September 11, 2017
48 mins read

ድርድር ከወያኔ ጋር? የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና መጪው ጊዜ! (ለውይይት መነሻ) – ባይሳ ዋቅ-ወያ

ይህንን የግል አስተያየቴን በጽሁፍ ካማስፈሬ በፊት ዛሬ አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታና የወደፊት ዕጣዋ ምን ሊሆን ይችላል በሚለው ሃሳብ ላይ ለረጅም ጊዜ በአዕምሮዬ ሳወጣና ሳወርድ ቆይቻለሁ። እንደኔው ጉዳዩ የሚያሳስባቸው ብዙ እንዳሉም ስለማውቅ ጭንቀቴን በውስጤ ዓምቄ ከምኖር ባጋራቸው ምናልባትም በውይይት ሂደት ወደ አንድ የጋራ መፍትሄ ልንደርስ እንችላለን ብዬም ስላሰብኩ ይህንን ለውይይት መነሻ እንዲሆነን ያህል ለመጻፍ ወሰንኩ። ዓላማዬም በተበታተነ መልኩ በየቦታው የምንወያይባቸውን ያገራችንን የፖለቲካ ቀውስ ከተቻለ ባንድ መድረክ ላይ በማምጣት ቅርጽ ያለው ውይይት እንዲካሄድበት ነው። በመሆኑም ይህ ጽሁፌ ውይይቱ በምን ዙርያ መካሄድ እንዳለበት ለመጠቆም እንጂ ሳይንሳዊ ጥናት ስላልሆነ ራሱ የውይይት ነጥብ እንዳይሆን ከወዲሁ ለማሳሰብ እወዳለሁ። የማቀርባቸው ሃሳቦች ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ ናቸው ወይም ሊከሰቱ ይችላሉ የሚል መቶ በመቶ የሆነና የተረጋገጠ ሂሳባዊ ስሌት የለኝም። ከፊት ለፊታችን የተጋረጠብንን ቀውስ አሸንፎ በድል አድራጊነት ለመወጣት ሂሳባዊ ስሌት ቢኖርማ ኖሮ ውይይትም ባላስፈለገም ነበርና!

የዚህ ጽሁፌ ጭብጥ፣ አገራችን አደገኛ ወደ ሆነ የርስ በርስ ግጭት እያመራች እንደሆነ የሚጠቁሙ ቅድመ ሁኔታዎች እየታዩኝ ስለሆነና ያንን አደጋ ደግሞ ለማስወገድና ሰላምና መረጋጋትን አምጥቶ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ኃላፊነት የሚሰጠውን የሽግግር መንግሥት የማቋቋም አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዕውን ሆኖአል የሚለው ነው። ይህን የሽግግር መንግሥት መመሥረት ደግሞ ተግባራዊ ለማድረግ በመጀመርያ ደረጃ ተቃዋሚ ኃይሎችና ወያኔ ለድርድር ለመቅረብ ፈቃደኛ መሆነ አለባቸው እላለሁ። በዚህ ሃቅ ላይ ተመሥርቼ ነው የሚከተሉትን ሶስት ጥያቄዎች ለውይይት የማቀርበው፣

ሀ) ከወያኔ ጋር መደራደር አስፈላጊ ነው ወይ?

ለ) አስፈላጊ ነው ከተባለ፣ ከተቃዋሚ ኃይሎች ወገን ለድርድር የሚቀርቡትስ እነማን ናቸው?

ሐ) ተደራዳሪዎቹ የሚደራደሩበት የመደራደርያ ነጥቦችስ ምን ይመስላሉ?

 

የውይይት ነጥቦች ይሆናሉ ብዬ ከላይ ወደ ጠቀስኳቸው ሶስቱ ፍሬ ነገሮች ከማለፌ በፊት ግን በቅንፍ ውስጥ፣ ዛሬ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ እንዲሁ ባጭሩ ብንመለከት የውይይቱን ወቅታዊነት በግልፅ ያሳያሉ ባይ ነኝ። የችግሮቹን ቅርጫት ክዳን ስንከፍት ከወያኔ ጋር ሥልጣን ለመጋራትም ሆነ ለመረከብ ተቃዋሚ ኃይሎች ከራሱ ከወያኔና ከርስ በርሳቸው ጋር መደራደር አለባቸው ወደሚለው መደምደሚያ ያደረሰኝን ዘርፈ-ብዙ አገራዊና ዓለም-አቀፋዊ ክስተቶችን ብንመረምር ከሞላ ጎደል የሚከተሉትን የችግር ልቃቂቶች የምናገኝ ይመስለኛል።

ሀ) ያገሪቷ ኤኮኖሚ ወያኔ በሁለት አኃዝ እያደገ ነው እንደሚለው ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ወደታች እያሽቆለቆለ ነው። እንደተለመደው አንድ-ሶስተኛው የአገሪቷ ዓመታዊ ባጀት የሚንቀሳቀሰው ከውጪ በሚገኘው ድጎማ ነው። ስለሆነም የኤኮኖሚ ዕድገት ተብሎ ሁሌም ለናሙና የሚወሰደው በአዲስ አበባና ሌሎች የክልል ዋና ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለው የፎቅ ግንባታ ሥራ ለከተሞቹ ጊዜያዊ ውበት ከመስጠት አልፎ ለዜጎች ምንም ዓይነት ጥቅም ሊሰጥ አልቻለም፤ የእርሻ ምርቱም ካመት ወደ ዓመት እያሽቆለቆለ ነው። እፍኝ የማይሞሉ “ልማታዊ ገበሬ” ከሚባሉትና የመንግሥቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከሆኑት ግለሰቦች በስተቀር መላው የኢትዮጵያ ገበሬ ዛሬም ልክ ከመቶ ዓመት በፊት ይጠቀምበት የነበረውን ማረሻና ቀንበር ይዞ ተደጋግሞ በመታረስ ብዛት የነጠፈውን ማሳ፣ መንግሥት በግዴታ የሚያበድረውን ማዳበርያ እየበተነበት አርሶ የሚያገኛትን የምርት እፍታ “የማዳበርያ ብድር” እየከፈለ በቀሪው ደግሞ ቤተሰቡን በትንሹም ቢሆን እየመገበ፣ ራሱን ሳይኖር “ባለጊዜዎችን” እያኗኗረ ይገኛል።

ለ) ያገሪቷ የሃብት ክፍፍል ከመቼውም ጊዜ በላይ የተዛባ ነው፤ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እየበለጸጉ ሲሆን ሰማንያ አምስት በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በታች ይገኛል። በጥቂት “ዘመን አመጣሽ” ሃብታሞች በሞኖፖሊ የተያዘው ብሄራዊ ኤኮኖሚ፣ ብሄራዊ የሃብት ክፍፍልን በጣም ያዛባ ከመሆኑም በላይ “ባለጊዜዎቹ” በህገወጥነት ያካበቱትን ሃብት ለማካፈልም ሆነ ካሁኑ የተለየ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ቢቀየስ እንደሚጎዳቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ወያኔ ሥልጣን እንዲለቅ በጭራሽ አይፈልጉም።

ሐ) የመለስ መሞት በኢህአዴግ ላይ ከፍተኛ የአመራር ችግር የፈጠረ ይመስላል፤  አንድ ጠንካራና የተማከለ አመራር ሊሰጥ የሚችል “ቆራጥ” መሪ በመጥፋቱ ፓርቲው ከርቀት ሲያዩት አንድ ወጥ ይምስል እንጂ ከውስጥ ግን የተከፋፈለና የተቦረቦረ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ቡድን የየራሱን ምጣኔ ህብታዊ ጥቅም ያሳድዳል እንጂ አገሪቷ ያለችበትን ቀውስና ሊከተል የሚችለውን አደጋ በቅጡ ገምግሞ መፍትሄ ሊያቀርብ የሚፈልግ ያለ አይመስልም። ክፍፍሉ እንዳለም ሆኖ ግን ሌሎች ተቃዋሚዎችን በተመለከተ፣ ወያኔ “የአባላቱን መብት ለማስጠበቅ” እንደ አንድ አካል ሆኖ ከመከላከል ወደ ኋላ እንደማይል ብዙዎች የደመደሙት ጉዳይ ነው። በዚያው አኳያ ደግሞ፣ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጅምላ “ይጠላናል” በሚል ፍራቻ፣ከዚህ “የጋራ ጠላት” “ራስን የመከላከል” ፖሊቲካቸው አንድ ወጥ ያስመስላቸዋል።

መ) የፖለቲካው ሁኔታ በጣም አወዛጋቢ እየሆነ  ሄዷል። ባንድ በኩል ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ሁሉ እየኮረኮመና እየጎነተለ ለማንበረከክ ብርቱ ጥረት እያደረገ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የበደሉ ብዛት ከልክ በማለፉ ሰፊው ሕዝብ ከቁጥጥር ውጪ በመሆን በአደባባይ የመንግሥቱን የጸጥታ ኃይሎች ጥይት በመጋፈጥ ብሶቱን እየገለፀ ነው። የመልካም አስተዳደር እጥረት ባገሪቷ ለተከሰቱት ሕዝባዊ ሁከቶች መንስዔ መሆናቸውን መንግሥት አምኖ የተቀበለ ቢሆንም ተጠያቂ የሆኑትን የመንግሥት ባለሥልጣናትና መንግሥታዊ አካላት ላይ እርምጃ ወስዶ የጎደለውን እንደማሟላት ፋንታ አመፁን አነሳስታችኋል በማለት በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ወጣቶች ላይ የወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል። እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ወጣቶች ከዩኒቬርሲቲ እየተመረቁ ሥራ በማጣታቸውና ቅሬታቸውንም ካሰሙ ደግሞ ታሥሮ መማቀቅ እንዳለ ስለሚያውቁ፣ አብዛኛዎቻቸው የተገኘውን ዕድል በመጠቀም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ካገር እየተሰደዱ ነው፤ ወጣት ሴቶችም የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ብለው ወደ ዓረብ አገሮች እየፈለሱ ሲሆን ብዙዎቹ ለትልቅ አደጋ ተጋልጠዋል።

