ሁለቱ አርበኞች ሳይጋጩ እንዲኖሩ | ገለታው ዘለቀ

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ህይወት ውስጥ ሁለት ዓይነት የአርበኝነት ስሜቶች ገዝፈው ወጥተዋል። በርግጥ በአንድ ሃገር ውስጥ የተለያዩ የአርበኝነት ስሜቶች መፈጠራቸው በራሱ የሚያመጣው ችግር የለም። በአንድ ማህበረሰብ ወይም አገር ውስጥ የአርበኝነት ስሜቶች በተለያየ መንገድ መገለፃቸው የሚያመጣው ችግር የለም ብቻ ሳይሆን ዜጎች የአርበኝነት ስሜት ሲይዛቸው ይህንን ስሜት በነፃነት የሚገልፁበትን መስመር መዘርጋት ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው። በዚህ በዛሬው ፅሁፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ጎልተው ስለሚታዩት ሁለት የአርበኝነት ስሜቶች እንወያይ። እነዚህ አርበኞች አንደኛ ብሄራዊ አርበኞች ሲሆኑ ሁለተኛ የብሄር አርበኞች ናቸው። ታዲያ እነዚህ አርበኞች ሲጋጩ ይታያል። ለምን ይጋጫሉ? ስለምን ይራራቃሉ? መቼም በአንድ ሃገር ውስጥ አርበኞች ከተጋጩ በዚያች ሃገር ውስጥ ሰላምንና ልማትን ማሰብ ወደፊት መራመድን ማሰብ እጅግ ከባድ ነው። አርበኞች እርስ በርስ ከተጠላለፉ መረጋጋት አይኖርም።

እስቲ የዚህን የአርበኝነት ስሜት ጉዳይ ከትርጉሙ ጀምረን በውስጡ የሚገዛቸውን የሰው ልጅ ስሜቶች ጥቂት እንመርምር። ሃሳባችንን ለማፋፋት መጀመሪያ አርበኝነት ምንድን ነው? ምን ምን ስሜቶችን ይቆጣጠራል? ካልን የሚከተሉት ስሜቶች ድምር ውጤት ነው። እነዚህ ስሜቶች ፤

ታማኝነት (Loyalty)
መውደድ (Love)
ቅንዓት (Zeal)
መሰጠት (Devotion)
መጣበቅ (Attachment)
ድጋፍና ተከላካይነት (Support and safeguard) ናቸው።

ስለ አርበኝነት ስናጠና ስሜቱ ከነዚህ ከፍ ሲል ከተዘረዘሩት ጉዳዮች የተገነባ እንደሆነ እንረዳለን። እንግዲህ አርበኛ ስንል ከነዚህ ስሜቶች የተገነባ ተክለ ሰውነት ነው ማለት ነው። በመሆኑም አርበኝነት ስንል ዜጎች ለሃይማኖታቸው ወይ ለብሄራቸው ወይ ለሃገራቸው ይህን ስሜት ያንፀባርቃሉ ማለት ነው – ማለት ነው። እንግዲህ ታዲያ አንድ ዜጋ ለራሱ ብሄር አርበኛ ሆኖ ብቅ ቢል የአርበኝነት ስሜቱን በተገቢው መስመር እስከገለፀ ድረስ ጤናማ አርበኝነት ነው። በማህበረሰብ ውስጥ ስለሚፈጠር የአርበኝነት ስሜት ስናነሳ ስሜቱ የሚገለፀው በጎሳ በሃይማኖት ወይም በሃገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን የሙያ አርበኞችም ይነሳሉ። እነዚህ የሙያ አርበኞች ከተራ ስሜት የዘለላ ተቆርቋሪ ይሆኑና ለሙያቸው ማህበር ለማቋቋም ይጥራሉ ሙያቸው እንዲከበር እንዲዳብር ብዙ ይደክማሉ። እነዚህ አርበኞች የነፃ ፕሬስ አርበኞች፣ የዳኝነት አርበኞች፣ የሰብአዊ መብት አርበኞች ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ስሜቶች መንከባከብ በአግባቡ እንዲደራጁ ማድረግ የዴሞክራሲ እምነት ነው። ዋናው ጉዳይ ማንኛውም የአርበኝነት ስሜት በአብሮ መኖር በአክብሮትና ትእግስት የሚስተናገድ ከሆነ ዜጎች የተነኩበትን የአርበኝነት ስሜት መግለፅ ይችላሉ። ዴሞክራሲም ዜጎች በትክክለኛው መስመር ለብሄራቸው አርበኞች ሆነው ቢኖሩ ያተርፋል እንጂ አይከስርም። ታላቁ መሪ ዊንስተን ቸርችል እንዲህ ብለዋል። “ፍቅረ ባህል ወይም ልማድ ብሄራዊነትን አያደክምም።”

