እንዴት ከረምሽ! አዲስ አበባ?

መንፈቅ ላለፈ ጊዜ ያህል ተለይቻት ነበርና ነው ናፍቆት በተሞላ ሰላምታ ሞቅ አድረጌ ሰላምታዬን ያቀረብኩላት፡፡ ታዲያ ትናፍቀኝ እንጅ አኩርፌያታለሁ፡፡ ሰላማዊ ወገኖቿ በሀገሪቱ በየቦታው በወያኔ ነብሰ በላ ወታደሮች ደማቸው በግፍ ሲፈስ እሪ! ብላ ኡኡታዋን ማቅለጥና ከጉያዋ የተወሸቀውን ግፈኛ አገዛዝ አንቃ ለፍርድ ማቅረብ ሲገባት ዓይታ እንዳላየች ሰምታ እንዳልሰማች ሆና ጸጥ በማለቷ የምር አኩርፌያታለሁ፡፡

 

ለነገሩ እሷ ምን ታድርግ? እኛ “አዲስ አበባ! እናት ሀገርሽንና ሕዝብሽን እረሳሽ እንዴ? ኧረ ተነሽ!” ብለንላቀረብንላት ጥሪ ቆራጥ ምላሽ ልትሰጥ ስትሰናዳ ሌላው ደሞ ይነሣና “ፊንፊኔ…… !” በማለት ተቃራኒ መልእክት ባዘለ ይዘት ጥሪውን ያቀርብላታል፡፡ ግራ ገባት! የማንን ትስማ? ጭራሽ የህልውና ሥጋት አደረባትና አንጀቷ እያረረ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ እርፍ ብላ ለመቀመጥ ተገደደች፡፡

በነገራችን ላይ ነገርን ነገር ያነሣዋልና አዲስ አበባ ከወያኔ ትዕዛዝ በተሰጣቸው ወገኖች ፊንፊኔ እያሉ በይፋ የመጥራታቸውን ነገር አግባብነት አለው ትላላቹህ? ምን አዲስ አበባ ብቻ ናዝሬትና ደብረዘይትንም አዳማና ቢሾፍቱ
እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ በምን አግባብ ነው እንዲህ ለማለት የቻሉት? እንዲህ ባዮቹ እነኝህንና ሌሎች የሀገራችንን ክፍሎች ከ16ኛው መቶ ክ/ዘ በኋላ በወረራና በመስፋፋት እንደያዙት እነሱም ይሁኑ የተቀረነው ጠንቅቀን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ እውነቱ ይህ ከሆነ የሀገራችንን ሥፍራዎች የነበራቸውን ስም አጥፍተው አዲስ የራሳቸውን ስም የመስጠቱን መብት እንዴት አገኙት? ማንስ ይሄንን የመስጠት መብት ኖሮት ሰጣቸው? ምናልባት እነኝህ ከተሞች ወይም ስፍራዎች በወረራ ከመያዛቸው በፊት የነበረው የቀድሞ አማርኛ ስሞቻቸው አዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት ወዘተረፈ ላይሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጅ ከእነዚህ ሥያሜዎች ያልተለየ አማርኛ ሥያሜ እንደነበራቸው ለመገመት ተመራማሪነትን የሚጠይቅ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት የነበራቸውን አማርኛ ወይም ግእዝ ሥያሜዎችን ትተው ሌላ ሥያሜዎችን መስጠት መጠቀም በፍጹም አግባብነት የለውም ከዚህ ድርጊትም ሊታቀቡ ይገባል!

አዲስ አበባ እኮ ከ229ዓ.ም. እስከ 461ዓ.ም. ድረስ ከአክሱም በተጨማሪ ለ232 ዓመታት ያህል የረር በመባል በሚታወቀው ምሥራቃዊ ክፍሏ ላይ የአክሱማውያን ነገሥታት ዋና መቀመጫ የነበረች ታሪካዊት ከተማችን ነች፡፡ ይሄም ወሬ ሳይሆን በስፍራው፣ በአቅራቢያውና በአካባቢው እንዲሁም ወያኔ ኦሮሚያ እያለ በሚጠራው የሀገራችን ክፍል ሁሉ በግራኝ አሕመድ ወረራ በፈራረሱ በርካታ ጥንታዊ አብያተክርስቲያናትና አብያተመንግሥታት አሻራዎችና ፍርስራሾች ማረጋገጥ የሚቻለው ጉዳይ ነው፡፡

እና ታዲያ እውነታው እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ወያኔ/ኦሕዴድና ኦነግ ምን ዓይነት ኅሊና ቢኖራቸው ነው እንዲህ ዓይነቱን ነውረኛ ተግባር ሊፈጽሙ የሚችሉት? ለነገሩ ኅሊና የሚባል ነገርስ የት አላቸውና! ወይ በግልጽ የጨዋታው ሕግ ውንብድናና ዝርፊያ ነው በሉንና አንድ ፊቱን በእሱ እንዳኝ! ነገር ግን በውንብድና የተገኘን ውጤት ሕጋዊ ለማድረግ እየተጣጣራቹህ ስለ ፍትሕና እኩልነት የማውራት የሞራል (የቅስም) ብቃት እንዴት ሊኖራቹህ ይችላል?
አዳማ የሚለው ሥያሜ እንኳን አማርኛ ወይም ግእዝ ከዕብራይስጥ ወይም ከሌላ የመካከለኛው ምሥራቅ ቋንቋ ከተዋሷቸው ቃላቶች አንዱ መሆኑ ስላልታወቀና ግእዝ ወይም አማርኛ ስላልሆነ ኦሮምኛ ሊመስል ቻለና ያንኑ ሥያሜ ሊጠቀሙ ቻሉ እንጅ ቃሉ ኦሮምኛ አይደለም፡፡

አዳማ ኖኅ ለልጆቹ ርሥት ወይም ግዛትን ሲያከፋፍል ለካም የደረሰች የነበረች በኋላም ለልጁ ለከነአን ከተሰጡት ግዛቶች ውስጥ አንዷ ሥፍራ ናት ዘፍ. 10፥19 ጎጃምም ውስጥ ዣንበራ ወረዳ ጨጎዴ ሐና በሚባል ሥፍራ ደጉ ንጉሥ (በቤተክርስቲያን የትንቢትና በማቴ. 24 ወንጌል ትርጓሜ ላይ ወደፊት ይመጣል ተብሎ የተተነበየለት ቴዎድሮስ በመባል የሚታወቀው ንጉሥ) ይወጣበታል ተብሎ የሚነገርለት አዳማ በመባል የሚጠራ  ገመገም ተራራ አለ፡፡ አገሩ ያማራ ሀገር ነው፡፡ በዚህ ሥፍራና አካባቢው የሚኖሩ አማሮች እራሳቸውን እንደ ንጥር (ኦሪጅናል) አማሮች አድርገው የሚቆጥሩ አማሮች ናቸው፡፡ ሕፃናት በዚህ ተራራ ላይ ከብት ሲያለቅሙ “አንዳንድ ጊዜ ከከብቶች ጋር ሳር ሲለቅም እናየውና የት እንደሚገባ ስንከታተለው ሳይታየን የሚሠወረን ነጭ ፈረስ አለ!” ይላሉ አረጋውያኑ “የቴዎድሮስ ፈረስ ነው!” ይላሉ፡፡ ይህ ሥፍራ ቴዎድሮስ ይወጣበታል ተብሎ ከሚነገርላቸው ቦታዎች ሁለተኛው መሆኑ ነው፡፡ ሌላኛው የረር መሆኑ ይታወቃል፡፡

አይይይ! የኔ ነገር! ነገርን ነገር አንሥቶት ነው እንጂ እኔ እንኳን ዛሬ ላወራላቹህ ያሰብኩት ይሄንን
አልነበረም፡፡ መግቢያዬ ላይ እንዳልኳቹህ ለወራት  አዲስ አበባ አልነበርኩም፡፡ ዛሬ መግባቴ ነው፡፡  ዛሬን
ጨምሮ ሰሞኑን ማዕከላዊ ወይም የፌዴራል ፖሊስ (የራስ ገዛዊ ጸጥታ አስከባሪ) በመባል የሚታወቀው የፀጥታ ክፍል
መሥሪያ ቤቱ ድረስ ተገኝቸ የመጥሪያ ወረቀት እንድወስድ በስልክ (በመናግር) ደውለው እያስታወቁኝ ነበር፡፡ አሁን
ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ነኝ ከ12 ሰዓት በፊት እንደማንገባ ከአሽከርካሪው ተነግሮኛል ይህም ማለት ከሥራ
ሰዓት ውጪ በመሆኑ ፌዴራል ፖሊስ ተገኝቸ መጥሪያውን ሳልወስድ ልቀር ነው ማለት ነው፡፡
እንደምታውቁት መጋቢት ወር ላይ 2006ዓ.ም. ላይ የአኖሌ የጥፋት ሐውልት በጥፋት ኃይሎች ተገንብቶ ሊመረቅ
አካባቢ ዕንቁ መጽሔት ላይ “የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሰቢያ ሐውልቶች የሠማዕታት ወይስ
የቅሱፋን?” በሚል ርእስ በዋናነት ስለዚህ የጥፋት ሐውልትና ተያይዞ ስላለው ስለወያኔ/ኦሕዴድና ኦነግ  የጥፋት
ኃይሎች ዕኩይ ሰይጣናዊ ዓላማ በሰፊው አትቸ ነበር፡፡ ያ ጽሑፉ ለዛሬው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ጅማሮ የሆነውን
የኦነግ ደጋፊ የሆኑትን የዩኒቨርሲቲ (የመካነ ትምህርት) ተማሪዎችን ቁጣ ቀሰቀሰና መጀመሪያ በጅማ ከዛ በሌሎቹ
ወያኔ ኦሮሚያ ሲል በሚጠራው የሀገራችን ክፍል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች (መካናተ ትምህርት) ዐመፅ ተቀሰቀሰና ንብረት
ወደመ፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ ለቀናት ተስተጓጎለ፣ ተማሪዎች ተቀጠቀጡ የተገደሉም አሉ፣ በርካቶች ታሰሩ፡፡
ጥያቄያቸው የነበረው እኔና ጽሑፉን ያስተናገደው የዕንቁ መጽሔት አርታኢ የነበረው ኤልያስ ገብሩ (ኤልያስ ትግሬ
እንዳይመስላቹህ ከኦሮሞና ጉራጌ የተገኘ ነው) “ለፍርድ ይቅረቡ!” የሚል ነበር፡፡ ብዙ ሳይቆይ የተረጋጋ
የመሰለው ዐመፅ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጨመረና የአዲስ አበባን የማስፋፊያ ዐቢይ አቅድ ወደ መቃወም
ተቀየረ፡፡

በተማሪዎቹ ጥያቄ መሠረትም ጽሑፉ ከተጻፈ ከወራት በኋላ ከሳሽ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ
“መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር” የሚል አንቀጽ ተጠቅሶብን ተከሰስን፡፡ በዋስ እስክንፈታ
ድረስም በተለያየ ጊዜ ማዕከላዊና ቅሊንጦ ታስረን ነበር፡፡ ይሄው ክሱ ሁለት ዓመታት አለፈው በከ20 በላይ
ቀጠሮዎች ፍርድ ቤት በመመላለስ ተንገላተናል፡፡ አብዛኛው ቀጠሮ የተቀጠረው ወኅኒ ቤቶቹ የመከላከያ ምስክሮቻችን
ጋዜጠኞችን እስክንድር ነጋን፣ ተመስገን ደሳለኝንና ውብሸት ታዬን ሊያቀርቧቸው ባለመቻላቸው ነው፡፡ በባለፈው
ቀጠሮ ባጋጠመኝ እክል ምክንያት አዲስ አበባ መምጣት ስላልቻልኩ አልቀረብኩም ነበረ፡፡ በዚህ ምክንያት ፍርድ ቤቱ
ፖሊስ (ፀጥታ አስከባሪ) አስሮ እንዲያቀርበኝ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በባለፈው ቀጠሮ ወኅኒ ቤቶቹ ምስክሮቻችንን አላቀረቡም ነበር፡፡ ምክንያት ሲጠየቁ እስክንድርን “መንገድ ላይ
ዐመፅ ያነሣሣብናል!” በሚል ሲሆን ተመስገንንና ውብሸትን ደግሞ “በመጓጓዣ ችግር” እንደሆነ ሲገልጹ
ምክንያቶቻቸው አሳማኝ እንዳልሆነ ተነግሯቸው ለነገው ታኅሣሥ 20 ቀጠሮ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ተብሏል፡፡
አሁን ላይ ተመስገንና ውብሸት በከባድ ሕመም ሆስፒታል መግባታቸው ተሰምቷልና ነገ አለመቅረባቸው እርግጥ ነው
ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ነገ በግላጭ ፍርድቤት ቀራቢ ነኝ፡፡ እና! ካላቹህ እናማ ምናልባት አልመለስ ይሆናል
ካልተመለስኩ ደኅና ቆዩ ወይም ደኅና ሁኑ ማለቴ ነዋ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com