ደመራ {በሃይማኖታችን፥ በታሪካችንና በባሕላችን አንጻር} – (በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ)

መስከረም ፳፻፬ ዓ.ም.

ቀሲስ አስተርዕየ

‘ደመራ’ ደመረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ ነው:: ትርጉሙ ጭመራ ማለት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው:: ጥሪት (ካፒታል) እንዳይጎድል እንዳይቀነስ ይልቁንም እየበዛና እያደገ እንዲቀጥል ጠብቆ መያዝ የሚያስችል ደመራ ነው:: ስሙ እንደሚያመለክተው ማስታወሻነቱ ለተጠራቀመ፥ ለተሰበሰበና ለተጨመረ ነገር ነው:: በያመቱ የምናከብረው የደመራው በዓል በድመር አካቶ የያዛቸዉ ማለትም፦ ሥርዓቱ የሚከናወንባቸው ቁሳቁሶች፥ የሚደመሩት እንጨቶች፥ ችቦዎች፥ አሽክቶችና፥ ሌሎችም የሕዝቡን ስሜት ለመቀስቀስ በወቅቱ የሚዘመሩትና የሚቀሰቀሰውን ህዝባዊ ስሜት አንድ ላይ ሰብስቦ ስለያዘ ደመራ ተባለ:: የደመራ ተቃራኒው ‘ቅነሳና ከፈላ’ ነው::

በነገረ መለኮት ከኛ ጋራ አንድ የሆኑት አኀት አብያተ ክርስቲያናት፤ ከኛ ጋራ በማይካፈሉት በአገራችን በተፈጠረው ታሪካዊ ክስተት ምክንያት፤ በተለየና በደመቀ ሥርዓት በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል:: ካህኑ “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” በሚለው በሊጦኑ ቃለ ቡራኬ የመጀመሪያዋን የደመራ መብራት ባርኮ፥ ከደመራው እንጨት ጋራ እንዲደምራት ሕዝቡን በአስተዳደር ለሚመራው ሰው ያቀብለዋል። የሀገሪቱ መሪ ከካህኑ በተቀበለው እሳት የደመራውን እንጨት ይለኩሰዋል:: ከዚያ በኋላ ያገር ሽማግሌና ባካባቢው ያለው ሁሉ በተዋረድ ችቦውን እያቀጣጠለ በደመራው ላይ ይጨምረዋል:: በዚህ ሥርዓት የሚከበረውን የደመራ በዓል በሃይማኖታችን፥ በታሪካችንና በባህላችን አንጸር በመጠኑ እገልጻለሁ::

በሃይማኖታችን፥
በታሪካችንና በባሕላችን
አንጻር በመዳሰስ ይሕችን ጦማር እደመድማለሁ:: በመጀመሪያ በሃይማኖታችን አንጻር እነሆ! ደመራ በሃይማኖታችን አንጻር የአምልኮታችንን ሥርዓት ተንተርሶ “The Wisdom Compass to Eternal Life” በሚል ርእስ

ጌታችን ያስተማረውን ጸሎት መሠረት በማድረግ በቅርቡ አቶ አቤል ጋሼ በቀመር መልክ ባቀረበው መጽሐፍ “While we keep reciting ‘Have mercy on us’ twelve times corresponding the name of the Father, the son and the Holy Spirit” እያለ ዳሶታል። (ምዕ 10 ገጽ 135)

አምልኮታችንን ጀምረን የምንፈጽመው ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ ፮ ከቁጥር ፪-፭ በገለጸው መንገድ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ አይቶ እንደነገረን፥ (ምዕራፍ ፬ እና ፭) የእግዚአብሔርን ዙፋን በተሸከሙት ኪሩቤል የአምልኮት ዘይቤ ነው:: ፬ቱ ኪሩቤሎች በላያቸው ላለው ፈጣሪ አምልኮት ሲያቀርቡ ሶስት ጊዜ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበርክ ያለህ፥ ወደፊትም የምትኖር” እያሉ ነው:: የቀደሙ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትም ይህን መሠረት በማድረግ “ንሕነሰ ነአምን ከመዝ እስመ ሥሉስ ቅዱስ እሩያን እሙንቱ በተዋሕዶተ መለኮት ወፍጹማን በ፫ቱ አካላት ዘውእቶሙ ፩ዱ አብ ቅዱስ፥ ወ፩ዱ ወልድ ቅዱስ፥ ወ፩ዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” (ሃይ ምዕ፷፪፡ ፲፭):: እያሉ የነገረ መለኮቱን መሠረት አስተማሩ:: ማለትም፥ “እኛም እንደ ሱራፌልና ኪሩቤል፥ ኢሳይያስ ባየው፥ ዮሐንስም በገለጸው መንገድ በአካል ሶስት፥ በመለኮት አንድ እያልን እናምናለን፥ አምነንም እናመልከዋለን፥ እናስተምረዋለን:: በኪዳን ተጀምሮ በቅዳሴው የሚፈጸመው አምልኮታችን የሚከናወነው በዚህ መሠረት አንድም ሶስትም እያልን ነው::

ሕጻናት ነገሮችን ማጤን የሚጀምሩት የራሳቸውን ጣቶች በማየት፥ በጣቶቻቸውም አካባቢያቸውን በመዳስስ እና የዳሰሱትን ለመቅመስ ጣቶቻቸውን በመጉረስ ነው:: ቅዱስ ጳውሎስ “ሕጻን ሳለሁ፥ እንደ ሕጻን አስብ ነበር እንደ ሕጻንም እቆጥር ነበር” እንዳለው በደመ ነፍስ እናድርገው እንጅ የጣቶቻችንን ቁጥርና የተሸከሟቸውን አጽቆቻችንን መማር መረዳት የምንችለው በእድገታችን ሂደት ነው:: እንደዚሁ ሁሉ በጸሎታችን የሰማዩንና የምድሩን ሁኔታ ከዳሰስን በኋላ ጸሎታችንን የምንደመድመው በጣቶቻችን ላይ ባሉት አጽቆች (phalanxes) ቀመር ነው:: ሆኖም Mutation (የተፈጥሮ ባሕርይን መቀየር) ከሚባለው አጋጣሚ በቀር ያንዱ እጅ ጣቶቻችን ከአምስት አለመጉደላቸውንና አለመትረፋቸው ብናውቅም፤ የአጽቆቻችንን ቀመር በመጠቀም “፲፪ ጊዜ እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ” ብለን ለጸሎታችን መደምደሚያ ለምን እንደምናደርገው የምንረዳው ዘግይተን ነው። በስፋት ስናየውም፦ የሰው ልጅ በየብስ፤ በባሕርና በአየር ውስጥ ተቆልፎ የኖረበትን የፍጥረት ምሥጢር እየበረገደ የገባውና በመግባት ላይም የደረሰው በአዝጋሚ እደገቱ ነው። ከዚህም የደረሰው በደመራ በተጀመረ ቁጥር እየተመራ እንደሆነ ግልጽ ነው::

ወደ ስርአተ አምልኮታችን እንመለስና፤ አውራ ጣታችንን ቆጣሪ በማድረግ በአራቱ ጣቶቻችን ላይ ያሉትን ፲፪ን አጽቆች መሰረትና ምልክት በማድረግ “እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ” እያልን እንጸልያለን። ፲፪ ቁጥሮች የሚያስታውሱን ብዙ ነገሮች አሏቸው:: በያንዳንዷ ጣት ላይ ያሉት አጽቆች ስብስብ መጠን ለማግኘት ስንደምራቸው ፲፪ ቁጥር እናገኛለን:: 12 ን አጽቆች ለ4 ጣቶቻችን ብናካፍላቸው የምናገኘው ውጤት ሥላሴ ማለትም 3 ነው:: 12 ን አጽቆች ባንዷ ጣት ላይ ላሉት ለ3 አጽቆች ብናካፍላቸው የምናገኘው ጸወርተ መንበር የሚባሉትን 4ቱን ኪሩቤል ነው:: እንደገና 3 እና 4 ብንደምር የሳምንቱን ዕለታት ልክ ቁጥር 7 ን እናገኛለን:: ፊደሎቻችንም የተዋቀሩት በሳምንቱ ዕለታት ላይ ነው:: በግዕዝ (፩) ተጀምራው የሚያልቁት በሳብእ (፯) ቁጥር ነው:: ፩፥ ፫፥ ፬፥ ፯ ና ፲፪ ቁጥሮች ለብዙ ነገሮች ምልክቶች ናቸው::

በአራቱ ጣቶቻችን ያሉት ፲፪ አጽቆች፥ አንዷን የብርሃን ቀን አካታ የያዘቻቸውን ሰአቶች ያስታውሱናል:: አንድ አመት የሚሰጡንን የአስራ ሁለቱን ወራት ጥርቅም ይሰጡናል:: የክርስቶስን ምድራዊ አካል ምንጭ ለማግኘት የምንቆጥራቸውን የ፲፪ቱን ነገደ ፳ኤል ቁጥር ይሰጡናል:: በመቀጠልም ከክርስቶስ ቀጥለው ክርስትናን ያስፋፉትን የሐዋርያትን ፲፪ ቁጥር ይጠቁሙናል::

ከዚህ በመነሳት፥ የሐዲሳት ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያናችን አባቶቻችን በስላሴ፥ በመድኃኔዓለም፥ በእመቤታችን፥ በመላእክት በጻድቃንና በሰማእታት ስም የሚመሰረቱት የጸዋዕ ማኅበራት በ ፲፪ ቁጥር ልክ ሰርተውታል። ህብረተ ሰቡን በማዋቀር የማይሞት የማይረሳ አድርገው በራዕየ ዮሐንስ ምዕ ፯ ላይ እንደተገለጸው፥ የያንዳድዱ አጥቢያ (ሰበካ) ቁጥር በአስራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል፥ በ፲፪ ሐዋርያት፥ በ፲፪ ወራትና በ፲፪ ሰዓተ መአልት መስርተውታል። አካለ መጠን የደረሰ ሁሉ በያለበት አጥቢያ (ሰበካ) በ ፲፪ እየተመደበ ይደመራል:: ሁሉም የጽዋዕ ማኅበራት፤ ለያንዳንዳቸው መምሕር ይመደብላቸዋል:: እያንዳንዱ አባል ከዓመቱ ውስጥ ካሉት ወራት አንዱን ይወክላል:: ከነገዶች ውስጥ አንዱን፥ ከሐዋርያትም አንዱን ይወክላል:: በዚህ መንገድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት አባል የሆነ ሁሉ በዚህ ቁጥር እየተካተተ (እየተደመረ) የጽዋው ተካፋይ ይሆናል::

በ፲፪ ቁጥር የተዋቀረችው የጽዋዕ እያንዳንዷ ማኅበር አባላት ከመካከላቸው በእምነትና በመንፈስ ላቅ ያለውን መርጠው በሙሴ ስም ለማኅበሩ መሪ ይሰይማሉ:: እያንዳንዷ የጽዋዕ ማኅበር የመረጠችው ሙሴ (መሪ) ደግሞ፥ የሚመራትን የጽዋዕ ማኅበር በመወከል አንድላይ ተሰብስበው ይደመሩና የራሳቸውን የጽዋዕ ማሕበር፦ ማሕበረ በኩር ብለው ይሰይማሉ:: ለማሕበረ በኩሩ መምሕር ሆኖ የሚሰየመው በሙያና በችሎታ ከሊቃውንቱ መካከል ተመርጦ የደብሩ አለቃ ነው:: የደብሩ አለቃ ዋና ኃላፊነት እየዞሩ የጽዋዕ ማኅበራቱን አባላት የሚያስተምሩትንና የማኅበረ በኩሩን አባላትና ሙሴዎች አንድላይ እየሰበሰበ ማስተማር ስለሆነ በጥንቃቄ ይመረጣል:: የመሳፍንቱ ሥርዓት ተጽእኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ባያዘናጋት ኖሮ የያንዳንዷን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መምራት የነበረበት ይህ ማኅበረ በኩር የተባለው ጉባዔ ነበር::

የማኅበሩ ዓላማ በየሰንበቱ በቤተ ክርስቲያን ሕንጻ በመሰብሰብ ከሚደረገው በተጨማሪ ምእመናኑ ተራ ገብተው በየቤታቸው የሚያደርጉት አምልኮ ነው። በዚህ ስርአት ተረኛው ቄጠማውን ጎዝጉዞ፥ ውሐውን ቀድቶ ይጠብቃል:: የማኅበሩ አባላትም ነጭ ልብስ ለብሰው ተሰብስበው ዮሐንስ “የታረደው በግ ኃይል ክብር፤ ምስጋናና አምልኮት ይገባዋል (ራእይ ፭፡፲፩᎗፲፬ እያለ በገለጸው ስርአት ክርስቶስን ያመልካሉ።

በሙሴያቸው አስተናባሪነት ካህኑ በራዕየ ዮሐንስ ላይ የተመሠረተውን ሥርዓት በመጠበቅ “እነማናችሁ ከወዴትስ መጣችሁ? (፯፡፲፫) በማለት የማህበሩን ዓላማ እየነገረ ጉባዔውን ይመራል:: ከዚያም የማኅበሩ ሙሴ “ባለወር፥ ባለሳምንት” ብሎ ጉባዔው የተሰየመበትን ስም እየጠራ “የጉባዔው ወዳጅ ማነህ እኔነ ነኝ የምትል” ብሎ ያውጃል::ተረኛው ተዘጋጅቶ በመጠበቅ ላይ ነውና “እኔ ነኝ” ብሎ ወደ መሐል ይቀርብና ይቆማል:: ካህኑ ይቀበልና “እኔ አለሁ ብለህ እንደቆምክ መድኃኔለም ይቁምልህ” ይለዋል:: ጽዋውን በመቀባበል በጽዋዕ ውስጥ ያለውን ጠበል ሁሉም በመካፈል እዚያው ላይ ያልቃል። ከዚህ በኋላ ጽዋውን የተቀባበሉ አካላት በጉባዔው ፊት ይወድቃሉ:: ካህኑ “እንደዚህ እንደወደቃችሁ ኃይለ አጋንንትን ያውደቅላችሁ” ብሎ ሰዓታቱን፥ ወራቱን፤ ነገደ እስራኤልን፥ ሐዋርያትን፤ በመጨረሻም ስላሴንና አራቱ ኪሩቤልን አጠቃሉ ደምሮ በያዘው ፲፪ ቁጥር “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ይልና፤ “ያለፈውን ይቅር ይበለን ከሚመጣውም ጠብቆ የወር ሰው ይበለን፤ በሚቀጥለው ጉባዔያችን ያገናኘን” ብሎ የአምልኮቱን ሥርዓት ይዘጋዋል:: ነፍሳቸውን ይማርና ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰበካ ጉባዔውን ሲነድፉት፥ በዚህ ቅዱስ ታሪክና ባሕል የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር ለማዋቀር ነበር፡፡

ደመራ በታሪክችንና በባህላችን አንጻር

በመግቢያው ላይ እንደገለጽኩት ደመራውን የጀመረችው በአራተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ እሌኒ የምትባለው የቆስጠንጢኖስ እናት ነበረች። የጀመረችበት ምክንያትም የክርስቶስ ተቃራኒዎች፥ የክርስትና ንክኪ ያለውን ፍንጭ ሁሉ ለማጥፋት ባደረጉት ጥረት፥ ከክርስትና ፍንጮች አንዱና ዋናው የክርስቶስ መስቀል ስለነበረ፥ በጉርጓድ ቀበረውት ነበረና፥ ፈልጋ ለማግኘት ነው:: መስቀሉን ለማግኘት የተጠቀመችበት ስልት፥ እሳት አንድዳ ጢሱ እንዲመራት በመጸለይ ነበር::

ተጨማሪ ያንብቡ:      "የጥላች ንግግር ህግ "  - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የታሪኩ መሠረትና መነሻ ንግሥት እሌኒ ትሁን እንጅ፤ እሷ በጀመረችበት ቦታ፥ እኛ በምናደርገው ሥርዓት ዓይነት አሁን ሊከበር ቀርቶ የሚያስታውሰውም የለም:: ታዲያ ለምን እኛ ብቻ በዚህ መልክ እናከብረዋለን? የሚል ጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም፥ ተገቢም ነው:: መልስ የሚጠበቀው በየዘመኑ ወደ አገራችን ከገቡት ድርጅቶችና ወኪሎቻቸው አይደለም። እነሱማ እንኳን ሊያከብሩት፤ ሊያስታውሱትና ሊመሰክሩት፤ ተልእኳቸው ከፈላና ቅነሳ ስለሆነ የደመራ ተቃራንያን ናቸው። እንዲያውም ነቅፈው ያስነቅፉታል። ንቀው ያስንቁታል። ጠልተው ያስጠሉታል። ከፈረንጁ ትምህርት ቤትም ሆነ በዘመኑ ከሚሰጡት አጫጭር ኮርሶች የሚገኝ አይደለም። የደመራውን ታሪክ የማስተማርና በደመራው ዙሪያ ለሚነሱት ጥያቄዎችም የመመለስ እዳ፥ ሸክምና ግዴታ ያለባቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተማሩ ቀሳውስትና፤ በካባቢም ሲወራ የሰሙ ሰዎች ነው።

የጥምቀቱን በዓል ከዓለም ክርስቲያኖች ለየት ባለ መንገድ እንደምናስታውሰው፥ በደመራው በዓል አማካይነትም በንግሥት እሌኒ ሕሊና ውስጥ ይነድ የነበረውን የክርስቶስን ፍቅር ለዓለም ለማሳየት፤ ቅዱስ ጳውሎስ “በማይከደን ፊት የጌታችንን ክብር እንድ መስታዋት እያብለጨለጭን ያን መልክ እንመምሰል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን”( ፪ኛ ቆሮ ፫፡፲፯) እንዳለውም፤ በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች በማያስቡበት በተለየ መንገድ ደመራ የሚል ስም ሰጥተን በያመቱ የምናከብረው እኛው (ጉደኞች) ነን:: ለምን ጉደኞች? የደመራ በዓል፤ ባንድ ወቅት በምክንያት ከሚጀመሩት በዓላት አንዱ ነው። በዓላት የታሪክ መነሻዎች ናቸው:: ተጠብቀው ሊቆዩ የሚችሉት ግን፤ በቅኝ ገዥዎች አዕምሯቸው ሳይዝል፤ ሳይዘነጋና የተጀመሩትን ሳይረሱ የሚታረመውን እያረሙ፥ የሚጨመረውን እየጨመሩ እስከ ዓለም መጨረሻ ጠንክረው በሚጓዙ እንደ ኢትዮጵያውያን ባሉ ኅብረተ ሰቦች ብቻ ነው::

ይህ የደመራ በዓል ከተጀመረበት ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ በገጠሙን ክፉ ቀናቶች ሁሉ ሳያቋርጥ ከኛ ደርሷል:: በዓላት ሁለት መንገዶች አሏቸው:: ከሁለቱ አንዱ ከጣዖትና ከባዕድ አምልኮት ጋራ የተያያዘ ቅዱስ መጽሐፍ የሚያወግዘው ነው:: ከሰይጣን አምልኮት በራቀ መንፈስ ባሕልን ታሪክን አዝለው በመመላለስ የሚታወሱ ሁሉ በዓላት፥ ይዘታቸው እየሰፋ የሚቀጥል መጻሕፍቶች ናቸው:: ይህ አይነት ህዝባዊ ትውስታን የተሸከመ (Social Memory) መጽሐፍ የሌላቸው እንስሳት ብቻ ናቸው::

ከዚህ ቀደም ቅበላ (http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/ISAT.pdf) በሚል ርእስ እንደገለጽኩት፥ በሐዘንና በደስታ፥ በልቅሶና በሳቅ፥ በመሸበርና በመረጋጋት በምትናወጠው ዓለም የሚኖር ሰው፥ በየዓመቱ ዞረው የሚመጡትን በዓላት የሚያከብራቸው፤ ባጋጣሚ ክስተቶች ነጸብራቃቸውን በመቀያየር ነው:: አንድ ጊዜ የተዘጋጁ መጻሕፍት በውስጣቸው የያዙትን ምዕራፍ በሚገጥሟቸው ተመሳሳይ አዳዲስ ክስተቶች እያሰፉ በመደጋገም እንደሚታተሙ ሁሉ፥ በዓላትም እንደዚሁ በየአመቱ የሚገጥሟቸውን እየጨመሩ ስለሚሄዱ የሕብረተ ሰቡ ትዝታ ወይም የ Social Memory መጻሕፍት ናቸው::

ለደመራው በዓል መነሻዋ እሌኒ ብትሆንም፥ እሌኒ ደመራ ብላ አልሰየመችውም:: ይህ በዓል ደመራ ተብሎ አሁን በምናከብረው ሁኔታና መንፈስ እጅግ ሰፍቶ ከመከበሩ በፊት፥ ወደ እኛ ተሻግሮ መጥቶ ሲከበርና ሲታወስ ቢኖርም፥ የመስቀል በዓል እተባለ እንጅ ደመራ እየተባለ አልነበረም:: በአጼ ገላውዴዎስ ዘመን አዲስ ታሪካዊ ክስተት ገጠመውና ሊቃውንት አበው፥ ከታሪካችን ጋራ ደምረውና አስፍተው ደመራ ብለው እንደ ሰየሙት ነግረውናል። ይህም ማለት፤ በዚያ አመት የተከበረው የመስቀል በአል የገጠመውን ክስተት ተሸከመ። ክስተቱን ለመግለጽ ከሊቃውንት አበው መምሕሮቼ የሰማሁትን ባጭሩ መግለጽ ሊኖርብኝ ነው። ግራኝ መሐመድ ኢትዮጵያን በወረራት ዘመን፥ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አጼ ልብነ ድንግል በዚያ ዘመን ገናና ይባል የነበረውን የፖርቹጋሉን መንግሥት እርዳታ ጠየቁ:: በዘመኑ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የጎመጁበት ዘመን ነበረና፤ የፖርቱጋል መንግሥት ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ፦

፩ኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሮማ ካቶሊክ ሥር፥
፪ኛ ኢትዮጵያንም በራሱ ቅኝ አገዛዝ ሥር ለማድረግ ከሮማው ፓፓ ጋራ ሲሸርብ ዘገየ::
የዘመኑ የጉዞ ሁኔታም ለመዘግየታቸው ተጨማሪ ችግር ነበር ይላሉ:: በዚያም ሆነ በዚህ፥ ከፖርቱጋል የተላኩት መልእክተኞቹ አጼ ልብነ ድንግል ከጠየቁበት ወቅትና ጊዜ እጅግ ዘግይተው ጦርነቱ ከበረደ በኋላ ደረሱ::

አጼ ልብነ ድንግል ሞተው፥ በጦርነቱ የደቀቀው ሕዝብ በአጼ ገላውዴዎስ መሪነት ተመልሶ በመቋቋም ላይ ሳለ፥ ዘግይተው የደረሱትን የፖርቹጋል ሰዎች፤ ጦርነቱ እንዳለቀና የነሱም እርዳታ እንደማያስፈልግ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በንጉሡ ተነገራቸው። ወደ አገራቸው በመመለስ ፈንታ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ በመኖር በሕዝቡ መካከል እየገቡ፥ አሁን ቻይናዎች በአገራችን ላይ እንደሚያደርጉት ማለት ነው፥ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን እየተጋቡ በመዋለድ ኑሯቸውን ማስፋፋት ጀመሩ::

የፖርቹጋል ሰዎች በባሕል፤ ሃይማኖትና ፖለቲካ እየገቡ የሕዝቡን አንድነት የሚፈታተን ሸርና ደባ መሥራት ጀመሩ:: በዚያን ጊዜ የፖርቹጋል ሰዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈፈጠሩት ሁኔታ፤ ዛሬ በዘመናችን በወያኔወች የተደገመ ይመስላል:: ማለትም፦ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መወገድ ጀምሮ ደርግ እስኪፈርስ ድረስ በውጭ ጠላት ባይሆንም፤ እርስ በርስ በተካሄደው እልቂት ያለቀው ሕዝብ ኢትዮጵያ ያመረተችው ምርጥ ዜጋ ነበር:: ኢትዮጵያ እነዚህን ሁሉ በኩራት ልጆቿን አጥታ፥ ህዝቡም ተዳክሞ ባለበት ወቅት፥ የዘረኛው ያቶ መለሰ መንግሥት ኢትዮጵያን በግላጭ ተቆጣጠራት::

በግራኝ መሐመድ ጦር ካለቀው ህዝብ የተረፈው ፤ ግራኝ ከፈጸመው መከራ ጥቂት ሳያርፍ ፖርቹጋሎች ከፈጡሩበት መከራ ውስጥ ገባ:: ፖርቱጋሎች የፈጸሙብንን ታሪክ፤ እነ አቶ መለሰ ከፈጸሙብን ደባ ጋራ ስናነጻጽረው፤ በንጉሡና በደርግ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከኤርትራ ጋራ በተደረገው ግጭት ካለቀው ሕዝብ ይልቅ፤ አቶ መለሰ በፈጠሩት ተንኮልና ደባ ያለቀው ወገን ሲታሰብ እጅግ የበዛ መሆኑን እንረዳለን። እዚህ ላይ ቆም ብለን ስናስብ፤ ወያኔ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ከፋፍሎ በጠላትነት እንዲተያይ ማድረጉ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው ደባ፤ ፖርቱጋሎች ከፈጸሙት ደባ እጅግ ርቆ መሄዱን እንረዳለን።

በፖርቹጋሎችና በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቸውና መናናቁ እጅግ እያየለ ሄዶ፤ በቅጽል ስምና በተረብ መዘላለፍ ተጀመረ:: ኢትዮጵያውያን ለፖርቱጋሎች ትኋን የሚል ስም ሰጧቸው:: ፖርቱጋሎች ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ቁንጫ የሚል ስም ሰጧቸው:: በመናናቅ እርስ በርስ የተሰጣጧቸው የቅጽል መግለጫዎች ትርጉም አላቸው:: ኢትዮጵያውያን ፖርቹጋሎችን በትኋን ጠባይ የገለጿቸው፥ ትኋን የሰው ደም መምጠጥ የምትጀምረው ጨለማ ተንተርሳ፥ እየተጠራራች ከየስርቻ በመውጣት ነው:: ደሙን የመጠጠችው ሰው ካያት ሮጣ አታመልጥም:: የመጠጠችውን ደም ተሸክማ ስትንገዳደገድ ትደፈጠጣላች:: ጥላው የምትሔደው ክርፋት በቶሎ የሚለቅ አይደለም:: ፖርቹጋሎችን እንዲህ ናችሁ ለማለት ኢትዮጵያውያን ትኋኖች ብለዋቸዋል::

ቁንጫ ቀንም ሌትም አትመርጥም:: ይዞ ለመግደልም የማትጨበጥ ፈጣን ናት:: ኢትዮጵያውያኖችንም አይያዙም፥ አይጨበጡም፥ ጠላታቸውን ለማጥቃት ቀንና ሌሊት አይመርጡም ለማለት ፖርቹጋሎቹ ኢትዮጵያውያንን ቁንጫዎች ብለዋቸዋል:: በዚህ መልክ መሰዳደቡና መተራረቡ አድጎ ጸቡና ጥላቻው እየከረረ ሄደ:: እንዲያውም በአድዋ አካባቢ ሰፍረው የነበሩት ፖርቹጋሎች ድርጅታቸውን የበለጠ አጠናከሩ።

ፖርቹጋሎች በአድዋ ለሚኖረው ህዝብ “መንግሥታችሁ በፖርቹጋል ምንግሥት ሥር ለመተዳደር ተስማምቷል፤ እናንተ ይህን ካልተቀበላችሁ ከመላ ኢትዮጵያ ተቆርጣችሁ የቀራችሁ ናችሁ” እያሉ ሀሰት በመስበክ በሌላው ክፍለ አገር ሕዝብ ላይ ከፈጸሙት የመከፋፈልና እርስ በርሱ የማገዳደል ደባ በአድዋ ሕዝብ ላይ የፈጸሙት እጅግ የከፋ ነበር ይባላል:: ይህንም ለማስታወስ በአድዋ አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ “ዓኾ ዓኾኋይ ሆይ ሆያዬ ንጎናይ በርሆ” በማለት ደመራውን በመዞር በያመቱ ያስታውሱታል:: ይህም ማለት፥ “እናንተ ተቆርጣችሁ የቀራችሁ እያሉ ይዘልፏቸው ስለነበረ፥ እኛ ኢትዮጵያውያን የተቆረጣችሁ እየተባልን በገዛ አገራችን ስንሰደብ ብንኖርም፥ ዛሬ በዚህ ችቦ የነጻነት ብርሃን በራለን” እንደ ማለት ነው ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ:: የትግርኛውን ቋንቋ ስለማላውቀው አበላሽቼ ላቀርበው እችላለሁ። ይቅርታ እየጠየቁ የማቃናቱን ኃላፊነት ባካባቢው ለተወለዳችሁ ወገኖቼ እተወዋለሁ:: ንጎናይ ማለት ቆራጣ ማለት ነው ሲሉ ሰምቻለሁ::

በዚያ ዘመን የአድዋ ሰዎች ብዙ መከራና ስቃይ አይተዋል። ከመከራውና ከስቃዩ ለመላቀቅ ብዙ መንገዶችን ተጠቅመዋል። ከተጠቀሟቸው ብዙ መንገዶች አንዷ በአማረኛ አሽከት በትግርኛ ጸጎጎት የምትባለውን የመጣበቅ ባሕርይ ያላት ሐርግ ነበረች። የትግራይ ሰዎች ከመላ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋራ ያላቸውን ጥብቅ አንድነት ለማሳየት የመጣበቅ ባሕርይ ያላት ሐርግ በራሳቸው ላይ በማሰርና በተለያዩ ምልክትነት ተጠቅመውባታል ይባላል። “ጽንዒ” እያሉ በአሽክቷ የተጠቀሙበትን ምሥጢር መስከረም ፲፮ ላይ በያመቱ ያስታውሱታል:: በዚያ አካባቢ ተወልደው ያደጉ ወጎኖቻችን አብራርተው ቢያቀርቡት፤ ታሪካዊነቱን የበለጠ ሊያጎላው እንደሚችል እገምታለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “የጆሮ ቀለብ ያ’ርገው” የሚባል እውነተኛ ድክረታ! | አቤል ምትኩ (ከአዲስ አበባ)

የፖርቹጋሎች ሁኔታና አዝማሚያ በየመንደሩና በየደብሩ የነበሩትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንት እጅግ እያሳሰባቸው ሄደ:: ሕዝባቸው ሳይጎዳ ትኋኖችን እንዴት እንደሚገላገሏቸው አሰቡ። የመስቀሉን በዓል እንዴት እንደሚጠቀሙበት ዘዴ አመነጩ:: ምሥጢር ማደላደል እየተባለ በየኔታ ፍስሐ ይመራ በነበረው ጉባዔ ላይ፤ ነፍሶቻቸውን ይማርና፤ የሐዲሳት መምህራችን፤ የኔታ ብርሃኑ። የሊቃውንት መጻህፍት መምህራቻን የኔታ ቢረሳው፤ የብሉያት መምህራችን የኔታ ጥበቡ፤ የቅኔ መምሕራኑ የኔታ አንዳርጌና የኔታ አምዴ ሆነው ሲነጋገሩ እንደሰማሁት፥ በገላውዲዎስ ዘመን የነበሩት ሊቃውንት፤ በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ ፱ ከቁጥር ፳ ላይ የተመዘገበው፤ “ለትጻዕ እሳት እምቤተ አቤሜሌክ፥ ከመ ትብላእ አብያተ ሴኬም፡ ወትሜሎም:: ወለእመ አኮ እሳት ትጻእ እምቤተ ሴኬም ወትሜሎም ከመ ትብላዕ ቤተ አቤሜሌክ” የሚለው ንባብ ትዝ አላቸው:: ስሜታቸውን ከንባቡ ጋራ በማገናዘብ “እኛ ኢትዮጵያውያን በአገራችን የ ውጭ ሰዎች የተደጋገመ ግፍ እየፈጸሙብን ነው:: ከየቤታችን እየተጫረች የምትወጣ የዘንድሮው የመስቀል በዓል እሳት፥ በሸርና በሸፍጥ በእርዳታ ስም መጥተው የወረሩንን ፖርቹጋሎችን ትብላ፥ ለአገራችን ለነጻነታችን መታገላችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥቶ ረድኤቱን ከነፈገንም፥ ለዘላለም በፖርቹጋሎች ሥር ተጠቅተን ከመኖርና ለልጆቻችንም የተገዥነትን ውርስ ከማውረስ ይሕች ከየቤታችን የጫርናት እሳት እኛኑ ትብላን” ብለው ቆርጠው ተነሱ::

“የመስቀል በዓል ፖርቹጋሎችን የማይደምር የግላችን ነው:: የምናከብረው ሌሊት ነው:: በበዓላችን የማይደመሩት ፖርቹጋሎች እንቅልፍ ላይ ይሆናሉ:: እናንተ ቱኋኖች ከአገራችን ውጡ፥ እያልን በምናበራው ችቦ ቤታቸውን እያቃጠልን በኛ ላይ የሚያደርጉትን ግፍና፥ በቅኝ ግዛት ለመቀጠል ያላቸውን ረዥም እቅድ ይህችን የመስቀል በዓል በመጠቀም ላንድና ለመጨረሻ ጊዜ መግታት አለብን” ብለው ያቀዱትን በየደብሩ ለሚኖረው አካለ መጠን ለደረሰ ወንድ ልጅ ሁሉ “ትድረስ” ብለው ሊቃውንቱ በቆራጥ መንፈስ አሰራጩት:: መልእክቱ የደረሳቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉም በመተባበር፤ ተግባራዊ አድርገውት አደሩ:: ካህናቱ ለወገን መጎሳቆል ተቆርቁረው ባንድ ልብ እንሙት ብለው መነሳታቸው ያስደነቀው ባለ ቅኔ፦

“ካህን ሞተ ተብሎ አይነግሩም አዋጂ

እንዲህ በየደብሩ መላክ ነበር እንጂ” ብሎ እንደገጠመ ይነገራል:: በነገራችን ላይ ከላይ የጠቀስኩትን ታሪክ መሠረት በማድረግ በደመራ ሌሊት የኔታ አንዳርጌ መወድስ ዘርፈውበት፥ እኛ ተማሪዎችም የሳቸውን ቅኔ እንደ ምሳሌ (ሞዴል) በመጠቀም የሳምንቱ የቅኔ መቁጠሪያችን ሆኖ መሰንበቱን አስታውሳለሁ:: ኢትዮጵያውያን ከወገኖቻቸው አንድ ሰው ሳይጎዳ የደመራውን ችቦ እንደ መሳሪያ በመጠቀም ፖርቱጋሎችን ከአገራቸው አስወጥተው አገራቸውን በራሳቸው ቍጥጥር ስር አድርገዋል።

ይህንም ለማስታወስ በደመራው በዓል “ትኋን ውጪ ቁንጫ ግቢ” ይባላል:: ይህ አባባል የመጣው ያለ ምክንያት አልነበረም። ትኋኗ ስትደፈጠጥ የምታስከትለው ክርፋት፥ የሮማውያንን ቂምና በቀል ለመግለጽ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በቅኔያቸው ሰም አርገው ደጋግመው ተቀኝተዋል። በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ በደረሰባቸው መጠቃት ቂምና በቀል ይዘው በየዘመኑ አጋጣሚ እየጠበቁ እትዮጵያን ለማጥቃት አልቦዘኑም። ወቅትና ጊዜ ብቅ የሚለውን ቂማቸውንም አባቶቻችን ከትኋኗ ሽታ ጋራ ያነጻጽሩታል። “ጥንተ አብሶ” ይሉሐል ይህ ነው:: ካህናቱ በደመራው ዙሪያ ቆመው

“ስማዕ እግዚኦ እለ ኪያከ ይስእሉ::

እግዚኦ እለ ዘንስእለከ ኢንሰተት አላ በስክየት ዲበ ጸላኢነ ነሀሉ::

ሀበነ ዘወትር ጸሎተነ እምኂጠተ ጸላኢ ንትአቀብ::

ተወከፍ ሲሩያነ በምሕረትከ አንጽሕ አብዳነ አጥብብ ወኅጉላነ”(ዘነግሕ):: እያሉ ይጸልዩ ነበር። የጸሎቱ ትርጉም፤ “አቤቱ በቅን ሕሊና የሚለምኑህን ስማ፥ የምንለምንህ እኛም ተሸንፈን እንዳንወድቅ እርዳን:: በወቀሳም በከሰሳም የምንከሰስበት እንዳይኖር ብንከሰስም እንድንረታ እርዳን:: ከጠላት ሸፍጥና ማታለል ነቅተን እንድንጸልይ እርዳን:: በስሕተታቸው ተጸጽተው የተመለሱትን ወገኖች ተቀበላቸው:: አርቆ የማሰብ ችሎታ ያጠራቸውንም ወገኖች ሕሊናቸውን ብሩህ አርግላቸው:: ወደ ጠላት ጎራ በመግባት ከመካከላችን የጠፉትንም ወገኖች ንቃቱንና ማስተዋሉን ስጣቸው” የሚል ነው።

በግራኝ መሐመድ የተጎዳውና የተጎሳቆለው ወገን፥ እንደገና ከፖርቹጋሎች ጋራ ፊት ለፊት በመጋፈጥ እጽፍ ድርብ ጉዳትና ሥቃይ ስለሚደርስበት ህዝባቸውም “ዕቀብ ኩልነ ዘእንበለ ጻሕብ ወዘእንበለ ተመውዖ ወዘእንበለ ማዕቀፍ:: አድኅን አእጋሪነ እምዳህጽ ወአዕይንቲነ እምአንብእ ወነፍስተነ እሞተ ኃጢአት ወደምረነ ምስለ እለ ድኅኑ ብከ በጸሎተ ኩሎሙ እለ እምዓለም አሥመሩከ” የሚለውን ጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው አቀርቡ። (ሊጦን ዘሠርክ) ይህም ማለት፥ “አምላካችን ሆይ! በፍልሚያ ውስጥ ገብተን ስንዋጋ ተደናቅፈን ከመሸነፍ ጠብቀን:: ጠላቶቻችንን ስናሳድድ አንዳልጦን ከመውደቅ አድነን:: እንባ ከማፍሰስና ተዋርዶ ከመሞት አድነን:: ባንተ ታምነው ባንተ መከላከል ከሚድኑት ጋራ ደምረን” ይሉ ነበር።

ድሉን ከተቀዳጁ በኋላ “መዝገበ ጽልመት እንተ ብነ በሥምረተ አቡከ አብራህከ ለነ ዘአውጻእከነ እማዕምቅ ውስተ ብርሃን:: ወወሀብከነ ሕይወተ እሞት:: ወጸጎከነ እምግብርናት ግዕዛነ:: ዘበመስቀልከ አቅረብከነ አምላክ:: አላ ብርሃነ ሀበነ”(መንፈቀ ሌሊት):: እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ:: ማለትም፥ “በጨለማ ውስጥ ለነበርን ለኛ ባባትህ በጎ ፈቃድ የደኅንነት ብርሃን አበራሕልን:: ከጨለማ አዘቅት አውጥተህ ወደ ብርሃን አፋፍ አወጣህን:: ከሞት አድነህ ሕይወትን ሰጠኸን:: ከመገዛትም ነጻ አወጠሀን:: በመሰቀልህ ያቀረብከን አምላክ ሆይ ሕይወትን ሰጠኸን” እያሉ የመከራውን ዘመን ሳይዘነጉ የደመራውን በዓል ማክበራቸውን ቀጠሉ::

ነቢዩ ዳዊት፦ በ(መዝ ፶፱፡፩-፭) ላይ ያለውን

“እግዚኦ ገደፍከነ ወነሠትከነ፥

ቀሰፍከነሂ ወተሣሀልከነ

አድለቅለቃ ለምድር ወሆካ

ወፈወስካ ቁስላ እስመ አንቀልቀለት

አርአይኮሙ ዕጹባተ ለሕዝብከ

ወአስተይከነ ወይነ መደንግጸ” እያለ የተናገረውንም በክስተት መልክ ከተቀባበሉ በኋላ ከዚያ ቀጥሎ ያለው ንባብ፤

“ወወሐብኮመ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ

ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት

ወይድኀኑ ፍቁራኒከ” የሚለውን ዲያቆኑ መስቀሉን ይዞ ከፍ ባለ ድምጽ አሰምቶ እንዲያዜም አደረጉ::

ይህም ማለት “የችቦውን ዘዴ እንደመከላክያ ጋሻ አርገን እንድንጠቀምበት አስተማርከን:: ከጠላቶቻችንም ጋራ ፊት ለፊት ተጋጥመን ጠላት ከሚወረወርብን ጦር እናመልጥ ዘንድ የችቦውን እሰአት እንድንጠቀም ዘዴውን ገለጽክልን” የሚል መንፈስ የያዘ ነው:: ይህ የደመራ ታሪካዊ መነሻና ይዘት ከአብነት ሊቃውንት አበው በጉባዔያቸው ሲናገሩት ብንሰማውና፤ በተብራራ ሁኔታ ለሕዝብ ባይቀርብም፤ ከላይ በገለጽኩት መንገድ አመታዊ ሥርዓት ሆኖ ሲካሄድ ኖሯል::

ሌላም ከደመራው ጋራ የማይረሳ ነገር አለ። እሱም ቁርጥ የሚባል ስም ተሰጥቶት የሚበላው ጥሬ ሥጋ ነው። ቁርጥ የሚባል ስም ተሰጥቶት ጥሬ ሥጋ መብላት የተጀመረውም፤ በዚሁ ዘመን፤ ስንቅ አልቆባቸው የዱር እንስሳት ሥጋ እየበሉ ይዋጉ በነበሩት ወንዶች ነው:: በሌሎች ክፍላተ ሐገሮች የሚደረገው ተመሳሳይ መሆኑንና አለመሆኑን ባላውቅም፥ ባደኩበት አካባቢ ይህንን ስርአት ለመጠበቅ፤ ቁርጥ ሥጋ እንዲበሉ የሚፈቀድላቸው የተዋጊነትን የጀግንነትንና ያርበኝነትን መንፈስ ወራሾች ናቸው ተብለው ስለሚገመቱ ወንዶች ብቻ ነበሩ።

በደመራው በዓልም ዳቦት(ችቦ) አብርተው ከቤት የሚወጡትም ወንዶች ብቻ ናቸው:: ወንዶች ብቻ የሆኑበትን ምክንያት አባቶች ሲናገሩ እንደሰማሁት፥ ከክርስትና ጋራ በተዛመደ ምክንያት ነው። “ብርሃን ዘበ አማን ዘያበርህ ለኩሉ ሰብዕ ለእለ ይነብሩ ውስተ ጽልመት” እንዲል፤ በጨለማ ለነበረው ዓለም ያበራው፥ ያለ ወንድ ዘር፤ ወንድ ሆኖ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። “እመ ብርሃን (የብርሃን እናት) ምሥራቅ (መውጫ)” እያልን የምናደንቃት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም በማሕጸኗ ከደረባት ቅጽበት ጀምራ፤ በሄደችበት ሁሉ ታቅፋ ያቋረጠችው የመከራ ዘመን በደመራው በዓል ይታወሳል:: አጋጣሚ ሆኖ አንድ አባ ወራ (የቤቱ ባለቤት) በሞት ወይም በሆነ ነገር በቤት ውስጥ ከሌለ፥ በደመራው በዓል በእናቱ እቅፍ ያለ ወንድ ሕጻን በእናቱ እጅ ችቦውን (ዳቦቱን) እያበራ ከቤት ይወጣል:: እሌኒ ደመራውን ከፖርቹጋሎች ጋራ በተፈጠረው ታሪካዊ ክስተት ላይ፥ ችቦ እያበራ ወጥቶ ፖርቱጋሎችን የደመሰሰው ወንድ ብቻ ነበር። እሌኒ ብትጀምረውም፤ ወደ አገራችን ተሻግሮ ከመጣ በኋላ፤ ከኢትዮጵያውነት ጋራ ተዳምሮ የያዘው ታሪካዊ ይዘት መልኩን እንዳይለውጥ ሴቶች ችቦ አብርተው ከመውጣት ተቆጥበዋል::

አምና በዘመነ ሉቃስ “የተወደደችውን የጌታን ዓመት እንስበክ” በሚል ርዕስ ባቀረብኳት ጦማር (http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/ethiopian_new_year_zemene_lukas.pd) ስለ መንፈሳዊው አባት ሚና ስገልጽ፥ “አምላኩን ወዶ ለማስወደድ፥ ሃይማኖቱን አክብሮ ለማስከበር፡ በህዝባዊ ፍቅር ልቡ የነደደ፥ ቅዱስ ተብሎ የተሰየመ አባት፡ የምሕረት ምንጭ በሆነው አምላክ ስም፡ በሚያቀርበው የምሥራች ቃል:: ዘመኑን ባርኮ ለሥጋውያን መሪዎች አውደ ምህረቱ ይለቅ ነበር” እንዳልኩት፥ በደመራው በዓል ለሚቃጠለው የእሳት ምንጭ በካህኑ እጅ ያለችው ችቦ ናት:: መጀመሪያ “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” ብሎ የሚጸልየው ያካባቢው ካህን የመጀመሪያዋን እሳት በእጁ ባለው ችቦ ላይ ይጭራታል::

ካህኑ በእጁ ላይ ካለችው ችቦ የአገር መሪው በራሱ ችቦ እሳቱን እንዲለኩስ ይፈቅድለታል:: የአገሪቱ መሪም በደመራው ላይ መለኮሱን ይመራል:: በተዋረድ የተከበሩ የአገር ሽማግሌዎች ይቀጥላሉ:: ከዚያ ጎረምሳው፥ ኮበሌው ወጣቱ እሳቱን በችቦው እየተቀባበለ ወደ ደመራው እየወረወረ የጀግንነት ምልክቱን ብትር ከፍ አድርጎ ይዞ ሆ! እያለ ደመራውን ይዞራል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ኢትዮጵያዉያን አይደሉምን ? ታዲያ ለምን?

ይህ የደመራ በዓል፥ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሐረግ እየዘመተ በቅኝ ገዥዎች ሳይቆራረጥ በደማችን በምግባችን በስሜታችን ሳይቀር ተቀርጾ ለረዥም ዘመን በመቀጠሉ፥ የታሪኩና የባሕል ይዘቱ እያሰፋ እስከኛ ዘመን ደርሷል::

ትውልድ በውጭም ሆነ ባገር በቀል ከሀዲዎች ካልተወረረ፥ ካልተበታተነ፤ ቋንቋውን ታሪኩንና ባሕሉን እንዲረሳው ካልተደረገ፥ ታሪኩ በግልጽ እየተነገረው በያመቱ የደመራውን ሥርዓት በሸፍጥ መጋረጃ ሳይሸፈን ከቀጠለ፥ ዘመኑ ያፈራውን ዘዴና ጥበብ ከባህሉ ጋራ በማስማማት እየተፈራረቀ የሚገጥመውን ሁሉ መከራና ስቃይ መቋቋም ይችላል። :

የመጀመሪያዋን የደመራውን እሳት የሚለኩሳት ማነው?

“ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” የሚለውን የጸሎት ምንባብ ከፍ ባለ ድምጽ ለህዝባ ካሰማ በኋላ፤ የደመራዋን እሳት ባርኮ ለአገሪቱ መሪ የሚያቀብላት ካህን ማነው? ከካህኑ ተቀብሎስ የደመራውን እሳት የማቃጠሉን ስርአት የሚመራው የአገሪቱ መሪስ የትኛው ነው? ሥርዓቱን ተከትለው በእጃቸው ያለውን የደመራ ችቦ እያቀጣጠሉ ወደ ደመራው መጨመር የሚችሉትስ ሽማግሌዎች የትኞቹ ናቸው? ሆ! ብሎ የሚከተለውስ ወጣት የቱ ነው?

መተርጉማን አባቶች በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፮ ላይ “ስድስቱ መሳብክት እለ እብን በዘ ያጥህሩ ቦቶን” ተብሎ በሚነበበው አረፍተ ነገር፥ ክርስቶስ የቃናውን ውሐ ወደ ወይን የለወጠባቸው ጋኖች የተሠሩበትን “ዕብነ አልማስ” የሚባለውን ማዕድን ያስታውሱበታል። ይህ የከበረ ማዕድን ድንጋዩን ሰብስበው ሲያቀርቡለት ያቀልጠዋል:: በዚህ የማዕድን ድንጋይ ሌላውን ድንጋይ እያነጡጡ፥ እየላጉ፥ በፈለጉት ቅርጽ ይሠሩታል:: የተዋህዶው ነገረ መለኮት፤ በክርስቶስ ፍጹም ትስብእትና ፍጹም መለኮቱ ውህደት ላይ የተመሰረተውን በምንም ነገር የማይናወጸውን የታነጽንበትን ኦርቶዶክሳዊ እምነታችንን ባንድምታ ትርጉሙ ይገልጸዋል። ሰው ከምንቼትነትና፥ ከቶፋነት እየተላቀቀ ወደ ጋንነት ለመድረስ ማንጠጫ፥ መላጊያና መቅረጫ “ዕብነ አልማስ” አለው:: በሊቃውንቱ ግንዛቤ “ዕብነ አልማስ” ማለት፦ መለኮቱን ከሥጋችን ጋራ ደምሮ ፤ እንደገና ያበጀንና የሰራን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::

ከክርስቶስ በኋላ ይህንን ያስተማሩ ሐዋርያት ናቸው። ቀጥሎም፤ ቅዱስ አትናቴዎስ “ቅትራተ ሐጺን ዘኢያንቀለቅል” ብሎ የገለጻቸው በእምነታቸው በሞራላቸው ሕዝቡ አምኖ የሚሰማቸው ካህናትና በእውቀትና በሞራላቸው ታንጸው በቤተ ክርስቲያን ዙርያ የተሰለፉ ያገር ሽማግሌዎች ናቸው” ይላሉ ሊቃውንት አበው:: ኢትዮጵያውያን አባቶች ፤ እውነትን እየፈለጉ ያለፉትን፤ ከእሌኒ በፊት የነበሩትንና ከዚያም ወዲህ በዓለም ያሉትን ሁሉ አርበኞች (ዕብነ አልማሶች) እያልን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለውናል:: ለምሳሌ “ተዘከሮሙ እግዚኦ ለኩሎሙ አበዊነ ወአኀዊነ ወአኃቲነ እለ ኖሙ ወአዕረፉ በርትዕት ሃይማኖት ወደምር ነፍሳቲሆሙ ውስተ ሕጽነ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ” ማለትም፥ “ሳይወላውሉ በቀናች እምነት ጸንተው ለወገናቸው ለነጻነታቸው መስዋዕት እየከፈሉ ያለፉትን አባቶቻችንን፥ ወንድሞቻችንን እናቶቻችንና እኅቶቻችንን በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ ሕጽን አንድ ላይ ሰብስብልን” እያልን በቅዳሴያችን እንድናስባቸው ነግረውናል።

ያዕቆብ እግዚአብሔርን ባናገረበት ቦታ ላይ ሐውልት ያቆመበትን ምክንያት ለመግለጽ ቦታውን ቤተ-ኤል (የእግዚአብሔር ቤት) እንዳለው፥ እኛም አባቶቻችን በደመራው ላይ የመሰረቱትን ታሪካዊ ሀውልት የሚገልጽ እውነተኛውን ህዝባዊ ታሪክ ከመናገር በቀር፤ ትላንት ሌላ፤; ዛሬ ሌላ፤ የሚናገሩና ሸፍጠኞች በህዝቡ ልቡና ላይ የራሳቸውን ተልእኮ እንዳያንጸባርቁበት ልንጠነቀቅ ይገባል።

“ወለነኒ አድኅነነ እምኩሉ አበሳ ወመርገም ወእምኩሉ ጌጋይ ወእምኩሉ ክሕደት ወእምኩሉ መሐላ በሐሰት ወእምኩሉ ግዘት ወእምተደምሮ በዕልወት ወርኩስ ምስለ ዓላውያን ወአረማውያን” በማለት ከከሐዲዎች ከሸፍጠኞችና ከአስመሳዮች ጋራ ከመደመር እራሳችንን እንድንጠብቅም መጽሐፈ ቅዳሴያችን በጽኑዕ ያሳስበናል::

የደመራውን ታሪካዊ ይዘት አብራርተን መናገር ካልቻልን፤ ከደመራ ሆታ ባሻገር የደመራውን ምሥጢር ለመረዳት የተሳናቸው ልጆች ይፈጠራሉ። የደመራውን ችቦ ባርከው እሳቱን የሚለኩሱ ካህናትም፥ ከሆታው ባሻገር ያለውን የደመራውን ምሥጢር ከሊቃውንት አበው ካልሰሙት፥ ለደመራው ምሥጢር ተቃራኒ የሆኑትን ቅነሳንና ከፈላን ለሚያርምዱ አጫፋሪ በመሆንም ሆባዮች ይሆናሉ:: (በግዕዝ ሆባይ ማለት ዝንጀሮ ማለት ነው) የደመራውን እሳት የሚጭሩ ካህናት፤ የደመራው እሳት፤ ለደመራው ታሪካዊ ይዘት ተቃራኒ ሆነው የተከሰቱትን የሚያቃጥል፥ ከሰልና አመድ የሚያደርግ፥ በእምነታቸው በሞራላቸው ጸንተው ለቆሙት ኢትዮጵያውያ ግን የሚያበራ፥ የሚያሞቅና የሚያደምቅ መሆኑን የተረዱ፤ መመስከር የሚችሉና የበቁ መሆን አለባቸው። :

