ሐምሌ ሁለት ሽ ዘጠኝ ዓ.ም
“ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውን እንመሰክራለን(ዮሐ 3፡11)
“ስለ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬና ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ “ያየነውን እንድንመሰክር የሰማነውን እንድንናገር በር ለከፈተልን አምላክ ምስጋና ይገባዋል።
አገራቸውንና ቤተክስርቲያናቸውን ከውጪ ነጣቂ ተኩላዎች ለመከላከል ሲዋትቱ የኖሩት ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤና መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ሞተውም አንዳያርፉ፤ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የውጭ ጠላቶች ለቀየሱት መርሀ-ግብር አስፈጻሚ በሆኑት ባለጊዜዎች አጽማቸው ፈልሷል፡፡ ክርስቶስ “ ያየነውን እንመሰክራለን የምናውቀውን እንናገራለን እንዳለው፤ ወጣቶች ቀኝ ጌታ የጻፏቸውን ትያትርና ግጦሞች፤ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ “ ወጣት ተመልከት እንዳትሳሳት እያሉ የጻፉትን መጽሐፍ በማንበባቸውና ሲወራላቸው በመስማታቸው ብቻ፤ ብሔራዊ ውለታቸውን በማይመጥን መንገድ በአጽማቸው ላይ በየተፈጸመው አዝነው የተሰማቸውን ቅሬታ ለመግለጽ ጥረዋል። የነሱን ፈለግ በመከተል ለሀገራቸውን ለቤተ ክርስቲያናቸው ሊያደርጉ የሚገባቸው ብዙ ነገር ቢጠበቅባቸውም፤ የተሰማቸውን ቅሬታ ለገለጡ ወጣቶች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
እኔ ግን የፃፉትን በማንበብ ብቻ ሳይሆን በተለይም መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የሰሯቸው የተናገሯቸው በጥልቅ በስፋትና በማስረጃ በሚነገርበት መንደር ተወልጄ፤በእጃቸው ተዳስሸና በድምጻቸውም ተመክሬ አድጌአለሁ። የሉቃንስ ወንጌል “ብዙ ከተሰጠው ሰው ብዙ ይፈለግበታል። ብዙ አደራ ከተሰጠውም አብዝተው ይሹበታል (ሉቃስ 12፡48)እንዳለው፤ መጻፋቸውን ባነበቡትና ሲወራላቸው በሰሙት ብቻ ተገደው የምስክር ሀላፊነታቸውን ከተወጡት ወጣቶች፤ በኔ ላያ ያለው የተደራረበው የሐላፊት ክብደት ይህችን ጦማር እንደ ክብሪት ጭሮብኛል፡፡
እንደሚታወቀው ክብሪት በሁለት ጎናቸው በየራሳቸው የእሳት ባህርይ የተሸከሙ የስንጥሮች ክምችት ጥቅል ስም ነው። እኔም ከተወልድኩባት መንደር ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ስለ ስለመላከ ብርሃን አድማሱ የሰማሁት፤ እራሴ ባይኔ ያየሁት ሲናገሩም የሰማሁት እንደ ክብሪት ስንጥሮች ሰብስቦ ሁለት ጎን ያለው የክብሪት ባኮ ሆንኩ ። ባንድ በኩል ያጽማቸው መፍለስ የቀሰቀሰው ጫጬታ ይጭረኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ባፅማቸው ፍልሰት ተቀስቅሶ ከሞላ ጎደል በመነገር ላይ ያለውን ሞልቼ የማቅረብ ሀላፊነት እንዳለብኝ የተማርኩት ሌላኛውን ጎኔን ይጭረኛል።
