“ካላበዱ ወይ ካልነገዱ…” – ነፃነት ዘለቀ

 

ዛሬ ጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓመተ ፍዳ ነው፤ በእስካሁኑ ጉዞ ከቀጠልን አዲሱንና ግፍና በደል ተባብሶ በወያኔዎች የሚወርድብንን የመከራ ዘመን ልንቀበል አራት ቀናት ብቻ ቀርተዋል፡፡ ለማንኛውም “ደግ ተመኝ ደግ እንድታገኝ” ይባላልና  መጪው ዓመት የኢትዮጵያ ጠላቶች ድል የሚሆኑበት፣ ሀገራችን ከገባችበት ማጥ ነፃ የምትወጣበት፣ የወያኔው ዘረኛ አገዛዝ አብቅቶ ለሁላችንም እኩል የምትሆን ኢትዮጵያ የምትመሠረትበት፣ ጉግማንጉጎች ከነሰንኮፋው ተነቃቅለው የሚጠፉበት፣ ሃይማኖት ለግብር ይውጣ ሳይሆን በሃቅ እውን የሚሆንበት፣ የጠፉብንን የፖለቲካና የእምነት እረኞች የምናገኝበት … እንዲሆንልን አምላካችን ይርዳን፡፡  የዕዳ ደብዳቤያችን የሚቀደድበት ዘመን ይሁንልን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት፡፡

ዕብደት ዓይነቱ ብዙ እንደሆነ የሙያ ዘርፉ ባለቤቶች ሲናገሩ ይሰማል፤ ከትበውትም ይነበባል፡፡ የአእምሮ መቃወስ ዓይነቱና ደረጃው ከሰው ሰውና ከሀገር ሀገር ሊለያይ ቢችልም ማንኛውም ሰው ከነዚህ በመዝገብ ከሚታወቁ የዕብደት ዓይነቶች በአንዱ ወይ በሌላው ቢያንስ ለተወሰነ አጭር ቅጽበት – አንድ ጊዜ ብቻም ሳይሆን በሚመላለስ መልኩ – እንደሚጠቃ ጠቢባኑ ያስረዳሉ፤ እኛ የዘርፉ ማይምናንም በተግባራዊ ኑሯችን ሳንረዳው የምንቀር አይመስለኝም፡፡ ለጠቅላላ ግንዛቤያችን ያህል እነዚህን መሰል የዕብደት ዓይነቶች በሥነ ልቦናው የትምህርት ዘርፍ በአራት ተከፍለው እንደሚጠኑ መጠቆሙ ክፋት ያለው አይመስለኝም – Bad-mad, Mad-mad, Sad-mad, and Glad-mad.

በግርድፍ ንባባዊ ግንዛቤየ የሰው ልጅ እስካሁን መቶ በመቶ ማበዱ እንዳልተረጋገጠ መረዳት ችያለሁ፡፡ የመቶ በመቶ ዕብደት የተመዘገበው በውሻ ነው ይባላል፡፡ ልብስን ሽክ አድርጎ ለብሶ በመሄድ ከሰው ጋር ተደባልቆ ማውራትና መጫወት አእምሮን ጨለፍ የሚያደርግ ነገር ሲመጣ ደግሞ ግምኛ ነገር በመናገር ወይም ከርዕስ የወጣን ነገር በመዘብዘብ ሰዎችን ማስደመም የዐውቆ አበዶች ወይም የንኮች ጠባይ ሲሆን ለይቶለት ጨርቁን የጣለና የትሚናውን የሚያድር ግን የዕብደት ደረጃው አርባና ሃምሳን አልፎ ወደ ሰማንያና ዘጠና በመቶ የተጠጋ “ጥሩ” ዕብድ ነው፡፡ በውሻ ዕብደት ግና አንዴ አይጀምር እንጂ ከጀመረ ራስን ያስትና መብላት፣ መጠጣት፣ አቅጣጫን ለይቶ መጓዝ፣ መራብና መጠማት የመሳሰሉ የባሕርይና የስሜት መገለጫዎች የሉም፡፡ ስለሆነም ሂደትን ጠብቆ መሞት ብቻ ነው፡፡ የሰው ዕብድ ግን ይርበዋልና ይበላል፤ ይበርደዋልና ይለብሳል ወይም ጥጋት ላይ ቁጭ ብሎ በብርድ ይንቀጠቀጣል፡፡ ስለዚህ ዕውቀቱንና ሙሉ ስሜቱን አልተገፈፈምና ወሰድ መለስ እያደረገው እንደምንም ይኖራል – መኖር ተብሎ፡፡

