እውነተኛ “አማራጭ ኃይል”

(ዮፍታሔ)

ከሚነገረውና ከሚጻፈው በላይ የማይነገረውና የማይጻፈው እየበለጠ ነው።

በተቃዋሚዎች መካከል በውጭም ሆነ በአገር ቤት፣ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ የሚካሄደው ሽኩቻና መገፋፋት በአረጋውያኑ እና በወጣቱ መካከል የሚካሄድ እየመሰለ ነው።

አረጋውያኑ ዘንድ ስም፣ ልምድና የውጭ ግንኙነት አለ። ወጣቶቹ ዘንድ አፍላ ኃይል፣ ቴክኖሎጂና የውስጥ ግንኙነት አለ።

በአገር ቤት ድንገት መሬት አንቀጥቅጥ እንቅስቃሴ ሲፈጠር አረጋውያኑ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ወጣቶቹ ግን እጅና ጓንት ሆነው ትግሉን እያርገበገቡት ነበር።

የአገር ቤቱ ተጋድሎ የደከሙበትን ሁሉ ውኃ የሚያስበላ ስለመሰላቸው አረጋውያኑ ደነገጡ። አንዳንዶች አረጋውያን ከድንጋጤያቸው ብዛት “አለንበት” ቢሉም ወጣቶቹ ደግሞ “ይህ የእኛና የሕዝቡ ሥራ እንጂ የላችሁበትም” ብለው ኩም አደረጓቸው።
አረጋውያኑ ሳይውሉ ሳያድሩ ለወጣቶች (እና ከጀርባቸው ላሉ የጎበዝ አለቆችና ቄሮዎች) ሌላ መልስ ነበራቸው። በአደራዳሪዎች (የውጭ ኃይሎች) ርዳታ ቶሎ ብሎ ወደ”ባለአደራ መንግሥት” ምሥረታ፣ ጎላ ብሎ ለመታየት ወደመተባበርና ወደ”ሽግግር መንግሥት ቻርተር” ማጽደቅ መሄድ። እንግዲህ ይህ የሚሆነው አንዳንዶቹ ምርጫ፣ ሌሎቹ ደግሞ “ሁለገብ ትግል” የሚሉትን ትተው መሆኑ ነው። ምን ያድርጉ! እጃቸው ላይ ያለውን ነው የተጠቀሙት።

የዚህን ጊዜ አንዳንድ ወጣቶች ለአረጋውያኑ “ቻርተሩ ውስጥ አስገቡን” አሏቸው። “ካልሆነ አገር እንበትናለን” ያሉም ነበሩ።
አረጋውያኑ ‘እነዚህ ልጆች ያደረጉትን ረሱት እንዴ?’ በሚል ዓይነት “ሃሳባችሁ ለአሁኑ አልተሳካም። ለወደፊቱ ተደራጅታችሁ ተመለሱ” ብለው እነሱም በተራቸው ኩም አደረጓቸው።

ከነዚህ ከሁለቱ የሕወሐት ልብ ለአረጋውያኑ ሊያደላ ይችላል። የመንግሥታቱም ልብ ከዚህ አይርቅም። ብዙ ትውውቅ አላቸው። አረጋውያኑ አስጊ ካለመሆናቸውም በላይ በባለአደራ መንግሥቱ በኩል የ “ምሕረት” እጃቸውን ዘርግተዋል። ይህ ለአረጋውያኑ ዕቅድ ስምረት ትልቅ ርዳታ ሊኖረው ይችላል። ሆኖም ሕወሐት የተሰጣትን “የወንድ በር” ትጠቀምበታለች ወይስ እስከወዲያኛው አትጠቀምበትም? የሚለው ጥያቄ ገና በይፋ መልስ አላገኘም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አገዛዙ ለሰላማዊ ሰልፉ ዕውቅና የሰጠው ፈጽሞ አማራጭ ስላልነበረው ነው - በእኔ አመለካከት!

ከሕዝቡና ከሚሊሽያው ሌላ የብአዴንና የኦሕዴድ ታችኛው አመራርና አባል ልቡ ከወጣቶቹ ጋር ነው። ሕወሐት ተገፍታ ከወደቀች ወጣቶቹ የበላይነት እንደሚኖራቸው መገመት ይቻላል።
አሁን ጥያቄው፡
1. የወጣቶቹ መልስ ምን ይሆናል? እነርሱስ እጃቸው ላይ ያለውን አውቀውታል? አውቀውስ ይጠቀሙበታል ወይስ አይጠቀሙበትም?
2. አረጋውያኑስ የጎደላቸውን ሞልተው፣ ያሰቡትን አደራዳሪ አግኝተው የተረጋጋ “ባለአደራ መንግሥት” ማቋቋሙ ይሳካላቸዋል ወይስ አይሳካላቸውም?
የሚለው ሆኗል።
ለወጣቶቹ “የሽግግር ቻርተር” ማጽደቅ ጉዳት ባይኖረውም ጥቅሙ ውስን ነው። ለወጣቶቹ ዋና ጉልበታቸው ተጋዳዩ ሕዝብ፣ የጎበዝ አለቆቹ፣ ቄሮዎቹና ደጋፊው ካድሬ ናቸው። ካወቁበት ሁሉ በደጃቸው ነው። ፍጥነት ቀኝ እጃቸው ነው።
ሆኖም ያስተዋሉ እንዲህ ይላሉ። ቢሳካ እንኳ የሁለቱም የተናጠል መንገድ አለው ሳንካ። አባጣ ይበዛዋል ጎርባጣ፤ አስተማማኝነቱና ዘላቂነቱ አይሆንም ብርቱ።
ስለዚህ አረጋውያኑ ከወጣቶቹ እንዲተማመኑ፣ አሁን ያላቸውን እንደያዙ ቢተባበሩ።
በአረጋውያኑ ወጣቶቹ ለአደራዳሪዎቹ፤ በወጣቶቹ አረጋውያኑ ለሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ ቅቡል ይሆናሉ። እውነተኛ “አማራጭ ኃይል”!
ያኔ አይደለም ሰላማዊ ሽግግር፣ የማይገሰስ የወገን ክብር፣ ሉዓላዊነቱ የታፈረ ድንበርና ዜጎች በፍቅርና በእኩልነት የሚኖሩባት አስተማማኝ አገር እውን ማድረግ ይቻላል።

Share