሩ የውጪ ዜጎች ተብሎ ክስ መክፈት አሊያም ልጆች ሆነው የተሳሳቱ ተብሎ የዜግነት ትምህርት(ታደሶ) ያሰጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከትርኢቱ የምንማረው ነገር ግን አለ፡፡…(!?)”
    ______________________!
    ….አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ ግዛት የፌዴራል አባላቱን ወሰን የሚያጠቃልል መሆኑን ሲያሳውቅ፣ አንቀጽ 40 (3) “ . . . መሬት…የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” ብሎ ያውጃል፡፡ ሕጉ ይህንን ቢልም መሬትን የየክልልና የየብሔር ብሔረሰብ ንብረት አድርጎ የቆጠረ ብሔረተኛ አስተሳሰብ ሕዝብ ውስጥና መንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ ሲያሳስትና ጥፋት ሲያሠራ እናገኛለን፡፡

    አንቀጽ ፰(፩) “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” ሲልም በማያሻማ ሁኔታ የአገሪቱ ሥልጣን አዛዥነት የፕሬዘዳንት ወይም የጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን የእነሱ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡ አዛዥነታቸው(የሥልጣን ባለቤትነታቸው)የሚገለጸውም በተወካዮቻቸውና በቀጥተኛ ውሳኔያቸው አማካይነት ነው(አንቀጽ ፰፡፫)፡፡ እነዚህ ንዑስ አንቀጾች በብሔረተኛ አዕምሮ ውስጥ ውላቸውን ስተው ልክ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ሉዓላዊ ህልውና ያለው ተደርጎ ይታሰባል፡፡

    በአንቀጽ ፰(፩) ንዑስ አንቀጽ የአማርኛ ቅጂ ውስጥ ያለው “የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን” በእንግሊዝኛው “”Ethiopia’s Sovereign Power/Ethiopian State Sovereignity” በሚል ዓይነት አገላለጽ በመቀመጥ ፈንታ፣ “All Sovereign Power” ተብሎ መቀመጡ ለአሳቻ ትርጉም ሳያመች አልቀረም ሊባል ቢችልም፣ የአማርኛው ቅጂ ውስጥ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠውን እሳቤ የተረዳና በአንቀጽ ፻፮ ላይ የሠፈረውን የመጨረሻ ሕጋዊ ዕውቅናን ለአማርኛው ቅጂ የሰጠ ድንጋጌ ያስተዋለ ሰው መምታታት አይደርስበትም!!፡፡ እውነቱን ለመናገርም የአሳቻ ግንዛቤው ምንጭ ከአንቀጹ ይልቅ ሉዓላዊነትንና የመሬት ድርሻን ከብሔረሰብነት ጋር ያያዘ ብሔረተኛ ፖለቲካ አዕምሮ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ነው፡፡ በንዑስ አንቀጹ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቅጂ ውስጥ የታየው የአገላለጽ ልዩነትም ሉዓላዊነትን የየብሔረሰብ ከማድረግ ፍላጎት ጋር በጊዜው የተደረገውን መጓተት የሚጠቁም የቃላት ጨዋታ ይመስላል፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ክልል በተመድ የታወቀ ይዞታ ያለው፣ የውጭ ግንኙነቱን ራሱን ችሎ የሚመራ ቁመና በኖረው፣ ኢትዮጵያም ፌዴራል ሪፐብሊክ ከመሆን ይልቅ ኮንፌደሬሽን ወይም የአውሮፓ ኅብረት ዓይነት ማኅበረሰብ በሆነች ነበር፡፡

    በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ክልላዊ መንግሥታት የኢትዮጵያ አካል እንጂ በየራሳቸው ሉዓላዊ አይደሉም፡፡ አገሪቱን በጥቅል የሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ የሚያገኙት ወደየክልሎች ወርደው ታይተው ሳይሆን፣ “ተጠሪነቱ ለአገሪቱ ሕዝብ በሆነው” በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ነው (አንቀጽ ፶፡፫)፡፡

    ከታች ጀምሮ እስከ ክልል፣ ከክልል እስከ ፌዴራል ደረጃ ያሉ የሥልጣን አካላት በሕዝብ ወሳኝነት እንዲደራጁና እንዲመሩ የደነገገ፣ ክልል ገብ ጉዳዮችን ለክልሎች፣ ክልል አለፍና ከክልል አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለፌዴራል ለያይቶ የሰጠ ሕገ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አስማምቶ ለማስተዳደር በፍፁም አያንስም፣ አይጠብም፡፡ አንዳንዶች ለልብ መከፋፈል የዳረገን ባሻ ጊዜ የራስ ክልል ከመፍጠር አንስቶ ከአገሪቱ እስከ መለየት ድረስ የሰፉ መብቶችን የሰጠው ሕገ መንግሥት ነው ብለው ያስባሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እነ እከሌን ምን አካሰሳቸው ብሎ ምክንያቱን ለማወቅ ከመሞከር ፈንታ የመክሰስ መብትን ጥፋተኛ በሚያደርግ መንገድ ውስጥ የሚነጉድ ነውና ችግራችንን ወደ ማወቅ አያደርሰንም፡፡

    የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንከኖች እንዳሉት አይካድም፡፡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ረገድ እንኳ አንቀጽ ፴፱ ውስጥ አሳሳች የሆነ አገላለጽ እናገኛለን፡፡ አብሮ ለመሆን በመስማማት ላይ፣ በአብሮነት የቅንብር አማራጮች ላይ፣ ወይም አብሮነትን በመቀጠልና በማቋረጥ ላይ የፖለቲካ ውሳኔ በመስጠትና በሕዝቦች ዕጣ/ዕድል መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ በራስ ቋንቋ መማርና መተዳደር፣ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የፖለቲካ ዕጣን በዴሞክራሲ መወሰንና የመሳሰሉት በተግባር እንዲሟሉ የሚፈለጉ መብቶች ናቸው፡፡ በዚሁ ረገድ “የብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን” የሚባል “መብት”ን በዛሬው የተሳሰረ ዓለም ውስጥ ለማግኘት ብንሻ መቃዠት ይሆናል፡፡

    ብሔረሰቦች ይቅሩና አገሮችም የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት ሁኔታ ዛሬ እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ የሕዝቦች የልማት፣ የግስጋሴ፣ የሰላምና የደኅንነት ዕጣ ፈንታ በራስና በሌሎች ፍላጎት (በውስጥና በውጭ ሰበዞች ተራክቦ) የሚወሰን ነው፡፡ እስከ መገንጠል በሚደርስ ደረጃ የፖለቲካ ዕጣን የመወሰን ጉዳይ ከእነ አፈጻጸም ሥርዓቱ በሕገ መንግሥት ሠፍሮ ባለበት ሁኔታ እንኳ፣ የውሳኔው ተጨባጭነት በፍላጎትና መሥፈርቱን ለማሟላት በመቻል ብቻ አይለካም፡፡ ፍላጎትን ለሰላምና ለግስጋሴ ከማበጀቱ አኳያ በቅጡ ማመዛዘንን ይጠይቃል፡፡ በስሜት ያልታወረ ትክክለኛ ግምገማ ቀደም ተይዞ የነበር ፍላጎትን ከማጥራትም አልፎ፣ በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ሊያስቀይር ይችላል፡፡ ግልብና የተጣደፈ ግምገማም ወደ መቀመቅ መንደርደሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ግምገማው ከናካቴው፣ የውሳኔ መብቴንና ውሳኔዬን በተግባር የሚያከብር ማኅበራዊና መንግሥታዊ አንጀት በዕውን አለ ወይ? ከሚል ጥያቄ የማያልፍ (አስቀድሞ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታን የማደላደል ሥራን የሚደቅን) ሊሆንም ይችላል፡፡(በገነት ዓለሙ)
    …የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ከሆኑት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና በአጠቃላይ ከ600 በላይ ከሚሆኑት የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ አብዛኞቹ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ስንኞች አያውቋቸውም፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ግጥም የታተሙባቸው ወረቀቶችን ለሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት ለማደል ተገዷል፡፡ የአንድ አገር ብሔራዊ መዝሙር ዓላማ በሕዝቦች ላይ የብሔራዊነት ስሜትን መፍጠር፣ ታማኝነትን፣ አንድነትን፣ የጋራ ሰብዕናን፣ ሰላምንና በአገር መኩራትን በሕዝቦች ወስጥ ለማስረፅ ወደር የሌለው መሣሪያ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
    የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጭማቂ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፬ የተደነገገውም ይህንኑ ያመለክታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡ የምክር ቤቶቹ አባላት ምንም እንኳን ከተሰጣቸው ወረቀት ላይ እያነበቡ ቢሆንም፣ አስተካክለው ስንኙን ለመጨረስ ሲታገሉ ያይቷል።…ወዴት እየሄደን ነው?ይልቅ ተመልሰው ተኙ መች ተነቃና?ባልህበት ሂድ!የት ድርስ አለ!

    • በለው!

