የካቲት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነጻነቱ የታገለበትና መስዋዕት የከፈለበት ታሪካዊ ወር – ሸንጎ

የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም.

የካቲት በኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የያዘ ወር ነው።ጣሊያን አገራችንን በወረረበት ጊዜ  ዜጎች በአንድ ቀን ጀንበር በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ከ30000ሺ ሰው በላይ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ብቻ በጠላት መትረየስ የታጨዱበት በአካፋ የተጨፈጨፉበት መስዋእት በመሆን ደማቸውን ያፈሰሱበት  ዕለት በመሆኑ ሊታሰብና ሊከበር ይገባዋል።በዚያን ዕለት ጣልያኖች እርምጃውን ሲወስዱ ሕዝብ ፈርቶ ያድርልኛል፣ይገዛልኛል በሚል እምነት ነበር።ውጤቱ ግን የብዙ ወጣቶችን ልብ የቀሰቀሰና ለትግል እንዲሰለፉ ያደፋፈረ ሆነ።

በዚያ ዓይን ያወጣ የጭካኔ እርምጃ የተጨፈጨፉት ዜጎች ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተወለዱና ከልዩ ልዩ ያገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው።የጣሊያን ወራሪ ሃይል ጠቅላይ አዛዥ የሆነው ግራዚያኒ ሕዝቡን ሰብስቦ  በሱ የሚመራውን የወራሪውን አስተዳደር እንዲቀበልና ባወጣው ሕግ እንዲተዳደር ለማድረግ ብሎም የጣሊያን መንግስት ለኢትዮጵያ እድገትና መሻሻል  እንጂ  ለመጉዳት የመጣ አለመሆኑን ለማሳመንና ለድሆች እርዳታ እሰጣለሁ በሚል የማታለያ ሰበብ ስብሰባ ጠራ።

ሕዝቡን ለመሰብሰብ ያስገደደው ዋናው  ምክንያት በየአቅጣጫው በዱር በገደል ተሰማርቶ ለአገሩ ነጻነት የሚታገለው አርበኛ ቁጥርና በጠላት ላይ የሚያደርሰው አደጋ እየጨመረ በመምጣቱ፣በከተማም ውስጥ ያለው ጫካ ባይገባም ልቡ ሸፍቶ ለጠላት አልገዛም ባይነት ስሜቱ እያደገ በውስጥ አርበኝነት ተግባር ላይ ተሰማርቶ ለአርበኞቹ የስንቅና የመረጃ ምንጭ በመሆኑ ይህን ሕዝብ በማታለልና በማስፈራራት በቁጥጥር  ስር ማድረግ እንዳለባቸው በመገንዘብ ነበር።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በጠላት ጦር አዛዦችና ሹማምንቱ ላይ በተለይም በግራዚያኒ ላይ አደጋ ለመጣል ምክርና ዝግጅት አድርገው በተግባር የገለጹት በኤርትራ  ክፍለ ሃገር የተወለዱት አገር ወዳድ ወጣቶች  አብርሃ ደቦጭና  ሞገስ አስገዶም ነበሩ።

ወጣቶቹ ግራዚያኒ በሰገነቱ ላይ ቆሞ ንግግር ለማድረግ ሲዘጋጅ ከመሃል ሳይታሰብ ፎክረው በመውጣት ያዘጋጁትን ሰባት  ቦምብ አከታትለው ወረወሩ።እንዳጋጣሚ ሆኖ የተወረወረበት ግራዚያኒና ከሃምሳ ሁለት በላይ አጃቢ ሹማምንቶቹ  የመቁሰል  አደጋ ሲደርስባቸው የሞሰለኒ አማች የነበረው አንድ ዓይኑ ጠፍቶ አንድ እግሩ ተቆርጦ ተዘረረ። ስብሰባው በሽብር ተናወጠ፤ በሁኔታው የተደናገጡትና የተበሳጩት ጣሊያኖችና  ባንዳዎቻቸው በእጃቸው ባለ ጠመንጃና ሌላም መሳሪያ ሕጻን፣ወጣት፣ ሽማግሌና አሮጊት ሳይለዩ በአደባባይ የተሰበሰበውን  ረፈረፉት።በማከታተልም የቤት ለቤት  ፍተሻ አድርገው የጠረጠሩትን ሁሉ አፍሰው ረሸኑት። የነዚያ የንጹሃን ደም በገዛ አገራቸው መሬት ላይ በውጭ ወራሪዎች እጅ ፈሰሰ። ያ ቀን  የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም.የጣልያኖችን ግፍና  ጭካኔ የኢትዮጵያኑን ድፍረትና ቆራጥነት በድጋሚ  ያረጋገጠ ዕለት ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንዴት ከረምሽ! አዲስ አበባ?

የኢትዮጵያኖቹ አልገዛም ባይነት ባገራቸው ብቻ ተወስኖ አልቀረም በጣልያኖቹ ከተማ በሮማ አደባባይ ሳይቀር የኤርትራው ክ/ሃገር ተወላጅ ዘርአይ ደረስም ያገሩ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ መሬት ላይ ተነጥፎ ጠላቶች ጫማቸውን እየጠረጉበትና እየረገጡት ሲሄዱና ሲያፌዙበት  ማየቱ አላስችል ብሎት እምቢ ላገሬ!፣እምቢ ለክብሬ!እምቢ ለባንዲራዬ !ብሎ ከጣልያኖች ጋር ግብግብ ገጥሞ የሚችለውን ያህል ጉዳት አድርሶ ህይወቱን ሰጥቷል።

በአደዋና በማይጨው ጦር ሜዳና ከዚያም በዃላ በተደረገው የአምስት ዓመት ትግል በዱር በገደል ተሰማርተው ደማቸውን ያፈሰሱት፣የቆሰሉትና ለድል ቀን የበቁት እኛም በነጻ አገር ተወልደን እንድንኖር  ያበቁን ከአንድ የህብረተሰብ ክፍል የተወለዱና ከአንድ አከባቢ ብቻ የመጡ ሳይሆን ከመላ የአገሪቱ ክፍል፣ ከጫፍ እስከጫፍ  ከሚኖሩት የተለያዬ  ቋንቋ የሚናገሩና በአንድ አገር ልጅነታቸው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የሚኮሩ ጀግኖች ነበሩ።ምንም እንኳን ጥቂቶቹ ደካሞች ለጥቃቅን ጥቅምና የጠላትን መሰሪ ዓላማ ካለመረዳት በባንዳነት ያገለገሉ መኖራቸው ባይካድም አብዛኛዎቹ ለአገራቸው ክብር ነጻነትና ዳር ድንበር በየጊዜው ከመጣ ጠላት ጋር እየተዋጉ አስከብረው የኖሩ ናቸው።የነዚያን ደፋርና ጀግኖች ውለታ ለመክፈል ያስከበሩትን የአገር ነጻነትና አንድነት ማስከበር የአሁኑ ትውልድ አላፊነት ነው።የአሁኑ ትውልድ ከትናንቱ ትውልድ አገር ወዳድነትን፣ጀግንነትን ሊወርስ ይገባዋል።ለተተኪውም ትውልድ የማውረስ አላፊነትም አለበት።ይህን ለማድረግ ታሪካዊ ዕለቶችን እያስታወሱ መዘከር አንዱ ነው።የኢትዮጵያ ጠላቶችና ተባባሪዎቻቸው ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ተጋድሎና ያረጋገጡትን ድል እያጥላሉ  ለመጭው ትውልድ ምሳሌ እንዳይሆን በልዩ ልዩ ዘዴዎች እንዲረሳ በማድረግ ላይ ቢሆኑም  ምኞትና ፍላጎታቸው እንዲሳካ መፍቀድ የለብንም።የማንነታችን አንዱ መግለጫ ነውና ልንዘናጋ አይገባም።በታሪካችን ላይ ዘመቻ ሲካሄድ  በዝምታ ማለፍ  የለብንም።አክብረን ማስከበር አለብን።

በዚሁ የካቲት ወር 1888 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊ አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህንኑ የጣሊያን ወራሪ ሃይል ለመጀመሪያ ጊዜ  ቅጣት ሰጥተው የመለሱበትን፣ለሌላው የቅኝ አገዛዝ ሰለባ ለሆነው በተለይም ለአፍሪካ ሕዝብ የነጻነት ትግል ደወል የሆነውን የአድዋን ድል እናከብራለን።የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያኖች ብቻ ሳንሆን የሌላውም አገር ጥቁር ሕዝብ ለነጻነቱ እንደ አርማ አድርጎ የሚወሰደው የታሪክ አምድ ነው።በዚህም የነጻነት ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ጎሳና ቋንቋ ሃይማኖት ሳይለየው  በአድዋ ጦር ሜዳ ተሰልፎ ለነጻነቱ መስዋእት ሆኗል። የዛሬ መቶ ሃያ ዓመት  የቀድሞዎቹ በከፈሉት የህይወት ዋጋ  የእኛ ትውልድ የሚኮራበትን የድል ውጤትና ነጻ አገር አስረክበውን አልፈዋል።ያንንም በሚገባ መዘከርና ታሪኩ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር የማድረግ ሃላፊነት አለብን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላማዊ ትግል በካዮች እና መከላከያ ምክሮች! (ግርማ ሞገስ)

ኢትዮጵያውያን በጣልያን ላይ ያደረሱት ውርደት ለአውሮፓውያን ቅኝ ገዥወች ቅሌትን ያከናነበ ፣ ለሌሎቹም የቅኝ ግዛት አስተዳደር ለሰፈነባቸው አገር ሕዝቦች የነጻነት ምሳሌ በመሆኑ ለመበቀል ኢትዮጵያ የምትባል አገርና ሕዝብ እንዳይኖሩ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል፤በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የሕዝቡን አንድነት በመቦርቦር  የእርስ በርስ ግጭት እንዲኖር ያልሞከሩበት ወቅት የለም።እንደ አብርሃ ደቦጭ፣ሞገስ አስገዶምና ዘርአይ ደረስ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የሚኮሩ ሌሎች ኤርትራውያን እንዳይበቅሉ፣ እንደ አሉላ አባ ነጋ ያለ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ ፣ በስለላ የጣሊያኖችን ጦር መቀመቅ የከተተው  እንደ አውዓለም በትግራይ መሬት ዳግመኛ እንዳይወለድ፣እንደ ጎበና ዳጬ፣እንደ ጃጋማ ኬሎ፣ ደረሱ ዱኪ፣አብዲሳ አጋ ፣ይልማ ደሬሳ ያሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ልጆች እንዳይፈጠሩ፣እንደ ሃብተጊዮርጊስ፣እንደ ወልደሥላሴ በረካና ሌሎቹም  ያሉ የጉራጌ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን የጦር አበጋዞች ዳግም እንዳይወለዱ፣ እንደ መኮንን ጉዲሳ( ሃ/ሚካኤል) እምሩ ሃይለሥላሴ፣ደስታ ዳምጠው፣በላይ ዘለቀ፣አሞራው ውብነህ፣መስፍን ስለሽ፣አበበ አረጋይ፣ ሃይለማርያም ማሞ፣አክሊሉ ሃብተወልድንና  ሌሎቹንም የመሰሉ የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ፣ እንደ ተፈሪ፣ምኒሊክ፣ ዩሃንስና ቴዎድሮስ ያሉ  ለጠላት  ያላጎበደዱ መሪዎች፣ ከሴቶችም ጣይቱ ብጡል፣መነን አስፋው፣ ጸሃይ ሃይለሥላሴ፣ሸዋረገድ ገድሌ፣ስንዱ ገብሩ፣ጽጌ መንገሻ፣ከበደች ስዩም፣ቀለመወርቅ ጥላሁን፣ላቀች ደምሰው፣ ቆንጅት አብነትንና ሌሎቹንም የመሰለ  አርበኞችና የጦር መሪዎች ዳግመኛ እንዳይነሱ ለማድረግና ኢትዮጵያዊነትን ለማደብዘዝ የቆዬ ፍላጎታቸውን  እውን ለማድረግ ለዘመናት ሲያውጠነጥኑት የቆዬ ሴራ ነው። ይህን ሴራ ተግባራዊ ለማድረግ በቀጥታ እራሳቸውን ለዳግመኛ ውርደት ከማቅረብ ይልቅ አገር በቀል ተባባሪዎቻቸውን በማደራጀትና በመርዳት አሁን በስልጣን ላይ በሚገኘው ጸረ ኢትዮጵያ ቡድን አማካኝነት   በታሪክ ና በሁሉም መልክ ተሳስሮ የኖረውን የኤርትራ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንዲክድና እንዲረሳ፣የባህር በሯን ለመንፈግ ኤርትራን አስገንጥለው ሌላውንም እንዲሁ ለማስገንጠል ሌት ተቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ።  የህወሃት/ኢሕአዴግ ስብስብ የሕዝቡን መብትና እኩልነት ለማረጋገጥ የሚሰራ ሳይሆን አንድነቱን አናግቶ አንድ ጠንካራ አገር እንዳይኖረው ፣በተበጣጠሰ ክልል ውስጥ በበረት ውስጥ ተቀፍድዶ እንደሚያድር እንስሳ እንዲኖር ለማድረግ  የሚሠራ የጥፋት መልእክተኛ ቡድን ነው።መሆኑንም በየቀኑ ከሚያካሂዳቸው አገር አጥፊ ክንውኖቹ ለመገንዘብ ይቻላል።  በቋንቋ፣በሃይማኖት፣በክልል ሳቢያ ልዩነት እየፈጠረና ጥላቻ እያሰራጨ  ሕዝብ እርስ በርሱ እንዳይተማመን አልፎ አልፎም እንዲዋጋ አድርጎታል።በፌዴራሊዝም ስም ዜጋ ከኢትዮጵያ(ከአገር) ባለቤትነት ወጥቶ በደባልነት እንዲኖር፣ሐሀገራዊ ሲሜቱና የጋራ እሴቱም እንዲሸረሸር ማድረግ እውነት ለእድገት የሚጠቅም ነውን?ሕዝቡን ከድህነት፣ከዃላቀርነት፣ያድነዋልን? ይህ ታዲያ ከጣሊያኖቹ ከፋፋይ ተግባር በምን ተለዬ?

ካለፉት ትግሎችና ከተከፈለው መስዋእት የምንወስደው ጠቃሚ ትምህርት ለአገር ክብር መዋጋት ማለት፣ለእራስ ክብርና ነጻነት መዋጋት እንደሆነና ያም በተናጠል ትግል የሚገኝ እንዳልሆነ ነው።ስለዚህም አገራችን ከገባችበት ቀውስና አደጋ ለመከላከል፣ነጻነቷንና አንድነቷን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ የተጣለብን የታሪክ አደራ ነውና እንደ ቀድሞ ትውልድ  እጅ ለእጅ ተያይዘን የተጋረጠብንን አደጋ በጋራ ልናሶግደው ይገባናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሙስሊሙ መሪዎች የፍርድ ሂደት ለ10 ቀናት ተቋረጠ

የዛሬ አርባ ሁለት ዓመት በ1966 ዓ.ም.የካቲት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ከዳር እስከዳር  ለመብቱ የተነሳበትና ትግል የተቀጣጠለበት ወር በመሆኑ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ሰፍሯል።በአሁኑም በያዝነው የየካቲት ወር 2008 ዓ.ም.የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች ለመብቱና ለአንድነቱ መስዋእት እየከፈለ የሚገኝበት የትግል ወቅት ነው።ካለፉት የካቲቶች ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ትግሉ በአንድነት ዙሪያ ገና ያልተቀናጀና ከአገራዊ ገጽ ይልቅ የአከባቢና የተከፋፈለ ስሜት የሚንጸባረቅበት መሆኑ ነው።ይህንን ክፍተት በአስቸኳይ በመሙላት እና  ብሔራዊ ስሜት ሳይላላ፣የአገር አንድነት አደጋ ላይ ሳይወድቅ  ሕዝብ ተባብሮ ሙሉ ነጻነቱና እኩልነቱ የተረጋገጠባት የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ባለቤት የሚያደርገውን ትግል ከግብ ለማድረስ እጅ ለእጅ ተያይዞ ዳግም የካቲትን እውን ማድረግ የወቅቱ ዋና ጥያቄ ነው። የተናጠል ትግል  ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።ከትንሽነት ትልቅነት፣ በትንሽ ክልል ነዋሪነት ከመታጠር ይልቅ የትልቅ አገር ዜጋ ሆኖ በፈለጉበት ቦታ የመኖርና የመስራት መብት፣የብዙ ሃብትና ዕድል ባለቤት መሆን ይሻላልና  የመነጣጠልን ጎጂ አዝማሚያና  መሰረታዊ አገራዊ ለውጥ እኩልነትና ነጻነት ፈላጊ የሆነ ሁሉ ሊታገለው ይገባል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ለየካቲት አስራ ሁለት 1929 ዓ.ም. ሰማእታትና ለየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ለአድዋ ድል ባለቤት ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ትልቅ ክብር አለው። በደማቸው ያስረከቡንን ነጻ አገርና የህዝቡን መብት ለማስከበር ከሁሉም   አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመስራትና  ለመታገል ቁርጠኝነቱን አሁንም ይገልጻል። በዚህ አጋጣሚም ለቀሩት ኢትዮጵያውያን እንደ ጥንቶቹ የአገር ፍቅርና የአንድነት መንፈስ እንዲኖረን ፣ለማንኛውም ከፋፋይ ተግባር ቦታና ዕድል ሳንሰጥ አገራችንና ሕዝባችን  ከገጠማቸውና ሊገጥማቸው ከሚችለው ግፍ በደልና አደጋ ተባብረን እናድናት ይላል።

የአድዋውን ድል በመዘከር ምሳሌነቱንም በመቅሰም ልዩነታችንን አቻችለን በዘመናችን ባለው የውስጥና የውጭ ጠላት ላይ ዘምተን ድል ማድረግ ይጠበቅብናል። አባቶቻችን የነበሩበትን የየካቲት ወር ለቁምነገር ስራ እንደተጠቀሙበት ሁሉ የእኛንም የዘመናችንን የካቲት ወር የቁም ነገር መስሪያ አድርገን በታሪክ የያዘውን ቦታ እንድንደግመው ሸንጎ ያሳስባል። ለዳግማዊ የካቲት በጋራ እንነሳ!

አንድነትና ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁን!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

 

1 Comment

  1. ሸንጎን የሚመራዉ አረጋዊ ሁኖ በግልጽ ሊነገር ያልተፈለገዉ ለምንድነዉ? በዚህ አይነት ኮለኔል መንግስቱ ለምን ፓርቲ አቋቁመዉ ብቅ አይሉም እንደዉመ ከአረጋዊ በረሄ በላይ የህዝብ ድጋፍ አላቸዉ።

Comments are closed.

Share