ስለዚህ ከላይ እንደተገለፀው ክርስቶስ “ያየነውን እንመሰክራለን የምናውቀውን እንናገራለን” እንዳለውና የመጽሐፍ ትርጓሚ መምህራችን የኔታ ብርሃኑ “እስመ ብዙሀን እለ ወጠኑ ይንግሩ . . . . ጥዩቀ ኩሎ በበመትልው ሊተኒ ረትአኒ እጽሐፍለከ ዐዚዝ ቴዎፊላ” ሉቃስ፦ 1፡1᎗4) ብሎ ቅዱስ ሉቃስ የተናገረውን ሲያብራሩ “ተቀባይና ቅንነት ያለህ ቴዎፍሎስ ሆይ ምንም እንኴ ሌሎች ቢጽፉትም ለየት ባለመንገድ እንደገና ልጽፍልህ ቀናኝ ብሎ በቴዎፍሎስ አማካይነት ለሌሎች እሱን ለመሰሉ ሁሉ እንዲደርስ ጻፈው” ብለው እንዳስተማሩን ያየሁትን ፣ የሰማሁትንና የማውቀውን እመሰክራለሁ፤ እናገራለሁ፡፡ ስናገርና ስመሰክርም የተስሎንቄ ክርስትያኖች የቀደመውን የሚያዛባና መሰረት የሚያስለቅቅ ወይም ቆርጦ በማቅረብ ፈተና ላይ ሲወድቁ፤ ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በአንደበታችንም ሆነ በመልእክታችን ያስተላለፍንላችሁን ትምህርት አጥብቃችሁ ያዙ”(2ኛ ተሰ 2፡14) ሲል ያስተማረውን አስታውሳለሁ፡፡
ዛሬ አጽማቸው የፈለሰው የነዚህ ታላላቅ አባቶች ታሪክ እንኳን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያደገ ይቅርና ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ላገራቸውና ለቤተክርስትያናቸው የሰሩትን ከመመስከር ቢሸሽ ከህሊናዊ ግዴታ የሚያመልጥ አይደለም። እነዚህ ሊቃውንት ሌላ አገር ያፈራቻቸው ቢሆኑ ኖሮ በስማቸው ብዙ መታሰቢያ ይደረግላቸው ነበር፡፡
መላከ ብርሃን አድማሱንና ቀኝ ጌታ ዮፍታሄን የኢትዮጵያና የቤተክርስትያናችን ጥሪ ያገናኟቸው የዘመናቸው አርባኛች ነበሩ። በመጽሀፈ መቃቢስ ” የነገር መወደድና ደም ግባት የነበራቸው፡፡ በኃይል አርበኞች ናቸው (መቃ 2፡11)”ተብለው እንደተገለጹት መቃብያን ነበሩ። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በዚህ ዓለም የኖሩት 52 ዓመት ነው። መላከ ብርሃን የኖሩት 77 ነው። ዮፍታሄ በእድሜ ለመላከ ብርሃን ታናሽ ነበሩ። ይሁን እንጅ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ከሞቱ በኋላ መላከ ብርሃን 25 ዓመታት ኖረዋል። ቀኝ ጌታ ቅኔውን ህዝባዊ በማድረጋቸው ፤ በነ አቶ መርስሄ ሀዘን አበበ እና አስማማው ገብረ ወልድ በነ አቶ አቤ ጉበኛ ህይወት የሚፍለቀለቁ ምንቸቶች ናቸው እየተባሉ ይደነቁ ነበር። መላከ ብርሃን አድማሱ ደግሞ ከመነጨበት ተነስቶ ጣና ሀይቅ እንደሚገባውና ሳይታይ ጎጃምን በሚዞረው ዓባይ ወንዝ ይመሰሉ ነበር፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ለዛና ውበት እውቀት ስፋትና ጥልቀት የነበራቸው ሃያላን አባቶች ነበሩ።
እናስታውስ!ባንድ ዘመነ መንግሥት የተከሰተ ነገር፤ የመንግስትን ድካም የሚገልጥ ከሆነ፤ መንግስት እስኪያልፍ ድረስ ይደብቀዋል። “የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም”(ማቴ 10፡ 26)ያለው የክርስቶስ ቃል የማይታበል ነውና፤ ባንድ ግፈኛ መንግሥት የተደበቀ እውነት በሚቀጥለው መንግስት ይከሰታል። ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ መላከ ብርሃንን በሞት በተለዩዋቸው በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዘመን አልፎ አልፎ በነ አቶ መርስሄ ሀዘን አበበ፤ አቶ አቤ ጉበኛና በቅኔ መምህራን ይነሱ ነበር።