ሠ) የማሰብ የመናገርና የመጻፍ መብቶች መገፈፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ የፖለቲካ እሥረኞች ቁጥር ከግምት በላይ ሆኗል፤ በእሥረኞች ላይ የሚፈጸመው የማሰቃየት ተግባር ከኢትዮጵያውያን አልፎ የዓለሙን ማኅበረሰብ እጅግ በጣም እያሳሰበ ነው። ፍርድ ቤቱ እንዳለ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ስለሆነ ዳኞች ፍትሓዊ የሆነ ፍርድ መስጠት አይችሉም። የሰው ልጆችን መብት መከላከልን በተመለከተ ለብዙ ዓመታት በተለይም ከተመድ (UN) መቋቋም በኋላ የግንባር ቀደም ሚና ሲጫወቱ የነበሩት የምዕራብ አገራት የሞራል በላይነት ማጣትና ዓለም-አቀፋዊውን ሽብርተኝነትን ለመከላከል ብሎም ለማጥቃት በሚል ሰበብ የምዕራብ አገራት የጀመሩትን የዜጎችን መብት መጣስ እንደ ኢትዮጵያ ላሉት አምባገነን መንግሥታት የየራሳቸውን ፀረ-ሽብር ሕግ እያወጡ የዜጎችን መብት መግፈፍ በሚያስከፋ መልኩ እንዲቀጥል ገፋፍቷል።

ረ) ያገሪቷ መከላከያ ሠራዊት እጅግ በጣም በከፋ ሙስና ውስጥ እንደተደፈቀ ይነገራል። በቱርክና በፓኪስታን ሞዴል የተጠፈጠፈው ያገሪቷ ሠራዊት “ራሱን በራሱ ፋይናንስ ማድረግ አለበት” ተብሎ በመለስ ስለተፈረጀ፣ እጅግ በጣም ብዙ መከላከያ ነክ ፕሮጀክቶች ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለምንም ጨረታ ስለሚሰጠው ትኩረቱ ያገሪቷን ዳር ድንበር መከላከል ላይ ሳይሆን በመከላከያ ሰራዊቱ ስም ቁንጮዎቹ ያከማቹትን ሃብት ከህዝብ ወደ መከላከል ዞሯል።

ሰ) የሕወሃት “የከፋፍለህ ግዛ” ፖሊቲካ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አኳኋን ሥራ ላይ እየዋለ ነው። ምንም እንኳ በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መካከል በፊውዳሉ ዘመን የነበረውን ቅራኔ እንደገና ነፍስ ሊዘራበት ፈልጎ ባይሳካለትም ሌሎች አናሳ ብሄረ ሰቦችን በስውር አደራጅቶ ጸረ ኦሮሞና ጸረ አማራ ግጭት እየቀሰቀሰ ይገኛል። ያም ሆኖ ግን የወያኔ የመከፋፈል ፖሊቲካ ሳያግዳቸው በብሄሮች መካከል እየተከሰተ ያለው የመቀራረብ ሁኔታ ተስፋ የሚጣልበት ጉዳይ ነው። በአማራና ኦሮሞ ክልላት ተካሂዶ በነበረው ዓመጽ ወቅት የሁለቱም ክልል ሕዝቦች ያሳዩት የነበረው ፍጹም የመግባባት መንፈስ አስደሳች ነበር። ለወደፊትም የጽንፈኛው ዲያስፖራ ከፋፋይ ፖሊቲካ ገብቶ ካላወከው በስተቀር ይህ የአማራና የኦሮሞ  ሕዝቦች መተባበር እየተጠናከረ እንደሚሄድ ከወድሁ ተገምቶአል።

ሸ) የብሄር ጥያቄን በተመለከተ፣ በፖሊቲካ ድርጅቶች መካከል ያለው የአስተሳሰብ ልዩነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ፖላራይዝድ ሆኖአል። “የኢትዮጵያ ህዝብ ድሮም አንድ ነበር አሁንም አንድ ነው፤ ለወደፊቱም የሚበጃት አሃዳዊ አስተዳደር ነው፣ለአንድነቷም ጋሻ ጃግሬዎቹ እኛ ብቻ ነን” በሚሉ ጥቂት ኤሊትና የዚህን ተቃራኒ ሃሳብ በሚያራምዱት “ለኢትዮጵያ  የሚበጃትና ብቸኛው መፍትሄ ፌዴራላዊ አስተዳደር” ነው በሚሉ የብሄር ድርጅቶች መካከል በጣም የሰፋ ገደል አለ። ትንሽ የሚያዝናና ነገር ቢኖር የብሄር ጥያቄ ሁሌም “ፊደል የቆጠረው” የአናሳ ቡድን እንጂ የሰፊው ህዝብ ጥያቄ ባለመሆኑ፣ ባገር ቤት ደረጃ በብሄሮቹ መካከል ጥያቄው ወቅታዊ ያለመሆኑ ነው።

 

መሆን ያለበትና የነበረበት፣

ህብረተሰብ፣ በፖሊቲካ ህይወትና አገር አስተዳደር ለዘመናት ካካበተው ልምድ በመነሳት ዛሬ በኢትዮጵያ ያለውን ማህበረሰባዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ ያገናዘበ ሰው የሚከተለውን ሊል ይችላል። እንደ ወያኔ አናሳ የሆነና ያገሪቷን ፖሊቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ሕይወት ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ መንግሥት አንድ ደረጃ ላይ ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር ተባብሮ “አልፈልግህም” ብሎ ካመጸበት በጣም ቀላል የሚሆነው ቁርጠኛ ውሳኔ፣ የፖሊቲካ  ሥልጣኑን በሰላም አስረክቦ፣ ሰርቀውም ሆነ በአግባብ ያካበቱትን ሃብት ይዘው ከፖሊቲካ መድረክ መውጣት ነበር። የደቡብ አፍሪቃ አናሳ የነጭ መንግሥት ያደረገው ያንን ነው። ህዝባዊ ዓመፁ እየጠነከረና እየሰፋ በሄደበት ጊዜ አናሳው መንግሥት ከጠላቱ ከ ANC ጋር በድርድር ጠረጴዛ  ዙርያ  ለመቀመጥ ወሰነ። በድርድሩም ሂደት ሥልጣኑን በሰላም በማስረከብ አገሪቷን ከጥፋትና ዕልቂት አዳነ። ዛሬ የፖሊቲካ ሥልጣኑን እነዙማ “ይዘው” በአለም መድረክ ሲፎልሉበት ነጮቹ ግን ራሳቸውን ከፖሊቲካ አገልለው ያገሪቷን ኤኮኖሚ ግን ሙሉ በመሉ ተቆጣጥረውት ይገኛሉ። ዋናው ነገር አገሪቷ ከጥፋት ድናለች።

