(ቁምነገር መጽሔት) የመጀመሪያውን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ታውቃቸዋለህ አይደል? እንዴታ አልክ? እነሆ እኝሁ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የኑሮ አቤቱታ ስለማሰታቸውን ዕለታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነግሮናል፤ እንዴት አልክ?
ፕሬዚዳንቱ ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ‹የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መሠረት የሚገባኝን ክብር አላገኘሁም› ስለማለታቸው ዘግቧል፡፡ እንዴት አልክ? ለመሆኑ ሀገሪቱን ለስድስት ኣመታት ያህል በመምራት በርካታ አምባሳደሮችንና ዲፕሎማቶችን ሲቀበሉና ሲሸኙ ስለኖሩት ዶ/ር ነጋሶ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ እንዴት አይነት ኑሮ እየኖሩ እንደሆነ ታውቃልህ? አታውቅም አይደል?
ይኸውልህ፤ እሳቸው እንዲህ ይላሉ፤
‹ አሁን ካለሁበት ቤት ውጣ ተብዬ ሁለቴ ተፅፏል፡፡ ለቤት ውስጥ እና ለኑሮ የማወጣውን ገንዘብ ተከልክያለሁ፡፡ የምኖረው በ1ሺህ 700 ብር የፓርላማ ደመወዝ ነው፡፡ መኪናም ተቀምቻለሁ፡፡ ይህን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቢያውቁት ጥሩ ነው፡፡ የቤት ሠራተኛ ባለቤቴ ናት የቀጠረችው፡፡ ጥበቃም በትንሽ ገንዘብ ቀጥሬ ነው። ለህክምና የባለቤቴ ጓደኞች መደሃኒት ገዝተው ባይልኩልኝ ከባድ ነበር የሚሆንብኝ፡፡ ጠዋት እና ማታ አምስት ኪኒን ነው የምወስደው፡፡ የደም ስሮቼ ይዘጋጋሉ፡፡ ለህክምና እና ምርምራ ከሄድኩኝ ሁለት ዓመት ሞልቶኛል፡፡ የስኳር እና የልብ በሽታ አለብኝ፡፡ ለመመርመር እና ውድ መደሃኒቶች ለመግዛት ገንዘብ የለኝም፡፡ ባለፈው ሳምንት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ፕሬዚዳንቱ ጋር በታክሲ ነው የሄድኩት፡፡ የአገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መጠን ክብር እና ጥቅም ይገባኝ ነበር። ይህ ለእኔ ተከልክሏል፡፡ ጥሩ ባለቤት እና የሰው ፍቅር ስላለኝ ደስ ይለኛል፡፡ ግን ይህ አገር እና መንግስት የሚገባኝን ጥቅምና ክብር አልሰጠኝም፡፡ ለወደፊትም ይህን ታሪክ ይፈርደዋል፡፡›
ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? አልክ?
ዶከተር ነጋሶ ይቀጥላሉ፡- ‹ወገንተኛ ሆነሃል ተብዬ ነው፡፡ እውነቱን ከተናገርን እኔ የ1997 ዓ.ም ምርጫ በግል ነው የተሳተፍኩት፡፡ በግል ተሳትፌ ፓርላማ ከገባሁ በኋላም በምን ጉዳይ ላይ ወገንተኛ እንደሆንኩ መረጃ የለም፡፡ አዋጅ 255/94 አንቀፅ 7 ጥሷል ነው የተባልኩት፡፡ በአንቀፅ 13 መሰረትም መቀጣት አለበት ተባለ፡፡ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ድረስ ሄጄ ፍርድ በትክክል አልተሰጠኝም፡፡ ግን የመጀመሪያው ፍርድ ቤትም በግል በምርጫ መሳተፉ ችግር የለውም ብሏል፡፡ «ርዕሰ ብሄሩ ለህገ መንግስቱ፣ ለአገሪቱ እና ለህሊናው ታማኝ መሆን አለበት» ይላል ህገ መንግስቱ፡፡ ይህ እያለ ነው ኢ- ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቅማ ጥቅም የተከለከልኩት፡፡ አሁን ካለሁበትም ቤት በማንኛውም ሰዓት በፖሊስ ያስወጡኛል ብዬ ነው በፍርሃት የምኖረው፡፡›
ታዲያ ይሄስ አሰራር ጥልቅ ተሃድሶ አያስፈልገውም ወይ አልክ? አንድ ወዳጄ ምን አለ መሰለህ? ‹ተሃድሶው ወደ ፊት ስለሚመጣው እንጂ ስላለፈው ነገር የሚጨነቅ አይደለም› በል ቻዎ. .