ጉልበት ሳይገፋው ዳር እሚደርስ ተስፋ የለም! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ልጅ ሳለሁ ጥጋበኛው አጎታችን የአንድን ሰው ማሳ ለቤት መስሪያና ለወፍጮ መትከያ በጉልበቱ አጠረው፡፡ አባቴን ጨምሮ አጎቶቻችን ተው ቢሉትም እያመናጨቀ አልሰማ አላቸው፡፡ ማሳውን የተቀማው ሰውየም በጉልበት መመከት ስላልቻለ ፍርድ ቤት ጥጋበኛውን አጎቴን ከሰሰው፡፡ የፍርድ ቤቱ ክርክር እየተኪያሄደ ሽምግልና ተጀመረ፡፡ ሽማግሌዎቹ “ሰላም ፍጠሩ!” እያሉ ሲመክሩ መሬቱን የተቀማው ሰው ብሽቅ አለና “ይኸ ጥጋበኛ እንደ አሞራ ከቁረኔ አርፎ ሰላም እንዴት ይፈጠራል” ሲል ለሽማግሌዎች መለሰ፡፡ (ቁረን ጤፍ ታጪዶ ከመሬት በሚቀረው የጤፍ እግር የተሸፈነ ማሳ ማለት ነው)

በምዕራባውያንና በአረቦች ትከሻ ወንበር ተቆናጦ፣ ጭልፋና ሊጥ ሳይቀር የሕዝብን ሐብት ዘርፎና የጦር መሳሪያ አካብቶ የጠገበው የትግሬ ነፃ አውጪ ግንባር ተፈጥሮና ታሪክ ያጠሩትን የተከዜን ድንበር ተሻግሮ ከአማራ ቁረን እንደ ጆቢራ ቁጢጥ ብሎ ሰላምና መረጋጋትን ሰበከ፡፡ ባህር ዳር፤ ጎንደር፣ ደብረ ዘይት ወዘተርፈ የረፈረፋቸው ወጣቶች ዓይን ሳይፈርጥ የፍቅር ቀን እያለ እንደ ዲያብሎስ አጭበረበረ፡፡ በጉልበት ተከዜን ተሻግረው ከአማራ ቁረን እየተጸዳዱ ምን ዓይነት ሰላም ይፈጠራል ጎበዝ? ደም እንደ ጅረት በየጥሻው እየፈሰሰ ምን ዓይነት ፍቅር ይነግሳል ሰዎች?

መጽሐፈ ኢዮብ “የድንበሩን ምልክት እሚያፈርሱ አሉ፤ መንጋዎችን በዝብዘው ያሰማራሉ”(ኢዮ፡፳፪፡፪) እያለ ድንበር አፍርሶ መንጋውን ወልቃይትና ጠለምት ሲያሰማራ ስለኖረው የትግሬ ነፃ አውጪ አበክሮ ተናግሯል እኮ፡፡ ኦሪት ዘዳግምም “አምላክህን እግዚአብሔርን ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ብምትወርሳት ርስትህ የቀደሙ ሰዎች የተከሉትን የባለንጀራህን የድንበር ምልክት አትንቀል ዘዳግ፡፲፱፡፲፪”  ሲል የተከዜን ድንበር ነቅሎ ወልቃይትን ስለወረረው የትግሬ ነፃ አውጪ አበክሮ ተናግሮ ነበር እኮ፡፡ መጽሐፈ ምሳሌም “ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል ሲል ምስ፡ ፲፭፡፳፰” አስጠንቅቋል እኮ፡፡

በመለኮትም ሆነ በምድራዊ ሕግ እማይገዛው ስስታሙ የትግሬ ነፃ አውጪ ግንባር ህሊናና ይሉኝታ ቢስነት እሚያሳየው ሁሉም ካልሰለጠነ በተወሰነ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ዓለም በሥልጣኔ ልትመራ እንደማትችል ነው፡፡ መሰልጠን በህሊና በተሞረደ አእምሮ መመራት ነው፡፡ ሥልጣኔ የጡጫን ሥራ በህሊና ወደ ተሞረደ አእምሮ የማሸጋገር ሂደት ነው፡፡ እንደ አለመታደል ዓለም በህሊና በተሞረደ አእምሮ ወይም ስልጣኔ የተመራችበት ዘመን የለም፡፡ ወደ ፈትም እንደ ትግሬ ነፃ አውጪ ግንባር ዓይነት ዓይን አውጣ ቡድን ስለማይጠፋ ዓለም በጉልበት እንጅ በስልጣኔ ልትመራ አትችልም፡፡ ጉልበት ሳያሽከረክረው ከዳር የደረሰ መርህ ወይም ተስፋ ኖሮ አያውቅም፡፡ ታሪክን መርምሮ ማጠቃለል እንደሚቻለው ጉልበት ሳይገፋው ከዳር እሚደርስ ተስፋ አይኖርም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተደብቃ ታረግዛለች፣ ሰው ሰብስባ ትወልዳለች - አስቻለው ከበደ አበበ

ሶቅራጥስ የዲሞክራሲንና የፍልስፍናን ብሩህ ተስፋ ፈነጠቀ፡፡ ዳሩ ግን ይህ ብሩህ ተስፋ በጉልበት ስላልተደገፈ እንኳን ሕብረተሰብን ሲጠቅም መርዝ ሆነና ሶቅራጥስንም ቀነጠሰው፡፡ የሶቅራጥስ ብሩህ ተስፋ በትንሹም ቢሆን ከዳር የደረሰው ከሺህ ዓመታ በኋላ ሕዝብ በጉልበት ገፍቶት ነው፡፡

ክርስትና ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ምድር በነበረበትና አስራ ሁለቱ ሐዋርያት በሚሰብኩበት ዘመን አልተሰፋፋም፡፡ እንዲያም ይህ እምነት የክርስቶስን በጦር ተወግቶ መሰቀል፤ የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ አንገት መቀላት አስከትሏል፡፡ ክርስትና ዓለምን ያዳረሰው የሮምና ሌሎች አገሮች ጉልበተኛ ንጉሶችና ገዥዎች ክርስትናን ተቀብለው በጉልበት ሲገፉት ነው፡፡ እስልምናም የተስፋፋው ጉልበተኞች ገፍተውት ነው፡፡

“ዲሞክራሲ፣ ክርስትናም ሆነ እስልምና የተሰፋፉት በጎ ተስፋ ስለተሸከሙ ነው!” ብሎ እሚከራከር ሊኖር ይችላል፡፡ ዳሩ ግን እንደ ክህደት፣ ውሸት፣ ዝርፊያ፣ ጭካኔ፣ ግድያ፣ ወዘተርፈ ያሉ የሰይጣን ተስፋዎች ከዲሞክራሲ፣ ከክርስትናና ከእስልምና በበለጠ ፍጥነት ተስፋፍተዋል፡፡ ከዓለም ታሪክ የበፊቱን ቅኝ አገዛዝና የአሁኑን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ያስተውሏል፡፡ በአገራችን ታሪክ በክህደት፣ በውሸት፣ በዝርፊያ፣ በስግብግብነት፣ በይሉኝታ ቢስነት፣ በጭካኔና በአረመኔነት መንፈስ የተሞላውን የትግሬ ነፃ አውጪ የዘርኝነት መንፈስ በአውሎ ነፋስ ፍጥነት መሰራጨት ልብ ይሏል፡፡ ሮም የተዘጋጀው ይህ አማራን ኢላማው ያደረገ የዘረኝነት ሥርዓት በትግሬ ነፃ አውጪ ግንባር ሰባኪነት በብርሃን ፍጥነት በኢትዮጵያ ተሰራጭቷል፡፡ በሞሶሎኒ የተሳለው ካርታም በዚሁ ግንባር ሥራ አስፈጣሚነት ከመሬት ተዘርግቷል፡፡

የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር መስራቾች እንደመሰረከሩትና ሕዝብም ለአርባ ሶስት ዓመታት በግብር እንዳየው አማራን በጭቁን ሕዝቦች ጠላትነት የሚፈርጅ ሃይማኖት እየሰበከ ስንቱን አጥምቋል፡፡ በዚህ ከንቱ መንፈስ የተጠመቁ የትግሬ ነፃ አውጪ ግንባር ሃይማኖት አማኞችም አማራን ለኻጫም ብለው ተሳድበዋል፤ የአያቶቹ ደም ከፈሰሰበት ምድር አባረውታል፣ ገድለውታል፣ አደህይተውታል፣ አሰድደውታል፣አሰቃይተውታል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አስከፊ ሰቆቃና ግፍ በጎሳ መደራጀትን ሲጸየፍና ሲታገል የኖረውን የአማራ ሕዝብ ህሊና ተፈታትኖታል፡፡ ይህ የሚደርስበት ገደብ ያጣ ሰቆቃና ግፍም ለአማራ ሕዝብ “ማርያምን ትወዳታለህ?” ዓይነት ጥያቄ አቅርቦለታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ቢተዋ አማረበት..."በእርቅ ይልስ ...

“ማርያምን ትወዳታለህ?” ከልጅነቴ ጀምሬ የማውቀው ጥያቄ ነው፡፡ ሰባተኛ ክፍል ሳለሁ ለመጫወት ከአጎቴ ቤት ባደርኩባት የመጀመሪያዋ ቀን ህልም አየሁ፡፡ ሲነጋም አጎቴ ጸሎት ከሚያደርስበት ሥፍራ ሄድኩና “አይያ! በህልም ታምናልህ?” ስል ጠየኩ፡፡ አይያም ጨረቃ የመሰለ ፈገግታውን አሳዬና ” ማርያምን ትወዳታህ? ብለው ቢጠይቁት ወድጄ ነው ተግንድ እሚያላጋ ልጅ ስላላት ነው እንጅ” ሲል በተለመደው ምሳሌአዊ አነጋገር መለሰልኝ፡፡ የአማራ ሕዝብም ዛሬ “በጎሳ መደራጀትን ታምናለህ ወይ?” ተብሎ ቢጠየቅ “ወድጄ ነወይ የዘረኝነት አውሎ ነፋስ ለአርባ ሶስት ዓመታት ተግንድ ስላላጋኝ ነው እንጅ” ብሎ ይመልሳል ባይ ነኝ፡፡ የዘረኝነት አውሎ ነፋስ አማራን ከወልቃይት እስከ አዲስ አበባ ከአዲስ አበባ እስከ ሞያሌ እንዳሰቃየው እንኳን በዘረኝነት አውሎ ነፋስ የተሰቃየው አማራ አውሎ ነፋሱን አራጋቢው የትግራይ ነፃ አውጪና ችላ ያለው የዓለም ሕዝብም ያውቃል፡፡

ይህንን በዘረኝነት አውሎ ነፋስ የሚሰቃይ አማራ ከመጥፋት እሚያድነው የዘረኝነት አውሎ ነፋስ መጥፋት አለዚያም አውሎ ነፋሱን የሚቋቋም ጥበብ ነው፡፡ የዘረኝነቱ አውሎ ነፋስ ከመጥፋት ይልቅ እየበረታ ለመምጣቱ ለአርባ ሶስት ዓመታት የወሰድነው ትምህርትና ልምድ ማስረጃ ነው፡፡ ከዚህ ረጅም ትምህርትና ልምድ ሳይማሩ አውሎ ነፋስ ይጠፋል በሚል ተስፋ መንዘላዘል ከጅብ ጫካ ስትግጥ እንዳደረች አህያ እግዚአብሔርንም መፈታተን ነው፡፡

