ወደለውጥ የማያመራው የትግላችን ጉዞ መሰናክሎች!

ያልተቃኙ እዉነታወች!!

የመጨረሻ ክፍል

…………እነ ሌንጮ ባቲ/ለታም የዚሁ በሽታ ፈጣሪዎችና ተጠቂዎች ናቸው:: እነሱ ቅልጥፍ ያለች አማርኛ እያወሩ የኦሮሞ ወጣቶች እንዳይግባቡ አድርገዋል:: አንድ ምሳሌ ልጣል:-
ስለአንድ አብሮ አደግ ጎደኛየ ታሪክ ምሳሌየን ላቅርብና ልለፍ:: የልጅነት ጥሩ ወዳጄ የግርማ ጴጥሮስ ኦማጎ ታርክ ነው ( ለደህንነት ሲባል ስሙ ተቀይሯል) እሱ ወንድሙና እህቱ ከጎጃሜ አማራ እናት እና ከኦሮሞ አባት ተወለዱ:: እናት እና አባታቸው ኮሌጅ ውስጥ ተዋወቁ: አፍላ ፍቅር ስር ሰደደና ሶስት ጉልቻ አስቀለሰቸው:: በአካም እና ሰላም ተስማምተው ፍቅር ከማንነት ባሻገር ከሞት ወዲያ ተስፋ ያለው መሆኑን አምነው ሶስት ቆንጆ ልጆችን ወልደው መኖር ጀመሩ:: ከብዙ ዓመታት የጎጃም ኑሮ በሁጛላ ይህ ቤተሰብ የባልን እና የአባታቸውን ወገኖች ለማየት ወደ አባት የትውልድ ቀዬ ተጓዙ:: ችግሩ እንግዲህ እዚህ ጋር ነው:: እነዚህ ልጆች ከአጎት እና ከአክስትታቸው ልጆች ጋር በምን ቋንቋ ይግባቡ: ያ አይደለም አስገራሚው አማርኛ ብቻ ስለተናገሩ ነፍጠኛ ተብለው መነቀፋቸውና መገለላቸው ነበር ችግሩ:: እነዚህ ልጆች በፍቅር የተፈጠሩ የእናት እና አባቶቻው ውጤቶች ናቸው፤ ቋንቋ የማንነታቸው መገለጫ ሳይሆን ነገር ግን ቋንቋን እንደ ማንነት መገለጫ አድርገው ያቀነቀኑት የአባቶቼ ትውልድ የፖለቲካ ውጤት ጉዳቱን በዚህ ደረጃ ለማሳየት ነው::

በነገራችን ላይ የአባቶቸን ትውልድ ስወቅስ እውነታውን ከመግለጽ አንጻር ነው እንጅ ጭፍን ጥላቻ የለኝም:: የዚያም ትውልድ በርካታ አባቶችና እናቶች የምመካባቸው አሉኝ:: የተወሰኑትን ልጥቀስ:- እናቴ የዚያ ትውልድ መከራን ተቋዳሽ ነበረች: እነደ ማንኛውም የሃይስኩል ተማሪ እሮጣ ያመለጠች፥ የእህል ጎተራ ውስጥ የተደበቀች፥ ታስራ የተገረፈች፥ መከራዋን ያየች ሰው ናት:: ዛሬም ድረስ ስለወቅቱ ትውልድ እና ትግል ስታወራኝ የትላንት ታሪክ እስኪመስል ድረስ በልበ ኩራት ነው። የእምነቷንም ጽናት እረዳላታለሁ:: ሌሎችም ዛሬም ድረስ የሚቆጩኝ ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችባቸው በግሌ የማከብራቸው በርካታ ሰውች አሉኝ እነ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ፥ ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፥ ኮሎኔል መግግሱት የገደላቸው ጀነራሎች በሙሉ : አንዳርጋቸው ጽጌ፥ ላገራቸው የሰሩ ምሁራኖችና በተለይም የሃገሬ ገበሬ እጅግ የማከብረው እና የማደንቃቸው የሁሉጊዜም አርኣየወችና ጀግናዎች ናቸው::

በፍጹም በሁሉም አባቴ ትውልዶች ላይ አጠቃላይ ጥላቻ የለኝም:: ተወደደም ተጠላም እኔም የነሱ ውጤት ነኝ ። የዚያን ዘመን ወጣቶች ሆነዉ ለሃገራችን የዕብደትን ፖለቲካ እንዳመጡት ሁሉ ፥ ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ፥ አርበኝነት እንዲፀና ሌት ተቀን የሚደክሙም ዛሬም አሉን ከነዚህም ዉስጥ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ግብ-አበሮቻቸዉ ግንባር ቀደምት ናቸዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እኔ ስለአንድነት/መድረክ እከራከራለሁ

ባጠቃላይ ማለትም የፈለኩት የዚያን ዘመን ችገር እና የዚህ ዘመን ወጣት ችገር ለማሳየት መሞከርን ነው:: ዓላማየም የዚያ ትውልድ የፖለቲካ ተሳትፎ አሁን ላለንበት ችግር ካደረሰን – የዚህ ዘመን ወጣት ደግሞ ለመጭው ትውልዳችን ምን ሊያቆይ ይችላል የሚል ምልከታየን ማሳየት ነው:: እኔ ትውልድ ደግሞ እጅግ ተስፋ መቁረጥ የተስተዋለበት መሆኑን የሚታይበት ጊዜ ላይ በመድረሱ ስጋቴን ለማጋራት ነው::

ምንም እንኳን ችግሩ የመጣው ቀደም ብሎ ( የዘመናዊ ትምህርት መምጣትን ተከትሎ ቢሆንም) በቋንቋ መከፋፈል እና እጅግ ጠባብ የሆነ ብሄርተኝነት በዚህ ትውልድ ላይ በስፋት ነግሷል:: ኢትዮጵያዊነትን ወያኔ ከገደለው የበለጠ ትውልዱ በፈቃደኝነት እያጠፋው ነው:: የብሄርተኝነት ማንነት በቋንቋ መዳኘት ዘመናዊነት ሆኗል:: ንጹህ አማራ፥ ንጹህ ኦሮሞ፥ ንጹህ ትግሬ እና መሰል ነኝ ማለት እንደ ጀብድ እየተቆጠረ ነው:: ለታሪክ፥ ለሃገር ፥ ለድንበር፥ ለክብር፥ ለባንዲራ ግድ የማይሰጠው ወጣት ሃገራችንን አጣቦታል:: አስተዋይ ልቦናን የጠፋው: የሚያስብ ህሊና የተሳነው: ወያኔ በቀደደው ቦይ የሚፈስ ትልድ እንደጎርፍ እየፈሰሰ ነው:: ከአፍንጫው ማዶ አርቆ የማያይ ፈላስፋ መሰል ፖለቲከኛ ሃገራችንን ወሮታል:: ይህንን ነው ማሳየት የምሻው:: የኔን ትውልድ: እንደ ከብት እየተነዳ ያለው የዚህ ዘመን መካሪ-አልባ የሆነውን ወጣት ነው!! ያባቶቼን ትውልድ መውቀሴም ይህ ትውልድ ከታሪካዊ ስህተቶቻችን በግልጽ እንዲማር ከመፈልግ ነው:: ያልምክንያት ይህን ወጣት ብወቅሰው ዋጋ የለውም:: የችግሩንም ምንጭ እና ያስከተለውን አደጋ ማሳየቱ ተገቢ ነው የሚል ደፋር አመለካከትም ስላለኝ ነው ሃቅ የመሰለኝን የዘረገፍኩት::

የሃገራችንን ሁኔታ ስመለከት የዚህ ዘመን ‘አክቲቭስት” ጨለማን በጨለማ አሸንፋለሁ ብሎ የሚዳክር መከረኛ ትውልድ የበዛበት ነው:: ከቶ ጨለማን በጨለማ ማን ሊያሸንፍ ይቻለዋልን? ጨለማን በበርሃን እንጅ በጨለማ ማሸነፍ አይቻልም ያለው ማን ነበር? እውነት ነው:: ወያኔ በዘር ስለተደራጀ በዘር ተደራጅቼ ላሸንፍ ማለት ጨለማንት ነው:: ወደ የትም የማያደርስ ጎዳና ነው! በብሄር አለመደራጀታችን ሳይሆን ወያኔን ስልጣን ላይ ያቆየው ቅን ልቦና ስላጣን ነው:: እኔ ብቻ የሚለው ራስ ወዳድ እምነታችን ነው ወያኔን ያፈረጠመው:: አብረን አለመቆማችን ነው ባሪይ ያደረገን::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዘውደ ወይ ጎፈረ ብሎ መመዳደብም መፍትሄ ነው።

የዚህ ዘመን ትውልድ ካለፈው ታሪካዊ ውድቀታችን መማር አለበት:: የነጃዋር መሃመድ እና ጽንፈኛ ኦነጎች አቋም እና የቤተ አማራ ጠባብ ብሄርተኝነት የጨለማ ጉዞ ነዉ። ወደየትም የማያደርስ መንገድ ነው:: ሃገር በስሜት አይገነባም:: ፖለቲካና ሃገር የሰከን ምልከታን ይሻል: ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሃገር አርቆ ማሰብን ይፈልጋል:: ከአባቶቻችን ( እነ ዋልልኝ መኮንን) የወለዱት የስሜት ፖለቲካ ወንድማማቾችን ከማጋደል በስተቀር ምንም ያተረፈው ነገር የለም:: ስሜታዊ ትግል መጨረሻው ጸጸት ነው! ይህ ትውልድ ግንባር ቀደሞች ወኔ አልባ ናቸው የምለውም ለዚህ ነው:: በኔ እምነት ጃዋር እና መሰሎቹ በአንድ ጎራ የአማራ አክራሪወች በሌላ ጎራ ተሰልፈው የቁራ ጩኸት መጮሃቸው ፈሪነታችውን ያሳየኛል:: በራሱ የማይተማመን ትውልድ ራሱን ፍክክር (competition) ውስጥ ማስገባት አይሻም:: ያም ማለት ጃዋር ወይም የቤተ አማራ ሰወች እኔ ብቃት አለኝ፤ ኢትዮጵያን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ አውጥቼ ወደተሻለ ጎዳና እመራታለሁ፤ የነበርውን የደካማ አመለካከት ህዝቡን አንድ አድርጌ አስተካክላለሁ፤ እኔ ከእከሌ የተሻለ ችሎታ አለኝ እና ወያኔን እጥለዋለሁ ብለዉ ቢቆሙ ተከታያቸው ወደር ባልተገኘለት ነበር ግን ፈሪወች ናቸው:: በራሳቸው አይተማመኑም ስለዚህ ቋንቋ መሰረት ባደረገ የብሄር ፖለቲካ ማእበል ገብተው ይናጣሉ:: በኔ እምነት እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለውም የነ ጃዋር ቡድን (Oromo First) እና የ ቤተ-አማራ ቡድን (Amhara First) ሌሎቹም የብሄርተኝነትን አምላኪወች በጠበበ የዘረኝነት አመለካከት መደራጀታቸው መሰረቱ ይሄው ነው:: ፍራቻ! በራስ አለመታመን! ኢትዮጵያዊ ሆነንን ብንታገል ከኛ የተሻሉ ኢትዮጵያኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ የምንፈልገው ደረጃ አንደርስም ስለዚህ በጠባብ ብሄርተኝነት መሰለፍ ያዋጣናል ከሚል የደካማ እምነት ተነስተው ነው እየዋዠቁ የሚገኙት:: አንድ ነገር ስናጤን ግን:- የነዚህ ጠባብ ቡድኖች ልዩነታቸውን አጥብበው በኢትዮጵያዊነት ቢሰለፉ ምን ሊፈጥሩ እንደሚቻል መገመት አይከብድም:: ችግራቸው ግን በራሳቸው መተማመን የሚባል ነገር የላቸውም ያ ደግሞ ትርፉ ድካም ነው::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጎጃም ክልል ይመስረት - ከይገርማል

የብሄር ፖለቲካ ያውም በቋንቋ የሚዳኝ ማንነት ከባድ ነው! በዚህ አምኖ የፖለቲካ መሪ ነኝ የሚል የዚህ ዘመን ወጣት ራሱን ሊፈትሽ ግድ ይላል:: ምክንያቱም መጨረሻው ወይ ሞት አልያም ስደትና ጸጸት ነው:: እነዚህ ጽንፈኛ ብሄርተኞች በአጉል ፖለቲካ ህዝቡን ወዳላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ ከተው (እንደው ቢገባ ለማለት የተጠቀምኩት ነው) እርስ በርሱ ቢጫረስ የሚያገኙትን እርካታ ወይም ቁጭት ቀድሞ ማሰብ ሊኖርባቸው ግድ ይላል:: እረጅም እድሜ ባላት ሃገራችንን ውስጥ በርካታ የህዝብ ፍልሰት፥ የስራና የትምህርት ዝውውር፥ የንግድ ልውውጦችን፥ ጦርነትና እና የተፈጥሮ መዓቶችንን ተከትሎ ህዝባችንን ከቦታ ቦታ በሰፊዉ የተዘዋወረ በመሆኑ በርካታ ሰወች ተጋብተው በረካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ልጆች ተወልደዋል:: ሃቁ ይህ ነው!! ጎበዝ ኢትዮጵያዊ ካለ እስከ ቅድመ አያቱ ታሪክ ድረስ አመጣጡን ያውቃል:: ወይም በራሴ ጥናት ያጋጠመኝ እስከ 10 አያቶቹ የሚዘረዝር ሰው አግኝቻለሁ: ያም ማለት ከ 300 ዓመት በላይ ያልበለጠ ታሪክ ያለዉ ማለት ነው ታዲያ የብዙ ሽህ ዘመን ታሪክ ያላት ሃገራችን ላይ ተፈጥሮ ከየት እንደመጣ ማረጋገጫ የለውም::
መብሰሉ ላይቀር እንጨት ጨረሰ ይባላል:: ይች ድንቅ ሃገራችንን ብዙ የጋብቻ ትስስር፥ ሃይማኖታዊ፥ ባህላዊ፥ ማህበራዊና: በአርበኝነት አጥንት ተሳስራ የተገነባች ሃገራችን ማፍረስ የማይቻል ነገር ነው ስለዚህ የዘመኑ ወጣት ፖለቲክኞች ስሜታቸው ሳይሆን ነባራዊ እውነታውን በመከተል በአንድነት በመቆም እድል እየሰጣችሁት ያለውን አሰቃቂ የወያኔ ስርዓት ለማሶገድ በጋራ እንድትነሱ እመክራለሁ::
የአማራ ደም የኔ ነው! የኦሮሞ ደም የኔ ነው እያለ እየጮኽ ያለውን የተባበረ የህዝብ ድምጽ ረስታችሁ በራሳችሁ መንገድ መጓዙ የትም አያድርስም ጉዞው የጨለማ ነውና:: ጨለማን በጨለማ ሳይሆን በብርሃን ነው ማሸነፍ የሚቻለውና!
” ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ”

Darkness can not drive out darkness; only light can do that. Hate can not drive out by hate; love can do that.
Dr. Martin Luther king, Jr.
ቸር ይግጠመን
***የግርጌ ማስታወሻ:- በዚያም ሆነ በዚህ ዘመን በጥፋት ጉዞ ላይ ያልተሳተፉ ያገሬን ዜጎች ሁሌም የማከብራቸዉ ናቸዉ!!****
ንጉሴ ነኝ!

Share