ከሚክያስ ግዛው
እኔ እንኳን ወያኔ በፈጠራቸው ዘረኛ የክልል ስሞች አካባቢዎችን መጥራት አልፈልግም ነበር። በዘር፣ ነገድ፣ ጎሳና ጎጥ የሚወሰን የማንነት ግንባታ (identity empowerment) አፍራሽ ይመስለኛል። ብቻ ይሁን እስቲ ወለጋ፣ አርሲ፣ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ወዘተ ማለቱን ትቼ እንደው እንደዘበት “ኦሮምያ” ልበል። ኦሮምያ ውስጥ ሙስና (corruption) እንደ አንድ ፖለቲካዊ ምጣኔ ኃብታዊ ዘርፍ (political economic sector) ተቆጥሮ ዋልጌዎች ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እየተገበሩት ይገኛሉ። ይህ በደጋግና ጀግኖች ሕብረተሰብ ማህል የተደነቀረው የክፋት ገጽታ የመልካም አስተዳደር መርሆችን (good governance principles)፣ ባህላዊ ትሥሥሮችንና ሥነ-ምግባርን በማጨለሙ ሕዝቡን ለድህነት ዳርጓል። እስቲ እኔ ከታዘብኩት ውስጥ ጥቂቱን ላካፍላችሁ።
እውነት (Truth)፣ እውነት እምነት ነች። ሰዎች ስለአካባቢያቸውም ሆነ የዓለም ዙርያ እንቅስቃሴና ክንውኖች እውነቱን የማወቅ መብት አላቸው። ሰዎች እውነትን ሲረዱ ወደፊት ሊተገብሩ ስላቀዱት ዓላማ ግንዛቤ ይጨብጣሉ። በኦሮምያ የስልጣኑ ባሌቤት ኦሕዴድ ቀድሞውም ቢሆን በእብለት መሠረት ላይ የታነጸ በመሆኑ እውነት ማንጸባረቅ አይችልም። ድርጅቱ ባለቀልም የዋርካ ሥዕል ያለበት ባንዲራ እያውለበለበ ወደ ስብሰባ አዳራሽ ከመንጎድ ውጭ ፋይዳው አይታይም። በአሮምያ ክንውኖች ሁሉ ህፀፅዊ(fallacious) ወደ መሆን ደርሰዋል። በየስብሰባው ውሃ የመይቋጥሩ አረፍተሃሳቦች (fallacious arguments) ይወረወራሉ። ባለስልጣናት ሕዝቡን በመናቅ አደናጋሪና አሳሳች (deceptive, misleading ; fallacious testimony) መረጃዎችን ይበትናሉ። የውስጡ መሠረታዊ ችግር ሳይመረመር ላይ ላዩን የተድበሰበሰ (disappointing; delusive) መፍትሄ መሰል ሃሳብ ቀርቦ ስብሰባው በተዳፈነ ሠላም (fallacious peace) ይጠናቀቃል። በእርግጥ ሁሉንም በአንድ ላይ መጨፍለቅ (generalization) ተገቢ አይደለም። የለበሱትን ሕዝባዊ አደራ በንፃት የሚጠብቁ ቢኖሩም የሙሰኞቹ ጥቁር ሥራ ግን በጎ ክንውኖችን ማጉደፉ አልቀረም። እውነት – ኦሮምያ ምድር ሞታ ልትቀበር ትንሽ ቀርቷታል።
መሬት (Land)፣ መሬት በሕዝባዊ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ስትውል ልማት ባግባቡ ይፋጠናል። በሃገራችን የመሬት ጉዳይ የፍትህ ጉዳይ አልፋና ኦሜጋ ነው። የተፈጥሮ ኃብት (Natural resources) ከጉልበትና ዓዕምሮ (labour and mental) ጋር ሲዋሃድ ምርትን (production) ያስገኛል። መሬት የተፈጥሮ ኃብት ዋነኛ መፍለቅያ ምንጭ ነች።
