የ‹‹እናውቅልሃለን›› የፖሊቲካ ፍልስፍና ውጤት! ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ

ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ, PH.D.*

‹‹የሕዝባችን ብሶትና የድሆች አሰቃቅ ሁኔታ እስከ አጥንታችን ድረስ ዘልቆ ተሰምቶናል›› ያሉን ‹‹ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች››፣ የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖሊቲካዊ ፍልስፍና ማራመድ ከጀመሩ እነሆ 42 ዓመት አስቆጠሩ። ከዛ ጊዜ ወድህ የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖሊቲካዊ ፍልስፍና በሀገራችን ባሕል ሆኖ ቆይቷል።

(1) በአንድ በኩል፣ አብዮታዊ መንግስት የመሰረቱ ‹‹ቡዳዎች›› ተነስተው ለሰፊው ሕዝብ መቆማቸውን አበሰሩን። የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አብዮታዊው መንግስት ከፊውዳሉ መንግስት ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ስሰማ፣ ጮቤ መርገጥ ጀመረ። እነኝህ ግለሰቦች፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንደሚኖር ለሰፍው ሕዝብ ቃል የገቡት፣ በኮምቶ ሥላሴ ስም ምሎ ሳይሆን፣

‹‹የአብዮቱ ሰይፍ አንገታችንን ይቀንጥስ›› በማለት ነበር። የአብየቱ ሰይፍ ወድያውኑ መቀንጠስ የጀመረው ግን፣ የሕዝቡን አንገት እንጅ የ‹‹ቡዳዎቹ››ን አልነበረም! የ‹‹እነውቅልሃለን›› የፖሊቲካ ፍልስፍና ከቀመሩ ‹‹ቡዳዎች›› መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ጅቦች ነበሩ። አብዮቱ በጅቦች እንደ ተጠለፈ የገባት ሄለን መሃመድ፣ ትዝብቷን እንድ ስትል አስፍራ ነበር፡-

አብዮት አብቦ—ጎምርቶ አሽቶ

የሚዘነጥፈው—የሚቆርጠው ጠፍቶ

ጅቡ በላው አሉ—ሌት ከማሳው ገብቶ

 

አብዮቱን ከጅቦች ማጥራት አልተቻለም ነበር። ሆድና ጅብ የአንድ ስሙኒ ሁለት ገጽታ በመሆናቸው፣ ለድሆች አሰቃቅ ሁኔታ ቁብ የሰጠ አልነበረም የ‹‹እናውቅልሃለን›› የፖሊቲካዊ ፍልስፍ ‹‹የግል ጥቅምን ብቻ ማሳደድ›› በሚል የጅቦች አስተሳሰብ ተተካ። ‹‹የሕዝብን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል ወንጀል ነው›› የሚሉትን ሰዎች በጥይት እንደ ንፍሮ ቀቀሏቸው። እንደ ነፍሮ ከተቀቀሉት አንዱ በዓሉ ግርማ ነበር። ወንጀል ስለሰራ ሳይሆን፣ ‹‹በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ኔጋዴዎች አብዮቱን ማጥራት ያስፈልጋል›› ብሎ ስለጻፈ ብቻ ነበር። ከበዓሉ ‹‹አንደበት›› እንስማ፡-

 

‹‹…ለግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ሥልጣን የሚያሳድዱ ሰዎች በዘተዋል።አደገኛ አዝማሚያ ነውየተንኮል ገበያ

ደርቷል። ከዚያ እንግዲህ ምናለ? መኪናና ቪላ ማማረጥ፥ ጥሩ መብላት፥ መጠጣት፡ መልበስ፥ መሽቀርቀር፥ በየዕለቱ

የበሰለ ብርቱካን እየመሰሉ መሔድእንድያም ሲል ቆንጆ ቆንጆዎችን እያማረጡ ሕይወትን መቅጨት። በስልክ ሀሎ!

እያሉ ቤት ለምትፈልገው ቤት፥ ሥራ ለምትፈልገው ማለፊያ ሥራ፥ የደመወዝ ጭማሪ ለምትፈልገው ማለፊያ ጭማሪ።

ተጠቅሞ መጥቀም፥ በለቶ ማብላት፥ ማብላትና መብላት። በሥልጣን እየተጠቀሙ ጥቅሞችን ለወደዱትና ለፈለጉት እንደ ጠበል መርከፍከፍ። ይህ ሁሉ እየታየ ነው። እኔ የምሰጋው በሕዝብ ስም ተነስተን ከሕዝብ እየራቅንለሕዝብ ባዳ እየሆን እንዳንሔድ ነው። ጥራት! ጥራት! በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ኔጋዴዎች አብዮቱን ማጥራት ያስፈልጋል። ለግል

ታርክ፥ ለግል ዝና ይበልጥ ስለምንጨነቅ ኀብረት ጠፍቶ ግላዊ ሩጫና ጀብደኝነት ይነግሳል።እኔ ከጠላት ይልቅ በጣም የሚያሰጋኝ ይህ ነው›› (ኦሮማይ፣ ገጽ 298-299።)

 

መቸም ሆዳም ሰው እምብርት የለውም፣ ጅብ ነዋ! ሰውየው ‹‹ድንቁርናና ስልጣን ሲጋቡ ውጤቱ አደገኛ ነው›› ብሎ የተነበየው ነገር ለካስ ትክክል ነበር! አብዮታዊው መንግስት ለዘለዓለሙ ላይመለስ ተሰናብቶን የሄደው ከ25 ዓመት በፊት

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትዕግሥተኛ ሰው - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ነበር! ነፍሱን ይማር!

 

(2) በሌላ በኩል፣ ከ17 ዓመት የትጥቅ ትግል ቦኋላ የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖሊቲካዊ ፍልስፍና ከአብዮታዊው መንግስት

‹‹የተረከበው›› ልማታዊ መንግስት፣ ‹‹በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ክራይ ሰብሳቢዎች ልማቱን ማጥራት ያስፈልጋል›› ብሎ

ከተነሳ 25 ዓመታትን አስቀጥሯል። ከኢሕአዴግ ‹‹አንደበት›› እንስማ፡-

 

‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት ፖሊቲካዊ ኢኮኖሚ የበላይነት ባገኘበት አገር የመንግስትን ሥልጣን መቆጣጠር ከሞላ ጐደል ብቸኛው የመበልጸግያ መሣሪያ ይሆናል። ሥልጣኑን የያዘና ሥልጣኑን ከያዘው ጋር በቅርብ የተሳሰረው ሁሉ ኪራይ

መሰብሰቡን በሰፊው በማስኬድ እንደሚከብርና መንግሥት ሁሉንም እንደ ልማት አስተዋጾኦ እኩል ማስተናገድ ሳይሆን

እንደ ቅርበቱ የኪራይ መሰብሰብ ዕድል እንደሚከፍትለት ስለሚታወቅ ሥልጣን መቆጣጠር የሞትና የሽረት ጉዳይ ይሆናል።ኪራይ ሰብሳቢነት የፖሊቲካ ትግሉ የአመለካከት ሳይሆን በዋናነት የኪራይ መሰብሰብ እድሎችን በሞኖፖል

በመያዝ ወይም በመጋራት ጥያቄዎች ዙሪያ የሚከናወን ነው። የሰለጠነና የተረጋጋ ትግልና የሥልጣን ሽግግር ሳይሆን

የኑሮ መሠረትን በመገንባትና በመከላከል ዙሪያ የሚከናወን ፍልሚያ የሚካሄድበት ዴሚክራሲ ይሆናል።…(ኢሕአዴግ፤ ልማት፣ ዲሞክራሲና አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ አድስ አበባ፣ 1999፣ ገጽ 83ff)

 

ከደኅረ ቅኝ-ግዛት አፊሪካ ፖሊተካዊ ፍልስፍና መነጽር ስንመለከት፣ የኢሕአዴግ አብዮታዊ ደሞክራሲ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በአንፃራዊነት የተሻለ ነበር። ይሁን እንጅ፣ ኢሕአዴግ በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ኔጋዴዎች ልማቱን ማጽዳት አልቻለም። ያለአግባብ መበልጽግ (ሙስና) ባህል ሆኗል፤ የመልካም አስተዳደር እጦት ሰፍኗል፤ የውሸት ባሕል ነግሷል፤ ለሆዱና ለፍትወት ብቻ ያደረ ትውልድ ተፈጥሯል፤ አድሏዊነት፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ጨቋኝነት ተንሰራፍቷል፤ ብሔርተኝነት ከመጠን በላይ ተለጥጧል፤ በሠላምና በፍቅር አንድ ላይ መኖር አልተቻለም፤ ሕዝብና መንግስት የጥይት ጨዋታ ውስጥ ግብቷል፤ ወጣቱ ተስፋ ቆርጧል፤ መግባባት፣ መደማመጥና መነጋገር ጠፍቶ መናናቅ ብቻ ሆኗል፤ የአብሮነት መንፈስ የሚባል ነገር ጠፍቷል፤ ለምዕራቡ ዓለም የአገብዳጅነት መንፈስ ሰፍኖ ሕዝቡ ስሜቱ ተሰለቧል፤ ደሃው በኋይልና በጉልበት ከተወለደበት ቀዬ ተፈናቅሏል፤ ወዘተ። በአጠቃላይ፣ እንደገና ተመልሰን የቆንጨራ ጨዋታ ውስጥ ገብተናል፤ ይህ የማይካድ ሐቅ ነው።

 

ዞሬም ቀረ፣ መንግስት በሕዝብ ብሶትና እንባ ማትረፍ የሚሹትን ሰዎች አያውቅም ማለት አይቻልም። ዝለዝህ፣ በሕዝብ ስም የራሳቸውን ኑሮ ያመቻቹና የሕዝብን ገንዘብ በጆንያ የምዘረፉት ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ለምን እንደማያመጣቸው ፈጽሞ ግልጽ አይደለም። በአሁኑ ግዜ በሥርዓቱ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ አብዛኞቹ ግለሰቦች (ሁሉም አይደሉም) ስለሆዳቸው እንጅ ስለሕዝቡ አሰቃቅ ሁኔታ የሚየስቡበት ሰዓትም የላቸውም። የሚከተለው የሞገስ ሃብቱ ግጥም የእነኝህን አድርባይ ግለሰቦችን የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖሊቲካዊ ፍልስፍና ውጤት በትክክል ይገልጻል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡-

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦነግ  (OLF) በአስቸኳይ ትጥቅ ይፍታ!! - ከሙሉቀን ገበየሁ

 

መቶ ሺህ ብር ይውጣ

ሰው ጠግቦ እንድወጣ

ውስኪም ብዙ ግዙ

ቢራም ብዙ ብዙ

ምግብም ብዙ ብዙ

ሁሉም በገፍ ይምጣ

ሰው ጠግቦ እንድወጣ

እየበላህ ብላ፣ እየጠጣህ ጠጣ

ከህዝብ ነው እንጂ ካንተ ኪስ አይወጣ

 

ይህ ነው እንግድህ ሰውየው ‹‹በሕዝብ ስም ተነስተን ከሕዝብ እየራቅን―ለሕዝብ ባዳ እየሆን እንዳንሔድ›› ያለው! ነፍሱን ይማርና የቀድሞ ጠቅላይ ምኒስተር መለስ ዜናዊ ‹‹የመንግስት ሌቦች እጅና እግራችንን አሰሩ›› ሲል፣ ‹‹መንግስት ሌባ እየሆነ መቷል›› ማለቱ ነበር እንጅ ሌላ ምስጥር የሌውም። መንግስት ሙስና የምሉት ካንሰር ሀገረቷን ከመግደሉ በፍት አስቀድሞ መድኃኒቱን ካለፈላለገለት መዘዙ አደገኛ መሆኑ አጠያያቅ አይደለም። በሕዝብ ስም እየነገዱ ከፈተኛ ሀብት ያካበቱትን ግለሰቦች እያጣራ ፍርድ ፍት የማቅረብ ሞራላዊ ግደታ አለበት። በሙስና ምክንያት 20 ሚሊዮን የናጠጠ ሀብታምና 80 ሚሊዮን መናጥ ድሃ ይዘን የሚንቀጥልበት ምንም ዓይነት መለኮታዊም ሆነ ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይገባም። ‹‹በቅርብ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ እንሰለፋለን›› የሚል ትንቢት ግቡን እንድመታ ከተፈለገ፣ መንግስት የሙሰኞች እጅ እንዴት መቀንጠስ እንዳለበት ከአሁኑ በደንብ ልያስብበት ይገባል! ይህ እስካልተደረገ ድረስ፣ ‹‹መጀመሪያ ሙስና ነበረ፣ ሙስናም በስልጣን ዘንድ ነበረ፣ ሙስናም ስልጣን ነበረ›› የሚል ‹‹የሙስና ወንጌል›› በኢትዮጵያ ምድር እየሰተበከና አየተተገበረ ይቀጥላል!

ባለፉት 42 ዓመታት፣ ፖሊቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮቻችንን በጤረጰዛ ዙሪያ መፍታት አልተቻለም፤ 17 ስደመር 25 ይሆናል 42! እንደ አንድ ወጣት ዜጋ ግራ ገብቶኛል! የ‹‹እናውቅልሃለን›› የፖሊቲካዊ ፍልስፍና ከጥይት ጨዋታ ወደ ጤረጰዛ ዙሪያ ማምጣት አልተቻለም። ችግሮች ስፈጠሩ ሰላም እንድወለዱ የሚያስችሉ ባህል የለንም። ከዝህ በፊት በግልጽ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት፣ በባሕልና በታሪክ በተሳሰሩ ሕዝቦች መካከል የቆንጨራ ፍልስፍናን ማቀንቀን፣ ለዝች ሀገር የሚበጅ አይመስለኝም። ግን ምን ያረጋል! አሁን በተጨባጭ እየሆነ ያለውን ነገር ስመለከት፣ ‹‹ኦሮማይ›› እንድል አስገድዶኛል። ዳግም ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳንገባ ትልቅ ስጋት አለኝ።

ዝለዝህ፣ ምሁራን፣ የሀገር ሹማግለዎችና የሃይማኖት አባቶችን ከባድ የቤ-ሥራ ይጠብቃቹዋል። በተለይ፣ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ኋላፍነት አለባቸው! ሕዝቡ በቆንጨራ እየተጨራረሰ ዝም የሚትሉ ከሆነ፣ በፈጣሪና በሕግ ፊት ተጠያቅዎች ናችው። እምነትና ፀሎት ብቻ በቂ አይደለም። ሰይጣንም እኮ እግዚአብሔር የዘለዓለም ኗር መሆኑንና ታላቅ አምላክ መሆኑን ያምናል። ግን መልካም ሥራ የለውም፤ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው! የኅይማኖት አባቶች ሆይ! ‹‹አድስ አማኝ ከጳጳሱ በላይ ለበቴክርስቲያን ተቆርቋር ነው›› እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ። ምንም ዓይነት መልካም ሥራ ሳይኖረው ያንን ለማለት የሚደፍር የእግዝብሔር አገልጋይ ካሌ ግን፣ ‹‹ፂም በማሳደግ ቢሆን ፍየል ትሰብክ ነበር›› የሚል ተመጣጣኝ ምላሽ ሰለሚሰነዝር ላንደማመጥ እንችላለን! ይልቅ፣ በልጅነት መንፈስ እናንተን ማሳሰብ የፈለኩት ነገር ቢኖር፣ ፍትሕ ስጓደል አይታችው ዝም አትበሉ ነው። የእግዝብሔር ቃልም የሚላችው ይህንኑ ነውና፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታማኝ እና ቴዲ ትላንት ምሽት (ከክንፉ አሰፋ) ጋዜጠኛ

 

ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ ተጸይፌውማለሁ፤ የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም። የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም።የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም። ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ።” (አሞጽ 522-24)

 

ይህ ማለት፣ አንድም፣ የሚተሰብከውን ኑር እንጅ፣ ፈሪሳዊ አትሁን፤ ሁለትም፤ ‹‹ከመጠምጠም መልካም-ሥራ ይቅደም›› ማለት ነው። ከምሁራንና ከሀገር ሹማግለዎችም ተመሳሳይ ተልዕኮ እንጠብቃለን፤ ተማርኩ ብሎ ጠሩንባ መንፋት በቂ አይደለም፤ ትልቁ ነገር ዕውቀትን ወደ ተግባር መቀየሩ ነው! የአስተሳሰብ ለውጥ ሳይኖር ተማርኩ ብሎ መንጠራራት፣ በፍልስፍው ዓለም ምሑራዊ ውስልትና ወይም የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ይባላል!

 

በመጨረሻም፣ መንግስትና ሕዝብ ከታረቁ ብሔራዊ እርቅ ላይ እንደርስ ይሆናል፤ ካልሆነ መበታተናችን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።ከማንኛውም እልቅት ፈጣሪ እንድጠብቀን ግን አጥብቀን መሥራት አለብን። ከሁሉም በላይ፤ ለዝች ሀገር የሚያስፈልጋት ሠላም ነው፤ ሠላም! ሠላም! ሠላም! ዘላቅ ሠላም! ሮናልድ ሬገን ያለውን ግን እንዳንረሳ ‹‹ሰላም የግጭት አለመኖር አይደለም፤ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም ነው፡፡›› ስለዝህ፣ ከራሷ ጋራ ሠላም የፈጠረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአንድነት እንስራ። ማርቲን ሉተር ኪንግ እንደሚለን ‹‹ጦርነትን ማወጅ የለብንም ማለት ብቻ በቂ አይደለም፤ ሠላምን መውደድና መስዋዕትነት መክፈልም ይኖርብናል፡፡› መንግስትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ስስታምነት ይብቃን፤ የንጹሐን ደም መፍሰስ የለበትም፤ አድሏዊነትን አጥብቀን እንዋጋ፤ ሰውን በሰውነቱ ብቻ እናከብር፤ የመጠላለፍ ፖሊቲካ ይብቃን፤ ሁሉም ነገር እኮ አለን—ሀገራችን ኢትዮጵያን ምን ጎደላት? ምንም! ግን አንድ የጐደለን ነገር አለ፤ መተሳሰብ፤ መቻቻል፤ መፈቃቀር፤ አንድነት፤ ደግነት ወዘተ። አዎን! እሱ ነው የጐደለን! የእኛ ጥረት ተጨምሮበት የጐደለውን ነገር የመሙላት አቅም ያለው አንዱ ፈጣሪ ብቻ ነው፤ እናም ፈጠሪ እያንዳንዳችንን ይርዳን። በሃይለመለኮት መዋእል ግጥም ልሰናበታቸው!

 

ምን ጠቀመዉ ቃየል—የመሳሪያ ቋንቋ

ሰጠመ ጠፋ እንጂ—ባቤል ደም አረንቋ

መኢኑም አባተ—ሰመረ መረሳ

ኦቦንግ አብዱል ከሪም—ጋቸኖ ቶሎሳ

አብረኸት ምንትዋብ—ኛዳክም ጋዲሴ

በላህ በነብዩ—በሶስቱ ስላሴ

ሰይፉም ዶማ ይሁን—ሞርተሩም አንካሴ

 

ምንጭ፡- ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ፣ የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ፣ ገጽ. 67-70

*Yoseph Mulugeta Baba can be reached at: kankokunmalimaali@gmail.com

 

4 Comments

  1. አይ ዶክተር ብሎ ዝም። የሚገርም ጽሁፍ ነው። ከአንድ ማይም ዶክተር የሚጠበቅ ነው። PHD ገዝተህ ነው እንዴ? እስኪ የተሻለ ለሃገር የሚጠቅም መፍትሄ ካለህ ንገረን። አለበለዚያ ዝም በል።

  2. በዚያ ላይ ፈራ ተባ እያለ ነው የጻፈው።Aiga forum እንደሚ
    ያወጣ ያውቅ ይሁን።

  3. ወንድም ካሳሁን! እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ያየውትን እና የታዘብኩትን ነው የጻፍኩት፤ ‹‹PHD ገዝተህ ነው እንዴ?›› ላልከኝ ደግሞ ‹‹በፍጽም አይደለም›› ነው መልሴ፤ እስከ አሁን ከደርስኳቸው 4 መጽሐፎቼ ውስጥ Metaphilosophy or Methodological Imperialism? የተሰኘውን የፍልስፍና መጽሐፌን አንብበው፤ (it is a revised version of my PhD dissertation which I defended in May 2014) ከእኔ የተሻለ ሐሳብ ካለህ ካንተ ለመማር በጣም ዝግጁ ነኝ፤ በተረፈ ስለ PHD የበለጠ ለማወቅ ከፈለክ ‹‹የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ›› በተሰኘ ሥራዬ ውስጥ ‹‹የ‹አቶ› እና ‹ፕሮፍ› ልዩነት—ከጫት ተራ እስከ ምርምር-ተቋም!›› የሚል ርዕስ ሥር የጻፍኩትን እንድታነብ በትሕትና ይጠይቃለሁ!
    ያንተ ወንድም
    ዶ/ር ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ

    ‹‹የ‹አቶ› እና ‹ፕሮፍ› ልዩነት—ከጫት ተራ እስከ ምርምር-ተቋም!

