አመት በአል ሲቃረብ ብዙ ነገር ይናፍቀኛል| በእውቀቱ ስዩም

አመት በአል ሲቃረብ ብዙ ነገር ይናፍቀኛል፡፡ ከሁሉም በላይ፤ እንደ አፍላ ጉም የሚሳብ የሉባንጃ እጣን – ብረት ምጣድ ላይ የሚጤስ ቡና -የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን -ብዙ ፍቅር- ብዙ ፈገግታ ውልውል ይለኛል፡፡ ከመከረኛ ህይወታችን ማህል ብልጭ ብሎ የሚጠፋ አመት በአል የተባለ አብሪ ኮከብ ለዘላለም ይኑር!

አመት በአል ቀን ዋናው የደስታና የክብር ምንጭ መብላትና መጠጣት ነው፡፡

ግማሽ ፈረስ ግማሽ መልአክ የሆነው ሰው የተባለው ፍጡር እስኪረካ ድረስ መጠጣት፤ እስኪጠግብ ድረስ መብላት ይፈልጋል፡፡ ግን ምንዋጋ አለው? ባለማችን፤ ይልቁንም በአገራች እንደልብ የሚገኝ ነገር ቢኖር የምግብ እጥረት ነው ፡፡ ብዙ የሚበላ ሰው የሌላውን ድርሻ እንደወሰደ ስለሚቆጠር በማኅበረብ ዘንድ የተጠላ ነው ፡፡ የተፈጥሮን ጥያቄ ባግባቡ በመመለሱ  ሆዳም አጋሰስ እየተባለ ይብጠለጠላል ፡፡ በተቃራኒው ከምግብ የሚቆጠቡ ሰዎች ይወደሳሉ ፡፡ ጾመኞች ይቀደሳሉ፡፡

የተከበረ ዜጋ በጎረቤቱ ድግስ ላይ በተጋበዘ ቁጥር እንደ የሰውነቱን ፍላጎት በማርካትና የማኅበረሰቡን የክብር መመዘኛ በማሟላት መሀል ይወጠራል፡፡ ይህንን ውጥረት የሚያረግበው ማግደርደር የተባለው፤ በመጥፋት ላይ ያለ ባህል ነው፡፡ ጋባዥ እንግዳውን አፈር ስሆንልዎ በጊዮርጊስ ”እያለ ይለማመጠዋል ፡፡ ጋሽ እንግዳ“ በቃኝ!”ኧረ በቃኝ ያለ ትንሽ ሲታገል ይቆይና ይረታል፡፡ የምበላው እርስዎ አፈር እንዳይሆኑብኝ ብየ ነው የሚል ገጽታ ተላብሶ ምግቡ ላይ ይወርድበታል፡፡ ይህ ማኅበራዊ ተውኔት ሰዎች ኩራታቸውንም ራታቸውንም እንዳያጡ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የሆነ ጊዜ ላይ አንዱ ከገጠር ወደ ከተማ ይመጣና ከተሜ ዘመዶቹ ቤት ያንዲት ሌሊት ጥገኝነት ጠየቀ ፡፡ ማታ ዘመዶቹ አጋም የመሰለ ዶሮ አቅርበውለት እንዲበላ ጋበዙት፡፡ ሰውየው ለወግ ያህል “ ፤ አሁን በልቸ ነው የመጣሁ፤ ማርም አልስ ”ካለ በኋላ አጥብቀው እስኪያስግደረድሩት ድረስ መጠባበቅ ጀመረ:) ጋባዦች ግን በልቶ ከመጣ አናስገድደውም ብለው የራሳቸውን እየተጎራረሱ ሞሰቡን ወደ ምድረበዳነት ከቀየሩት በኋላ አነሡት፡፡ ሰውየው ባዶ ሆዱን እሪታ በሳይለንሰር አፍኖ ሲገላበጥ አድሮ ሲነጋጋ ሎንቺና ተሳፍሮ ወደ ገጠር ተመለሰ፡፡ እግሩ ገና የቤቱን ደጃፍ እንደረገጠ ሚስቱን“ አቺ! እንጀራ በጨው አምጭልኝማ ” አላት፡፡ ሚስቱ“ ዋ! በሄዱበት አገር አልበሉም እንዴ !”
ባል – “ኧሯ!አቦና ማርያም የሌሉበት አገር ህጀ ጦሜን ተደፍቸ አደርኩ እንጂ!”

ከተሜ ዘመዶቹ፤ “ ባቦ፤ በማርያም” እያሉ ለማግደርደር አለመሞከራቸው ገርሞት ነው፡፡

ባገር ቤት ጨዋታ ውስጥ ዋና ገጸባሕርይው የቆሎ ተማሪ ነው፡፡ ያገር ቤት የቆሎ ተማሪ የዶንኪሆቴ የማኪያቬሊና የካሳኖቫ ቅልቅል ነው፡፡ ገድለኝነትን ብልጣብልጥነትንና ሴትአውልነትን አስተባብሮ ይዟል ፡፡ ባንድ አመት በአል ስላውዳመቱ ብሎ ሲለምን የቤቱ አባዋራ ገብቶ እንዲጋበዝ ፈቀደለት፡፡ ራት ቀረበ፡፡ ተሜ በልቶ እንደመጥገብ ሲል ሚስትዮዋን ለማጉረስ ይንጠራራ ጀመር፡፡ አባዋራው “ተሜ አርፈህ የራስህን ብላ ፤ ሚሽቴን የማጉረስ የኔ ፋንታ ነው” ብሎ ገሰጸው፡፡ ተሜ ግን“ግዴሎትም ጌታው ላግዝዎት ብየ ነው”እያለ በባልየው ፊት በኩል አመዳም እጁን እያሳለፈ ሚስትዮዋን ማጉረስ ቀጠለ፡፡ ጉዳዩ ትንሽ እየተካረረ መጣና አባዋራውና ተሜ ትግል ተያያዙ፡፡ሚስትዮዋም በመገላገል ፋንታ ሞሰቧን አንስታ ቡናዋን እያፈላች ትግሉን በጥሞና መከታተል ጀመረች፡፡ አባዋራና ተሜ ለረጅም ጊዜ ሲታገሉ ከቆዩ በኋላ ጉልበት ወደ ተሜ እያደላ የባል መገጣጠምያ እየላላ መጣ፡፡ አባዋራው ለማሸነፍ መጣሩን ትቶ ፤ እሱንም አካባቢውንም ሳይጎዳ የሚወድቅበትን ስትራቴጂ መንደፍ ጀመረ፡፡ በተሜ ብብት መሀል ሆኖ፤ ባጭር ባጭሩ እየተነፈሰ ሚስቱን ቁልቁል እያየ “ንሽማ እቃውን አነሳሽው” አላት፡፡

ሚስት ምድጃውን እያራገበች “ሊወድቁ እንዳይሆን?”ስትል ፡፡
“አይ ነብራሬ እና አንቺ ባመጣሽው እዳ ተገትሬ ልደር?

አመት በአሉ ከገላጋይ ኣልባ ጠብ የጸዳ ይሁንልዎት!!

4 Comments

 1. የአመት በአል ቀን ዋናው የደስታና የክብር ምንጭ መብላትና መጠጣት ነው??

  ለዚህ ነዋ ከሚበላው ይልቅ የሚደፋው በሚበልጥበት አለም የሚኖር አበሻ አመት ባህልን የሚናፍቀው?? ለመብላት ነው ማለት ነው አመት ባህል በመጣ ቁጥር ምግብ ከሞላበት ቤቱ እየወጣ በርካታ ማይሎችን እያቆረጠ ወደ ዘመድ አዝማዱ የሚተመው??

  አመት ባህል ዛሬ ሀገራችን በወደቀችበትና ሕዝባችን በተራበበት ዘመን የተፈጠረ ነገር አይደለም። ከብት እና በግ ቆዳ መልስ በነበረበት ዘመን አመት ባህል ነበረ። ኢትዮጽያ ለሌሎች ሀገራት ሳይቀር እርዳታ ባደረገችበት ሰሀት አመት ባህል ነበረ።ብሉልኝ ጠጡልኝ የሚለው ባህላችን ሕዝባችን እንግዳን እንደ ንጉስ በሚያየው የቀድሞው ባህላችን ላይ የተመሰረተ እንጅ የለበጣ ማግደርደርም አይደለምም አልነበረምም። መንገደኛን እኔ ቤት እኔ ቤት እያለ ተሻምቶ፣ እግሩን አጥቦ፣ ለሳምንታት የሚሆነውን ስንቁን ቆጥሮ የሚሸኑ አባቶቻችን ቅሪት ባህል እንጂ በዚህ መልኩ የሚተነተን ባህላችን አልነበረም።

  ለነገሩ አመት ባህል ለ ኢ-አማናዊ (ፖጋን) ትርጉሙ ምንድን ነው?? ።ለማንኛውም አመት ባህል ሁሌም የምትዘልፈው (በዚህም ፅሁፍህ ላይ የቆሎ ተማሪን በሳልክበት መልኩ) የምዘባበትበት የክርስትናችን ገፀ በረከታችን ነው።

  መልካም ፋሲካ ለክርስትና እምነት ተከታዮች!!!

 2. ኣመት በኣል ለማያምን ስው ሆዱ ነው ትዝ የሚለው ላንተም ከሄድክበት ውጭ ትርጉም የለህም በዛም አለ በዛ የቆሎ ተማሪውን ለመንቀፍ ነው አነሣስህ የኦርቶዶክስ ጠላት ነህና

 3. I pray for Bewketu as he is going to be a victim of a smear campaign of Evil Tigres and sick OLF historians and propagandists as he destroyed their false and fabricated hate propaganda they were spreading against Menilik and Amharas.
  Bewketu destroyed the hate propaganda and history of these stupid groups in one single book and they will not rest till they silence him from speaking and writing the truth.

  I hope Hodam and coward Amhara elites and Good for nothing Amhara Historians and professors would follow Bewketu example and write books to counter the hate and fabricated propaganda being preached against Amharas and Menilik.
  The silence of Amhara elites from writing the truth helped and enabled OLF , Shabia and Tigrian historians to tarnish Amharas as colonizers and beneficiaries of the previous regimes while the truth is otherwise

  The new generation of Amhara people is clueless and don’t know how to defend themselves from the accusations coming from Tigrians and OLFites as colonizers as Hodam Amhara Historians lacks the courage the truth about Amhara people and the sufferings Amharas they went through a case in point Is the Wollo Famine and the bombardment of Gojjam peasants by Derg and the Haile Sillase regime and the massacre of Gojjam and Gonder and Wollo people by Yohannis

Comments are closed.

Previous Story

ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳና ሳዲቅ አህመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ | በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ቁጣ ብሔራዊ መልክ አለመያዙ ምክንያቱ ምንድነው? – ያዳምጡት

Next Story

Hiber Radio: በኢትዮጵያ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ በዓል ብዙሃኑን ሕዝብ የሚያሳቅቅ መሆኑ ተገለጸ፣ ኢትዮጵያ ሰራዊቷን በ/ደ/ሱዳን ግዛት ውስጥ እንዳታስገባ የአገሪው ማህበረሰብ ተወካዮች አጥብቀው አስጠነቀቁ፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ገዚዎች ዛሬም ቀንደኛ የነጻ ፕሬስ ጠላቶች ተብለው ተፈርጀዋል ሌሎችም

Go toTop