April 13, 2016
14 mins read

ጎዶሎ ሃሳብ (በአዲሱ ሀይሉ)

(በአዲሱ ሀይሉ_ [email protected])

Facebook page- znewpower

ወጣትነቴን መከታ አድርጌ ሰብዓዊነትን ገደል ከትቼ ነበር ወደ ሆዷ ውስጥ የዘለቅሁት:: የእናትነትን ክብር ዝቅ አድርጌ፣ እህትነትን ንቄ፣ አዛውንትነትን አርቄ ጥዬ:: ስትፈጠር ጎዶሎ ሆና ምግባሬንም አጎደለችው፤ ሶስት ቁጥር እጣ ክፍሏ ሆኖባት፡ ከንቱነቷ ነው እንጂ “ሞልተናል” ያሉትም አልሞሏት፤ እንኳን እሷ ጎድላ መጥታ:: ብቻ ክልው! ክልው! ክልው! ማለት፡፡

ህዝቡ እንደ ግንቦት ልደታ ንፍሮ መሬት ላይ ተበትኗል – መጓጓዣ ጠፍቶ ፡፡

“ምን ሆነው ነው ዛሬ ባጃጆች ስራ ያቆሙት?” ብዬ ሾፌራችንን ጠየኩት

በግራና በቀኜ የተቀመጡት የጉዞ ባልደረቦቼ ለጥያቌዬ የአዘኔታ ከንፈር በመምጠጥ አጽንኣት ሰጡት::

አንዲት ባጃጅ ስትመጣ ግርርር ብለው በሯን ይዘው እርስ በእርስ ይገፈታተራሉ:: ሶስት ሰዎች ሊሳፈሯት ሰባት ስምንት ሆነው ይጋፋሉ:: ዓለም እንግዲህ እንዲህ ናት፤ በርትቶ የተጋፋ ከሶስቱ የባጃጅ ሆድ እቃዎች አንዱ በመሆን መጓዝ ይችላል:: በሉላዊነት ምክንያት እንደባጃጇ ጥብብ እንዳለች የሚነገርላት አለምም እንዲሁ ንፉግ ናት፤ ለሁሉም እኩል ቸር አትሆንም:: ሁሉንም አታሳፍርም::  አቅመ ፈርጣማው አቅመ ቢሱን ወዲያ አሽቀንጥሮ የሚሳፈራት ሆናለች::

ረዥም ትኩስ ትንፋሹን ለቀቀውና

“ኧረ ተወኝ እንደው የኛ ችግር መቋጫም የለው” አለ የባጃጇ አሽከርካሪ::

ችግሩ እጅግ ስር የሰደደ ለመሆኑ ብግን ማለቱ ይናገራል፡፡ አንጀቴን በላው:: ወሬውን መቀጠል ፈለኩና

“ደግሞ ተነሳበት” አልኩ እንዲሁ የችግሩን ዝርዝር ሁኔታ ሳልሰማ በደፈናው ከተማ ውስጥ ከሚኖሩት መሰረታዊ ነገሮች ይልቅ የማይኖሩት እንደሚበልጡ የተለመደ በመሆኑ፡፡

የጉዞ ባልደረቦቼ አሁንም አላሳፈሩኝ  ”አይዞህ፣ በርታ፣ ከጎንህ ነን!“ ለማለት በማሰብ ከተማዋ ባፍ ጢሟ እስክትደፋ ድረስ የተጫነችውን የችግር ጭነት ዘረገፉት:: ሲጨርሱ ልክ ጭነታቸውን ያራገፉ ያህል ተሰማቸው መሰለኝ በረጅሙ ተነፈሱና ተከዙ::

የባጃጅ ሹፌሩ ቆሽቱ አሯል፡፡ እንደኔ የቦና ጥጃ ያስመሰለው ይኸው ውስጥ ውስጡን መድበኑ ሳይሆን አልቀረም፡፡

“መሰለፍ! መሰለፍ! ለሁሉም መሰለፍ ለዳቦ መሰለፍ፣ ለዘይት መሰለፍ ፣ለስኳር መሰለፍ፣ ለመሳፈር መሰለፍ፤ አሁን ደግሞ ሰልፉ ከሰብዓዊ ፍጡር አልፎ ለግዑዙም መጣ:: ለነዳጅ መሰለፍ!” ብሎ የሰልፉን አይነትና ብዛት ዘረዘረ፡፡

“ይኸ ከተማ የማነው ፣ወላጅ አልባ ህፃን የመሰለው?” አልኩ በውስጤ ::

“ለከርስ ጥያቄ መልስ ለማግኘት መሰለፍ ይበረታታል፤ህገ ከርሳዊ ግዴታም ጭምር በመሆኑ:: የማታ ማታም ቢሆን አዛኝ መሪዎቻችን ውለው ይግቡ እንጂ የምትቆነጠርልንን ይዘን በወታደር ታጅበን ወደ ማደሪያችን እንመለሳለን:: ቢበዛ የቀበሌ ሹማምንት ከነጀሌውቻቸው የሚያወርዱብንን ስድብና ግልምጫ መቻል ነው የሚጠበቅብን::

“ሆዱን ያለ ሆዱን ተወጋ” የሚሉት ተረት ዘንድሮ ቀርቷል:: ዛሬ “አፉን የሚያፋሽግ ካለ አፉን እሽግ!” ሆኗል መፈክሩ:: ለመንፈስ ረሀብ መሰለፍ ውጉዝ ከመ አሪዮስ ነው::” ያስወግዛል፤ አለፍ ሲልም ያስወግራል::

አይኑ እያየ አፉ የተለጎመ ህዝብ ልክ እንደ ጋሪ ፈረስ ነው:: አንድ ነገር ትዝ አለኝ:: የጋሪ ፈረስ ወደ ኋላው ዞሮ ማየት አይችልም ያለው ማነው? “እስቲ አንድ ግዜ ወደ ኋላህ ዙር! ብሎ እድሉን የሰጠው ሰው አለ ግን?”  አንገቱ ቢረዝምም መዞር ይችላል ብዬ አስባለሁ ::  አንገት ሲያጥር እንጂ መዞር የማይችለው ሲረዝምማ በደንብ ይዞራል ነገር ግን እዳይዞር የተፈረደበት ፈረስ ቢዞር ትርፉ ምንድነው? በአለንጋ መተልተል ::

አላያችሁም እንዴ አንድ ጊዜ ወደ ኋላዬ ዞሬ ልመልከት ያለ ፈረስ በነጂው አለንጋ እንዴት አርባ እንደሚገረፍ? ምክንያቱም ወደ ኋላው ዞሮ እየተጫነበት ያለውን ጉድ ቢያይ አሻፈረኝ ይል ይሆናል:: ታዲያ የነጂው “ከኔ በላይ ላሳር” ባይነቱ አልታያችሁም?  “እኔ አውቅልሃለሁ” ማለቱንስ አልታዘባችሁም?

“እኔ የማሳይህ መንገድ ልክ ነው እያለ በልጓምና በብረታ ብረት ወድሮ በቅራቅንቦ አይኑን ሸፋፍኖ ነጻነቱን ነጥቆ ወደ ፊት! ብሎት እንጂ ፈረስማ ወደ ኋላም ዞሮ ማየት ይችላል:: ”

በኛ “በሰዎቹ” እና በጋሪ ፈረስ መካከል ያለው ልዩነት ብዙም አይደለም::

ፈረሱ አፉ ላይ በገባው ልጓም፣ ጀርባው ላይ በተተበተቡት ኮተቶችና ጎንና ጎኑን ቀስፈው በያዙት መወጠሪያዎች አማካኝነት ለነጂው ሰጥ ለጥ ብሎ እነዲገዛ ይደረጋል:: ከዚህ ሁሉ ውጭ እሆናለሁ ካለ ደግሞ በአለንጋ ይዳኛል::