      FATHER OF RUMER , HERESAY AND TERET TERET

      “የዩኒቨርሲቲ ምደባ ይፋ ሆኖ 400 ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ አይደለሁም በማለታቸው እንዳልተመደቡ ሰማን፡፡ ”

      THESE STUDENTS ARE ACTUALY ERETRIANS , SOMALIES AND DJIBOUTIANS STUDING IN ETHIOPIAN HIGH SCHOOLS

      LEWERE YECHEKOLECH …………..

      • ናኒናኑ..የትግራይ ልጆች ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ የዓዞ እራት፡ የዓረብ ሀገር ገረድ..የሻቢያ እረኛና የጭን ገርድ ስታድረጉ፡ ተምራ ይላችሁት በየሻይ ቤቱ ዝንብ ስታስቆጥሩ የምታወሉትስ? እንዴት ሌላውን አስወደዳችሁ? እንኳን ሁለተኛ ደርጃ ትምህርት መጠለያ የሌለው ብሔር በሔረሰብ እያላችሁ ለጭፈራ ጠርታችሁ የምታላግጡበት ይህ ዕድል አለው ውይስ ተጨቁነህ ነጻ አውጥተንህ እያላችሁ ትሸቅሉበታላችሁ ንብረቱን እንደመዥገር ተጠብቃችሁ ትግጣላችሁ?…”THESE STUDENTS ARE ACTUALY ERETRIANS , SOMALIES AND DJIBOUTIANS STUDING IN ETHIOPIAN HIGH SCHOOLS…ሰው በራሱ ድንቁርናና ድድብናውን ሮጦ መጥቶ ይመሰከራል አይ ህወሓት እንዲህ ጀዝባ ትውልድ ያርባ!? ዘይገርምዩ

  6. ኦቦ ባይሳ ሐሳብዎን በጣም እጋራለሁ በአሁኑ ወቅት የሀገራችን ጉዳይ እንቅልፍ የማይነሳው ሰው ያለ አይመስለኝም ወያኔንም ጨምሮ ማለቴ ነው ነገር ግን ወያኔ ለመጨረሻው ቀን የሚሆን ፕላን “B “ አዘጋጅቶ እንደተቀመጠ ያለምንም ጥርጥር መገመት ይቻላል ለዝህም ሲባል ይመስላል ገና ከአሁኑ የመክላካያውንና የአየር ኃይሉን ቤዝ በአብዛኛው ወደ መቀሌ እንደወስደ የሚነገረው የሰይጣን ጆሮ አይስማውና እነዚህ የባንዳ ውላጆች ሀገራችንን ዘርፈው ህዝባችንን እርስ በርስ በማጫረስ ወደ ታላቅዋ ትግራይ ገብተው በሰላም የሚኖሩ ስለሚመስላቸው ምንም ነ ገር ከማድረግ ወደ ሁውላ የማይመለሱ ስለመሆናቸው የአገዛዛቸው ዘመናት ቁልጭ አድርገው አሳይቶናል

    ይህን አደጋ ለመከላከል ብሎም ለማስቅረት የሚቻለው በአንድ መፍትትሔ እንደሆነ አምናለሁ ይሄውም በኦሮሞና በአማራ ልጆች ኢትዮጵያን የማዳን የጋራ ታሪካዊ ተልዕኮ ሲፈፀም ብቻ ነው በተንኮል የተካነው መለስ ዜናዊ ከመሞቱ በፊት በአንድ ወቅት ለወያኔ አባላት ተናገረ የሚባለው ይህንኑ ያርጋግጣል ” አማራና ኦሮሞ በአንድነት የቆሙ ዕለት ሕወሐት ያበቃላታል ” ብሎ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ማስረጃ ነው በመሆኑም ወቅቱ ሐገርንና ሕዝብን በጋራ ተነስተን ማዳን እንጂ የምናባክነው ጊዜ ሊኖረን አይገባም እለሁ

  7. “ይህን የሚያክል ከባድና ቁልፍ የሆነ ጥያቄ ደግሞ አሁን “በሰላሙ ጊዜ” በሰከነ መንፈስ ካልተወያየንበትና መቋጠርያ ካላበጀንለት አራት ኪሎ ከተደረሰ በኋላ ጊዜው በጣም ያጥራል።”

    “የዚህን ወይም የዚያን ብሄር ህዝብ መወንጀል፣ መራራቅን እንጂ መቀራረብን እንደማያመጣ መገንዘብ የነበረባቸውና ያለባቸው ይመስለኛል።”

    ከፀሃፉው ያወረክዋቸውን ሁለት ጥቅሶችን በበለጠ ላሰምርባቸው እወዳለሁኝ!

  8. የተከበሩ የጽሑፉ አቅራቢ ሀሳቦትን በነጻ የማቅረብ እድል ያለ ከልካይ አግኝተው ለማቅረብ መቻልዎ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ሌላውም በዲያስፖራ የሚገኘው እርስዎ የወቀሷቸው ያደረጉት ይሄንኑ ነው። ቁምነገሩ ግን ማን መብቱን በአግባቡ ተጠቅሞ ለዚያ መከራና ስቃይ ለታከተው ነገር ግን ጸጥ ለጥ ብሎ ላለመገዛት እየተዋደቀ ላለው ወገኑና አገሩ የሚበጅ ሸፍጥ የለለበት መፍትሄ አቀረበ ነው። በጽሑፎት ስለ ቼኮዝሎቫኪያና ዩጎዝላቪያ ያጣቀሱት የተለያዩ ጎሳዎች አብሮ መነኖርና በጋብቻ መተሳሰር ብቻውን ለአብሮነት በቂ አለመሆኑንና የሰውን ልጅ መልካም አስተሳሰብ ወደ አውሬነት ለመለወጥ ቀላል መሆኑ የገለጹት ትክክል ነው ነገር ግን ምሳሌ ፍለጋ ያን ያክል ርቀት መጓዞት ነው። ወያኔኮ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ረግጦ የገዛን ተራ በተራ ወደ አውሬነት ቀይሮን በማጨራረስ ነው።

    ሌላው መፍትሄ ብለው ያቀረቡትን በተመለከተ፡-

    ሀ. ባጭሩ፣ ወያኔን ያላካተተና እሱን እንደ ዋነኛ ተደራዳሪ አካል የማይወስድ ሙከራ ሁሉ ከንቱ ይሆናል ባይ ነኝ።

    ያሉት ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ ባይሆንልኝም ከወያኔ ባህሪ ከተነሳን በውይይት የማያምን ሰጥቶ መቀበልን የማያውቅ 27 ዓመት ሙሉ ተለምኖ ማን ከማን ጋር ተጣልቶኖ የምንታረቀው እያለ የሚያሾፍ ስጨንቀው ለጊዜ መግዣና ዓለም አቀፍ ህብረተስብን ለማደናገር አሁን እርሱ ጠፍጥፎ ከፈጠራቸው ድርጅቶች ጋር እንድሚያደርገው ካልሆነ በቀር ሌላ የማይፈልግ ነው። ተወያይቶ ችግርን መፍታት ድሞክራሲያዊ አካሄድ ነው ዲሞክራሲ ደግሞ ለብዙሀኑ ውሳኔ ተገዢ መሆን ነው ይህ ድግሞ ወያኔን ስልጣን ያሳጣዋል። በዚህ ሁኔታ የፈጠርከውን ችግር አብረን እንፍታው እያሉት እምቢ ማለቱ እየታወቀ ያቀረቡት አማራጭ እርስ በርሱ የሚጋጭ ይመስለኛል።
    ለ. አንቀጽ 39 ኢትዮጵያ እንዳትበታተን ረዳት እንጂ አልጎዳትም ብለዋል እንዳሉትም መብቶት ነው ነገሩ አውቆ የተኛን ብቀሰቅሱት አይሰማም ነገር ነው። ከመቶ ዓመት በፊት ተፈጸመ የሚባል በመረጃ ያልተደገፍ ውንጀላ ምንም ሳይሉ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት በዓይናችን ያየነውን እውነታ የጉራፈርዳ እልቂት ለምን ይነገራል ማለት ብልህነትም ሰብአዊነትም አይደለም። መንስኤው ደግሞ የንቀጽ 39 ውጤት የሆነው አካባቢዬን ለቀህ ሀብት ንብረትህን ጥለህ ጥፋ ፖሌቲካ መሆኑን ሳይረዱ ቀርተው አይመስለኝም።

    በማጠቃለያ ያሉት መወያየት በጣም አስፈላጊ ነው ነገር ግን የጠላተ ጠላት ወዳጀ ነው ከሚል ታክቲካል እሳቤ ከሆነ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነው የሚሆነው። ሌላው እንደምሰሪያ አንቀጽ የተጠቀሙት ተረት የሚያሳብቀው ቅንነት የጎደለው ነገር እንዳረገዙ ነው።

    ለውይት ስላበቁን አመሰግናለሁ

Comments are closed.

Previous Story

ማንን እንመን? – ገብርኤል ብዙነኀ

Next Story

ከዘረኛው ሰርዓት የሚጠቀሙ ኢህአዴግ ምን ያድርግህ? ሲሉ እንደ ሀገር ክህደት የሚቆጠር ወንጀል ነው! – በቶማስ ሰብሰቤ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop