ማን.ሲቲ Vs ቼልሲ (ቬንገር ይብቃቸው?)

ካታላኖችና ማድሪስታኖች በባላንጣነታቸው የሚታወቁ ክለቦች ናቸው፡፡ ባርሴሎና ካታላንን ሪያል ማድሪድ ደግሞ ማድሪስታን የሚባሉ ደጋፊዎቹንና ገዢው ፓርቲን ይወክላል፡፡ በሁለቱ የኤልክላሲኮ ግጥሚያ ካታላኖቹ ያላቸውን ተቃውሞ ለማሰማት ጨዋታው በተጀመረ በ8ኛ ደቂቃ ላይ ጩኸት ካሰሙ ከ10 ወራት በኋላ ከወደ እንግሊዝ ተመሳሳይ ዜና ተሰምቷል፡፡ የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ያለ ዋንጫ የቆየባቸው ዓመታትን ተመርኩዘው ደጋፊዎቹ ‹‹ቬንገርን አንፈልግም›› የሚል ጩኸት ሲያሰሙ ቢከርሙም ዛሬ አስቶንቪላን 2ለ1 አሸንፏል።፡ ቬንገርና አርሰናል ዋንጫ ካጡ ዛሬ 8 ዓመት ከ8 ወር ከ3 ቀን ሞልቷቸዋል።

ሳይሸነፍ ዋንጫ የወሰደው ቡድን ፈጣሪ፣ በእንግሊዝ እግርኳስ ላይ አዲስ አብዮት ከሳች፣ አርሰናልን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረጉ መሪ፣ ከረጅም ዓመታት በኋላ ለፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አርሰናልን ያበቁ ባለውለታ፣ የበርካታ ኮከቦች ማደሪያና መገኚያ፣ የኢምሬትስ ስታዲየም ጠንሳሽ፣ የክለቡን የአመጋገብ ስርዓት ቀያሪ… የተሰኙት አርሴን ቬንገር ‹‹we trust in Arsene (በቬንገር እናምናለን)›› የተሰኙበት ታሪክ ያበቃ ይመስላል፡፡ ይተማመኑባቸው የነበሩት ደጋፊዎች፣ ከጎናቸው የነበሩት የቅርብ ሰዎች ሳይቀሩ ቬንገር ላይ ፊታቸውን እያዞሩ ለመሆኑ እየታየ ያለ ሀቅ ነው፡፡ ቬንገርና ዋንጫ ከተነፋፈቁ በቃ ምን ያደርጉናል የሚሉ የክለቡ ደጋፊዎች ቬንገርና ዋና ስራ አስኪያጁ ኢቫን ጋዚዳስን ለመቃወም ያዘጋጁት የተቃውሞ ጥሪ መስመር የያዘላቸው ይመስላል፡፡

በኢምሬትስ በኤፍ.ኤ.ካፕ ከታችኛው ዲቪዚዮን ክለብ ብላክበርን ጋር ያደረጉት ጨዋታ በ1ለ0 ሽንፈት ሲጠናቀቅ ደጋፊዎቹ ጋብ ያለውን ተቃውሞ አጠናክረው ገፍተዋል፡ ፡ ባለፉት 8 ዓመታት አርሰናል ቤት የድል ፍላጎት የለም በሚል ወደ ተለያዩ ክለቦች ስደት የመረጡ 26 ተጨዋቾ 72 ዋንጫ በአጠቃላይ ሲወስዱ አርሰናሎች ጋር ግን ጠብ አለማለቱ ደጋፊዎቹን አበሳጭቷል፡፡ ከፓትሪክ ቪየራ እስከ ሴስክ ፋብሪጋዝ፣ ከአሌክሳንደር ሀሌብ እስከ ማቲው ፍላሚኒ፣ ከሳሚር ናስሪ እስከ ጋኤል ክሊቺ ድረስ በአርሰናል ቤት ያጡትን ዋንጫ በስደት አግኝተውታል፡ ፡ በኢምሬትስ ስታዲየም ወጪ የተነሳ በዝውውር መስኮት መካፈል አልቻልንም በሚል በክለቡ የቦርድ አባላት የሚቀርበው ሰበብ ደጋፊዎቹን አላሳመነም፡፡ ከሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ለተተኪዎች አለመዋሉ፣ የቡድኑ ድክመትና ሽንፈት እየታየ ቡድኔን የሚመጥን ተጨዋች ካልተገኘ አልገዛም የሚለው የቬንገር ጉራ ቀመስ አስተያየት፣ ከምንም በላይ ኮከቦችን አሳምኖ ለማቆየት አለመቻልን መድፈኞቹን የበታች አድርጓቸዋል፡፡ ይህን መቀበል ያልቻሉ ደጋፊዎቹ ታዲያ ቬንገርን በቃህ እያሉ ነው፡፡ ከሰሞኑ የታየው የደጋፊዎቹ ተቃውሞ ጠንከር ያለ ሆኗል፡፡ “we trust in arsene” ሲሉ የነበሩ የመድፈኞቹ ደጋፊዎች አሁን ደግሞ ‹‹Arsene thanks for the memories but its time to say good bye›› የሚል ባነር ይዘው በመውጣት 7.5 ሚሊዮን ፓውንድ ዓመታዊ ደመወዝ የሚከፈላቸው የቬንገርን ስንብት እየተመኙ ነው፡፡ ይህን የሰሙት ቬንገር ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት በሰጡት መግለጫ ተቃውሞው ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአርሰናል ደስተኛ ነኝ፡፡ ከዚህ ክለብ ጋር ያለኝ ፍቅር የሚበርድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ለደጋፊዎቹ የምለው ነገር ቢኖር 16 ዓመታት በአርሰናል አሰልጣኝነት እንደቆየ ሰው ትንሽም ክብር ሊሰጠኝ ይገባል፡፡ በእናንተና በጋዜጠኞች ግን ይህን ክብር አላየሁም፡፡ ይሄ አሳዛኝ ሆኖብኛል፡፡ ለዚህ ክለብ ብዬ ያገኘኋቸውን ምርጥ የአሰልጣኝነት እድል ገፍቻለሁ፡፡ የትኞቹ እድሎችን እንደተውኳቸው ሌላ ጊዜ እናገራለሁ፡፡ እናም ልትታገሱኝ ይገባል፡፡ ከክለቡ ከወጣሁ በኋላ ግን አልመለስም፡፡ ያን ታዲያ እናፍቃችኋለሁ፡ ፡ ለዚህ ክለብ የማስፈልገው ትክክለኛ ባለሙያ እኔ ነኝ›› ሲሉ መረር ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በእርግጥ የፈረንሳይና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድኖች፣ ሪያል ማድሪድና ኤሲሚላንን ጨምሮ አሰልጥንልን ተብለው ለአርሰናል ባላቸው ፍቅር ጥያቄውን ያለመቀበላቸው ታሪክ እግርኳስ ውለታ የማያውቅ ሆነና በቃህ የሚባሉበት ዘመን መድረሱ አሳዝኗቸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የቬንገር ቡድን ከሻምፒየንስ ሊግ ውድድር አለመሰናበቱ በርካቶች እንደስኬት የሚያልሙት ቢሆንም አርሰናል ቤት ግን የሚወደድ አልሆነም፡፡ ቬንገር ላይ የሚሰማው ተቃውሞ ወደ ቦርዱም ከፍ ብሏል፡፡ የክለቡ 2ኛ ባለአክሲዮን ኦሊቨር ኡስማኖቭ ‹‹የክለቡ ቦርድ ለአርሰናል የሚያስብ አልመሰለኝም፡፡ ቬንገር ከዚህ በላይ ምንም ሊያደርጉ አይገባም›› ሲሉ ቦርዱን ተንኮስ አድርገዋል፡፡ ኡስማኖቭ ቬንገር ዴቪድ ዴንን የመሰሉ አጋር ካጡ ወዲህ አርሰናልን በድል ጎዳና ማስቀጠል አለመቻላቸው የቦርዱ ችግር መሆኑን ያምናሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦሮሚያ ልዩ ዞኖችን በሚያጠቃልለው ማስተር ፕላን ላይ መግባባት አልተቻለም

‹‹አሜሪካዊው የክለቡ የከፍተኛ አክሲዮን ባለቤት ስታን ክሮንኬ ለአርሰናል እያሰቡና ጊዜ እየሰጡ አይደለም›› የሚል የደጋፊዎች ድረገፅ ‹‹ፀረ ክሮንኬና የአርሰናል ቦርድ አቋም እያራገበ መሆኑ የደጋፊዎችን ድጋፍ እያስገኘለት ይገኛል፡ ፡ ‹‹በፒተር ሂልውድ የሚመራው አሮጌው ቦርድ አዲስ ሀሳብ የሚያፈልቁ ወጣት የቦርድ አባላት ያስፈልጉታል›› የሚለው የኡስማኖቭም አስተያየት ድጋፍ እያገኘ ነው፡፡ አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሊግ ካፕ በብራድፎርድ በኤፍኤካፑ ደግሞ በብላክበርን መሸነፉና በፕሪሚየር ሊጉ በመሪው በማን.ዩናይትድ 11 ጨዋታ እየቀረ በ21 ነጥብ መበለጡ ከሶስቱ ዋንጫዎች ውጭ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በሻምፒየንስ ሊጉ ደግሞ በባየር ሙኒክ 3ለ1 መሸነፉ የክለቡን ጉዞ አስፈሪ አድርጎታል፡፡ በጨዋታው ምርጥ እንቅስቃሴ ያደረገው ጃክ ዊልሼር ሁሉም ቬንገር ከመናገር ሊቆጠብ ይገባል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ‹‹በኤፍ.ኤ ካፑ በብላክበርን መሸነፋችን በሻምፒየንስ ሊጉ በባየር ሙኒክ መረታታችን የእኛ ችግር እንጂ የቬንገር አለመሆኑን ልታውቁ ይገባል›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡ ፡ ዊልሼር ይህን ቢልም የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞዎቹ ኮከቦች አለን ሺርር እና ኢያን ራይት ግን ቬንገር ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል፡፡ ሺረር ‹‹ቬንገር ባለፉት 8 ዓመታት ላስመዘገቡት አሳፋሪ ውጤት ሊያፍሩ ይገባል›› ሲል ራይት በበኩሉ ‹‹የቬንገር ዘመን አብቅቷል፡፡ ለሌላ ባለሙያ ቦታውን ሊለቁ ይገባል›› በማለት ጠንካራ ትችቱን ሰንዝሯል፡ ፡ ቬንገር በሻምፒየንስ ሊግ ለ82ኛ ጊዜ ድል ለማድረግ የነበራቸው ፍላጎት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ባርሴሎናዎች የአርሰናልን ጭንቀት የሚያባብስ መረጃ የሰጡትም ሰሞኑን ነው፡፡ ካታሎናውያኑ የአርሰናልን ልብ የሆነውን ጃክዊልሼር እና ተከላካዩን ቶማስ ቬርማለንን ለማስፈረም እንደሚፈልጉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ቬንገርና ዊልሼር ‹‹የማይሆን ድርጊት›› በማለት ወዲያውኑ ውድቅ ቢያደርጉትም የቬርማለን ዝምታ ግን በመድፈኞቹ ቤት ሌላ ሀሳብ ጭሯል፡፡ ያም ሆኖ በአራቱም ዓመታዊ የዋንጫ ጉዞዎች ላይ ስኬታማ ባለመሆን የተሰባሰቡበት መርከብ እየሰመጠ እንደሆነ እየተሰማቸው ያሉት መድፈኞቹ መፃኢ እድል አጓጊ ሆኗል፡፡ (ምንጭ ኢትዮቻነል ጋዜጣ ቢሆንም አንዳንድ ውጤቶችን መስተካከል አድርገንበታል)

ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: ጌታነህ የዓለም ዋንጫውን እየናፈቀ ነው

ዛሬ እሁድ የሚደረገው የቢሊየነሮቹ ፍልሚያ የማን. ሲቲ እና የቸልሲ አሸናፊ ማን ይሆን? ግምትዎን ያሳውቁን።

Share