ግዱን ለመጣል ቅርንጫፉን መመልመል – ይገረም አለሙ

በሀገራችን ጥበበኛ ዛፍ ቆራጮች አሉ፡፡ከርዝመቱ የውፍረቱ, ካዳገበት ቦታ ጠባብነት፣ የቅርንጫፎቹ ብዛት፣ የሚያሳፈራውን ዛፍ አንድም ጉዳት ሳያደርሱ እንዳልነበረ ያደርጉታል፡፡ ቆረጣውን ለመጀመር ዛፉ ላይ ሲወጡ ተመልክቶ እንዴት ተደርጎ ያለ ሰው ፍጻሜውን ሲያይ አጀኢብ ማለቱ አይቀርም፡፡ በስራው የተካኑት እነዚህ ባለሙያዎች በቅድሚያ ዛፉንና ዙሪያውን በደንብ ያጠናሉ፡፡ ከዛም ከአናት ይወጡና ተራ በተራ ቅርንጫፎቹን በመመልመል ግንዱን መለመላውን ያስቀሩታል፡፡ በመጨረሻም ግንዱን ለመጣል ያላቸውን ቦታ ይገምቱና ከላይ ጀምረው በመጠን በመጠን እየቆረጡ ከአሳነሱት በኋላ ከስሩ ቆርጠው ይጥሉታል፡ አንድም የቤት ጣራ ላይ ጉዳት ሳይደርስ፡፡

የፖለቲካው ትግል ሰላማዊም ይሁን ሁለገብ በዚህ ስልት መካሄድ ያለበት ይመስለኛል፡፡በቀጥታ ግንዱ ላይ አተኩሮ የሚደረግ ትግል ጉዳቱ ያመዝናል፤ግንዱ መውደቁ ላይቀር በመውደቁ በራሱ የከፋ አደጋ ያደርሳል፡፡እናም አደጋውን ለመቀንስ፤መስዋዕትነቱን ለማሳነስ ብሎም ውጤቱን አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ግንዱንና ቅርንጫፎቹን ለይቶ ማወቅ፤የቅርንጫፎቹን ብዛት ውፍረትና ርዝመት ማጤን ከዛም እቅድ አውጥቶ የአፈጻጸም ስልት ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ይበጃል፡፡

ወያኔ ይህን ስልት በራሱም ውስጥ በተቀዋሚዎችም ላይ በሚገባ ተጥቅሞ ውጤታማ ሆኖበታል፣ ወያኔ ብቻውን ባይሰራውም ደርግ መጨረሻ ሲወድቅ ኮረኔል መንግሥቱ ብቻቸውን ነበሩ፡፡ ከጠላትም መማር ብልህነት ነውና ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡

1-ወያኔ ስልጣን በያዘ ሰሞን አዲስ አበባ ከተማን ያጥለቀለቀ የተባለ ሰላማዊ ሰለፍ ያካሄደ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ህብረት የተሰኘ ፓርቲ ነበር፡፡ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም የሚለው ወያኔ የቤት ስራውን ሰራና የፓርቲውን ሊቀመንበር አቶ ጸጋየን አሰረ፡፡ ለካንስ የአቶ ጸጋየ ቅርንጫፎች በወያኔ የቤት ስራ ተመልምለው ከግንዱ ተለያይተው ኖሮ ለምን ታሰሩ ብሎ የሚጠይቅ ይፈቱ ብሎ የሚጮህ አንድም የአመራር አባል ሳይታይ ቀረ፡፡ እንደውም እነርሱ በስልጣን ሽኩቻ ተጠመዱ፡፡ አቶ ሙላቱ ጣሰው (  በቅርብ ግዜ አንድነት ፓር ውስጥ ነበሩ) ሊቀመንበር ቢባሉም ፓርቲው ስም ብቻ ሆኖ ኖሮ በምርጫ 97 ዋዜማ አከተመ፡፡ አንድነትን በምርጫ ቦርድ የተሸለሙት አቶ ትእግስቱ አዎሉ የዛ ፓርቲ አመራር አባል የነበሩ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመረራ ጉዲና እና የዳውድ ኢብሳ ነገር (ሰማነህ ጀመረ)

2–የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት(መአህድ) ተመስርቶ በአጭር ግዜ ከተማ ከገጠር ተንቀሳቀሰ፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል ያለው ወያኔ ፕሬዝዳንቱን ፕ/ር ዓስራት ወልደየስን በሆነ ባልሆነው ፖሊስ ጣቢያ እያመላለሰ በውስጥ ቅርንጫፎቹን የመመልመል ስራውን ሲያጠናቅቅ አንደዛ የገዘፈ ፓርቲ ፕርዝዳንትን ያለምንም ኮሽታ  ወህኒ አወረዳቸው፡፡ ከዛም ምክትል ሊቀመናብርቶቹ አንዱ ለቀቁ አንዱ ሀገር ጥለው ወጡ፣ መአህድም በቀኝ አዝማች ነቅአጥበብ እጅ ላይ ሆኖ በደህንነት ሹሙ ክንፈ የሚመራ ፓርቲ ሆኖ  አንድ ቀን ለይምሰል አንኳን አስራት ይፈቱ የሚል ሰላማዊ ሰልፍ ሳይጠራ አስራት በወህኒ ማቀው ሞቱ፡፡

3–ወያኔ ሳያስበው በድንገት የተፈጠረውና በሙጫ የተጣበቁ ናቸው የትም አይደርሱም ብሎ የናቀው ቅንጅት በምርጫ ካርድ ያደረሰበትን ሽንፈት በጠመንጃ ሀይልና በአሜሪካ ዲፕሎማሲዊ ድጋፍ ከቀለበሰ በኋላ ዳግም ሽንፈት ላለማየት የቅንጅትን መንፈስ ለማጥፋት ሲጣጣር ወ/ት ብርካን ሚደቅሳ ከእስር መልስ የቅንጅትን ቤተሰቦች አሰባስባ የቅንጅት ወረሽ ነን ብላ አንድነት የተሰኘ ፓርቲ መስርታ ብቅ አለች፡፡ ከሀገር ቤት አልፎ አውሮፓና አሜሪካ የሚኖረው የቅንጅት ደጋፊ በአንድነት ደጋፊነት ተሰለፈ፡፡ አንድነት በዚህ ከቀጠለ ምን ሊከተል እንደሚችል ግልጽ ነበርና ወያኔ በጎቹ እንዲበተኑ እረኛውን ምታ ብሂሉን ተግባራዊ ለማድረግ ግዜ አላጠፋም፡፡ብርቱካንን ከእስር የተፈታሽበትን ቅድመ ሁኔታ ጥሰሻል አስተባብይ እያሉ እያዋከቡ ጎን ለጎን ቅርንጫፎቹን የመመልመል  ስራቸውን ቀጠሉ፡፡ በመጨረሻም ይሄ ጉዳይ የሊቀመንበሯ የግል ጉዳይ ነው የፓርቲ ጉዳይ አይደለም የሚል ማረጋገጫ ከአመራሩ ሲያገኙና ብርቱካን ብቻዋን መቆሟን ሲያረጋግጡ አንደ ወንበዴ ከመንገድ ጠልፈው አሰሯት፡፡ የአንድነት አመራሮች በምርጫ 2002 ሲወዳደሩ  ለአፋቸው አንኳን በምርጫ የምንወዳደረው ሊቀመንበራን ከተፈታች ነው ለማለት ሳይደፍሩ ቀሩ፡፡

4-ሀወኃት በተሰነጠቀበት ወቅት አፈንጋጭ የተባለው ወገን ካድሬውም ታጋዩም በእጃችን ነው ብሎ ሲኩራራ ይህን የተረዱት መለስ ርምጃ ለመውሰድ በቅድምያ ግንዱን ከቅርንጫፎቹ መለየት ነበረባቸውና መቀሌ ላይ የካድሬ ስብሰባ ጠሩ፡፡ አፈንጋጭ የተባሉቱ የተደገሰላቸውን ሳያውቁ አቶ መለስ ባዘጋጁዋቸው ሰዎች በሰማእታት እየተባሉ እየተለመኑ ያንን መድረክ ረግጠው ወጡ፡፡ ይህም የአቶ መለሰን እቅድ ያሳካ ተግባር ሆነና ሲለምኑዋቸው ካድሬውና ታጋይ ተጋዳላዩ ሰማእታትን ረግጠው የሄዱ በማለት ከእነርሱ ተለየ የአቶ መለስ ደጋፊም ሆነ፡፡ እንዲህ ሆነና አቶ መለስ ሁሉንም በግላጭ ስላገኙዋቸው የሚያባርሩትን አባረሩ ሌላውንም ወደ ወህኒ አወረዱ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ሶስተኛ ጉባዔ ተከናወነ

ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ቢቻልም ይበቃል፡፡ አሁን ወደ እኛ አንምጣ ግንዱ ግልጽ ነው ይታወቃል ህውኃት ነው፡፡ ቅርንጫፎቹ ግን ብዙ ናቸው፡፡ እና መጀመሪያ ለይቶ ማወቁና ደረጃ ማውጣቱ ዋና ስራ ነው፡፡ ከዛ ደግሞ እንደየደረጃቸው እንደ ማንነት ምንነታቸው  ከግንዱ ለመለየት የሚያስችል ስልት ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ከባዱ ተግባር ይሆናል፡፡ ለአንዳንዶቹ ከግንዱ መለየት ህልውናቸውን ማጣት ሆኖ ስለሚሰማቸው እነዚህ  ፤ላይ ግዜም ጉልበትም ማባከን ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ የሚል ጭንብል ለህውኃት ያጠለቁለት ብአዴን ኦህዴድና ደኢህዴግ ቅርንጫፎች ሲሆኑ ከግንዱ ሊለዩ የሚችሉበት ምንም አጋጣሚ አይኖርም ብሎ መደምደም ባይቻልም በተቀዋሚ ወገኖች ስራና ጥረት መለየት ይቻላል ብሎ መገመት ይቸግራል፤ስለሆነም እነሱን ለመለየትም ሳይደክሙ ከግንዱ ጋር አንድ አድርጎም ሳያዩ የተለየ ስልት መጠቀም፡፡

ሊሎች ከአጋር ድርጅቶች እስከ ስመ ተቀዋሚዎች፤በጥቅም ከተያዙት በሙስና እስከተነካኩት፤ አማራጭ በማጣት ከተጠጉት በዘረኝነት ስሜት እስከሚደግፉትከቀበሌ ሹማምት እስከ መከላከያ ሰራዊት ወዘተ ድረስ ያሉት ቅርንጫፎች የነጻነት ትግሉን አላማና ግብ ተረድተው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እያደረሱት ያለውን ጥፋት ተገንዝበው ቢቻል የትግሉ አጋር አንዲሆኑ ካልተቻለም የጥፋት ተባባሪነታቸውን አንዲያቆሙ ማድረግ ከተቻለ ጠቃሚ ነውና  የትግሉ አንድ አካል ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው፡፡

ለነጻነት የሚደረገው ትግል ወያኔን ማስወገድ የሚል ብቻ ሳይሆን ሶስት ነገሮችን ያጣመረ ቢሆን ይመረጣል፤እንደሆነም ተስፋ አለኝ፡፡ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ጠንቅ የሆነው ወያኔ ከዚህ ልክፍቱ የሚድን አለመሆኑ ሀያ አራት አመታት በተደረጉ ጥረቶች የተረጋገጠ በመሆኑ መፍትሄው ከሥልጣን ማውረድ መሆኑ ከትናንት ዛሬ የማያከራክር ሆኗል፡፡ በመሆኑም ቀዳሚውና ዋናው ጉዳይ ይህ ሲሆን ከሥልጣን መሰናበቱ ላይቀር በአጉል  መንፈራገጥ ጉዳት አንዳያደርስ ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ሶስተኛው እንደ ቀደሙት ሁለት ለውጦች ለዴሞክራሲ የተከፈለው መስዋዕትነት ሌላ አንባገነናዊ ሥርዐት አንዳይወልድ ከድል በኋላ አስተማማኝ የዴሞክራሲ መሰረት መጣል የሚቻልበትን መንገድ ከወዲሁ ማመቻቸት ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ኃይሌ ፕሬዘዳንት ከሚሆን የሪዞርቱ አስዳደር ቢሆን ይሻለዋል" - አቶ ግርማ ሰይፉ

ይህ ሁሉ አንዲህ እንደሚጻፈውና እንደሚነገረው ቀላል አይደለም፡፡በተለይ ደግሞ ወያኔ ሥልጣኑን ከሚያጣ ሀገር ቢፈራርስ ህዝብ ርስ በርሱ ቢጨራረስ ደንታ የሌለው ነውና የታጋዮቹን ኃላፊነት ድርብ ድርብርብ ስራቸውንም ከባድ ያደርገዋል፡፡ስለሆነም በየትኛውም መንገድ ይሁን በማንም ከምር የሚካሄድ የነጻነት ትግል ነጻነት የሚሻውን ዜጋ ሁሉ ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ ግንዱን በቀላሉ ብዙ ጉዳት ሳያደርስ ለመጣል አንዲቻል ቅርንጫፎቹን የመመልመል ስራም ሁሉም አንደ ችሎታና ዝንባሌው በያለበት ሆኖ ሊከውነው የሚችል ተግባር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በምንም ሁኔታ ወያኔን የሚጠቅምና የነጻነት ትግሉን የሚጎዳ ተግባር ካለመፈጸም ይጀምራል፡፡ በዚህ አስቸጋሪና ከባድ ግን አኩሪ ተግባር ላይ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉ ወገኖቸ የሚያካሂዱትን ትግል የሚጎዳ ተግባር መፈጸም ግን በታሪክም በትውልድም ይቅር ሊባል የማይችል ነው፡፡

ስለሆነም ወያኔ በስልጣን እንዲቆይ የሚፈልገውና የማይፈልገው ከተለየና ከታወቀ በኋላ፤የማይፈልገው ወገን ከላይ የተጠቀሱት ሶስት  ጉዳዮች ማለትም ወያኔን ከሥልጣን ማውረድ፤ሲፈራገጥ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ፤ከድል በኋላ አስተማማኝ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት መመስረት የሚያስችል መደላድል መፍጠር ላይ እየተነጋገረና እየተጋገዘ የድሉን ቀን ማሳጠር አንጂ ምክንያት እየፈጠሩ ተለያይቶ መቆም የወያኔ ቅርንጫፍ መሆን ነው፡፡

 

Share