የአርበኝነት ስሜት ችግር የሚያመጣውና ብሄራዊነትን የሚያዳክመው በአንድ አገር ውስጥ የአርበኝነት ስሜቱ ፈሩን ለቆ ሲሄድና ሁሉን ለመጠቅለል ሲነሳ የብሄር ፓለቲካ ፍቅር ሲይዘው ነው። ያን ጊዜ መንግስት ያንን የአርበኝነት ስሜት መመርመር አለበት። የብሄር አርበኛ በፍቅረ የብሄር ፓለቲካና ፍቅረ ነዋይ ከተነደፈ ያ ብሄራዊነትን ያደክማል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማለዳ ወግ ... በአዲስ አመትም ያላባራው ስቆቃ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እነ ልናገረው የከበደኝ ሮሮ !

ከፍ ሲል እንደተገለፀው በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች አገሮች ባልታየ መልኩ ሁለት የአርበኝነት ስሜቶች ጎልተው የወጡ ሲሆን እነዚህ ብሄራዊ አርበኞች እና የብሄረሰብ አርበኞች ባላንጣዎች ሆነዋል። የብሄረሰብ አርበኛው ቁጥር በቅርብ ጊዚያት ከፍ ያለ ይመስላል። እነዚህ አርበኞች ከብሄራዊ አርበኞች ጋር ከሚያጋጫቸው ምክንያት አንዱ የብሄረሰብ አርበኞች አርበኝነታቸውን ሊገልፁ የፈለጉበት መንገድ ነው። የማንነት ፓለቲካን ሲመኙ ነው ከብሄራዊ አርበኞች ጋር የሚጋጩት። በአሁኑ ሰዓት በአንዳንዶች ዘንድ አብቦ የሚታየው የብሄር አርበኝነት ለብዙዎች የሚያስፈራው ይህን የአርበኝነት ስሜት የያዙ ወገኖች ወደ ፓለቲካ ስልጣን ሲመጡ ይህ በብሄር አርበኝነት ስሜት ላይ የተገነባ ተክለ ሰውነት ብሄራዊ የሆኑ ጉዳዮችን አይሸከምም በውስጡ ያለውን ፍቅር ቅንዓት ታማኝነት መጣበቅ ከለላ መሆን የመሳሰሉትን ወሳኝ ስሜቶች ብሄሩ ስለወሰደበት ፍትህን በሃገር ደረጃ ለማስፈን የአርበኝነት ስሜቱ ተከፍሏል ወይም አልቋል ብለን እንድናምን ስለሚያደርግ ነው። ህወሃት ላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን እምነት የሚያጡት የመሪዎቹ የአርበኝነት ስሜት ቡድናዊነቱ ያይላል ብለው ስለሚያምኑ ነው። ህወሃት ንግድ ውስጥ ሲገባ ይጠረጠራል፣ በሃገር ዳርድንበር ጉዳይ ላይ ይጠረጠራል፣ በሃገር ፍቅር ላይ ይጠረጠራል። ይታማል። ለምን ሲባል ህወሃት ብሄራዊ አርበኛ ሳይሆን የቡድን አርበኞች ማህበር ነው ብሎ ብዙ ኢትዮጵያዊ ስለሚያምን ነው። የመንግስት ተቃዋሚዎች ሆነውም በብሄር ፓለቲካ በጣም የከነፉትን ወገኖች ሁሉ ህዝቡ እንደ ሃገር የፓለቲካ መሪ አድርጎ አይቶ ተስፋ ሊጥልባቸው አይችልም። በአማራ አካባቢ ይሁን ወይም በሌሎች ብሄሮች አካባቢ ብሄርተኝነት እያበበ መሆኑ ሲሰማን ብዙ ሰው ምቾት የማይሰጠው ይሄ የብሄር የፓለቲካ አርበኝነት ለወደፊቷ አገራችን እጣ ፈንታ ጠቃሚ ባለመሆኑ ነው። በአሁኑ ሰኣት ብሄርተኝነታቸውን በብሄር ፓለቲካ መግለፅ የሚሹ ወገኖች ይህ ነቀፌታ ከሰፊው ህዝብ እንዳለባቸው የሚያውቁ ቢሆንም የቡድን አርበኝነታቸውን መልቀቅ አይሹም። ይልቁን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለየብሄሩ አርበኛ እንዲሆን ያበረታታሉ። ይህ የአርበኝነት ስሜት አቅጣጫውን ስቷል በሌላው ዓለም ወንጀል ነው ሲባሉ ደግሞ ዓለም ሁሉ የሚደግፈውን ዴሞክራሲ የተባለውን ቅዱስ ስም ከጎናቸው ለጠፍ ያደርጉታል። እናም ዴሞክራቲክ የብሄር አርበኝነት ይሉታል። ዴሞክራቲክ ብሄርተኞች ነን ይላሉ። ይህ ስያሜ የብሄር ፓለቲካን ለመቀደስ የተደረገ ካልሆነ በስተቀር ዴሞክራሲና የብሄር ፓለቲካ ፀብ ናቸው። የብሄር ፓለቲካ በሁለት መንገድ ብቻ ሊፈጠር ይችላል። አንድም አገሪቱ በኮንፌደሬሽን የምትተዳደር ከሆነ ሁለትም ለመገነጣጠልና የራስን መንግስት መስርቶ ለመለያየት ካማረን፣ ከቆረጥን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ በፌደራል ሥርዓትም ሆነ በአሃዳዊ ሥርዓት የብሄር የፓለቲካ አርበኝነት ሊኖር አይችልም። አይገባም። በብዙ ዓለም ወንጀል የሆነውም ለዚህ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምልከታ (ክፍል-2) ሸንቁጤ – ከካናዳ

በሌላ በኩል ደግሞ የብሄራዊ አርበኞች ስሜት መበረታታት አለበት። በርግጥ ይህ ስሜት በፌደራል ስርዓት ጊዜ ወይ በአሃዳዊ ሥርዓት ወይም በአንድ ሃገር የፓለቲካ ህይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ስሜት ነው። እንዲህ ዓይነት አርበኞች መብዛት አለባቸው። የተባበረችውን አሜሪካ ፣ እስራኤልን፣ ታላቋን ብሪታኒያን፣ የመሳሰሉትን ሃያላን ሃገራት ስናይ ለሃያልነታቸው ትልቁ መሰረት ወታደሮቻቸው ብሄራዊ አርበኞች ስለሆኑ፣ ሳይንቲስቶቻቸው፣ የፓለቲካ መሪዎቻቸው በሃገር ፍቅር የተመሰጡ ታማኝ የሆኑ ስለሆኑ ነው። ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ የኢትዮ እስራኤላውያንን ወታደሮች እያሰብኩ ነበር። በርግጥ ለሃገራቸው ያላቸው ታማኝነት፣ለሙያቸውና ለባንዲራቸው ያላቸው ፍቅር ለእስራኤል ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ያስደምማል። አንዲት ወጣት ጀግና የእስራኤል መከላከያ ኦፊሰር “ህልሜ እውን ሆኗል” ብላ ለሙያዋ ያላትን መሰጠትና ፍቅር ስትገልፅ አየሁ። ይህ ቃል ትልቅ ነው። በውስጡ የአርበኝነት ስሜቶችን ሁሉ ጠቅልሎ ይዟል። ይህ ነው የሙያ ፍቅር። ይህ ነው አርበኝነት ማለት። ይህ ነው ወታደራዊ ሴንትመንት የሚባለው።

ጀርመናውያን የበርሊንን ግንብ አፍርሰው ወደ ውህደት ሲመጡ አንድ ሃበርማስ የተባለ ምሁር አንድ ድንቅ አሳብ ይዞ መጣ። ይህ ሳይንቲስት በርግጥ አርበኛ ነበር። ሃበርማስ ያመጣው አሳብ ሁለቱ ጀርመኖች ወደ ውህደት በሚመጡበት ዋዜማ የማንነት ጥያቄ ተነስቶ የነበረ ሲሆን ለዚህ ጥያቄ ይዞት የመጣው መልስ ለጀርመናውያን ሁሉ ህገ መንግስታዊ አርበኛ (constitutional patriots) እንሁን የሚል የብሄራዊ አርበኝነት አሳብ ነበር። ይህ አሳብ በርግጥ ሁሉን አሳምኖ ጀርመኖችን ሁሉ በአንድ የፓለቲካ ጠገግ ሥር አርበኞች ያደረገ አሳብ ነበር። ሃበርማስ እንዳለው የዜጎች አርበኝነት ስሜት አንድ ማእከል ሲኖረውና በዚያ ላይ የጋራ ማንነት ሲሰራ ያኔ ነው አንድነት የሚመጣው።

ከፍ ሲል እንደተገለፀው ከራሳቸው በላይ ማሰብ በሚችሉ ብሄራዊ አርበኞች ነው ይህቺ አለም የቆመችው። በየትኛውም አገር በየትኛውም መስክ የነዚህ ብሄራዊ አርበኞች በረከት ዛሬ ለዓለም ተርፏል። በሳይንሱ በሚሊተሪው በሲቪሉ በኩል የአለም ጥበብ ያደገው በአርበኝነት ስሜት ነው። አንድ ሰው ከግል ህይወቱ እርካታ በላይ እንዲሰራ ዋጋ እንዲከፍል የሚያደርገው ሃይል የአርበኝነት ስሜት ነው። ታላቁ መሪ ጆን ኤፍ ኬነዲ ሃገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለሃገሬ ምን አደረኩ ብለው ዜጌች እንዲጠይቁ መክረዋል። እኝህ መሪ ብዙ ብሄራዊ አርበኞች ከተፈጠሩ ሃገር እንደሚለውጥ በርቀት ስላዩ ነው። ይህ ስሜት የአርበኝነት ስሜት መሰረት ነው። አርበኞች ለሃገሬ ምን ሰራሁ? የሚለውን ያስቀድማሉ። በእንዲህ ዓይነት የአርበኝነት ስሜት የተነኩ ዜጎች ወደ ፓለቲካው አለም ሲመጡ ብሄራዊ አርበኝነታቸውን የሚገልፅ የፓለቲካ ድርጅት ይመሰርታሉ። ኢትዮጵያውያን መረዳት ያለብን ይህንን ነው። ብሄራዊ አርበኝነትን ማበረታታት ያስፈልጋል። መኮትኮት ያስፈልጋል። ይህ አርበኝነት በርግጥ የቡድኖችን ማንነት ያከበረ ብዝሃነትን የአርበኝነቱ መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ነው ብሄራዊ አርበኞችም ስሜታቸውን መመርመር አለባቸው የሚያሰኘን። የብሄር ፓለቲካ አርበኝነትን እየኮተኮትን አሳድገን ሰማኒያ ሁሉት የብሄር ፓለቲካ አርበኞች ክንፍ መስርተን እንለወጣለን፣ እንበራለን ማለት አልመከር ያለ አርቆ ማሰብ የተሳነው አሳብ ነው። በመጀመሪያ የብሄር አርበኛ እንሁንና ይህ መንግስት ሲወድቅ አዲስ አበባ ላይ ስለሃገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ እንመካከራለን ማለት በጣም ማስተዋል የጎደለው ያልተመረመረ አሳብ ነው። ከፍ ሲል እንደተገለፀው የቡድን አርበኝነት ስሜት ብሄራዊ ማንነትን ሳይጋፋ ሲመጣ ደግሞ ዜጎች ሊያጨበጭቡለት ሊደግፉት ይገባል። ይሄ ነው ብዝሃነት ማለት። በዘመናችን ንፁህ የብሄር ማንነት አርበኝነትን ይዞ ከተነሳ ዜጋ መካከል የኮንሶው ንጉስ ይጠቀሳል። ይህ ንጉስ የፓለቲካ ስልጣን አላማረውም። በሃገሩ ይኮራል። ነገር ግን የኮንሶ ባህል ተጠብቆ ይኖር ዘንድ ይሻልና ለዚህ ማንነት ይታገላል። ነፃ የሆነ የባህል አስተዳደር ይሻል። ይህ ጤናማ የብሄር አርበኝነት ይባላል። በርግጥም የኮንሶ ባህል የኢትዮጵያ ባህል ነውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይደግፉታል። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ስሜቶቻችንን መፈተሽ ግድ ይላል። ወደ ተሻለ ሥርዓት አገራችን ትገባ ዘንድ በሃገራችን የተነሱ አርበኞች መጋጨት የለባቸውም። በቅርቡ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምርና ፓሊሲ ተቋም የተጠናው ጥናት ይህን አሳብ ይደግፋል። በዚህ ጥናት ውስጥ የተገለፀው የብሄራዊ ማንነትና የብሄር ማንነት መገለጫ መርሆዎች በርግጥ ለሃገራችን ፓለቲካ መሰረታዊ ለውጥን የሚያመጣ ነው። በመሆኑም በተለይ የብሄር ፓለቲካ አርበኞች ይህን የአርበኝነት ስሜት የዴሞክራሲ ጠበል የተረጨ አስመስለው ይህን አርማ ይዘው ከመነሳት ተቆጥበው ለሃገራችን ለውጥ ብሄራዊ አርበኞች ሊሆኑ ይገባል። በአንፃሩ ብሄራዊ አርበኞች ብሄራዊነትን ከአንድ ቋንቋና ባህል ጋር ሳያያይዙ ለዴሞክራሲ ለእኩልነት መታገል ይገባል። እንዲህ ሲሆን ነው ወደፊት መራመድ የምንችለው። አርበኞች እርስ በርስ የሚጋጩበት አገር የትም አይደርስም። በአጠቃላይ በተለያየ ማንነት ላይ ተቆርቋሪ ሆነው የሚነሱ አርበኞች ይህን ስሜታቸውን በፓለቲካ ማንነት ለመግለፅ አይሞክሩ። በሴቶች መብት ዙሪያ ልቧ የተነካ እህታችን በዚህ ማንነት ላይ ሆና የሴቶች የፓለቲካ ድርጅት አታቋቁም፣ ለሃይማኖቱ የቀና ሰው ይህን አርበኝነቱን ለመግለፅ የሃይማኖት የፓለቲካ ድርጅት አያቋቁም፣ በብሄሩ ማንነት በፍቅር የተነደፈ የብሄር አርበኛ በዚህ ማንነት ላይ የፓለቲካ ድርጅት አያቋቁም፣ ነገር ግን ይህን የአርበኝነት ስሜት በነፃ ማህበራት መግለፅ ዴሞክራሲያዊ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለሕዝብና ለሀገር፣ ፍቅር እና ክብር ያለው ትውልድ ለመቅረጽ (ከይገርማል)

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

geletawzeleke@gmail.com

2 Comments

Comments are closed.

Share