በሰብዓዊ ስሜት (common sense ?) የሚመራ ማንም መንግሥት የዛሬይቷን ኢትዮጵያ ሁኔታ ካጤነ በኋላ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለድርድር ለመቅረብ አለበት ባይ ነኝ። ለወያኔ አባላትና ሥርዓት ተጠቃሚዎች ግን ይህ ሃቅ ለጊዜው የተገለጠላቸው አይመስልም። ዕብሪትና ድንቁርና ተደማምሮ በራሳቸው ላይ የተጫነባቸው ይመስል የፖሊቲካ ሥልጣኑንም ሆነ የኤኮኖሚ ዘርፍ ባለቤትነቱን ይዘው ለዘላለም የሚኖሩ እየመሰላቸው ካገር ውስጥም ሆነ ከውጪ የሚደወልላቸውን የሰላም ጥሪ ከመጤፍ የሚቆጥሩም አይመስሉም። ከዚያም በተጨማሪ ወያኔ በጥቅማ ጥቅምና በሙስና እጃቸውን አጨማልቆና በአፋላማ የያዛቸው በርካታ ግለሰቦችም የወያኔ ከሥልጣን መወገድ ማለት የነሱም የመጨረሻ በመሆኑ በተቻላቸው መጠን የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም ሲታገሉ ይታያሉ። ይህ ግን የሚያዛልቅ ሂደት አይመስለኝም። ህዝባዊ ዓመፁ እየሰፋና  እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር የወያኔ መሪዎች፣ ሥልጣን ካጋሩ ወይም ካስረከቡ አንዳችም አደጋ እንደማይደርስባቸው ዋስትና ካገኙ፣ “በክብር ለመሸኘት” (dignified exit) ለድርድር ለመቅረብ ፈቃደኛ ይሆናሉ ባይ ነኝ።

ወያኔ ለድርድር ዝግጁ ያለመሆኑን ያህል ተቃዋሚ ኃይሎችም ባብዛኛው ለድርድሩ አስፈላጊነት አስተዋጽዎ ሲያደርጉ አይታዩም። አንዳንዶቹ ወያኔን በተባበረ ክንድ ለማሸነፍ በስትራቴጂ ደረጃ ጊዜያዊ ወዳጅነት ሲመሰርቱ ሌሎች ደግሞ ከመሰሎቻቸው ጋር “የሽግግር መንግሥት“ ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ አልፈን በአግባቡ ተደራጅተናል በማለት ራሳቸውን ይፋ ያደረጉ አሉ። ያገሪቷን ችግር ለመፍታት የሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሚመሰረተው ግን ባሃሳብ በሚጣጣሙ ግለሰቦችና ቡድኖች መካከል በሚደረገው ስምምነት ሳይሆን የተለያየ አስተሳሰብና አቋም ያላቸውን ድርጅቶችና ቡድኖችን ሁሉ በማቀፍ ነው። በንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ያ አልበቃ ብሎ፣ ሌሎች ደግሞ ባገሪቷ ላይ በማንዣበብ ላይ ያለውን አደጋ እንዴት በጋራ ሆነን በሰላም እንፍታው እንደማለት፣ ምንም ዓይነት መፍትሄ ሊያመጣ የማይችለውንና  አወዛጋቢ የሆነውን ያለፈን የታሪክ ትንተና ወደ ኋላ ተመልሰው ከተቀበረበት ጎርጉሮ በማውጣት፣ በሱ ላይ በመወያየትና በማወያየት “የታሪክ ታጋች”  – hostage – ሆነው ዛሬን ሳይሆን ትናንትን እየኖሩ ይገኛሉ። ያም ሆኖ ግን ሁላቸውም ያለማወላወል በወያኔ ከሥልጣን መወገድ ቢያምኑበትም፣ ወያኔን እንዴት ከሥልጣን መድረክ እናወርደዋለን ወይም እንዴት አርገን ለድርድር እንዲቀርብ እናስገድዳለን፣ ወይንም ደግሞ ወያኔ በተፈጥሮ ግዴታም ሆነ በውጪ ግፊት ዛሬ ከሥልጣን ቢወርድ፣ ድህረ ወያኔዋን ኢትዮጵያ ማን ነው ተረክቦ የሚመራት በሚለው ላይ አንዳችም የጋራ ነጥብ የላቸውም።

አዎንታዊ ክስተቶች፣

በተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል ሊከሰት ያልቻለውን የጋራ ነጥብ ጉዳይ ወደ ጎን ብንተውና ያገር ቤቱን ነባራዊ ሁኔታ ስናጤነው በጥቂቱም ቢሆን የሁኔታዎችን መለወጥ አይቀሬነት የሚያመለክቱ አዎንታዊ ክስተቶች አሉ፣

አንደኛው፣ ወያኔ እንደ ማንኛውም ከዚህ በፊት በታሪክ እንደታዩት መንግሥታት ዲያሌክቲካዊ ህግን ተከትሎ አንድ ቀን መሞቱ የማይቀር መሆኑ ነው። የማይታወቀው ነገር ቢኖር ግን የመሞቻው ቀንና የአሟሟቱ ሁኔታ ነው። በጠብመንጃ ኃይል ተደግፈው “በአሸናፊነት” ሥልጣን የያዙና ሁሉንም ያገሪቷን ችግር በጠብመንጃ ድጋፍ የሚፈቱ የሚመስላቸው አንጋፋዎቹ የወያኔ አባላት የተፈጥሮ ሕግን ተከትለው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ማለፋቸውም እርግጠኛ ነው። በቅርቡ ኢሕአዴግን የተቀላቀለውና ለወደፊትም የሚቀላቀለው ደግሞ የትግራይ ተወላጅን ጨምሮ ከጫካ ያልመጣ፣ በጠብመንጃ ብርታት የማያምንና “በአሸናፊነት” ስሜት የተሞላ ስላልሆነ፣ እስካሁን በኢህአዴግ አባላት ድርጅቶች መካከል ይታይ የነበረው “የፊትና የኋላ ረድፍ” የደረጃ ተዋረድ የሚቀር መሆኑ ሌላ አዎንታዊ ክስተት ነው። አዲሶቹ የኢህአዴግ አባላት አብዛኞቹ እንደ አንጋፋዎቹ “ታግለው በጠብመንጃ ብርታት አሸንፈው” የመጡ ስላልሆነ በመካከላቸው ዕዳ ያለበት አባል አይኖርም። “ታጋዩና አሸናፊው” አንጋፋው ትውልድ በተፈጥሮ ሂደት ቦታ ሲለቅ አዲሱና እኩልነት የሚሰማው ወጣቱ የኢህአዴግ አባል ለለውጥ ዝግጁ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ። ይህንን ሃቅ ነው እንግዲህ ተቃዋሚ ኃይሎች ከግንዛቤ ለመክተት ያልቻሉት!

ሁለተኛው፣ በተለያዩ ብሄሮች በተለይም በኦሮሞና በአማራው ህዝብ መካከል ከአንድ ምዕት ዓመት በላይ በያኔው የገዢ ሥርዓት ሰፍኖ የነበረው ጥላቻ የደርግን የመሬት ዓዋጅ ተከትሎ የከሰመ ቢሆንም ወያኔ ግን በተቻለው መጠን በህዝቦች መካከል መቀራረብና ብሎም ወዳጅነት እንዳይመሰረት የተቻለውን ሁሉ ቢያደርግም ህዝቦቻችን ግን ያንደኛው መብት መገፈፍ የሌላኛውም መብት መገፈፍ ብሎ በመነሳት የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊቲካ አሽቀንጥሮ መጣሉ ተስፋ ከሚጣልባቸው አዎንታዊ ክስተቶች ዋነኛው ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም።

የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ተቃዋሚ ኃይሎችና በአስቸኳይ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች

የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይሎች በሁለት ጎራ፣ ማለትም ብሄራዊና (national) አገር-ዓቀፍ (multi-national) ብሎ መመደብ ይቻላል።  ሁላቸውም ያለማወላወል የሚስማሙበት አንድ ነገር ቢኖር ወያኔን ከሥልጣን ለማስወገድ ሲሆን ከወያኔ በኋላ ሊኖር ስለሚችለው መንግሥታዊ ሥርዓት ወይም አወቃቀር ግን እንኳን ተስማምተው የጋራ አቋም ሊወስዱ ይቅርና በየግል ድርጅታቸው ውስጥ ከአባሎቻቸው ጋር እንኳ የተወያዩበት አይመስልም። ይህ ዋነኛውና ያለመዘግየት መፈታት ያለበት ቀዳማዊ ችግር ይመስለኛል።

ያም በመሆኑ ያገራችንና የህዝባችን ጉዳይ ያገባናል ለምንል ሰዎች የሚከተለውን ጥያቄ ማቅረብ እሻለሁ፥ ከላይ እንዳልኩት ኢህአዴግ እንደማንኛውም መንግሥት በዲያለክቲካዊም ሆነ በሰው ሰራሽ ምክንያቶች አንድ ቀን ወይ ህልውናውን ያጣል ወይም ደግሞ መልኩን ቀይሮ ኑሮን ይቀጥላል። ታዲይ ወያኔ በዛሬ መልኩ አንድ እሁድ ዕለት መኖሩን አቆመ እንበልና ሰኞ ጧት በአራት ኪሎ  የሚሰየመው የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስተዳደር የሥልጣን ኃላፊነት የሚረከበው አካል ማን ነው? ምንስ ይመስላል? ብለን ብንጠይቅ፣ እንኳን አግባብ ያለው መልስ ልናገኝ ቀርቶ መለስተኛ ውይይት እንኳ ያልተደረገበት መሆኑን እንረዳለን። የዚህ ጽሁፌ ዓላማም በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ያለምንም መዘግየት ጉዳዩ ይመለከተናል በሚሉ አካላት መካከል ውይይት መጀመር እንዳለበት ለማሳሰብ ነው።

የዛሬውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ካለኝ የሙያ ልምድ አንጻር ስዳስሰው ሁለት ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ

አንደኛው፣ የማንመኘውና ግን ደግሞ ሊከሰት የሚችል ዕውኔታ፣ የወያኔ መሪዎች ልክ እንደ ጋዳፊ ወይም ሙባራክ የህዝብን ቁጣና ዓመጽ እየናቁ እስከ መጨረሻው የሥልጣን ወንበሩን ላለመልቀቅና ብሎም ህዝቡን አንበርክኮ ለማኖር ወስኖ የሞት የሽረት ትግል ማካሄድ ነው። ለብዙ ዓመታት ህዝቡን ለመግዛት የተጠቀሙበትን የሥልጣን አለንጋና ተደላድለው የኖሩበትን የቅንጦት ህይወት በቀላሉ ትቶ መሄድ በጣም ከባድ ስለሚሆንባቸው በተቻላቸው መጠን ተከላክሎ ካልተቻለም አጥፍቶ አብሮ ለመጥፋት ይወስናሉ። ይህ ማለት አገሪቷን ወደ ትልቅ የርስ ብርስ ጦርነት ይመሯታል፣ ነፍሳት ይጠፋሉ፣ ንብረት ይወድማል ማለት ነው። ከንደዚህ ዓይነቱ የርስ በርስ ግጭት በኋላ የሚገኘው “ድል” ደግሞ ፈረንጆች እንደሚሉት pyrrhic victory (አሰቃቂ ድል) እንጂ እውነተኛና የሚያጓጓ ዓይነት ድል አይሆንም። አንድ ቀን ከዛሬዋ የሶሪያ ተፋላሚ ወገኖች መካከል አንደኛው ወገን አሸንፎ የሚቀዳጀው ድል ዓይነት ማለት ነው።

ሁለተኛው፣ የምንመኘውና ሊከሰትም የሚችል የአገሪቷንም ሆነ የወያኔን ህልውና የማይነካው የሰላም መንገድ ነው። ይህም፣ ወያኔ በራሱ ፍላጎትም ሆነ ከውስጥና ከውጪ በሚደረግበት ጫና ምክንያት ሥልጣንን ለማካፈል ወይም ሊያስረክብ ሲስማማ ነው። ይህ ነው እንግዲህ የሁሉም አገር ወዳድና ሰላም ፈላጊ ዜጋ ምኞት መሆን ያለበት። በመጀመርያ ረድፍ ያስቀመጥኩትን ዘግናኝ ትንቢት ወደ ጎን ትተን በዚህ በሁለተኛው ላይ ብናተኩርና ወያኔም እንደምንመኘው ሥልጣንን ለማጋራት ወይም ለማስረከብ ከወሰነ፣ ዛሬ ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱት ኃይላት ከወያኔ ሥልጣን ለመረክብም ሆነ ለመጋራት ዝግጁ ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ ተገቢ መልስ ያገኘ አይመስለኝም።

ከወያኔ ጋር ስለመደራደር።

የዚህ ጽሁፌ ጭብጥ፣ አገራችን ወደ አላስፈላጊ የርስ በርስ ግጭት እያመራች መሆኑን የሚጠቁሙ ቅድመ ሁኔታዎች እየታዩኝ  ስለሆነ ያንን አደጋ ለማስወገድና፣ ሰላምና መረጋጋትን አምጥቶ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ኃላፊነት ሊሰጠው የሚችል የሽግግር መንግሥትን ማቋቋም ብቸኛ መፍትሄ ነው የሚለው ነው። ይህንን የሽግግር መንግሥት ደግሞ ለማቋቋም በመጀመርያ ደረጃ  ተቃዋሚ ሃይሎችና ወያኔ በድርድር ጠረጴዛ ዙርያ ለመቀመጥ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው ባይ ነኝ። ከዚሁ በመነሳት ነው ከላይ ያነሳኋቸውን ሶስት ዓብይ ጥያቄዎች ዘርዘር አድርጌ ከዚህ በታች የማቀርበው።

 

) ከወያኔ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን ወይ? ድርድሩስ አስፈላጊ ነው ወይ?

ወያኔ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈፀመው ግፍና በደል ይህ ነው አይባልም። የግፉም አለንጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያልገረፈው ዜጋ የለም ብል ማጋነን አይሆንብኝም። የቤተሰቡ የጎረቤቱ ወይም የዘመዱ አባል የሆነ ዜጋ በወያኔ ገዳዮች ያልተነካበት ሰው አለመኖሩን ሁሉም ያምንበታል። ያላግባብ በታሰሩት ዜጎች ላይ የሚፈፀመውን አሰቃቂ የመብት ገፈፋ በዓለም ደረጃ የታወቀና የተኮነነ በመሆኑ እዚህ ላይ ማስታወሱ ራሱ ዘግናኝ ነው። የእነዚህን ሁሉ አሰቃቂ ግፍ ሰለባ የሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ፣ ሁሉም ነገር እንዳልነበር ይቆጠርና “ለተሻለው ነገ” (better future) ሲባል ከግፈኛው ወያኔ ጋር ተደራደር ማለቱ ራሱ በተበዳዩ ህብረተሰብ ቁስል ላይ ጨው የመጨመር ያህል የሚያንገበግብ ይመስለኛል። የተደፈረችን ሴት መልሰሽ የደፈረሽን ሰውዬ ራሱን አግቢው የማለት ያህል ቅንነት የጎደለው ፍርድ ይመስላል።

 

ግን ደግሞ፣ ከዚህ ከበዳዩ  መንግሥት ጋር በእኩልነት ለመደራደር ከመቅረብ የተሻለ ምርጫ ምንድነው ነው? በኔ ግምት፣ ሁለት እኩል ጎጂ ወይም መራራ የሆኑ አማራጮች አሉን ባይ ነኝ። አንደኛው፣ አንደራደርም ብሎ ልክ ወያኔ እንዳደረገው በጠብመንጃ ኃይል ሥልጣን ለመውሰድ ከወያኔ ጋር ጦርነት መጀመር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ወያኔ እስካሁን ላደረሰው በደል ይቅርታም ባይደረግለት፣ የርስ በርስ ጦርነት ሊያስከትል የሚችለውን ዕልቂት በመረዳትና ላገርና ለወገን ደህንነት ሲባል ከራሱ ከወያኔ ጋር መደራደር ነው። ፈረንጆች እንደሚሉት በዓለትና በደረቅ መሬት ላይ ከመውደቅ የቱ እንደሚሻል ማማረጥ ማለት ነው። ሁለቱም ላይ መውደቅ በጣም ጎጂ ነው፣ ግን መውደቁ የግድ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ከሁለቱ ጎጂዎች መካከል “የተሻለውን ጎጂ” መምረጥ ማለት ነው።

በግሌ ከሁለቱ ጎጂ አማራጮች መካከል፣ ከወያኔ ጋር መደራደሩ የተሻለ ጎጂ አማራጭ ነው እላለሁ። በጠብመንጃ ትግል ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ መሞከር አስከፊ የሆነ የርስ በርስ ጦርነት ከማስከተሉም በላይ በጠብመንጃ ብርታት ሥልጣን የሚወስደው መንግስትም ደግሞ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን ዓቀፍ ለመሆኑ ማስተማመኛ የለም። በኔ ግምት ወያኔ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ድርጅት ከፈለገ እንደ አንድ የትግራይ ብሄር ድርጅት አለያም እንደ አንድ የአገር አቀፍ ድርጅት የድርድሩ አካል የመሆን መብት አለው። ወያኔ ወደድንም ጠላንም የችግሩ መንስኤ የሆነውን ያህል ለችግሩም መፍትሄ የመሆን ግደታ አለበት። በሥራዬ ጠባይ ምክንያት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ካየኋቸውና ከተካፈልኩባቸው ባንዳንድ አህጉራት ይከሰቱ የነበሩትን የርስ በርስ ግጭቶች መነሻና መድረሻ ገምግሜ፣ የዛሬው የኢትዮጵያ ፖሊቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ሊፈታ የሚችለው በድርድር ብቻ መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምንበታለሁ። ሌላው ምርጫ የጥፋትና የዕልቂት ነው። እንደው ያለጥፋትና ያለ እልቂት ወያኔ ያኔ እንዳደረገው በጠብመንጃ ኃይል ሥልጣን መውሰድ ይቻላል ቢባል እንኳ፣ (ያን ያህል የታጠቀና የተደራጀ ኃይል አለ ብለን እንኳ ብንወስድ) በጠብመንጃ ኃይል ሥልጣን ላይ የሚወጣ ኃይል ከላይ እንዳልኩት፣ ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ያገሪቷን ችግር ፈትቶ ሰላም ሊያሰፍን አይችልም ባይ ነኝ።

) ከተቃዋሚውስ ወገን ለመደራደር የሚቀርበውስ ማን ነው?

 

ይሄኛው፣ ከላይኛው ያላነሰ አወዛጋቢ ይመስለኛል፣ ቁጥራቸው ከሃምሳ በላይ የሆኑት አገር ዓቀፍ ተቃዋሚ ኃይሎችና ብሄራዊ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ለድርድር የሚቀርብላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀበሉ እንበልና፣ እስቲ ማነው ከነሱ መሃል የኢትዮጵያን ህዝብ ወክሎ ከወያኔ ጋር ለድርድር የሚቀርበው? በኔ ግምት ተቃዋሚ ኃይሎች በአደረጃጀትም ሆነ በዓላማ የሰማይና የምድር ያህል ተራርቀዋል ባይ ስለሆንኩ፣ የነሱ ተወካይ ሆኖ በድርድር ጠረጴዛ ዙርያ የሚቀመጠው ማን ሊሆን ይችላል የሚለው የሁላችንም ራስ ምታት ይመስለኛል? እነዚህን በቅርጽም ሆነ በይዘት የማይጣጣሙትን ድርጅቶች እንዴት ተደርጎ ነው አንድ ላይ አምጥቶ የሁላቸውንም ጥቅም የሚያስጠብቅና በቅንነት የሚደራደር ቡድን መምረጥ የሚቻለው? ይህ ፈረንጆች የሚሉት የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው።

) የመደራደርያ ነጥቦቹስ ምን ይመስላሉ?

ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት አብይ ችግሮች ትንሽ ረገብ ያለው ሶስተኛ ችግር ደግሞ፣ የመደራደርያው ነጥብ (ነጥቦች) ጉዳይ ነው። በመሰረቱ ተደራዳሪ ወገኖቹ ከተሰየሙ በኋላ ድርድሩ መጀመር ያለበት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ለድርድሩ ያላቸውን ቀናነት ለማሳየት አንዳንድ እርምጃዎችን አስቀድመው መውሰድ ያለባቸው ይመስለኛል። ለምሳሌ ያንዳንድ ፖሊቲካ ድርጅቶች መሪዎችና ደጋፊዎች እስር ቤት ስላሉ የነሱን መፈታት እንደ ቅድመ ሁኔታ ማሰቀመጥና በወያኔ በኩል ደግሞ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ያሉት ድርጅቶች ለጊዜውም ቢሆን ማጥቃቱን እንዲያቆሙ መጠየቅ አግባብ አለው ባይ ነኝ። ዋናው የመደራደርያ ነጥብ ግን ወያኔ የሥልጣን መንበሩን ለጊዜያዊ መንግሥት ማስረከብ ሲሆን የጊዜያዊ መንግሥቱን ይዘት፣ አሰራርና የሥራ እንቅስቃሴን በተመለከተ ደግሞ ተደራዳሪዎቹ ራሳቸው በድርድሩ ጠረጴዛ ዙርያ የሚወስኑት ይሆናል።

መደምደሚያ

ከጠላት ጋር፣ በተለይም እንደ ወያኔ ዓይነት ለዓመታት ህዝባችንን ሲያስር፣ ሲገድልና ሲያሰቃይ ከነበረ መንግሥት ጋር ለድርድር መቅረብ ማለት ለሰው ልጅ ህሊና በጣም የሚከብድ ነገር ነው። እንኳን ከገደለና ካሰቃየ ባዕድ አካል ጋር ይቅርና በትንሽ ነገር እንኳ ካስቀየመ የቅርብ ወዳጅ ጋር መታረቅ በጣም ከባድ ነገር ነው። ግን ደግሞ ሰው የሚደራደረው ከጠላቱና ከተቃዋሚው ጋር እንጂ ከወዳጁ ጋር ስላልሆነ ከወያኔ ጋር መደራደር ብቸኛ አማራጭ ነው እላለሁ። ያገር ጉዳይ ደግሞ በመቀያየምና በመኮራረፍ ወይም አንዱ አንደኛውን በማጥፋት የሚፈታ አይደለም። ኢትዮጵያ ለሁላችንም እኩል እናት ናት፣ ማንም ከማንም በላይ ልጇ ሊሆን አይችልም፣ የሚያስብም ካለ ተሳስቷል። ይህ እስከሆነ ድረስ ደግሞ፣ ወያኔም እንደ አንድ የፖሊቲካ አካል ከሌሎች ተቃዋሚ አካላት ጋር በእኩልነት ቀርቦ ለመደራደርና የወደፊቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መሰረት ለመገንባት ተካፋይ መሆን አለበት ባይ ነኝ። ይህም የሚሆነው ደግሞ በድርድሩ ሂደት እንደሚወሰነው፣ ወያኔ አሁን ካለበት የሥልጣን መድረክ ወርዶ ከሌሎች ተቃዋሚ ኃይላት ጋር በፍፁም እኩልነትና ተዋረድ በሌለው የድርድር ጠረጴዛ  ዙርያ ተደራዳሪዎቹ በሚስማሙበት ውሳኔ መሰረት ይሆናል ባይ ነኝ።

በበኩሌ ለማለት የፈለግሁትን በግልጽ ያስቀመጥኩ ይመስለኛል። የውይይት ነጥቦችን ለማንሳት ሞከርኩ እንጂ ከድርድሩ አስፈላጊነት ሌላ፣ ተቃዋሚ ሃይሎች እንዴት አርገው ተወካዮቻቸውን እንደሚመርጡ ወይም የድርድሩ ይዘት ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ስሌት (formula) የለኝም። እያንዳንዳችን ያገሪቷ ሁኔታ ያሳስበናል የምንል ወገኖች ደግሞ፣ በየግላችን የምናምንበትን የአስተሳሰብና የአቋም ዘውድ በየኪሳችን ይዘን ከመዞር፣ በግልፅ በአደባባይ አምጥተን ብንወያይ ይበጃል ባይ ነኝ። በኔ ግምት፣ ለማንኛውም ዓይነት ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊገኝ የሚገኘው በድርሻ አካላት (stake holders) መካከል በሚካሄደው ቅንነት የተሞላበት ውይይት ብቻ ነው። ያንን እስካላደረግን ድረስ ደግሞ ያገሪቷ ሁኔታ አሁን ካለበት መጥፎ ደረጃ ወደ አስከፊነት ከተሸጋገረ፣ ባልጠበቅነው ሰዓትና አኳኋን “ዳግማዊ 1991” ይከሰትና፣ የሄርማን ኮሄን ልጅ የአሜሪካንን መንግሥት ጥቅም ሊያስጠብቁ ይችላሉ ብሎ የሚተማመንባቸውን ግለሰቦች ከተቃዋሚ ድርጅቶች መሃል መልምሎ፣ ለንደን ላይ ይሰበስብና “ዳግማዊ የሽግግር መንግሥት” ያቋቋምልናል። ምርጫው እንግዲህ የኛው ነው፣ ውሳኔውም በእጃችን ነው። እስቲ የእናንተን ደግሞ ልስማ!

በቸር ይግጠመን።

******

 

ባይሳ  ዋቅወያ

ጄኔቫ፣ መስከረም 11, 2017

[email protected]

[1] ጸሃፊው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን የነበሩ የዓለም ዓቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸው።

 

 

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop