ከዲሲ እስከ ሮድ ደሴት በባቡር የሰባት ሰዓት መንገድ ያስጉዛል ፡፡ ባጭሩ ከጤፍ እንጀራ የሰባት ሠዓት መንገድ ርቄ ነው የምኖረው፡፡ በሠፈራችን የሩቅ ምስራቅ ብጫ ሰዎች ይበዛሉ ፡፡ አንዳንዴ አሜሪካ ተኝቼ የሆነ ሆንግ ኮንግ ምናምን የሚባል አገር ላይ የነቃሁ ሁሉ ይመስለኛል ፡፡ ከቻይና ሬስቶራንት ሸሺቼ ስሮጥ ኮርያ ሬስቶራንት እገባለሁ፡፡
ያን ቀን ፤የምግብ ዝርዝሩ መግለጫውን ብድግ አድርጌ ሾፍኩት ፡፡ ምኑም ምኑም አልገባኝ ፤ አገሬ ናፈቀኝ፡፡ ሀቁን ለመናገር ኤልሣ ሬስቶራንት ናፈቀኝ፡፡ (እዚህ ላይ “ ሆዳም!” የምትለኝ ሁላ ፤ አንድ ቀን፤ እንጀራ ከሆድ በላይ መሆኑ እስኪገባህ ጠብቅ፡፡ )
ተከተልከኝ ብየ ፤ ዞሬ ዞሬ ሳይ
የኔታ ምስር ወጥ፤ ሸገር ቀረህ ወይ
አስተናጋጇ ማንዣበብ ጀመረች ፡፡ ቀና ብየ አየኋት፡፡ ሮድ ደሴት ውስጥ ብዙ እንደ ቆየሁ የገባኝ በቻያና እና በኮርያ ፊት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ስጀምር ነው፡፡ በቻይና ፊት እና በኮርያ ፊት መካከል ያለው ልዩነት ፤ በፌንጣና በአንበጣ ግልገል መካከል ያለውን ልዩነት የማወቅ ያክል ፈታኝ ነው፡፡ ግን ጊዜ የማይፈታው ምን እንቆቅልሽ አለ? ተመስጌን እየለየሁ ነው፡፡
በነገራችን ላይ እኛ የፈረንጆች ፊት እንደሚምታታብን የኛ ፊትም ይምታታባቸዋል፡፡በቀደም ለት ከወዳጄ ከአብርሽ ጋር የሆነ ክለብ ሄድኩ፡፡ ክለቡ፤ አዳምና ሄዋን በቅድመ እጸ- በለስ የነበራቸውን ያለባበስ ዘይቤ የሚንጸባረቅበት ክለብ ነው ፡፡ ኦኬ!ኦኬ! ማድበስበሱን ትቼ እቅጩን ልናዘዝ፤የርቃን ዳንስ ቤት ነው፡፡ ፤ርቃን ቤት የሄድኩት ሌላ ነገር አይደለም፡፡ አሪፍ የብርቱካን ጭማቂ ይሸጣሉ ሲባል ሰምቼ ነው፡ ፡ እሺ ይሄ ካላሳመነ ሌላ ልሞክር፡፡ ባልባሌ ቦታ ጊዚያቸውን የሚያጠፉትን ፈረንጆች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለመምከር ነው፡፡
ልገባ ስል መታወቂያ እንዳልያዝኩ ገባኝ፡፡ በተመጣጠነ ምግብ ስላላደግሁ ነው መሰል ለፈረንጆች ሁሌም አንድ ፍሬ ልጅ ነው የምመስላቸው፡፡ የግንባሬን መስመር እንኳ ቆጥረው ላቅመ ኣዳም ረታ እንደረስኩ መገመት አይችሉም ፡፡ ወድያው አብርሽ የሱን መታወቂያ ሳያስነቃ አቀበለኝ ፡፡ በኔና ባብርሽ ፊት መካከል ያለው ልዩነት፤ በኃይለሥላሴና ሚስታቸውን በሚጠብቀው ባርያ መካከል ያለው ልዩነት ያክል ሠፊ ነው፡፡ ፈረንጁ ዘበኛ ግን ይህንን ልዩነት ማጤን ተስኖት አስገባኝ፡፡ ለብዙ ፈረንጆች ጥቁር ሁሉ አንድ ነው፡ ፡በተለይ ትንሽ ሞቅ ሲላቸው ግር ይላቸዋል፡፡ በወጣት ጉንዳንና በሽማግሌ ጉንዳን መካከል ያለውን ልዩነት የመለየት ያክል ይከብዳቸዋል፤
አሁን ወደ ኮርያ ሬስቶራንት ግር ብለን እንመለስ፡፡ የሚበላውን ሳያውቅ ነው እንዴ የመጣው እንዳልባል ጅንን ብየ፤ ቅንድቤን ከፍ ከፍ እያረግሁ ዝርዝሩን ስሾፍ ቆየሁና ዝምብየ አንዱን አዘዝኩ፡፡
ምግቡን እየጠበቅሁ ዙርያ ገባየን ከለምኩት ፡፡ ወይባ ፊት ያላቸው አጫጭር የሩቅ ምስራቅ ሰዎች በየሰሀናቸው ላይ ተደፍተዋል፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ጥቁር፡፡ ከሩቅ ምስራቆች ጋር አንድ የሚያደርገኝ ነገር ቢኖር የቁመቴ ማጠር ነው፡፡ ወድያው፤ ባይተዋር የመሆን ስሜቴ ጠፍቶ የዝምድና ስሜት ተሰማኝ ፡፡
ሰዎች በብሄራቸው ፣ በሃይማኖታቸው ፣በሙያቸው እና በጾታቸው መደራጀት የሚችሉትን ያክል በቁመታቸው የማይደራጁበት ምክንያት ይኖራል?አጫጭሮች ፤በቁመናቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ጭቆና በእምነታቸውና በጾታቸው ከሚደርስባቸው ጭቆና ይተናነሣል?
ኣጭር መሆኔን መርዶ የተረዳሁበትን ቀን አልረሣውም፡፡ በልጅነታችን ካብሮ አደጌ ከተንሣይ ጋር አንለያይም ነበር፡፡ ለሱ የሚደርሰው በረከት ሁሉ ለኔም ይደርሰኝ ነበር፡፡ የመንደሩ እናቶች ተንሣይን አስቁመው ቆሎ ሲሰጡት ለኔም ይሰጡኛል ፡፡ የሱን ጉንጭ ከሳሙ እኔም ወረፋየን ጠብቄ ድርሻየን ስምያ እቀበላለሁ፡፡ አንድ ቀን፤ ከትምርት ቤት ስንመለስ በመንደራችን በሐቀንነታቸው የሚታወቁ ሴትዮ አስቆመውን ሲያበቁ ፤ ወደ ተንሣይ ዞረው ” እሰይ እሰይ !እንዴት አደግህ! ያብማይቱ እናቴ ካይን ታውጣህ ፤ “ብለው ደጋግመው ጨመጨሙትና እኔን ዘለሉኝ፡፡ ማደግ ማቆሜን የተረዳሁት ያኔ ነው፡፡ ማደግ ያቆምኩት በስንፍናየ ምክንያት ይመስል ስለምን፤ ስምያን ነፈጉኝ እያልኩ ተከዝኩ፡፡ ቀስበቀስ፤ ህብረተሰቡ ለረጅምነት የሚሰጠው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ደረስኩበት፡፡ በየትኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ለረጅሞች ትልቅ ከበሬታ አለ፡፡ ለምሳሌ እልል ያልሁ ያስቴር አወቀ አድናቂ ነኝ። ሸክላዋን እየጣድሁ፤ ካሴቷን በቢክ እክሪብቶ እያጠነጠንሁ፤ ሲዲዋን እያገላበጥሁ ሳደምጣት ኖርያለሁ ። ግን አንድም ቀን አጭር ወንድን አወድሳ ስትዘፍን አልሰማሁም፡፡ የሰማ አለ?
