ሐሙስ፣ ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓመተ ምህረት
አሁንም ቀኑን እንቆጥራለን። ሌሊቱንም እንዲሁ። አሁንም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን ተግባር እንዘረዝራለን። አሁንም ሰዎች በገዛ ሀገራቸው እንዳውሬ እየታደኑ፣ እየተያዙ፣ ይታሰራሉ፣ ከሀገር ይሰደዳሉ፣ ይገደላሉ፣ እንላለን። አሁንም በየቤተክርስትያኑና በየመስጊዱ እግዚዖ እንላለን። አሁንም የሀገራችን ለም መሬት ከባለቤቱ ኢትዮጵያዊ እየተነጠቀ፤ ለሹማምንትና ለውጪ ሀገር ባለሀብቶች ተሠጠ እያልን እናላዝናለን። አሁንም ሹማምንት ጀኔራሎችና ዘመዶቻቸው፤ ከተማዎችን ፎቅ በፎቅ አድርገው፤ ድሃን ማደሪያ አሣጡት እንላለን። ምን የማንለው አለ! ብቻ በገባንበት አረንቋ አሁንም እንረግጣለን። የምንረግጠው ጭቃ እየላላ፤ ከሥሩ ያለውን መሬት እያወዛ፤ ያ ደግሞ በተራው ጭቃ ሆኖ የአዘቅቱን ጥልቀት እያረዘመ፤ ከጉልበታችን በታች የነበረው አድጎ ወገባችንን ቀፍድዶ ይዟል። አሁንም ባለንበት እንረግጣለን። እስከመቼ? “እስከመቼ!” ይሄማ እያንዳንዳችን ስንለው የምንውለው አይደል እንዴ! ምን አዲስ ነገር ነው! ወይ ጉድ! ጉድ እኮ ነው። መቼም ጭቃው ራሱ ደርቆ ለእግራችን መደላድል እየሠራ፤ እኛን ከፍ አድርጎ ገፍቶ አያወጣን! የለም ተመችቶናል! ባለንበት መርገጡ ተመችቶናል። “ወይ ንቅንቅ!” ብለን ተቸክለናል። ለወጉማ!
አንበሳን ለጫካ፡ ዝንጀሮን ለገደል
ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል!
ተብሏል እያልን እንፎክር የለ! ማቅራራቱንስ መቼ ተውን! ምን ጎድሎን። ብቻ ባለንበት እንረግጣለን። “ግፍና በደል ሲበዛ አመጽ አይቀሬ ነው!” ይባላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍና በደል አልበዛበትም? ሕዝቡስ አልተነሳም? ወጣቱ ሀገር እየለቀቀ፣ ካለበት እየፈለሰ ለውቅያኖስ ዓሳ እራት መሆኑ፣ አካሉ እየተዘለዘለ መሸጡ፣ በየሰው ሀገር ለእስር ቤት መዳረጉ፤ መመዘኛው ምንድን ነው? ተው እንጂ! ግፍና በደሉማ ሞልቶ ተርፏል። እኛም ባለንበት እንረግጣለን። አደራጅቶ የሚመራና ነፃ የሚያወጣን እስኪመጣ እየጠበቅን ነው።
አንዱ ድርጅት፤ “እኔ ብቻ ነኝ ትክክል! እኔን ተከተሉኝ! እኔ ነፃ አወጣችኋለሁ!” ይላል። የለም! ተው እንጂ! ይኼማ ሁሉም ድርጅቶች የሚፎክሩት ቀረርቶ፣ የሚያሰሙት ዜማ፣ አይደል እንዴ! እስኪ፤ “ብቻዬን መሄዱ አያዋጣም። ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ስለሆነ፤ ከሌሎች ጋር አብራለሁ። ሳብርም፤ ‘እኔ የምለውና የምፈልገው ብቻ!’ ብዬ ግትር አልልም።” ያለና የሚል ድርጅት ታውቃላችሁ? ብቻ ባለንበት እንረግጣለን። ጭቃውም ላልቷል። እግራችን እየሸሸን፤ የአዘቅቱ ሥርም እየረዘመ ነው።
