መገናኛ ብዙሃንን መቼ እና እንዴት መጠቀም እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ግን እንደ በረሃ ተኩላ እያደፈጠ ይናከሳል። ሲናከስ ደግሞ ማንንም አይምርም። ውለታ የሚባል ነገር አያውቅም። ይሉኝታ አይነካካውም። እፍረትም በእርሱ ዘንድ የለችም። ከቶውን መቀበል እንጂ መስጠትን አያውቅም። አስር ተቀብሎ በዜሮ የሚሸኝ ጀግና ነው። በዚህ ተግባሩ አድናቂው ነኝ። “እኔ-ነኝ” ያለ የዲሲ ፖለቲከኛን ሳይቀር ከአንዴም ሁለቴ እንደማስቲካ እያኘከ መትፋቱን እንመሰክራለን። የጡት አባቱ የሆነው ኦነግንም ቢሆን ‘A Critical Assessment of the Oromo Liberation Front” በሚለው መጣጥፉ እንዳይሆን እንዳይሆን አድርጎ የጠረበ ፍጡር ነው። ይህ ሰው እንደገና ተመልሶ የ”ነፍጠኛውን ሜድያ” ለመጠቀም የማይሞክርበት ምክንያትም የለም።
ጃዋር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ብቅ ያለው በቅርቡ ነው። በመጀመርያም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተማረባቸው ዱሙጋም እና ጭላሎ፣ አዳማም ሆን ሲንጋፖር ሆኖ ድምጹ አልተሰማም። የፖለቲካ ሂሳቡን ሰርቶ ሲያበቃ የበግ ለምድ ለብሶ ብቅ አለ። በሚኖሶታ ያለመውን ቅዠት ይዞ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ሲደርስ ባነነ። እዚያው ላይ ፈነዳ። ከዚያ በፊት ስሙም ተሰምቶ አያውቅም። እስከ ዲሲ ጉዞ ድረስ የኦሮሞ ህመም አይሰማውም ነበር። “ትንሽ ቆሉ ይዞ ወደ አሻሮው… “ እንዲሉ የኦሮሞነት ጆከሩን ይዞ ፖለቲከኞችን እና መገናኘ ብዙሃኑን መቅረብ ነበረበት። እነሱም ከሚገባው በላይ አስተዋወቁት። በደንብ አድርጎ ቦነሳቸው። ምሁር በሃገር የጠፋ እስኪመስል ድረስ መድረኩን እሱ በቻ ተቆጣጠረው። ቪ.ኦ.ኤ.፣ አልጃዚራ፣ ሲ.ኤን. ኤን፣ እና ዶች ቬለ ላይ ሳይቀር እየወጣ የኛን እጣ ፈንታ እስኪበቃን ነገረን። “ወጣቱ ምሁር” አንቱ የተባለ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተንታኝ ሆኖ ከረመ። ድምሩን ካወራረድ በኋላ ፊቱን አዞረ። አዟዟሩ አደገኛ ነው። የፍሬቻ ምልክት ሳያሳይ እንደሚታጠፍ መኪና አይነት። “ይህ ሰው በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጫነው ዲግሪ ነው ወይንስ ድንጋይ?” እስኪያስብል ድረስ በዘርና በሃይማኖት በፖለቲካ ፈነዳ።
ባጣ ቆዩን ትግል ሲቀላቀል ለአፍ ሟሟሻው አጼ ምኒሊክን አነሳ። የእምዬ ምኒሊክ አጽም እና ሃውልት ላይ ክተት አወጀ። ግዜ የሰጠው ቅል… እንዲሉ እንጂ የመላው ጥቁር ሕዝብ ማንነት መነሻ የሆኑት ምኒሊክ በሱ አፍ የሚጠሩ እንኳን አልነበሩም። ዳሩ መነሻውን የማያቅ መድረሻ የለውም። ሁለት አይን ያለው፤ ከሁለት አቅጣጫ ይመለከታል። ሁለት ጆሮ ያለውም ሁሉንም አመዛዝኖ ይሰማል። አንገት ያለው ደግሞ አዙሮ ያለፈውን ይመለከታል። ያለፈው ከሌለ የወደፊቱ ከምን ሊነሳ? ጃዋር በአምሳሉ የፈጠራቸውን ምስለኔዎችን በሱ የፖለቲካ ዜማ ቃኝቶ ሲያበቃ በፓልቶክ ክፍሎች አሰማራቸው።
ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ ገና ነብስ ያላወቁ ሕጻናትን ፎቶ በማህበራዊ ድረ-ገጾች እየበተኑ ለራሳቸው የፖለቲካ ግብ መጠቀም መሞከራቸው ነው። በሞራልም፣ በስነ-ምግባርም ሆነ በባህል ፍጹም ነውር የሆኑ ነገሮችን እያሰሙን አብረን ከረምን። በቃ! የጃዋር ፖለቲካ ይኸው ነው። ይህ ነው የሱ ጀግነነት። ምኞቱ ጀግና መሆን ከሆነ ደግሞ ቦታው ሚነሶታ አልነበረም። ስለ አመጽ የሚሰብክ ወንድ ልጅ መኖርያው ልክ እንደ አንበሳ ከወደ በረሃው ነው።
ይህ ሰው በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረውን አንድ ጽሁፍ ካነበብኩ በኋላ፤ ለዚያ አሳፋሪ ጽሁፍ ምላሽ በመስጠት እና ባለመስጠት ላይ ከራሴ ጋር ሙግት ገጥሜ ነበር። በጃዋር ገጽ ላይ የሰፈረው በዚያ አስጸያፊ ጽሁፍ ያልቆሰለ ቢኖር ጉዳዩ ያልገባው ብቻ መሆን አለበት። በእርግጥ ሌሎች እንዳደረጉት ነገሩን ንቆ መተው ይቻላል። ታድይ የሰው ዝምታ እንደስምምነት የተወሰደ ይመስል የሰውዬው ሙቀት እየጨመረ ሄደ። በተቀረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ላይ የጥላቻ ዘመቻውን ገፋበት። በዓድዋ እና የአጼ ምኒሊክን ቅኝት በአዲስ ዜማ ይዞ ዳግም ብቅ አለ። እንደራሴውን በስውር እየሰበሰበ በባንድራችንና በኢትዮጵያዊነት ላይ ዘመቻ አቀደ። ይህንን በሰፊው እመለስበታለሁ።
በፌስቡክ ገጹ ላይ የሰፈረው የጃዋር መልእክት እንዲህ ይነበባል፤
…Enjoy the show, the bill is on us… ወደ አማርኛ በግርድፉ ሲመለስ “(የኦሮሞ አመጽ) ትዕይንቱን እያያችሁ ተዝናኑ። ሂሳቡን በኛ ተውት።” እንደማለት ነው።
አሳዛኙን የኦሮሞ ወገኖቻችን እልቂት ነው ተዝናኑበት እያለን ያለው። ይህንን አሰቃቂ ድራማ ከሚነሶታ ሆኖ ሲመለከተው አስቂኝ ነው የሆነበት። እሱ ምን አለበት? እሳቱ ውስጥ አልገባ። ወላፈኑም ፈጽሞ አይነካው። ምሰቆቃውን እንደ ሆሊውድ ፊልም ቁጭ ብሎ መመልከቱ ሳይንሰው ሌሎችንም በራሱ ወጪ ለመጋበዝ የሚዳዳው ደፋር። ይህ ስላቅ ነው ወይስ ፌዝ? ከሞቀ ቤቱ መሽጎ በሰው ልጅ ሰቆቃ መቀለዱ አንድ ነገር ነው። ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ በዚህ ጽሁፍ ስር ድጋፋቸውን የሚገልጹ እንደራሴዎቹ ብዛት ነው። ሰው በዘር ፖለቲካ ሰክሮ ማሰብና ማገናዘብ ተስኖታልም ያሰኛል። ጽሁፉ በግልጽ እንደሚያስረዳው እየተካሀደ ያለው እልቂት ላይ ጃዋር ማፌዙ አልገባቸው ይሆን? በዚያው የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የሚወጡ ዘግናኝ ፎቶዎችን እየተመለከተ የሚዝናና ሰው ካለ ይህ ጤነኛ አይደለም። የአእምሮ ችግር ያለበስ ሰው እንኳን በዚህ አይነቱ የሰዎች ሰቆቃ የሚዝናና አይመስለኝም። ግን የዚህ ሰው ፍላጎት ምን ይሆን?
በዚያ ሰሞን ወዳጄ ሄኖክ የሺጥላ የለቀቀው ጽሁፍ ጃዋርን በደንብ አድርጎ ይገልጸዋል።
“እንጀራውን” በተገፉ እና በተከፉ ሰዎች ታሪክ ላይ ያደረገ ሰው ፣ ህይወቱን በሰዎች መከራ ላይ የገነባ ፣ ኑሮውን ባጋጣሚ ለድምጽ አልባ እና አቅም አልባ ወገኖቹ ለታይታ የሚቆጭ…. ራሱን ትልቅ ለማድረግ፣ ከፊት ሆኖ ለመታየት እና ለመግነን ማናቸውንም አይነት ክፋት ከመፈጸም ልቡ ተው የማይለው ሰው። ሲል ሄኖክ ይገልጸዋል። እኔም ጃዋርን ከዚህ በተሻለ አልገልጸውም።
ሲጀመር እየተካሄድ ባለው የኦሮሞ ወንድሞቻችን የመብት ትግል ውስጥ የእነ ጃዋር እጅ መግባቱ አብዛኞችን ጥርጣሬ ውስጥ ከትቷል። ምክንያቱም ግልጽ ነው። የኦሮሞ ወጣቶች እና ገበሬዎች ስለ መብት ሲሟገቱ የእነ ጃዋር አጀንዳ ደግሞ ሌላ በመሆኑ።
የኦሮሞ ተማሪዎችና ገበሬዎች ይዘውት የተነሱት ጥያቄ አግባብ ያለውና በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊደገፍ የሚገባው ጉዳይ ሆኖ ሳለ ሌላው ወገን ዳር ቆሞ የመመልከቱ ምስጢር ግልጽ ይመስላል። እነዚህ ወገኖች መብታቸውን ለማስከበር የማያባራ ትግል እያደረጉ ባሉበት ወቅት እነጃዋር በረጅሙ ምላሳቸው ሌላውን ወገን የሚያስበረግጉ መፈክሮችን ይዘው ብቅ አሉ። “ኦሮሚያ ለኦሮሞ!” እና “የክርስትያኑን አንገት መቁረጥ!” መፈክር!
እርግጥ ነው። ጃዋር ረጅም ምላስ አለው። ወገን የሚሻው ደግሞ ረጅም ምላስ ሳይሆን ረጅም ጭንቅላት ነበር። የሁለቱ ልዩነት የትየለሌ ነው። ረጅም ጭንቅላት አርቆ ሲያስብ ረጅም ምላስ ደግሞ ከሩቅ ይስባል። እንደ አለመታደል ሆኖ ባለ ረጅም ምላሶች የህዝብን የመብት ጥያቄው እየነጠቁ በራሳቸው አጀንዳ ይተኩታል። እናም የዚህ ትግል ውስጥ ሌላው ወገን ተመልካች ብቻ እንዲሆን ያደረጉት ጃዋር እና በሱ የፖለቲካ ቅኝት ውስጥ ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ይዘውት የተነሱት መፈክር ሌላውን ወገን ባያስበረግግ ነበር የሚገርመው። አንዳንድ ቦታዎች የጃዋርን መፈክር የያዙ ሰልፈኞችን የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ማሰማራታቸውን ማስተዋሉ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል።
በአንድ ወቅት በጃዋር የሚመራ ይህ ቡደን ዋሽንግተን ዲሲ ስቴት ዲፓርትመንት በር ላይ ቆሞ፣ “Ethiopia out of Oromia”! “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ጥውጣ!” እያለ ፈረንጆችን ይማጸን የነበረበትን ማስረጃ ከዩቱብ ላይ መመልካት ይቻላል።
በሌላ ግዜ ደግሞ “…እኔ በምኖርበት አካባቢ ቀና የሚል ክርሲያን ከተገኘ አንገቱን በሜንጫ ቆርጠን እንጥላለን::”
ሲል የአይሲስን አንገት ቆረጣ በአደባባይ ያበሰረ ሰው ነው። እዚህ ላይ ልብ በሉ። ወንጀል የሰራን ክርስትያንን ሳይሆን “ቀና የሚል” ከተገኘ ነው እናርዳለን ያለው። ልቡ ያሰበውን እና አእምሮው የሚትያሰላስለውን ነው ያፈነዳው። የተናገረው በስህተት እንኳን ቢሆን ንግግሩን ባስተባበለው ነበር።
ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር አንድ ምሽት በአምስተርዳም ስንጫወት፣ “በእርግጥ ጃዋር መሃመድ የክርስቲያን አንገት እቆርጣለሁ ብሎ ተናግሯል?” ሲል ጠየቀኝ። አብሮን የነበረው ገረሱ ቱፋም “ንግግሩን ከኮንቴክስት መረዳት አለብን…” እያለ ሲያስረዳ ሞከረ። ገረሱ ቱፋ በዩኒቨርሲቲ ለኦሮሞ መብት ሲታገል ቆይቶ በኋላም በአስመራ በኩል ሞክሮ ሲያበቃ በሆላንድ በስደት የሚኖር ወጣት ነው። ኮንቴክስቱ ባይገለጽልንም ከዩትዩብ ላይ ያወጣሁት ቪድዮ አንገት በሜንጫ ስለመቁረጥ በግልጽ አማርኛ አስቀምጦታል። በዚያ እለት ነበር የኦሮሞ ሕዝብ በብዛት የሚኖረው በሸዋ እንድሆነና ይህም የክርስትና እምነት ተከታይ መሆኑን ዶ/ር መረራ ያስረዳን።
በእነ ማልኮሜክስና በእነ ማርቲን ሉተር ምድር ቁጭ ብሎ አይሲስን አንገት መቅላት ወንጀል መናገሩ አይደለም የሚገርመው። ይህንን በአደባባይ በኩራት ሲናገር ህግ ባለበት ሃገር ዝም መባሉ እንጂ።
አል ጃዚራ ላይ ወጥቶ ኢትዮጵያዊነት በላዩ ላይ እንደተጫነበትም ደስኩሯል። ይህንን ዲስኩር ከሱ ውጭ ከሌሎች የኦሮሞ ልሂቃን አልሰማንም። በማንነት ቀውስ ውስጥ ካለ ሰው ይህንን መስማቱም ሊደንቀን አይገባም። ይልቁንም ይህንን ከነ በቀለ ገርባ ፣ ከዶ/ር መረራ፣ ከበአሉ ግርማ ፣ ከሎረት ጸጋዬ ገ/መድህን፣ ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ወይንም ከአቶ ቡልቻ ደመቅሳ አንደበት ብንሰማው እበር የሚከብደን። በእንደዚህ አይነት የጥላቻና የዘረኝነት እምሮው የታወረ ሰው እመራዋለው የሚለው አመጽ ላይ ለማበር የኢትዮጵያ ህዝብ ፈቃደኛ ባይሆን ሊደንቀን አይገባም። ከየትኞቹም የኦሮሞ ልሂቃን እንዲህ አይነት የኦሮሞ ሕዝብን ክብር የሚነካ ንግግር ሰምተን አናውቅም። “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ” “የክርስትያኑን አንገት በሜንጫ እንቆርጣለን” ሲል የትኛው የኦሮሞ ወገን ወይንም የትኛው የሙስሊም ህብረተሰብ ጃዋርን እንደወከለው አናውቅም። ልቡን ሞልቶ ሲናገር ግን የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው ወገን ነጥሎ ለማስመታት የታቀደ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ግልጽ ነው።
የፖለቲካውን ምህዳር ጠቆጣጥረው ዘረኝነትን እና ጥላቻን ሲሰብኩ ምን እናደርጋለን? ንቆ መተው ወይንስ ቀይ መብራት ማሳየት? ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ ስለጥቃቅን ነገሮች ሲናገር፣ “በጥቃቅን ነገር ተጠንቀቅ፤ ትንሽ ፍሳሽ – ትልቅ መርከብን ታሰምጣለች።” ብሎ ነበር። በእርግጥ መርከቡ ሊሰምጥ የሚችለው ውሃ መርከብ ውስጥ እንዲገባ ስንፈቅድላት ብቻ ነው።
የጃዋርን አካሄድ ሳሰላስለው ቦካሳ ይታወሰኛል። የትም አይደርስም የተባው የማእከላዊ አፍሪካው አስር አለቃ ቦካሳ፣ ሁለቱም ተመሳሳይ አመጣጥ አላቸው። ሁለቱም በማንነታቸው የሚያፍሩበት የበታችነስ ስሜት ውስጥ የኖሩ ናቸው። ሁለቱም የማንነት ቀውስ ውስጥ የነበሩ ናቸው። ጃዋር በአንደበቱ እንደነገረን የአማራ እና የኦሮሞ፣ የክርስትያን እና የሙስሊም ቅልቅል ነው። እንደዚህ የተበሳተሩ ብዙ አሉ። አብዛኞቹ ታዲያ በማንነታቸው ይኮራሉ። እንደ ጃዋር ያሉ ጥቂቶች ግን የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ቢገቡ አይደንቅም። አባት እና እናቱን የማያውቀው ቦካሳ ከ 12 አመቱ ጀምሮ የማንነት ጥያቄ ሲያንገላታው የነበረ ሰው ነው። የም ሆኖ የትም አይደርስም እየተባለና የተናቀ ወታደር ነበር። የሃገሪቱ ርእሰ ብሄር ይሆናል ብሎ ያሰበ አልነበረም። አስር አለቃ ቦካሳ በለስ ቀንቶት እ.ኤ አ. 1966 በመፈንቅለ መንግሰ ስልጣን ይዞ ሲያበቃ የማእከላዊ አፍሪካን ህዝብ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ፈጀ ሀገሪቱን እንዳልነበረች አደረጋት።
ሰዎች ለአዶልፍ ሂትለርም የነበራቸው አመለካከት ከዚህ የተለየ ልነበረም። አንድ የጀርመን ታሪክ ተመራማሪ ሁኔታውን ሲገልጸው “They all had one thing in common – they underestimated Hitler” ነበር ያለው። ሁሉም የሚጋሩት አንድ ነገር ነበር። ሁሉም ሂትለርን ንቀውት ነበር። በመጨረሻ ሂትለር የጀርመን አዲሱ ቻንስለር ሆኖ ብቅ ሲል የናዚ ፓርቲ አባላት በደስታ እና በእንባ ተቀበሉት። በሀገሪቱ ህግ ሳይሆን በሂትለር አምላኪ ሆኑ። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ሳይሆን የጃዋር አምላኪዎች እያደረጉ እንዳሉት ማለት ነው። ጃዋር “የእልቂቱን ትእይንት በኔ ሂሳብ እያያችሁ ተዝናኑበት” ያለውን አጢነው አይመስለኝም። በደፈናው ስለሚያመልኩት እንጂ።
ቦካሳም ሆነ ሂትለር በጥላቻ የመጡ ስለነበሩ ከምደር-ገጽ ጠፍተው ታሪክ ሆነው አልፈዋል። ጥለውት የሄዱት አሻራ ግን እስካሁን አለ።