ሱፉን ግጥም አርጎ፤ ጠጉሩን አበጥሮ
መላክ መስሎ ታየኝ የኔ ማር ስንዝሮ
ብሎ የሚጀምር ተወዳጅ ዘፈን ሰምተህ ታውቃለህ?
የሆነ ጊዜ ላይ ጓደኛየ ምኡዝ ስለ ኣጭርነት ያቀረበው ትንታኔ ሰዎች በቁመታቸው መደራጀት ብቻ ሳይሆን ርእዮተ አለም የመገንባት አቅም እንዳላቸው ሁሉ ፍንጭ ሰጠኝ፡፡አንድ ቀን ኤልሣ ሬስቶራንት ስንቀመቅም የነገረኝ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡
” ለረጅም ሰው የማዳላት ልማድ ” ይላል ምእዝ “ ለረጅም ሰው የማድላት ልማድ ከህብረተሰብ ታሪክ ጋር የተያያዝ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጥንታዊው ሰው በጋርዮሽ ስርኣተ ማኅበር ውስጥ በፍራፍሬ ለቀማ ተሠማርቶ ይኖር ነበር ፡ ፡ ቀስ በቀስ፤ ተንጠራርቶ ብርቱካንና ሙዝ መሸምጠጥ የሚችለው ሰውየ ከሌሎች በላይ ተመራጭ ሆነ ፡፡ ሎጋ ሎጋዎች ለባልነት እና ለመሪነት ተፈላጊ ሆኑ፡፡ረጅሞች የቤተ- መንግስቱንና የጫጉላውን አልጋ ተቆጣጠሩት፡፡ እየሰነበቱ ፤ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ልማድ ፈጠሩ፡፡ ቀስበቀስ ፤ረጅምነት -ታላቅነት “በጎነትና ቆንጆነት ሆኖ ተተረጎመ፡፡ ታድያ ዛሬም ከፍራፍሬ ለቃሚ ምንጅላቶቻችን የወረስነው አድሎ ሳናውቀው ይጫነናል፡፡ ልቀጥል?“
”ቀጥል“
“ አጫጭሮች ለመኖር በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ የተፈጥሮ ምራጭ ሆነው እንዳይቀሩ ይታገላሉ፡፡ በታሪክ ውስጥ ብዙ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ይህን ለማስረዳት ጅንጅስካን ናፖሊዮን ድረስ መሄድ የለብንም፡፡ ሎጋዎቹ ልጅ ኢያሱና ተፈሪ በንቴ ባጫጭሮቹ ተገርስሰዋል፡፡ መለስ እና መንጌ አጭር ቢሆኑም ረጅም ዘመን ነድተዋል፡፡ የኃይለ ሥላሴ አባትና አያት ፎቶ ደርሶናል ፡፡ አጫጭሮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አጭሮች ለመኖር ሲሉ አጭርነታቸውን የሚያካክስ ክሂል በትጋት ያዳብራሉ፡፡መሰላልን ለመጀመርያ ጊዜ የሠራው ሰውየ ማን እንደሚባል ኣላቅም፡፡ ግን ስለቁመቱ በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ በፍራፍሬ ለቀማ ውድድር ውስጥ አጭሩ ሰውየ ረጅሙን ለመብለጥ የፈጠረው መሆን አለበት”
“ አጫዋች ሆነው ስንት ሎጋ ጀግኖች ደጅ ወደሚጠኑበት ቤተመንግሥት ይገባሉ፡፡ ወይ በብልጠት በሴራና በመላ አእምሯቸውን አሰልጥነው ራሳቸውን ለማካሪነት ያቀርባሉ፡፡ ቀስ በቀስ በትግላቸው ድል ይቀዳጃሉ፡፡ የቀድሞውን ልማድ ይነቀንቁታል፡፡ ማኅበረሰብ ”አ ጭር ሰው ለምክር ረጅም ሰው ለጦር ” የሚል ብሂል ፈጥሮ ቦታ እንዲሰጣቸው ያስገድዱታል፡፡ በሎጋ ወንዶች ደረት ላይ ተተክሎ የኖረውን የሴቶችን ትኩረት ይጠልፋሉ፡፡ ኮረዳይቱንም ያቅፋሉ፡፡ ድንክ አምሳያቸውን ተክተው ያልፋሉ፡፡ ”
ከዚህ የምኡዝ ንግግር በኋላ አጭርነቴን እንደ ወፍራም ደመወዝ በደስታ ተቀበልኩ፡፡
ከኤልሣ ሬስቶራንት ወደ ኮርያ ሬስቶራንት እንመለስ፡፡
አስተናጋጇ መብሌን ይዛ መጣች ፡፡ ሰሃኔ ላይ የተቆለለው ነገር ምን እንደሆነ ስላልገባኝ የንባብ መነጽሬን ከሰገባው መዘዝኩ፡፡ በደንብ ስሾፈው የተቀቀለ ቄጤማና ክራብ የተባለ የባህር እንስሳ መሆኑን ኣረጋገጥኩ፡፡ ክራብ ማለት፤ ክራብ ማለት፤ ክራብ ማለት ምን ብየ ላስረዳችሁ፡፡ መልኩ ፤ ከምግብነት ይልቅ ወደ ኮንስትራክሽን እቃነት ይጠጋል ፡፡ ዶሮ አስራ ሁለት ብልት እንዳላት ክራብ ደግሞ አስራ ሁለት ጉጠት ይዞ ተፈጥሯል፡፡ በየት በኩል እንደሚበላ ለማየት ሁለት ሦስቴ አገላበጥሁት፡፡ ቡለኑን እያወለቅሁ ብፈትሸውም የጾምም ይሁን የፍስክ ነገር ሰውነቱ ላይ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ መቸም ዘንድሮ በየኮርያ ቤቱ እየዞርኩ የበላሁትን ፍጥረት እናቴ ብታውቅ ቄድር የምታስጠምቀኝ ይመስለኛል፡፡ የየሩቅ ምስራቅ ሰዎች ከሰጠመ ታንኳ በቀር በባህር ውስጥ ከሚገኝ ነገር በሙሉ ይበላሉ ፡፡ ደሞ ከምግቡ በላይ ደሜን የሚያፈላው ባህላዊ ማንኪያቸው ነው ፡፡ቾፕ ስቲክ ይሉታል፡፡ ሁለት ቀጫጭን በትር ነው፡፡ ማነሺ !አስተናጋጅ፤ ምናለ ይሄን የታምቡር መምቻሽን ወስደሽ የረባ ማንኪያ ብታመጭልኝ!
ከምግብ ቤቱ እንደወጣሁ ጺሜን ለመቆረጥ አንድ የሊባኖስ ጸጉር ቆራጭ ዘንድ ጎራ አልኩ፡፡ ሙክታር ጺሜን ለማረገፍ ካስር ደቂቃ በላይ የማይፈጅበት ሆኖ ሳለ አርበ- ሰፊ ወሬ እየቀደደ ከግማሽ ሰአት በላይ አገተኝ ፡፡ ጺሜ እንዳያልቅበት እየቆጠበ፤ ከግራ ጉንጨ የነቀለውን ጸጉር በቀኝ ጉንጨ ላይ እየተከለ “ to make a long story short “እያለ ያስረዝማል፡፡ ቀዳዳውን ሳይጨርስ እንዳልሄድበት በመቀስ እያስፈራራ እንደ ተረከልኝ ነው የምቆጥረው ፡፡ እንደምንም ትረካውን ታኮ አስይዞ ለቀቀኝ፡፡ የጢሜን ቅሪት ከፎጣው ላይ እያራገፈ ሰላሳ ዶላር እንድከፍል ጠየቀኝ፡፡ ንዴቴንና ድንጋጤየን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡
” ሰላሳ ዶላር ለጢም ብቻ ነው ወይስ ለትረካህም ታስካፍላለህ?” (ይቀጥላል)