በተለምዶ ጤነኛ የሚባሉ ሰዎች (ዕብደታቸውን ማወቅ የማይፈልጉ ብላቸውም ግዴለኝም) ዕብዶችን በጣም ይፈራሉ፡፡ ሁሉም ዕብዶች ሊፈሩ እንደማይገባ ግን ከፍ ሲል የተጠቀሱትን የዕብደት ዓይነቶች ዝቅ ሲል በተቀመጠው አድራሻ ሄዶ ማንበብ ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳንድ ዕብዶች አዛኝና ሩህሩህ ናቸው – ያላቸውን የሚያካፍሉና ለተቸገረ የሚንሰፈሰፉ፡፡ በሌላ በኩል ያገኙትን ነገር እያነሱ አጠገባቸው ወደሚገኝ ሰው የሚወረዉሩና አደጋ የሚያስከትሉ አንዳንድ ዕብዶችም አሉ፡፡ አንዳንዶች በሣቅ እየተንከረከሩ ራሳቸው ለራሳቸው በሚፈጥሩት ደስታ የሚዝናኑ አሉ፡፡ አንዳንዶች በሀዘን ድባብ ተውጠው ዘላለማቸውን እንደቆዘሙና እንደጨፈገጋቸው የሚኖሩ አሉ፡፡ አያድርስ ነው …

ከነዚህ ሁሉ የዕብደት ዓይነቶች ወያኔ የተያዘበትን የአእምሮ ደዌ ለማወቅ ሞክሬ በመጠኑ የተጠጋጋልኝ የመጀመሪያው የዕብደት ዓይነት ነው – “ክፉ ዕብድ” ወይም “መጥፎ ዕብድ” የሚለው፡፡ መጥፎ ዕብድ እየሣቀ መጥቶ በደቦል ድንጋይ ደረትህን ወይም ማጅርህን መትቶ ሲጥ ያደርግህና በሞትህ እየሳቀና እየተዝናና በመጣበት መንገድ ሊመለስ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕብድ ቀድሞውን የተለከፈበት የአእምሮ ህመም ከግድያና ስቃይ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሚያስደስተው ነገር ግድያና ስቃይ ነው፡፡ ለዚህ ዕብድ ሰዎችን ማሰቃየት ብቸኛው የደስታ ምንጩ ነው – እንደሕወሓት፡፡

መጥፎ ዕብድ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ መረጃ ያጋራኝ ሰነድ ስለነዚህ ዕብዶች እንዲህ ይላል-

If you meet a bad-mad person, especially when on your own, your priority must be to protect yourself. When self-defence is impossible, you should flee. ( [እንደሕወሓት ያለ]መጥፎ ዕብድ አያጋጥምህ እንጂ ካጋጠመህ – በተለይ ደግሞ ብቻህን ሆነህ – የመጀመሪያው እርምጃህ መሆን ያለበት ራስህን ከአደጋ መከላከል ነው፡፡ ራስህን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ ደግሞ አጥብቀህ ሽሽ፡፡)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ገረብ ገረብ ትግራይ መቃብር አምሃራይ

ትክክለኛ የባለሙያ ምክርና አስተያየት ነው፡፡ የተራ ዕብድን ጥቃት ታግለህም ሆነ ሮጠህ ትከላከላለህ፡፡ ይሁንና በመንግሥት መልክ ተደራጅቶ የመጣብህን ጎጠኛ ዕብድ እንዴት ትጋፈጠዋለህ? ከዚህ ዓይነቱ በጠላት ድጋፍ ከተደራጀ ዕብደት እንዴት ታመልጣለህ ? በቀላሉ መልስ የማይገኝለት ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያውያን ከዕብዶቹ ሕወሓታውያን የሲዖል ግርፋት ይልቅ በበረሃ አውሬዎች መበላትን እስከመምረጥ የደረሱት፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያውያን ውብ ሀገራቸውን በቀንና በሌሊት እየለቀቁ የባሕር እንስሳት ሲሳይ ሆነው መቅረትን የመረጡት፡፡ ለዚህ ነው ውድ የሀገሬ ወጣቶች ከዕብዱ የወያኔ አፓርታይድ አገዛዝ ይልቅ የዐረብ ጀማላ የቤት ውስጥ ገረድ መሆንን የሚመርጡት፡፡ ለዚህ ነው ሀገራቸው የማትበርድ እቶን የሆነችባው ኢትዮጵያውያን በሚሊዮኖች እየተሰደዱ በሰው ሀገር እንደሁለተኛና ሦስተኛ ዜጋ ሆነው መኖርን የሚመኙትና በተግባርም እየሄዱ የሚማገዱበት፡፡ ለዚህ ነው ወገኖቻችን ከዚህ ከወያኔዎች የዕብደት ሥራ ለመዳን ሲሉ የአይሲሶች ካራ ሰለባ የሚሆኑት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ከመኖር የለየለት ገሃነምም ሳይሻል አይቀርም፡፡ መብላት መጠጣት፣ መጥገብ መራብ፣ ማግኘት ማጣት ሌላ ጉዳይ ሆኖ ሰው ሆነህ እንደሰው መኖር የማትችልባት ሀገር ሆናለች – ኢትዮጵያ (የምለው ግልጽ ከሆነልህ በገንዘብ ሀብታም ሆነህም ወያኔ ካልሆንክ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አትችልም እያልኩህ ነው ወዳጄ፡፡) እንደሰው ለመኖር ቢያንስ በቅድሚያ የማሰብ ነፃነትህ ሊገፈፍ አይገባም፤ እንደዜጋ ይቅርና ቢያንስ እንደሰው የሚቆጥርህ የራሴ ነው የምትለው መንግሥት ሊኖርህ ይገባል፡፡ የራሴ ነው የምትለው የፖሊስ፣ የፀጥታና ደኅንነት፣ የመከላከያ ወዘተ. ኃይል መኖር አለበት፡፡ አንዱን የእንጀራ ሌላውን የሠይፍ ልጅ አድርጎ ማኛውንና ቁርጡን ለዘሩ፣ ዘንጋዳውንና ሳላይሰጡን ለአሽከሩ የሚሰጥ የመንግሥት መዋቅር ስታይ ምን ሊሰማህ ይችላል? እነዚህን ዓይነት የተንሻፈፉ አካሄዶች ሲስተካከሉ ያኔ  ነው ሀገሬ ልትል የምትችለው፡፡ እንጂ ስታየው የሚያቅርህ ባንዴራና እንደጠላት እያዬ የሚደበድብህ መለዮ ለባሽ ይዘህ በየትኛው አእምሮህ የሀገር ስሜት ይመጣልሃል?   ምን መናገርና መጻፍ ቀርቶ ምን ማሰብ እንዳለብህ ተለክቶ የሚሰጥህ በወያኔዎች ነው፡፡ ኧረ ባይገርምህ ይህ መንግሥታችን ማመልከቻም የሚጽፍልህ ራሱ ሆኖ አርፎልሃል! ንቀት ሲበዛ እንዲህ ነው፡፡ በየቀበሌው ለጉዳይ ስንሄድ እኛ እንደምንፈልገው ሣይሆን እነሱ እንደሚፈልጉት ተጽፎ “ማመልከቻችን” ግርጌ ላይ እንደ ቅጽ ፈርመን እንድናስገባ እንገደዳለን፤ ራስህ መጻፍ አትችልም፤ በዚህስ ተገላግለናል፤ መጻፍ የማንችል ዜጎች ጸሐፊ ፍለጋ አንንከራተትም፡፡  በአያያዛችን ሰሜን ኮሪያንም ሳናስንቅ አንቀርም ( እነሱ የሞተውን መሪ ትተው ልጁን ሲያመልኩ እኛ በሞተ ባምስት ዓመቱ በዐፅም እንገዛለን – ለዐፅምም እንድንሰግድ እንገደዳለን! ይቺ ናት የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንቃትና ዕውቀት ማለት! ዱሮ መፈክራችን “ወደፊት!” ነበር፤ አሁን ደግሞ “ወደኋላ!” ሆኗል፤ የማመልከቻውን ናሙናው ከሥር ተመልከት) ዜጎች በሁለት ጎራ ተከፍለው አንዱ ነዋሪ ሌላው አኗኗሪ የሆነባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ የዕብደት ውጤት እንደዚህ ነው፡፡ ዕብደት ማለት አእምሮን በአግባቡ ያለመጠቀም እስከሆነ ድረስ በሆዳቸው የሚያስቡት ደናቁር ወያኔዎች ሀገራችንን እንዳታንሰራራ አድርገው እየገደሏት ነው፡፡ የዕብድ ገላጋዩ ድንጋይ አቀባይም ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር እጅግ በዝቷል፡፡ መጨረሻችንን እንዲያሳምረው ለአንድዬ መጸለይ ነው፡፡

 

በርዕሴ ከጠቀስኩት “ካላበዱ ወይ ካልነገዱ…” ከሚለው ሀገርኛ ብሂል በተጨማሪ  ስለዕብድ ሌላም አባባል አለ፡፡ እሱም “ዕብድና ዘበናይ የልቡን ይናገራል” የሚለው ነው፡፡ አንድ ሰው ካላበደ መቼም በአንድ ጊዜ ጨለማና ብርሃን ለመሆን አይሞክርም፡- ዕብዱ ወያኔ አንዴ “የፍቅር ዓመት ይሁንልን” ይልና በዚያው አንደበት ስለፍቅር ብቻ የሚያዜመውን ብላቴና የሙዚቃ ምረቃውን መከልከሉ አላንስ ብሎ ልጁን በአሸባሪነት መፈረጁና በጦር ለመውጋት ሲዘጋጅ ማየቱ ስም የማይገኝለት ዕብደት ነው፡፡ በአንዲት ትልቅ ሀገር ውስጥ አንድ ግዙፍ መንግሥት ከአንድ ተራ ዜጋ ጋር የእልህ ግብግብ ውስጥ ገብቶ ሲዳክር ማየት ዓለምን ሳያስገርምና የመጀመሪያው ትንግርት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቴዎድሮስ ካሣሁን ከጊታርና ከማሲንቆ ያለፈ መሣሪያ ሳይኖረው ወያኔን በፍቅር ስብከቱ ብቻ እንዲያ ሲያንበጨብጨው መታዘብ አስደማሚ ከመሆን አልፎ የወያኔን ሰብኣዊ ተፈጥሮ እንድንጠራጠር የሚያደርግ ልዩ ክስተት ነው፡፡ ወያኔ እንደሚመስለኝ ከጦር መሣሪያና ከባዶ ጉራና ፉከራ  ይልቅ ይህን  መሰሉን እንደሐምሌ ዝናብ እየሰረሰረ የሚገባን የፍቅር መዓዛና ጠረን በጣም ይፈራል፡፡ ፍቅር የሚያርደውና የሚያሸብረው ደግሞ ሰይጣንንና የሰይጣን የሆነን ብቻ ነው፡፡ እናም ወያኔ ባጭር ቃል ሰይጣን ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮረና በኢትዮጵያ ከባድ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ሁሉም ያስብበት – ሰርፀ ደስታ

