ልጆች ሆነን ታላላቆቻችን ጉልበት አለን ብለው በደል ሲፈጽሙ ‹እግዚአብሔር በቀዳዳ ይየው!› እንል ነበር፤ ለመርገምም እየፈራን አንዲያው ድርጊቱ እንዲመዘገብልን ማሳሰባችን ይመስለኛል፤ አሁንም እንደዚያ ለማለት ይቃጣኛል፤ ግን አግዚአብሔር በሰማይ ላይ መኖሩን፣ በእያንዳንዳችን ውስጥ መኖሩን የቤተ ሃይማኖት ሰዎች እንኳን ማመናቸው በሚያጠራጥርበት ዘመን ለዓለማዊ ባለሥልጣኖች የእግዚአብሔርን ስም ማንሣት ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፤ ሆኖም እኔ ስለማምንበት የራሴን አሳውቃለሁ፤ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር አገር ነች፤ ኢትዮጵያን ጎድቶ የተጎዳ እንጂ የተጠቀመ የለም፤ ኢትዮጵያን አዳክሞ የደከመ እንጂ የበረታ የለም፤ ኢትዮጵያን አደህይቶ የደኸየ እንጂ የበለጸገ የለም፤ ኢትዮጵያን አዋርዶ የተዋረደ እንጂ የተከበረ የለም፤ ይህ የታሪክ ሐቅ ነው፡፡
የኢትዮጵ ባለሥልጣኖች ዓላማችሁ ምንድን ነው? እስከዛሬ ድረስ በየትም አገር በሰማይ ጠቀስ መቃብር ውስጥ የተጋደመ ባለሥልጣን የለም፤ ደግሞስ ሰማይ ጠቀስ መቃብር ካስፈለገ ለአንድ ባለሥልጣን ከነቤተሰቡ ስንት ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ ስንት ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ያስፈልጉታል? ከዚህ በፊት ምጽዓት በሚል ግጥም የሚከተለውን አመልክቼ ነበር፡፡
ከራስ በላይ ነፋስ ትልቁ ሃይማኖት፤
ዘረፋን ሲያውጀው ቂም ሲያስረግዝ ጥቃት፤
ዓይን አያይም አሉ፤ ጆሮም አያዳምጥ፤
ተለጉሞ አንደበት ሁሉም ይዞታል ምጥ!
በቁንጣን፣ በስካር ጥቂቶች ሲንሩ፣
ብዙዎቹ ደግሞ በረሀብ መንምነው በቁንጫ ሲያርሩ፣
የደሀ እንባ ሲጎርፍ መሬቱ ሲሸበር፣
ዝብርቅርቁ ወጣ፤
ሕይወት ትርጉም አጣ፤
ኧረ የት ነው ጉዞው ዓላማው ምንድን ነው?
ቀድመው የሄዱትን ምነው አናያቸው?
የት ገቡ? የት ጠፉ? ፋና እንኳን አይታይ፤
ብልጭ የሚል የለ ከመሬት ከሰማይ!
መንገዱ ጠበበ፤ ትርምስምሱ በዛ፤
እሪታው ኡኡታው ቀለጠ እንደዋዛ!
መሬቱም ዓየሩም በክፋት ጠነዛ!
ጥላቻና ቂሙ በሰፊው ተነዛ፡፡
እምቢልታው ሲጣራ ነጋሪት ሲያገሳ፣
የአለው ሁሉ ሞቶ የሞተው ሲነሣ፣
ምጽዓት መድረሱ ነው ሊስተካከል ነው ፍርድ፤
በግና ፍየሉ ሊለዩ በገሃድ!
እንደሚመስለኝ በአሁኑ ጊዜ ይህንን አቅጣጫ ማየት የሚያዳግተው ሰው በራሱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በቤተሰቡና በአገሩ ሕዝብ ላይ መቅሠፍትን የሚጠራ ነው፤ እየተማረርን ነው፤ የርኅራኄ ወዛችን እየደረቀብን ነው፤ መጨካከን እንደጀግንነት እየተቆጠረ ነው፡፡
በሌላ ሞት ማለት በሚል ግጥም፡–
ሞት ማለት፡-
አለመናገር ነው፤ ጭው ያለ ዝምታ፣
የመቃብር ሰላም የሬሳ ጸጥታ፤
ደሀ በሰሌኑ ሣጥን ገብቶ ጌታ፤
የውሸት ልዩነት ተጋድሞ በተርታ!
እኔ እንደምገምተው ጉልበተኞች የሆናችሁ ሁሉ ዓላማችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዓላማ የተለየና በቅራኔ ላይ ያለ አይመስለኝም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብልጽግና፣ እድገትና ክብር የናንተም ነው፤ በየትም አገር ስትሄዱ የሚነጠፍላችሁና የሚጨበጨብላችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመወከላችሁ ነው፤ ዛሬ በአውሮፓና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ክብርና በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረው ክብር በጣም የተለየ ነው፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ያገኙትን ክብር ከሳቸው በኋላ የመጡት አላገኙትም፤ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አዋርዶ ከየትም ክብርን ማግኘት አይቻልም፤ የራስን ሕዝብ ንቆ መከበር አይቻልም፤ የራስን ሕዝብ አንገቱን አስደፍቶ ቀና ብሎ መሄድ አይቻልም፡፡
እስር ቤቶችን ሁሉ ዝጉ፤ የዘጋችሁትን አንደበት ሁሉ ልቀቁ፤ ያፈናችሁትን አእምሮ ሁሉ ለነጻነት አብቁት፤ ጭካኔን በርኅራኄ፣ ጉልበትን በእውቀት፣ ዱላን በክርክር፣ ቁጣን በፍትሐዊነት እየለወጣችሁና እያበረዳችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታረቁ፤ በተለይ ከኢትዮጵያ ወጣት ጋር ልብ ለልብ ተገናኙ፤ ነገ የወጣቱ ነው፡፡
አይተናል፤ አንበሶች ነን የሚሉ ቀሚስ ለብሰው ሲሸሹ! አይተናል፤ አለኛ ማን? እያሉ ሲወጠሩ የነበሩ እንዳይጥ በጓሮ ተደብቀው የሙጢኝ ሲሉ! አይተናል፤ ጀግኖች ነን ብለው ሲያቅራሩ የነበሩ በየፈረንጅ አገሩ አንገታቸውን አቀርቅረው ትሕትና ሲማሩ! አይተናል፤ የዘረፉትን ሁሉ ሳይበሉ፣ ሳያጌጡበት ሲቸገሩ! አይተናል! ሰምተናል አይደለም አይተናል!
ሌላ ዙር ግፍ ቂምን እየወለደ፣ ቂም በቀልን እየወለደ፣ በቀል አዲስ ግፍን የሚወልድበት ሁኔታ ሲፈጠር ለማየት አንፈልግም፤ በቃን ግፍ! በቃን ቂምና በቀል! በቃን እየተዋረደ የሚያዋርደንን ማየት! በቃን መንፈሳዊ ወኔ በሌላቸው ጉልበተኞች መነዳት! በቃን ጠመንጃቸውን ሲነጠቁ አይጥ የሚሆኑ አሻንጉሊቶች! በቃን በደሀ ጉልበት ጉልበተኞች፣ በደሀ ሀብት ሀብታሞች መስለው የሚታዩ ኅሊና-ቢሶችን መሸከም! እስቲ እኛ ደካማዎቹ ሰዎች እንሁን! አስቲ እናንተም ጉልበተኞች ሰዎች ሁኑልን! እንደሰዎች በሰላም እንድንነጋገር ድፍረቱን፣ መንፈሳዊ ወኔውን ከቅን መንፈስ ጋር እንዲሰጠን እግዚአብሔርን እንለምነው! ክፋትን እንሻረው! ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው ‹‹ለክፉዎች ሰላም የላቸውም፤ ይላል እግዚአብሔር፤›› እንዳይሆንብን!