የኢትዮጵያ ምሑራን በዲሞክራሲ ትግል ውስጥ በስፋት አለመሳተፍ በለውጥ ትግሉ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ

October 26.10.2015

ጃናሞራ ከስዊዘርላንድ

ወቅቱን በትክክል አላስታውሰውም ብቻ በግምት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2010 አጋማሽ ወይም መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል። በጀርመናዊቷ ከተማ በፍራንክፈርት አንድ ሕዝባዊ ሥብሰባ ይዘጋጃል። የሥብሰባው አዘጋጆች የያኔው የግንቦት 7 ንቅናቄ የጀርመን አስተባባሪዎች ነበሩ። የስብሰባውም አላማ የግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ የጀመረውን የነጻነት ትግል አስመልክቶ ከኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ለመወያየት ሲሆን በስብሰባው ላይ የተጋበዙት እንግዳ የግንቦት 7 ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ የነጻነት ታጋዩና ጀግናው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ነበሩ።

ስብሰባው እጅግ የተሳካና በስብሰባው ላይ የተካፈሉትን ኢትዮጵያውያን ሥሜት ያረካ ፤ በብዙዎች ጭንቅላት ሲመላለሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የመለሰ እንደነበረም ትዝ ይለኛል። በተለይ የተወሰኑ የአገዛዙ ደጋፊዎችና ካድሬዎች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ያነጣጠሩ አሉባልታዎችንና የስም ማጥፋት ተረት ተረታቸውን ባሰሙበት ወቅት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ትዕግስት እና በሳል አስተያየቶች መቼም አይረሱኝም። ከሁሉ በላይ ግን ቀልቤን የሳበውና ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ እንዲሆነኝ ያነሳሳኝን አቢይ ጉዳይ ግን እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ። የእለቱን ሥብሰባ ለማገባደድ በስብሰባው ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን አስተያየት መስጠት እንደጀመሩ አንድ በፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ካህን ከመቀመጫቸው በመነሳት መስቀላቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው ካማተቡ በኋላ በስብሰባው ላይ የነበርነውን ታዳሚዎች ሁሉ ያስደመመ እና ያስደነቀ ታሪክ እንዲህ በማለት ጀመሩ።