ከሰሞነኛ ጉዳዮች ጥቂት ልበልና ላብቃ፡፡ የወያኔው ጉጅሌ ያማረውን ሁሉ በዐዋጅ እየቀማ 26 ዓመታትን በመንግሥትነት ዘልቋል፡፡ ፈጣሪም መጨረሻውን ሊያጃጅልለት ያቀደ ይመስላል እስካሁን እንደልቡ እንዲፈነጭ ሜዳውንም ፈረሱንም ሰጥቶታል፡፡ እነሂትለርም፣ እነሙሶሊኒም፣ የኛው ማፈሪያ ጉድ መንግሥቱም እንዲሁ ቅጥ አምባራቸው የጠፋ ባለጌዎችና ቅል ራሶች ነበሩ፡፡ መጨረሻቸው ግን አላማረም፡፡ አምባገነኖች ዋልጌዎች ናቸው፤ አምባገነኖች ታህተ-ሰብዕ (sub-humans) ናቸው – ለዚህ አባባሌ እነኢዲያሚን ዳዳና እነአፄ ቦካሣ ምሥክሮቼ ናቸው፡፡ ሁሉ ነገር በጉልበትና በወኔ የሚያልቅ ይመስላቸዋል፤ ጭንቅላታቸው የገማ ነጭ ጭቃ እንጂ የሰው ልጅ አንጎል የለበትም፡፡ እውነቱ ታዲያ ሌላ ነው፡፡ ሥልጣንና ዝና የሚቆየው ወይም የማይቆየው በመሣሪያ ብዛት አይደለም፤ በዕውቀት ብዛትም አይደለም፤ በወታደር ብዛትም አይደለም፤ በዓላማ ጽናትም አይደለም፡፡ በሀብትና በገንዘብ ብዛትም አይደለም፡፡ ይህን ምሥጢር አምባገነኖች አያውቁትም፤ ለምን ቢባል ድንጋይ ራስ ናቸውና፡፡ ቀኑ ሲደርስ ሁሉም ነገር ይከዳቸውና እንደወጡ ተንኮታኩተው ይወርዳሉ፤ እንደወፈሩ ሟሽሸው ይኮሰምናሉ፤ እንደታበቱ በሀፍረት ተሸማቀው ይዋረዳሉ፡፡ ቀኑ ነው፤ አለቀኑ ዝናብ አይጥልም፡፡ አለቀኑ እህል አይበቅልም፤ አያፈራምም፡፡ አለቀኑ ሽልም አይወለድም፡፡ “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” ይላል መጽሐፉም፡፡….

