ስትሄድ የመታህ ድንጋይ ስትመለስ ከደገመህ ከራስህ ጋር  ስብሰባ መቀመጥ ይገባሀል – ከያሬድ አውግቸው

የህውሃት መንግስት 2010 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ለማክበር የጀመረውን  ከባህሪው የወጣ ድርጊት ተመልክተው አንዳንዶች ስርዓቱ እውነተኛ የመንግስትነት ባህርይን እየያዘ  ነው ሲሉ ይደመጣል። እነዚህ የዋሆች  ሰሞኑን ከነሀሴ 26 ቀን ጀምሮ  የፍቅር ቀን ፣ የእናቶችና ህፃናት ቀን ፣የአረጋውያን ቀን ፣ የሰላም ቀን፣ የንባብ ቀን፣ የአረንጓዴ ልማት ቀን፣ የመከባበር ቀን ፣የሀገር ፍቅር ቀን ፣ የአንድነት ቀን  እና የኢትዮጵያ ቀን  በሚሉ መለያዎች አዲሱን ኣመት ለመቀበል ህወሀት የያዘውን ፕሮግራም እንደ አንድ ማስረጃነት ሲጠቅሱ ይታያል። ታርሟል በሚል።  መሬት ላይ የምናያቸው የስርኣቱ ባህርያት በምክንያት ለገመገመ ሰው ግን ስርዓቱ  ለመሻሻል ፍላጎት እንደሌለው ይገነዘባል። በእኔ ምልከታ ችግሩ  ከድርጅቱ  ፍጥረታዊ ባህርይ ጋር የተያያዘ  እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ።

በመጀመሪያ ደረጃ ህወሀት  ከምስረታው ጀምሮ በጠላትነት የሚያሳድደው አመለካከት ፍቅር፣ አንድነት እና ኢትዮጵያ የሚለውን ሀይል አይደለም እንዴ? እስከዚህ ሰዓት ድረስ  የተበዳይና የበዳይ ድርሰት እየደረሰ  በህዝቦች መካከል ቁርሾ የሚዘራው ማነው?  በሌላ በኩል  የዘር ብሄርተኝነትን ከሚገባው በላይ በማራገብ ኢትዮጳዊነትን ያኮሰመነ  መንግስትስ ማን ነው?  የህወሀት መንግስት አይደለምን? ታዲያ አሁን ምን ተገኘ የሚለው በደንብ መታየት ያለበት ይመስለኛል። በእኔ ምልከታ ይህ እርምጃ  ህወሀት በአሁኑ ወቅት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በአንድነት የተነሳበትን ተቃውሞ ለማቀዝቀዣነት የዘረጋው ስልት ነው።የአንድነት ሀይል ነው ተብሎ የሚታሰበውን የአማራ ሀይል ጉርሻ ነገር በመስጠት ማስታገስ ላይ ያነጣጠረ ስልት። በዚህም  በቅርቡ በአማራ ክልል በክልል  ደረጃ  ለመተግበት ህዝቡ በእቅድ የያዘውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ ህዝባዊ አድማ ማለዘብ የስልቱ ዋና አላማ ነው።   ይህም ህወሀት ሙሉ ሀይሉኝ በኦሮሚያውና ሌሎች ክልሎች  ላይ እንዲያተኩር ይረዳዋል።  ህውሀት እንደዚህ እይነት  ብልጣ ብልጥ እርምጃዎች  ይዞ ሲመጣ ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን  እንዳለብን ልምዳችን  አስተምሮናል።  ከትንፋሽ በሃላ ይበልጥ አሳሪ  ህግና አሰራሮችን ይዞ  በበቀል የመጣባቸው ብዙ ልምዶች ስላሉን።  ከ1997 ምርጫ ተከትሎ  የአንድነት ህይሉን፣ ነጻ ፕሬስ እና ማህበራትን  ለማጥፋት የወሰዳቸው እርምጃዎቹን ማስታወስ ይገባል።  ድርጅቱ ግለሰብና ፓርቲዎች  ብቻ ሳይሆን ከተማዎችንም በቂ በቀል የሚቀጣ  መሆኑን ማስታወስ ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ውሸት ቁጥር የለውም” እና “አያ ጅቦ - ኦሮሙማ መጣብህ” !!

የህወሀት እታደሳለሁ የሚሉ ለቁጥር አታካች መሀላዎች ያመጡልን ነገር ቢኖር በተደራጀ መንገድ የሚያካሂደው የሀገር ሀብት ዘረፋ መባባስ ነው። የባርነት ሰንሰለቱ  ይበልጥ መጥበቅ ነው። የህዝቦች እርስ በርስ ጥላቻ መበራከት ሌላው ህወሀት እድሜው በጨመረ ቁጥር አብረው የጨመሩ ክስተቶች ናቸው።  ስለዚህ  “ስትሄድ የመታህ ድንጋይ ስትመለስ ከደገመህ ከራስህ ጋር  ስብሰባ መቀመጥ ይገባሀል” ብለናል ።  ለዲሞክራሲያዊ  ስርዓት መመስረት ሀገራችን ያላት መንገዱ አንድ ብቻ ነው። ህዝቦች መሪዎቻቸውን በምርጫ ካርድ ወደ ስልጣን የሚያመጡበት    የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መዘርጋት ብቻ። ለዚህም ከተጽህኖ  ነጻ የመከላከያና ፖሊስ ሰራዊቶች፣ ነጻ የምርጫ  ቦርድ እንዲሁም እንደ ኬንያው  ነጻ ፍርድ ቤቶች በህዝቦች ንቁ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት በአጭር ወቅት መገንባት ይኖርባቸዋል።

 

 

1 Comment

  1. ወያኔ፥አንድም፥የህሊና፥እስረኛ፥ሳይፈታ፥ጋዜጠኞችንና፥ሠላማዊ፥ፖለቲከኞችን፥እነ፥ፕሮፌሰር፥መራራ፥ጉዲናን፥አስሮ፥እያሰቃየ፥ ”ፍቅርና፥የኢትዬጲያ፥ቀን” እያለ፥ያሾፋል:እንደ፥ወያኔ፥ያለ፥ተራ፥አጭበርባሪ፥፥መንግሥት፥በዓለም፥ላይ፥ያለ፥አይመስለኝም፥፥

Comments are closed.

Share