ድህነት ዋናው የምግብ ዋስትና አለመኖር ምክንያት ቢሆንም ብቸኛ ግን አይደለም፡፡ ሌላም ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ አፍቅሮተ-ቁስ (Materialis) አንዱ ነው፡፡ አፍቅሮተ-ቁስ የሥነ-አዕምሮና የምግብ አጠቃቀም አጥኝዎች አልጠግብባይነት የሚል ፍች ይሰጡታል፡፡ ዳውሰን የተባሉ የመስኩ ተመራማሪ ሀብትን በመሰብሰብ የደስታ ምንጭና የስኬት መለኪያ ከዚያም አልፎ የመኖር ዋስትና አድረጎ መውሰድ በአፍቅሮተ- ነዋይ ለተለከፉ ሰዎች መለያ ባህርያት ናቸው ይላሉ፡፡
የስግብግብነት ምንጩ ብዙ ነው፡፡ ዋና ዋና የተባሉት፤ በህጻንነት በቂ መሰረታዊ ነገሮችን(በተለይ ምግብና ልብስ) አለማግኘት፣ የቤተሰብ መበታተን፣ ጥራት ያለው ጥምህረት አለማግኘት፣ በወጣትነት ጊዜ የሚከሰት የማንነት ችግር፣ የሕይወት አጋር ስለ አፍቅሮት ነዋይ ያለው ግንዛቤ፣ ወላጅና ሌላም ሊጨምር እንደሚችል አጥኝዎች የተስማሙበት ይመስላል፡፡ ስለ አልጠግብ ባይነት ይህን ካልሁ ወደ ዋናው አጀንዳ ልለፍ፡፡
በኢትዮጵያ ከ 1880- 1884 ዓ.ም (ለአምስት አመታት) ክፉ አመታት ነበሩ፤ ይህ ጊዜ በህዝቡም ክፉ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ እነዚህ ዓመታት በተለያቱ የሀገሪቱ ክፈሎች ታላቅ ፍጅት አስከትለው አልፈዋል፡፡ አንድ ጸሐፊ ወደ አንድ ሶስተኛው የሀገሪቱ ህዝብ በረሃብና በተያያዥ ምክንቶሞች እንዳለቀ በመጽሐፋቸው አስፈረዋል፡፡ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች በወቅቱ የማይበሉ እንስሳትን ከመብላት አልፈው ሰውም እንደበሉ ተጽፎ አንብበናል፡፡
የዚያን ጊዜው የረኃቡ ምክንት ኢሊኖይስ አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ፈረንጅ አመጣው ተብሎ በሚገመት የቀንድ ከብት በሽታ ባስከተለው የከብት እልቂት ነበር፡፡ ዋናው መንስኤ የከብቶች ማለቅ ቢሆንም አልጠግብ ባይነት (ስግብግብነትም) የራሱን ሚና ሳይጫወት አልቀረም፡፡ እስኪ በ 2002 ዓ.ም በታተመውና የኢትዮጵያ ታሪክ በአለቃ ተክለ ኢየሱስ፤ ሐተታ በዶክተር ሥርገው ገላው ከሚለው መጽሐፍ ከተጻፈው ሐተታ እንጨልፍ፤
ያን ወራት የሽዋ አራሽ ጉዛም እህሉን በጉርጓድ እየከተተ ለመንድሙ፣ ለእኅቱ፣ ለዘመዱ እህል አየነፈገ በገበያ እህል ታጣ፡፡ በዚህ ጊዜ ዳግማዊ ምኒልክ በየጉዛሙ ቤት ወታደር ሰደደ፡፡ ለባለ እህሉ የአንድ አንድ ዓመት ቀለብ እየተወለት ትርፉን በደብዳቤ አግብቶ ተበድሮ ለድሀ ናኘው፡፡ ከዚህ በኋላ ወታደር ከሚዘርፍን ገበያ ብንሸጠው ያሻለናል እያለ ገበያ አወጣው፡፡ ያን ጊዜ እህል በገበያ ተረፈ፡፡
ይህ አንዱ የምንማረው የአጼ ምኒልክ የአመራር ጥበብ ይመስለኛል፡፡ ይህ እርምጃ የህዝቡን ሕይወት ያተረፈ፤ ስግብግቡንም ያልጎዳ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ስኳር የደበቁ ስግብግቦች ይህን እድል ያገኙ አልመሰለኝም፡፡ ይህ ከዛሬ 120 ዓመት በፊት የሆነ ድርጊት ነው፡፡ ለስግብግቡ የአንድ አመት ቀለብ እየተወ ትርፉን በደብዳቤ አግብቶ ተበድሮ ለተቸገረው በነጻ ሰጠው፡፡ ሕይወትም አተረፈ፤ ገበያውንም አጠገበ፡፡ ለእኔ፤ ህዝባዊነት ማለት ይህ ነው፡፡
በዚሁ መጽሐፍ ላይ ሌላም ያስደነቀኝ ነገር ልጨምር፡፡ “ዳግማዊ ምኒልክም ለህዝቡ ትጋትና ትሕትና አስተማረ፡፡ መጥረቢያ አበጅቶ ካንቻ መታ፡፡ መቆፈሪያ አበጅቶ ዳገት ቆፈረ” ይላል፡፡ በወቅቱ የንጉሱን አርአያነት መበከትል ከከፍተኛ ሹማምነት እስከ ቤትሰራተኛው አይረባ ኩራቱን እየተወ መሬቱን አየመነጠረና እየቆፈረ ከረሃብና ከችግሩ ወጣ፡፡ ድህነቱን በስራው ድል መታው፡፡
በዚህ ወቅት ከንጉሱ ድርጊት የምንማረው አይኖር ይሆን? መቸ ይሆን ከልመና (ምጽዋት) የስነ ልቦና ጫና የምንወጣው?