ወያኔዎች በሁሉም ረገድ ትግራይን አሳብጠው ወደሚቃዡበት “የትግራይ ሪፓፕሊክ” የሚያደርጉትን ጉዞ ቀጥለዋል – ያላንዳች ሀፍረትና ይሉኝታ፤ ክፉ ዕብድ ሀፍረትም ሆነ ይሉኝታ የለውምና፡፡ ኢትዮጵያውንን ርስ በርስ አባልተው እነሱ ጎጆ ለመቀለስ ሽር ጉድ እያሉ ናቸው፡፡ ይህ ግን ቅዠት ነው፡፡ የቅዠት ቅዠት፡፡ እኔ ትንሹ ሰው እንዴት እንደምስቅባቸው ቢያዩ ምናልባት እነሱም እኔን ዐበደ ይሉኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ገድለው እነሱ በሰላም የሚኖሩ ከሆነ በርግጥም እግዚአብሔር በመንበሩ የለም፡፡ የአማራን ሕዝብ ጨርሰውና የአማራን መሬት ለሱዳንና ለ”ትግራይ ሪፓፕሊክ” ሰጥተው እነሱ በሰላም እንኖራለን ብለው አስበው ከሆነ ይህም ሃሳባቸው ደረጃ ሊወጣለት የማይችል ዕብደት ውስጥ መግባታቸውን በግልጽ የሚናገር ነው፡፡ የሚያደርጉትን ሁሉ ስታዘብ የወያኔነት ቫይረስ የሌለብኝ ጤናማ ትግሬ ነኝ የሚለውም ሆነ ሌላው ሕዝብ ቁጭ ብሎ እህህ ማለቱን ስቃኝ እነዚህ ሰዎች በዚህች ሀገር ሊያመጡ የፈለጉትን መቅሰፍት አስባለሁ፡፡ እነዚህ ዕብዶች የሚያስቡትንና የሚያደርጉትን ነገር የሕጻን አእምሮ እንኳን ይጠየፈዋል፤ ይንቀዋል፡፡ የማይምነታቸው አሰቃቂነት የሚገዝፈው ደግሞ ብሔረሰቦችን ለማናከስ አዲስና ያልነበረ የማንነት ጥያቄ በነሱው ሠርጎ ገቦችና በገንዘብ ኃይል በማስነሳት የረጋውን ኩሬ ለማደፍረስ የሚያደርጉትን ጥረት ስንታዘብ ነው፡፡ ቅማንት የሚል ሕዝብ የለም አልተባለም፡፡ ግን ግን በቅማንት የማንነት ጥያቄ ሰበብ 12 ቀበሌዎችን ወደ ትግራይ ለመውሰድ ማለም – አሁን ሕዝበ ውሳኔም ሳያስፈልጋቸው እንዲሁ ሊወስዱትም ይችላሉ – “አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ” ያለችውን ተረት ያስታውሰናል፡፡ ሥራቸው ሁሉ የሚገርም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፊታችን መስከረም ሰባት ሊካሄድ ዕቅድ የተያዘለት የቅማንት የማንነት ጥያቄ ተብዬና የሕወሓት መፍትሔ ለትግራይ ተጨማሪ የእቶን እሳት የሚያወርድባት እንጂ አንድም ዕድገትና ብልጽና አያስገኝላትም፡፡ ወያኔ ዕድገቱን ጨርሶ ሊሰናበት የቀረው ጊዜ ትንሽ ነው፡፡ በዚህችን አጭር ጊዜ እንኳን አደብ ሊገዛ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ማለት ለኢትዮጵያ  ውድመት ሲባል በፈረንጆች ተረግዞ በፈረንጆች የተወለደና ለወግ ማዕረግ የበቃ የድውያን ቡድን በመሆኑ ግብዓተ መሬቱ እስካልተፈጸመ ድረስ ከጥፋት ሊቆጠብ አይችልም፡፡ የነጋበት ጅብ ያገኘውን እየዘነጠለ ወደ ጎሬው እንደሚገባ ወያኔም ያገኘውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከምድር በታች ሳያስገባ ማንንም ፈርቶ ከጥፋት ተልእኮው ይታቀባል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ በየጊዜው ችግር እየተፈጠረለት ለስቃይ የሚዳረገው የትግራይም ሆነ ሌላው ሕዝብ ግን ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ ለምሣሌ የወያኔን ችግር ፈጣሪነት ይረዳዋል ብዬ የምገምተው ሰፊው የትግራይ ሕዝብ በራያና በወልቃይት ሰበብ የተጠመቀው መርዘኛ ጠላ ተጠጥቶ ሳያልቅ ሌላ አስካሪ መጠጥ ሊያስተናግድ  እንደማይገባው ማወቅ ይኖርበታል፡፡ የዛሬ ገናናነት ነገ አይኖርም፤ የዛሬ ሁሉን አዛዥነት ነገ አይደገምም፤ የዛሬ እዩኝ እዩኝ ማለት ለነገ ሀፍረትና አንገት መድፋት እንደሚዳርግ የማይረዳ ሰው ባይፈጠር ይሻለዋል፡፡ አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነበር፡፡ አሁን ግን ብዙ ወንድሞቻችንን ስናይ አንገታቸው ቦርጫቸው ውስጥ ተወሽቆ ሁሉን ነገር የሚመለከቱት በሆዳቸው ሆነና ከሰብኣዊ የይሉኝታ ማዕቀፍ በፀሐይ ብርሃን ፍጥነት እየራቁ ሄዱ፡፡ ስለዚህ ጤናማ ነኝ የሚል የትግራይ ሰው ልጆቹ ጥጋባቸውን በልክ እንዲያደርጉት በጸሎትም በምክርም ሊሣተፍ ይባል፡፡ ነገር ከተበላሸ በኋላ – እስካሁን ተበላሽቶ ካልሆነ – ቢጸጸቱ ዋጋ የለውም፡፡ የፈሰሰ አይታፈስምና፡፡ በወያኔ ጥጋብ ትግራይ ብትነድ ጉዳቱ የሁሉም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ እንዲህ የምለው ማንንም ለማስፈራራት አይደለም፡፡ “የተሸነፈ” አያስፈራራም፤ የዕልቂት ዐዋጅ ታውጆበት “ጅራቱን ወትፎ” እግር አውጭኝ የሚል አያስፈራራም፡፡ ከሥር ያለ ከላይ ያለ የሚመስልን አያስፈራራም፡፡ ግን ግን ቀኝ ኋላ ዙር መኖሩን አለማሰብ የለዬለት ድንቁርና ነው፡፡ መጽሐፉም “ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ” ይላል፡፡ ግን ማን ሲያስተውለው!