ማንም ሠላምንና ጸጥታን፣ ልማትንና እድገትን የሚፈልግ ስብስብ የመሬትን ጉዳይ ፍትሃዊ (justify) ለማድረግ ሲል ጠቃሚ መሠረታዊ ህጎችን (system of rules)በቅጡ ይቀርጻል። ይህ ጉዳይ ፈጽሞ ተግባራዊ መሆን ካልቻለ ጥቁር ገበያዎች (black markets) እንደ አሸን ይፈላሉ። ጥቁር ገበያ በሙስና (Corruption) የሚመራ ፖለቲካዊ ምጣኔ ኃብታዊ ፍዳና ዕዳ ነው። መሬት የመንግሥት ኃብት እንዲሆን ፈላስፎችና የምጣኔ ኃብታዊ ሊቆች እጅግ ሠፊ ሳይንሳዊ ትንታኔ ሠጥተዋል። “መሬት ላራሹ” በኢትዮጵያ ተራማጆች ዙርያ ዘወትር ሲነሳ የቆየ ታሪካዊ መፈክር ነበር። የተጨቋኖችና አጋሮቻቸው እምቅ አስተሳሰብ የወለደው ይህ ታሪካዊ መፈክር ተንቆ ይባስኑ የኦሮምያ መሬት የቀማኞችና ሙሰኞች መገልገያ ሆኗል። በኦሮምያ መሬት አሞሌ ጨው ተሸክሞ ለመጣ ሁሉ በቀላሉ እንደምትቸረቸር ኮማሪት ተንቃለች። መሬት “በሶስተኛ ደላሎች” ስም እንደዋዛ የምትለወጥ ጉቦኛ ባለሥልጣናትና መዝባሪው ነጋዴ የሚሻሟት አሳዳሪ የራቃት ባለቤት አልባ ሆናለች። መሬት በኦሮምያ ምን ያልሆነችው አለ? አሜሪካ የተፈጠረችው በቀይ ሕንዶች ደም ላይ ነው። አሜሪካ የተገነባችው በአፍሪካውያን ባርያዎች ግፍና ሰቆቃ ነው። ይህን ግፍ የዲሞክራሲ ቋሚ ምሰሶ ወይም ዓምድ አይደለም። ገዥው መንግሥት ሰዎችን በፌደራል ፖሊስ ጥይት ካስገደለ በኋላ “ለዲሞክራሲው ግንባታ ገና ነን፤ አሜሪካ እስከ ስድሳዎቹ መባቻ ድረስ ሰዎች ይገደሉ ነበር” ብሎ ያወራል። አገዛዙ ልማቱን እየዘረፈ፣ ሰዎችን እንደ ቀይ ሕንዶች ከቀዪአቸው እያፈናቀለ፣ ጥሬ ሃብቱን ለባዕድ እየቸረቸረና “መሬቴን አትንኩ” ያሉትን ነዋሪዎች እያሽመደመደ “ዲሞክራሲው ገና አልጎለበትም” ብሎ ያሾፋል። ይህን ትምህርት የቀሰሙት ከሱዛብን ራይስ ከሆነ ያሳዝናል። መልካሞቹን የዲሞክራሲ እሴቶችና የመልካም አስተዳደር መርህን ካደጉት ሃገሮች ተሞክሮ እየቀሰሙ ማዳበር ሲቻል መሬትን ለመቀራመት ብሎ ተወላጁን፣ አገር በቀሉን (indigenous) መግደል የዲሞክራሲ ባህሉም ወጉም አይደለም።
ኢንቨስትሜንት፣ (investment) እኔ ራሴ investment, establishment, department, እንደው ምናለፋችሁ «ment» ያለበት እንግሊዘኛ ሲነገር እፈራ ነበር። ግናስ የሠፈራችን አንድ አጉራ ዘለል “ኢንቬስተር” ተብሎ ከውጭ ሲመጣ ቃሉን ተለማመድኩኝ። ምን ሊቨሰትር ነው? ብዬ ስጠብቅ አቀባባይ ረድፈኞችን በእንግሊዘኛ ደልሎ አስደልሎ መሬት ጨመደደ። መሬቱን ደግሞ ሸጦ ገንዘቡን መሬቱን ከሰጡት ከባለስልጣናት ጋር ተካፈላው ሲባል ሰማሁ። በኦሮምያ ብዙ ኢንቬስተሮች ይስተናገዳሉ። ከባለሱቁ አንስቶ እስከትላልቅ ሳሙና፣ ዘይትና ብስኩት ፋብሪካ ድረስ በሙስናው ማህደር ተመዝግቦ በጉቦኛው ማህተም ይለፍ የተመታለት የንግድ ተቋም ሁሉ “እንቬስትሜንት” ተብሎ ይወደሳል። ባንዳንድ አካባቢዎች የኢንቬስትሜንቱ ባለቤቶች (clandestine wealth) “የማይታዩት ባለስልጣኖች” ወይንም ተባባሪዎቻቸው ሲሆኑ የንግድ ፈቃዱ የተመዘገበው ባንድ ጭቁን የኢንቬስተሩ ሎሌ ነው። ይህ ዘመናዊ የሎሌነት ሥራ የተቀዳው በቅኝ ግዛት ሥር ከነበሩት የአፍሪካ ሃገሮች ነው።
ስብሰባ (session)፣ አስተማሪያችን “ስብሰባ ሎጂክ (logic) መጠቀምያ ጠቃሚ ጊዜ ነው” ሲሉ እሰማ ነበር። የፍርድ ሸንጎ ሠብሳቢ የነበረው አጎቴ ደግሞ “የስብሰባ አዳራሽ ዝም ብሎ ተሰባስቦ እንቅልፍና ራስ ምታት መሸመችያ ቦታ አይደለም” ይል ነበር። ሰው ከተሰበሰበ ንድፈ ሃሳብ አፍልቆ፣ እልባት ያለው ውሳኔ ሸክኖ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አለበት (Theory + practice = Praxis)። ኦሮምያ ስብሰባ ታበዛለች። በሃያ አምስት ዓመታት ኦሮምያ ያስተናገደችው ስብሰባ በሜትር ሲለካ የዓለም ሊግና የተባበሩት የዓለም መንግሥታት ማህበር ካደረጉት ስብሰባ በሶስት እጥፍ ይበልጣል። ምን ንድፈ ሃሳብ ተወረወረ? ምን ተወሰነ? ምን ተፈየደ? ምንም። በእርግጥ እድሜ ለሙስና ሠማይ ጠቅስ ሕንጻዎች ቆመዋል፣ ጥሬ ኃብቱንና ምርቱን ማጓጓዣ ይሆን ዘንድ መንግሥት ዘመናዊ መንገድ አንጥፏል። የሕዝቡ ኑሮ ግን አልተሻሻለም። የሕዝቡ ባህልና እሴቶች ተደፍጥጠዋል። ተሰብሳቢዎች የሙስናንና ጉቦ መርሆችን በሰምና (wax) ወርቅ (gold) አሽሞንሙነው ይለያያሉ። ሰሙ “ሙስና ይጥፋ” ሲሆን ወርቁ ደግሞ”ሙስና እጥፍ ይሁን” ነው። የመናገር ችሎታ፣ በእጅ የመሄድ አክሮባትና ድፍረት መለማመጃ የሆነው የኦሮምያው ሙስና ወለድ ስብሰባ ብዙ ገንዘቦች አባካኝ ጎጂ ባህል እየሆነ መጥቷል። ሃቀኛ ነጋዴዎች የመንግሥት ገቢ ለመክፈል ማለዳ ወደ አገር ውስጥ ገቢ ሲሄዱ “ፋይሉ አልተገኘም” ተብለው በኪራይ ሰብሳቢዎች ይባረራሉ። ችግሩን ለማን አቤት ይባላል። አለቆች ስብሰባ ላይ ናቸው። ሃቀኞች ዓመታዊውን ግብርና መንግሥት የደነገገውን ቫት ለመክፈል እንኳን ተቸግረዋል። የመንግሥትን ገቢ ለማስገባት ሙስና ለምን አስፈለገ? ፋይሉ ጠፍቷል በመባሉ ምክንያት ግብር የተቆለለበት ሃቀኛ ነጋዴ ሲጉላላ ማየቱ አሳዛኝ ነው። ይህ ክፋት ኬንያና ናይጄርያም እንኳን አልተከሰተም። በኦሮምያ “ስብሰባ” ሙስናን ማጠናከርያና ኪራይ ሰብሳቢዎችን ማሰልጠኛ ሠንበቴ ከሆነች ሰነበተች።
ፍትህ (justice)፣ በኦሮምያ ፍትህ ደብዝዛለች። ደብዳቢውና ተደብዳቢው ፖሊስ ጣብያ ቢሄዱ ተደብዳቢው ይታሠራል። ዘራፊና ተዘራፊ ሸንጎ ፊት ቢቀርቡ ተዘራፊው ተሸማቆ ከእልፍኙ በአፋጣኝ እንዲወጣ ይደረጋል። ዳኛና ጠበቃ የጥቅም ትሥሥር አድርገዋል። ፍርደ ገምድል ዳኛው የባለጉዳዩን ሳይሆን የጠበቃውን እጆች ያያል። ደህና ጉቦ ሰጪ ጠበቃ ዝናን ያተርፋል፣ በርካታ ደንበኞች ያፈራል። ለፍትህ የቆሙ ጠበቆች ደግሞ ሥራ ፈተዋል። “ፍትህ ይስፈን” እያሉ ሲጮኹ ሙሰኛው ዳኛና መሠሪው ጠበቃ ይሳለቁባቸዋል። ፍትህ በኦሮምያ እጅግ ተረግጣለች። ታድያ በአቋራጭ ለመክበር ኢፍትሃዊ ነገሮችን ሳይፈሩ መፈጸም እየተለመደ መጥቷል። በኢፍትሃዊ አሠራሮች ልምድን የቀሰሙት ደላሎችና አቀባባዮች የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ። እነርሱ ለዳኞችና ጠበቆች ሐሰትን አደልቦ እንደምን ማሸነፍ እንደሚቻል ህግን ሳይፈሩ፣ ሰውን ሳያፍሩ ምክር ያካፍሏሉ። ክፉዎች የምክር አገልግሎት በሚሰጡባቸው ቢሯቸው ውስጥ የፍትሃብሄር ህግና መጽሃፍ ቅዱስ ሁለቱም ጠረቤዛው ላይ ተቀምጠዋል። እግርግዳው ላይ ደግሞ “እግዚአብሄር ያያል” የሚል በእንግሊዘኛና ኦሮምኛ የተጻፈ ጥቅስ ተሰቅሏል። አይ ዘመን!
አቀባባይ ረድፈኛ ሚና (liaison role between the corruptor and corruptors of public officials) አቀባባይ ረድፈኛ (እንደ ራሴ አተረጓጎም) በሙያው ደላላ ያልሆነ ስልታዊ ደላላ ነው። ከደላሎች የሚለየው ነገር ቢኖር ባለስልጣኖችን በጥቅም አሳውሮ መቅረብ መቻሉ ነው (dangerous liaison)። የመናገርና የማሳመን ፣ የማዘበራረቅና የማዛባት ችሎታ የተላበሱት አቀባባይ ረድፈኞች አገዛዙ ባመቻቸው የሙስና መሠላሎች ወደ ላይ የወጡ የዘመኑ አራዶች ናቸው። እነዚህ አቀባባይ ረድፈኞች ጉቦ ሰጪንና ጉበኛን፣ ሠነፍ ተማሪንና ቦዘኔ አስተማሪን፣ ባለስልጣንንና አራጣ አበዳሪውን፣ ፍርደገምድል ዳኛውንና ቆቁን ጠበቃ፣ ወዘተ፣ አገናኝ ናቸው። ካለነዚህ አቀባባይ ረድፈኞች እገዛ ውጭ ባለስልጣን ሊመዘብርና ሙስና ሊቀበል ያዳግተዋል። መሥሪያ ቤቶችን ሁሉ የሙስናና ምዝበራ አርማ ተሸካሚ ያደረጉት እነዚህ በስልታዊ ብረዛ ሳይንስ የተካኑት አቀባባይ ረድፈኞች ዋዛ አይደሉም። ህግና ፍትህ ሚኒስቴር – ሙስናና አድልዎ ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴር – የምዝበራ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር – መሃይምነት ማስፋፍያ ሚኒስቴር፣ መከላከያ ሚኒስቴር – የጨረታና መሬት ሽሚያ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር – የዋጋ ንረት ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር – ኢንቬስትሜንትና ሃዋላ ሚኒስቴር፣ የእርሻ ሚኒስቴር – እንጀራና በርበሬ ላኪ ሚኒስቴር፣ ወዘተ፣ እንዲሆን ሚናውን የተጫወቱት መለኞች ከአስመጭና ላኪዎቹ ወይም ሕንጻ አከራዮቹ ባለስልጣኖች ቢሮ ላፍታም ቢሆን የማይርቁ የሙስናና ዝርፍያው ተቋም (kleptocracy) ባለውለታዎች ናቸው።
ቋንቋ (mother tongue)፣ በኦሮምያ ኦሮሚፋ ብቻ ነው የሥራ ቋንቋ። ልጆቿ ሌላ ክልል ሄደው መሥራት አይችሉም። እሷም ከትግራይ ወይም አማራ አልያም ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ ወይም ደቡብ ክልሎች የሚመጡትን ልጆች አታስተናግድም። አትድረሱብኝ – አልደርስባችሁም – ብላለች። ኦሮምያ አማርኛ ቋንቋን እንደ መጨቀኞ መሣርያ ያህል በመጥላትዋ ሳብያ አፈሯን ፈጭተው፣ ውሃዋን ጠጥተው ያደጉትን ኦሮምኛ የማይችሉትን አንጡራ ልጆቿን እንኳን የጉዲፈቻ ዜግነት ከልክላቸዋለች። ኦሮምያ – አማርኛ የነፍጠኞች ቋንቋ መሰላት እንጂ የጋራ መግቢያብያ ቋንቋ ልማትን እንደሚያፋጥን ቴክኖሎጂንም እንደሚያስፋፋ አላጤነችም። አማርኛ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ ለብዙ ዓመት ማገልገሉ ማንንም ባልጎዳ ነበር። የሆነስ ሆነና የኢትዮጵያ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ እንግሊዘኛ መሆኑስ ይታወቃል? ኦሮምያ ይህን የልማት እንቅፋት ሽራ ይልቅስ ብዝህነትን በማስተናገድ የኢትዮጵያ አንድነትን ማጠናከር ቀዳሚ ሚናዋ ሊሆን ይገባል።
ባጠቅላይ ሃቀኝነት፣ ደግነት፣ ፍትሃዊነት፣ ሙስናንና ጉቦን መጸየፍ – እነዚህ የሕዝቡ የመልካም ባህርይ መገለጫ የሆኑት እሴቶች በኦሮምያ ውስጥ ወደ ጉሮኖ ተወርውረዋል። እነዚህን እሴቶች ዳግም ሊያንጸባርቅ የሞከረ ሁሉ መሳለቅያ ይሆናል። ኬንያና ናይጄርያ በሙስናና ጉቦ ጫፍ ላይ የደረሱ ሃገሮች እየተባሉ ሲነገር ቆይቷል። ኦሮምያ ደግሞ በጥቂት ዓመታት ክብረወሰኑን አልፋ የሙስናና ጉቦ ፍልስፍና የተሃድሶ ምድር እንዳትሆን ያሰጋል። ይህን የመሳሰሉት ግፎች ናቸው ዛሬ ሕዝቡን ለአመጽ ያነሳሱት። የፍትህ መዛባት፣ እስር፣ ግድያና የምጣኔ ኃብቱ ይዞታ ልዩነት ካልተገደቡ በቀር ሕዝቡን ለመብቱ ከመታገል የሚያቆመው አንዳች ኃይል የለም። የፌደራል መንግሥቱ እጆች “አመድ አፋሽ” ወይም የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ እንዳሉት”የኢትዮጵያ ሕዝብ ወርቅ ቢያነጥፉለት…”ሆኖ አይደለም ይህ ሁሉ አመጽ የበረከተው። ሙስናው፣ የአስተዳደር በደሉ – ኑሮውን አናግተውበት – በድህነትና ሰቆቃ ጅራፍ መገረፉ፣ በአምባገነኖች (tyranny, timocracy, oligarchy, plutocracy) ውሳኔ ብቻ መነዳቱ አልበቃ ብሎ ቀማኞች መሬቱንና የመሬቱን የተፈጥሮ ገጸበረከት በጠመንጃ አስገድደው (military command) በጠራራ ፀሃይ ስለሚዘርፉት እንጂ። የእርምቱ እርምጃ ከሰላው ጫፍ ይጀመር።
ጥቂቶቹ የትግራይ ሕወሓት መሪዎች ለም የሆኑትን የጎንደርና ወሎ አጎራባች መሬቶች በማናለብኝነት ተነሳስተው ወደ ትግራይ ክልል መደባለቃቸው ያስከተለውን አደጋና የህዝብ ቁጣ በሚቀጥለው ጊዜ እዘግባለሁ።
እግዚአብሄር ቸር ዘመን ያምጣልን፣ አሜን