ለተከበሩት አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ
ፕሮፌሰር ጌታቸውና አቶ አብርሃም ቀጄላ ከላቲን ይልቅ የግዕዝን ፊደል መጠቀም ለኢትዮጵያውያንና ኦሮሞ ወገኖቻችን እንደሚሻል ያቀረቡትን ጦማር በመተቸት ያቀረቡትን አስተያየት አይቸዋለሁ። ኢትዮጵያዊ በመሆኔና ነገሩ እኔንም ስለከነከነኝ አስተያየቴን ባጭሩ እገልጻለሁ፦
በመጀመሪያ አቶ ባይሳ ኢትዮጵያዊነትን በእኩልነት የሚያዩ ዜጋ ከሆኑ የአብርሃም ቀጄላ የዘር ምንጭ የሚጨንቅዎት ባልሆነ ነበር። አንተ አብርሃም ቃጄላ ሆነህ አብርሃም ቀጄላ ብለህ ስምህን መጻፍህ ኦሮሞ አለመሆንህን ያጋልጣል ብለው የማያስፍልግ ትንትና መስጠትዎም ይልቅ ራስዎ ወያኔ በፈጠረችው የዘር በሽታ ውስጥ ገብተው ስለመቸገርዎ ራስዎን ያጋለጡ ይመስለኛል። ሆጃ በአንዳንድ አካባቢ ደለጋ እንደሚባልና ደለጋ በሌላው አካባቢ ደግሞ አምልኮት መሆኑና እንዲህ ያሉ ልዩነቶች መኖራቸውን እንዴት አላወቁም?
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በማንኛውም ቋንቋ ቃላት ወይም ሐረጎች እንደአግባብነቱ የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው መቻሉን የዘነጉት ወይም ከአጻጻፍዎ ያላወቁት ይመስላል፤ ምናልባት ሶፎሞር ኢንግሊሽ ወስደው ከሆነ በዓለም በቢሊዎን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ባሉት የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንኳ ከቃላትና ሐረጎች አልፎ ዓረፍተነገሮች እንኳ በይዘታቸው ካልሆነ ልዩነት ያለው ትርጉም ሊኖራቸው እንደሚችል ማወቅ ነበረብዎት፤ እርስዎ የሚያውቁት የኦሮሞኛ ቃጄላ እንኳ በሌላ የኦሮም አካባቢ ቀጄላ እንደሚባል እንደ ዱፌ፣ ዋቀ፣ ሲቢለ፣… ወዘተ ያሉ የኦሮሞ ቃላት እንደአግባባቸው የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው እንደሚችል አለማወቅዎን ነው የሚገልጹልን።
የግዕዝን ፊደል መጠቀም ቀልጠፋ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ደግሞ ፊደሉን ጽፎ እንዳለ በማንበብ ረገድ ለምሳሌ “ተማሪ” ለማለት በላቲኑ ፊደል እንደምእራባውያኑ “temari” ወይም “tamari” በቁቤ ደግሞ “tamaarii” ተብሎ ሲጻፍ፤ በኦሮሞኛ “ለጴ” ለማለት “laphee” ብሎ መጻፍ … ወዘተ ምን ያህል ብዙ ፊደሎች እንደሚያስፈልጉት ማንም የሚያየው ነው።
በአንድ በኩል “… ኦሮሞዎች የላቲንን ፊደል ተውሰው መጠቀሚያ ማድረጋቸው የሌሎቹን ብሄር ብሄረ ሰቦች መብት ተጋፍቷል… “ ብለው ሲጽፉ በሌላ በኩል ደግሞ በቁቤ ጉዳይ ጊዜን ማጥፋት፣ የማያስቸግር ነገር የቸገራቸው፣ ወዘተ በማለት ምሁራኑ የሰጡትን አገራዊ አስተያየት ባለመገንዘብ ዘለፋ አዘል ሐተታ በጥሩ ቋንቋ ለመግለጽ ሞክረዋል። ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትንም ወደው አንድ የሚያደርገን ነገር ላይ የጎሣው ፖሊቲካ ልጓም የያዘዎት ይመስላል። ደግነቱ ሐሳብ የምንለዋወጠው በአማርኛ መሆኑ ራሱ ሁላችንም ምን ያህል አንጀት የሚበሉና ልብ የሚነኩ ስሜታችንንና ሐሳቦችን መለዋወጥ መቻላችን ብሔራዊ ቋንቋ ስላለን በመሆኑ አንድ የሚያደርገንን ነገር አለማጣታችን እግዚአብሔር ይመስገን እላለሁ። ሆኖም በሳይንስ ባልተደገፈ ሁኔታ ቁቤን መቃወም ተገቢ አይደለም የሚል ሐተታ እና ግዕዝ ራሱ ፊደሎቹን ያገኘው ከሳባ ነው ብለው የራስዎን ግንዛቤ በማብራራት በሰፊው ጽፈዋል፤ ነገር ግን በ፲፻፱፻ ዓ ዓለም ሳባውያን ወደኢትዮጵያ መግባታቸውን የገለፀው በዘመኑ በግዕዝ የተጻፈ ጽሑፍ ስለነበር ከሳባውያን መግባት በፊት ማለት ከ፬ ሺህ ዓመታት በፊት ግዕዝ በመንግሥት ደረጃ ጥቅም ይሰጥ የነበረ ሥነጽሑፍ እንደነበረ በሚያምኑበት ሳይንሳዊ ጥበብ ተረጋግጧል። እንዲየውም የሳባ ምንጭ ኢትዮጵያ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ መረጃዎች እንዳሉ የሚያስረዱ ሊቃውንትም አሉ። ሆኖም ሳባውያን እና ኢትዮጵያውያን ዝምድና እንዳላቸው ሳይሆን የተለያዩ መሆናቸውን ብቻ የሚገነዘቡ ስለሆነ የታሪክ ዕውቀትዎን ቢያዳብሩት መልካም ይመስለኛልና የበለጠ ጥቆማ ለማግኘት “Ethiopia Risks of Omnipotence by Tefera Dinberu, April 2009” የተባለውን መጽሐፍ እንዲያነቡ እጋብዝዎታለሁ። ከጎሣ ፖሊቲካ ተፅእና ነፃ በሆነ ሁኔታ አንብበውም ሆነ የቋንቋ ምሁራንን ጠይቀው ወይም ከሳይንሳዊ ምርምር ውጤት ፈልገው ዕውቀትዎን እንዲያዳብሩ ነው። በፖሊቲካ ሳይሆን በሕዝቦች መስተጋብርና በዝግመታዊ ለውጥ (evolution) የመጣውንና ቢያንስ ከሺህ ዓመታት በላይ በማገልገል በሥነጽሑፍ የዳበረውን አማርኛ ደካማ ነው ካሉ ላቀረቡት ዘለፋውን ትተው በብሔረሰብ ደረጃ የተደራጁትን የቁቤ ምሁራን ብቻ ሳይሆን ራስዎን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በማየት ዓለም አቀፍ ቋንቋ ምሁራንን ጠይቆ በመረዳት ለሕዝቦችና ለጋራ አገራችን የሚበጀውን ቢያስተውሉ ይሻል ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ግዑዝ ነች ማለትዎ ደግሞ የአገርን ትርጉም ማሳነስዎን ያሳያል፤ አገር የሚባለው መሬቱ ብቻ ሳይሆን በመሬቱ ላይ ያሉት ሕዝቦች፣ የተለያዩ ባህሎች ስብስብ፣ አዕዋፉ፣ ወንዙ፣ ጫካው፣ ተራራው፣ ቁጥቅዋጦው፣ አውሬው፣ እንሰሳው፣ ሣር ቅጠሉ ሳይቀር ካሉን የጋራ ታሪኮች ጋር ተደማምሮ መሆኑን አጥተውት ወይም ዘንግተውት ይሆን? አፋሮች የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቁታል ያሉት ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል የጠለቀ አስተሳሰብ እንደሆነ ይመልከቱት። የነአብዲሳ አጋን፣ የነገረሱ ዱኪን፣ “ገበየሁ ቢሞት ባልቻ ተተካ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” የተባለላቸውን ባልቻ አባነፍሶን፣ የነራስ አበበ አረጋይን፣ የነእቴጌ ጣይቱ ብጡልን፣ በአድዋ ላይ ታሪካዊ ተጋድሎና መስዋዕትነት በመክፈል የኢጣሊያን ጦር ድል ያደረጉት ፈረሰኞች የኦሮሞ ተዋጊዎችን (Orom Cavalry) እና ሌሎች በቁጥር ለመግለጽ የሚያዳግቱ ኢትዮጵያውያን ቅድመአያቶቻችን በጀግንነት በደማቸው ያቆዩንን ሀገር በመጠበቅ በዚያ ላይ በባህል፣ በምጣኔ ሀብት፣ በዲሞክራሲና ፍትሐዊነት በጋራ እንድናድግ ማሰብ ኢትዮጵያዊነት ነው።
በአንቀጽ ፴፱ መሠረት እንገንጠል ያለ የለም ማለትዎም ዶሮን ሲያታልልዋት በመጫኛ ጣሏት እንደተባለው ነው፤ ወያኔ ሕዝቦቻችንን ለመከፋፈል ልትጠቀምበት ስትፈልግ ይህችን አንቀጽ በክት ያስቀመጠቻት መሆኑን አለመረዳትዎ ወይ አውቀው ለማደናገር አሊያም ጨርሶውኑ የወያኔ ሴራ አልገባዎትም ማለት ነው። የጽሑፍዎ መንፈስ እንደሚያመለክተው የጎሣን ጉዳይ የልዩነታችን መሠረት እድርገው ነው የሚያዩት፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚኮሩበት ዜጎች ደግሞ ዥጉርጉርነታችን ውበታችን ነው ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ ታዲያ እኛ የኢትዮጵያውያን በአለባበሳችን፣ በአነጋገራችን፣ ልዩነታችንን እንወቀው እንጂ ለመሆኑ የማን አገር ሰው ነው እንዲሁ ቁመናችንን አይቶ አንተ ኦሮሞ ነህ፣ አንተ ጉራጌ ነህ፣ አንተ አማራ ነህ፣ አንተ ከምባታ ነህ፣ አንተ ሐዲያ ነህ…. ወዘተ የሚለን፧ እንኳን በገጻችንና በቆዳችን በአረማመዳችን፤ በአመጋገባችን፣ በአስተሳሰባችንና በስሜት አገላለጻችን ሳይቀር እጅግ እንቀራረባለን። እርስዎ የሚያትቱት ዓይነት ልዩነት ከሆነ ግን ከአንድ እናትና ከአንድ አባት የሚወለዱ ልጆች እንኳ ልዩነት አያጡም።
ዲሞክራሲ ልዩነቶችን ገርቶና አቻችሎ ለጋራ ጥቅሞች መተባበር ሲሆን ይህም የሚተገበረው በነፃ የሕዝቦች እንቅስቃሴና መቀላቀል ነው። ምሁራኑ የጨነቃቸው የሁሉንም ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞች በማየት ኢትዮጵያውያን ሁሉ የነበሩንን እሴቶች በኅብረት በማዳበር ሌሎች የበለጸጉ አገሮች ወደደረሱበት እድገት በጋራ እንድንደርስ፤ በአንፃሩ ደግሞ በአመራር ችግር የተነሣ ኅብረት አጥተን በየዘመኑ በሚነሡ አዳዲስ የፖሊቲካ ፈሊጦችና ተዛማጅ ሽኩቻዎች ሁላችንም ሳንበለጽግ ደህይተን ወደኃላ እዳንቀር የሁሉም ሕዝቦች የጋራ እድል ስለሚያሳስባቸው ነው እንጂ ምንም ዓይነት የግልም ሆነ የቡድን (የጎሣ) ጥቅም ታይቷቸው ወይም ተነክቶባቸው እይመስለኝም።
የላቲን ፊደል መጠቀሙ ሕዝቦቻችንን በቀላሉ አንዳይግባቡ ያደርጋል በማለት፤ ለ ፳፭ ዓመታት የኦሮሞ ልጆች ቁቤ እየተማሩ እንደተደሰቱ ገልጸዋል። ምን ያህል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን መግባባት አለመቻላቸውን እንደደስታ መቁጠርዎ ይገርማል። አዎን በኦሮሞ የጎሳ ሊቃውንት/ፖሊቲከኞች የተመሩ ብዙ የዋህ ኦሮሞዎች ቁቤን ሊያደንቁ ይችላሉ፤ በኦሮምኛ “ሲርበ ጊዲ” እንደሚባለው ማለት ነው። ከ”ሴረ ኬኛ” ላለመውጣት ማለት ነው፤ “ሴረ ኬኘ” ጥሩ ይሁን አይሁን አይጠየቅም፤ የኦሮሞ ልጅ በኦሮሞ ላይ ጥፋት አይፈጽምም ተብሎ ስለሚታመን። ቁቤ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በመታወጁ በሸዋ፣ ደቡብ አካባቢዎች፣ ከፋ፣ ሐረርና ሌሎች ክፍለሀገሮች ቁቤ ለመማር ያልፈለጉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ብዙ ማእቀብ እንግልትና እሥራት ጭምር እንደደረሰባቸው በሰፊው ሰምተናል፤ ለምሳሌ በ፩፱፻፹፯ ዓም አካባቢ ድምፅ ስጡ ተብለው አንድ አባት በምዕራብ ሸዋ ውስጥ እኛ እርስበርሳችን ኦሮምኛ መነጋገር ማን ከለከለን? ልጄ ሌላው ሕዝብ የሚነጋገርበትን አማርኛ ቢያውቅና ከኅብረተሰቡ ጋር ቢተዋወቅ እመርጣለሁ በማለታቸው በቀጣዩ አዝመራ ወቅት ማዳበሪያ እንደተከለከሉ፤ እንዲሁም ልጆቻቸው ኦሮምኛ ለማይችሉ ልጆች ኅብረተሰቡ በአማርኛ የሚያስተምር የግል ትምህርት ቤት ለመክፈት ፈልገው እንዳልተፈቀደላቸው ሰምተናል፤ ይህን ነው እንግዲህ እርስዎ የዲሞክራሲ መብት መከበርና ደስታ የሚሉት።
በተጨማሪም ቁቤ ከታወጀ በኃላ የተማሩ ወጣቶች ከኦሮምኛ በስተቀር በአማርኛ ማንበብና መጻፍ ባለመቻላቸው በሥራና ማህበራዊ ጉዳዮች መቸገራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፤ ለምሳሌ ኦሮምኛ የሚናገር በቁቤ የተማረ ሰው በአማርኛ ደብዳቤ ለመጻፍም ሆነ በአማርኛ የተጻፉ መጻሕፍትንም ሆነ ሌሎች ጽሑፎችን ማንበብ እንደማይችል ሁሉ፣ አማርኛ የአፍ ቋንቋው የሆነ ሰው የግዕዝን ፊደል ተጠቅሞ የሚያውቀውን ያህል በኦሮምኛ ለማንበብና መጻፍ እንዳይምክርና ብሎም የማወቅ ፍላጎቱ እንዲታቀብ ተደረገ ማለት ነው። በማስመሰል እንኑር ካልተባለ በስተቀር እኔ የማውቃቸው የኦሮሞ ጉዋደኞቼ በቁቤ ከመጠቀም በአማርኛ መጠቀም እንደሚቀናቸው ነው የሚነግሩኝ።
ቋንቋ ዘር፤ ሃይማኖትና የፖሊቲካ ልዩነትን ተከትሎ የማይወረስ አድልዎን(discrimination) የማያውቅ የመግባቢያ መሣሪያ ነው። ማንኛውም ቋንቋ ከማንኛውም ቋንቋ አያንስም፤ እንዲሁም ማንኛውም ባህል ከማንኛውም ባህል አይበልጥም የሚባለው የአንድን ኅብረተሰብ ባህል የኅብረተሰቡ ቋንቋ ለኅብረተሰቡ ባህል በቂ ስለሚሆን ነው። ይህ ማለት ግን ቋንቋም ሆነ ባህል ማደግና መሻሻል የለበትም ማለት አይደለም፤ ማደግና መሻሻልማ ለቋንቋና ባህል የግድ አስፈላጊ ናቸው፤ በተለይ ባህል መሻሻል፣ መዳበር፣ ማደግ ይኖርበታል፤ አለበለዚያ ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር መራመድ ይቸገራል። ስለሆነም በቋንቋ ድንበር መነጣጠል (isolation) ሳይሆን ማህበራዊ መቀላቀል (integration) ለባህልና ቋንቋ እድገት እጅግ አስፈላጊ ነው። ቋንቋ የማንነት ጉዳይ ሆኖ ቢገለጽም በፊደል መለያየት ግን የጠባብ ፖሊቲካ ባሪያ መሆን እንጂ የእኩልነት መለኪያ ሊሆን አይችልም፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አልነበረም፤ አማርኛን ማወቅም ግፍ ነው” በማለት የገለጹት ከበሰለና ከጎሣ ፖሊቲካ ነፃ ከሆነ ዜጋ የሚሰጥ አስተያየት ሳይሆን እነመለስ ዜናዊ/ ወያኔ/ አገርን ከፋፍሎ ለመግዛት ባጠመዱት ወጥመድ ውስጥ የገቡ ቆቅ መሆንዎ በግልጽ ስለሚታይ ስለአገራችን የጋራ ጉዳዩች ከነፃ ምንጮች ተጨባጭ መረጃዎችን ቢከታተሉ ከዚህ ወጥመድ ወጥተው ነፃ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በጋራ ቋንቋ የማይጠቀም ሕዝብ ለመግባባትና በእኩልነት ለመተያየት ይቸግረዋል፤ በቋንቋ የማይግባቡ ሰዎች ደግሞ አስተርጓሚ ስለሚያሻቸው ግንኙነቱንና መተማመኑን ጭምር ያላላዋል፤ ቋንቋ የመቀራረቢያ ድልድይ መሆኑ ቀርቶ መለያያ ድንበር ከሆነ ሕዝቦቻችንን ከማቀራረብ ይልቅ ከፖሊቲካው ጋር ተጨማምሮ እንደባይተዋር እንዲተያዩ የሚያደርግ ሁኔታን ይፈጥራል፤ ስለሆነም የዳበረውን የግዕዝ ፊደል መጠቀም ለጋራ መግባባትና የባህል እድገት የሚበጅ ሲሆን በአንፃሩ ለአንድ ሀገር ሕዝብ ተጨማሪ ሥነጽሑፍ በማስተማር ጊዜና አቅምን ከማዳከም የነበረውን የጋራ ፊደል መጠቀም ለጋራ እድገት ከመርዳቱም በላይ ለኦሮሞ ቋንቋ መበልፀግም እንደሚጠቅመው ማየት ይቻላል። የላቲንን ፊደል መጠቀሙ ግን ኦሮሞኛን ወደ ፈረንጆቹም አያደርሰውም፤ ከኢትዮጵያውያንም አያቀራርበውም፤ ያራርቀዋል እንጂ፤ ለማቀራረብ ሳይሆን የመራራቂያ ድንበር መፍጠር ለመነጣጠል (isolation) እንጂ ለማኅበራዊ ትሥሥር (social integration) አያገለግልም፤ የጋራ ፊደል መጠቀሙ ለቋንቋ መወራረስና ብሎም መስፋፋት የሚጠቅም ሲሆን በሕዝቦች መቀራረብ የባህልና የምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚ) ዕድገትን ያመጣል። ስለሆነም ኦሮሞኛ ቋንቋ ላለፉት ፫፻ ዓመታት በነፃ ሲስፋፋ የቆየበትን ዕድል አሁን ደግሞ በብሔር/ብሔረሰብ ድንበር ሲከለል እድገቱን ይገድበዋል እንጂ ስለማያሳድገው የዋህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ኦሮሞዎች ሲጉዱ እኛም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጉዳቱ ስለሚሰማን እንዳለየን ማለፍ እይገባንም።
መነጣጠል አቅምን ማሳነስና ለውጭ ተጽዕኖዎች መመቻቸት ሲሆን፣ የማኅበራዊ መተሣሠር ደግሞ በጋራ ሰብአዊና ቁሳዊ እሴቶችን አስተባብሮ በማሳደግ በዓለም ላይ ያሉትን ፉክክሮች በአሸናፊነት ለመወጣት ነው። በዚህ መሠረት የኦሮሞ ቋንቋ እንዲዳብር/እንዲያድግ የሁላችንም ፍላጎት ነው፤ ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው የኦሮሞም ሆነ ሌላ ቋንቋ ሊዳብር የሚችለው ኢትዮጵያውያን የሚጠቀሙበትን ፊደል ትቶ በላቲን ከመጠቀም ይልቅ ኅብረተሰቡ የሚያውቀውን ፊደል መጠቀም የተሻለ መሆኑ ላማንም ግልጽ ነው፤ የዛሬዎቹ ኦሮሞዎች ሳይሆን ከ፪ ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ በሌላ ስያሜ የሚታወቁት የኦሮሞ የቅድመአያት ቅድመአያቶች እነንግሥት ሕንደኬ፣ በኃላም ከዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ሰሎሞናዊውን ሥርወ መንግሥት ከተረከበው እነ ይኩኖ አምላክ እና ከጎንደር ኢትዮጵያን ሲገዙ የነበሩት አገር መሪ የጁዎች ይገለገሉ የነበሩት በግዕዝ ፊደልና ቋንቋ ነበር። የነበረውን የግዕዝ ፊደል መጠቀም የሚረዳው የኦሮሞን አፍሪቃዊ ባለታሪክነትና የቀደመ ኢትዮጵያዊነት የሚያሳየውን የታሪክ ቅርስ ለአሁኑና ለወደፊቱ ኢትዮጵያዊና የኦሮሞ ትውልድ ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን ጋር ጠብቆ ለማስተላለፍም ይረዳል እንጂ አይጎዳውም። የግዕዝን ፊደል መጠቀም ሌሎች ሕዝቦች ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር እንዲቀራረቡና ኦሮሞኛ ራሱ እንዲበለጽግ ይረዳዋል፤ አንድን ፊደል በጋራ መገልገል የሚጠቀሙ ቋንቋንና ባህሉን በማስተጋበር ለማበልጸግ ነው። ለምሳሌ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን የጋራ ፊደል ስለሚጠቀሙ ከመቀራረባቸውና ከመዛመዳቸው የተነሣ አንዱን ቋንቋ የሚያውቅ ሰው ሌላውን ለመማር ብዙ ጊዜ አይወስድበትም። የባዕድ ያውም የታሪክ ጠላታቸው ፊደልና ቋንቋ የነበረውን እንግሊዝኛ የተጠቀሙት አሜሪካኖች ከሁሉ የበለጠ በለፀጉ እንጂ የተጎዱበት ነገር የለም። ስለሆነም ፊደል ሳናጣ ከሌላ ከመዋስ ያለንን ኮርተንበት በማዳበር ይልቁንስ ለፍትሕና ለጋራ የሕዝቦቻችን ጥቅሞች ብንተጋ።
ተፈራ ድንበሩ