Sport: የተጨዋቾች ዝውውር ዋጋ ንረት ምክንያቱ ምን ይሆን?

የተጨዋቾች የዝውውር ሂሳብ እየናረ ከመጣ ከራርሟል፡፡ በእርግጥ ጭማሬ ማሳየቱ የማይቀር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ለዝውውር እየወጣ ያለው ሂሳብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ግን እንቆቅልሽ ነው፡፡ በክረምቱ የዝውውር ገበያ እስካሁን ለራዳሜል ፋልካኦ፤ ኤዲንሰን ካቫኒ፣ ኔይማር፣ ፈርናንዲንሆ፣ ማሪዮ ጎትዘ፣ ጀምስ ሮድሪጌዝ፣ አሲደር ኢላራሜንዲና ጎንዛሎ ሂጓይን ግዢዎች በአጠቃላይ 325 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቷል፡፡ በአማካይ ለአንድ ተጨዋች 40 ሚሊዮን ፓውንድ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ግዢዎች የተፈፀሙት የክረምቱ የዝውውር መስኮት ከተከፈተ ገና አጋማሽ ላይ እንኳ ሳይደርስ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሁሉም ተጨዋቾች አስደናቂዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ምርጡ ተጨዋች ከ30 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ እንዲሁም ኮከብ የሆነ ተጨዋች 50 ሚሊዮን ፓውንድና ከዚያ በላይ ሊከፈልለት ይገባል የሚል የተፃፈ ህግ የለም፡፡ ይህ ሂሳብ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ላይ የተጨዋቾቹ የደመወዝ መጠንም አልተካተተበትም፡፡
የታሪክ መዛግብትን መለስ ብሎ ለቃኘ የዝውውር ሂሳብ በምን ያህል ፍጥነት መጨመሩን ይመለከታል፡፡ ጂያንሎዊጂ ቤንቲኒ በ1992 በ12 ሚሊዮን ፓውንድ ሲዘዋወር የወቅቱን የሽያጭ ሪከርድ በመስበር የራሱ አድርጎት ነበር፡፡ የሌንቲኒ ዝውውር ከተፈፀመ ከ14 ዓመታት በኋላ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሪከርዱን 80 ሚሊዮን ፓውንድ አድርሶታል፡፡ በአጠቃላይ የዝውውር ሂሳብ ከፍተኛ ንረት ታይቷል፡፡ የዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ በተንኮታኮተበት ወቅት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ግን የበለጠ ያስገርማል፡፡

የዦን ማርክ ቦስማን ወይም በአጭሩ የቦስማን ህግ መጽደቁ የዝውውር ገጽታውን በአጠቃላይ ቀይሮታል፡፡ የቦስማን ህግ በዝውውር ጉዳይ የበለጠውን ኃይል ለተጨዋቾችና ወኪሎቻቸው አጎናፅፏል፡፡ የተሻለ ኮንትራትና ክፍያ ለማግኘት በሚያደርጉት ድርድር የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዙ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ አካሄድ የተጨዋች የዝውውር ሂሳብና ደመወዝ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ የዩሮ መገበያያ ገንዘብ በ1999 ስራ ላይ ከዋለ ወዲህ 54 ተጨዋቾች በ35 ሚሊዮን ዩሮ ወይም በላይ በሆነ ሂሳብ ተዘዋውረዋል፡፡ ይህ ቁጥር የክረምቱ የዝውውር መስኮት ከመዘጋቱ በፊት ሊያሻቅብ ይችላል፡፡ ቤል፣ ዌይን ሩኒ እና ሉዊስ ሱአሬዝ የመሳሰሉት ተጨዋቾች በከፍተኛ ሂሳብ ሊዘዋወሩ እንደሚችሉ መዘገብ ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: በትዳር መካከል ጸብ ሲነሳ እንዴት መፍታት ይቻላል?