ብዙዎች ለማስተማር እንደሞከሩት የዘረኝነት አውሎ ነፋስን ለመቋቋም ብዙ ጥበቦች ይኖራሉ፡፡ ስህተት እሚሆነው አንድ ዓይነት ጥበብ ወይም አደረጃጀት ብቻ አውሎ ነፋሱን ይቋቋማል በሚል ግትርነት ማነቂያ ውስጥ እንደ ገባ በሬ ወደ ፊት መሄድን ትቶ እርስ በርስ መገፋፋትና ሐይልን ማባከን ሲመጣ ነው፡፡ ስህተት እሚሆነው በደደቢት መመርያ በምዕራብ፣ በምስራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ ከውጪ እሚዋሰንባቸውን ድንበሮችን ተነጥቆ እስተንፋሱን እንዲያጣ የተፈረደበትን አማራ ችግር ከሌሎች ጎሳዎች ችግር ጋር ማመሳሰሉ ከቀጠለ ነው፡፡ ስህተት እሚሆነው በጠላትነት ተፈርጆ ዙሪያውን ተከቦ እንደ ተቆላ ኑግ ለመወቀጥ ሙቀጫ ውስጥ እየገባ ያለውን አማራ እንደሌሎች “ጭቁን ጎሳዎች” መመልከቱ ከቀጠለ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የአድዋን 127ኛ በዓል የዐብይ ብልጽግና ሲያኮላሸው ዝም ልንል አንችልም" አክሎግ ቢራራ (ዶር)

መንዘላዘሉና ተዘፍዝፎ እንዳደረ ባቄላ ንክር መሆን እሚቀጥለው እንደ ማሞ ሙጬ አፍሪካ አንድ ስትሆን አማራ ከጥፋት ይድናል ዓይነት የሞኝ ህልም ማለም ካልቆመ ነው፡፡ ጆሮዋን ቀስራ የበሬን ቆለጥ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ መታለሉ እማያቆመው አማራን ለማጥፋት እየጎለበተ የመጣው አውሎ ነፋስ ካለጉልበት በጥበብና በሰነፍ ጸሎት ብቻ ይጠፋል ብሎ ተስፋ ማድረጉ ከቀጠለ ነው፡፡

ሕዝብ ሆይ! ጉልበት ሳይገፋው ዳር የደረሰ ተስፋ አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ካለኃጥያትህ በመመርያ ጥፋት የተደቀነብህ አማራ ሆይ! ጉልበት ሳይገፋው ከዳር እሚደርስ ተስፋ እንደማይኖር ከረጅሙ ታሪክህ ታውቃለህ፡፡ መጥሐፉ እርዱኝ እረዳችኋለሁ ማለቱንም ትገነዘባለህ፡፡ ስለዚህ እየተገፋህና እየጠፋህ በተስፋ ብቻ መኖር ይብቃህ! ተስፋህን መጥፋት እንዳያጨልምብህ እንደልማዱ ጉልበትህ ጠንጠን ይበል፡፡ ጉልበት ሲኖርህ ከመጥፋት ተርፈህ እንደ ባህልህ ጎረቢቶችህን አስከብረህና አክብረህ፤ አንተም ተከብረህ፤ ድንበርህን ጠብቀህ ትኖራለህ፡፡ ከመጥፋት ለመዳን የምታደርገውን ጥረት በቅየህ፣ በወህኒ ቤት፣ ጉድጓድ ውስጥ፣ ባልታወቁ  ቦታዎች፣ በማጎሪያ በረቶች፣ በትምህርት ቤት፣ በአምልኮት ሥፍራ፣ በሥራ ቦታና በስደት እሚደርስብህን አድሎና እሚወርድብህን የግፍ ጎርፍ እሚመለከተው እግዚአብሔር ከዳር ያድርስልህ፡፡

 

ጳጉሜ ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓ.ም.

Share