አንድ አባት ለጉብኝት ወደ ሀገረ አሜሪካ ይሄዱና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ወዳጆቻቸውን ከጠያየቁ በኋላ ወደ እናት ሐገራቸው ለመመለስ ይዘጋጃሉ።ታድያ ወደ ሐገር ቤት ከመመለሳቸው በፊት በአንዱ ቀን ወደ አንድ የጉብኝት ሥፍራ ይጓዙና ጉብኝታቸውን ይጀምራሉ። ከጥቂት ደቂቃ በኋላም ወደ አንድ በአጸድ የተሞላ የመቃብር ሥፍራ ይደርሳሉ። እኚህ አባት አጸዱን እያቋረጡ በሚሄዱበት ወቅት አይናቸው ወደ አንድ የመቃብር ሥፍራ ያመራል። ሐውልቱን ትኩር ብለው ሲመለከቱት በሐውልቱ ላይ የተጻፈው የሟቹ የህይወት ታሪክ እጅግ ያስገርማቸዋል። ፕሮፌሰር እከሌ በተወለደ በ 8 ዓመቱ አረፈ ይላል ጽሁፉ፤ እኚህ አባት በጣም ይገረሙና እንዴት ነው ነገሩ? እንዴት አንድ ሰው በስምንት አመት እድሜው ፕሮፌሰር ሊሆን ይችላል? እያሉ በውሥጣቸው እያብሰለሰሉ ወደ ሌላኛው መቃብር ሲጠጉ ሐውልቱ ላይ ዶክተር እከሌ በተወለደ በ3 አመቱ አረፈ የሚል ሌላ ጽሁፍ ይመለከታሉ። አይናቸውን ይጠራጠሩና በመሀረባቸው ጠረግ ጠረግ አድርገው እንደገና ቢመለከቱት ጽሁፉ ተመሳሳይ ሆኖ ያገኙታል። በጣም ተገረሙ! ግራ ተጋቡ! እዚህ ሐገር ደግሞ ትምህርቱ እንዴት ነው? ሲሉ ራሳቸውን ይጠይቁና መልሱን ስላላገኙት ሥለ ጉዳዩ ለመጠየቅና ለመረዳት በማሰላሰል ላይ እያሉ ትንሽ እንደተራመዱ አይናቸው ሌላ መቃብር ላይ ያርፋል። ይህኛው ደግሞ ኢንጂነር እከሌ በተወለደ በ5 አመቱ አረፈ ይላል። እጅግ በጣም ግራ የተጋቡት አባት ሥለ ሁኔታው ለመረዳት በአካባቢያቸው ሥለ ጉዳዩ ሊያስረዳቸው የሚችል ሰው እንዳለ በዓይናቸው ይቃኛሉ። በግርምት ከቆሙበት ሥፍራ ከደቂቃዎች በኋላ አንድ በእድሜያቸው ጠና ያሉ አሜሪካዊ አዛውንት ጠጋ ይሉና የምረዳዎት ነገር ይኖር ይሆን? ሲሉ ይጠይቋቸዋል። እኚህ ኢትዮጵያዊ አባትም ደንገጥ ብለው ኧ ኧ አዎ አዎ አንድ ነገር እንዲያስረዱኝ እፈልጋለሁ ይሉና በአመልካች ጣታቸው ወደ መጀመሪያው ሐውልት እየጠቆሙ በሐውልቱ ላይ ያነበቡትን ታሪክ መናገር ይጀምራሉ። እዚህ የመቃብር ሐውልት ላይ ፕሮፌሰር እከሌ በተወለደ በ8 ዓመቱ አረፈ የሚል ጽሁፍ ይነበባል። እንደገና ያኛው ሐውልት ላይ ደግሞ ዶክተር እከሌ በተወለደ በ3 ዓመቱ አረፈ ይላል። ይህኛው ደግሞ ኢንጂነር እከሌ በተወለደ በ5 ዓሙቱ ማረፉን ይገልጻል ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የዚህ ሐገር ሥርአተ ትምህርትሥ እንዴት ነው? አንድ ሰው በስምንት ዓመት እድሜው ፕሮፌሰር በአምስት እና በሶስት አመት እድሜ ደግሞ ዶክተር እና ኢንጂነር ለመሆን የሚቻለው ብለው ይጠይቃሉ። አሜሪካዊው አዛውንትም ሲመልሱ አዩ አባቴ ይህ ሰው በርግጥ ፕሮፌሰር ነው የተፈጥሮ እድሜውም እዚህ ሐውልቱ ላይ እንደሰፈረው አይደለም። የትምህርት ሥርአቱም ቢሆን ከሌላው ዓለም ብዙም የተለየ ሆኖ አይደለም። ነገር ግን ይህ ይህ ፕሮፌሰር በህይወት ሲኖር ለሐገሩና ለወገኑ የሚጠቅም ተግባር ያከናወነው ስምንት ዓመት ብቻ በመሆኑ በተወለደ በስምንት ዓመቱ አረፈ ተብሎ ሊጻፍ ችሏል። ሌሎቹም ያዩዋቸው ዶክተር እና ኢንጂነር በሕይወት ዘመናቸው ለሕዝባቸውና ለሐገራቸው የሚጠቅም እና የሚበጅ ተግባር የፈጸሙት አምስት እና ሶስት አመታት በመሆኑ የመቃብር ሐውልታቸው ላይ ለትውልዱ ጠቃሚ የሆነ ተግባር የፈጸሙበት አመታት ብቻ ተጻፉ ብለው ያስረዷቸዋል። እኚህ ኢትዮጵያዊ አባትም ባዳመጡት ታሪክ እጅግ ተገርመው እና ተደንቀው ማሰላሰል ይጀምራሉ። ራሳቸውንም እኔስ ለሐገሬ እና ለወገኔ የሚጠቅም ምን ተግባር አከናውኜአለሁ ሲሉ ይጠይቃሉ። በርግጥ እኚህ አባት በሕይወት ዘመናቸው እንደ ሃይማኖት አባትነታቸው የሚጠበቅባቸውን አድርገዋል። ነገር ግን እኚህ አባት በተመስጦ ሲያስቡት እሳቸው በሕይወት ዘመናቸው የፈጸሟቸው ተግባራት ሁሉ አንሰው ይታያቸዋል።

ኢትዮጵያዊው አባትም አሜሪካዊውን አዛውንት አመስግነው የመጨረሻ ጥያቄ አነሱ ። እንዲህ ሲሉ!! በእውነት ከነገሩኝ ታሪክ ብዙ ተማርኩ፤ ወደ ውስጤም ለመመልከት ቻልኩ፤ ራሴንም እኔስ ለወገኔ ምን ሰራሁ ሥል ጠየኩት። ካሉ በኋላ ለመሆኑ እኔሥ ስሞት በመቃብሬ ላይ ምን ተብሎ ሊጻፍ ይችላል ? ሲሉ ጥያቄአቸውን ይሰነዝራሉ። አሜሪካዊው አዛውንትም ጥቂት አሰቡና ለመሆኑ በሕይወት ዘመንዎ ለሐገርዎ እና ለወገኖችዎ የሚጠቅም እና የሚበጅ ምን በጎ ነገር አበርክተዋል ሲሉ ይጠይቃሉ?

