April 3, 2016
62 mins read

በዘመነ ወያኔ ዐባይ ቢገደብ የነዳጅ ዘይት ቢገኝ ለሀገራችን በረከት ወይስ መርገም?

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
[email protected]

ይሄንን ጽሑፍ ለንባብ ያበቃሁት ታች አምና ነው፡፡ በወቅቱ ካነሣኋቸው ነጥቦች አሁንም ጥያቄ እንደሆኑ ያሉ ብዙ ነገሮች አሉና ግድቡ ይጠናቀቃል ተብሎ ተይዞለት በነበረው ጊዜ ገና ሃምሳ በመቶ አጠናቀቅን እያሉ የሚቀልዱበትን ምክንያቶች ሁሉ ትረዱበታላቹህና አንብቡት መልካም ንባብ፡-

ከምርጫ 97ዓ.ም. በኋላ በሀገራችን በርካታ የልማት ሥራዎች ተሠርቷል እየተሠራም ይገኛል፡፡ በአስተውሎት ለማያይ ሰው እነኝህ የልማት ሥራዎች አስደሳችና አጥገቢ ናቸው፡፡ “ላንተስ?” የሚለኝ ቢኖር እውነት ለመናገር እነኝህ የልማት ሥራዎች ለእኔ እያንዳንዳቸው በእየራሳቸው የልማት ሥራ ሳይሆኑ የጥፋት ሥራዎች ናቸው፡፡

ሁለቱን በምሳሌነት ላንሣ፡- ዛሬ ላይ በጥራት ችግር ምክንያት አገልግሎቱን ለደንበኞቹ በቅጡ መከወን አቅቶት ከፍተኛ ችግር ላይ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም ደረጃውን ባልጠበቀ የመሣሪያ የጥራት ችግር ምክንያት ለዚህ ዓይነት ችግር እንደሚዳረግ የተረዳ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው በዚያው መሥሪያ ቤት በኃላፊነት ደረጃ የነበረ የድርጅቱ ሠራተኛ በቢልዮኖች (በብልፎች) ዶላሮች ልብ በሉ በሚልዮኖች (በአእላፋት) ሳይሆን በቢልዮኖች (በብልፎች) ዶላር በጀት ሥራው እየተሠራ እያለ በሞያውና በኃላፊነቱ ከቻይና መጥተው ሊገጠሙ ያሉ መሣሪያዎች ከተመደበላቸው ወጪ እጅግ የወረደ ጥራት ያላቸውና ከደረጃ በታች በመሆናቸው ችግራቸውን በመግለጥ ለአገልግሎት ሊውሉ ስለማይችሉ ፊርማውን ላለማሥፈር በመቁረጡና በእንቢተኝነቱ በመጽናቱ ለአሳዛኝ ውክቢያ ተዳርጎ በመጨረሻም በገዛ ሀገሩና ሕዝቡ ፊት በቻይኖቹ በጩቤ ተወግቶ መጣሉ ከሥራም መሰናበቱ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በወቅቱ በኅትመት የብዙኃን መገናኛዎች የተዘገበና የዜጎችን ልብ እጅግ ያሳዘነ ተግባር ነበር፡፡

ይህ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ጥራታቸው ከደረጃ በታች ነው ልንሠራባቸው አንችልም ያላቸው ዕቃዎች ተገጥመው አገልግሎት እንዲሰጡ ሲደረግ በቴሌ አገልግሎት ላይ ምን ዓይነት የተወሳሰበ ችግርና እጅግ አስቂኝና አስገራሚ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል የሞተ አገልግሎት እንደፈጠሩ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ ልብ በሉ ይሄንን እርባና የሌለው ሥራ ለማሠራት ግን በትውልደ ትውልድ ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ ሀገር ተዘፍቃለች፡፡ በዚህ ስም የተበደርነው ገንዘብ መበላቱ ብቻ አይደለም ብዙ ሳይጨክኑ ከፊሉን ብቻ በልተውም በተረፈው እርባና ያለው ሥራ ቢሠራበት ምንኛ ዕድለኞች በሆንን ነበር፡፡

ሌላው በመንገዶች ሥራ ላይ ያለው ጉድ ነው፡- በአጋጣሚ የተዋወኩት ሰው ነው በመንግሥት የተመደበ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ (supervisor) ሆኖ ይሠራ የነበረ ነው፡፡ ከሥራ የተፈናቀለበትን ምክንያት ሲነግረኝ በሥራ ላይ እያለ ቻይኖቹ ቀኑ አይበቃንም ሌሊትም መሥራት እንፈልጋለንና ይፈቀድልን ብለው ጠይቀው ይፈቀድልቸውና ሌሊትም መሥራት ጀመሩ፡፡ እሱ ግን የሚከፈለው በመደበኛ የሥራ ሰዓት በመሆኑ ሌሊት ተገኝቶ ሥራውን ሊሠራ ወይም ሊቆጣጠር አልቻለም ነበር፡፡
ሥራቸውን መሥራት እንደቀጠሉ አንድ ቀን የቀን ሠራተኞቹ ለዚህ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አንድ ጥብቅ ጉዳይ ሹክ ይሉታል “ይሄውልህ ቻይኖቹ ቀን ያሠርነውን የአርማታ ብረት ሌሊት ሌሊት ግማሹን አስፈትተውን ካወጡት በኋላ ነው የኮንክሪት ሙሊቱን የሚሞሉት” ብለው ይነግሩታል፡፡ አጅሬ ምንም ነገር የሰማ ሳይመስል ጸጥ ብሎ ይቆያል፡፡ ቻይኖቹ ሥራውን እየሠሩ በሠሩት መጠን ሒሳብ እንዲለቀቅላቸው የሚያደርግ አሠራር ስላለ ሒሳባቸውን ለማስለቀቅ በተገቢው መንገድ ለመሠራቱ የተቆጣጣሪው መሐንዲስ ፊርማ አስፈላጊ ነበርና እንዲፈርም ተጠየቀ፡:

አጅሬው ሲጠብቀው የነበረው ጊዜ ይሄ ነበርና ተቋራጮቹን ይዟቸው ሔደና ከድልድዩ መሐል ቆሞ “ጥሩ ፊርማዬን ነው የምትፈልጉት አይደል? ምንም ችግር የለም! ብቻ እዚች ላይ ቴስት ማድረግ (መፈተሽ) እፈልጋለሁና ከልሎ እያሳየ በዚህ ስፋት እዚህ ላይ ቆፍሩልኝ!” አላቸው ቻይኖቹ ደነገጡ፣ ተሸበሩ እንደጉንዳን ወረሩት ለመደራደር ሞከሩ 200,000ብር መደለያ አቀረቡለት አጅሬ ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ አለ፡፡ ቻይኖቹም “አይ እንግዲያውስ ምንም አታመጣም! የት እንደምትደርስ ምን እንደምታደርግ እናይሀለን!” አሉት፡፡ ያልሔደበት ይመለከተዋል መፍትሔ ይሰጠዋል ብሎ የገመተው የከፍተኛ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አልነበረም፡፡

ጭራሽ አርፎ ካልተቀመጠ በሕይወቱ እንደፈረደ እንዲቆጥረው ዛቻና ማስፈራሪያ ከየአቅጣጫው ይመጣበት ጀመር፡፡ ጭራሽም ከሥራው አውጥተው ጣሉት፡፡ የምላቹህ በትክክል እየገባቹህ ነው? በሙስና ምክንያት መንገዶቹ እየተሠሩ ያሉት ደረጃውን ባልጠበቀ ግብአትና አሠራር ነው እየተሠሩ ያሉት፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ይሄ ከዚህ ሳይባል መንገዶቹ ጭራሽም ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ከመሆናቸው በፊት ውኃ ውስጥ እንደገባ ካርቶን ፍርክስክሳቸው የሚወጣው፣ የሚቀበሩት ቱቦዎች ለከፍተኛ መንገድ አይደለም ለመንደር ውስጥ መንገዶች እንኳን በማይበቃ ስፋት ተሠርተው የሚቀበሩትና የክረምቱን ጎርፍ የማሳለፍ አቅም አጥተው ጐርፉ አስፋልቱን አጥለቅልቆ የሚፈሰው፡፡ እነኝህን ብላሽ መንገዶች ለማሠራት ግን ሀገሪቱ በትውልደ ትውልድ ተከፍሎ ሊያልቅ ከማይችል የዕዳ ማጥ ውስጥ እንደተዘፈቀች ከማንም የተሠወረ አይደለም፡፡

የልማት ሥራ እየተባሉ በከፍተኛ ወጪ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ባለባቸው የተወሳሰቡና በርካታ የጥራት ችግሮች ምክንያት ችግር ሲያጋጥም ያለባቸው ችግር ይቀረፍና እንደገና በጥራት ይሠሩ ቢባል መጀመሪያ ለአጠቃላይ ግንባታ ከጠየቁት ወጪ እጥፍ እንደሚጠይቁና ከብዙ አቅጣጫ ቀድሞውኑ አለመሠራታቸው ይመረጥ እንደነበር ባለሙያዎች አበክረው ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ ብላሽ ሥራዎች ሀገርና ሕዝብ ምን ያህል እንደሚጎዱና እየተጎዱ እንደሆነ ለመግለጽ እጅግ ከባድ ነው፡፡

ከኪሳራው በተጨማሪ አስከትለውት የሚመጡት የችግር ዓይነት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ እንግዲህ የዚህ ሁሉ መንስኤው ኃላፊነት የማይሰማው ሀገሬ ሕዝቤ የሚል ቁጭትና ሐሳብ እውስጣቸው በሌላቸው የዘራፊ ቡድን (ወያኔ) የሚሠራ ሥራ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቡድን ከዚህ የዘለለ ነገር መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ ይሄ ይሄ ችግር ነው የተሠሩትን ሥራዎች የልማት ሳይሆኑ የትፋት የሚያደርጋቸው፡፡

በመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት ዙሪያም ያለው ጉዳይ ከዚህ የከፋ እንጅ የተሻለ አይደለም፡፡ ለማሳያ ያህል እነዚህን ሁለት ባለሙያዎች አነሣን እንጂ በተመሳሳይ ሁኔታ በየ መሥሪያ ቤቱ ችግር ላይ የወደቁና ዜጎችና የተፈጸሙ ችግሮች ቁጥር የትየለሌ ናቸው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በምን ምክንያት የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ኃላፊን አቶ ምሕረት ደበበን በምን ምክንያት ከኃላፊነታቸው አንሥቶ ምን ሥራ እንደተሠራና የዚያ ውጤትም መብራት ኃይል አገልግሎቱን በብቃት ማቅረብ ሳይችል ቀርቶ በምን ዓይነት የኃይል መቆራረጥ ችግር ከቶን እንደከረመና በቢሊዮን (በብልፍ) ዶላር የሚቆጠር የሀገር ሀብት ፈሶ በሙስና በተገዙት ደረጃቸውን ባልጠበቁ የኃይል ማስተላለፊያዎች (ትራንስፎርመሮች) ወደፊትም ላሳለፍነው ዓይነት ችግር እንደሚዳርጉን፤ በዚህ መሀል ሀገርና ሕዝብ ለከፍተኛ ኪሳራና ችግር እንደተዳረጉና እንደሚዳረጉም በተለይ በአሁኑ ሰዓት የአደባባይ ምሥጢር ነውና ይሄንን መዘርዘር አይጠበቅብኝም፡፡

ወያኔ ዐባይን ለመገደብ የተነሣባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች፡-

የሕዝብን የምርጫ ድምፅ ለመንጠቅ፡- ይሄን የምለው ወያኔ ይሄንን ግዙፍ ሥራ የጀመረው በእርግጥም የሕዝብ አቅም ይህን ፕሮጀክት (የሥራ ዐቅድ) ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑን አውቆና አምኖ ከሆነና እውነታውም እንደዚያ ከሆነ ነው “ገንዘባችሁ ባለበት በዚያ ልባቹህ አለ” እንዲል መጽሐፍ አቶ መለስ ቦንድ ግዙ እያልኩ የእያንዳንዱን ዜጋ ገንዘብ ከያዝኩበት ለእኔ ሲል ሳይሆን ለራሱ ሲል “ገንዘቤን ይዞብኛል ተበልቶብኝ እንዳይቀር! ሲል፣ የግዱን የእኔን መኖር በሥልጣን መቆየት ይፈልጋል፡፡ ምርጫ ሲመጣ ሳያወላውል ይመርጠኛል በዚህም ዘዴ ቢያንስ ግድቡ ካለቀም በኋላ ገንዘቡ እስኪመለስለት ድረስ ለዐሥርት ዓመታት መቆየት የሚያስችለኝን ዋስትና መጨበጥ እችላለሁ፡፡ ገንዘቡ ጥሩ መያዣ ይሆንልኛል፡፡ ምርጫን ማጭበርበር ሳያስፈልገኝ በቀላሉ ማሸነፍ ያስችለኛል” በሚል ብልጣብልጥ መሰል አስተሳሰብ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተፈጠረች ዘዴ ናት፡፡

እጥረት ወይም ችግር በመፍጠር ዐመፅን ለመቆጣጠር ከሚል የአንባገነኖች ስልት፡- ወያኔ በግድቡ ግንባታ ሰበብ የየወር ደሞዙን በመቆንደድና ሕዝቡን ለችግር በመዳረግ ሀሳቡንና ትኩረቱን በጓዳው ችግር ብቻ እንዲወሰን እንዲጠመድ በማድረግ እሱን (አገዛዙን) እንዲረሳ እንዳያስብ ማድረግ እንደሚቻል በጽኑ ያምናል፡፡ ዋነኛ የአገዛዝ ስልቱም ነው፡፡ ደስ የማይለው አዝማሚያው የማያምረው አንቅስቃሴ በተፈጠረ ቁጥር እጥረት በሌለበት ሁኔታ መብራትና ውኃን ጨምሮ ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር መሠረታዊ ፍጆታዎች እንዳይኖሩ እንዲጠፉ ያደርጋል፡፡ የፈራውንም ነገር በቀላሉ ይቆጣጠራል፡፡ ይህ አሠራሩ እስከ አሁን ቢይዝለትም እስከመቼ እንደሚያዘልቀው ግን አላውቅም፡፡ ለማንኛውም ለዐባይ ግድብ እያለ አንደኛ ዙር ሁለተኛ ዙር ሦስተኛ ዙር ገናም ይቀጥላል፡፡ ከሕዝቡ የሚነጥቀው ገንዘብም በዚህ ረገድ እንዳሰበው አድርጎለታል ሕዝቡን በየጓዳው ችግር ለመጥመድ ስላስቻለው ባሰበው መንገድ ለመቆጣጠር አብቅቶታል፡፡

አሥጊ ወቅታዊ የሕዝብ ትኩረትን ለማስቀየስ፡- እንደሚታወሰው የዐባይ ግድብ ፕሮጀክት በድንገት ታውጆ ሥራው በተጀመረበት ወቅት በተለያዩ ሀገራት ሕዝባዊ ዐመፆች እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለና ኢትዮጵያንም እንደሚያሠጋት ይወራ የነበረበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን የሕዝብን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስና ሕዝብን በመደለል ለዐመፅ እንዳይነሣሣ ለማድረግ ድንገት የተፈጠረ ፕሮጀክት (የሥራ ዐቅድ) ነው፡፡ ለዚህም ነው ይሄንን ለሚያክል ግንባታ ግንባታው ከመጀመሩ በፊት ሊከወኑ የሚገባቸው መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ሒደቶችና ዝግጅቶች ሁሉ ሳይፈጸሙለት ሥራው የተጀመረው፡፡ ለምሳሌ አግባብነት ባለው አካሔድ ግልጽ ጨረታ፣ በእጅ ያለ በጀት፣ ሌላው ቀርቶ የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ሥራ ከተጀመረ በኋላም እንኳን ይሄንን የሚያህል ፕሮጀክት (የሥራ ዐቅድ) በአንዲት መለስተኛ የመቆፈሪያ ማሳልጥ (Excavator Machine) ብቻ ሥራው ከወር በላይ ሲሠራ የነበረው፡፡

ጠያቂን አካል በማስመታት ከተጠያቂነት የማምለጫ መንገድ የመፈለግ ሸር፡-ወያኔ የዐባይን ግድብ ኘሮጀክት (የሥራ ዐቅድ) ይፋ ሲያደርግ ግድቡን ለመሥራት አስቦ አልነበረም፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የግድብ ሥራ ይፋ ሲደረግ የደነገጥኩትን ድንጋጤ እኔና እግዚአብሔር ነን የምናውቀው “መቀመጫቹህ ላይ ፈንጅ ቀበርኩባቹህ!” የተባለ ነው የመሰለኝ፡፡ ሀገራችንን ጥቅልል አድርጎ ወደ ገደል የወረወራት ነው መስሎ የተሰማኝ፣ ያለ የሌላትን በዚህ ሰበብ ጠራርገው ሲበሉት ቀልጦ መና ሆኖ ሲቀር ነው የታየኝ፡፡

ከዚህ ሐሳብ ጀርባ ሊኖሩ የሚችሉ ነገሮች ወዲያው ነበር ይታዩኝ የጀመሩት “አይ! በቃ ወያኔ ሰለቸች ታከተች ማለት ነው፣ የሚገላግላትን ነገር ፈለገች ማለት ነው” ነበር ያልኩት፡፡ ምክንያቱም ዐባይን በተመለከተ የሚሰሙ ምንም ዓይነት ሹክሹክታዎችን ግብጽ እንደማትታገስ አቶ መለስ ስለሚያውቁ በጠባብነት ፖለቲካቸው (እምነተ አሥተዳደራቸው) ታንቀው በሚዘውሩት አገዛዛቸው ቢሉት ቢሉት አልሆን ስላላቸው፣ የራሳቸውን የንግድ ድርጅቶችና የተሟሳኝ ባለሀብቶችን ዕድገት የሀገር በማስመሰል ደላላ (ሎቢ) እየገዙ የሚያሥወሩት የውሸት የሀገር እድገት የትም እንደማያደርሳቸው ስላወቁና ተስፋም ስለቆረጡ፣ የሌለን ነገር ያለ ለማስመሰል የቻሉትን ሁሉ ቢያደርጉም ገሀዳዊው እውነታ ድንገት ተገልጦ መዋጣቸው አይቀሬ መሆኑን ስለተረዱና በሌላ አማራጭ ሥልጣን ከለቀቁም የሚከተላቸውን የሚያጋጥማቸውን ያውቃሉና ይሄንን አስልተው ከዚህ ሁሉ ጣጣ ሊድኑ የሚችሉበትን ዕድል ሲያፈላልጉ የተከሰተላቸው መላ ነው፡፡

በእኔ እምነት የዐባይን ግድብ ግንባታ የወለደው ይሄ “የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አስተሳሰብ ነው እንጅ ወያኔ ብሔራዊ ሐሳብ ማሰብ ችሎ የተተለመ ትልም አይደለም፡፡ ሰብእናውና ተሞክሮው ይሄን አያሳይምና አያረጋግጥምና፡፡ ነገር ግን የሚያሳዝነው ነገር በአጋጣሚ ሆኖ ግብጽ በራሷ ችግር ተመሰቃቅላ ከመጠመዷ ጋር ተያይዞ አቶ መለስ በግልጽ ግብጾችን በዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ “ወንድ ከሆናቹህ ኑ እንዋጋ!” እያሉ የጦርነት ግብዣ ቢያቀርቡም ግብጽ ልታርገው አልቻለችም፡፡ አቶ መለስ ጉዳቸው ፈላ ተጋለጡ፡፡ ያሰቡት ቀርቶ ያላሰቡት ሆነ “አይ እግዚአብሔር ደጉ!” አቶ መለስ ባላሰቡት የልማት ሥራ እንደተጠመዱ ጭንቅላታቸው ፈንድቶ አለፉ፡፡

ግንባታው እስከ አሁን ባለው ሒደት በገንዘብ እጥርት ምክንያት በጣም ተጓቷል፡፡ በተያዘለት የጊዜ ቀጠሮ መሠረት በዚህ ወቅት 60% ያህሉ መጠናቀቅ ነበረበት፡፡ የተጠናቀቀው ግን መጠናቀቅ ከነበረበት ከግማሹ የሚበልጥ አይደለም፡፡ ቀጣዩ ወቅት ትኩረት የሚስብና ልብ አንጠልጣይ ነው፡፡ ከሀገሪቱ ካዝና የለም የተባለው ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ብድር አልተገኘም አስቀድሞም ይገኛል ተብሎ ተስፋ አልተደረገም፡፡

በጃንሆይና በደርግ የነበረው እንቅፋት ዛሬም አለና፡፡ በቀደም ከሕዳሴው ግድብ ሦስተኛ ዓመት ክብረ በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ እንደሰማነው እስከ አሁን 34% ቢሊዮን ብር ማለትም ለግንባታው ያስፈልጋል ከተባለው ወደ ግማሽ የሚጠጋ ወጪ እንደተደረገ እየተናገሩ ነው፡፡ አንድ ሦስተኛ ለማይሞላ ክንውን ይህንን ያህል ወጣ ማለት ግድቡን ለመጨረስ ለማጠናቀቅ ከ 113 ቢልዬን (ብልፍ) ብር በላይ የግድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

አሁን በያዙት ፍጥነት ከቀጠለ ግድቡን ለማጠናቀቅም 10 ዓመታት ይወስዳል ማለት ነው፡፡ እሱም ገንዘቡ ከተገኘ ነው፡፡ ሳያስቡት የተጠመዱበትን ነገር ከመፈጸም ውጭ አማራጭ የለም ብለው ከተመዘበረው የሀገሪቱ ገንዘብ ጥቂቷን አምጥተው ሥራውን ለማጠናቀቅ ካሰቡ ምናልባት ግድቡ ይፈጸም ይሆናል፡፡ ይህ ዕድል ከሌለ ግን ኳሷን ወደ ሕዝቡ እግር በመምታት ማስተባበርና በግድም በውድም ከጎናቸው ማሰለፍ የቻሉት የሕዝብ አቅም የታየውን ያህል እንደሆነና የማያወላዳ አለመሆኑን እያውቁ ሕዝቡን “ግድቡ ማለቅ ካለበት አውጡ አናወጣም! የለንም! አንችልም! ካላቹህ ግን ሥራው መቆሙ ነው!” ውሳኔው የናንተ ነው በማለት ኃላፊነቱን ከራሳቸው ለማውረድ እንደሚሞክሩ እገምታለሁ፡፡

አቶ ኃይለማርያም ባላቸው መረጃ ደግሞ ከላይ በኮሚቴው ከተጠቀሰው በ7 ቢሊዮብ ወርዶ ለእስካሁኑ ክንውን 27 ቢሊዬን (ብልፍ) ያህል ብር ወጪ ሆኗል ብለውናል፡፡ በዚህም መሠረትም ለማጠናቀቅ ከ90 ቢሊዬን (ብልፍ) ብር በላይ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

የዐባይ ግድብ በሕወሓት ኢሕአዴግ መገደቡ ተገቢ የማይሆንበት ወይም አደገኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ ነጥቦች፡- ጠላት ካልሆነ በስተቀር ጤነኛ አእምሮ ያለው ዜጋ ሁሉ የዐባይን መገደብ የማይፈልግ ይኖራል ብዬ አልገምትም አይኖርምም፡፡ እንዲያውም ዐባይ መገደብ ከነበረበት ዘመን በጣም ዘግይቷል፡፡ ግብጽ የምትፈጥረው እንቅፋት እየተሳካላት ቀደማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዐባይን ለመገደብ የሚያስችል ብድር አጥተው ዐባይን የመገደብ ሕልማቸው ሳይሳካ ቀረ፡፡ በደርግም ዘመን እንዲሁ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ሰላም እጦት ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት እንቅፋት ሆኖበት ደርግም ሳያሳካው ቀረ፡፡ ከዚህ የእርስ በእርስ ጦርነት ጀርባ የግብጽና የሱዳን ሙሉ እጅ እንደነበረበት ይታወቃል፡፡

የግብጽንና የሱዳንን ድጋፍ ያገኘ በነበረው በሕወሓት ኢሕአዴግ ዘመን ግን እንኳን ዐባይን ስለመገደብ ሊያስብ ይቅርና በግብጽ ትእዛዝ መሠረት ደርግ ከፍተኛ ወጪ መድቦለት ሥራው ተጀምሮ በመቀጠል ላይ የነበረውን የጣና በለስን ፕሮጀክት እንዲዘጋ አድርጎት ነበር፡፡ ወያኔ ይህ አድራጎቱ ስሕተት እንደሆነ ለመረዳት የአንድ ታዳጊ ወጣት ዕድሜ አስፈልጎት ነበር፡፡ የደርግ መውደቅንና የወያኔን ሥልጣን መያዘ ተከትሎ በደርግ ዘመን በእንግሊዝ ሐሳብ አቅራቢነት የላይኞቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገራት የውኃ ድርሻ እንዲኖራቸው ያቀረበችው ሓሳብ ግብጽ “ያለው የውኃ መጠን ሳይታወቅ እይሆንም!” ብላ በመቃወሟ ይሄንን ጉዳይ የሚያጠና ቡድን ተቋቁሞ እየተደረገ የነበረው ጥናትና ድርድር ሳይቋጭ ደርግ በመውደቁ ተቋርጦ ወያኔም ቅጥረኛነቱና አገልጋይነቱ ገና አፍላ ነበርና ይህ ድርድር እንዲቀጥል ፍላጎት ስላለነበረው እንደተቋረጠ ቀይቶ ነበር፡፡

ከጃንሆይ ጀምሮ እስከ ደርግ ሲጠና ሲከለስ ሲጠና ሲከለስ የቆየውና በደርግ ዘመን ተነቃቅተው የነበሩት ዐባይን መሠረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችም (የሥራ ዐቅዶች) ውኃ ተቸልሶባቸው ተዳፍነው ለመቆየት ግድ ሆኖ ነበር፡፡ ይህ ወቅት ለግብጽና ሱዳን የእፎይታ ዘመን ነበር፡፡ ወደ ኋላ ላይ አዲስ አበባ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ሲመጡ በግብጹ መሪ ሆስኒ ሙባረክ የግድያ ሙከራ በመደረጉ ሳቢያ የሦስቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ወያኔ እንደ ማስፈራሪያ አድርጎት አዳፍኖት የነበረውን ዐባይን መሠረት ያደረጉ የሥራ ዐቅዶችን በብዙኃን መገናኛ በአለፍ ገደም ማሳየትና ማሰማት ጀመረ፡፡
በተጨማሪም አንገብጋቢ እየሆነ የመጣው የሀገሪቱ የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ማሟላቱ ግዴታ ሲሆን የተቀያየሙት ወዳጆቹ ስለነሱ ሲል በዐባይ ላይ ምንም ዐይነት ፕሮጀክት ላለማሰብ ሥልጣን በያዘ ማግሥት ግብጽ ድረስ በመሔድ ቃል ገብቶ የነበረውን ለማጠፍ ቅያሜው ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮለት በደርግ ተጀምሮ የነበረውንና ሽሮት የነበረውን የጣና በለስን ፕሮጀክት ካዳፈነበት በመቀስቀስ ሥራው ተጠናቆ ከ 4ዓመታት በፊት ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ይህም ጉዳይ በግብጽና በሱዳን ቅሬታ አሳድሮ የተግባቡት ቃል እንዲፈርስ ጥሩ ተጨማሪ ሰበብ ሆነ፡፡ አሁን እንደምናየውም ከ 50 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲታሰብ የነበረው የዐባይን ግድብ እውነት የሚገነባ መስሎ እራሱ ለሚያውቀው ዓላማ ማለትም የመገላገያ ሰብብ ለመፍጠር አስቦ የጀመረው እስከአሁን እንደምናየው ከሆነ እየሆነ ያለው ያሰበው ሳይሆን ያላሰበው ነው፡፡
የዚህ ግድብ እውንነት በጃንሆይ ዘመን እንደታቀደው ተከውኖ ቢሆን ኖሮ የሀገራችንና የሕዝባችን ገጽታ ምንኛ የተቀየረ በሆነ ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ዘንድም መታወቂያችን የሆነው የ1977ቱ ዓ.ም ድርቅና ረሀብም ባልተከሰተ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ለዚህ አሳፋሪ አዋራጅና ቅስም ሰባሪ ድህነት ባልተጋለጥን ነበር፡፡ በመሆኑም የዚህ ግድብ የመገደቢያ ትክክለኛ ሰዓት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ዐባይን ለመገደብ ያቀዱበት ያ ጊዜ ነበር፡፡ አልሆነም አልተሳካም፡፡ ይህ የዐባይ ግድብ በሕወሓት ኢሕአዴግ ዘመንና በዚህ ወቅት መገደቡ ተገቢ ጠቃሚ እንዳይሆን የሚያደርጉት ስድስት ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-

ቀደም ሲል መግቢያዬ ላይ ካየናቸው ባለ ቢሊዮን(ብልፍ) ዶላር በጀት (የገንዘብ ምድብ) የወያኔ የልማት ሥራዎች ተሞክሮ እንዳየነው አሳሳቢና አደገኛ የጥራት ችግር ነው፡- ይሄንን ይሄንን የሚያካክል የግንባታ ሥራ በወያኔ የነቀዘ ትከሻና ክንድ፣ የተመረዘ ጭንቅላት በጥራት ይሠራል ብሎ ማሰብ እጅግ እጅግ ሲበዛ የዋህነት ነው፡፡ የቀደመው ተሞክሮው በሙሉ የሚያሳየው ይሄንን ነውና፡፡ እምነት እንድንጥልበት የሚያደርጉ አይደሉምና፡፡ የለብ ለብ እና የማታለል የዚያችው የዕለቷን ምስጋናን ማግኘት ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ብላሽ ሥራዎች ናቸው፡፡

ወያኔ ሁሌም ሲያስብ ዛሬን እንደምንም ብሎ ማለፉን ነው እንጂ ስለ ነገ አያስብም አይጨነቅም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሥራዎቹ ከባባድና ከፍተኛ የጥራት ችግሮችን እንዲያስተናግዱ የተገደዱት፡፡ እሱም አባይ ውሸታም አጭበርባሪ የሆነው፡፡ ውሸቱ እብለቱ እንደ ውሸትነቱ እንደ እብለትነቱ ሁሉ በተጋለጠ ጊዜ “ያኔ ምን ይውጠኛል!” ብሎ ፈጽሞ አያስብም አይጨነቅም፡፡ “አይነጋ መስሏት ከቆጡ ላይ ምን አለች” የሚለው ብሂላችን ወያኔን አንድም ቀን ገብቶት አስፈርቶት አያውቅም፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ (mentality) ባለው ግለሰብም በሉት ቡድን ጥራት ከነ አካቴው ቦታ አይሰጠውም፡፡ ስለሆነም የጥራት ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ፡፡

2. አቶ መለስ እንዳስታወቁት ይህ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ በሕዝቡ አቅም ይገነባል በማለታቸውና የሕዝቡ አቅም የምናየውን ያህል መሆኑ፡፡ በነገራችን ላይ ሕዝቡ ይህ የልማት ሥራ ግብዣ የቀረበለት በማያምነውና በክፉ ነገር ሁሉ በቁጥር አንድ በሚጠረጥረው በወያኔ በመሆኑ እንጅ ኢትዮጵያዊ በሆነና የሕዝብ ፍቅር ባለው መንግሥት ቢቀርብለት ኖሮ ይሄንን አይደለም ሌላም ቢጨመር በስኬት ለመደምደም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ከሀገር ውጭ ያሉ ልጆቹ አቅም ብቻ ከበቂ በላይ በሆነ ነበር፡፡ የሀገሪቱ ካዝናም ቢሆን እዚህ ድረስ ባላሳበቀ ባላሳጣ ነበር፡፡ እናም ሀገርም ሕዝብም አቅም አልባ የሆኑት መሐንዲሱ ታማኙ ተወዳጁ ተፈቃሪው ወያኔ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ሕዝቡ እንደምታውቁት ይሄንን ያህል ወገቡ ተሠብሮ አዋጥቶም ከሚፈለገው ዐሥር በመቶ እንኳን አልተገኘም፡፡ ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ሕዝቡ ለወያኔ ያለው መነሣሣትና እምነት ይታወቅ ስለነበረ ጊዜው አለመሆኑን መረዳት ከባድ አልነበረም፡-

3.ሙስና፡- ወያኔ ሙስናን አንዱና ዋናው የአሥተዳደር ሥርዓቱ የህልውና ስልት (strategy) አድርጎ የሚጠቀም ምናልባትም የዓለማችን ብቸኛ “መንግሥት” ነው፡፡ እያልኩ ያለሁት ሙስና የሚፈጽም አይደለም፡፡ አይፈጽምም ማለቴ አይደለም ሀገራችን ዐይታው የማታውቀው ሙሰኛ መንግሥት እንደሆነ ይታወቃልና፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ወያኔ ዜጎችን የዘለዓለሙ ባሪያው አገልጋዮቹ እንዲሆኑ ተሽቆጥቁጠው እንዲገዙለት እንዲታዘዙለት ሲያስብ ሲፈልግ ሆን ብሎ ሙስና ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡

ከዚያ በኋላ ያችን ይይዝና በማስፈራሪያነት እየተጠቀመ ያንን ዜጋ እንደፈለገ አድርጎ የሕሊና ጥያቄ እንዳያነሣ የታዘዘውን ብቻ እንዲሠራ አድርጎ ይገዛዋል፡፡ ለወያኔ እንደ ሙስና ዋና ጠቃሚ መሣሪያ የለም፡፡ እንዲህ ዓይነት የወደቀ የዘቀጠ አስተሳሰብ አመለካከት የያዘ ቡድን እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ የልማት ሥራ በጥራትና በብቃት መሥራት አይደለም ማሰብም እንኳን ከቶውንም አይችልም፡፡

በዚህ ግድብ ዙሪያ የሚነሡ በርካታ የሙስና ጉዳዮች አሉ፡፡ የግድቡ ሥራ ግልጽ ጨረታ አልወጣበትም፣ የግብአት አቅራቢ ድርጅቶችን በተመለከተ ግልጽና የተለያዩ የሙስና መገለጫ ገጽታዎች በሰፊው እየታየበት ይገኛል፡፡ በመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ መሠረት በወያኔ ዘመን 25 ቢሊዮን ዶላር ከሀገሪቱ እንደተመዘበረ ተነግሯል፡፡ ይህ ገንዘብ አንድ ብቻ አይደለም ከ5 በላይ የዐባይ ግድብ ሊገነባ የሚችል የሕዝብ የሀገር ሀብት ነው፡፡ እናም ሙሰኝነቱም ሌላው ዋነኛ ችግር ነው፡፡
የወያኔ ወያኔያዊ ባሕርይ ፡- ማለትም “ጠባብነቱ” ወያኔ በተፈጥሮው ጠባብ ነው ጎጠኛ ነው ብሔራዊ (ሀገር አቀፍ) አስተሳሰብን ሽታውንም አያውቀው፡፡ ኃላፊነት የማይሰማው ሀገሬ ሕዝቤ የሚል ሥዕል ከጭንቅላታቸው ውስጥ በሌለ ቡድን ጭንቅላት ውስጥ ከጎጥ አጥር ውስጥ ወጥቶ ከልብ (genuinely) ሀገርንና ሕዝብን ታሳቢ አድርጎ ብሔራዊ የልማት ሥራ ሊታሰብ ስለማይችል፡፡

በመሆኑም ወያኔ እንዲህ ዓይነት ግዙፍ የልማት ሥራ (mega project) አቅዶ በብቃት የመሥራት የሞራል (የቅስም) ብቃት አይኖረውም፡፡ ቅስምን ያህል ኃያል አቅም ሳይይዝ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ እንደ እንቧይ ካብ ናቸው፡፡ ወያኔ የማይድን በሽታ አለበት “የጎጠኝነት ነቀርሳ” ይህ በሽታው ከጎሳው በላይ የሆነ ሐሳብ ሊያሳስበው አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬም ከ23ዓመታት በኋላ ይሄ በሽታው ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከአፋር ሌላ ተጨማሪ መሬቶችን ወደትግራይ እንዲከልል ያደረገውና እያደረገው ያለው፡፡ ለምን ይምስላቹሀል? ምንስ እያሰበ? ያለ ዓላማ እንዲህ የሚያደርግ ይመስላቹሀል?

ታዲያ በእንደዚህ ዓይነት ጠባብና ጎጠኛ ጭንቅላት ላይ ነው ኢትዮጵያ እንደ ኢትየጵያነቷ ታስባ እሷንና ሐዝቧን ተጠቃሚ የሚያደርግ በብቃትና በጥራት ግዙፍ የልማት ሥራ የሚታለመው? በሽታው በየት በኩል አሳልፎት? በነገራችን ላይ ከዚህ ከጠባብነት በሽታው ሳልወጣ ወያኔ ለትግሬም ሕዝብ ቢሆን አሳቢ ተቆርቋሪ እንዳልሆነ ታውቃላቹህ? ጠቀምኩ ብሎ የሚያደርገው የሚሠራው ሥራ ሁሉ ከወያኔ “መንግሥት” ህልፈት በኋላ የትግሬ ሕዝብ ከተለያዬ አቅጣጫ ለችግር ለፈተና ለበቀል እርምጃ የሚዳርጉ ናቸውና፡፡ ወያኔ ለትግሬ ሕዝብ አሳቢ ነው ተቆርቋሪ ነው ልለው እችል የነበረው ወያኔ ኖረም አልኖረ መቸም ጊዜ ቢሆን የትግሬ ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በፍቅር በሰላም በመተሳሰብ መኖር የሚችልበትን ሁኔታ ቢፈጥር ኖሮ ነበር፡፡

አስተዋይነት ብልህነት አርቆ ማሰብ መሪነት ማለት ይሄ ነው፡፡ ወያኔ ግን እየኖረ ያለው በ21ኛው መቶ ክ/ዘ ይሁን እንጅ ሥራውና አስተሳሰቡ ግን ገና የድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም ወያኔ ለማን እንደሚሠራና ምን እንደሚሠራ እንኳን የማያውቅ ፍጥረት ነው፡፡ “መንግሥት” ከሆነ በኋላ ኃላፊነቱ ለሁሉም እኩል መሆኑን መቀበል ተቸግሮ ሕዝቡን እየለየ ይሄ ሕዝቤ ይሄ ጠላቴ እያለ አንድን ብሔረሰብ በጠላትነት የፈረጀ በተቻለውም መጠን ለማጥፋት የሚጥር፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘርና በሐይማኖት ከፋፍሎ ለማባላት ለማፋጀት ለማስተላለቅ የሚጥር መሠሪና ክፉ አገዛዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚያስችልን ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡

አቶ መለስ ምን ሲሉ እንደነበር አታስታውሱም? “አንዲት ግራም ጉልበት እስክትቀረኝ ድረስ ድርጅቴን አገለግላለሁ!” ልብ በሉ ሀገሬን አይደለም ያሉት “ድርጅቴን” ነበር ያሉት፡፡ ለነገሩማ በትክክልም ያገለግሉና ያስጠብቁት የነበሩት የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ሳይሆን የድርጅታቸውንና ድርጅታቸው የቆመለትን የጎሳቸውን ጥቅም በመሆኑ ሀገሬን አለማለታቸው ትክክል ነው፡፡

በዚህ መርሐቸው ሳቢያ የቱንም ያህል ለሀገር የሚጠቅምና የሚበጅ ነገር ግን ለድርጅታቸው የማይበጅና የማይጠቅም ጉዳይ ቢኖር ጥንቅር ይላል እንጂ አይ የሀገር ጥቅም ይበልጣል ይቀድማል ብለው ለሀገር ከበጀ ይሁን አይሉም፡፡ የአስተሳሰባቸው መሠረት “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንስሳ ነውና፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሀገርን የማይጠቅምና የሚጎዳ ነገር ግን ድርጅቱን የሚጠቅም ቢሆን ሀገርን ሽ ጊዜ ይጉዳ እንጅ የድርጅቱ ጥቅም ቅንጣት ታክል እንኳ እንድትቀር አይፈልጉም፡፡ በዚህ ምክንያት ሀገረችን ቢዘረዘሩ የማያልቁ ብዙ አጥታ ብዙ ተጎድታለች አንዳንዶቹ ለመቸውም መልሰን ልናገኛቸው የማንችላቸው ናቸው፡፡

የጦር ኃይል አቅም ውስንነት፡- ግብጽ አሁን ለጊዜው ኃይል መጠቀም አልፈለገችም ማለት በቃ! ትታለች ማለት አይመስለኝም፡፡ ጦር ልታነሣ የምትችልበት ሥጋት ሰፊ ነው፡፡ ጦር የምታነሣበት አጋጣሚ ቢፈጠር ከወታደራዊ ትጥቋ አንጻር መመከት የሚያስችለን ተመጣጣኝ የትጥቅ ዝግጅት ሊኖረን የግድ የተገባ መሆን ነበረበት፡፡ ይሄንን የቤት ሥራ ማጠናቀቅ የቻለ መንግሥት ሲኖረን ግብጽም ራሷ ትንፍሽ ሳትል ግንባታችንን መፈጸም የምንችልበትን ሁኔታ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ይህ ጉዳይ ለኔ ምሥጢር ሊሆን ይችላል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ቅርብ ለሆኑ ተቋማት ግን አይመስለኝም፡፡

በቅርቡ V.O.A. “ግሎባል ፋየር ፓወር” የተባለን ድረ ገጽ ጠቅሶ እንደገለጸው ግብጽ ባላት ትጥቅና ወታደራዊ ዝግጅት ወይም አቅም ከዓለም 13ኛ ስትሆን ሀገራችን ደግሞ 40ኛ ናት ብሏታል፡፡ እንደነሱ ትንታኔ የግብጽና የእኛ ወታደራዊ ትጥቅ አቅም ጨርሶ የማይመጣጠን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ጥቃት ቢሰነዘርብን በብቃት ልንወጣው በማንችልበት ሁኔታ ዐባይን ለመገደብ መሞከር አስቀድሜ እንደገለጽኩት መደፍጠጣችን ተፈልጎ ካልሆነ በስተቀር ፍጹም ተገቢ ያልሆነና ያልበሰለ ውሳኔ ነው፡፡ “ስለሆነም ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንቢያው ቁጢጥ” በመሆኑ ወይም “ከፈረሱ ጋሪው” በመቅደሙ፡፡

ይህ ግድብ እንዲያው ብሎለት ከእነኝህ አሳሳቢ ችግሮቹ ጋር በዚያም በዚህም ተብሎ ቢጠናቀቅና እየተናገሩ እንዳሉት ሁሉ የሚመነጨውን ኃይል ለሀገር ውስጥ ለገበሬው ሳይሆን ለውጭ ገበያ አቅርበው፤ መቼም አሁን ለጅቡቲና ለሱዳን እየተሸጠ ያለው ከእኛ ተርፎ ነው የሚለኝ እንደማይኖር ተስፋ አደርጋለሁ እንኳን መብራት የሌላቸው አከባቢዎች መብራት ሊያገኙ ይቅርና አዲስ አበባን ጨምሮ የከተሞችን መብራት በማጥፋት ጭምር እንደሆነ ሁሉ ለጅቡቲና ለሱዳን እየተሸጠ ያለው ከዐባይ ግደብ የሚገኘው ኃይልም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል ተብሎ አይጠበቅም ለነገሩ እነሱም አላሉም፡፡ ከወዲሁም ውል እየፈጸሙ ቸብችበው ጨርሰውታል፡፡ እናም ከዚህ ግድብ የሚመነጨውንም ኃይል ለውጭ ገበያ በማዋል ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት ቢሆን የሚጠቅመው የሚያፈረጥመው የወያኔን ጡንቻ እንጅ ሀገርን ባለመሆኑ፡-

ወያኔ በሀገር ውስጥ የኃይል እጥረት እየፈጠረ የሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎትን እያስተጓጎለ ለጅቡቲና ለሱዳን በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚጥረው በመብራት ኃይል መቆራረጥና መስተጓጎል ምክንያት በፋብሪካዎች፣ በድርጅቶች፣ በሕክምና ማዕከላት፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየደረሰ ያለው የሀገር ኪሳራና ጉዳት ለጅቡቲና ለሱዳን ተሸጦ ከሚገኘው አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ እጅግ ብዙ ጊዜ እጥፍ እንደሚበልጥና እንደሚያስጎዳ ስለማያውቅ ስላልገባው አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ አገዛዙ አቋምና አስተሳሰብ የቱንም ያህል ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ቢሆን የአገዛዝ ቡድኑን ግን የሚጠቅም ከሆነ የማያደርጉት ነገር ስለሌለና ስለማይኖርም ነው፡፡

የሀገርና የሕዝብ ጉዳት ጉዳታቸው ስላልሆነ ነው፡፡ የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ከእነሱ ጥቅም ጋር የማይጣጣምበት ወቅትና ሁሌታ ስላለ ነው፡፡ ወያኔነታቸው የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ከቡድኑ ጥቅም አስበልጠው አስቀድመው እንዲያዩ እንዲያስተናግዱ ፈጽሞ ስለማይፈቅድላቸው ነው፡፡ እናም አንድ ዐባይ አይደለም ዐሥር ዐባይ ቢገነባ ተጠቃሚው አገዛዙና ግብረአበሮቹ እንጅ ሀገርና ሕዝብ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል የለም፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ ለምሳሌ የነዳጅ ዘይት በሀገራችን ቢገኝና ወያኔ ፔትሮ ዶላር (የዘይት ገንዘብ) ማፈስ ቢችል ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስባቹህት ታውቃላቹህ? “ሰብአዊ መብት ካላከበርክ” ከሚል ሊሰማው ከማይፈልገው ቅድመ ሁኔታ ጋር በሚሰጠው የእርዳታና የብድር ገንዘብ ይሄንን ያህል መፈናፈኛ መላወሻ አሳጥቶ የደቆሰን፣ የረገጠን፣ ያሰቃየን፣ የጨቆነን በአፍጢማችን ሊደፋን የተቃረበ አገዛዝ ማንም የማያዝበትን፣ ቅድመ ሁኔታ የሌለበትን፣ ለዚህ ለዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይባል እንደፈለገ የሚያደርገውን የራሱን የካበተ ገቢ ያገኘ ጊዜ ምን ሊያደርገን እንደሚችል አስባቹህታል? ምናችንን ያስተርፍልናል? ዕኩይና እርኩም ዐቅዶቹን ሁሉ በእኛ ላይ ለመፈጸም ዕድል ያገኛል ያጠፋሀልም እንጅ አንተ ተጠቃሚ አትሆንም፡፡

እስከዛሬም እኮ የጭካኔውን የሐሳቡን የምኞቱን ያህል ሊያደርግብን ያልቻለው አቅም ገድቦት ነው፡፡ አቅም ሲያገኝስ? ያኔማ “እነሱን አያርገኝ!” ነዋ የሚለው! የነዳጅ ዘይት ለናይጄሪያ ምስኪን ሕዝብ ምን የተከረለት ነገር አለ? በድህነት ከመማቀቅ ፈቀቅ አደረገው ወይ? ጄኔራሎቹን ከማድለብ በስተቀር፡፡ ወያኔ ደግሞ ከናይጄሪያ መንግሥት ምን ያህል የከፋና መሠሪ ዕኩይ እርጉም እንደሆነ የምታውቁት ነገር ነው፡፡ እነ ኤፈርትንና የግል ኪሳቸውን ነበር የሚያደልቡበት እንጅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ጠብ የሚልለት እንዲት ነገር አይኖርም፡፡

እናም ነዳጅ በወያኔ ዘመን አንዲገኝ የምትፈልጉ የምትመኙ የምትሳሉ ወገኖች ካላቹህ የዮፍታሔን ስእለት (መጽሐፈ መሳፍ. 11፤30-40) እየተሳላችሁ ነውና ወዮ ለራሳቹህ! ኢትዮጵያዊ የሆነ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ያማከለ የሕዝብ ፍቅር ያለው፣ ተጠያቂነት የሚሰማው፣ ግልጽነት ያለው መንግሥት ሲኖረን ቢወጣ ግን የእያንዳንዷ የዘይት ነጠብጣብ ዋጋ በእያንዳንዱ ደሀ ገበሬ ታርፋለችና በጅቦች ተበልቶ እምጥ ይግባ እስምጥ ሳይታወቅ ከሚቀር፣ ለእኛም መሰቃያ መሣሪያ ከሚሆን “የተባረከ መንግሥት በቶሎ ለመፍጠር ተነሥተናልና የተቀደሰ ሐሳባችንን ታሳካልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃድህ ይሁንና ይሄንን ቶሎ እስክታስፈጽመን ድረስ እንደሠወርከው አቆይልን” የሚለው የዘወትር ጸሎቴ ነው፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በወያኔ እየተቦጠቦጠና ሊቦጠቦጥ ያለውን የሀገር ሀብት እንዳይቦጠቦጥ ባዶ ቀፎውን ትቶልህ እንዳይሔድ በቃ ብለህ ብትሸኘውና የሀገርህ ሀብት ለሀገር የሚውልበትንና ሀገር ያላትን ሰፊ አቅም ተጠቅማ ፈጣኑን እድገት እንድታገኝ ብታደርግ ነው የሚሻልህ፡፡

እንግዲህ በእነዚህ ሰባት ዋና ዋና ፈተናዎች ችግሮች ምክንያት በዚህ ወቅትና በወያኔ እጅ የዐባይ ግድብ መሠራቱ ለሀገርና ለሕዝብ ሊሰጠው የሚችለው ጥቅም ሳይሆን ጉዳት ነው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ግንባታ የችግሮች ቋት በሆነው በወያኔ እንዲገነባ መፍቀድ መተባበርመም ፍጹም ኃላፊነትና ማስተዋል የጎደለው ተግባር ነው፡፡

“እና መቸ ነው ጊዜው?” ካላቹህኝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎኑ ማሰለፍ የሚችል፣ የሚታመን፣ ጠባብ ያልሆነ፣ ከጎጥ ተሻግሮ ማሰብ ማየት የሚችል፣ ኃላፊነቱን በቅጡ የተረዳና የሚሰማው፣ የበቃ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲኖር መሆኑን እናንተም ለገማቹህ ፈራቹህ ትዕግሥቱን አለቅጥ አበዛቹህት እንጂ ታውቁታላቹህ፡፡ ወያኔን የምናውቀው የሀገሪቱን ጥቅምና ሉዓላዊነት አሳልፎ በመስጠቱ ለጠላቶቻችን ቅጥረኛ ሆኖ ሲሠራላቸው እንጅ ለሀገራችን ሲሠራ አይደለም፡፡

እያልኩት ያለሁትን ነገር እየተረዳቹህ ነው? ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ እንዴት ታዩታላቹህ? ምን ይሰማቹሀል? አስኪ አሰላስሉ፡፡ ወያኔ እራሱን እንደገና መፍጠርና ኢትዮጵያዊ መሆን ካልቻለ በስተቀር እንዲህ መሆኑንም በማያሻማ ሁኔታ ሊያረጋግጥልን ካልቻለ በስተቀር ምንም ተስፋ አታድርጉ፡፡ የዐባይ ግድብም ሆነ የነዳጅ ዘይት መገኘቱ ለሀገሪቱ መርገም እንጅ በረከት አይሆኑም፡፡ ወያኔ አሁን ባለበት ማንነቱ የሚሠራ ሥራ ሁሉ ለትውልደ ትውልድ የሚተላለፍ ድርብ ድርብርብ ኪሳራ እንጂ ኪሳራና ጉዳት ብቻ ነው የሚያተርፍልን፡፡

ጭፍን ሆኜ አይለም ማሳያዎቸን መከራከሪያዎቸን ይዠ ነጥብ በነጥብ የጠቀስኩ በመሆኑ፡፡ ጨለምተኛም ሆኘ አይደለም ያልኩት ሁሉ ውሸት በሆነና እኔ ጨለምተኛ ሆኜ በዚህ አስተሳሰብ የማፍር የምዋረድ ብሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ጨለምታኛ (pessimist) ላለመባል ብሎ በዲያብሎስ እጅ መሆንን ወዶ ፈቅዶ እያለ አንድ ሰው ሽ ጊዜ ተስፈኛ (optimist) ቢሆን ምን ይጠቅመዋል? ምን ጠብ ይልለታል? ጨለምተኛ ማለት ተስፋ እያለ ተስፋ ለማድረግ አለመቻል ማለት እንጅ ተስፋ በሌለበት ተስፋ አለማድረግ ማለት አይደለም፡፡

የመንግሥት ሠራተኛ የሆነና የእንጀራ ምጣዱ ከመንግሥት ጋር የተገናኘ ነጻነቱን አሳልፎ ሰጥቷልና በእጁ ለማድረግን ሲንቀሳቀስ አይታይምና “ሴትዮዋ ናት አሉ የፍል ውኃ ጠበል ለመጸበል ወደ ጸበሉ ስትገባ ፍል ጸበል ነውና ለምጥጧታል ያኔ “ዋይ!” ብላ ጮኸች ጸበልተኛው “ኧረ ተይ! እንደሱ አይባልም! እሰይ እሰይ ነው የሚባለው” ብለዋታል:: ያኔ ሴትዮዋ “የግድ እሰይ የግድ እሰይ” እያለች ተጸበለች አሉ፡፡ አሁንም የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ከዚህ የተለየ አቋም ለማንፀባረቅ ሠራተኛው ሊፈጥረው የቻለው ወይም የተተወለት ዕድልና ቁርጠኝነት የለምና “የግድ እሰይ” ነው ነገሩ፡፡
ደግሞ ሌሎች አሉ ዳቦው የራሳቸው ሆኖ እያለ አሳልፈው ሰተው ሲያበቁ ፍርፋሪ የሚለቃቅሙ፣ ፍርፋሪ ለመለቃቀም ተስፋ አድርገው ደጅ የሚጠኑ፡፡ እነዚህ ሁሉ ይሄ ያልኩት ሁሉ በሚገባ ቢገባቸውም ፈጽሞ የገባቸው መምሰል አይፈልጉም “ልማት” እያሉ ብቻ በአጫፋሪነት አብሮ የሚያጨበጭብ ነው፡፡ ለፍርፋሪ ብቻም ሳይሆን ያለመብሰልና ደካማ ሰብእናም ነው ጥቅምና ጉዳትን ትርፍንና ኪሳራን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ደምሮ ቀንሶ አካፍሎ የማስላትና የመረዳት አቅም ከማጣትም ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ ናቸው እንግዲህ የወያኔ አገዛዝ እስትንፋሶች፡፡ እንደነዚህ ዓይነቱ ዜጋ ባይበዛ ኖሮ ወያኔ 23 ዓመታት አይደለም 23 ቀናትም እንኳን የመቆየት ዕድል ባላገኘም ነበር፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop