ወቅቱ ሰው የሚፈለግበት እንጅ ሰው የሚገፋበት አይደለም (ከይገርማል)

ሞረሾች አንድነት ከማን ጋር፣ አንድነት ለምን፣ አንድነት መቼ? በሚል ያወጡትን መግለጫ አንብቤ መሀል አናቴን በዘነዘና የመቱኝ ያህል ሲያመኝ፣ ጆሮዬ እውውውውው እያለ ሲጮህ ተሰማኝ።

ከአፍ የሚወጣ ነገር ጠላትን ከሚያቆስለው በላይ በራስ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ይበልጣል። በክፉ ያየነውን ሰው ለመወረፍ ወይም ለማሸማቀቅ የምንወረውራቸው ቃላት ለተመልካችም የሚጎረብጡ ስለሚሆኑ ከምንም በላይ ራስን ያስገምታል። አንዳንድ ሰዎች አስበው የሚናገሩ ሳይሆን ከተናገሩ በኋላ ሀሳብ የሚወዘውዛቸው ናቸው። ያም ቢሆን ህሊና ያላቸው ከሆኑ ነው። ይኸ የጠረባ ፖለቲካ ቢቀር ምናለ? በጅምላ የመወንጀል አባዜ ቢበቃ ምናለ?

“— ተደጋግሞ በተሄደበትና ምንም ዓይነት አዎንታዊ የሆነ ገንቢ ውጤት ባልታየበት መንገድ ደጋግመን እንድንጓዝ የሚገፋፉ ቡድኖች፣ለአንድነችን የጓጉ ሳይሆኑ፣ ልክ እንዳለፉት ሁሉ ውድቀታችን የናፈቃቸው መሆን አለባቸው።” ይላሉ ሞረሾች አማራው በአንድ ጠንካራ ድርጅት ሥር ብቻ እንዲሰባሰብ የሚጠይቁትን ሁሉ።

በዚህ ፍረጃ ውስጥ እኔም አለሁ፤ ምክንያቱም እኔም አንድ ጠንካራ የአማራ ድርጅት ብቻ ተፈጥሮ የሕዝብን ሁለንተናዊ አቅም እንዲያስተባብር ስለምፈልግ። በቡድን ከፋፍላችሁ ሃይላችንን አትበትኑ እያልሁ ስለምከራከር። በጣም ያሳዝናል! ምናለ

“ሳንጠናና ውህደት መፍጠሩ ለትግላችን መሰናክል ሊያመጣ ስለሚችል ጊዜ ወስደን ማን ምን እንደሆነ ማየት ስለሚኖርብን ወገኖችቻችን ይህን እንድትረዱልን እናሳስባለን” ቢባል።

በመሰረቱ ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ ብሎ የሚነሳ ማንኛውም ድርጅት የስልት ካልሆነ በቀር የአላማ ልዩነት አለው ብየ አላምንም። አዎ! ከጣሊያን ጋር ወግነው ኢትዮጵያን ያደሙ ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። የዛሬው ግን ይለያል። አማራው መጥፋት አለበት ተብሎ እየተሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት የራሱን ቤተሰብ ከጠላት ጋር ወግኖ ለማጥፋት የሚተጋ ጤነኛ ሰው በምንም አይነት ስሌት ሊኖር አይችልም። በብአዴን ውስጥ ያሉት አማሮችም ቢሆኑ በወገናቸው ላይ የሚወርደው መአት የማይሰማቸው አይደሉም። የምናካሂደው ትግል እነሱንም የሚጋብዝ ቢሆን የተሰጣቸውን ተልዕኮ ሊወጡ የሚችሉ፣ መረጃ በማቀበል የሚያግዙ አይጠፉም። ዋናው ነገር ሁሉም አማራ የተጠነሰሰበትን ሴራ አውቆ የሚታገለው ለራሱ እንደሆነ አምኖ እንዲቀበል ከማድረጉ ላይ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ያገኘውን ሁሉ የሚለክፍ ሳይሆን በዕውቀት እና በአመለካከት የዳበረ የራቀን የሚያቀርብ፣ ያለን የሚያጸና አሳታፊ የሕዝብ ግንኙነት ሲኖር ነው።

ይህን ስል ዝርክርክ መሆን አለብን ለማለት አይደለም። ለጥንቃቄ ያህል ወሳኝ የሆኑ ቦታወች ላይ የሚሰማሩ ሰዎችን ብልሀት በተሞላበት መንገድ መርጦ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑ የሚያከራክር አይሆንም። ሚስጥራዊ ሰነዶችን ማንም ከማይደርስባቸው ቦታ ማስቀመጡም ተገቢ ነው። ያም ቢሆን የማንንም ስሜት ሊረብሽ በማይችል መንገድ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አስከፊው ስርዓት ከውስጥም ከውጭም ተወጥሯል።

ሁሉም አማራ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው እና በነጻነት ተሳትፎ እንዲያደርግ ዴሞክራሲያዊ አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል። አደረጃጀት እና የርስ በርስ ግንኙነቱ በውስጠ ዲሲፕሊን እየተመራ በሂደት ግንኙነቱ እየጠበቀ፣ ችግሮች እየጠሩ የሚመጡበት ሁኔታ መልክ እንዲይዝ አድርጎ ማቀድ ያስፈልጋል። የሆነ ጥርጣሬ ቢያድርብን እንኳ ማንንም ሊያሸማቅቅ በማይችል መንገድ በክትትል እና ግምገማ ማጥራት ተገቢ ነው። ያ ካልሆነ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ የሚደርሰው ወከባ በሌላው ላይ የሚያሳድረው አፍራሽ ተጽዕኖ ስለሚኖር ለአንዱ የተወረወረው ምዝግዝግ ሌሎችንም ሙጭ የሚጠርግ ይሆን እና በቁጭት ተነሳስተው በደምና በአጥንታቸው የአማራውን ህልውና ለማስጠበቅ የቆረጡትን ግለሰቦች ቀስ በቀስ የሚያሸሽ ይሆናል። የፖለቲካ ሥራ በደም ፍላት የሚተገበር ሳይሆን ጥበብ እና ማስተዋልን የሚጠይቅ፣ ከጉልበት ይልቅ ሳይንሳዊ ዕውቀት መላበስ የሚሻ ሥራ ነው።

በፖለቲካ ውስጥ ልብን አሻክረው ከሚበትኑ ነገሮች መሀል ዋናው የስልጣን ጥያቄ ነው። የስልጣን ጥያቄ አይደለም በውህደት አንድ ሊሆኑ በሚደራደሩ የተለያዩ ቡድኖች ዘንድ ይቅርና በአንድ ወጥ ፓርቲ አባላትም መሀል የሚከሰት መቸም፣ የትም፣ የሚያጋጥም ጤናማ የሆነ ወይም ያልሆነ ፍላጎት ነው። ነገር ግን ስልጣን የሚያዝበት አግባብ እና የመተዳደሪያ ደምቡ አሻሚ አለመሆን ለችግሩ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ ይሆናሉ። ሁሉም አባል የሚገዛው ለመተዳደሪያ ደንቡ ከሆነ ለኃላፊነት የሚያሳጨውም ሆነ በሀላፊነት የሚያስጠይቀው ወይም የሚያስቀጣው በህጉ ላይ የሰፈሩትን ቁምነገሮች አክብሮ በመስራቱ ወይም በማዛነፉ ማለትም በሥራው ይሆናል። ሞረሾች የስልጣን ጥያቄን እንደስጋት በማየት «ትንሽ አሻሮ ይዘን ወደ ቆሎ በመጠጋት የሌለ ሥልጣን ለመጋራት መሆን የለበትም።” በማለት ለውህደት የሚመጡት ቡድኖች የስልጣን ፍላጎት ምቾት አይሰጥም በሚል መልኩ ለመዋሀድ እንደአንድ መሰናክል አድርገው ያቀርቡታል። በተጨማሪም ተዋህደናል ወይም ግምባር/ቅንጅት ፈጥረናል ብለው ብዙም ሳይራመዱ ፍርስርሳቸው የወጣውን ድርጅቶች በስም እየጠቀሱ እንደማስረጃ በማቅረብ ሳይተዋወቁ በአንድ ዕዝ ስር መሰባሰቡ ችግር እንዳለው ሊያሳምኑን ሲሞክሩ በውህደት የተገኘ ጠንካራ ሰብአዊ፣ ቁሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስለመኖሩ ግን ሊያስረዱን አልደፈሩም። ደርግ እስከመጨረሻው እስትንፋሱ የዘለቀው በሰደድ ሰዎች ብቻ እንዳልሆነ ሊነግሩን አልፈለጉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያና ጎሳነት (በአልማዝ አሰፋ - ዘረ ሰው)

በትግል ወቅት ከፊት መሰለፍ አደጋ እንጅ ጥቅም አያስገኝም። በትግል ጊዜ ስልጣን ትልቅ ሸክም እንጅ ሹመት አይደለም። አሁን የሚያስፈልገው ተባብሮ የተደራጀውን የጠላት ኃይል መመከት ብሎም በሕዝባችን ላይ መከራ እያወረደ እንዳይቀጥል ከነጭራሹ ለማስወገድ መስራት ነው። በአምባገነኖች ሥር የመተዳደር ታሪክ ያላትን ሀገር ወደተሻለ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመቀየር የአንድ ወቅት ትግል ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ የቅብብሎሽ ትግል ማድረግን ግድ ይላል። በዚህ የትግል ወቅት ብዙ ውጣ ውረድ ይኖራል። ትግሉን የጀመሩት በመስዋዕትነትም ሆነ በሌላ መልክ እየተለዩ መጨረሻ ላይ የሚገኙት በአብዛኛው ቆይተው የተቀላቀሉ ይሆናሉ። ወያኔ በረሀ ሲወርድ በአመራር ላይ ከነበሩት ሰዎች መሀል ከድል በኋላ በህይወት የተገኙ ወይም ስልጣናቸውን አስጠብቀው በአመራርነት የዘለቁ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ደርግን በመመስረትና በመምራት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ወታደራዊ ሃላፊወች በተለያየ መንገድ ሲገለሉ/ሲወገዱ ብዙ ጊዜ አልወሰደም። ቶሎ ውጤት ማየት ያልቻሉ ሰዎች ከተወሰነ ጉዞ በኋላ ራሳቸውን ከትግሉ አግልለው የግል ህይወታቸውን ለመኖር የሚወስኑ እንደሚኖሩም የሚጠበቅ ነው።

ደጋግሜ ለማስገንዘብ እንደሞከርሁት ማንም እየተነሳ ወያኔ ይህችን ቀን፣ ወር፣ ዓመት አያልፋትም እንደሚለው ሳይሆን እጅግ መራራ እና እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ እንደሚጠብቀን ግምት ውስጥ አስገብቶ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ይህ ዘረኛ መንግሥት ቢወድቅ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በተፈጸሙት ወንጀሎች ተጠያቂ እንሆናለን፣ ካላግባብ ያካበትነው ሐብት ይወረስብናል የሚሉ ብዙ የወቅቱ ተጠቃሚወች ያሉ በመሆናቸው እና እስከመጨረሻው ትንፋሳቸው እንደሚፋለሙ ስለሚታሰብ ነው።

የስልጣን ወፍለቁን ተቆናጥጨ፣ “ታድሸ መጣሁ!” እያልሁ በልጓምና በአለንጋ ገርቸ እጋልባለሁ በሚለው ወያኔ መር ግምባር እና በጠላትነት ተፈርጆ የግፍ ሰለባ እየሆነ ባለው አማራ መሀል የሚደረገው ፍልሚያ እንደሚገመተው ቀላል አይሆንም። አማራውን በፍቅር የማይመለከቱ፣ ሞቱን የሚናፍቁ ሌሎች ወገኖች መኖራቸውንም ታሳቢ ማድረግ የፈተናውን ከባድነት ያስገነዝበናል። ለዚያም ነው የጥቃት ሰለባወች ተሰባስበው ለመመከት መዘጋጀት ግድ የሚሆነው።

ይህ ወቅት ሰው የሚፈለግበት እንጅ ሰው የሚገፋበት ወቅት አይደለም። ይህን ታሳቢ ካደረግን በአሁኑ ወቅት ስልጣን ማለት ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ከኋላ ሳይሆን ከፊት መሰለፍ፣ የጥይት አሩርን በደረቱ መክቶ ከጀርባ የተሰለፈውን ወገን ማትረፍ ነው ብሎ ማመን እና በተግባርም ማስመስከር ያስፈልጋል። ዛሬ የፉክክር ጊዜ አይደለም። እንደሚታወቀው ለነጻነት ለሚደረገው ትግል አማራውን ሊደግፍ የሚፈልግ ማንም የጎረቤት ሀገር ወይም ኃይል የለም። በእንዲህ አይነት አስከፊ ሁኔታ ላለ ሕዝብ ነጻነቱን ለመጎናጸፍ ያለው ብቸኛ አማራጭ የራሱ ትግል ብቻ ነው። ስለዚህ በቅድሚያ ጭንቅላታችንን እንጠቀም። እና ከመጥፎም መሀል ቢሆን ጥሩ ነገር እንዴት ማፍለቅ እንደምንችል እናስብ፤ ከዚያም በሀሳቦች ዙሪያ እንወያይ፤ ከሁሉም አቅጣጫ መዝነን የሚሻል ነው ያልነውን ሀሳብ በተግባር ለማዋል እንጽና። የትኛውም አማራ የዐዕምሮ/ የግንዛቤ ችግር እስከሌለበት ድረስ በአማራ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ከማንም በላይ ያብሰለስለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስለ መንበረ ፕትርክናው ዕጩዎች የቅድመ ምርጫ ግምት

ብአዴን ሙሉ በሙሉ የወያኔ አገልጋይ የሆነ ድርጅት ነው፤ አባላቱም በሕዝባቸው ላይ የሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ግፍ የማይቆረቁራቸው ህሊናም ልቦናም የሌላቸው ባዶ ሆድ የተሸከሙ ፍጡሮች ናቸው ብሎ ማሰቡ ትክክል አይደለም። የአማራ ካባ ደርበው አማራውን ለማስጠቃት በአመራርነት የተቀመጡትን ሳይሆን በተለያዩ አስገዳጅ ሁኔታወች አባል ሆነው ግን እንደማንኛችንም የሚታመሙ ብዙወች ይኖራሉ። አዎ እኔም ብሆን በአማራው ላይ አዲስ ነገር በደረሰ ቁጥር “የወያኔ ተባባሪ ሆነው አስጨረሱን፤ ህሊና የሚባል ያልፈጠረባቸው ከንቱወች” እያልሁ በብአዴን ውስጥ ያሉትን ሁሉ በጅምላ ስከስ ኖሪያለሁ። ይኸ ድርጊቴ ግን ትክክል አልነበረም። በድርጅቱ ውስጥ በተለያየ የስልጣን ደረጃ ያሉትን አማራወች በሚያምኗቸው ሰዎች አማካኝነት ቀርበን እንዲተባበሩ ማድረግ እንችላለን። አማራ እኛ ብቻ ሳንሆን እነሱም ናቸው። ትንሽ ትልቅ የሚባል አማራ ሊኖር በፍጹም አይችልም። ጥቃቱ የጋራ ነው። ይህን በተመለከተ ተቀራርበን መነጋገርና በጋራ መታገል ይኖርብናል። በጣሊያን ጊዜ ከጠላት ወግነው ከጎዱን ይልቅ ከጠላት ተጠግተው የጠቀሙን ይበልጣሉ። ከስሜታዊነት ወጥተን አስፍተን ማሰብ ካልቻልን ጉዟችን ባለንበት መርገጥ ይሆናል።

ስለዚህ የትኛውም የአማራ ተወላጅ የራሱን፣ የቤተሰቡን እና ለመከራ የተጋለጠውን የወገኑን ጥቃት ለመመከት ያስችላል ብሎ ያሰበውን ሀሳብ ቢያካፍል ወይም ተደራጅቶ የድርሻውን ሊያዋጣ ቢነሳ በአሸማቃቂ አነጋገር ቀልቡን ገፍፎ እንዲያፈገፍግ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ነገሮች የሚገለጹባቸው ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ሊኖሩ ይገባል። ሁሉም አማራ እኩል ዕድል ከተሰጠው እያንዳኑ ለድርጅቱ ታማኝ መረጃ አቀባይ እና ተዋጊ ኃይል ሆኖ እንደሚሰለፍ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። እንታገልለታለን የምንለው የሕብረተሰብ ክፍል አባል/አካል ስሜት የሚያደፈርሱ፣ ክብርን የሚገፍፉ ንግግሮችን ማድረግ/ጽሁፎችን ማውጣት ትክክልም ጠቃሚም አይደለም።

 

7 Comments

  1. ይገርማል ወንድማችን በጣም ጥሩ አስተያየት ነው። በጣም እናመሰግናለን። የእኔ እምነትና ጥኑ ፋላጎት ሁልም የአማራ ድርጅቶች ተወያይተው ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲመጡና በአንድ ላይ እንዲሰሩ ነው። በአንድ ላይ ስንሆን እኛ እንጠንከራለን። ያለንንም ጉልበትና ገንዘብ አጠራቅመን በአንድ አቅጣጫ እናውላለን። በተከፋፈልን ቁጥር ገን ሁልም ነገራችን ይከፋፈላል።

  2. Tekle yeshaw fear for his position of leader when the young vibrant Amhara come to unity. Thus why he wants to be alone instead of unity.
    Dear writer your advice appreciated I agree fully with you.

  3. ማክሰኞ ግንቦት ፳፱ቀን ፪ሺህ ፱ ዓ.ም. ቅፅ፭፣ ቁጥር ፲፯
    አንድነት ከማን ጋር? አንድነት ለምን? አንድነት መቼ? ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት
    ***(የሞረሽ ዘፈን ምርጫ መጀመሪያ ማወቅ..መተዋወቅ..ቀጥሎም በፍቅር መሳሳብ/መሳሳም)ይልሃል ይህ ነው።
    ፩) ኢማሌድኅ (የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት) ይህ ማኅበር የመኢሶን፣ የወዛደርሊግ፣ የማሌሪድ፣ የኢጭአት፣እና የአብዮታዊ ሠደድ ድምር የነበረ መሆኑ ይታወቃል።አቶ ተስፋዬ መኮንን የተባሉት «ይድረስ ለባለታሪኩ» በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ለመወያየት ያልቻሉ አብዮታውያን በመንግሥቱ ኃይለማርያም እስር ቤት ባንድነት ታስረው ባንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን በቁጭት የገለጹት የሚታወስ ነው።
    ፪) ኢሕአፓ ፦ ኢሕአፓ ፣ የአብዮት ቡድን (የነጌታቸው ማሩ ቡድን)፣ የዴሞክራሲያ ቡድን (ይህ የነፀጋየ ገብረመድኅን፣ዘሩ ክሸን፣ ፀሎተ ሕዝቀየል፣ ተስፋዬ ደበሳይ እና ዮሐንስ ብርሃኔ ቡድን መጠሪያ ነው) ፣ የነሙሄ አብዶ ቡድን እና የነአሰፋ እንደሻው ቡድን } በመዋሐድ የተመሠረተ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል።በዚህ ሂደትም ድርጅቱ ከፊሉ ወደ ውጭ ሲሰደድ፣ አብዛኛ «አብዮቴ ማሪኝ» ብሎ ወደ ሰላማዊ ሕዎቱ መግባቱና በፀጋየ ገብረ-መድኅን የሚመራው በቋራ ትግሉን መግፋቱ ይታወቃል። ውጭ የተሰደደውም ኢሕአፓ እና ዴ-ኢሕአፓ ተብሎ ከሁለት መከፈሉ ግልጽ ነው።
    ፫) ኢሠፓአኮ (ኢሠፓ)፦ ይህ ድርጅት ከኢማሌድኅ መበተን በኋላ ሕይዎታቸውን ለማትረፍ በፈለጉ የመኢሶን፣ የወዛደር ሊግ፣ የማሌሪድ እና የፖለቲካ ሥጣኑን የአንበሣውን ድርሻ የያዘው አብዮታዊ ሰደድ ያልተባረከ ጋብቻ የተመሠረተ እንደሆነ ይታወቃል።ይህ በኢሠፓ አባላትና አመራሮች መካከል የነበረ የመሥመርና መሰል የሥልጣን አጣን ጥያቄዎች አባላቱንና ሕዝቡን በአንድነት አስተባብሮ ለመምራት ያለመቻል ውጤት አንዱና መሠረታዊ ምክንያት ነበር።
    ፬) አማራጭ ኃይሎች ከአሥራ ስድስት በላይ የነገድ ድርጅቶችን አካቶ አዲስ አበባ ጊዮን ሆቴል በ1985 ዓም የተመሠረተና በዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ይመራ የነበረው የድርጅቶች ስብሰብ ነበር። ይህም ስብስብ ለረጅ ጊዜ አለመቆየቱ ይታወሳል።
    ፭)ኅብረት፣ኢሕአፓን፣ መኢሶንን፣ታንድ እና ኦብኮን ጨምሮ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙትን ከአሥር በላይ ኅብረብሔራዊና ብሔራዊ ድርጅቶችን አካቶ የያዘ ስብስብ እንደነበር ይታወሳል። ይህም ከ1997 ዓም ምርጫ ዘመቻ በኋላ ዕድሜ እንዳልነበረው ይታወቃል።
    ፮)በኦነግና በቅንጅ መካከል ተመሠረተ የተባለው ኅብረት፣ ከሣምንታት ጩኸት በኋላ ስለመኖሩ ቀርቶ፣ ስለመመሥረቱ መናገር የተቻለበት ሁኔታ እንዳልነበር የሚታወስ ነው።
    ፯)ኢዴኃቅ የተሰኘው በርካታ ድርጅቶችን አሰባስቦ የነበረው ኅብረት ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ የውኃ ሽታ ሆኖ እንደቀረ አይዘነጋም።
    ፰)ግንቦት ፯ በከማል ከልቹ ከሚመራው ኦነግ ጋር፣ ከዴምት፣ከዐማራ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ ወዘተ ጋር ተፈጠሩ የተባሉት ጥምረቶችና ኅብረቶች የት እንደደረሱ በተጨባጭ እያየን ነው። ሁሉም ተስማሙ ከመባሉ ተጣሉ፣ ተበታተኑ የሚለው እየቀደማቸው አንዳችም ለውጤት የሚያበቃ ሥራ ተሠርቶ ሕዝባችን የኅብረትን፣ የቅንጅትን፣ የአንድነትን፣ የውኅደትን ፋይዳ ከንድፈ-ሀሳብ ባሻገር በተግባር ሳያይ ዘመናት መቆጠራቸው ዕውነት ነው።
    ***********************!
    (ሀ)አንድነት ከማን ጋር? ለሚለው ጥያቄ፣ በወረቀት ላይ የሰፈረ የዓላማ አንድነት ሳይሆን፣ በተግባር የታዬ መሆን ይኖርበታል።
    ** ከትግሬ ነፃ አውጭ ግንባር እና ከትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ውኅደት እና ከተገኘው ውጤት የምንማረው ሌላ አሳዛኝ ጉዳይ እንዳለ ልብ ልንል ይገባል!።
    (ለ)አንድነት መቼ? የሚለው ጥያቄ የጊዜን አስፈላጊነት የሚያመላክት ነው። ለሁሉም ነገር ማንነትና ምንነት ጎልቶ የሚታዬው በጊዜ ነው። ጊዜ የሁሉንም ነገሮች ዕውነተኛ ቅርጽና ይዘት፣ ፍሬ ነገርና ክስተት ማሳያ ነው። «የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ» እንዳይሆን በማስተዋልና በርጋታ ልናየው ይገባል።
    (ሐ) አንድነት ለምን? የሚለው መልሱ የሚያሻማ አይሆንም። አንድነት የብቃት፣ የሁለንተናዊ ኃይል መገለጫ፣ የማድረግ ብቃት መለኪያ ወዘተ በመሆኑ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም። ከዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ አንድነቱን የፈለጉት ኃይሎች እነማን ናቸው? ከኋላቸው ማን አለ? አንድነቱን የፈለጉት በእርግጠኝነት ከአንድነቱ የሚመነጨው ሁለንተናዊ ጉልበት ለተፋጠነ ድል ያደርሰናል ከሚል ነው? ወይስ በአንድነት ስም ገብቶ የጠነከረውን ለማላላት፣ ሰላሙን ለማናጋት፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማጉላት ነባር አንድነቱን ለማሳጣት? በአንድነቱ ስም በአቋራጭ የሌለ ሥልጣን ባለቤት ለመሆን? የሚሉት ሊጤኑ ግድ ይላል።አራት ነጥብ።
    “ወቅቱ ሰው የሚፈለግበት እንጅ ሰው የሚገፋበት አይደለም!” (ከይገርማል)
    (ዝም ብለህ ሸክሽክ የተሰኘው ሙዚቃ ምርጫ!)እውነትም ይገርማል!?

  4. Mr yegerem kkk

    awo sew yemefelegbet weqt neq !!

    Gin sew hulu sew aydelem eko ! asesun gesesun yeje liramed kak
    yedenakifhal ! enqifat denqara yehonibhal

    le Ethiopia selem kehone , shabyam hone ye shabya Qitregnoch netsa leyawetun aychlum !

    ke tegentay ena ke shabya G7 gar Hibret yemefetir kale tsre Ethiopia new !

    ena eyetestewale !

  5. ይገርማል የጻፈውን በትክክል ያለመረዳት ችግር ከአንዳንድ አስተያየት ሰጭወች ይታያል
    ይገርማል ያለው
    የትብብር ጥያቄ የሚያነሱትን ሁሉ የተለየ ተልኮ ያላቸው ናቸው ብላችሁ አትዝለፉ
    ራሳችሁን ብቸኛ ሀቀኛ ያማራ ተቆርቋሪ አርጋችሁ ሌላውን ተጠርጣሪ ሳታደርጉ ለሁሉም አማራ እኩል እድል ስጡ
    የተለየ ተልኮ ይዞ የቀረበ ካለ በአደረጃጀት በክትትልና ግምገማ መለየት ይቻላል
    የተለያየ ያማራ ድርጅት እየፈጠራሁ ልክ እንደወያኔ ሀይላችንን አትከፋፍሉ
    በውህደት የሚገኝ ጥንካሬ አለ
    የስልጣን ጥያቄ ለውህደት መሰናከል መሆን የለበትም
    ከአፋችሁ የሚወጣው ነገር የበለጠ ራሳችሁን ያስገምታችኋል ስለዚህ በጅምላ አትወንጅሉ
    ባዴን ውስጥ ያሉ ተቆርቋሪ አማሮች ፈልጋችሁ እንዲተባበሩ አድርጉ
    ሁሉም አማራ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው አድርጉ የሚል ነው

  6. በለው የሚባለው ሰው ተክሌ የሻው መሆን አለበት የማይገባው
    ሞረሽ ያልበሰለ ድርጅት ለመሆኑ መግለጫው ያሳያል። የሚቃወመውን ሁሉ በአንድ ሙቀጫ ከቶ መውቀጥ። አነጋገር ማንነትን ይገልጻል። ለመሆኑ እናንተ ማን ስለሆናቹ ነው ሌላውን የምታገሉ። ቀና አይደላችሁም። የትም አትደርሱም። በጥርጣሬ ማራቅ ሳይሆን አቅርቦ ጥርጣሬን ማጥራት ነው የሚያስፈልገው ደሞስ ውጭ ሀገር ተቀምጦ የሚያወራ ድርጅት ምን የሚደብቀው ሚስጥር አለውና ነው የሚያስጨንቀው። ቢኖርስ ሚስጥር እንዴት እንደሚጠበቅ አያውቅም? ሁሉም አባል ሁሉንም ነገር ማወቅ አለበት? ለነገሩ የጎንደር ህብረት ሊቀመንበሩም አትከፋፍሉ የሚሉትን የወያኔ ተላላኪወች ናቸው ብሏል። የጎንደር ነገር ግራ ያጋባል

    • > እናንት አማራ ቤት አተላ ልሳችሁ ያደጋችሁ ሆይ፤ አማራ የራሱ ሥርዓት ግብረገብ አለው ለነገሩ እናቱን እንጂ አባቱን የማያወቅ ፌሮ ማለት በጥሊያን ብረት ማለት ነው እንኳንም ፌሶ አልሆነ!? ይህ ጎንእደር…ሸዋ ወሎ ጎጃም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉም ግፍ የሚደርስበት በአማራነቱ ነው። በተናጠል እየተደራጀ በጋራ መመከት አለበት! አንድ ላይ መጨፍለቁ ግን አደጋ አለው። ይህ የጋራ ጠላታችን ወያኔ የሚሉ ቱማታ የአዳራሽና የፌስ ቡክ ላይ መቆላት ለማንም አይጠቅምም።ይልቁንም እጃቸው እስኪካጠል የሚያጨበጭቡ የሚዲያ ላይ ተረበኛ አማራ መሳይ አማሳዮች አማራን ጎድተውታል ኅብረት አንድነት ስላልክ ደሜ ደምህ የሚሉ መጃጃልም ብዙ አያስኬድም አብዛኛው ልዩ ጥቅማጥቅመኛ ነውና!ይገርማልና ይገረም እዚህ ላይ ስላናፉና ዕድሉ እንዳያመልጣችሁ ስላሉ ገብቶ የሚመሰግ ድንኳን ሰባሪ አማራ ወይም የእማራ ሰፈር ከብት ነው። እሰማለሁ? አማራ ሁሉ ተክሌ የሻወን መከተልና መምሰል አለበት አላልኩም የትም እና ምንም ያልሆናችሁ ግን ምን ማለት እንደፈለጋችሁ በማይገባ ጽሑፍ አማራ ለመሆን ትንከላወታላችሁ..ስታዛዝኑ ድንቄም አማራው አልቀረባችሁም።

Comments are closed.

Share