ወያኔ የጅብ ባህሪውን በግልጽ ማውጣት ጀምሯል።መብላት ሲፈልግ ይጮሃል ያጯጯሁ ሁኔታ በየግዜው የተለያዩ ናቸው። ከዚህ ቀደም የወያኔ ጩኸቶችን በትንሹ ጠቋሚ የምላቸውን ሃሳቦች በማንሳት ለመግለጽ ሞክሬአለው ዛሬ ደግሞ ስለ ሰሞኑ የወያኔ ጩኸት ኢትዮጵያኖችን ለመብላት ጅቦችን እየጠራ እንደሆነ እናያለን። የጅቦች ነብስ በከንቱ የሚቀሩ ድምጻቸውም በህይወት እስካሉ ድረስ ብቻ የሚሰማ ነው። ኢትዮጵያኖች ሆይ ሰው እንሁን ሰው የሆንን ለታ ነብሳችን በክብር ያርፋል ድምጻችንም ዘመን ተሻጋሪ ይሆናል።
የሰሞኑ የወያኔ ጩኸት በወደ ጎንደር እና በወደ አዲስ አበባ ዙሪያ እየጮኸ ይገኛል። በግፍ ሃብት ንብረቱ ለሚነጠቅ የኢትዮጵያ መሬቱ ተቆርሶ ለሱዳን አይሰጥም የሚለው የጎንደር ገበሬ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚደረገውን የገበሬዎችን መፈናቀል ይቁም ብለው ሰላማዊ ሰልፍ በወጡት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በግፍ ለሚሞተው ኢትዮጵያዊ ወገኔ ልቤ እየደማ አይኖቼ እንባን እያዘነበ መሬት መሬቱን እየጫርኩኝ ግፈኞች እና በደል አድራሾች በቆፈሩት የግፍ ጉድጓድ እራሳቸው ይግቡ እያልኩኝ ሃዘኔን እገልጻለው። በደል ለሚያደርሱት በደላቸውን እንዲተዉ ምህረትን አውርድላቸው ወደ ልቦናቸው ተመልሰው መልካም እንዲያደርጉ ብዬ እንዳልጸልይ ሰይጣን ሆኑብኝ ሰይጣን ደግሞ ምህረትን አይፈልግም ወደ ምህረትም መምጣትም አይፈልግም። የወያኔ ሰዎችም ወደ ምህረት አንዱም አይመጡም መምጣትም አይፈልጉም። ሰይጣንም የሚወጣው በጸበል ኃይል ወያኔም በግድ አስገድዶ ካልሆነ በቀር ከስህተቱ ይማራሉ ብሎ ማሰብ ከንቱነት ነው።
ወያኔ (ህውሓት) ነጭ ጅብ ሆኖ ማለትም የጅቦቹ ንጉስ ሆኖ ለመብላት ሲፈልግ ጮኾ የሚጠራቸው ጅቦች አሉት። ብአዴን፣ ኦፒዲዮ፣ እና ደህዴን ይባላሉ። እነዚህ ጅቦች ወያኔ ካልጮኸ የማይጮኹ ወያኔ ካልበላ የማይበሉ በራሳቸው ምንም ማድረግ የማይችሉ ብቻ ሁሉንም በዘር ከፋፍሎ እንደ መዶሻ በመጠቀም አማራውን በብአዴን ኦሮሞውን በኦፒዲኦ ደቡቡን በደህዴን ለመምታት የሚጠቀምባቸው የግፍ በትሮቹ ናቸው። ወያኔ በራሳችሁ ሰዎች እና በመረጣችሁት ነው የምትመሩት በሚል ቁማር ሁሉንም በተናጠል እየሄደ መብላት ጀምሯል። ልዩነታችንን ትተን አንድ ሆነን በአንድነት እስካልታገልን ድረስ ኦሮሞውን በኦፒዲኦ አማራውን በብአዴን ደቡቡን በደህዴን ተመስሎ ወያኔ እያንዳንዳችንን እንደሚጨርሰን የታወቀ ነው። ለዚህም የሚሆነውን እና የሚሰራውን ስራ እያየን ነው። ኦሮሞ ለኦሮሞ የሚለውን ትተን አማራ ለአማራ የሚለውን ትተን ደቡብ ለደቡብ የሚለውን ትተን እጅ ለእጅ ተያይዘን አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ፣ ትግሬ፣ አፋር፣ ጋንቤላ፣ ሁላችን አንድ ነን ሁላችን ኢትዮጵያዊ ነን ብለን በመነሳት ከመጥፋታችን እና ከመጠፋፋታችን በፊት ቀድመን አስበን አገርን ከጥፋት ህዝባችንንም ከመከራ መታደግ ያለበት ወሳኝ ግዜ ላይ ነን። ተነጣጥለን በወያኔ ተበልተን ከማለቃችን በፊት ለግል ፖለቲካዊ ጥቅም በማሰብ በመለያየት ስራ ውስጥ ያሉት ሃይሎች ከግል ጥቅማቸው ይልቅ አገራዊ ጥቅምን በማስበለጥ ከግላዊ ክብራቸው ይልቅ ለህዝብ ክብር ቅድሚያ በመስጠት በአንድነት ሆነን በአንድነት ቆመን ጠላትን ማሳፈር አንባገነኖችን ማጥፋት የሚያስፈልግበት ግዜ ላይ ነን። ካለበለዛ ግን ከዚህ እስከዚህ የምንለው ክልል ጠቦብን ከዚህ እስከዚያ የምንለው ግቢ አጥተን ለመቀበሪያ የሚሆነንንም ጉድጓድ እንዳናጣ እሰጋለው። በፍቅር በአንድነት ሆነን መታገል አቅቶን ለቁጥጥር እንዳያመች አድርገን ነገሮችን አስፍተን በትነናቸው መሰብሰብ አቅቶን መከራችንን ለልጆቻችን እንዳናተርፍ በትግሉ ጎራ ያላችሁ ፖለቲከኞች ወደ አንድ አላማ በመምጣት ኢትዮጵያን ለሁል ግዜ የሰላም ቀጠና እና የፍቅር አገር የማድረግ ሃላፊነት አለባችሁ። ህዝቡም እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ሊከታተላቸው ይገባል።
በጎንደር ብአዴን የተባለው የወያኔ ቅጥር የጎንደርን ሃብቱን እና መሬቱን ለሱዳን ለመስጠት ብአዴን የተባለውን ጅብ ፈርሞ እንዲያስረክብ ወያኔ እየተሯሯጠ ነው። ምን ጎንደርን ብቻ ከወለጋን ከጋንቤላንም ጭምር እንጂ። ወያኔ ቀጥታ እንዳይፈጽመው ህዝቡ ከተነሳ ማብረድ ስለማይችል ይሄንን እየሰራ ያለው እናተው የመረጣችሁት ብአዴን ነው ለማስባል ነው። ወያኔ በደል ሰሪ ሆኖ ነገር ግን ነገሮቹ ከከፉ አስታራቂ መስሎ በመግባት እራሱን በአፈር ውስጥ እንደሚቀብር እባብ በመምሰል በፈጠራቸው ድርጅቶች ውስጥ እራሱን ቀብሮ በተመቸው ግዜ እየወጣ ህዝባችን ላይና አገራችን ላይ መርዙን በመርጨት እያጠፋ እና እየገደለ ነው።
ወያኔ በአዲስ አበባ ዙሪያ በማስተር ፕላን አማካኝነት የምስኪኑን ኢትዮጵያዊ ገበሬ መሬት ለመብላት በኦፕዲኦ አማካኝነት መጥቷል። ሌሎቹ እንደ ብአዴን እና ደህዴን ያሉት እዚህ ጋር ምንም አይመለከታቸውም ሁሉም ቦታ የሚመለከተው ወያኔ ብቻ ነው። በኦፕዲኦ ውስጥ ተሰውረው እራሳችሁ የመረጣችኋቸው መሪዎቻችሁ ናቸው በሚል ሰበብ ገበሬዎች አይፈናቀሉ በሚል በወጡት ሰላማዊ ሰልፈኖች ላይ ጥይት በማዝነብ በግፍ የንጹሃንን የሰው ክቡር ህይወትን እያጠፉ ይገኛል።
ወያኔ ዛሬ ኦሮሚያ ክልል፣ አማራ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ሱማሌ ክልል፣ ትግራይ ክልል፣ አፋር ክልል፣ ጋንቤላ ክልል፣ እያለ ከፋፍሎ የሰጠውን ካርታ አይተን የኛ ግዛት እዚህ ድረስ ነው ግዛታችን ይሄንን ያክላል ብለን የምንናገር ነገ ወያኔ ይሄ የተከለለው ክልል የናተ አይደለም እናተ የሚገባችሁ እዚህ ድረስ ነው ብሎ ማሳነስ እንደማይችል ምን ያህል እርግጠኖች ነን። እናተ ምን አገባችሁ ለሁሉም ክልሎች አጥር አጥሬ የሰጠኋችሁ እኔ ነኝ እንደውም ከአሁን በኋላ የናተ ግዛት እንደዚ አይደለም እንደዚህም የሚባል ክልል አከላለል የለም ብለው የሚከለክል አዋጅ እንደሚያወጣ ምን ዋስትና አለን። በየግዜው አዲስ ነገር ሲከሰት አዳዲስ ህጎችን በማውጣት እራሱን እንደ እስስት እየቀያየረ የሚቀርበው ወያኔ ክልል የሚባል የለም እንደማይል ምን ያህል እርግጠኛ ሆነን ነው የኔ ክልል ይሄ ነው ብለን የወያኔን የመከፋፈል ግዛ ስራን እየሰራልነት የምንገኘው ድል የምናደርገው ወያኔ ባስቀመጠልን መንገድ ስንጓዝ ሳይሆነ በፍቅር እና በአንድነት ለኢትዮጵያ ስንቆም ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰአት ሰጪም ከልካይም አሳሪም ፈቺም አቁሳይም ገዳይም ሁሉንም አድራጊ ሆኖ ማን ከኔ በላይ ማን ወንድ እያለ ነው። እኛ ደግሞ ለዚህ አላማው መንገድ ላይ በመገኘት ስለምንድነው ለጥፋት እና ለመጠፋፋት የምንጋለጠው? ለምንድነው ባዘጋጀልን የጥፋት ፈረስ ላይ የምንጋልበው? ነገ የሰጠንን የክልል ካርታ አግባብ አይደለም ብለው ቢያነሱት እኛ ምንድነው የምንለው? ይሄ ካርታስ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ሊያኖረን ይችል ይሆንን? በአገራችን በሰላም እንድንኖር ገበሬዎቻችን ያለ አግባብ እንዳይፈናቀሉብን መሬታችን ለሱዳን እንዳይሰጥብን ፖለቲከኖች ያለ አግባብ እንዳይታሰሩብን ወጣቱ ያለ አግባብ እንዳይገደልብን ጋዜጠኞች በነጻነት እንዲዘግቡልን በአጥር ተከፋፍለን አጥር ውስጥ ላለው ብቻ መጮህ ሳይሆን ከአጥር ውስጥ በመውጣት ወደ ትልቁ አገር ኢትዮጵያ በሚለው ሁላችንም በአንድነት አገራችንን ነጻ ለማውጣት በጋራ መታገል ይኖርብናል።
ህዝባችንን እና አገራችንን ከወደድን ኦሮሞን ለኦሮሞ አማራን ለአማራ የሚለውን ተረት ትተን በአንድነት ለአንዲት ኢትዮጵያ መቆም አለብን። ዛሬ እየተገደልን ያለው ስለተለያየን ነው ዛሬ አገር እየተዘረፈች ያለችው ተከፋፍለን ስላለን ነው ተከፋፍለን የምናደርገው የግል ትግል አሸናፊው እና ተሸናፊው ወደማይታወቅበት አዘቅት ውስጥ የሚከተን በመሆኑ እና ለወያኔም አመቺ ስለሆነ አንደነታችንን በግልጽ አውጀን ኢትዮጵያኖች እንደማንለያይ አንድ እንደሆንን አውጀን እውነተኛ ነጻነት ለማምጣት በጋራ እንታገል። አንድነት አሸናፊ ነው፣ አንድነት ፍቅር ነው፣ አንድነት ነጻነት ነው፣ አንድነት ኃይል ነው። አንድነት አንድነት አንድነት ለኢትዮጵያዊነት።
ከተማ ዋቅጅራ
07.12.2015
Email- [email protected]