እኛ ሰዎቹ ደግሞ የወረቀቷን ያህል እንኳ ዋጋ በሌላት ብጣሽ ወረቀት ላይ በሰፈረች ቃል ባስ ካለ በእርሳስ እንዳኛለን::

እኛም ፈረሱም እኩል ሁለት ሁለት ምርጫዎች ቀርበውልናል:: ፈረሱ ልጓም ወይም አለንጋ እኛ በበኩላችን ከተወላገደ ብዕርና ከእርሳስ ያሻንን እንመርጣለን::

አንደኛው ተሳፋሪ ”ወራጅ አለ“ ሲል ብሶት የወለደው ጀግናውና ቆራጡ የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግን አባርሮ አራት ኪሎ ለመግባት ካደረገው ትግል ያላነሰ ጀብድ ፈጽሜ በገባሁባት ባጃጅ ውስጥ ሆኜ በዙ እንደተፈላሰፍኩ ትዝ አለኝ፡፡ የባጃጁ ሹፌር ይህንን የመሰለ ፍልስፍና  ውስጥ እንደነበርኩ ቢያውቅ ኖሮ እጥፍ ያስከፍለኝ ነበር ፡፡

“ሀይ ባይ ያጣ ከተማ ሆኖ እንጂ እኮ ይሄን ጊዜ ነዳጁም ፣ ስኳሩም ፣ ዘይቱም ሁሉም አልጠፋም” አልኩ የሾፌሩን ሃሳብ በደንብ መረዳት ፈልጔ::

ከአፌ ንጥቅ አድርጎ “እንዴ ምን ማለትህ ነው ሰው ነው እንጂ የጠፋው ሁሉም ነገር አልጠፋም ፤ ግን ማን ያስተዳድረው፤ ማንስ ይጠይቃቸው” አለ ከፍ ባለ ድምጽ::

“የሚገርምህ ትላንትና ቤንዚን ሲሸጥ የነበረው አንድ ማደያ ነው ፣ዋጋ ጨምረህ ሸጥክ ብለው ዛሬ አሸጉት፡፡ ይኸው አሁን ከተማው ውስጥ ካሉት ባጃጆች አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ቤንዚን አጥተው ቆመዋል፡፡ ለጥፋቱ ተገቢውን ቅጣት ቀጥቶ እንዲሸጥ ማድረግ ይቀላል ወይስ ጭራሽ አሽጎ ህዝብን እንዲህ ማጉላላት?” አለ የአስተዳዳሪዎቹ ማን አለብኝነት አንገብግቦት፡፡

በረጅሙ ተነፈሰና “ተወው እስቲ ሁሉን እናውቃለን ብንናገር…” ብሎ ሳይጨርስ አምባረቅሁበት

“እንዳትጨርሰው! እንዳትጨርሰው! ሆሆሆ ወንድሜ አልሰማህም እንዴ?” አልኩት::

“ምነው? ምኑን?” አለኝ ደንገጥ ብሎ መሪውን እንደጨበጠ ወደ ኋላ አንገቱን ለማዞር እየሞከረ

“ባጃጆች ሰማያዊ ቀለማቸውን ወደ ሌላ ከሰማያዊ ውጭ ወደሆነ ማንኛውም ቀለም እንዲቀይሩ አዋጅ ሊወጣ መሆኑን? ማንኛውም የሲቲ ወይም የቸልሲ ደጋፊ የሆነ ሁሉ ከአሁን በኋላ በይፋ መደገፉን እንዲያቆም”

“ታዲያ ይሄ ከኔ ተረት ጋር …”

“ቆይ አልጨረስኩም ” አሁንም አቋረጥኩትና

“ዛሬ ስላሴ ናቸው እያላችሁ አስር ጊዜ የምታወሩ ማህበረ ቅዱሳን ነኝ ባዮች፣ ልደቴ ሚያዚያ ሰባት ነው፣ ህዳር ሰባት ነው ወ.ዘ.ተ እያልሽ በቀን 7 የምትመፃደቂ ሞልቃቃ ኮረዳ በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስቴ ከመብላት ወደ ሰባት ጊዜ ማደግ አለበት እያላችሁ የምትደሰኩሩ የምጣኔ ሃብት ባለሞያ ነን ባይ ጸረ ልማት ሁሉ”

ሳልጨርስ አቋረጠኝና

“እንዴ ታዲያ ይኼ እኔ ካወራሁት ጋር ምን አገናኘው?” አለ በጣም ተገርሞና ግራ እንደመጋባት ብሎ

“የኔ ወንድም ካገናኙት የማይገናኝ ነገር የለም” ብዬ እምወርድበት ቦታ ከመድረሴ በፊት ድምጼን ከፍ አድርጔ “ወራጅ አለ!” አልኩ::

“እባብ ያየ በልጥ በረየ” አልኩና ሂሳቡን ሰጥቼው ወደ ቤቴ የሚያመራውን መንገድ በእግሬ ተያያዝኩ፡፡

ግን ራሴን በጣም ታዘብኩት “ፈሪ ! ቦቅቧቃ !” ብዬ ሰደብኩት ፡፡

ቆይ አሁን በባዶ ሜዳ መደናበርን ምን አመጣው ? እኔን ብሎ ተቆርቋሪ ፡፡

ማን ነበር “የማኪያቶ አርበኛ” ብሎ የተናገረው (የተሳደበው ልበል እንጂ፣ ይሄ አሳዳጊ የበደለው ስድ አደግ )

“ምን ማለት ነበር?” የሚለው ሀሳብ ውስጤ መጣ::

በየቡና ቤቱ ማኪያቶ እየጠጡ “መንግስት እንዲህ አደረገ፣ እከሌን አሸባሪ ብሎ ፈረጀው፣ ወደባችንን አሳጣን፣ መሬት እንደ ዳቦ እየቆረሰ ይሸጣል፣”  እያሉ የሚያንሾካሽኩትን ለመግለፅ ይሆን? ልክ እንደኔ የባጃጅ ውስጥ አርበኝነት ማለት ነው፡፡

እንዲህስ ቢሆን ማኪያቶ የሚዘጋጀው ወተትና ቡናን በማቀላቀል አይደል? ስለዚህ ወተት የገዛ ማንነቱን አጥቶ ቡናም ሳይሆን ወተትም ሳይሆን ሲቀር ቡናም እንዲሁ ቡናነቱን አሳልፎ ሰጥቶ ወተትም ሳይሆን ሲቀር በቃ ሁለቱም ከሁለት ያጣ ጎመን ሆነው የማንነት ቀውስ ውስጥ ሲገቡ የግል መለያ ቀለማቸውን ሲያጡ::

ምናልባት የማኪያቶ አርበኞችም የራሳቸው የሆነ ስብዕና፣ የራሳቸው የሆነ ቀለም ስለሌላቸው ይሆናል ተሳዳቢው “የማኪያቶ አርበኛ!” ያለው::

ሰፈሬ ካለች ትንሿ አቧራማ ግሮሰሪ ስደርስ ነገር ከማብሰልሰል መለስ ብዬ ዙሪያዬን አስተዋልኩ፤ የአድማስ ሰፊ ጉሮሮ ጀንበርን እየዋጣት ነው:: ገባሁና ቢራ አዘዝኩ፤ እኔስ ቢራ ለምን አልውጥም? የቢራ አርበኝነቴ ሊቀጥል ነው ደግሞ፡፡ በአንድ ጊዜ ከባጃጅ ውስጥ አርበኝነት ወደ መጠጥ ቤት አርበኝነት ተሸጋገርኩ:: ሌላ ሮሮ ፣ሌላ አቤቱታ ፣ሌላ ችግር ፣ እልፍ አዕላፍ ሌላ…..

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop