(ዘ-ሐበሻ) በብዙዎች ዘንድ 6ኛው ፓትርያርክ እንደሚሆኑ ሲገለጽላቸው የነበሩት፣ በድምጽም አሸንፈው የነበሩትና ራሳቸውም “መንግስት እኔን ፓትርያርክ አድርጎ መሾም ይፈልጋል” በሚል ሲናገሩ የቆዩት አቡነ ሳሙኤል ባለቀ ሰዓት ከእጩ ፓትርያርኮች ውጭ ሊሆኑበት የቻለው ምክንያት ከአቡነ ጳውሎስ ደጋፊ ከሆኑትና አሁን አቡነ ማቲያስን ማሾም የሚፈልጉት እነ ንቡረ እድ ኤልያስ እና ወ/ሮ እጅጋየሁ ግሩፕ በአሸናፊነት በመውጣቱና ለመንግስት “አክራሪ ናቸው” የሚል ጥቆማ በማቅረባቸው እንደሆነ ተዘገበ።
እንደ ሃራ ተዋህዶ ዘገባ አካሄዱን ተቃውመዋል የተባሉትን የአስመራጭ ኮሚቴውን አባላት በተናጠል በማስፈራራትና ተስማምተው እንዲፈርሙ በማድረግ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከዕጩነት ዝርዝር እንዲወጡ የተደረገበት ዋነኛው ምክንያት ‹‹በሃይማኖት አክራሪነት ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የበላይነት ብቻ ነው የሚሠሩት›› የሚለው የተዛባ አመለካከት፣ ቂምና ጥላቻ የወለደው ክሥ ነው፡፡ የመንግሥትን የደኅንነት መዋቅር የሚታከከው ይኸው “የጨለማው ቡድን” የሚል ስያሜ የተሰጠው አካል ይህን ክሡን ያጠናከረው ብፁዕነታቸው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት በጅማና በኢሉ አባ ቦራ በጽንፈኞች የተፈጸመውን አሠቃቂ ሽብር በሀ/ስብከቱ ጋዜጣ – ኆኅተ ጥበብ – እንዲዘገብ አድርገዋል፤ በሃይማኖት መቻቻልና በእስላማዊ አክራሪነት ዙሪያ ያሳተሟቸውን መጻሕፍት በመጥቀስ ነው ሲል ሐራ ዘግቧል።
“የጨለማውን ቡድን” እኒህን ክሦቹን በማጠናከር፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከዕጩዎች ዝርዝር ተካተው በፓትርያሪክነት ለመመረጥ ከበቁ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል እንዳይኖር ያደርጋሉ›› የሚል ለመንግሥት የሚስብ መስሎ የሚታይ፣ በሐቀኛ ገጹ ግን አንድም÷ የአድርብዬ ጠባይ የተጠናወተው፣ አንድም በቡድኑ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ድጋፍ የሚሰጡ ሕገ ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች መሠሪ ተንኰል በተገፋ አቋሙ ለጊዜውም ቢኾን ያሰበው የተሰካለት መስሎ ታይቷል፡፡ ያለው ድረ ገጹ “ታድያ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ቡድን ነፍስ ዘርቶ ሊጠናከርበት ያደባበት የምርጫ ሂደትና የምርጫ ውጤት አካል አንኾንም፤ አናደምቅም ቢሉ ቅር ያሰኛልን? የብዙዎች ጥያቄ ነው” ሲል ዘገባውን አጠናቋል።
በነገራችን ላይ ሐበሻ ድረ ገጽ ኦክቶበር 11 ቀን 2012 ዓ/ም መንግስት በፓትርያርክነት ለማስቀመጥ ከሚፈልጋቸው መካከል አቡነ ማቲያስ አንዱ መሆናቸውን ዘግባ ነበር። (ይህን ዘገባ ለግንዛቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)