ኣንድ ግደይ ገብረኪዳን የተባለ የሴራ ታሪክ ተንታኝ ወጣት፤ ብዙ ጽፎ ጽፎ ደከመውና “የሰይጣን ማሕበርተኞቹ ‹‹እኛ ሰይጣንን እናመልካለን፣ በደስታም ወደ እሳቱ እየዘለልን እንገባለን›› ሲሉ እኛ “ሃይማኖተኞቹ” ግን እየወረብን፣ እያሸበሸብን እየዘመርን ወደ ገሃነም መሄዳችን ነው ልዩነቱ ሲል የገለጸበት መንገድ አስታውሳለሁ…!
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነገሮች በሙሉ ግልጽ እየሆኑ የመጡ መሆናቸውን እየተረዳን ነው፡፡ ይሕም ሲባል ሥለ ፍትህ፣ ሕጋዊነት እና የአራዊቶች መስመርን ለመከታተል እናም ለመግታት የሰውአዊ መተዳደሪያ ደንቦች/ሕገ-ኀልዮት/ ይስፈን እያልን ለዘመናት ተሟገትን…፡፡
ትላንት ስለ ፖለቲካ እና ስለ ማሕበረሰባዊ ኢፍትሃዊነት ጆሮ ዳባ ይሉ የነበሩ ዜጎች ፤ አሁን ላይ አፎቶቻቸው ከማንም በላይ የሠለ/ሉ “ፖለቲካዊ ኂሰኞች” ሲሆኑ እያየን ነው፤ ፖለቲካ እና ስለ አገር መቆርቆር ማለት ዘረኛ መሆን እስኪመስላቸው ድረስ፤ አሁን ስለ አገሬ እቆረቆራሉ በሚል ስሜት የዘረኛነትን የዘመን መንፈስ እንደ ድግምት ተቀብለውታል፡፡
/ድግምት በፈቃድ የሆነበት ዘመን/
ጽጌ ሽሮ የሚባል ዝነኛ ቤት ከተከፈተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡ ትግራይ በሽራሮ ብቻም ሳይሆን በሽሮ ጥበብ እንደምትታወቅ ፤ በኢትዮጵያ በታሪክ መስመር ውስጥ መሠረት የጣለች መሆኗን እያስገነዘበች፤ ያስመሰከረች ሴት/ቤት ናት፤ እንደውም ከአንድም 6 ቅርንጫፎችን ከፍታ ከመካከለኛ ደረጃ በላይ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እያበላች ነው፡፡ ልብ በሉ ዜጎች ነው ያለኩት!
ታድያ በገላጣው ኢፍትሃዊነትን የሚመለከት ሰው አሁን አሁን በቀላሉ ስስ የአስተሳሰቡ ብልት እየተነካ ዘረኛ የሆነውን የፖለቲካ ኂሱን ሲሰጥ የሚውል ሰው አጋጥሞን ይሆናል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
ጽጌ ሽሮም ሆነ አዝመራ ሽሮ የሚታወቁበት ሁለት ነገር አለ፡-
አንደኛው የወፈረ ድፍድፍ ሽሮ ማብላታቸው ሲሆን
ሌላኛው ደግሞ ለተከፈለበት ሽሮ ደረሰኝ አለማቅረባቸው ነው፡፡ የጠላ ድፍድፍ አሁን አሁን እየቀረ ባለበት ሰዓት፤ የሽሮ ድፍድፍ ማዬት ያስመሰግናል፤ ጣዕሙም አብሮ እጅ ያስቆረጥማል፤ የኪስንም ቁርጥማት ሲቀሰቅስ በዛው ልክ ነው፡፡
ደረሰኝ ያለመስጠቱ ጉዳይ ግን የዘመኑ ፖለቲካ ውጤት እና የዘመኑ የፖለቲካ ኂስ ሰጭዎች የተንጠላጠሉበት ገመድ ነው፡፡
ልጁ በምን መልኩ ስለ ፖለቲካ ኣያገባኝም ሲል የነበረ ልሳን ታቅፎ፤ አሁን ደረሰኝ ለምን አይሰጡኝም ያላቸውን ምግብ ቤቶች በመቁረጥ ዘረኛ እነዲሆን ምክንያት ሆኖታል!
ይሕ ትክክል እደለም፤ ስንቃወምም ሆነ ሐሰባችን ስናነሳ አጠቃላይ አውነት እና ሕጋዊ መስመርን ተንነርሰን መሆን ነበረበት፤ አሁን አሁን ከዛሬ 25 ዓመት በፊት እንዳይሆን ስንታገል የነበረውን የዘረኝነት ፖለቲካ አስተሳሰብ አሁን በዚህ መልኩ ቀለብ ሲያደርገን፤ ከላይኛው የዘረኝነት መንፈስ ጋር አብረን ስንሳከር ማዬት ያሳዝናል፡፡ ምን ለማለት ነው…፡፡ ትላንት መለስ ዜናዊን ሲያመልኩና ሲያወድሱ የነበሩ ዜጎች ዛሬ እርሱ በፈጠረው የዘረኝነት የፖለቲካ ባሕር ውስጥ እየዋኙ በዘረኝነት ሰክረው አገርን ያሳብዳሉ! “እርሱ ቢኖር እኮ እንዲህ አይሆንም ነበር” እያሉ ያሟርታሉ!!
የዘረኝነት አስተሳሰብ ለዬት ያለበት ዋናው ምክንያት መንፈስን ከማበላሸቱ እና ከማቀላቀሉ በላይ ኪሳራው መመለሻ የሌለው ንጉደት ነው! ሽሮ ተወደደ፣ ደረሰኝ አይሰጡንም እና ትግሬን ሁሉ እጠላለሁ ብሎ ወደ ዘረኝነት ባሕር መድፈቅ መታመም ነው! አሁን በከተማችን ብሎም አገራችንን እያጠቃ ያለው አስተሳሰብ ይሕ ነው! እየሸበሸቡ እየዘመሩ ወደ ገሃነም መውረድ ይሉታል ይሄ ነው!! አሁን የፖለቲካ ኂሶች እንደ ከተማችን የመኪና ሽያጭ ቤቶች፣ ሽሮ ቤቶች፣ የጀበና ቡና ቤቶች እና የግል እስር ቤቶች ተበራክተዋል!!
ከዚህ ሁሉ የሚቀድመው አስተሳሰብን ወደ ሕግ፣ ፍትህ እና ነጻነት እንዲሁም እኩልነት መግራት ነው! የአሁን የዘረኝነት ጥላቻ ነገ ባዶ በተሞላነው የብሄር አጽቅ ውስጥ ለመታሰር እና ሌሎችን ለማሰር ነው…!