ለተጨዋቾች ግዢ የሚወጣው ገንዘብ ለማሻቀቡ ምክንያት የቦስማን ህግ ብቻ አይደለም፡፡ እግርኳሱ እያገኘ ያለው ያልተቋረጠ የሚዲያ ሽፋን ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ከቴሌቪዥን ስርጭት የሚገኘው ዳጎስ ያለ የገንዘብ ስምምነት ለስፖርቱ የበለጠ አቅም ሰጥቶታል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች ለማስተላለፍ ስካይና ሲቲ የተሰኙት ድርጅቶች ለሶስት ዓመታት ኮንትራት 5.5 ቢሊዮን ፓውንድ ይከፍላሉ፡፡ ይህን መሰሉ ስምምነት ሌሎች ስፖንሰሮችም ይስባሉ፡፡ ክለቦች ከማሊያና ቁሳቁሶች ንግድ እንዲሁም ከስፖንሰሮች በሚሊዮን የሚገመት ገቢ ያገኛሉ፡፡ ይህ ግዙፍ የሆነ ገቢ ለዝውውር የበለጠ ገንዘብ እንዲያወጡ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡
በዘመናዊው እግር በስፋት የሚሳተፉትን የራሺያ ቢሊየነሮችም ይጠቀሳሉ፡፡ በእርግጥ በርካታ ክለቦች ቱጃር ባለሀብቶች የተያዙ ናቸው፡፡ በሮማን አብራሞቪች፣ ሼህ መንሱር አልናህያን እና የካታር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሚሊዮኖችን በክለቦች ላይ ማፍሰሳቸው ሌሎችም ወደ እግርኳሱ ተግተልትለው እንዲመጡ አድርጓል፡፡ የእነዚህ ባለሀብቶች ለዝውውር የሚጠየቀውን ሂሳብ መክፈላቸው ወይም ትንንሽ ክለቦች ከሽያጩ ጥሩ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ክለቦች ከሽያጩ ጥሩ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ውሳኔያቸውን ግትር በማድረግ ብዙ ተጨዋቾች በማይገባቸው ሂሳብ እንዲዘዋወሩ ያደርጋሉ፡፡

የክለቦች ዓለማ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ነው፡፡ እነዚህ ድሎች ደግሞ ጠቀም ያለ ሽልማት ያስገኛሉ፡፡ ደጋፊዎችና ተጨዋቾች ዋንጫዎችን ማንሳት ቢወዱም የክለብ ባለቤቶች ግን ብዙ ገንዘብ ያስገኝላቸዋል፡፡ ከዋንጫ አሸናፊነት የሚገነው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የክለቡ እውቅናም ይናኛል፡፡ አምና ባርን ሙኒክ የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ በመሆኑ 36 ሚሊዮን ዩሮ አግኝቷል፡፡ እነዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን ስንመለከት በእግርኳሱ ላይ ገንዘብ ወሳኝነቱ መላቁን እንረዳለን፡፡ ባየርን ከቻምፒየንስ ሊጉ ድል ያገኘውን ሂሳብ ብቻ ለጎትዘ ዝውውር አውሏል፡፡ ባቫሪያኑ ወጣቱን በስኳዱ ውስጥ ማካተታቸው በመጪው የውድድር ዘመን ለስኬት ያላቸውን እድል የበለጠ ያሰፋዋል፡፡ ዋንጫ በድጋሚ ካነሱ ደግሞ የበለጠ ገቢ ያገኛሉ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ 100 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያገኝ ክለብ ለተጨዋች ዝውውር 10 ሚሊዮን ፓውንድ ፓውንድ ከሚያወጣው ጋር ልዩነት የለውም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አምስት ወረዳዎች “ኦነግ ሸኔ” በሚል ስም የሚጠራዉ በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ኃይል ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ገለፁ

ከስፖርቱ ውጪ ያለውን ዓለም በአንፃራዊነት ስንመለከት ለአንድ ተጨዋች ዝውውር 40 ሚሊዮን ፓውንድና 250 ሺ ፓውንድ ሳምንታዊ ደመወዝ መክፈል ተገቢ አለመሆኑ ይታያል፡፡ ይህ ከፍተኛ ገንዘብ ድህነትን ማስወገድና አደጋዎችን መከላከልን በመሳሰሉት መስኮች ላይ ፈሰስ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ የበርካቶች ፍላጎት ነበር፡፡ ሆኖም በእግርኳሱ መጠኑ ከልክ ያለፈ ገንዘብ ይንሸራሸራል፡፡ ገደብ እስከሚበጅለት ድረስ ወጪው እየናረ መሄዱን አያቋርጥም፡፡ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የፋይናንስ ጨዋነት ደንብ ወጪው ገደብ እንዲኖረው ተብሎ የተቀረፀ ነበር፡፡

ክለቦች ስኬታማ ለመሆን የገዘፈ ወጪ ማውጣት አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ አዎ የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም በአብዛኞቹ ሀገራት ሊግ የበላይነት ያላቸው ጥቂት ቡድኖች ብቻ አልያም በቢሊዮኖች ታግዘው የሚመጡት መሆናቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሆኖም በአነስተኛ ሂሳብ ውጤታማ የሆኑ ውስን ቡድኖችም ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ለመመልከት የሚያስደስተው የዶርትሙንድ ቡድን አጠቃላይ ወጪ ግን ያነሰ ነው፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ላይ የተሰለፉት የዶርትሙንድ ቋሚ 11 ተጨዋቾች የተገዙበት ድምር ዋጋ ከ38 ሚሊዮን ፓውንድ ያነሰ ነበር፡፡ ከእነርሱም ውስጥ 15 ሚሊዮን ፓውንዱ የማርኮ ሩስ ግዢ መሆኑ ሲታሰብ ቁጥሩ የበለጠ ያንሳል፡፡ ይህ ወጪ ጎትዘን አለመካተቱ ልብ ይሏል፡፡ በጀርመን ሱፐር ካፕ ዶርትሙንድ የፔፕ ጋርዲዮላን ባየርን 4-2 ሲረታም የተጫዋቾቹ የተገዙበት ዋጋ ተመሳሳይ ነው፡፡

አርሰናልና ባርሴሎና በአነስተኛ ወጪ ስኬታማ በመሆን ሌሎቹ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የሰሜን ለንደኑ ቡድን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዋንጫ ማንሳት ባይችልም በመደበኛነት በሊጉ እስከ አራተኛ በመውጣትና በቻምፒየንስ ሊጉ ጥሎ ማለፉ ደረጃ መድረስ ችሏል፡፡ አርሰን ቬንገር ለዝውውር ከፍተኛ ሂሳብ አለማውጣታቸው የመድፈኞቹን ደጋፊዎች ባያስደስትም ያመጡት ስኬት ግን የሚደነቅ ነው፡፡ ባርሳ በቀደመው ጊዜ ለዝውውር ከፍተኛ ገንዘብ ቢያፈስም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ላስመዘገበው ስኬት መሰረቶች የላ ማሲያ ውጤቶች ናቸው፡፡ ቪክቶር ቫልዴዝ፣ ካርሎስ ፑዩል፣ ዤራርድ ፒኬ፣ ዣቪ ሄርናንዴዝ፣ አንድሬስ ኢኒዬሽታ፣ ሰርጂዮ ቡስኬትስ፣ ፔድሮ ሮድሪጌዝና ሊዮኔል ሜሲ የቡድኑ ምሰሶዎች ሲሆኑ ሁሉም የተመረቁት ከላ ማሲያ ነበር፡፡ ከዚሁ አካዳሚ ተገኝተው ለሌሎች ክለቦች በመጫወት ላይ የነበሩትን ሴስክ ፋብሪጋዝና ዮርዲ አልባን ወደ ቀድሞ ቤታቸው ለመመለስ ግን ከፍ ያለ ሂሳብ ተከፍሎባቸዋል፡፡
እነዚህ የተጠቀሱት ምሳሌዎች በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ጠቃሚነቱ ያሳየናል፡፡ የጀርመን እግርኳስ በወጣቶች እንዴት ስኬታማ እንደሚሆን አሳይቷል፡፡ ሀገሪቱ ለወጣት አካዳሚዎች ስርነቀል ለውጥ በማድረጓ አሁን ፍሬውን እያጨደች ትገኛለች፡፡ ስፔንም ብትሆን በየዓመቱ ወጣት ከዋክብት ማውጣቷን እንደቀጠለች ነው፡፡ ይህን ማሳካት ግን እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የታሪክ መዛግብት ሲፈተሹ ወልቃይት ማንነቱም ክብሩም አማራ ነው" መምህር ታየ ቦጋለ

በክለብ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ግን በሂደቱ እንደ መሰናክል ይታያል፡፡ ገንዘብ ለእግርኳሱ ኃይል በመጨመሩ አሰልጣኞች በወጣቶች ስብስብ ቡድን ለመገንባት በቂ ጊዜ አይሰጣቸውም፡፡ ደጋፊዎችና ባለቤቶችም ፈጣን ስኬት መመኘታቸው ሌላው የአሰልጣኞች ፈተና ነው፡፡ አሰልጣኞች ስራቸውን በፍጥነት ማጣታቸው ተለመደ ሆኗል፡፡ አዲስ የሚሾመው አሰልጣኝ ደግሞ የተለየ ፍልስፍና ይዞ ስለሚመጣ ቡድኑ ቀጣይነት እንዳይኖረው ይደረጋል፡፡ በዝውውርና ደመወዝ ላይ ብዙ ገንዘብ የሚፈስ በመሆኑ በርካቶች ቅሬታቸውን ያሰማሉ፡፡ ሌሎች በአንፃሩ ለዝውውር የተመደበው ሂሳብ ወጪ ባለመደረጉ ያማርራሉ፡፡

Share