[email protected]; www.girmaseifu.blogspot.com
ሰሞኑን በሀገራቸን ያለው ትኩሳት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው በአብዛኛው ተማሪውን ያሳተፈው “እንቢ የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በሚል የተነሳው ንቅናቄ ነው፡፡ ለዚህ ንቅናቂ መንሰዔ ናቸው በሚል የኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ የኦህዴድ ሾሞች መግለጫ እየሰጡ ይገኛል፡፡ በእነሱ መግለጫ መሰረት ደግሞ ጥያቄው ከዚህም አልፎ የመልካም አሰተዳደር ጭምር መሆኑን አምነዋል፡፡ ሁላችንም እንደምናሰተውለው ኦህዴድ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ከተወሰኑ ሰዎች ውጭ ለማየት እድል አልሰጠንም፡፡ ይህ ባጠቃላይ በኢህአዴግ ውስጥ ያለ ችግር ነው፡፡ የዚህ ችግር ምንጭ ገዢው ፓርቲ የሚከተለው መስመር ለተማረ ቀርቶ ለሚያመዛዝን ሰው እንኳን ምቾት የሚሰጥ አለመሆኑ ነው፡፡ ኤርሚያ ለገሠ የሚባለው የቀድሞ ኢሕዴግ ሹም ሂሣብ ተምረህ እንዴት ኢህአዴግ ሆንክ? የሚል ጥያቄ እንደቀረበለት ሰምቻለሁ፡፡ ይህን ለዛሬ እንለፈው፡፡
ሰሞኑን በተፈጠረው ንቅናቄ ሁለት ጎራ ተፈጥሮዋል፡፡ አንዱ መንግስት ያወጣውን የተቀናጀ ፕላን እንደወረደ ደጋፊ ሲሆን ሌላው ደግሞ እንደወረደ ተቃዋሚ፡፡ ከዚህ ውጭ ሃሳብ መያዝ በሁለቱም መስመር “ፀረ ህዝብ” በሚል ያስፈርጃል፡፡ ይህ ፅንፍ ግን ፀረ ኃሳብ በመሆኑ፣ በእኔ እምነት ተቀባይነት የለውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የግሌን ሃሳብ ላክፍላችሁ የወደድኩት እዚህም እዚያም በፌስ ቡክ የሰጠሁትን ሃሳብ ለማጠናከር ጭምር ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁን የተፈጠረው ችግር የኢህአዴግ እና በሽግግር ጊዜ ጀምሮ ኢህአዴግ ህገመንግሰቱን ሲያረቅ አባሪ ተባባሪ የነበሩ ቡድኖች የተከተሉት የፖለቲካ መስመር ችግር ውጤት ነው፡፡ ማለትም አሁን መንግሰት እተገብረዋለሁ የሚለው ዕቅድ ለማሳረፍ የሚፈልግበት የመሬት ፖሊስ አሁን እየተቃወመ የሚገኘው ኦነግ በዋነኝነት የተሳተፈበት የሽግግር ወቅት ሃሣብ ነው፡፡ የመድረክ አባል ድርጅቶች በሙሉ (የቀድሞ አንድነትን ሳይጨምር) የዚህ ፖሊሲ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ አሁንም በፊት አውራሪነት የሚቃወመው የዶክተር መረራ ጉዲና ኦፌኮ ጭምር መሬት የመንግሰት መሆኑን ከምር ይደግፋል፡፡ በቅንፍ ውስጥ ኦሮሞው መሬት እንጂ ገንዘብ ስለሌለው እንዳይፈናቀል በሚል የተሳሳተ ታሳቢ ማለት ነው፡፡
የኦሮሚያ ርዕሰ መሰተዳድር እንዲሁም አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ በተከታታይ በሰጡት መግለጫ ህዝበ ካልተሰማማ “ይህ የተቀናጀ ማስተር ፕላን” ተግባራዊ አይሆንም የሚል ቃል ሰጥተዋል፡፡ ይህን ቃል ሲሰጡ በተለይ ለአባዱላ ጋዜጠኛው ተገዳችሁ ነው ወይ? ስትላቸው አዎ የመረጠን ህዝብ ቢያስገድደን ምን አለበት ብለው መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይህን መልስ ወድጄዋለሁ፡፡ በፌስ ቡንክ ቋንቋ ላይክ አድርጌዋለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ታዲያ ይህን ማሰገደድ በመቀጠል አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሚያ ልጆች ገበሬ ሆነው እንዳይቀሩ፤ ከከተሜነት ትሩፋት እንዲቋደሱ መሬታቸው አሁን ከሚባለው የመጠቀም መብት ከፍ እንዲል የመሸጥና መለወጥ መብት እንዲጨምር የፖሊሲ/ህገ መንግሰታዊ ማሻሻያ/ እንዲደረግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በለገጣፎ አካባቢ አንድ ካሬ ሜትር ቦታ ከስምንት ሺ ብር በላይ መንግሰት መሸጡን ሰምተናል፤ ሰለዚህ መንግሰት ቢያንስ ከገበሬው በአንድ ሺ ብር ለመግዛት መዘጋጀት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ካልሆነም መንግሰት ማስተር ፕላኑን ሰርቶ መሰረተ ልማቱን ይዘርጋ ለማልምታ የሚፈልግ ደግሞ ከገበሬው ጋር ተደራድሮ ይግዛ፡፡ መቼም ይህቺ የኒዎ ሊብራል አስተሳስብ የምትዋጥ አትመስለኝም፡፡ ጉዳዩ ግን ይህው ነው፡፡ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የሚቃወሙ ወገኖች በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች ባሉበት ሁኔታ እንዲቆዮ ከሆነ በእርግጥ የአስተሳሰብ በሸታ ያለበት መሆን አለበት፡፡
ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ እና ለገዢው ፓርቲም ግልፅ መደረግ ያለበት “ውይይት ተደርጎ ህዝቡ ካመነ ብቻ ነው የሚተገበረው” የሚለው የርዕሰ መስተዳድሩ ፈራ ተባ እያሉ የሰጡት መግለጫ እና አፈ ጉባዔው በተመሳሳይ ፈራ ተባ ሲሉ የገለፁት ጉዳይ ነው፡፡ በኢቲቪ የርዕሰ መሰተዳድሩን መግለጫ ተከትሎ በተያያዘ ዜና በሚል የኢህአዴግ ዝቅተኛ ሹሞች “ይህ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ለአርሶ አደሩ ጠቃሚ ነው” በሚል መንፈስ በተቃውሞ የቆሙ ፀረ -ሰለም እና ፀረ-ህዝብ መሆናቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ ኦህዴድ/ኢህአዴግ ከዚህ በፊት ባለው ታሪካቸው አቶ አባዱላ እንደሚሉት አሳምነው ሳይሆን አስገድደው በመስራት ነው የሚታወቁት፡፡ አስገድደው እንደተመረጡም ረስተውት በተደጋጋሚ የመረጠን ህዝብ ሲሉ ሰው ይታዘበናል ማለት የተዉ ይመስላል፡፡ ሰለዚህ ህዝቡን ለማሳማን ኢህአዴግ ያመነበትን ማስተር ፕላን ይጠቅምሃል ተቀብል ሳይሆን፤ ውይይት ሲባል ለማሳመን ብቻ ሳይሆን ለማመንም ተዘጋጅቶ መሄድን ይጠይቃል፡፡ በነገራችን ላይ በብዙ መስፈርት ጠቃሚ መሆኑ ግንዛቢ ኖሮ ቢሆን እንኳን በማነኛውም ተራ ምክንያት አልቀበልም ካለ ይህን ለመቀበል ኢህአዴግ መዘጋጀት ያስፈልገዋል፡፡ ዲሞክራሲ ማለት መሳሳት ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ የተቀናጀ ማሰተር ፕላኑ በግልፅ ባልታወቀ ይዘቱ ጠቃሚ መሆኑ ቢታመን እንኳን አሁን ባለው የመሬት ፖሊሲ ቢተገበር የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርገው ከመሬቱ ከሚፈናቀለው አርሶ አደር ይልቅ ሌላውን ክፍል ነው የሚል አስተሳሰብ በፍፁም ውድቅ ሊደረግ የሚችል ምልከታ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው አሁን የተፈጠረው ችግር መሰረታዊው መንሰዔው ህገ መንግሰታዊ መሰረት የያዘው የዜጎችን ንብረት ማፍራት መብት የሚፃረራ የመሬት ባለቤትነት መብት ነው የምለው፡፡ ሰለዚህ ትግላችን መሆን ያለበት ዜጎችን ባለሀገር የሚያደርግ የመሬት ፖሊስ እንዲኖረን በሚያስችል ሁኔታ ህገ መንግሰታዊ ማሻሻያ መጠየቅ ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በዚሁ ጥያቄ መነሻነት አብዮት እንዲነሳ የሚፈልጉ መኖራቸው አንዱ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ይህ መንግሰት በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እየተሳነው መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ኢህአድጋዊያንን ሊጠርግ የሚመጣ አብዮት ሰለማዊውን ዜጋ እንደማይበላ ማረጋገጫ ሰለሌለኝ አብዮትን አልወዳትም፡፡ በቅርቡ የታተመውን የቀድሞ የደርግ ከፍተኛ ሹም የነበሩት ፍስሃ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” በሚል የፃፉትን መፅሃፍ እያነበብኩ አብዮቱ እንዴት አድርጎ ዜጎችን ሲቀረጥፍ እንደነበር ሳነብ ዳግም አብዮት የሚያሰኝ ነገር አልታየኝም፡፡ ገዢው ፓርቲ መሪዎች ይህን የሚያክል ጥራዝ ለማንበብ ጊዜም ሆነ ሞራል ባይኖራቸው እንኳን የዚህን መፅሃፍ መጨረሻ ክፍል ማጠቃለያውን አንብበው ለብሔራዊ ዕርቅ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ እፈልጋለሁ፡፡ እዚሁ መፅኃፍ ላይ አንባገነኑ መንግሰቱ የሚሰጠወን መክር አልሰማ ብሎ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ቢወራጭም መፍትሔ ሊያመጣ እንዳልቻልም፡፡ ኢህአዴግም እድሉን ቢጠቀምበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡
በሀገራችን ያሉ ተቃዋሚዎች አብዛኞቹ በሚያሳዝን ሁኔታ የሚገኙ መሆናቸው የሚያጋልጠው የሰሞኑን ክስተት አስመልክተው የሚሰጡት መግለጫ በፍፁም ፓርቲያቸው ቆሜለታለሁ ከሚለው መርዕ ጋር የሚሄድ አለመሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ፓርቲዎች ይህን አስታካው ህዝቡን ወደ ለውጥ እንዲመሩ አንድ አንድ ግለሰቦች/ቡድኖች ጥሪ እስከ ማቅረብ ደርሰዋል፡፡ እንኳን ሊመሩ መሪ የሚያስፈልጋቸው ደንባሮች እንደሆኑ ግን መግንዘብ ያልቻሉት ጥሪ አቅራቢዎቹ ናቸው፡፡ ለማነኛውም አብዮት እንደ ቱኒዚያው ቡሃዚዝ አይነቱ በሚጭሩት ትንሽ ጉዳይ ነገር ግን ሁሉም በሚሳተፍበት ሁኔታ ሊነሳ እንደሚችል ባምንም፤ አሁን ባለው ያልተቀናጀ ሁኔታ ባልጠራ መንገድ እብዮት መጥራት ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥል ይቸላል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ግን በፍፁም አንባገነኖችን እሺ ብለን እንገዛ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የሰሞኑ ጥያቄ በመሰረታዊነት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ በኦሮሚያ አርሶ አደሮች መፈናቀል የለባቸውም የሚል ነው፡፡ በተመሳሳይ በከተማ ያለም ነዋሪ ተገቢ ካሳ ሳይከፈለው በልማት ሰም መነሳት የለበትም ማለት ይኖርብናል፡፡ በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች በከተማ ማሰፋፋት ስም እየተነሱ ያሉ ሰዎች ተገቢ ካሳ ሊያገኙ ይገባል ማለት ይኖርብናል፡፡ በዚህ መንፈስ ጥያቄው ከተነሳ በከተማም በገጠርም ያለነው በጋራ ለመቆም እድል ይስጠናል፡፡
በመጨረሻ በመላው ሀገሪቱ ጥያቄያቸውን በተለያየ መንገድ ያቀረቡ ወጣቶች ህይወት በአንባገነኖች ጥይት እንዲቀሰፍ እርምጃ የወሰደው መንግሰት ከሃያ ዓመት በኋላም ግጭቶችን በጉልበት እንጂ በሰላማዊ መንገድ ለመቆጣጠር አቅም እንደሌለው ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ግድያዎች ደግሞ በፍፁም የሚረሱና የሚተዉ አይደሉም፡፡ የሞቱት ሁሉ በኢትዮጵያ ለለውጥ የተሰዉ ሰማዕታት ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ገዢው ፓርቲና መንግሰት ዜጎች ጥያቄ የማቅረብ መብታቸውን በመጋፋት በቁጥጥር ስር ውሎዋል የሚለው ቀረርቶ እና በምናብ ከሚስላቸው ፀረ-ህዝብና ፀረ-ሰላም ጋር የሚፈጥረው ምናባዊ ቁርኝት ድክመቱን ከማጋለጥ ውጭ ማንንም ግርታ ውስጥ እንደማይከት ማወቅ አለበት፡፡ አሁን በሚዲያ የምናያቸው የህዝብ አደረጃጀት ብሎ የሚሰበሰባቸው የፎረም አባለት የሚነግሩትን ከመስማት መታቀብ እና ትክክለኛውን የችግር ምንጭ ተቃዋሚ ከሚላቸው ቢያዳምጥ ይሻለዋል፡፡
ቸር ይግጠመን!!