ምሁራን አርቆ አስተዋዮች ናቸው። በትምህርት ያገኙት ዕውቀትና በልምድ ያካበቱት ተመክሮ፤ ከግለሰብ ሕይወታቸው አልፎ፤ ለኅብረተሰቡ መሪና አስተማሪ በመሆን፤ የአጠቃላይ ሕይወታችን ቀጣይ ይሆን ዘንድ ይረዳሉ። ለችግሮቻችን መፍትሔ ያስገኛሉ። አዎ! ብዙ፤ እጅግ ብዙ ምሁራን አሉን። ግን አሁንም ባለንበት እንረግጣለን። የምንረግጠው ጭቃ እየላላ፤ ሥሩ ሥር እየሰደደ፤ የሄደበትን እያወዛ፤ አውዝቶም እያጨቀየና እያላላ፤ እኛ ቀርተን እሱ እግር አውጥቶ እየረዘመ፤ አዘቅቱን የበለጠ አዘቅት አድርጎታል።
የኑሮ ትምህርት ቤት ያበለጸጋቸው አዛውንት ሞልተውናል። በየትኛውም ትምህርት ቤት የማይገኘውን የኑሮ ትምህርት ከነሱ የበለጠ የሚያውቅ ለማግኘት፤ ብዙ አስርታት ዓመታትን መጥገብ ያስፈልጋል። እናም ያለፈውን ኖረውበት፣ ለዛሬዎቹ ኮትኳች አስተማሪ ሆነው፣ የነገ ስብስብ ሕልውናችንን ገሃድ ሊያደርጉልን ኃላፊነት አለባቸው፤ ለነሱም ቀደምቶቻቸው እንዳደረጉላቸው። ኧረ! አሁንም ባለንበት እንረግጣለን! ተመችቶናል። የበዳዮችን ተግባር በመዘርዘሩ ተጠምደናል። ጭቃውም ላልቷል።
አዛውንትና ምሁራን ብቻ መሰሏችሁ! አይደለም! ሌሎቻችን ደግሞ፤ ሰላማዊ ሰልፍ እንውጣ ሲባል፤ ሃምሳ ሺ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት ከተማ፤ አምስት በመሆን፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ብቅ ይባላል! ወይ ጉድ! ጉድ እኮ ነው! በትንታኔያችን መጥቀናል። በጉራችን ወፍረናል። በቃል ስንጠቃችን ሠልጥነናል። ማን የሚበልጠን ተገኝቶ! ለውጪ ሀገር መንግሥታትና በጎ አድራጊዎች የኛን አቤቱታ ለነሱ ለማሰማት ፊርማ ሲባል፤ አንድ ሚሊዮን በሚገኘው ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን መካከል፤ አንድ መቶ ሺ ማግኘት፤ ተዓምር ነው። ብቻ ባለንበት እንዳክራለን። ጭቃውም ላልቷል።
ለትብብር ጠሪነት አንደኛ፤ ለመተባበር የመጨረሻ ታጋይ ድርጅቶቻችን አሁንም ባሉበት ይረግጣሉ! ከሥራቸው ያለው ጭቃም ላልቷል። ወይ መጥኔ! መጽሐፍት ይደረሳሉ። ሬዲዮኖች ያቧርቃሉ። ተናጋሪዎች ይናገራሉ። ግጥሞች ይደረደራሉ። ድረገጾች ይቀልማሉ። ፓልቶኮች ይንበለበላሉ። ዓመታትም ይቆጠራሉ። እኛም እንደለመድነው ባለንበት እንረግጣለን። ተመችቶናል። ጭቃውም ላልቷል። ከወገባችን ከፍ እያለ ነው። ወይ ጉዴ! እኛ ተቀምጠን ጭቃው እግር አውጥቷል! ባንድ አዘቅት ነውና ያለነው፤ እስኪ “እንመካከር! እባካችሁ!” የሚል ከመካከላችን ጠፍቷልና፤ እኔ ለሁላችንም ስል እባካችሁ! ባንድ እንመካከር!