በዕውቀቱ ስዩም ሰሞኑን “ከአሜን ባሻገር” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አውጥቷል፡፡ ከ“መግባትና መውጣት” በኋላ ብዙ ጊዜ መታገሱን ልብ ይሏል፡፡ በመካከል ባለው ረጅም ክፍት ጊዜ በሕትመትና ማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃንና በሚያወጣቸው መጣጥፎች ነበር የታደምነው፡፡ በውቀቱን የምናውቀው በቁምነገር አዘል ሸንቋጭ ጽሑፎቹና በሳል ቅኔዎቹ ነው፡፡ ስለልጁ የጽሑፍ ባለጸጋነት መተንተን ጊዜን ባጉል ማጥፋት ነው የሚሆነው፡፡ የተሰጥኦው ነገር “ሀ”ና“ለ” የለውም፡፡ ማንም የሚምልለት ነው በተለይ ግጥሞቹ፤ ነገሮችን የሚያይበትና የሚያቀርብበት መንገድ፡፡ የሰሞኑ “ከአሜን ባሻገር” መጽሐፉ ከወትሮዎቹ በተለዬ ቁም ነገር ይበዛበታል፡፡ የአቀራረብ ሁኔታው ከፍታ ላይ ነው አሁንም፡፡ በተለይ የዳሰሳቸው ታሪካዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች “ፕሮፌሰር” ያክል የማዕረግ ማማ ላይ ተቀምጠው፣ የዕውቀት ጥግ ላይ አለን ብለው የሚኮፈሱ የአገራችን ልሂቃን “በልጄን ላሳድግበት” ልማድ ያልደፈሩትንና ያልዳሰሱትን ጉዳዮች “ይበል” በሚያሰኝ የአቀራረብ፣ የንባብ፣ የመረጃና የምክንያታዊነት ርቀ’ት ሲተነትን እናገኘዋለን፡፡ መጽሐፉ በጥቅሉ ግሩም ቢሆንም ቅሉ አንዳንድ ስንኩል እይታዎችን ታዝቤበታለሁ፡፡ እነሱን መዳሰስ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡
ዘመናዊነትን ፈጥኖና በቀላሉ መቀበል፣ ዘመናዊነት በሃገር እንዳይሰርፅ ማነቆ የሆኑትን መንቀፍ መልካምነት አለው፡፡ ይህን ሁኔታ ሲነቅፍ በተደጋጋሚ እናስተውላለን፡፡ መንቀፉ ባልከፋ፤ የበውቀቱ ነቀፋ መነሻውና መድረሻው እዛው ድሮና የድሮው ማኅበረሰብ ላይ መሆኑን ነው የማያስማማኝ፡፡ በራሱ አገላለፅ“በዘመኑ መንፈስ” ንፅፅሩ ቢሰራ መልካምነቱ ይጎላል ባይ ነኝ፡፡ ያለፈው ማኅበረሰብ ላይ የሚሰነዘር ታሪክ ቀመስ ትችት ግቡ ያሁኑን ማኅበረሰብ ለማደስ እንጂ ያለፈውን የቀድሞውን ነቅፎ በዚያው ለመርካት መሆን የለበትም፡፡
ስለ አፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ምኞት፣ የቴክኖሎጂና ዘመናዊነት ትውውቅ፣ አንድነት፣ ለዚያም ስለከፈለው መስዋዕትነት ከቧልት በዘለለ አንዳች ቁምነገር ለማለት ያልደፈረ፤ ስለቴዎድሮስ “እጅ ቆረጣ” ዲስኩር ለማውራት ግን ብዕሩ ይሰላል፡፡ የአሁኑን ስርዓት አምባገነንነት ለመግለጽ የስርዓቱ አምባገነንነት በራሱ በቂ ነው፤ የግድ ወደአጼዎቹ ዘመን ወደኋላ መንደርደር ያለበት አይመስለኝም፡፡ በቴዎድሮስ ዘመን’ኮ አብዛኛው የዓለም መንግሥት በፈላጭ ቆራጭ የፊውዳል ስርዓት ስር ነበር፡፡ የኛዎቹን ነገሥታትነጥሎ መወረፍ አይጠበቅበትም፡፡
ስለ ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ሐውልት የመጎብኘት ነገር ሲያወሳ “ባጋጣሚ ከንጉስ ከመወለዱ ውጭ” ምን ሠራ? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ልዑል ማለት በደምሳሳው የንጉሥ ልጅ ነው፡፡ የየትኛውም ሃገር ንጉሥ ልጅ ዝናው ናኝቶ ነው የምናውቀው፡፡ የሚናኘውም ምንም ስላደረገ ሳይሆን የንጉሥ ልጅ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ የኦስትርያው ንጉሥ ልጅ መቃብር የሚጎበኘው ለምንድነው? ባጋጣሚ የንጉሥ ልጅ ከመሆኑ ውጭ የሰራው ነገር የለም፡፡ በርግጥ ለሁለተኛ የዓለም ጦርነት መጀመር የልዑሉ መገደል ፊሽካ ነበር፡፡ ቢሆንስ በሴራ ተገደለ እንጂ ምን አስደናቂ ስራ ሰራ? እንቀጥል፡፡ የእንግሊዝ ልዑላን በእንግሊዛውያን ዘንድ ታዋቂና ተከባሪ ናቸው፡፡ ሹመታቸውና ጋብቻቸው ታላቅ ግርግርታና ሽፋን አለው፡፡ ታዲያ እኒህ የእንግሊዝ ልዑላን በትዕዛዝ ነው እንዴ የተወለዱት?
የበዕውቀቱ ሸፋፋ ዕይታ ባብዛኛው የሚመነጨው ለሃይማኖት ካለው ግንዛቤ ነው፡፡ የልጁ የብዕር ሰይፍ ብዙውን ግዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ይወረወራል፡፡ ብዙ ጊዜ መሠረታዊ ያልሆነ ትችጭ ይሰነዝራል፡፡ ለትችቱ መሸሸጊያ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያለው ለማስመሰል ይጥራል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዳለው የሚያሳይ አሳማኝ ምልክት አላይበትም፡፡ ያደገበት ባህል ለቤተ ክርስቲያን ጉልህ ቅርበት ስላለው ጠቅሞት ይሆናል፡፡ ከዚያ የዘለለ ድፍረት ግን “አወቅሁሽ ናቅሁሽ ነው” ይመስላል፡፡ ብዙው ሰው ከቤተ ክርስቲያን ታዛ “ዘኬ” አነፍንፏል፤ ይህን ግ የእውቀት እማኝ አድርጎ መውሰድ ያስታል፡፡ ልጁ ከአንዴም ሁለቴ “ኢ-አማኒ” ነኝ ብሎ ድምጹን ከፍ አድርጎ ይናገራል፡፡ ራሱን ኢ-አማኒ ያደረገ ሰው የሉላውን ሰው እምነትና ሃይማኖት መጎንተል ዘላንነት፣ ወንጀልም ነው፡፡ በተለይ ካህናትን በሸንቋጭ ቋንቋ የመዝለፍ ልማድ አለው፡፡ ነገር ግን ከኢ-አማኒ ወደአማኒ የሚሰነዘር ማንኛውም ሃይማኖት ነክ ጉንተላ ምክንያታዊ አይደለም፡፡
መቼ ነበር ይህ ልጅ እስልምናን ወይምፈረንጅ ጠቀስ አመጣሽ ቤተ እምነቶችን የሸነቆረው? ይህ ልጅ አቡነ ተክለ ኃይማኖትን በተቸበት አግባብ መሃመድን ቢነካ በእውኑ የበዕውቀቱን አንገት ከተቀረው ሰውነቱ ላይ ተሰክቶ ማግኘት የማይታሰብ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ እስልምናም ሆነ ሌሎች የክርስትና ቅርንጫፎች በዚች ሃገር ታሪክ ውስጥ ጎታች ምዕራፍ አልነበራቸውም?
ልጅ በውቄ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ሳይንስ-ጠል ሊያደርግ ሲዳክር በ“ከአሜን….” መጽሐፉ ታዝበነዋል፡፡ ስለ “ መሬት መዞር” አንድ ፈረንጅ ለሊቃንቱ ሲናገር እንዳልተቀበሉትና አለቃ ለምለም ወደሚባሉ የላቁ ሊቅ ፈረንጁን እንደመሩት ይነግረንና አለቃ ለምለምም ጉዳዩን ሰምተው ከነጩ ጋር ጠጅ ጠጥተው ሲዞርባቸው “ያገሬ መሬት አሁን ዞረች” ብለው ሳይንስን ላለመቀበል ከፌዝ ጋር እንዳቅማሙ ከትልቅ ነቀፋ ጋር ይተርክልናል፡፡ ይህን የሚለው ከማን ጋር አነፃፅሮ ነው? እኔ እስኪ ይኼን እውነት ከፈረንጆች ጋር ላነፃፅር፡፡ መቼም ከእውነቱ ጋር እንጂ ከፈረንጅ ጋር አታነፃፅር እንደማይለኝ ተስፋ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ለርሱም ሆነ ለሌሎች “ዘመናዊ ትምህርት” ቀመስ ነቃፊዎች መነፅራቸው ምዕራባውያኑ ናቸውና፤ ይልቁንም ልጅ በዕውቀቱን ራሱ እንደነገረን “በአንድ ሃባ መፅሐፍ” የልጅነት ማኅተቡን አስበጥሰው ሃይማኖትን ያስተውት ሐዋሪያዎቹ ናቸውና፡፡ “የመሬት መሸከርከር” ነገር ሲነሳ የሳይንሱ መገኛ ምዕራብ አውሮፓውያን ራሳቸው በእልልታ አልተቀበሉትም ነበር፡፡ በተለይም የሮማካቶሊክ ልሂቃን፡፡ ስሙን የዘነጋሁት ተመራማሪ “መሬት እንደምትዞር” አረጋገጥኩ አለ፡፡ የዘመኑ ፈላጭ ቆራጭ ፓፓዎች ንስሃ ግባ አሊያ አንገትህ ይከላል ብለው አስፈራሩት፡፡ “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው” ብሎ “ተፀፀተ”፡፡ ቀጥሎ እውቁ የግኝት ሊቅ ጋሊሊዮ ጋሊሊ “አውነቱን” አገኘሁት አለ፡፡ “ሰይጣን አሳሳተኝ” በል ተባለ ፓፓዎች ዘንድ ቀርቦ፡፡ ፈቃደኛ ሊሆን ባለመቻሉ አንገቱን ሊቀላ ችሏል፡፡የልጁን ክፍተት እዚህ ላይ በሰፊው ማየት እንችላለን፡፡ ይህ እንግዳ ግኝት ለሳይንስና ፈጠራ ቅርብ በሆኑትን ነጮች እንኳ በቀላሉ ቅቡል አልነበረም፡፡ የሮም ቤተክርስቲያን ፓፓዎች አውሮፖ ውስጥ ብዙ ግኝት ያመጡ የሳይንስ ሊቆችንና የተለየ ሃይማኖታዊ አቋም ያራመዱ ሊቃውንትን በእሳት አቃጥለው መጨረሳቸው ታሪክ ያወራው ሃቅ ነው፡፡ ጉዳዩ ወደ እኛ ሃገር እና ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ነው እንዴ ለበዕውቀቱ ለአቅመ- ወሬነት የሚበቃለት? የእኛዋቹ ሊቃውንት መልሳቸው ሁለት ነው፡፡ አንደኛው አንቀበልም፤ ሁለተኛው ደግሞበቀላል ፌዝ አዘል “ቤተ-ሙከራ” “ሰክረህ ሲዞርብህ” መሬት ትዞራለች አትበል! የሚል ነው፡፡ እንደ ሮማዎቹ ከዶግማ ጋር አላያያዙትም፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደ ዛቻና ማስፈራሪያ አላደገም፡፡ አውሮፓውያኑ ግን “የሰይጣን ሃሣብ” ነው፡፡“ትምህርተ-ሃይማኖት” አፋለሰ ብለው ሰው ሰቅለዋል፡፡
በአዲሱ መጽሐፉ ገፅ 91 ላይ “አንድ ፍሬሽንብራ የሚያክል ቄስ በአንዲት ቃል’አሰርሁ ፈታሁ’ እያለ ሃገር ሊያምስ ይችላል” ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? “አንድ ፍሬ ሸንብራ” የሚለው ሃረግ የስድብ ቃና ነው ያለው፡፡ እንዲህ ብሎ አንድን ክብር ያለው የሃይማኖት አባት መዝለፍ ተከታዩን ከማሳዘኑ አልፎ የፀሐፊውን ደረጃም ያወርዳል፡፡
እዛው ገፅ ላይ ሌላ ሸንቋጭ ገለፃ አለ፡፡ “መንፈሳዊ ባለስልጣኖች ከዓለማዊ ባለስልጣኖች የሚበልጥ እንጂ የማያንስ ጉልበት ነበራቸው” የሚል፡፡ ከዚህ ዓረፍተ ነገር፤ ሁለት ህፀፆችን መንቀስ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው“መንፈሳዊ ባለስልጣኖች” በሚል ድፍረት በተቀላቀለበት ገለፃ መንፈሳዊ አባቶችን ይወርፋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትውፊትና በአማኞቹ ዘንድ ክብር ባለው አጠራር ነው የሃይማኖቱ አባቶች የሚጠሩት፡፡ በስድ ውከላ ቤተ ክርስቲያኗን ማንኳሰስ አላማው ስለሆነ እንጂ የዛሬዎቹን “ጥቂት” ፖለቲካ መር የኃይማኖትመሪዎች ቢተች ጥቅሙ ለራሷ ለቤተ ክርስቲያኗም በሆነ ነበር፡፡ ሁለተኛው የመንፈሳዊ አባቶችን ስልጣን /power/ ሊያሳይ የሞከረበት ነው፡፡ አሁንም በንፅፅር ነው የማሳየው፡፡ ከየትኛው ቤተ እምነት ራሶች ጋር ተወዳድረው ነው የኛዎቹ “ባለጉልበት” የሆኑት፡፡ እስልምና አረብ አገራት ላይ ራሱ መንግስት ነው፡፡ አባቶችም አድራጊ ፈጣሪ መሆናቸው ግልፅ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓለም አብያተ-እምነት ታሪክ እንደ ሮማ ካቶሊክ ፓፓዎች ጉልበተ ብርቱ መንፈሳዊ መሪ ተከስቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ እኒህ ፓፓዎች ታላቁን የሮም መንግስት በትረ ስልጣን ይዘውሩ ነበር፡፡ በጉባኤ ኬልቄዶን ለአንዷ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሁለት መከፈል፣ በ16 መ/ክ/ዘመን ፕሮቴስታንቲዝም ለተባለው እንቅስቃሴ መጀመርና ለቤተ ክርስቲያን ወደ ሶስት ቅርንጫፍ ማደግ፣ ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድነቷ እንድትመለስ በተጠሩ የተለያዩ ጉባኤዎች ላይ እንቅፋት በመሆን የሮማ ፓፓዎች ጡንቻ ከባድ ድርሻ ነበረው፡፡
የላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት “አዳራሾች” (ገጽ 25፣26፣28፣31) ብሎ ከእምነትም ከሥነ ውበትም ጎራ ገፍቶ ያወርዳቸዋል፡፡ የላሊበላ ቤተ መቅደሶችየተሰሩትም፣የሰራቸው ቅዱስም መንፈሳዊና ለመንፈሳዊ ዓላማ ነው፡፡ ከታሪክና ሥነ-ህንፃ ፋይዳቸው፣ ከቅርስነታቸውም ጎን ለጎን አምልኮ የሚፈፀምባቸው መንፈሳዊ መካናት ናቸው፡፡ አዳራሽ ብሎ መንፈሳዊና ቅርሳዊ ይዘትና ልዕልናቸውን ያንቋሸሸበት ምክንያት ግልፅ አልሆነልኝም፡፡
በሌላ መልኩ በገፅ 162 ላይ እንዲህ ይላል፡ “ብዙ ያገራችን ገዳሞችና ጥንታዊ ህንፃዎች በሰላሙ ቀን ለቤትነት የሚያገለግሉ ምሽጎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡” አሁን ይኼ ምን ማለት ነው? ዓረፍተ ነገሩም ይዘቱም ግራ አጋቢ ነው፡፡ ገዳማት በሰላም ቀን መኖሪያ ቤቶች ናቸው ማለት ምንድነው?“አምልኮ ቦታን የሙጢኝ የሚል እምነት እንደሚወገድ” (ገፅ 171) ሲተነብይ እናገኘዋለን፡፡ አሁንም ቢሆን በዚህ አባባሉ ከዚች መከራ የበዛበት ቤተክርስቲያን ራስ ላይ ሊወርድ አልፈለገም፡፡
ቤተክርስቲያንን ለመጐንተል ቀልቡ የማያርፈውን ያህል ስለሰራችው መልካም ትሩፋት ለመዘከር ብዕሩ ይዶለዱምበታል፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የቀመሙትን ቅኔ ሲነጥቅ እንጂ ሲያሞግስ አንብበን አናውቅም፡፡ ስለ ሊቃውንቱ የዘመን አቆጣጠር (Calendar) ጥበብ /ግኝነት፣ ስለ ሥነ-ፈለክ ምርምራቸው፣ ሒሣብ፣ ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ሥነ-ህንፃ፣ ሥነ-ፅሑፍ፣ ፊደል፣ አሃዝ፣ ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው እውቀት ስለማቆየታቸው በስህተት እንኳ ለማውራት ወይ ለመፃፍ ሲደፍር አላየሁትም፡፡ ለመንቀፍ፣ ለማንኳሰስና ለማላገጥ ግን ከብርሃን ፈጥኖ ይደርሳል፡፡
ሌላ ቦታ ላይልጅ በዕውቀቱ “ኡ ኡ” ብሎ ጮኾ ኢ-አማኒነቴን እወቁልኝ ሲል እናገኘዋለን፡፡ ኢ-አማኒነትን ለመግለጽ ሁለት ጊዜ ቃል በቃል አንድ ቦታ ላይ ደግሞ በአገባብ ሞክሯል- በ“ከአሜን ባሻገር” ላይ፡፡ ይህን ለማሳወቅ መጽሐፍ መፃፍ አይጠበቅም በህይወት ፍልስፍናውና በእለት-ተለት የኑሮ ዘይቤው ሊገልፀው ይችል ነበር፡፡ ምናልባት አማኒው ክፍል ከተከፋ ብሎ ይመስላል አንድ ቦታ ላይ ደግሞ “ለፋሲካ በዓል ማንኩስ” ሄጄ ይላል፡፡ ይህን የማመጣጠን ፓለቲካውን አልወደድኩለትም፡፡ በ“ማመጣጠንፓለቲካ” ብዙ ገፆች ላይ ሲዋዥቅ ይዤዋለሁ፣ በተለይ ታሪክንና ማንነትን በተነተነባቸው ክፍሎች፡፡ ኢ-አማኒ መሆን መብቱ ነው፤ በነጋሪትም አሳወጀ በህይወት ዘይቤው፡፡ ግን በእሱ ኢ-አማኒነት ውስጥ የሌላውን አማኒነት አንኳሶ መሳል ተንኳሽነት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ቂም ሊጋባ ይችላል፣ በህይወት መንገዱም ላትመቸውት ችላለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን በሰበብ አስባቡ መጎንተል ግን የተከታዩን ግለሰባዊ መብት እንደመፃረር ነው፡፡ በልጅነቱ በቁንጥጫ የመዘለጉትን ቄስ ሲጠላ አድጎበት፣ የኢትዮጵያን ቄስ በጅምላ ሊጠላ አይገባውም፡፡ የእሱ የጥላቻ አገላለፅ አዕላፋት የሚሆኑ የቄሱን ልጆች ያሳዝናልና፡፡
ከዚህ ወጣ ስንል፣ “ጉግስ፣ ጊጤ፣ ሰንጠረዥ አካዱራ፣ ገና የተባሉት ጨዋታዎች የጦርነት ቃና ነበራቸው” ይለናል፡፡ (ገፅ 162)፡፡ የየትኛውም ሃገር ጨዋታዎች (Games) በሁለት ተቃራኒ ቡድኖች መካከል የሚካሄዱና አንዱ ቡድን ወይም ግለሰብ ሌላኛውን ቡድን ወይም ግለሰብ ለማሸነፍ የሚደረግ ግብ ግብ ነው፡፡ እሱ ካልሆነማ የጨዋታው አጓጊነት አይኖርም፡፡ አሁን ያሉ ዘመናዊ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ስንወስድም በዚህ መንፈስ የተቃኙ ናቸው፡፡አሸናፊነት ግባቸው ይሆንና ያልቻለ ተሸናፊ ይሆናል፡፡ በዚህ ግብግብ ውስጥ መጎዳዳት አልፎ ተርፎምመገዳደል ሊኖር ይችላል፡፡ በዘመናዊ ስፖርት እንደ American football ጦርነት አካል ጨዋታ የለም፡፡ የኛን ጨዋታዎች የጦርነት ታሪካችን መግፍኤና ቆስቋሽ ሊያረጋቸው ይዳዳል፡፡ ጨዋታዎች እርሱ እንዳለው የጦርነት ቀደምት ሽሎች ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ በጥናት እስካልተረጋገጠ ድረስ ከግለሰብ ግምት ያለፈ እውነታ አይኖረንም፡፡
ስለጡት ቆረጣ ባወራበት አንቀፅ ዮዲት ጉዲት ወደ አክሱም ወርዳ “በሴተኛ አዳሪነት” እንደተሰማራች ይነግረናል፡፡ “የቄስ ሚስት አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት…” የሚለው ብሒል የሚሰራው እዚህ ጋር ነው፡፡ ከሚገባው በላይ ተጨብጭቦልህ ማማ ላይ ከወጣህ መውረጃው ነው የሚጠፋህ፤ ወጥም ትረግጣለህ፡፡ ሴተኛ አዳሪነት የተጀመረው ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ነው በስፋት የሚታወቀው፡፡ ሴተኛ አዳሪነት /Prostitution/ እንደ ስራ ዘርፍና መተዳደሪያ ነው፡፡ በየት በየት አድርጎ ነው ከዛሬ 1100 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ (አክሱም) ውስጥ ሴተኛ አዳሪነት አለ የሚለን? ምን አልባት ዘማዊነትን ሴተኛ አዳሪነት ብሎ ተረድቶት ከሆነ በትልቁ ስቷል፡፡ ሴተኛ አዳሪነት ነጮቹ commercial sex የሚሉት ነው፡፡ እሱም ገንዘብ ማግኛና ኑሮን ማሸነፊያ መንገድ ነው፡፡ ይህ ስራ ከሺ ዓመታት በፊት አገራችን ውስጥ ነበር ማለት ጸሐፊውንም ሆነ ምንጩን ከስህተት አያድናቸውም፡፡
የጉዞ ማስታወሻ “ጊዜ አልፎበታል” ይለናል ልጅ በውቀቱ፡፡ ገጣሚው የሚያስገርመኝ ጠባዩ እርሱ በግሉ ያመነበትን ጉዳይ ነባራዊ እውነታ አድርጎ መሳሉ ነው፡፡ “የጉዞ ማስታወሻ”ን Google Earth ተክቶታል አይነት ስብከት ያስቀምጣል፡፡ “የጉዞ ማስታወሻ” ሲባል “ደብረ ብርሃን ከአ/አ በስተሰሜን አቅጣጫ 130 ኪ.ሜ ርቀት ላይ፣ ከባህር ጠለል በላይ ምንትስ ጫማ ከፍታ…” ምናምን አይደለም`ኮ፡፡ የሕዝቡን ባህል፣ ወግ፣ ተረት፣ መልክዓ ምድር፣ የኑሮ ዘይቤ፣ የስልጣኔ ባህል፣ ትምህርት፣ ፍልስፍና፣ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ሐዘን፣ ደስታ፣ ሌሎችም ይገለጹበታል፡፡ የ“ገለጻ” ችሎታ በራሱ አንድ የሥነ ጽሑፍ ስልት ነው፡፡ እስኪ ዛል አንበሳን ከመሐመድ ሰልማን “ፒያሳ…” ልቆ የሚከስትልን ድረ ገጽ ይጠቁመን፡፡ እስኪ በሞቴ ስለአርማጭሆ በቂ መረጃና ምስል የትኛው ድረ ገፅ ላይ ነው ያለው?
ታሪክ ቀመስ ትንተና ከሰጠባቸው ምዕራፎች ባንዱ “ስምና ማንነት” በተሰኘው ጥግ ስር ጎጃም ኦሮሞ ልትሆን ለጥቂት ነበር የተረፈችው፡፡ እውነት ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ የተጋባ ነው፡፡ ይህን ማሳወቅም በጎ፡፡ ግን ይህን እውነታ ለመግለጽ ቀይረውበት ነው እንጂ አያቴኮ “ከበደ” ሳይሆን “በዳዳ” ነበር አይነት ዲስኩርን ምን አመጣው? እዚህ ድረስ መሄድስ ለምን አስፈለገ? ስለምኒልክና የሃገር አንድነት ዘመቻው ያቀረበው ትንታኔ እጅግ ግሩም ነው፡፡ እውነትና በታማኝ ዋቢዎች የተጣቀሰ ነው፡፡ እውነት ነው ዳግማዊ ምኒልክ በዘመቻው የአንድ ንጹህ ሰው ጡት አላስቆረጠም፡፡ ይህን እውነት በእውነትነቱ ብቻ ማስረዳት የምሁርነትም የጀግንነትም ምልክት ነው፡፡ በዕውቀቱ የዲግሪ መዓት የቆለለ “የታሪክ ምሁር” ነኝ ባይ ያልደፈረውን ነው የደፈረው፡፡ ለዚያውም በፍቱን ምክንያታዊነትና ማስረጃ ከግሩም ጥናት ጋር- ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህን ለ“ማመጣጠን” ግን “የጎጃም ነገሥታት ኦሮሞ ናቸው”፤ “ነገሥታቱ ከኦሮሞ ሲጋቡ ነው ክብራቸው የሚጨምረው”፤ “የጎጃም አካባቢዎች ‘ኦሮሞ-ወረስ’ ናቸው”፤ ሌላው ቀርቶ “ከኦሮሞ ያልተቀላቀለ ጎጃሜ ክብሩ ያነሰ ነው” የሚለው ዲስኩር ግነት አከል አዎ-ኦሮሞ አገላለጽ ነው፡፡ የአካባቢውን ባህል የሚያውቅ ሰው ደግሞ ገለጻው ከእውነታ ምን ያክል እንደጎነ አያጣውም፡፡ ያለፈ የታሪክ ስህተት የሁላችንም ቀደምቶች መፈጸማቸው እሙን ነው፡፡ እሱን ለእነሱው ትተን እኛ የጸዳ ዛሬና ነገን ለመገንባት መትጋት አዋጪው ነገር ነው፡፡
ስለራስ ጎበና የሰጠው ታሪካዊ ትንታኔ ግሩም ነው፡፡ ራስ ጎበናን ለማክበር ግን “ንጉሥ ምኒልክ ‘አንቱ’ ብሎ ጎበናን ይጠራዋል” ማለት፣ አልፎም “የጎበና ንብረት ከምኒልክ ይበልጣል” ብሎ መቀኘት በእውኑ አጓጉል ግነትና ኢ-ምክንያታዊ ነው፡፡ አንድነታችን እንፈልገዋለን፤ ለዚያ የሚያሻውን መስዋዕትነት እስከመክፈል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊነት ውሁድ፣ ቅልቅል እየሆነ መጥቷል፡፡ ይኼን ለማሳየት የሄደበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ግን አበበንም እንዳይከፋው ጫላንም እንዳይከፋው “በማመጣጠን” የሚቀርብ ነገር ሁሌም በጎ አይሆንም፣ ሕጸጽ ሊያስከትል ይችላልና፡፡ እንደውም ይሄን ክፉ ነገር የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሳናስበው ያሰረፁብን ይመስለኛል፡፡ እውነት በማመጣጠን አትቀርብም፣ እውነት ያው ራሷ እውነት ናት፡፡
በታሪክ የተከሰተን ድክመት ተምረንበት ለዛሬ በጎነት ትርፍ ማግኘት መልካም ድርጊት ነው፡፡ በሌላው ዓለም ወተትና ማር የመዝነብ ታሪክ እንደተመዘገበ ሁሉ በእኛ ላይ መሳለቅ ግን ደግ አይመስለኝም፡፡ “በታሪክ ውስጥ ያሉ ቁልፍ ቃላቶች (ቃላት?) ‘ታሠረ፣… ነገሠ… ዘመተ… ተሰቀለ’ የሚሉ ብቻ…” (ገጽ 80) ይለናል፡፡ የዓለም ታሪክም ከዚህ የተለዬ ዘገባ የለውም፡፡ የታላቋን አውሮፓ ታሪክ እንኳ ብንወስድ “ወረረ፣ አስገበረ፣ ቅኝ አደረገ፣ በዘር አገለለ፣ ገደለ….” እና መሰል ትርክቶች የዘለለ አይደለም፡፡ ዛሬ በዘር ማግለላቸውን በአንጻሩ ከማስቀጠላቸው በቀር ከታሪካቸው ተምረው አሁን የዓለማችን ቁንጮዎች ሊሆኑ ችለዋል፡፡ የዓለም ታሪክም እንዲሁ ነበር የእኛ የተለዬ አይደለም የሚለው አይደለም የእኔ መከራከሪያ፡፡ እርግጥ ነው ዓለም ከሰራው የተለዬ የእኛ ቀደምት አልሰሩም፡፡ ግን ግን የቀደሙትን በመተቸት ላይ ብቻ በዕውቀቱ ለምን ረክቶ ይቀራል ነው የእኔ መነሻ፡፡ የታሪክ ክስተቶችን የአሁኑን ለማስተማርና ለመገሰጽ ይጠቀምበት እንጂ የቀደሙትን ብቻ ዘልፎ አይቁም ነው፡፡ በዚህ ዘመን የታሪክ ደካማ ጎኖችን በማስቀጠል ለማትረፍ ደፋ ቀና የሚሉ ልሂቃንን መተቸት በአንጻሩ የበለጠ ጠቃሚ ይሆን ነበር፡፡ ታሪክን በዘመኑ አውድ ስንመዝነው በዓለም መድረክ ከተከሰተው ውጭ በእኛ ሃገር ብቻ ተለይቶ የተከሰተ ነገር የለም፡፡ የተከሰተውንም በ“ዘመኑ መንፈስ” ስናጤነው መጥፎም ቢሆን ቅሉ ጭራቅ ጎኑ ብቻ ገኖ ሊወጣ አይገባም፡፡ አሁን ያለውን ነባራዊ እውነታ መተቸቱ ግን የበለጠ ሃገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
በዕውቀቱ ስዩም ከዚህ ሁሉ ያልፍና አንድ ዘለላ የፈረንጅ መጽሐፍ አንብቦ ‘ኃይማት ለምኔ’ ማለቱን ይነግረናል፡፡ እስኪ አብረን እንከታተለው፤ “The Future of an Illusion የሚል የፍሮይድን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከሃይማኖት ጋር ፍቺ ፈጸምኩ” ይለናል፡፡ ለስንት የጠበቅነው ግሩም ልጅ ለአንድ ባህር አቋርጦ ለመጣ መጽሐፍ እጅ ወደላይ ብሎ ማንነቱን ሲሰጥ እናየዋለን፡፡ ከራሱ አንደበት ሲወጣማ አብሶ በጣም ያስደነግጣል፡፡ እንዲህ ብሎን በሕዝብ ጭብጨባ ከወጣበት ማማ ላይ ወርዶ ሲከሰከስ እናየዋለን፡፡ የበዕውቀቱ ጠንካራ መንፈስ በአንድ የፈረንጅ መጽሐፍ የሚፈረካከስ አይመስለኝም ነበር፡፡
ወደ ሃይማኖት ቀመስ ጉዳዩ አንዴ ልመለስና በገጽ 216 ላይ “ክርስትና በጥንታዊ ቁመናው… ሌሎችን የሚችልበት…” ትዕግስት እንዳልነበረው ይነግረናል፡፡ ከክርስትና በዓለም መሰበክ በኋላ ኃይማኖቱ በአገራችን ገናናና ብሄራዊ ሆነ፡፡ በማይካድ ሁኔታ ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ ቢሄዱ ክርስትና በአገራችን ባህልና አስተሳሰብ ላይ ከባድ አሻራ ማኖሩን ይገነዘቧል፡፡ ሌሎችን የማሳነስ ነገር እንኳ ቢኖር የሃይማኖቱ አስተምህሮ ሳይሆን የግለሰቦች ዘዬ መሆኑ እርግጥ ሆኖ በየዘመኑ ደግሞ ሁሉም ኃይማኖቶችና የኃይማኖት መሪዎች ይፈጽሙት የነበረ ነው፡፡ ምስራቃውያኑ በተለይ ጃፓን በሕግ ለክርስትና በራቸው ዝግ ነበር፡፡ እስልምና በአረብ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የዓለም ጥግ አብላጫውን ይዞታ በተቀናጀበት ግዛት ሁሉ ‘የእኔ ብቻ’ አምባገነንነትን አብዝቶ ይተገብረዋል፡፡ የሮማ ካቶሊክ በግዛቷ ሌላውን የምትሰማበት ጊዜ አልነበራትም፡፡ ሌላው ቀርቶ በኃይማኖቶች ታሪክ ቅርብ ክስተት የሆነው ፕሮቴስታንቲዝም እንኳ በመካከለኛው ዘመን በርካታ ተከታዮች ባፈራባቸው የአውሮፓ ግዛቶች እንዳቅሙ ጉንተላና ማስፈራሪያ ይፈጽም ነበር፡፡ በዕውቀቱ ከታሪክ መዘዝኩ ብሎ ነው የኢትዮጵያን ክርስትና ከመጭራቅ የሚከሰው፡፡ ባለንበት ዘመን እስልምና ሳዑዲ ውስጥ ክርስትና እንዲገባ አይፈቅድም ብዬ የሞኝ መከራከሪያ አላቀርብም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያ ውስጥ እስልምና በብዛት በሰፈነባቸው ግዛቶች ውስጥ በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ላይ ግፍ አልፈጸመም? ካቶሊኮች በመካከለኛው ዘመን በነፔድሮ ፓኤዝ፣ አልፎንሱ ሜንዴዝና ቤርሙዴዝ ጊዜ በተለይ ሱስንዮስን ከቀየሩ በኋላ ከጉንተላና ስራ ማስፈታት አልፈው ወደ16 ሺህ ገደማ የላስታና ጎንደር ንጹሃን ሰዎች መገደል ምክንያት አልነበሩም? ፕሮቴስታንቲዝም ዛሬ የኢትዮጵያን ክርስትና “ድንጋይ ከመሳም” ጋር አመሳስሎ አይወርፍም? የቅዱሳንን ገድል “ገደል” ብሎ መጽሐፍ አይጽፍም? ከዚህ የበለጠ የሌላውን ባህልና እምነት ያለማክበር ምን አለ? ፍትሃዊ ይሁን’ጂ እይታችን ጎበዝ! ገና ለገና ‘እኔን’ ባይ የለም ብሎ ምሳር ማብዛት ምንድነው?፡፡ ይህን የምለው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ሆኜ አሊያም የቤተ ክርስቲያኗ አባላትም መሰል ድርጊቶችን አይፈጽሙም ከሚል ጭፍንነት ላይ ቆሜም አይደለም፡፡ እንደየድክመቱ ሁሉም ይነቀፍ ዘንድ የተገባ ነው፡፡ ለአብሮነታችን የሚበጀውም እርሱ ነውና፡፡ ነገር ግን ልጅ በውቀቱ ሌላ ሌላውን አይዳስስም፣ አዚችኛዋ ላይ ግን ሳይበላው ያካል፡፡ ፍርደ-ገምድል ሆነብኝ፡፡ ሌላው ሌላውን ሁሉ እንተወውና እስልምና አሁን ላለው ተክለ ቁመና ለመብቃቱ ያኔ በተጀመረበት ዘመን የመጀመሪያዎቹ አማኞች ሲሰደዱ፣ አሳዳጆቹን አሳፍሮ መልሶ ተከታዮቹን ያስጠለላቸው እኮ በፍጹም ክርስቲያናዊ ባህልና እምነት የበለጸገው ንጉሥና ሕዝብ ነው፡፡ ይህን ይህንም መጥቀስ ይገባው ነበር፡፡ በቅርበት የሚያውቀውን ባህልና ቤተ እምነት በ“አወቅሁሽ ናቅሁሽ” ስልት ለርካሽ መስዋዕትነት ማቅረብ አጉራ-ዘለልነት ነው፡፡
በሌላ ጎኑ በጽሑፉ ውስጥ ለሥነ ጽሑፋዊ ውበት ሆን ተብሎ የተደረገ ማፈንገጥ በማይባል መልኩ እንደ “ምሽት” እና “ቢስማር” አይነት ቀበልኛ ቃላት መጽሐፉ ውስጥ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
እንደመውጫ፡- ስለዳግማዊ አጼ ምኒልክና የዘመቻው ትርክት የተከራከረበት መንገድና ቀረበው በፍጹም ማስረጃ የታሸ እውነነታ፣ ፍትሃዊነትና ምክንያታዊነት በእውነት የደራሲውን ከፍታ አሁንም የመሰከረ ነው፡፡ በማር ስለተለወሰው አደገኛ መርዝ፣ ጸረ-ኢትዮጵያዊው ተስፋዬ ገ/አብን ተንኮሎችና ውሸቶች ፉርሽ ያደረገበት መንገድ እጅግ ግሩም ነው፡፡ እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ቧልታይ (Satiric) ወጎቹ በበጎ ጎን የሚነሱ ናቸው፡፡ በ“ከአሜን ባሻገር” ላይ የብዕሩን ከፍታ ማዬት ችለናል፤ ነገር ግን በእስከአሁን ቀይታው (ማለትም “መግባትና መውጣትን” ከጻፈ በኋላ ባገኘው የእፎይታ ጊዜ)፣ ካለው የሥነ-ጽሑፍ ተሰጥኦ፣ በነ“እንቅልፍ እና ዕድሜ” ካሳየን አቅም አንጻር ስንመዝነው ግን ከዚህ የተሸለ ነገር ይዞልን ሊመጣም በተገባው ነበር፡፡