    አበው ስፈላሰፉ ‹‹81 መጽሐፍ ከተማረ ሰው፣ መከራ የመከረው ይሻላል›› ይላሉ። አንድም፣ ‹‹እውቀት የሚንገበይበት ትልቁ ት/ቤት፣ የሕይወት ልምድ ነው›› ፤ ሁለትም ‹‹ልምዱ የሌለህን ነገር አታውቀውም››፤ ሦስትም ‹‹ ሆዳቸውን እንዴት እንደሚያማቸው የሚያውቁት የሚሰቃዩት ብቻ ናቸው›› የሚል አንደምታ አለው። ጃማይካዊያን ‹‹በመፃሐፍቶች ውስጥ የማናገኘውን ጥበብ የሚናገኘው ስናዝንና ስንሰቃይ ብቻ ነው—only through suffering and sorrow do we acquire the wisdom not found in books››—እንደሚሉ ማለት ነው። ለምሳሌ፡- ሕይወቱን ሙሉ ‹‹አንዷን ሳያቅ›› በሥነ-ወስብ (sexology) ዙሪያ 85 መጽሐፎችን ከደረሰ ‹‹ምሑር›› ይልቅ፣ ስለ ወስብ ምንነት የተሻለ ግንዛቤ ያለው፣ አንድ ሁለት ቀን በተግባር ወስብ የፈጸመ ግለሰብ ነው! እዝ ላይ፣ ‹‹የዕውቀት ምንጭ ልምድ ነው ወይስ ከልምድ ውጭ (ተፈጥሯዊ)?›› ለሚለው ፍልስፍናዊ ጥያቄ መልስ ለማፈላለግ አይደለም። እንድህ ዓይነቱን የቅንጦት ጥያቄ የተረጋጋ ማኅብረሰብ ውስጥ መኖር ስንጀምር አንድ ቀን እንፈላሰፍበታለን! ይልቅ፣ ‹‹የጥበብ መገኛ የምርምር-ተቋም ወይስ ጠጅ-ቤት?›› የሚለውን ጥያቄ ትንሽ ለመቃኘት ያህል ብቻ ነው። ‹‹ትምህርት የአመለካከት ለውጥ የማምጣት አቅም አለው ወይ?›› የሚል የብዙዎች ጥያቄ ነው። ለምሳሌ፡- ‹‹በ‹አቶ›ና ‹ፕሮፍ› መካከል የአመለካከት ልዩነት ከሌለ፣ የመማር ጥቅም ምኑ ላይ ነው?›› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