ተጨማሪ ያንብቡ:  በፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ላይ ስለቀረበው ትችት- ጥያቄ ለተከበርከው ለአቶ አኒሳ አብዱላሂ !

ወያኔዎችን እኔ ልምከራቸው፡፡ ምንም ወጪና አታካራ ሳያበዙ ኢትዮጵያን በሙሉ ትግራይ ይበሏትና በአንዴ ይገላገሉ፡፡ ዕብድ የያዘው ገንዘብ አንዴውኑ የተረገመ ነውና ሰውንም ገንዘቡንም ተቆጣጥረው እንዲህ አበሳችንን ከሚያሳዩን ከተቻለ ሁላችንንም እንዳወጣን ሸጠው ይረፉ፡፡ እኛም እንረፍ፡፡ ከመጥፎ አሸናፊ የማይሻል ክፉ ነገር የለም፡፡

“የሌባ ዐይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” ይባላል የነሱ ዓይነት ልብ አውልቅ፡፡ የሚፈልጉትን ለማድረግ የሚከለክቸው ህግም ሆነ ሌላ ኃይል በሌለበት ሁኔታ ማንን ለማታለል እንዲህ እንደሚቸገሩና እንደሚለፉ አይገባኝም፡፡ ምርጫውን እንደሚያጭበረብሩ ሁሉ ምንም ነገር ከማጭበርበር አይመለሱምና ለታይታና ለይስሙላ የሚያደርጉትን ክርክርና ህዝበ ውሳኔ ተብዬ የሚባል ጡት ያልጣለን ሕጻን ሳይቀር ማታለል የማይችል ቁጩ ነገር ትተው መውሰድ የሚፈልጉትን ተራራም ይሁን ሜዳ፣ ህንጻም ይሁን አስፋልት መንገድ፣ ከተማም ይሁን ገጠር በወሬ ቱማታ ሳያደነቁሩን ዝም ብለው ይውሰዱ፡፡ የተቸገሩትም በዚህ ጉዳይ ይመስለኛል – ሕንጻና መንገድ ዘርፎ መውሰድ የሚያስችል ዘዴ ባለመገኘቱ ሳይናደዱ አይቀሩም፡፡ ሌላውንማ አጓጉዘው ጨርሰዋል፡፡ ለነገሩ  ማጓጓዝ ለማይችሉት መሬትንና ምርጥ የሀብት ምንጭን ለመቀራመት ሰዎቻቸውን ከትግራይ እያመጡ በመላው ሀገራችን አስፍረዋል  – ሌላውንና ባለመብቱን እያፈናቀሉና እየገደሉ፡፡ የማስመሰያ ቲያትር ሳያስፈልጋቸው ያሻቸውን እያደረጉ እንደኖሩት አሁንም እንደዛው ማድረግ ይችላሉ፡፡ የማንም ቡራኬም አያስፈልጋቸውም፡፡ በቀሺም ድራማ ሰውን ይበልጥ ከማናደድ ቢቆጠቡ ለኛም አንድ ዕርዳታ ነው፡፡ በጣም ያንገሸገሽን ወዝ የሌለው ቲያትራቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ መሬትና ሕንፃ እንዲሁም መንገድ ተነቅሎ ቢወሰድ ኖሮ ይሄኔ ኢትዮጵያ ባድማ ሆና ነበር – ምን ዓይነት ስግብግብ ናቸው በእግዚአብሔር! የማይጠግቡ እምብርት የለሾች፡፡…

ለማንቻውም መስከረም 7 2010 ጎንደር ላይ ሊያካሂዱት ያቀዱትን የቅማንት ማንነት ህዝበ ውሳኔ ተብዬ ነገር ይተውትና የሚፈልጓቸውን መንደሮች እንዲሁ ይውሰዱ፡፡ ከፈለጉ ሸዋሮቢትንም፣ ደብረ ብርሃንንም፣ ሞላሌንም፣ የኔይቱን ቅምብቢትንም … ወስደው ትግራይ ላይ ይለጥፏቸው፡፡ ማን ይቆጣቸዋል? እነዚህንና ሌሎችንም ቦታዎች ከመሬት ሰቅስቆ ማንሳትና ማዛወር የሚችል ክሬን ካገኙ አዲስ አበባንም ወስደው መቀሌ ላይ ይለጥፏት፡፡ እንጂ አንዴ ፊንፊኔ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ እያሉ ልባችንን አያውልቁ፡፡ ለትግራይ ትልቅነት ስንል መከራችንን በላን – አንዳንዶቻችን ያልበላንን አከክን፤ አንዳንዶቻችን ባልገባንና በማይገባን  ነገር ከወዳጆቻችን ጋር ተቆራረጥን፤ አንዳንዶቻችን እንደኤሣው ለቁራሽ እንጀራ ስንል ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀልና ምሕረትን የሚያስከለክል ኃጢኣት ሠራን፡፡ ግልብነታችንን በገሃድ ያወጅን በሚሊዮን የምንቆጠር ተማርን የምንል ወገኖች አገር ምድሩን ሞልተናል፡፡

ፌዴራል ተብዬ የሌለ መዋቅር እንዳለ በማስመሰል በዚህ ወያኔ ብቻ በሚቀናጣበት የማስመሰያ ጭምብል ኢትዮጵያ መታመስ ከጀመረች ጀምሮ ሁላችንም መቅኖ አጥተን፣ ሰላምና የአምላክ በረከትም ርቆን በስቃይ እንኖራለን፡፡ እምብርት የሌላቸው ወያኔዎችን ተሸክመን የድቅድቅ ጨለማውን መንገድ እየተጓዝን ነው፡፡ መቼ እንደሚያልቅ ዕንቆቅልሽ ሆኖብናል፡፡ ( netsanetz28@gmail.com)

 

ማመልከቻ

 

እኔ አቶ ነፃነት ዘለቀ የክ/ከ 75 ወረዳ 128 የቤት ቁጥር 1219 ነዋሪ ስሆን ያለኝን መኖሪያ ቤት መንግሥት በፈለገው ጊዜ ለቅቄ ለመሄድ የተስማማሁ መሆኔን በፊርማየ አረጋግጣለሁ፡፡

ፊርማ

 

ዋቢ – https://www.psychologytoday.com/blog/spiritual-wisdom-secular-times/201501/four-types-m

1 Comment

  1. “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” ፵፫ዓመት ተባብረው የፈጠፈጧት ኢትዮጵያ ወይስ በጥቅማጥቅም ሊፈጠፍጧት ያዘጋጇት!?
    >”በአዲስ አበባ ከተማ የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት የፅሁፍ ፈተና ከወሰዱ ፭ ሺህ ፻፷፯ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ውስጥ ፱ መቶ ፷፩ዱ መምህራን ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ መቻላቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
    ከ፪ሺህ5 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ፪ሺህ8፰ ዓ.ም በተከታታይ በየአመቱ በተሰጠው የብቃት ማረጋገጫ የፅሁፍ ፈተና ፲፰ ነጥብ ፰ በመቶ መምህራን ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን በትምህርት ቢሮ የሞያ ፍቃድ አሰጣጥና እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሪክተር አቶ አስማማው እስተዚያ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡
    በከተማዋ በአጠቃላይ ወደ ፲፩ ሺህ ገደማ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ያሉ ሲሆን እስካሁን የምዘና ፈተናውን የወሰዱት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን አቶ አስማማው ገልጸዋል፡፡የብቃት ማረጋገጫ ምዘናው ፹ በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው የፅሁፍ ፈተናው መሆኑና ቀሪውን ፳ በመቶ የማህደር ተግባር ምዘና የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል፡፡ የመምህራኑ የምዘና ውጤት መምህራኑ ከሚያገኙት ትምህርትና ከስልጠና ጀምሮ በፈተና ሂደቱ ውስጥም ያለውን ክፍተት እንደሚያሳይ ፤ነገር ግን እንደጅምር ከሌሎች አገራት ተሞክሮም አንፃር በጊዜ ሂደት የሚሻሻልና ጥሩ የሚባል እንደሆነ አቶ አስማማው ገልፀዋል፡፡ የብቃት ምዘና ፈተናው መሰጠቱ መምህራኑ በአጠቃላይ በመማር ማስተማር ሂደቱ የሚገኙበትን አቋም ለማሳወቅ የሚያስችልና ያለባቸውን ክፍተትም በመጠቆም ተገቢ ስልጠና ለማግኘት ያስችላል ተብሏል፡፡
    የህዳሴ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህር የሆኑት አቶ ኃይለጊዮርጊስ ሙሉነህ ፈተናው የመምህሩን ሁለገብ ብቃት በሚገባ የሚፈትን እንደሆነና እሳቸውም ውጤቱን እንደጠበቁት ባይሆንም ከትምህርት ቤቱ ያለፉ ብቻኛ መምህር መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
    የሞያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና በአንድ ጊዜ ሁሉንም መምህራን ለመመዘን ከአቅም አንፃር አዳጋች እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በሂደት ግን ሁሉንም መምህራን በመመዘን የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡ (በናትናኤል ጸጋዬ)
    **************!ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊነት ቀለጠ በለው!
    ____” የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አምስት ኃላፊዎች፣ በድምሩ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት ገለጸ፡፡(ጉዳቱ በቦንብ ነው? በሜንጫ?)”
    ____”በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት 63 የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደሆኑ፣ በመንግሥት ላይ የ170 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዳደረሱ ተገልጿል፡፡በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ የተያዙ ተጠርጣሪዎች 125 ደረሱ ፡ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ነው፡፡ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ታደለ ደመቀና የደረቅ ቆሻሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ ፋንታሁን የምርመራ መዝገብ እስከ ቢሮ አስተዳደር ጸሐፊ ድረስ የተካተቱበት 24 ተጠርጣሪዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የተጠርጠሩትም በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸው ነው።”
    ______ “የማነ ግርማይ ጠቅላላ ስራ ተቋርጭ ኃ.የተ. የግል ማህበር የተባለ ድርጅት በድምሩ 920 ሚሊዬን 529 ሺህ ብር ተገቢ ባልሆነ መንገድ ክፍያ ስለተፈፀመለት ምርምራ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል::”ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት 20 ሚሊዮን ብር ያላግባብ ተከፍሏቸዋል የተባሉትና ለባቱ ኮንስትራክሽን የተሰጠ የመሬት ምንጣሮ በመንጠቅ ለየማነ ጠቅላላ ተቋራጭ በመስጠት ከ216 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩት አቶ የማነ ግርማይ፣ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ መሣሪያ ማስተኮሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ይዞ የሄደ ቢሆንም፣ መሣሪያ በማስተኮስ ላለመያዝ ሙከራ ካደረጉ በኋላ፣ ወደሚያውቁት ባለሥልጣን ከደወሉና እጃቸውን እንዲሰጡ ሲነገራቸው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ መቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸውም ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸውንም አክሏል፡፡ ”
    ____ በኦሮሚያ ክልል በ3 ከተሞች በህገወጥ መንገድ የተያዘ ከ264 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማስመለስ ተችሏል
    ____የትግራይ ባለሃብቶች ከ498 ሚሊዬን ብር በላይ ማጭበርበራቸው ተገለጸ
    _____”በአማራ ክልል የተሿሚዎች ሀብት ተመዘገበ አቶ ዮሐንስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልሉ ውስጥ ካሉ ተሿሚዎች መካከል የ1,945 ወንድና የ508 ሴት በጠቅላላው የ2,453 ተሿሚዎች ንብረት መዝገቦ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡”
    _____” የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከዓመት ከመንፈቅ በኋላ ወደ ሁለት አኃዝ ተሸጋገረ፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ ባወጣው የነሐሴ ወር መረጃ፣ የዋጋ ግሽበቱ 10.4 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡”
    _____ ” በአሁኑ ወቅት ከ8.5 ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተጎጂዎች ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. የሚያቆይ የምግብና ሌሎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታዎችን ለማቅረብ 487.7 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ፡፡”
    _____ “ለ፲ ዓመት ተከታታይ ዕድገትን ለማስረጽ ለአሥር ቀናት ‹‹መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› በሚል መሪ ቃል እየተደረገ ያለው ክብረ በዓል፣ እስከ አራት ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡”
    ___፟ ነጻነታችን ሲዘልቅ የጫካው ማኒፊስቶ የከተማው ሕገመንግስት የገባው፡ ከከፍታው በታች ‘አስፈቅዶና አሳወቆ’ የሚንቀሳቀስ ፡ከአያት ቅደመ አያቱ የወረሰው ሀገርና ቤት የአውራው ፓርቲና ገዢው መንግስት የሆነ፡ የጣሪያና ግድግዳ ባለቤት ብቻ ሆኖ የቀረ ሰው፡ “ካላበዱ ወይ ካልነገዱ” ዜጋ ሳይሆን መጤ/ሰፋሪ ተብሎ የተፈረጀ ፡የበይ ተመልካች፡ እንደ አኗኗሪ የተመዝገበ እንደተንቀሳቃሽ ንብረት የተቆጠረ፡ የነበረበትን ዘመን በትዝታ፡ ያለበትን ዘመን በአግራሞት ትዝብት ፡ የከፍታው ዘመን ሲያስፈራው እንግዲህ ያውላችሁ ጣሪያና ግድግዳችሁ።አራት ነጥብ።
    ማመልከቻ

    “እኔ ነፃነት ዘለቀ የክ/ከ 75 ወረዳ 128 የቤት ቁጥር 1219 ነዋሪ ስሆን ያለኝን መኖሪያ ቤት መንግሥት በፈለገው ጊዜ ለቅቄ ለመሄድ የተስማማሁ መሆኔን በፊርማየ አረጋግጣለሁ፡፡

    ፊርማ

Comments are closed.

Share