አጽማቸውን የፈለሰው መላከ ብርሃን አድማሱ  ከአምስቱ ዘመን  ተጋድሎ በኋላ   ክፍል አንድ

ቀሲስ አስተርአየ (nigatuasteraye@gmail.com) መስከረም ሁለት ሺህ አስር ዓ.ም

የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውን እንመሰክራለንዮሐ 311)

ቀሲስ አስተርዕየ

ከዚህ በፊት በተከታታይ በወጡት ጦማሮች ተዋጊ ፋኖዎች በእነ በላይ ዘለቀ፣ መንገሻ ጀንበሬ፣ ራስ ሀይሉ በለው፣ በበዛብህ ነጋሽና ሌሎችም የየጦር መሪነት፤ አርበኞች ካህናት በእነ ሊቀጠበብት አድማሱ ጀንበሬ፣ መላከ ሰላም አለማየሁ ሻሾና ሌሎችም ካህናት አስተባባሪነት፤  በእነ ክቡር ሀዲስ አለማየሁ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴና ሎችም አርበኞች ደራስያን አስተማሪነትና ቀስቃሽነት እንደዚሁም በእነ ራስ ሀይሉ ተክለሃይማኖት የጦር አማካሪነትና የጣልያንን ምስጢር አውጪነት የተፈፀመውን የጦር ጀብዱና የተገኘውን ድል ጨልፌ አቅርቤአለሁ፡፡ በቀጣይ ጦማሮቼ ደግሞ ሊቀጠበብት አድማሱ ጀንበሬ ከድህረ ጦርነት በኋላ የፈፀሟቸውን ገድሎች ለማሳሰብ አቀርባለሁ፡፡

ከድል ማግስት የሊቀጠበብት አድማሱ ጀንበሬ ለሱባኤ ገዳም መግባት

ሲራክ ሰሎሞን በተናገረው መሰረት በቤተክርስቲያናችንና በባህላችን ለእውነት፣ ለፍትህና ላገር  በጀግንነት ለተሰዋ መታሰቢያ ይደረግለታል፤ ገድልና ድርሳንም ይጻፍለታል።

“የሞተን አትርሳ፤የወደቀን አንሳ”

እየተባለም በሚነገረውም ማሳሰቢያ አርበኞች የፈጸሙት ገድል ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፡፡  በህይወት ዘመናቸው የሰሩትን ለመዘከር ወይ ለማስታውስ ለሞቱ ሰወች ተዝካር ይወጣል። በህወት ዘመን የሰሩትን ለመቃኘት ሳይሞቱ የቁም ተዝካር ይወጣል። ወደ ገዳም የሚከደውም፦  “

እግዚኦ ሰማእነ በእዘኒነ።

ወአበዊነህ   ዜነውነ።

ግብረ ዘገበርከ በመዋዕሊሆሙ በመዋዕለ ትካት (መዝ 43፡1)

ይህም ዜማ ለብሶ የቀረበው የግእዙ ትርጉም፦አባቶቻችን በዘመናቸው ሲያደረጉት ያየነውንና ከነሱ በፊት የነበሩትም  አባቶች ያደረጉትን አንተም ያደረክላቸውን ረድኤት  ሰማን፤  ማለት ሲሆን፦ ያባቶቻቸውን ምሳሌነት መከተላቸውን ከፈጣሪያቸው ፈቃድ አለመውጣቸውን ለመፈተሽና ከሞት ተርፈው የቀረቻቸውንም ጥቅት ዘምን እንዴት እንደሚያቋርጧት እንዲያስቡ የሚያስገነዝብ ነው።

በዚህም መሰረት ሊቀጠበብት አድማሱ  ጣሊያን ተባሮ ጦርነቱ ሲቆም በጦርነቱ ወቅት የተረሸነውን፣ ገደል የተወረወረውን፣ ከእነ ቤቱ የተቃጠለውን፣ የቆሰለውን፣ የተሰበረውንና በመንፈስ የተጎዳውን ሕዝብ በጾሎታቸው እያሰቡ እርም ለማውጣት፤ ብርታት  የሰጣቸውንም አምላክ ለማመስገን፤ የወደፊት ቀሪ ዘመናቸውንም እንዴት እንደሚፈጽሙት ለመወሰን  ከዲማ በታች ግርኛ ከሚባለው ቆላማ ቦታ ከደብረ ጥሞና ገዳም ለሱባኤ ገቡ።

ሊቀጠበብት አድማሱ  ወደ ገዳም የገቡት ለማንም ሳይናገሩ ነበርና መላከ ብርሃን ተብለው ለብቸና ጊዮርጊስ ታላቅ ደብር መሪ ሆነው እንዲሰየሙ በሊቃውንቱና በአዛውቱ ተመርጠው  ቢፈለጉ ጠፉ፡፡  በዚያን ዘመን  በብቸና ቅዱስ ጊዮርጊስ  ደብር የሚሰየሙት ሊቃውንት  ከመላው ጎጃም ካሉት ሊቃውንት በእውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል ልቆ የተገኘ ነበር፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ጅብ ከሄደ ዉሻ ጮኸ”  ማደናገሪያ እንጅ ህዝባዊነት አይደለም !!! - ማላጂ

ከብዙ ማፈላለግ በኋላ ሊቀጠበብት አድማሱ ደብረ ጥሞና ከሚባለው ጠፍ ቦታ ካለው ገዳም እንዳሉ ተደረሰበት፡፡ ሊቃውንቱና አዛውንቱም  ደብረ ጥሞና ገዳም ሄደው አገኟቸው፡፡ ሊቃውንትና አዛውንትም ሊቀጠበብት አድማሱን በሌሉበት መላከ ብርሃን ብለው እንደሰየሟቸውና ደብሩንም እንዲመሩ ፈቃዳቸውን ጠየቋቸው፡፡ ሊቀጠበብት አድማሱ በዚያን ዘመን ወጣት ነበሩ፡፡

በዚያ ዘመን በታላላቅ አድባራት የሚሰየሙት እንደ ዛሬው የሰንበት መምህራን በሀሰት ስም እየተሸፈኑ የግል ዝናና ብልጽግና  ለማትረፍ እራስን እያብለጨለጩ በሚደረግ እሽቅድምድም አልነበረም።

በእድሜ የበሰለ፣ በእውቀት የላቀና በሥነ-ምግባር እጅግ የታነፀ ስለነበር  ሊቀጠበብት አድማሱ ይህን ስርአት በማክበር”ይህ ሀላፊነት ከእኔ አቅም በላይ ስለሆነ  የተሻለ ፈልጉ” አሉና  የተላኩትን ካህናትና አዛውንት አሰናበቷቸው፡፡

ተሰናበተው የተመለሱት ካህናትና አዛውንትም ሊቀጠበብት አድማሱ የነገሯቸውን ለህዝቡ አካፈሉ፡፡ ሕዝቡም ተፈልገው በመገኘታቸው ተደሰተ፡፡ የተደሰተው ሕዝብም “ ከእርሳቸው የበለጠ በእውቀትና በመንፈስ ልእልና የታነፀ፤ ከእርሳቸው በላይ ቤተክርስቲያናቸውን በትጋት ያገለገለ፣ ከእርሳቸው በላይ ለፍትህና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት በአርበኝነት የታገለ ስለሌለ ከእግራቸው ወድቀን እናመጣቸዋለን ” ሲል ወሰነ፡፡

በዚያን ዘመን የብቸና ጊዮርጊስ ደብር መሪ የሚመረጡት ሊቃውንት በንጉሡ መጽደቅ ስለነበረባቸው ሕዝቡ ለንጉሡ አመለከተና መሪነታቸውን አፀደቀ፡፡ መሪነታቸውን በንጉሡ ካፀደቁ በኋላ ከደብሩ የተውጣጡ ሊቃውንታና አዛውንት እንደገና ሱባኤ ከገቡበት ገዳም ሄደው ከእግራቸው ወድቀው ለምነው እሽታን አገኙ፡፡ ሊቃውንቱና ሕዝቡም በዓለ ሲመቱ በ1934 ዓ.ም እንደሚከናወን ወስኖ የተላላቅ አድባራትና ገዳማት ሊቃውንትና አዛውንት እንዲገኙ ጥሪውን አስተላለፉ።

በብቸና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሥርዓት ከጀግንነት የተለየ ሊቅ  ከዜግነት የተነጠለ እምነት የሞተ ነው ተብሎ ስለሚታመን ሕዝቡ በሊቀ ጠበብት  አድማሱ ጀንበሬ መሰየም ተደስቶ  የብቸና ጊዮርጊስ  ደብር እንደገና ተሰራች አበበች፤ አፈራችእያለ ደስታውን ገለጠ፡፡  በብዓለ ሲመቱ ቀንም ከየደብሩ የተጋበዙት ሊቃውንት፤ አዛውንትና ህዝቡ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ሞልተው ሊቀጠበብት አድማሱን በዝማሬ ተቀበሏቸው። ሊቀ ጠበብት አድማሱም የወርቅ አክሊል ደፍተው፤ የወርቅ ጫማ ተጫምተውና የወርቅ ለምድ ለብሰው መላከ ብርሃን ተብለው በብር ወንበር ላይ ተሰየሙ።

ሊቃውንቱት፣ ካህናቱና አዛውንት መላከ ብርሃን በእሳት የተፈተኑ ሊቅ መሆናቸውንና በዚህ ታላቅ ደብር መሰየማቸው  የሚገባቸው መሆኑን ለመግለጽ ተመስጠው ፦

መኑ ይቀውም ውስተ መካነ መቅደሱ፤

ዘንጹህ ልቡ ወንጹህ እደዊሁ፤

ወዘኢነስአ ከንቶ በላዕለ ነፍሱ” (መዝ 23 3) በሚለው  ዲያቆን በሚያዜመው ምስባክ  ስርአተ ሲመቱን ጀመሩ።

በዓለ ሲመቱ የተጀመረበት ዜማ፤  ወቅቱን ባገናዘብ መንፈስ ደአማርኛ ሲመለስ”የህሊናውን  ነጻነት  በግብር ካስመሰከረ፤ በወገኑና ባገሩ  እንከን ፈፀመ ተብሎ ከማይከሰስና ከማይወቀስ  ይልቁንም የስነ ህሊና ምንጭ ከሆነው ከሊቀ ጠበብት አድማሱ በቀር በዚህ ቅዱስ ቦታ ሊሰየም የሚችል ማነው? ”  የሚል ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:     ህወሃት የመከላከያ ሠራዊቱን  የገቢ ምንጭ በማድረግ ይጠቀምበታል፦

በዓለ ሲመታቸው የሚከበርላቸው መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ግን በጣልያን ተረሽነው በየዱሀና በጎፍጭማ ገደል የተጣሉት አርበኞች ካህናት፣ የጣሊያንን ምሽግ ሲደረምሱ ያለቁት ፋኖዎች፣ በየፍልሚያው የወደቁት አርበኞች፣ ጣልያን ቤት ሲያቃጥል አብረው የተቃጠሉት  ህጻናትና አሮጊቶች በዓይነ-ህሊናቸው መጡባቸውና ለሳቸው ክብር የሚሰበከውን ምስባክ የጀመረውን ዲያቆን አስቁመው ከዚህ በታች የሰፈረውን እንዲያዜም አዘዙት፡፡

ነብርኩ ትኩዝየ  ወሀጣእኩ ዘይናዝዘኒ

ወወደዩ ሀሞተ ውስተ መብልእየ

ወአስተዩኒ ብሂአ ለጽምየ”(6820)

ትርጓሜውም የሚያረጋጋኝ አጣሁ የምመገበው ምግብ እንደ ሬት መረረኝ። የምጠጣውም ውሀ እንደ ሀሞት ኮመጠጠኝ ማለት ነው።

ይህንን የሐዘን መዝሙር ሕዝቡና ካህናት እየተቀባበሉ ሲያዜሙ መላከ ብርሃን በጦርነቱ ወቅት የረገፈው ሕዝብ ትዝ አላቸውና ሰቅስቅ ብለው አለቀሱ፤ እንባቸው በፊታቸው እንደ ጎርፍ ፈሰሰ። ለበዓሉ የታደመው ሕዝብ፣  ካህናቱና  ሊቃውንቱ ስሜትም ወደ ሀዘን ተለወጠና ሁሉም በእንባ ተራጨ፡፡

ለእርሳቸው ክብር መግለጫ እንዲሆን የተዘጋጀውን ቀን በጦርነቱ ወዳለቁት ወገኖቻችን እርም ማውጫና የተዝካር ቀን ለወጡት። የደስታ እለት እንዲሆን የታሰበው ቀን የቀብር ቀን መሰለ፤ ጠላትን ሲፋለም የረገፈው ሕዝብም በዚች ቀን ታሰበ፤ ተዝካሩ ወጣ፡፡

ረዘም ላለ ጊዜ ሕዝቡ ተላቀሶ ጸጥታ ከሰፈነ በኋላ መላከ ብርሃን ስሜታቸውን ገተውና እንባቸውን ጠርገው ሕዝቡን አረጋጉ።  ከዚህ በታች የሰፈረውን አጪር ንግግር አደረጉ።

ጠላት ወደ አገራችን ከገባበት ደቂቃ እስከ ለቀቀባት ቅጽበት የሞቱትን ጀግኖች ልንመልሳቸው አንችልም። ስለነሱም ስናለቅስ አንኖርም። ነገር ግን እንደነሱ እስክንሞት ድረስ ልናደርገው የሚገባን ግዴታና ሀላፊነት ማሰብ፣ መዘጋጀትና መፈፀም አለብን፡፡ ሹመትና ሞት አንድ ናቸው ይህንን ሹመት ስቀበል እንደ ሞትኩ ነው የምቆጥረው፡፡  ለፍትህና ለነፃነት እንደረገፉት ወገኖቼ በአካል አልሞትኩም። ይሁን እንጅ በዚህ ቦታ ለዚህ ታላቅ ሀላፊነት ስታሰለፉኝ እንደ ሙት እንደ ገነዛችሁኝ እረዳለሁ ገንዛችሁ ያስረከባችሁኝ ሀላፊነት ብሰራበት ለዘላለም ህይወት ባልሰራበት ለዘላለም ሞት ሚያዘጋጀኝ ነውና ጸልዩልኝ  አሉና ተደፍተው መሬቱን  በግንባራቸው ነኩ። በግንባራቸው ከተደፉበት መሬት ተነስተውም  “ጣሊያን ያፈረሰውን የደመሰሰውን መገንባት፤ ያረከሰውን መቀደስና  የደፋብንን አተላ መጥረግ ይኖርብናል፡፡ ሲታገሉ የሞቱትን ሰማእታት የምናከብራቸውና ወሮታውን የምንከፍላቸው የሞቱለትን አላማ ስንጠብቅና ለወጣቶቹም አስተምረን እንዳይረሷቸው ስናገርግ ነው ብለው ንግግራቸውን ፈፀሙ፡፡ በበዓሉ ሢመቱም ፍፃሜ  የደብሩ ሊቃውንትሲመቶ  ነአምን እምአርያም። ይሰግዱ ሎቱ ካህናት ማለትም “ዛሬ የተከናወነው ሲመት አምላክ  ለፈቀደለት ነው፤ የተሾመውም ለቦታው የበቃ ነውና እንታዋለን”  እያሉ በደስታ ዘመሩ፤ አሸበሸቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሃይማኖት፤ እምነትና ፖለቲካ፤ ሕዝብ አደናጋሪ የዘመኑ ውዥንብር

በተቃራኒው ዛሬ ለአገራችንና ለቅድስር ቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ የውለታ ሰው ያድማሱ ጀንበሬ አጽም  ሲፈልስ፤  እራሳቸው መላከ ብርሃን አድማሱ ከባእዶች ግብጻውያን ባላቀቁት መንበር ላይ የተቀመጡ ጳጳሳት አፋቸውን አፍነው ጪጭ ሲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ይታዘብና ይህንንስ ዘመን ከየትኛው ዘመን ጋራ ያንጻጽረው ይሆን?

ወጣቶች ሆይ፡ እንደ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የመሳሰሉ ቀደምት አባቶቻችሁ ሰርተው አልሰራንም፤ ችሎታው እውቀቱና ብቃቱ ሲኖራቸው ችሎታና ብቃት የለንም እያሉ ከግል ክብርና ጥቅም የሚሸሹ ነበሩ፡፡

ዛሬ ግን ዘር እየቆጠሩ፣ ከምእመናን በዘረፉት ገንዘብ እንደ ዘመኑ ፖለቲካ የምርጫ ቅስቀሳ እያኪያሄዱና ጉቦ እየሰጡ በተሰማሩ ጳጳሳትና የቤተክርስትያናችንን ስነ ሁለንተና ባልተገነዘቡ የግል ክብርና ጥቅም በማሳደድ ላይ ባሉ የሰንበት ተማሪዎችና ቆሞሳት  ቅድስት ቤተክርስትያናችን መወረሯን ተረዱ እንጅ፤   እንደ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የመሳሰሉትን የቀደሙ መንፈሳውያን አባቶቻችሁን በዚህ ዘመን ከምታዩን ጋራ ደምራችሁ በማየት ቤተ ክርስቲያናችሁን ከመንቀፍ ተጠንቀቁ!

መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የብቸና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር መሪ ከሆኑ በኋላ የፈፀሟቸውን ገድሎች በምንቃኛቸው ጦማሮች እንገናኝ፡፡

 

 

በፊት የተፃፉትን ጦማሮችን ለማንበብ እነዚህን ቦታዎች ይጎብኙ፡-

ክፍል አንድ ፡-የመላከ ብርሀን አድማሱ ጀምበሬና የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ አጽም ፍልሰት

http://www.mereja.com/amharic/542371 ወይም http://amharic.abbaymedia.com/archives/33517


ክፍል ሁለት፡ -አጽማቸው  የፈለሰው መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ማናቸው

http://www.mereja.com/amharic/542371 ወይም https://zehabesha.info/?p=79344

 

ክፍል ሶስት፡ አጽማቸው የፈለሰውመላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬአምስቱ ዘመን ተጋድሎ

http://amharic.abbaymedia.com/archives/34806

 

ክፍል አራት፡ የአድማሱ ጀንበሬ፣ አለማየሁ ሻሹና ራስ ሀይሉ የአምስቱ ዘመን ተጋድሎ ክፍል አራት

http://www.mereja.com/amharic/544553

Share