    በበኩሌ፣ በጫት-ተራ እና ቤተ-መጽሐፍት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ያደረኩት ጥረት እስካዛሬ ድረስ አልተሳካልኝም። ምክንየቱም፣ በጥልቀት የተመራመረና ሕዝቡ ‹‹ፕሮፍ›› ወይም ‹‹ዶ/ር›› የሚለውን ግለሰብ 2 ለ 0 የሚሸኝ ነጋዴ ወይም ሾፌር ጫት-ተራ አከባቢ እንደ አሸን በፈላበት ዘመን፣ በሁለቱ መካካል ያለውን ልዩነት ማወቅ አይቻልም የሚል አቋም አለኝ።። ቢሊ ሴንደይ፤ “ጋራዥ ውስጥ መቆም መኪና እንደማያሰኝህ ሁሉ፣ ቤተ-ክርስቲያን መሄድም ክርስቲያን አያሰኝህም” ያለው ነገር ትክክል ሳይሆን አይቀርም! በእርግጥ ድግሪ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ በሚሸመትበት ዘመን ላይ ሆኜ፣ በምርምር-ተቋም እና ጠጅ-ቤት መካከል ያለውን ልዩነት መጠየቅ አልነበረብኝም! ያም ሆነ ይህ፣ በትምህርት ዓለም አንድን ሰው ምሑር የሚያሰኘው ‹‹እራስህን እወቅ—know thyself›› የሚለው የግብጻዊያን መምህራን አባባል (የሶቅራጠስ አይደለም!) በሕይወቱ መተግበር ከቻለ ብቻ ነው። በ‹‹አቶዎችና ››ና ‹‹ፕሮፍዎች›› መካከል ያለውን የአመለካከት ልዩነት በትክክል ለመረዳት ታድያ፣ ‹‹እራስህን እወቅ›› የሚለው የጥቁሮች/የግብጻዊያን አባባል ብቸኛው መለኪያ ይሆናል ማለት ነው። ለምሳሌ፡- የ‹‹እራስህን እወቅ›› ጥያቄን በተመለከተ ጠጅ-ቤት አካባቢ አራት ዓይነት ሰዎች አሉ፡- (1) ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ “ሌላ” ሰው ማንነት ግልብ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፣ (2) ስለ “ሌላ” ሰው ማንነት ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው፣ ግን ስለ ራሳቸው ማንነት በጣም ትንሽ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች፣ (3) ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ “ሌላ”ው ሰው ማንነት ጠለቅ ያለ እውቀትና ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች፣ (4) ስለ ራሳቸው ማንነት ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው፣ ግን ስለ “ሌላ” ሰው ማንነት ምንም ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች-ናቸው።
    ከዝህ አንፃር ካየነው፣ ብዙ ‹‹ፕሮፍዎች››ና ‹‹አቶዎች›› በተራ ቁጥር 1 እና 3 ሥር በየተራ (respectively) የሚደለደሉ ሲሆን፣ ጥቂት ‹‹ፕሮፍዎች››ና ‹‹አቶዎች›› ደግሞ እንደየሁነታው በተራ ቁጥር 2 እና 4 ሥር በየተራ የሚደለደሉ ናቸው። የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ በስም ‹‹አቶዎች›› ሆነው በአስተሳሰብ ግን ‹‹ፕሮፍዎች›› የሆኑ እንዳሉ ሁሉ፣ በስም ‹‹ፕሮፎች›› በአስተሳሰባቸው ግን ከ‹‹አቶዎች›› ያነሱ ግለሰቦች በእርግጠኝነት እንዳሉ በግልጽ ለማሳየት ነው። ለዝህ ምን ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ አለ? የጓደኛዬን የፕሮፍ ‹‹ጐንዳ››ን አመለካከት ለአብነት ማንሳት ይቻላል። (በነገራችን ላይ፣ በሀገራችን ባህል የሰዉን ስም መዘርነቅ ነውር በመሆኑ፣ በግለሰቡ ትክክለኛ ስም ምትክ “ጐንዳ” የሚለውን የአፋን-ኦሮሞ ቃል ተጠቀመያለሁ። ትርጉሙም “ጉንዳን” ማለት ሲሆን፣ የ‹‹ጐንዳ››ና መሰሎቹን አስተሳሰብ/ጸባይ አስቸጋርነት ለማመልከት ታስቦ የተሰጠ ስም ነው። ዝለዝህ፣ ይህ ምሳሌ ለሁሉም ‹‹ፕሮፍዎች›› የሚሰራ ነው) ፕሮፍ ‹‹ጐንዳ›› ራሱንና ለሎችን የሚመለከትበት ‹‹መነጽር›› ከማስገረምም አልፎ ያሳብዳል! ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ብሎ በግትርነት የሚፀና ሰዉ ለድንቁርናዉ ምስክር ነዉ›› የሚለው የሚካኤል ሞንቴን አባባል የ‹‹ጐንዳ››ን ማንነት ከ ሀ እስከ ፐ ይገለጸዋል የሚል እምነት አለኝ። ፕሮፉ ስበዛ ጥፋት-ጎምጅ (fault finder) ነው! የሌላ ሰው ሥራ (አመለካከት) ውስጥ ስሕተትን መፈለግ እንጅ፣ ጭብጥን በጭብጥ መመከት አይሆንለትም። ለላው ቀርቶ፣ የሌሎች ሰዎች ‹‹ኀጥያት” እንጅ፣ የራሱ የበሰበሰ አመለካከት አይታየውም። እንደ መዝሙረ-ዳዊት የሚደጋግማት አንድ ሐረግ አለችው፤ “እገሌን ታዘብኩት!” ግን “ወንፊት ለመርፌ ‹ጭራህ ላይ ቀዳዳ አለብህ› ትለዋለች” የሚለውን ነገር አንድም ቀን አስቦት አያውቅም። ሂስና ትዝብት ከራስ እንደምጀምር የተረዳ አይመስልም፤ ሰዎችን የሚያጃጅለው በአበባ ቃላቱ ነው፤ “የቃላቶች መጥለቅለቅ ባለበት ቦታ፣ የጥበብ እጥረት አለ” የሚለውን አባባል ጓደኞቹ በሚገባ የተረዱ አይመስልም። ስለዝህ፣ የራስን ሥራ አወዝፎ የሌላውን ሥራ መንቀፍ እንጅ፤ ከነባራዊ እውነት (objective truth) አንፃር ነገሮችን ማየት አይሆንለትም፤ በዝህ ምክንያት ሰውን የሚለካ በሰውነቱ ሳይሆን በትምህርት ደረጃ፣ በሀብት፣ በጾታ፣ በብሔር…ወዘተ ነው። እና ጐንዳ ዝነኛ ነኝ ብሎ የሚያስብ ዓይነት ሰው ነው! የጐንዳ “ጽድቅ” እና “ዝና” ከምን እንደመነጨ ግን አይታወቅም፤ ለትዳሩ ታማኝ ነው እንደይባል፣ “የብልት ፍልስፍናው” ያመዝናል! በዕውቀቱ ነው እንዳንል፣ የትምህርት ማስረጃዎቹ በአድርባይና ወሮ-በላ ምሁራን አማካኝነት
    ከዩንቬርስት እንደ ቻይና ዕቃ በርካሽ ዋጋ የተሸመተ ነው፤ ከድሃ ሕዝብ ክስ በወጣ ገንዘብ ዘርፎ ቤትና መኪና መግዛቱ፣ በሃብቱ እንደይኮራ እንቅፋት ሆኖበታል፤ ስልጣኑ በዝምድና የተገኘ እንጅ በብቃቱ አይደለም፤ የፍውዳል አስተሳሰብ
    ስላለው፣ በአመለካከቱ ካለፈው ትውልድ አንሶ እንጅ ተሽሎ የተገኘበት ጊዜ ፈጽሞ አልነበረም። ይህ ሁሉ ወራዳ ተግባር
    ስመለከት፣ “እገሌን ታዘብኩት!” የሚትለው መዝሙሩን በፍልስፍና መነጽር መመልከት ወደድኩ፤ እናም “ታዛቢውን
    ታዘብኩት!” የሚለው መደምደሚያ ላይ ደረስኩ! ከአንድ የጫት ነጋዴ ወይም የካፌ አስተናጋጅ ያነሰ አመለካከት (አስተሳሰብ) ይዞ ለሎችን ለማስተማር ወይም ለመገጸጽ ወይም ለመምራት የሚቋምጥ ‹‹ፕሮፍ››ን ማዬትን የመሰለ አሳዛኝ ነገር የለም። እሱ የሚንቃቸው ‹‹አቶዎች›› ስለ እውነታ ከእርሱ በጣም የተሻለ ግንዛቤ እንዳለቸው ቢያውቅ ኖሮ፣ እንድህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ይዞ በአደባባይ አይዘባርቅም ነበር። ዝለዝህ ነው፣ ጫት-ተራ አካባቢ በስም ‹‹አቶዎች›› ሆነው በአስተሳሰብ ‹‹ፕሮፍዎች›› እንዳሉ ሁሉ፣ በምርምር ተቋም ወስጥም በስም ‹‹ፕሮፎች›› ሆነው በአስተሳሰባቸው ግን ከ‹‹አቶዎች›› ያነሱ ግለሰቦች አሉ የሚንለው። አንድ የአሌክሳንደር ፑሽክን ግጥም የ‹‹ጐንዳን››ና መሰሎቹን የአስተሳሰብ ቅሬ አስታወሰኝ፡-
    ግማሽ ክቡር―ግማሽ ነጋዴ፣
    ግማሽ ታማኝ―ግማሽ ወንበዴ፣
    ግማሽ ሩህሩህ―ግማሽ መደዴ፣
    ከሆነ ቡድን ጋር፣
    ይቻላል ወይ አብሮ መኖር?
    (አያልነህ ሙላቱ እንደቶረጎመዉ!!)
    ‹‹እራስህን እወቅ›› የሚለው አባባል ራስን የሚያስኮፍስና ሌባ የሚያረግ ሳይሆን፣ ትሕትናና ሐቀኝነትን የሚያስተምር ነው። እንኳንስ በማጨበርበር የተገኘ ድግሪ፣ በትክክለኛ መንገድ የተገኘ የትምህርት ማዕረግ ዋና ዓላማ፣ ሕዝቡን በቅንነት እንድናገለግልበት እንጅ፣ ሌላው ላይ ለመዘነጥ/ለመሰልጠን አይደለም። ‹‹መዘነጥ እንዳለ ሁሉ መዘነጣጠልም አለ›› የሚለውን አባባል መርሳት የለብንም። የአንድ ግለሰብ ዕውቀት (ስልጠና) ብዙኅኑን ካለጠቀመ፣ የፕሮፈሰርነት ማዕረጉ ለሕዝቡ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ወይም ድንች ሊሆን አይችልም። በተግባር ያልተገለጠ ዕውቀትና ከመልካም ሥራ የተለየ እምነት አንድ ነው። ሰው መከበር ያለበት በተግባሩና በአስተሳሰቡ እንጅ በማዕረጉ አይደለም፣ ከባለጌ ክቡር የድሃ ሥልጡን ይሻላልና! ጥሩንባ የሚነፉ ሰዎች አላጣንም! ጋንዲ ‹‹ከአንድ ኩንታል ወሬ አንድ ኪሎ ተግባር›› ብሎ የለ! ስለዝህ፣ ስብከቱን ለሕሁድ እናቆየው! በደበበ ሰይፉ ግጥም ልሰናበታችሁ፡

    ከህይወትህ ወዲያ ላያልፍ—የጥናትህ መደቡ
    ከህዝብ ጉያ ላይርቅ—የምርምርህ ክበቡ
    ምንም ብትረቅ ምንም ብትርቅ—እምትደርስበት ግቡ
    ወይ የመነሻህ ርካቡ………..
    ……የስንቱን አይነ ልቡና አታለልክ
    አስተዋይነቱን አጭበረበርክ
    በቋንቋ ግርዶሽ እየተጠለልክ
    ተጠበብኩ ስትል ጠበብክ
    አወቅኩ ስትል ደነቆርክ

Comments are closed.

Share