ትንሽ ድፍረት፤ ራስን ለማየት | ይገረም አለሙ

በማናቸውም  እንቅስቃሴ የበላይነትን/ አሸናፊትን ለመቀዳጀት መሰረታዊ ቁልፍ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ራስንና ተፎካካሪን/ ጠላትን ማወቅ ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለቱን በሚገባ ሳያውቅ የሚነሳ ወይንም በሂደት እነዚህን ለማወቅ የማይጥር ግለስብም ይሁን ቡድን ውጤታማ አይሆንም፡፡ይህ ጉዳይ በተለይ በወታደራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ሲሆን ውድቀቱ በግለሰብና በቡድን ብቻ የሚገታ አይደለም፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ይተርፋልና፡፡

 

ስለ ራስ ለማወቅ መስተዋቱን ወደ ራስ አዞሮ በድፍረት ማየትን ይጠይቃል፡፡ ስለ ራስ በትክክል ማወቅ ሲቻልም ነው ስለ ተፎካካሪ/ጠላት በቅጡ ለማወቅ የሚቻለው፡፡ በዚህ ረገድ በየዘመናቱ በኢትዮጵያ ለሥልጣን የበቁትም ሆኑ ሥልጣን በመሻት በተቃውሞ የተሰለፉቱ ሁሉም  ተመሳሳይ ችግርና ድክመአለበቻው፡፡ ይሄም ነው ለመስዋዕትነት እንጂ ለድል የማያበቃን፣ ቢያንስ ሶስት ትውልድን  በአንድና ተመሳሳይ የውድቀት ጉዞ የሚያነጉደን፡፡

ደርግ ራሱን በትክክል ቢያውቅ ኖሮ ጠላቶቹንም በትክክል ማወቅ በቻለና ለአስራ ሰባት አመት የርስ በርስ ጦርነት ባላተዳረገ  የባለሥልጣኖቹ መጨረሻም እስር ስደትና ሞት ባልሆነ ነበር፡፡በዘመኑ  ይጣወቁ ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱና ዋናው  ኢህአፓም ራሱንና ጠላቴ የሚለውን ደርግ በቅጡ ማወቅ ቢችል ኖሮ በተለቀመ ሽጉጥ እስከአፍንጫው ከታጠቀው ደርግ ጋር የከተማ ውጊያ ለመግጠም ባልዳዳውና ለነጭኛ ቀይ ሽብ እልቂት ምክንያት ባልሆነ ነበር፡፡ ግና ከዛም አልተማርንምና ወያኔም የደርግ ተቀዋሚዎቹም የመሰሎቻቸው ግልባጭ ሆነው ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ እየሄድን ነው፡፡

ወያኔ ራሱን አኩራርቶ ተቃዋሚዎቹንም አግዝፎ የሚያይ በመሆኑ ስለ ራሱም ሆነ ስለ ጠላት ስለሚላቸው ያለው እውቀትም ሆነ ግንዛቤ ትክክል አይደለም  ብቻ ሳይሆን የተቃረበም አይደለም፡፡ ከእኔ በፊትም የነበረ ከእኔ በኋላም የሚመጣ ማንም አልነበረም የለምም በሚል መንፈስ ብበሰብስም እየታደሰኩ ኢትዮጵያን የምገዛው እኔና እኔ ብቻ ነኝ ይላል፡፡ በተግባር ግን ነኝ  ከሚለው በእጅጉ ፊትና ኋላ በመሆኑ ችግር ፈቺ ሳይሆን አባባሽ፣ አልሚ ሳይሆን አጥፊ/ ዘራፊ ነውና  ሀያ አምስት አመት ሙሉ የህዝብን ተቀባይነት ሳያገኝ በጉልበት እየገዛ ቀጥሏል፡፡