ከቀኝ ጌታ ቶፍታሄ ሞት በኋላ፤ መላከ ብርሃን ላገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ህያው ቅርስ ለማትረፍ ቀሪ ዘመናቸውን በመሻማት ይንቀሳቀሱ ነበር። ላገራቸውና ለቤተክርስትያናቸው ያበረከቱት ግን እስከዚህም በመንግስትና በሕዝብ ዘንድ አይወሳም ነበር፡፡ ይባስ ብሎም ሃይማኖት ሊያፈርስና አገር ሊገዛ የመጠውን ፋሽሽት በእነዚህ ሊቃውንት አስተባባሪነት በብዙ ሺዎች ከሚቆጠሩት ጀግኖች ጋራ ድባቅ የመታው የበላይ ዘለቀ ታሪክም ተቀብሮ ይኖር ነበር፡፡
ዳሩ ግን ”የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ ባዓይናችሁ እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር። ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማነው?“ (ገላ 3፡1 )እንዳለው፤ ስለ በላይ ዘለቀ ለመጻፍ የሞከሩ ቢኖሩም፤ እስር ቤት ሰብሮ ሊያመልጥ ሲል ተገደለ በማለት በራሱ ስህተት እንደተሰቀለ አድርገው በማቅረብ ጀግናውን ተወቃሽ በማድረግ ነበር ሲጽፉ የኖሩ፡፡ በንጉሡ ዘመን በላይ ዘለቀ በዘፈንና በቀራርቶት የታወስ የነበረው በብቸና አውራጃና ግፋ ቢል በመላ ጎጃም ብቻ ነበር።
በላይ ዘለቀ፤ ተሰቅሎ በተቀበረበት ቦታ ታሪኩ ዘልቆ ብቅ ያለው፤ ለመታሰቢያውም መንገድና ትምህርት ቤቶች የተሰየሙለት ሰቅሎ የገደለው ሥርዓት ፈርሶ ደርግ ሲተካ ነው። ደርግ በዘመኑ በላይን ማስታወሱ መልካም ቢሆንም፤ ደርግ የራሱን ፖለቲካ ማብለጭለጫ ለማድረግ እንጅ የበላይን ስራ አክብሮ ወዶ ያደረገው አይመስልም። የበላይ ዘለቀን ስሜትና ጀግንነት አክብሮና ወዶ ቢሆንማ ኖሮ፤ የበላይ ዘለቀን መንፈስ ይዘው የታገሉትን ሁሉ ጀግኖች በመግደል አገሪቱን ባዶ ባላደረጋት ነበር። ስለዚህ ደርግ ለበላይ ያሳየው ክብር ጎደሎ ስለነበረ ምስጋናውን ፍጹም አላደረገውም።
በፈርንጅ ሴራና ትልቅ እርዳታ ደርግን ጥሎ የራሱን ህዝብ እየበላ እና እያስበላ ህዝብ እየከፋፈለ ኦርቶዶክስንና አማረውን እየሰበረ ብቅ ያለው ወያኔም የራሱን ፖለቲካ ለማብለጭለጭ ደርግ የገደላቸውንም እራሱም የገደላቸውን ደርግ እንደገደላቸው አድርጎ ከመቃብር እያወጣ ሕዝብን አስለቀሰ፡፡ ይህንን ያደረገው የራሱን መርሆ ለማኪያሄድና ደርግን ለማስነቀፍ ብሎ እንጅ ለሞቱት አዝኖ አይደለም። ለሞቱት አዝኖ ቢሆን ኖሮማ የነ በላይ ዘለቀን መንፈስ ተከትለው የተነሱትን የተቆረጠውን ያገራቸውን አንገት በቀዶ ጥገና ሊጠግኑ የጣሩትን ፕሮፌሰር አስራትንና ሌሎችንም እስካሁን ድረስ ላገራቸው የሚታግሉትን ዜጎች ባልጨፈጨና ባላሳደደም ነበር። “የቤተ ክርስትያንንና የአማራን አከርካሪ ሰብረናል” እያሉ ሊፎክሩ ይቅርና ባላሰቡም ነበር፡፡ ላገራቸው ላበረከቱት ምሁራዊ አስተዋፅዎና ያርበኝነት ተጋድሎ መታሰቢያ ሊሰራላቸው የሚገባቸውን የመላከ ብርሃን አድማሱና የቀኝ ጌታን መቃብር ባልቆፈሩ ነበር፡፡
ይህ ከሁሉም የከፋ የወያኔ አገዛዝ ላገራችንንና ለቤተክስትያናችን ራሳቸውን አሳልፈው የሰጥቱን አባቶቻንን እያሳደደ ሲገል፤ መቃብራቸውን እየቆፈረ የጀግኖችን አጽም ሲጥል፤ ለምን ብለን የመጠየቁ አደራ እሚወድቀው እኛ ቋሚዎች ላይ ነው፡፡ አደራ በልቼ ማለፍ ስለማልሻ እነዚህ ሊቃውንትና አርበኞች በተለይም በመከራ ጊዜ አብረዋቸው ተሰልፈው ከነበሩት ጓደኞች ብዙ እየሰማሁ ያደኩና፤ በእጃቸው የዳሰሱኝ በቃላቸው የመከሩኝ መላከክብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተው ለቤተክርስትያናችን ያበረከቱትን በረከትና፤ ለእነ በላይ ዘለቀ ድል ያበረከቱትን ግዙፍ አስተዋፅዎ በተከታታይ ጽሑፎች አቀርባለሁ፡፡
“መጥፎ ነገር ለመልካም ይመጣል” እንደሚባለው ምናልባትም አጽማቸው በታሪክ አጥፊዎች ተወርውሮ የተጣለው፤ ተደፍኖ የኖረው ታሪካቸው ተቀስቅሶ ምሳሌ ላጣው ትውልድ ምሳሌነታቸው እንዲነሳ ያገለገሉት መለኮት ፈቅዶ ይሆናል፡፡ እኔም ያጽማቸውን ፍልሰት ተመርኩዤ በአየር መርዝ እየረጨ፣ በምድር ታንክና መትርየስ እያርመሰመሰ፣ በረቀቀ ስለላ እየታገዘ፣ በባንዳዎች እየተመራ የመጣውን የፋሽሽት ጣልያን ሰራዊት የድንኳን መትከያ ትንፋሽ እንዳያገኝ ለማድረግ እነ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ በላይ ዘለቀንና ሌሎችም ዝናቸው ገና ያልተነገረላቸውን ጀግኖች የጦር መሪዎችን በማጠናከርና በመርዳት ለድል ብቃት የተጫወቱትን ጥበብ እገልጻለሁ፡፡
በበላይ ዘለቀ ይምሩ የነበሩት የጎጃም አርበኞች፤ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ያውሮጳን ጦር፤ በወጨፎ፣ በውጅግራ በአልቢን፣ በቤልጅግ፣ በጦር በጎራዴ በብትር በድንጋይ በቀራርቶና በፉከራ ድባቅ እንዲመቱት ያድረጉበትን የመላከ ብርሃን አድማሱን ምስጢር “በዚህ ዘመን ያለው ወጣት እንዲመለከተው እንደምሳሌም እንዲጠቀምበት አቀርብለታለሁ፡፡
በዚህ ዘመን በእኔ እድሜ ያላችሁ አባቶች! ወልዳችሁ የልጅ ልጅ ያያችሁ መላከ ብርሃን አድማሱ በቁማቸው እንዳደረጉት ሞተውም በመጽሓፎቻቸውና በደቀመዛሙርቶቻቸው አማካይነት ለቤተክርስቲያናቸውንና ላገራቸው ያደረጉትን ለወለድናቸው ልጆቻችን ማቀበል ባለመቻላችን ከኛ አብራክ የፈለቁት በኛ አባትነታት እንዳፈሩብን የተረዳን አይመስለኝም ።
ወጣት ልጆቻችን እኛ እንደካድናቸው ተገንዝበውና ታዝበው መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የመሳሰሉትን አያቶቻቸውን እያስታወሱ እርስ በርሳቸው ላለመከዳዳት በስማቸው እየማሉ አገራቸውንና ቤተክርስቲያናቸውን ወደነበሩበት ክብር ለመመለስ በመታገል ያሉትን ብንችል እንደግፋቸው። ባንችል እንቅፋት አንሁንባቸው።
በመታገል ላይ ያላችሁ ወጣቶች ሆይ!የመላከብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ምሳሌነት ለኢትዮጵያዊነታችሁ ብርሃን ሆኖ የማስታዋል አድማሳችሁን እግዚአብሔ እንዲያሰፋላችሁ እጸልያለሁ፡፡
ይቆየን፡፡