ኢትዮጵያዊው አባትም ጥቂት ሲያሰላሥሉ ቆዩና እኔሥ ለሀገሬም ሆነ ለሕዝቤ ይሄ ነው የሚባል የረባ ነገር የፈጸምኩ አይመስለኝም ሲሉ መለሱ። አሜሪካዊው አዛውንትም እንግዲያው እንደ መልስዎ ከሆነና ለሐገርዎና ለሕዝብዎ የሚበጅ በጎ ነገር ያላደረጉ ከሆነ የርስዎ መቃብር ላይ እንደተወለደ አረፈ ተብሎ ይጻፋል አሏቸው !!!!! ብለው ታሪኩን ደመደሙት።

እጅግ አስደናቂ እና አስተማሪ ታሪክ ፡ የሰው ልጅ ያለውን እውቀት ሁሉ ለሌላው ሲያካፍል ፤ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በጎ ተግባራትን ለመፈጸም ሲዳክር እና ሲደክም ፤ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ አስተሳሰብ እና ተግባራት ሲኖሩት ከዚህች ከምንኖርባት አለም ቢያልፍ እንኳን በሕይወት ዘመኑ የፈጸማቸው መልካም ተግባራት ሕያው ሆነው ሥሙ ከመቃብር በላይ ከትውልድ ትውልድ ሲዘከር እንደሚኖር ታሪክ ያስተምረናል።

እንግዲህ ለመግቢያ ያህል ይህንን በኔ አመለካከት ታላቅና አስተማሪ ሊሆን የሚችል ምሳሌአዊ ቁም ነገር ካቀረብኩ በዚህ ጽሁፍ ለማስተላለፍ ወደ ተነሳሁበት መሰረተ ሃሳብ ልለፍ፡

በአንድ ሃገር ውስጥ የተረጋጋ ሰላም እና እድገት እንዲመጣ በሐገሪቷ የሚኖሩ ምሁራን እውቀታቸውን እና ልምዳቸውን አስተባብረው ሙያዊ አስተዋጽኦቸውን ለሚኖሩበት ሓገርና ማህበረሰብ በማካፈል፤ በማስተማር ፤በማስተባበርና፤ አብሮ በመስራት እንዲሁም የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማሳየትና በማመላከት የዜግነት ድርሻቸውን ሲወጡ እንደሆነ ከተለያዩ ሓገራት ልምድ በመነሳት መናገር ይቻላል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያውያን ምሑራን ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ በሓገራችን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን በተደረገው ትግል በተለያዩ ጊዜያት ቀላል የማይባል መስዋእትነት ሲከፍሉ መቆየታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግል ላይ የተካፈሉት ኢትዮጵያውያን ምሑራን ከቁጥራቸው አኳያ ሲታይ ኢምንት ቢሆንም በነጻነት ትግሉ ላይ ትተው ያለፉት አሻራ ግን በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም።

የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ በዋናነት ኢትዮጵያዊ ምሑራንን የመተቸት ወይም የመውቀስ ሳይሆን በኔ እይታ ለዘመናት የተደረገው የለውጥ ትግል አመርቂ ውጤት አለማምጣት ዋና ዋና ምክንያቶች ሆነው ያገኘኋቸውን ነጥቦች ለማንሳትና ከተቻለ ጽሁፉን በቅንነት በመመልከት ውይይት ለመጫር እንዲረዳ ነው።

የኢትዮጵያ ምሑራን በዲሞክራሲ ትግል ውስጥ በስፋት አለመሳተፍ በለውጥ ትግሉ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ

ሓገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ጎልማሳ እና ዕድሜ ጠገብ ምሑራን ባለቤት ናት።በተለያዩ ጥናቶች ላይ እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት እጅግ በርካታ የተማሩ ዜጎች እና ምሁራን ከሚሰደዱባቸው ሓገራት መካከል የመጀመርያውን ደረጃ ይዛ የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደሆነች በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ሲገለጽ ሰንብቷል። እነዚህ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ምሑራን ከትውልድ ሓገራቸው ለመሰደዳቸው ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በሐገራችን ኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ቀውስ መሆኑ አያጠያይቅም።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ቁጥራቸው እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሑራን በየዘመናቱ በነበሩ አምባገነን ገዢዎች ጭቆና እና ዘረኝነት ተማረው የሚወዷትን ሐገራቸውን ጥለው በመሰደድ በተለያዩ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ከተሞች የተሳካላቸው በሙያቸው፡ ዕድል ፊቷን ያዞረችባቸው ደግሞ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰልፈው ኑሮአቸውን በመግፋት ላይ ይገኛሉ።እንግዲህ በተለያዩ ምክንያቶች ከሚወዷት የትውልድ ሐገራቸው ከተሰደዱት ምሑራን መካከል የአምባገነኖችን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ አሽቀንጥሮ በመጣል በምትኩ ፍትህ የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት በሚደረገው ትግል ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ምሑራን ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑ በለውጥ ትግሉ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም።

ይህንን ስል ግን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል ላይ የግምባር ሥጋ በመሆን በተለያየ የትግል ዘርፍ መስዋእትነት እየከፈሉ ያሉና የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምሑራን እንዳሉ በፍጹም አይዘነጋም ።ለነዚህ ወገኖቼም ታላቅ ክብር እና ፍቅርም አለኝ።

ለመሆኑ በርካታ ምሑራን ወደ ፖለቲካው ትግል መድረክ የማይመጡበት ምክንያቶች ምንድናቸው ?

ምሳሌ ላንሳ ከ6 ዓመት በፊት ይመስለኛል በሳይበር ታሪክ የመጀመርያ የሆነ ፓናል ዲስከሽን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች መወያያ መድረክ (ECADF በወቅቱ እንዳሁኑ በርካታ ሚዲያዎች አልነበሩም ) ይዘጋጃል። በዛ ፓናል ዲስከሽን እንዲሳተፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሑራን ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፤ አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞች ተጋብዘው የነበረ ሲሆን የውይይቱ ርዕስም በርካታ የሆኑ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚታገሉለት ዓላማ እና ማኒፌስቶአቸው ሲታይ በአብዛኛው ተመሳሳይ መሆኑና ሁሉም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ለመመሥረት የሚታገሉ መሆናቸውን እየገለጹ ነገር ግን የጋራ ጠላታቸውን ለመታገል በህብረት ሲሰሩ አለመታየታቸውን አስመልክቶ እነዚህ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በጋራ ሊያሰራቸው የሚችል ሚኒመም አጀንዳ ምንድነው የሚል ነበር። በዚህ ውይይት ላይ እንዲሳተፉ ከተጠየቁት በርካታ ምሑራን መካከል ጥቂቶቹ ፈቃደኝነታቸውን በመግለጽ በውይይቱ ላይ በመሳተፍ እውቀታቸውን እና ልምዳቸውን በመጠቀም ለውይይቱ ተሳታፊዎች እና ለታዳሚዎቻቸው ይበጃል ያሉትን አስተያየታቸውን ያካፈሉ ሲሆን በርካቶቹ ግን በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኞች አልነበሩም። በውይይቱ ላይ ላለመሳተፍ ያቀርቡ የነበረው ምክንያት ግን እጅግ አሳዛኝ እና አስገራሚ ነበር። ለምሳሌ አንዳንዶቹ ካነሷቸው ምክንያቶች ውስጥ በውይይቱ ቢሳተፉ በገዢው መንግስት ካድሬዎች ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል ፤ ወደ ሐገር ቤት ለመሄድ በዝግጅት ላይ በመሆናቸው እንዲህ አይነት ውይይት ላይ መሳተፍ እንደማይችሉ ፤ አንዳንዶቹም ጉዳዩ ፍጹም እንደማይመለከታቸው እና እንደማያሳስባቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከውይይቱ በኋላ ሊደርስባቸው ስለሚችል ትችት እና ዘለፋ በነሱ አገላለጽ ስድብ ምክንያት በውይይቱ ላለመሳተፍ እንደወሰኑ ነበር የገለጹት። ሌላው እጅግ የሚያሳዝነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የገዘፈ ስም ያላቸው ምሑራን ጭምር ለውይይት ሲጋበዙ የሌሎችን ተጋባዦች ስም በመጠየቅ እሱ ብሎ ምሑር፤ እሷ ብሎ ምሁር ፤ እሱ ካለ አልመጣም፤ እሷ ካለች አልመጣም በማለት ከአንድ እድሜ ጠገብ ምሁር ፖለቲከኛ የማይጠበቅ አሳፋሪ እና አሳዛኝ መልስ በመስጠት በውይይቱ ሳይሳተፉ መቅረታቸውን አስታውሳለሁ። ይህ አይነቱ ችግር አሁንም ድረስ የቀጠለ እና አፋጣኝ መፍትሄ የሚያስፈልገው አቢይ ችግር እንደሆነ የተለያዩ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ጋዜጠኞች ሲናገሩ ይደመጣል።

ከነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል በተለይ ትችትን እና ስድብን በመፍራት ወይም በመጥላት ራስን ገለልተኛ በማድረግ ከምንም ነገር ነጻ አድርጎ ለመቀመጥ መሞከር ከአንድ ፊደል ከቆጠረ እና ከፍተኛ እውቀትን ከገበየ ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም። ይህ የተያያዝነው የነጻነት ትግል እንዲህ በቀላሉ የማይታይና እጅግ ከባድ የሆነ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑም መዘንጋት የለበትም። ነጻነትም በነጻ እንዲሁ ሳይደክሙ እና ሳይለፉ የማይገኝ ክቡር እና ውድ ከፈጣሪ የተሰጠን ጸጋ መሆኑን ለአፍታ እንኳን ልንዘነጋው አይገባም። በአንድ ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ስለተሳዳቢዎች ተጠይቆ የመለሰውን መልስ ልዋስ * ተሳዳቢ ለመሆን ትምህርት ቤት መሄድ አያስፈልግም ተሳዳቢ ለመሆን የሚያስፈልገው ክራይቴሪያ ባለጌ መሆን ብቻ ነው ነበር ያለው * እናም የባለጌዎችን ስድብ እና ትችት ፈርተን እጅግ ክቡር የሆነውን ነጻነታችንን ለመቀዳጀት ከሚደረግ ትግል መራቅ ከሕሊና ተጠያቂነት አያድንም። በዚህ የነጻነት የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ምትክ የማይገኝላትን ሕይወታቸውን ለነጻነታቸው እና ለሐገራቸው ሉአላዊነት ለመሰዋት በበረሃ የተሰለፉ ጀግኖች ወንድሞች እና እህቶች አሉና !! ከጊዜያዊ ከበሬታ ይልቅ ዘላቂ እና ቋሚ የሆነው ነጻነታችን ከምንም ነገር በላይ ቀዳሚ ነውና !!

ሌላው በተለያየ የሙያ ዘርፍ ከፍተኛ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ምሑራን በተለያዩ ምክንያቶች በዴሞክራሲያዊ ትግሉ ላይ ባለመሳተፋቸውና ቸልተኝነት በማሳየታቸው የተለያዩ የማህበረሰብ መገናኛ ዘዴዎችን እና የፖለቲካ መድረኩን ሐገራዊ ራዕይ የሌላቸው፤ በስሜት የሚመሩና ካለነሱ ሰው ያለ የማይመስላቸው፤ ለግል ጥቅማቸው የሚዳክሩ የዕውቀት እና የእውነት ድሖች የሆኑ ብልጣብልጦችን በየመድረኩ ላይ እንዲፈነጩበት አድርጓቸዋል። እነዚህ የአስተሳሰብ እና የዕምነት ድሆች ደግሞ በነጻነት ትግሉ ላይ ደንቃራ በመሆን ትግሉን ወደኋላ ለመጎተት ሲፍጨረጨሩ ይስተዋላሉ። እነዚህ ከራሳቸው ጥቅም ውጭ ሌላ ነገር የማይታያቸው ስግብግብ ግለሰቦች ተልኮአቸው ከአንዱ የፖለቲካ ድርጅት ወደ ሌላው በመዝለል ድርጅቶችን ማዳከም ሲሆን በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን የሚሰባሰቡባቸውን ኮሚኒቲዎች እና የእምነት ተቋሞችን ሳይቀር በማዳከም እና በማፈራረስ ኢትዮጵያዊው ተስፋ ቆርጦ ቤቱን ዘግቶ እንዲቀመጥ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ። በአንዳንድ አካባቢዎች በሐገሩ መኖር ተስኖት ሕይወቱን ለማስተካከል የሚሰደደውን ኢትዮጵያዊ ሥደተኛ የድጋፍ ወረቀት እንጽፋለን በሚል ለፍቶ የሚያገኛትን ሳንቲም መዝረፍን፤ በእምነት ተቋማት ውስጥ ሰርጎ በመግባት ከምእመናን የሚሰበሰበውን ሙዳየ ምጽዋት መስበርን ኑሮአቸው አድርገው ተያይዘውታል። በመሆኑም እንደነዚህ አይነቶቹን ደካሞች በቃችሁ ካላልናቸውና ብቃቱና ችሎታው ያላቸውን ዜጎች መተካት ካልቻልን በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉት ሆድ አደሮችና የግልጥቅም ያሳወራቸው ደካሞች ኮሚኒቲዎቻችንን ማዳከምና ማፈራረስ በእምነት ተቋሞቻችንም ውስጥ ገብተው ሙዳየ ምጽዋት መስበራቸውን አያቆሙም።

ሌላው ሳልጠቅሰው የማላልፈው በአንዳንድ ምሑራን ዘንድ የሚንጸባረቀውን የርሥ በርስ መጠላለፍ እና አለመከባበር እንዲሁም የራስን ድክመት ለመሸፈን የሌሎችን ግድፈት ነቅሶ የማውጣት አባዜ ነው። የተያያዝነው የነጻነት ትግል እጅግ አድካሚና ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ መሆኑ እየታወቀ ሁሉም ጠጠሩን በጋራ ጠላቱ ላይ ከመወርወር ይልቅ ትኩረትን ወደ ጎን አዙሮ እርሥ በርስ መናቆር እና እኔን ብቻ ስሙኝ ፖለቲካ የትም ሊያደርሰን እንዳልቻለ ካለፈው ተሞክሮአችን መረዳት ይቻላል። ሁሉም አካባቢውን ቢያጸዳ ከተማችን የጸዳች ትሆናለች የሚል መፈክር ትዝ ይለኛል። አዎ ሁላችንም ትኩረታችንን ወደ ዋናው ጠላታችን በማዞር የድርሻችንን ብንወጣ የምንመኘውን ነጻነት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርአት እውን ማድረግ እንችላለን።

አንድ ምሳሌ ላንሳ ከ 5 ዓመት በፊት የተከናወነ ጉዳይ ነው። በወቅቱ በጣም ያስገረመኝ እና ያሳዘነኝ ጉዳይ በመሆኑ ከላይ ለመጥቀስ የሞከርኩትን የመጠላለፍ እና እኔ እበልጥ አተካራ ሊያስረዳልኝ ይችላል በማለት አነሳዋለሁ።

Mr. X በሙያቸው ኢኮኖሚስት የሆኑ ታዋቂ ፖለቲከኛ እና ምሑር ሲሆኑ በነጻነት ትግሉውስጥ ከፊት በመሆን የዜግነት ድርሻቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ ናቸው።   Mr. Y እንዲሁ በሙያቸው ኢኮኖሚስት የሆኑና በተለያዩ ድህረ ገጾች ላይ አስተማሪና ጠቃሚ የሆኑ አርቲክሎችን በመጻፍ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ናቸው።

ታድያ ከዕለታት በአንዱ ቀን በአንድ የአውሮፓ ከተማ ሥለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጉዳይ ለመወያየት እና ሐገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለማስረዳት ሥብሰባ ይዘጋጃል። በዚህ ውይይት ላይ ተገኝተው ንግግር እንዲያደርጉ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት ምሑራን ይጋበዛሉ። የሥብሰባው አዘጋጆች ውይይቱን Mr. X የኢትዮጵያን ፖለቲካ አስመልክቶ ንግግር እንዲያደርጉ ሲነገራቸው በደሥታ ተቀብለው ለውይይቱ ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ።  Mr. Y ደግሞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አስመልክቶ ንግግር እንዲያደርጉ ይነገራቸውና ተስማምተው የስብሰባው ቀን ይጠበቃል። እንዳይደርስ የለም የስብሰባው ቀን በጉጉት እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ውይይቱ ሊካሄድ አንድ ቀን ሲቀረው Mr. Y ለስብሰባው አዘጋጆች በውይይቱ ላይ እንደማይገኙ በኢሜል ያሳውቃሉ። የውይይቱ አዘጋጆችም በሁኔታው ተደናግጠው ሥለ ሁኔታው ማብራርያ ይጠይቃሉ Mr. Y ግን ሌላ ቀጠሮ ሥላላቸው መምጣት እንደማይችሉ ይገልጻሉ። የውይይቱ አዘጋጆችም በዛ ሁኔታ ሌላ ሰው ለመጋበዝ በቂ ጊዜ ባለመኖሩ ለ Mr. X የተፈጠረውን ችግር አስረድተው እሳቸው ሁለቱንም አርዕስት እንዲሸፍኑ ይደረግና ውይይቱ በዕለቱ ይከናወናል።

ታድያ እጅግ የሚገርመው እና የሚደንቀው Mr. Y በውይይቱ እንደማይካፈሉ በገለጹበት ወቅት ማለትም ከውይይቱ አንድ ቀን በፊት ለውይይቱ አዘጋጆች ኢሜል በላኩበት ቅጽበት ማለት ነው 15 ገጽ ያለው ጽሁፍ በኢንተርኔት ይበትናሉ። ጽሁፉም የሚያጠነጥነው በውይይቱ ላይ አብረዋቸው እንዲሳተፉ የተጋበዙት Mr. X በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አስመልክተው የጻፉትን ጽሁፍ የሚያጣጥልና ግድፈት ያለበት መሆኑን የሚገልጽ ነበር። Mr. Y ጽሁፉን ማውጣታቸው መብታቸው ቢሆን እንኳን ጽሁፉን ለማውጣት የመረጡት ቀን ሆን ተብሎ የ Mr. Xን ሙያዊ ብቃት ለማሳነስና በውይይቱ ላይ እንቅፋት ለመፍጠር ሆን ብለው ያደረጉት መሆኑን መገመት ይቻላል። በተጨማሪም Mr. Y በውይይቱ ላይ ተካፍለው ለውይይቱ ተሳታፊዎች እና ውይይቱን በተለያየ መንገድ ለሚያደምጡ ዜጎች ከእውቀታቸው ቢያካፍሉ የተሻለ ይሆን ነበር። እዚህ ላይ Mr. Y ሃሳባቸውን ለምን በጽሁፍ አቀረቡ የሚል አመለካከት የለኝም ነገር ግን የሌሎችን ድክመት በማሳየት አዋቂ ለመምሰል ከመጣር የራሥን ጥንካሬ በተግባር በማሳየት ሌሎችን ለማስተማር መሞከር ብልህነትና አዋቂነት መሆኑን ለማሳየት ነው።

በአጠቃላይ ይሉኝታ ፤ ፍርሐት ፤ቸልተኝነት ፤ራሥ ወዳድነት ፤ጊዜያዊ ከበሬታን ፍለጋ ፤መጠላለፍ ፤እኒ እበልጥ እኒ እበልጥ፤ እኒ ከሌለሁ አፈርሰዋለሁ የሚሉት በሽታ ፤በሕዝብ ትግል ራስን ለማሳደግ መጣር ፤ሥግብግብነት ወዘተርፈ የሚባሉ ጥርቅምቃሚ አመሎች የነጻነት ትግሉን ክፉኛ እየጎዱ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል።

በነገራችን ላይ በዚህ ጽሁፍ ላይ ከሌላው የማሕበረሰብ አባላት የተሻለ ግንዛቤና እውቀት ስላላቸው አስተያየቴን በምሑራን ላይ አተኮርኩ እንጂ ይህ ችግር በሁሉም ኢትዮጵያዊ በአብዛኛው የሚንጸባረቅ መድሀኒት የሚያሻው የፖለቲካ ኢቦላ ነው:: በተጨማሪም ምሑራኖች በተለያዩ ዘርፎች የሚያነሷቸው የግል ሃሳቦችና ውሳኔዎቻቸው ፈጣን የሕዝብ ድጋፍና መነሳሳትን በመፍጠር በሐገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካ ላይ ጉልሕ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል በመሆኑ የኢትዮጵያ ምሑራንም ሐገራችን ከገባችበት አዘቅት የምትወጣበትን መላ በመዘየድ የመሪ እና የአቅጣጫ አመላካችነት ሚናቸውን በግምባር ቀደምትነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል የሚል የጸና እምነት ስላለኝ ነው።

ዛሬ በስደት የምንኖርባቸው የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሐገራት ከመሬት ተነስተው አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እንዳልደረሱ ግልጽ ነው። እንደሚታወቀው የቀደመው ትውልድ ምሑራን ሕዝብን በማስተባበር ከፍተኛ መስዋእትነት እና ከባድ ዋጋ ከፍለው ለዛሬው ትውልድ መሰረት እንደጣሉ ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው። እንግዲህ እኛም ሐገራችን እንደ ሐገር እንድትቀጥል እና ሌሎች የደረሱበት ደረጃ እንድትደርስ የምንፈልግ ከሆነ ሁላችንም ዛሬ ነገ ሳንል አሁኑኑ የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል። አለበለዚያ ያቺ የምንመኛት ዘመናዊት ዴሞክራሲያዊት ኤትዮጵያ እንደ መና ከሰማይ አትወርድም። እኛው አምጠን ካልወለድናት።

በመጨረሻም ምንም እንኳን መማር የተፈጥሮን ባህርይ ሙሉ በሙሉ መለወጥ ባይችልም የሰውን ልጅ ባህርይ ለመግራት ያለው አቅም ግን ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም። መማር አይነ ልቦናን ይከፍታል፤ ክፉና ደጉን ለመለየት ያግዛል፤ ተፈጥሮን ለመመርመር ይረዳል ። አይነ ልቦና ሲከፈት ደግሞ የችግሮቹ ሁሉ መንስኤዎች ፍንትው ብለው ይታያሉ ። ያኔ መፍትሔውም በእጃችን እንዳለ መረዳት ከባድ አይሆንም።

እንግዲህ ከላይ በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተቀመጠው ሁላችንም ለሀገራችንና ለወገናችን ሊጠቅም የሚችል በጎ ነገር መስራታችንን ራሳችንን እንጠይቅ። አንድ ሰው በዚህ ምድር ላይ ይሄን ያህል ጊዜ ኖሮ አለፈ የሚባለው በህይወት ዘመኑ ለሐገር እና ለወገን የሚበጅ እና የሚጠቅም መልካም ነገር አበርክቶ የድርሻውን ተወጥቶ ሲያልፍ ብቻ ነው። መልካም የሰራ ሥራው ለዘላለም ሕያው ሆኖ ይኖራልና !! ሥም ከመቃብር በላይ ይኖራል ይባል የለ !!

 

ጃናሞራ

janamoraeth@gmail.com

Previous Story

በጎንደር ከተማ 6 የፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት ተፈፀመ፡፡

Azeb Mesfin
Next Story

የባራክ ኦባማና የወይዘሮ አዜብ መስፍን ታሪካዊ ግንኙነት

Latest from Blog

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት

የኢካን ዓላማ በኔዘርላንድ የሚኖረውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ኮምዩኒቲይ የማሰባሰብ ሳይሆን የመከፋፋልና የማዳከም ተልኮን ያነገበ ነው።

አገር ! ለየአንድ ሠው ቋንቋው፣ ልማዱ፣ ባሕሉ፣ እምነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ ወጉና በአጠቃላይ እሱነቱና ማንነቱ የሚከበርበት ብቸኛ ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያውያንም በስደት በሚኖሩባቸው አገራት ሁሉ እነኝህን በስደት ያጧቸውን የግልና የጋራ ማንነቶቻቸውን በአንድ ላይ ሆነው ለመዘከር

ፋኖ ምሽጉን ደረመሰው ድል ተሰማ | ” ስልጣን እለቃለሁ ” ፕረዚዳንቷ | ህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ | “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ

-966+9-የኦህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ – ስልኩ ተጠለፈ “እኛ የምን’ዘጋጀው ለፋኖ ሳይሆን ለኤር-ትራ ነው” አበባው|”በጊዜ ቦታ አዘጋጁልኝ” አረጋ

አንድ በኢኮኖሚና በሌሎች ነገሮች ወደ ኋላ የቀረች አገር አንድን ኃያል መንግስት በመተማመንና ጥገኛ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣትና የተሟላ ነፃነትን መቀዳጀት ትችላለች ወይ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ሰኔ 4፣ 2016 (ሰኔ 11፣ 2024)   በዚህ አርዕስት ላይ እንድጽፍ የገፋፋኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑኑ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቻይንንም ሆነ የቬትናምን በኢኮኖሚ ማደግ አስመልክቶ ሁለቱ አገሮች እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከአሜሪካ ጋር

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት አብይና ዳንኤል ክብረት ጉድ አሰሙ-|ጀነራሉ በቁ*ጣ ተናገሩ-‘ህዝቡ ጉድ ሰራን’-|“ብልፅግናን ራ*ቁቱን አስቀርተነዋል”-|ታዳሚው ባለስልጣናቱን አፋጠጠ
Go toTop