ስለ ደመራችን ስናወጋ፤ ከችቦውና ከደመራው ጋራ በመዳመር ትልቅ መታሰቢያ ያላት፤ በአጥርና በዛፍ ስር የምትበቅለዋ በአማርኛ አሽክት በትግርኛ ጸጎጎት የምትባለዋ ሐረግ መረሳት የለባትም። ይሕች ሐረግ በዚያ ዘመን ትልቅ ሚና የተጫወተች ናት:: ፓርቹጋሎች አንድነታችንን አፍርሰው ሊለያዩን አይችሉም በሚል ጽኑዕ ውሳኔ የተስስማማ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ ልዩ መግባቢያ ሆና አገልግላለች:: እኔ ካገር ቤት የመጨረሻውን ደመራ አክብሬ ወደ ደብረ ሊባኖስ እስከሄድኩበት ዘመን ድረስ ልጆች ሆነነ በራሳችን እናደርጋት ነበር:: እናቶችና ሽማግሌዎች ደግሞ ለቁርጥማት መድኃኒትነት አላት እያሉ በደመራው አመድ ላይ ጎዝጉዘው ይቆሙባት ነበር::

ቁርጥማት ማለትም፤ የቆራጥ ጀግኖችን ኃይል የሚፈትን፤ የቆራት ሊቃውንት ጭንቅላት የሚጠይቅ ፈተና ማለት ነው ይላሉ። ይህም ከቁርጥ ሥጋ ጋራ የተገናኝ ነው።

የደመራው እንጨት እርጥብና ደረቅ ነው:: “በርጡብ እጽ ለእመ ኮነ ከመዝ እፎ በይቡስ” እንዳለው ክርስቶስ፥ ርጥቡ እንጨት ባሕርዩን፥ እሱነቱን ያልቀየረ፥ በቀላሉ ለእሳት ያልተጋለጠ ወገንን ይገልጻል። ደረቁ እንጨት ባሕርዩን የቀየረውን፥ እራሱን ከወገኑና ከታሪኩ አግልሎ አድር ባይና ወላዋይ የሆነውን፥ በቀላሉ የሚሸነፈውን ገለባ መሳይ ባህርይ ያለውን ደካማ ዜጋ ይወክላል:: በመከራ ጊዜ ሁሉም እየተቀላቀለ መለየት ያስቸግራል። ይህን ለመግለጽ፦

“አጓጉረውና እርጥቡን ከደረቅ፥

እዚያው ጤሶ ጤሶ እዚያው ነዶ ይለቅ” የሚለው ሽለላ (ቅራርቶ) የመነጨውም ከዚህ ነው ይባላል::

እንግዲህ የደመራው በዓል ይህን አስደናቂ ምሥጢር ያዘለ ከሆነ፥ “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” ብሎ ይህን ምሥጢር በቃሉ አስተምሮ፥ በተግባሩ አከናውኖ የደመራዋን እሳት ችቦ የሚባርካት በዘመናችን የትኛው ካህን ነው? ከካህኑ ለኩሶ ደመራውን በመጀመሪያ የሚያቀጣጥለው መሪስ የትኛው ነው? ወጣቱንስ በየመንደሩና በየቤቱ በዚህ ኢትዮጵያዊ እምነት ታሪክና ባሕል የሚቀርጽ፥ የሚልግና የሚያስተካከል የትኘው ያገር ሽማግሌና የቤተ ሰብ ሐላፊ ነው?

ዛሬ ከመቸውም ዘመን በከፋ ሁኔታ የተዋሕዶውን ሃይማኖት አፍርሰው፥ በፖርቹጋላዊ ከፈፋይ መንፈስ ለመተካት የሚታገሉ አስመሳዮች ደፍረው ወደ ቤተ መቅደሳችን የገቡበት ዘመን ነው። ከሃይማኖቱ፥ ከታሪኩና ከባሕሉ ይልቅ ለመንደርተኝነት ቅድሚያ በመስጠት ኢትዮጵያን በማመሳቀል ላይ ያለው መንግስት በፖርቱጋሎች መንፈስ የሚመራ መሆኑን እያወቁ ድጋፍ ለመስጠት ሽንጣቸውን ገትረው የተነሱ ጳጳሳት የተከሰቱበት ዘመን ነው። ዛሬ በአገራችን ላይ የሚካሄደውን ጠቅላላ ሁኔታ ስንመለከተው “ዓኾ ዓኾኋይ ሆይ ሆያዬ ንጎናይ በርሆ” በማለት የአድዋ ሰዎች ያባረሩት ፖርቹጋላዊውን መርሆ አይመስልም ብሎ ማስተባበል የሚችል ማነው?

እነዚህ ካላይ በጥያቄ ያቀረብኳቸው መጠይቆች፥ የወቅቱ መጠይቆች ናቸው ብለን ተስማምተን ከተቀበልናቸው፤ የቀደሙ ሊቃውንት አበው በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ ፱ ከቁጥር ፳ ላይ የሰፈረውን “ለትጻዕ እሳት እምቤተ አቤሜሌክ፥ ከመ ትብላእ አብያተ ሴኬም፡ ወትሜሎም:: ወለእመ አኮ እሳት ትጻእ እምቤተ ሴኬም ወትሜሎም ከመ ትብላዕ ቤተ አቤሜሌክ” የሚለውን ተመርኩዘው፥ “እኛ ኢትዮጵያውያን በራሳችን አገር የተደጋገመ ግፍ እየተፈጸመብን ነው:: ይህች ከየቤታችን እየተጫረች የምትወጣ የደመራ እሳት፥ በሸርና በሸፍጥ መጥተው የወረሩንን ፖርቱጋሎችን ትብላ፥ ለአገራችን ለነጻነታችን መታገላችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥቶ ረድኤቱን ከነፈገንም፥ በፖርቱጋሎች ሥር ተጠቅተን ለዘላለም ከመኖርና ለልጆቻችንም የተገዥነትን ውርስ ከማውረስ እኛኑ ትብላን” ብለው ቆርጠው የተነሱበትን ያባቶችን መንፈስ ልንቃኘው ይገባናል::

የጥንት ኢትዮጵያውን ችቦውን አንድ ላይ አስረው፥ እንጨቱን አንድ ላይ ደምረው ያቃጠሉት፥ ቅድስት እሌኒ የተደበቀውን መስቀል ለማግኘት በደመራው እንደተጠቀመችበት፤ በዘመናቸው የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት ነበር። ዛሬ እኛ እንደምናደርገው በጎሳ በቋንቋ፤ በሃይማኖትና በተለያዩ የፖለቲካ ትርጓሜ በመለያየት አልነበረም:: አሁን በምናየውና በምንሰማው መልክ ደመራውን የማናስታውሰው ከሆነ፤ ትርጉሙንና ይዘቱን ቀይሮ የቀረበ ድራማ እንዳይሆን ልናስብበት ይገባናል። በተረፈ “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” እያሉ የደመራውን እሳት የሚጭሩ ካህነት፥ “ትኋን ውጭ፡ ቁንጫ ግቢ” እያሉ የደመራውን ችቦ የሚያበሩ ሽማግሌዎች፥ በጽኑእ ወኔና ፍላጎት የደመራውን መንፈስ በሆታ የሚያስተጋባ ትውልድ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ እንዲፈጠር እንጸልይ: ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ::

Share