ስለተቀዋሚዎችም ያለው እውቀትና ግምት እንደዚሁ የተሳተ በመሆኑ ብእር ላነሱ፣በሰላም ለሚቃወሙ፣የሙያ ማህበር ላደረጁ፣ ሀሳብ እምነታቸውን በአደባባይ ለገለጹ ሁሉ  ቡድን ግለሰብ ሳይልና ሳይለይ ጠመንጃ ይወለውላል ጦር ያዘምታል፡፡ በሺህዎች ይገላል በአስር ሺዎች ያስራል፡፡ ተቀዋሚ የሚል ካባ ደርበው በተግባር ግን ከርሱ ጉያ  ተሸጉጠው ከሚኖሩት በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ በወያኔ እውቀትና የመረጃ ብልሀት ሁሉም አሸባሪ ያ ቢቀር ጸረ ሰላም ናቸው፡፡ ከዚህ አስተሳሰቡ በመነሳት የሚወስዳቸው ርምጃዎች ደግሞ  ስለ ራሱም ስለ ተቀዋሚዎችም ያለውን አመለካከትና ግምት ይበልጥ እያዛባበት ወደ ባሰ ችግር፣ ወደ ባሰ ጭንቀት ውስጥ እየገባ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ የሚያስችለውን መንፈሳዊ ብቃት ወይንም ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት የሚያበቃውን ወታደራዊ አንባገነንት ሳይዝ ተቃውሞ በተነሳበት ቁጥር በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ እየሆነ ህዝብ እየፈጀ ባህልና ታሪክ እያጠፋ ሀገሪቱን የቁልቁለት እያስጓዛት ይገኛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰው ለሰው እረኛ መሆን ካልቻለ ሠላምን አያገኛትም - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የተቀዋሚው ወገን ድክመት ደግሞ ራሱን አግዝፎ ጠላቱን /ወያኔን አሳንሶና አናንቆ የሚያይ መሆኑ ነው፡፡ ተቀዋሚ የሚባለው ርስ በርሱ ከመቀዋወም በሽታ የሚድንበት መድሀኒት ዛሬም ያልተገኘለት ሆኖ ሁሉም ግን በየራሱ በየጎጆው ራሱን አግዝፎ የሚያይ ነው፡፡ድርጅት ለመባል የሚያበቃ ቅርጽም ሆነ አቅም የሌላቸው አረ እንደውም በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎቸ ሰብስብነት ያልዘለሉ ራሳቸውን አግዝፈው ቤተ መንግሥት ልንገባ ነው እያሉ ሲፎክሩ፣ ወያኔን አሳንሰውና አኮስሰው      ለመውደቅ ትንሽ ግፊት ብቻ የሚበቃው አድርገው ሲናገሩ ሰምተናል፣እየሰማንም ነው፡፡ በተግባር ግን ቢከፍቱ ተልባ ናቸው፡፡ በድፍረት በቅንነት በአርቆ አሳቢነት ወዘተ ራስን ማየት ካልተቻለ ስለ ራስ ትክክለኛው ቀርቶ ወደ ትክክለኛው የሚጠጋ እውቀት መያዝ ግንዛቤ ማግኘት አይቻልም፡፡ራስን ካላወቁ ደግሞ ድክመትን አስወግዶ ስህተትን አርሞ ከፉከራ ወደ ትግበራ የሚሸጋገር ተገዳዳሪ ኃይል ሆኖ ሊወጣ አይቻልም፡፡

ሀያ አምስት አመታት በወያኔ አገዛዝ ለመዝለቃችንና ለመጻኢ እድላችንም ብሩህ ነገር ላለመታየቱ ዋናው ምክንያት ይህ ራስንና ጠላትን በትክክል ማወቅ አለመቻል በተለይም ራስን ለማወቅ ፍላጎትም ድፍረትም አለመኖር ነው፡፡ ለርስ በርስ ንትርኩ፣ከመደጋገፍ ይልቅ መወራረፍን ምርጫ ለማድረጉ ወዘተ ዋናው ምክንያትም ራስን አለማወቅ፣ ለማወቅም አለመፈለግ ቢያውቁም ትክክለኛውን የራስ ማንነት አምኖ አለመቀበል ነው፡፡

ሁሉም በድፍረት ትክክለኛ እሱነቱን ለማወቅ ቢጥርና ቢደርስበት ባልሆነው አይደለም ሊሆን በማይችለው ነገር መኩራራቱን ያቆማል፤  የሥልጣን ጥሙ በእውን የማይሆን የቀን ቅዠት መሆኑን ይገነዘባል፣ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው ከሚል እኩይ አስተሳሰብ ይፋታል፡፡ ይህም ሲሆን እንደ ወርድ ቁመቱ፣ እንደ ቅለት ክብደቱ ራሱን ያኖራል፡፡ በከማን አንሼ ከዛም ከዚህም አይጋፋም አይገፋፋም፤ ሁሉንም ወደ ርሱ ደረጃ ለማውረድ ያለ ቁመቱ እየተንጠራራ የሚፈጽመውን የነገር ተኩስና ትንኮሳ ያቆማል፡፡ እኔ የሌለሁበት በሚል ስሜትም እንደ አበደ ውሻ ሁሉንም ለመልከፍ አይልከፈከፍም፡፡ በጥቅሉ ራሱን ያወቀ አቅሙን በትክክል የተረዳ ግለሰብም ይሁን ቡድን ቦታው የት ከእነማን ጋርና አንዴት አንደሆነ በውል ስለሚረዳ ከሌሎች ጋር አብሮ ለመኖርም ሆነ ተባብሮ  ለመስራት አይገደውም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዶ/ር አብይ ንግግር

አስገራሚው ነገር እነርሱ ፖለቲከኛ ነን ባዮቹ ራሳቸውን ለማወቅ አለመድፈራቸው ወይንም አለመፈለጋቸው ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም ፖለቲከኞቹን ለማወቅ ድፍረትም ፍላጎትም የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ፖለቲካው ለወያኔ ሥልጣን ሀብት እንደሆነው ሁሉ በተቃውሞውም ሰፈር የተቀዋሚ መሪነት ሥልጣንም ሀብትም ሆኖ ደካሞቹ ብርቱ ነን እያሉ፣ ግለሰቦች ድርጅት ነን እያሉ፣ለማሸነፍ ቀርቶ ተፎካካሪ የሚያስችላቸው  ለመሆን የሚያስችላቸው አቅም ሳይፈጠሩ አካኪ ዘራፍ እያሉ አታሞ ሲደልቁና አምቢልታ ሲነፉ እያየንና እየሰማን በእውቀት ሳይሆን በስሜት እየተነዳን  ማጨብጨቡ ጎድቶናል እየጎዳንም ነው፣ ከዚህ መላቀቅ ካልቻልን ነገም ከነገ ወዲያም እየጎዳን ይቀጥላል፡፡

ይህ እንዳይሆን ከፈለግን በጎሳ ስሜት ተስበንም ይሁን በጥቅም ተሳስረን፣በአካባቢ ልጅነት ተሰባስበንም ይሁን በእከክልኝ ልከክልህ ተቆራኝተን፣ በአባልነትም ይሁን በደጋፊነት ወግነን ለምናጨበጭብለት ድርጅትም ይሁን ግለሰብ  ትንሽ ድፍረት ይኑራችሁና ራሳችሁን ፈትሹ/እወቁ፣ ለዓመታት ከተጓዛችሁበትና አንድ ርምጃ ወደ ፊት ፎቀቅ ካላዳረጋችሁ መንገድ ውጡና አዲስ አስተሳሰብ ያዙ፣ በአዲስ መንገድ መጓዝ ጀምሩ፡ አለበለዚያ በዚህ አካሄዳችሁ የወያኔን እድሜ ማራዘም አንጂ ህዝብን ከአገዛዝ ለማላቀቅ ምንም አስተዋጽኦ አላደረጋችሁም፣ በማለት ለማረም እንጣር፣ የሚታረሙ ካልሆኑ ደግሞ በዚህ አያያዛችሁና አድራጎታችሁ ለምንም አትበጁምና ገለል በሉ  አንቅሮ ለመትፋት እኛም ዘንድ ትንሽ ድፍረት ይኑረን፡፡ አጥፊዎችን እየደገፍን ጥፋትን ማውገዝ አንደምን ይሆናል፡፡

ፖለቲከኞቻችን ራሳቸውን፣ እኛም እነርሱን ላለማወቃችን የሚያሳይልኝ ማስረጃ ላቅርብ፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ማስረጃን ከቤት ቁጭ ብሎ በገፍ ማግኘት በሚቻልበት ዘመን ያለ ማስረጃና መረጃ የሚጻፉ  ጽሁፎችን (ማስረጃ ያልቀረበለት ጽሁፍ አሉባልታ ነው) የሚያስተናግዱ ድረ ገጾች  ምክንያታቸው ምን ይሆን! መቼም  ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማክበር ነው የሚል ክርክር ያቀርባሉ  ብዬ አልገምትም፡፡ ሁሉም መብት ገደብ አለው፡፡ የኢዶትሪያል ፖሊሲ የሚዘጋጀውም ለዚሁ ይመስለኛል፡፡ ወደ ጉዳየ  ልመለስ፤

ማሳያ አንድ ሀገር ውስጥ፣ በምርጫ 2007 የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት እናሸንፋለን የሚሉ ፖለቲከኞችንና ፓርቲ ነን ባዮችን ሰምተናል፡፡ እናሸንፋለን ሲሉ የተሸላ ይባ የነበረው ድርጅት እንኳን ለ547 የፓርላማ ወንበር ሁለት መቶ የሚሞላ ተወዳዳሪ  አላቀረበም፡፡ የተሸነፍነው ምርጫው ተጭበርብሮ ነው ሲሉም ትንሽ አላፈሩም፡፡ እኛም የሚሉትን ተቀብለን  ከማስተጋባት ወጣ ብለን አረ ለመሆኑ እናሸንፋለን ስትሉ ምን ይዛችሁ ነው? ማለት አልቻልንም፡፡ይህ ታዲያ ፖለቲከኞቹ መቼም በምንም ሁኔታ ራሳቸውን እንዳያዩ አበረታቷቸዋል፡፡እናም ዛሬም በትናንቱ መንገድ በባዶ እየፎከሩ ቀጥለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዕውቀቱ ቡዳው በላን!

ማሳያ ሁለት በውጪ ሀገር፤አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጠው በምን ሁኔታ በየትኛው ሰልትና መንገድ ለማሸነፍ አንደሚበቁ አይደለም መሬት ላይ በወረቀት ላይ አንኳን የረባ እቅድና ስትራቴጂ የሌላቸው ወገኖች ምኒልክ ቤተ መንግሥት ልንገባ ነው እያሉ ሲያቅራሩና ሲፎክሩ፣ወያኔን አሳንሰውና አኮስሰው ሲደሰኩሩ አረ የት ሆናችሁ፣ ምንኑስ ይዛችሁ በየትስ ተረማምዳችሁ ብሎ መጠየቅ አልቻልንም፡፡ ከዚህ ሲያልፍም እነርሱ ሊያዩት ያልቻሉትን ወይንም ያልፈለጉትን ትክክልኛ ማንነታቸውን ማሳየት ለእነርሱም በአሉበት ከመርገጥ ወጣ ብለው የመሻሻሉን መንገድ ሀ ብለው አንዲጀምሩት ማገዝ ነበር፡፡ ግና በእውነት ላይ ተመስርተው ሳይሆን በስሜት ሰክረው  ሆይ ሆይ ማለቱን የሚመርጡ በመኖራቸው ጉዞአችን የእንቧይ ካብ ስራችን ለወያኔ የተመቸ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ነገም ይቀጥላል፡፡

ፖለቲከኞ ነን እየታገልን ነው ወዘተ ባዮቹ ስ ራስቸው በደንብ አውቀው ጠላታችን የሚሉትንም በትክክል ለማወቅ ችለው  የማይሰሩ፣ እኛም ማህበረሰቡ ለመምከርም ትክክለኛ ማንነታውን ለማሳያትም  ትንሽ ድፍረት በማጣት እያለባስን እያረስን አርም ስናመርት  ኖረናል፤ ለወደፊቱም ያሰጋናል፡፡ የሀገራችን አርሶ አደር ጥራት ያለው ብዙ ምርት ለማምረት መሬቱን የአየር ሁኔታውን ወዘተ በሚገባ ያጠናል፡፡ ከዛም እሱ የሚሻውን ሳይሆን መሬቱ የሚፈልገውን ዘር ይመርጣል፡፡በወቅቱ ያርሳል ጊዜውን ጠብቆ ይዘራል፡፡ ይህን ሳያደርግ ጥንድ በሬ ይዞ አራሽ እያለ ቢፎከር አንኳን ለገበያ የሚቀርብ ለቤተሰቡ ቀለብ የሚበቃ  ምርት አያገኝም፡፡ ፖለቲከኛም እንዲሁ ነው ፓርቲ መሰረትን እያሉ በማወጅ፣ ከእኛ ወዲያ ታጋይ እያሉ በመፎከር፣ ወያኔን አንኳሶና አኩስሶ በመደስኮር እንኳን ወያኔን ማስወገድ ወንበር መጋራትም አይቻልም፡፡ አርሶ አደሩ ጥሩ ምርት ለማግኘት እሱ  የሚሻውን ሳይሆን መሬቱ የሚፈልገውን እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ፖለቲከኞችም ከምር ለለውጥ የቆሙ ከሆኑ እነርሱ የሚፈልጉትን ሳይሆን ትግሉ የሚጠይቀውን በጽናትና በድፍረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ለመቻል መሰረቱ ደግሞ ራስን ማወቅ ነው፡፡ ከዛም ጠላትን፡፡

Share